ማኅበረ ቅዱሳን: ዐውደ ርእዩ የታገደው በመንግሥት አካላት መመሪያ መኾኑን ገለጸ፤ ፓትርያርኩ እንዳሉበት “በኦፊሴል የምናውቀው ነገር የለም”ብሏል

 • ተለዋጭ ጊዜና ቦታው፥ የመመሪያውን መነሻና አግባብነት በማጣራት እንደሚወሰን ተገልጧል
 • ብዙ የተደከመበት እና አያሌ ለውጥ የሚያመጣ ዝግጅት ሲታገድ ስሜቱና ጉዳቱ ከፍተኛ ነው
 • ያለአሠራሩ ለመሰረዝ የተገደዱት የማዕከሉ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ትብብር፣ “ቀና ነበር” ብሏል
 • በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይካሔድ በመከልከሉ ታላቅና ተገቢ ዓላማው አይከሽፍም፤ በፍጹም!
 • አስፈላጊው ጥረት ከተደረገ በኋላ ተወስኖ መታየት ይኖርበታል ብሎ የማኅበሩ አመራር ያምናል
 • ማኅበሩ፥ ዓላማውን ለምእመኑ ለማድረስ የሚያስበው በተገቢ፣ ትክክለኛና ሰላማዊ መንገድ ነው

*                     *                    *

Ato Tesfaye Bihonegn

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ፤ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ

ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከመጋቢት ፲፭ እስከ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን: አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል በኤግዚቢሽን ማዕከል ለማካሔድ ዐቅዶ ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀበት ዐውደ ርእይ ለጉብኝት ክፍት የሚኾንበት የመጨረሻ ሰዓት ሲዳረስ በእንግዳ አሠራር ተደናቅፏል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በሰፊው የሚያስተዋውቅና ከምእመኑ የሚጠበቀውን ድርሻ በአግባቡ የሚያሳይ ዐውደ ርእይ አዘጋጅተን በምናቀርብበት ሰዓት መከልከላችን ከፍተኛ ስሜት የሚፈጥር ነው፤” ብለዋል የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ – ትላንት ማምሻውን በማኅበሩ የዋናው ማዕከል ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ በተካሔደ ጋዜጣዊ ጉባኤ፡፡

የማኅበሩ አመራር፣ ዐውደ ርእዩ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይታይ የተከለከለው ከመንግሥት አካላት በተሰጠ መመሪያ ነው፤ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ የትኛው የመንግሥት አካል በምን መነሻ እንደከለከለ ግን ለጊዜው አለመታወቁንና ይህም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በቀጣይ በመወያየት ይፈታል የሚል ተስፋ እንዳለ አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ይመለከተዋል የተባለው የአዲስ አበባ አስተዳደር ክፍል፣ ለዐውደ ርእይ ፈቃድ የሚሰጥበት አሠራር ይኹን ልምድ እንደሌለው ለማኅበሩ ይግለጽ እንጂ፣ ዝግጅቱ በማዕከሉ እንዳይካሔድ የተከለከለው ከበላይ አካል በተላለፈ መመሪያ መኾኑንና ጥያቄውንም በመቀበሉ ጭምር መወቀሱን የአስተዳደሩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ከመኾኑ አንጻር ሰሞኑን ከነበረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ፓትርያርኩ በእገዳው ይኖሩበት እንደኾን አቶ ተስፋዬ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ከቅዱስ አባታችን ጋር በተያያዘ እስከ አኹን ባለን መረጃ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፤” ሲሉ የተደረሰበት ይፋዊ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ከተነሡት ጥያቄዎች፣ ዐውደ ርእዩ በዋናው ማዕከል ጽ/ቤት እንደሚካሔድ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለተሠራጩ መረጃዎችና በቀጣይ ስለታሰበው አካሔድ የሚመለከት ይገኘበታል፡፡ የማኅበሩ አመራር፣ ዐውደ ርእዩ መታየት ይኖርበታል የሚል እምነት እንዳለው የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፣ “የት እና መቼ እንደሚካሔድ ግን እስከ አኹን አልወሰንም፤ በቀጣይ አስፈላጊውን ጥረት አድርገን ከወሰንን በኋላ የምናሳውቅ ነው የሚኾነው፤” ብለዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይካሔድ በመከልከሉ ዓላማው ፈጽሞ እንደማይከሽፍ ያስረዱት አቶ ተስፋዬ፣ ማኅበሩ ዓላማውን ለሕዝብ በተገቢ፣ ትክክለኛና ሰላማዊ መንገዶች የሚያደርስበት ቀጣይ ጥረቶች እንደሚያደርግ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡ ከገንዘባዊ ወጪ በላይና ባሻገር ለዐውደ ርእዩ መሳካት ሌት ተቀን በብዙ የደከሙ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ወንድሞችንና እኅቶችን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚቻል እምነታቸውን የገለጹት ዋና ጸሐፊው፥ ዐውደ ርእዩ እንዴት፣ የት እና መቼ እንደሚካሔድ  የሚወስኑትም እኒኽ ጥረቶችና ሙከራዎች እንደኾኑ አስታውቀዋል፡፡ የጋዜጣዊ ጉባኤው ሙሉ ይዘት በሚከተለው መንገድ ተቀናብሮ ቀርቧል፡፡


የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የጋዜጣዊ ጉባኤው መግለጫ፤

እንደሚታወቀው፣ ዛሬ የዐውደ ርእዩ መክፈቻ መርሐ ግብር ስለነበረ 10፡00 ላይ ጥሪ አድርገን ነበር፡፡ በታሰበው ጊዜ ልክ አልጀመረም፤ ይኼ ዐውደ ርእይ ፈቃድ የተጠየቀበት 2007 ዓ.ም. ጳጉሜን ላይ ነው፤ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከዓመት በፊት ነው ፕሮግራም የሚያዘው፤ 2007 ዓ.ም. የማስፈቀዱን ሒደት የጀመርንበት ነው እንጂ ፕሮግራሙን ቀድመን ነው ያስያዝነው፤ ለኹለት ሳምንት ለማካሔድ ዐቅደን ነበር ፕሮግራም ያስያዝነው፤ ነገር ግን በአንዳንድ የፕሮግራም መጨናነቅ ምክንያት የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ እንዳለው በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ስለተገለጸልን ሰባቱን ቀናት በአግባቡ ለመጠቀም ወስነን ከማዕከሉ አስተዳደር ጋር ተወያየን፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የፈቃድ ደብዳቤ እንድናመጣ ጠየቁን፤ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ ፊርማ ተፈርሞ ይዘን ሔደን በዚኽ መሠረት ከኤግዚቢሽን ማዕከል ጋር ውል ፈጸምን፤ የመጀመሪያ ክፍያም ከፈልን፡፡

በዚኽ መሠረት የዐውደ ርእዩ ዝግጅት ተጀመረ፤ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው የቆየነው፤ በየመሐሉ ከኤግዚቢሽን ማዕከል ጋር ብዙ ውይይት እያደረግን ቆይተናል፤ በየጊዜው ነው የምንሔደው፤ በነገራችን ላይ ቀና ትብብር ነው አላቸው፤ እስከ መጨረሻው ድረስ ቀና ትብብር ነው የነበራቸው፤ እኛም መርሐ ግብራችንን በሰፊው አዘጋጀን፡፡ ሰኞ፣ መጋቢት 12 ቀን የመጨረሻ ክፍያ ከፍለናል፤ ማክሰኞ የዲዛይን ሥራዎችን ለመሥራት፣ አንዳንድ ነገሮችንም ለማስገባት ብቅ ብለናል፤ ምንም ችግር አልነበረም፤ ችግሩ የተፈጠረው ትላንትና ጠዋት ነው፡፡ የዐውደ ርእዩ ዐቢይ ኮሚቴ ለትዕይንቱ ዝግጅት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ይዞ ሔዶ የአዳራሾቹን ቁልፎች ሲጠይቅ፣ አይ፥ ችግር አለ፤ የሚል መልስ ነው የተሰጠው፡፡

የዐቢይ ኮሚቴው አባላት ወዲያው ለእኛ ደውለውልን ሔድን፡፡ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ከአቶ ታምራት ጋርና ከተወሰኑ ስታፎች ጋር ውይይት አደረግን፡፡ ለእኛ እንግዳ ነው፤ በርግጥ፣ ለእነርሱም እንግዳ ነገር እንደ ኾነ ነው የነገሩን፡፡ እነርሱ እንደሚሉት፣ ኹለት ዓይነት አሠራር አለው፡፡ አንደኛው፥ ንግድ ፈቃድ ያላቸው አካላት ዐውደ ርእይ ወይም ኤግዚቢሽን እንዲሳተፉ ከንግድ ቢሮ ደብዳቤ ሲያጽፉ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ኹለተኛው፥ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ዕውቅና ከሰጧቸው አካላት ደብዳቤ ያጽፋሉ፤ ቢበዛ የሚጠበቅባቸው ያ ደብዳቤ ነው፡፡ በዚኽኛው መሠረት ነው ማዕከሉ እኛን ለማስተናገድና ውል ለመፈጸም የፈቀደው፤ ሌሎቹንም የሚያስተናግደው በዚኹ አሠራር ነው፡፡

ትላንት ከማዕከሉ ማኔጅመንት ጋር በነበረን ውይይት፥ ማዕከሉ፣ “የአዲስ አበባ አስተዳደር አልፈቀደም፤ ከእርሱ ደብዳቤ ይዛችኹ ኑ፤” የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡ እኛም፣ እንዲኽ ያለ አሠራር እንዳልነበረ ተናግራችኋል፤ ስለዚኽ ከየት መጣ? ከጠየቃችኹንስ ዛሬ በዋዜማው ነው ወይ የምትጠይቁን? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አነሣን፡፡ ከእነርሱ ያገኘነው ምላሽ፥ “ጥፋቱ የኛ ነው፤ በማንኛውም በሚዲያም በምንም ይቅርታ እንጠይቃለን” የሚል ነው፡፡

የማኅበሩ አመራር፣ ይህ ኹኔታ እንዳጋጠመ ከሰማ በኋላ በጣም ሰፊ ጥረት አድርጓል፡፡ አንደኛው፣ ወደ አዲስ አበባ መስተዳደር መሔድ ነው፡፡ መስተዳድሩ፥ ለዐውደ ርእይ እንደማይጠየቅ፤ ተጠይቆም እንደማያውቅ፣ አሠራሩም እንግዳ እንደኾነበት አሳውቆናል፡፡ ስለዚኽ ዐውደ ርእዩ የተቋረጠው በመንግሥት ነው፤ ወደሚለው ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡ ማንኛው የመንግሥት አካል ነው ለሚለው፣ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ አኹን የምናውቀው መንግሥት እንደከለከለ ነው፡፡ ይኸው ነው፡፡ ጥያቄዎች ካሏችኹ የተወሰኑትን ማስተናገድ እንችላለን፡፡

ከጋዜጠኞች የተሰነዘሩ ጥያቄዎች፤
 1. በቀጣይ ዐውደ ርእዩን እዚኽ በማኅበሩ ሕንጻ ላይ የማሳየት ኹኔታ አለ ይባላል፤
 2. በመንግሥት ነው የተከለከለው የሚል ድምዳሜ ተሰጥቷል፤ ምን ተጨባጭ ነገር ይዛችኹ ነው? በቀጣይስ ምን ርምጃ ለመውሰድ ታስቧል? በማኅበራዊ ሚዲያ በገንዘብ እንዳከሰራችኹ ያየኹት ነገር አለ፤ ከገንዘብ ባሻገር በዚኽ ኹኔታ ውስጥ ምን ዐጣን ትላላችኹ?
 3. አዲስ አበባ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ከመኾኑና በቅርቡ ከነበረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ቅዱስ ፓትርያርኩ ዐውደ ርእዩን እንዳገዱት ይወራል፤ ምእመናን በዚኽ እንዳይሰናከሉ ማኅበሩ ሊሰጥ ያሰበው መልስ አለ? ዐውደ ርእዩ በመታገዱ የማኅበሩን ርእይና ዓላማ ያደናቅፋል ብለው ያስባሉ?

የዋና ጸሐፊው ምላሾች

ዐውደ ርእዩ የት እና መቼ እንደሚካሔድ እስከ አኹን አልወሰንም፤ በቀጣይ የምናሳውቅ ነው የሚኾነው፡፡ ምናልባት እዚኽ በዋናው ማዕከል ጽ/ቤት እንደሚካሔድ የተሠራጩ ወሬዎች ይኖራሉ፡፡ የማኅበሩ ሥራ አመራር ግን የት፣ መቼ ዐውደ ርእዩ እንደሚታይ እስከ አኹን አልወሰነም፡፡ ወደፊት እናሳውቃለን፤ ምክንያቱም ቀጣይ ጥረቶች አሉ፡፡ በትክክል፣ ማንኛው የመንግሥት አካል ነው ያገደው? በምን መነሻ ነው ያገደው? የሚለውን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመወያየት ይፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ያ ሙከራ ከተካሔደ በኋላ እንዴት፣ የት እና መቼ እንደሚካሔድ ወደፊት የምናሳውቅ ነው የሚኾነው፡፡

መንግሥት ለመኾኑ ምን ተጨባጭ ምክንያት አለ? ለሚለው፤ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ አዲስ አበባ መስተዳድር ፈቃድ መስጠት ይኖርበታል የሚል እንግዳ አሠራር ጠይቋል፡፡ አዲስ አበባ መስተዳደርን ስንጠይቅ ደግሞ፣ እንዲኽ ያለ እንግዳ አሠራር አላውቅም፤ ለኤግዚቢሽን ማዕከል ፕሮግራም ፈቅደን አናውቅም፤ ብሎናል፡፡ ስለዚኽ በመንግሥት እንደታገደ ከዚኽ በላይ ምንም ማረጋገጫ ሊኖር አይችልም፡፡ በመደበኛ አካሔድ ባይኾንም በተለያዩ መንገዶች ይህን አረጋግጠናል፡፡ ያ አካል ግን በትክክል ማን ነው? የሚለውን ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ቀጣይ ውይይት የሚታወቅ ነው የሚኾነው፡፡

ዐውደ ርእዩ ባለመታየቱ ምን ጉዳት አምጥቷል? ለሚለው፣ በርግጥ ከገንዘብ አንጻር ኤግዚቢሽን ማዕከሉ፥ የከፈላችኹትን እመልሳለኹ፤ ብሏል፡፡ ይህም ኾኖ ዐውደ ርእዩ ታላቅ መርሐ ግብር ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሰፊው የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ ምእመኑን በአግባቡ የሚያስተምር ነው፡፡ ከምእመናን የሚጠበቀውን ድርሻ በአግባቡ የሚያሳይና ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ዐውደ ርእይ ነው፡፡ ብዙ ድካም ተደክሞበታል፡፡ ብዙ አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ብዙ ወንድሞች፣ ብዙ እኅቶች ብዙ ደክመዋል፤ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ እንዲኽ ያለ መርሐ ግብር በታሰበው ጊዜ ሳይጀምር ሲቀር ያለጥርጥር ብዙ ጉዳት አለው፡፡

ርግጥ፣ ወደፊት በሚደረጉ ጥረቶች ዐውደ ርእዩ ይታያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ መታየት አለበት፤ እንዲታይ አስፈላጊው ጥረት መደረግ አለበት፤ አስፈላጊው ጥረት ከተደረገ በኋላ ተወስኖ መታየት ይኖርበታል ብሎ የማኅበሩ አመራር ያምናል፤ እኒኽ እንቅስቃሴዎች ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ይቀንሱታል እንጂ ይህን የመሰለ መርሐ ግብር በሰፊው አዘጋጅተን በምናሳይበት ሰዓት መከልከላችን ከፍተኛ ስሜት ነው ሊፈጥር የሚችለው፡፡

MK AWude ReEye Meg2008በኤግዚቢሽን ማዕከሉ የአብነት ት/ቤቶች መንደር በመገንባት የአብያተ ጉባኤያቱን ሥርዐተ ትምህርት እና ብሂላት በተግባር ማሳየት፣ ከ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ የክውን ጥበባት መሰናዶዎች አንዱ ነበር፤ ለዚኽም ከ80 ያላነሱ ከተለያዩ የአብነት ት/ቤቶች የመጡ መምህራንና ደቀ መዛሙርት ተዘጋጅተው ነበር፤ ትላንት ማምሻውን በዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ቅጽር ስለ መምህራኑና ደቀ መዛሙርቱ ክብር በተከናወነ የቅምሻ መርሐ ግብር፣ ዐውደ ርእዩን በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ ብዙዎች መጽናናታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ሞራላዊ ጉዳታቸውን ይቀንስ ይኾን?


ኤግዚቢሽን ማዕከል በመከልከሉ ብቻ የዐውደ ርእዩ ዓላማ ሊከሽፍ ይችላል ወይ? በፍጹም! ማኅበረ ቅዱሳን በዚኽ መልኩ አይደለም ጉዳዮችን የሚይዘው፡፡ ዓላማው በሰላማዊ መንገድ፣ በትክክልና በአግባቡ ወደ ሕዝቡ፣ ወደ ምእመኑ የሚደርስበትን መንገድ ያስባል፡፡ በዚኽም ጉዳቱን በሒደት ልንቀንሰው እንችላለን እንጂ ሲታገድ የሚፈጠረው ነገር ቀላል አይደለም፡፡

ከቅዱስ አባታችን ጋር በተያያዘ እስከ አኹን ባለን መረጃ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ዐውደ ርእዩ የታገደው ከመንግሥት አካላት በተሰጠ መመሪያ እንደኾነ ነው የምናውቀው፡፡ በሒደት ግን በውስጡ ምን እንዳለና እንዴት እዚኽ ውሳኔ ላይ እንደተደረሰ፤ እንዲኽ ዓይነት መመሪያ ሲሰጥ በምን አግባብ እንደተወሰነ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተወያየን ስንሔድ አንዳንድ ነገሮችን ልናውቅ እንችላለን፡፡ አኹን ባለው ኹኔታ፣ ኦፊሴሊያዊ የኾነ የምናውቀው ምንም ነገር የለም፡፡

 

Advertisements

15 thoughts on “ማኅበረ ቅዱሳን: ዐውደ ርእዩ የታገደው በመንግሥት አካላት መመሪያ መኾኑን ገለጸ፤ ፓትርያርኩ እንዳሉበት “በኦፊሴል የምናውቀው ነገር የለም”ብሏል

 1. Pawli Ze Axum March 25, 2016 at 8:43 am Reply

  ፓትርያርኩ፡- ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት
  click here for pdf
  ‹የክርስቶስ አንዲት በግ መከራን ስትቀበል ከማይ እኔ የበጉ እረኛ መከራ መቀበልን እመርጣለሁ›

  ይህንን የተናገረው ዮሐንስ አፈወርቅ ነበር፡፡ የቁስጥንጥንያዋ ንግሥት አውዶቅስያ የአንዲት ክርስቲያን ምእመንን መሬት ወስዳ ባሰቃየቻት ጊዜ ለተግሣጽ የተናገረው ነው፡፡ እንዳለው አልቀረም አውዶቅስያ ባደረሰችበት መከራ ተግዞ በዚያው ሞትን ተቀብሏል፡፡ እውነተኛ አባት ስለ በጎቹ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል እንጂ በጎቹን ለራሱ ክብርና ጥቅም ሲል አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ፓትርያርክ ማለት በግሪክ ‹ታላቅ አባት› ማለት ነው፡፡ የታላቅ አባት ተግባር የልጆቹን ሥራ ማፍረስ አይደለም፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፤ የታላቅ አባት ሥራ ልጆቹን መክሰስ አይደለም፤ ለዚህማ ሰይጣን እንጂ አባት አያስፈልግም፡፤ የታላቅ አባት ሥራ ልጆቹን ጠርቶ መውቀስ እንጂ በር መዝጋት አይደለም፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፡፡ የታላቅ አባት ሥራ ልጆቹን ማቀፍ እንጂ ማባረር አይደለም፤ ለዚህማ ሰይጣን አለ፡፡
  ፓትርያርኩ እንጨት የሚሸጡ እናቶች ካወጡት የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደዋዛ በአንድ ሙሰኛ ሲነጠቅ ተኝተዋል፤ በመሐል ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተሠሩ ሕንጻዎች በጎጆ ቤት ዋጋ በሙስና ለዐሠርት ዓመታት ሲከራዩ ተኝተዋል፤ ከመንበረ ፕትርክናቸው ሥር ባለች አጥቢያ የቤተ ክርስቲንን ገንዘብ አናስበላም ያሉ ካህናትና ምእመናን ሲባረሩ ተኝተዋል፡፡ በሕዝብ ጥያቄ ሽፋን ጽንፈኛ አቋምን በሚያራምዱ ሰዎች አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ይተኛሉ፤ የስልጤ ዞን ምእመናን በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ እየተቀበልን ነው ሲሉ ይተኛሉ፤ ቤተ ክህነቱ የኑፋቄ ማኅደር ሲሆን ይተኛሉ፤ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሲዘጉ፣ ገዳማትና አድባራት ሲፈርሱ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሲበተኑ ይተኛሉ፤ በመሥዋዕትነት የተመሠረቱት የደቡብ አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት በሙሰኛ አመራሮች አደጋ ላይ ሲወድቁ ይተኛሉ፣ ይሄ ሁሉ ዘለፋና ኑፋቄ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲዘንብ ይተኛሉ፡፡

  መናፍቃንን የሚተች ጽሑፍ በኦርቶዶሳውያን ተጻፈ ሲሏቸው፤ ምእመናንን የሚያጸና ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣ ነው ሲሏቸው፤ ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያኑን ለማገልገል እየተጋ ነው ሲሏቸው፤ ዲያስጶራው ሕዝብ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ሆነ ሲሏቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚገልጥ ዐውደ ርእይ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሊቀርብ ነው ሲሏቸው ያን ጊዜ ብዕራቸውን ይዘው ለማገድና ለመክሰስ ይነቃሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ‹ድንግል ሆይ የአንቺን ምስጋና ለመጻፍ ምንጊዜም ብእሬ ቀለም እንደያዘ ነው› ነበር ያለው፡፡ የፓትርያርኩ ብእር ግን ምእመናንን የሚያጽናና ጦማር ለመጻፍ ወይም ድንግልን የሚያመሰግን ድርሳን ለመድረስ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ እንደ ጠንቋይ ብዕር ለማፍዘዝና ለማደንገዝ እንጂ፡፡
  የፓትርያርክ ዋናው ሥራው የሀገር ደኅንነት እንዲጠበቅ ‹ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ› እያለ መጸለይ፤ የምእመናን ድኅነት እንዲረጋገጥም ሃይማኖት ማስተማር፣ በጎችን መሠማራትና ቀኖናን መጠበቅ ነበረ፡፡ ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹በጎቼን ጠብቅ፣ አሠማራ› ነበር የተባለው፡፡ መጠበቅ- ከክህደት፣ ከኑፋቄ፣ ከኃጢአት ከበደል፤ ማሠማራት – በትምህርት፣ በምግባር፣ በትሩፋት፣ በአገልግሎት፣ በጽድቅ መስክ ላይ፡፡
  ‹ባለሞያ ሴት የሠፋችውን ወራንታ፣ ጅል ትተረትረዋለች› እንደተባለው በደኅና ጊዜ ትጉኃን አበው የሰበሰቧቸውን ወጣቶች ካልበተንኩ ብሎ እንዴት አንድ ፓትርያርክ ይነሣል፡፡ ወጣቶቹ ሊሳሳቱ፣ ሊያጠፉም ይችላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ለዚህም መንገድ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሳይቀሩ የገዛ ልጆችዎን ያወያዩ ሲሏቸው በራቸውን ጠርቅመው የሚዘጉ ፓትርያርክ በታሪክ የሚጀመሪያው መሆን አለባቸው፡፡ በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተ ክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፡፡ ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ጋር ለማነጋገር የደከሙ እነ ክርስቶስ ሠምራን የመሰሉ ቅዱሳን ባሉባት ቤተ ክርስቲያን እረኛው ከመንጋው ጋር መነጋገር አቃተው፡፡ ኢየሱሳውያንን በዐደባባይ ሳናነጋግራቸው መሄድ የለባቸውም ብለው የተሟገቱ እነ እጨጌ በትረ ጊዮርጊስ በነበሩባት ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቹን ለማነጋገር በር የሚዘጋ እጨጌ ተፈጠረ፡፡ የመካ ቁራይሾችን አሳልፈን ለጠላቶቻቸው አንሰጥም የሚሉ አበው በነበሩባት ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቹን አሳልፎ የሚሰጥ አባት መጣ፡፡
  የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በ1972 እኤአ ካይሮ ላይ ባደረጉት ጉባኤ ከተስማሙባቸው ነገሮች አንዱ የኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ተልዕኮ ነበረ፡፡ እንዲህ ይላል ‹ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት አምስት ተልዕኮ አላቸው፡፡ እነዚህም
  1. ወንጌልን መስበክ(Preach the Gospel)
  2. ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም(Administer the Sacraments of the Gospel.)
  3. የቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ አንድነትና ቀኖና መጠበቅ(Guard the faith, unity, and discipline of the church.)
  4. ለካህናትና ለምእመናን የቅድስና ምሳሌ መሆን(Be a moral example of holiness and wholesomeness.)
  5. በእረኛውና በበጎች መካከል ያለውን ክፍተት ማጠበብ(Diminish the distance between bishops and their flock.)
  ለመሆኑ የእኛ አባት የቱን ነው እየፈጸሙ ያሉት? ወይስ ከኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ውጭ ሆነናል?
  ዐውደ ርእዩ የማይደረግበት በቂ ምክንያት ከነበረ ቢያንስ ከሳምንት በፊት መግለጥ ይቻል ነበር፡፡ ዓላማው ግን ማበሳጨት፣ ዐመጽ ማስነሣት፣ ተሥፋ ማስቆረጥና ምእመናንን ወደማይፈልጉት መሥመር መውሰድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ፈያታዊ ዘየማን ገነት በገባባት ሰዓት ዐውደ ርእዩ እንዲዘጋ የተደረገው፡፡ የዚህች ሀገር ሰላም አይፈለገም? ምእመናን ሀገር እንደሌላቸውና መብት እንደሌላቸው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ ይፈለጋል? ‹ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል› እንዲል ሀገሪቱ ያለባት ችግር አይበቃትም? ተጨማሪ ችግር ማምረት ይፈለጋል?
  ችግሩ ሁሉ እየተፈጠረ ያለው በመንግሥት ስም ነው፡፡ ‹መንግሥት አዞናል፤ እገሌ የተባለ ባለ ሥልጣን ብሎናል፤ ፖሊስ እንጠራለን፤ ደኅንነት እናዛለን› ነው በቤተ ክህነቱ ዘንድ የሚባለው፡፡ እውነት መንግሥት በስሙ የሚሠራውን ያውቀዋል፤ ካወቀውስ ዝም ይላል? ቤተ ክህነቱ በሚያመጣው ዳፋ መከራ ለመቀበልስ ዝግጁ ነው? ይህ አካሄድስ ለሀገሪቱ ደኅንነት የሚበጅ ነው? ዐውደ ርእዩ እንዲዘጋ ያዘዘውስ የትኛው መንግሥት ነው? አንዱ የሚፈቅድ ሌላው የሚዘጋ ስንት መንግሥት ነው ያለው? ወይስ ‹ደብዳቤ መጻፉ አላዋጣምና ዝጋልኝ› ተብሎ እጅ የተሰነዘረለት አካል ያደረገው ነው? መጽሐፉ እንደሚል ‹የማይገለጥ የተሠወረ› አይኖርምና ዐውቀነዋልም፣ እናውቀዋለንም፡፡
  የገዛ ፓትርያርካችን ለእኛ ለምእመናን ድኅነትን እንዳናገኝ ሥጋት ሆነውብናል፡፡ የታገሡትን ሁሉ ለክፋት በማነሣሣት ደግሞ ለሀገሪቱ ደኅንነት ሥጋት እየሆኑ ነው፡፡ የምእመናኑን ሥጋት ሲኖዶሱ፤ የሀገሪቱንም ሥጋት መንግሥቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ከቤተ መቅደስ የተነሣ ችግር መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው አይታወቅምና፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች የምእመኑን የአስተሳሰብ ቅርጽ ይቀይራሉ፡፡ የሐበሻን ሥነ ልቡና ለሚረዳ ደግሞ ሲረገጥ እንደሚጠክር ጭቃ ያጠነክራሉ፡፡ ሲሞረድ እንደሚሳል ቢላዋ፣ ሲቀረጽ እንደሚሾል እርሳስ ያደርጋሉ፡፡ በዐውደ ርእዩ የሚማሩት የሚያዩት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ያላዩትም እንዲማሩ አድርገዋል፡፡ ሐሳብና ርእዮት ሊያስተባብረው የማይችለውን ተጠቂነት ያስተባብረዋል፡፡ ተጠቂነት ክርክርና ውይይት፣ ማስረጃና መረጃ አይጠይቅም፡፡ መጠቃቱን ያወቀ ሁሉ ራሱ ገብቶት ይተባበራልና፡፡ ምናልባትም ምእመናንን ከገድል ተራኪነት ወደ ገድል ሠሪነት ያሻግራቸው ይሆናል፡፡ ‹እዚያም ቤት እሳት አለ› አሉ አለቃ፡፡
  እንደ ሶምሶን ከአንበሳ ሬሳ ማር ለማውጣት ግን በሳል አመራር ይጠይቃል፡፡ የማኅበሩ አመራርም ቢሆን ጊዜውን አይቶ የሚሣለጥ አመራር እንጂ የተቸከለ አመራር መሆን የለበትም፡፡ የፓትርያርክ ማትያስ ዘመን እንደ ፓትርያርክ ጳውሎስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም ዘመን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አይደለም፡፡ አሁን የሆነው ነገር ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ እየታወቀ ከግንቡ ጋር እስኪጋጩ ድረስ ቆሞ መጠበቅ ብልህነት አይደለም፡፡ አሁንም ‹እገሌ የተባለ ባለሥልጣንን አናግረናል፤ እገሌ የተባሉ አባት አይዟችሁ ብለውናል› እያሉ መጓዝ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ለጉባኤ ተሰብስቦ ‹ ለፓትርያርኩ የተጻፈው ደብዳቤ አንጀት አርስ ነው› ብሎ አጨብጭቦ የሚበተን አመራር ጊዜው ሊያልፍበት ይገባል፡፡ ከዲሚትሪ ሆቴል እስከ ፌዴራል ጉዳዮች የተደረጉትን ውይይቶች ገምግሞ አዲስ አቅጣጫ መያዝ ይገባ ነበር፡፡ የሚሰበሰብ ብቻ ሳይሆን የሚተነብይ አመራርም ያስፈልጋል፤ ካልሆነ ግን
  ‹ከክምር ድንጋይ ላይ ይበቅላል ደደኾ
  የፈራሁት ነገር መጣ ድኾ ድኾ› የተባለው ይደርሳል፡፡

  Posted by ዳንኤል ክብረት

  • Eske March 26, 2016 at 6:05 am Reply

   ሥላሴ:
   ለማትያስ ሐዋርያ መናፍቃነ-ቃል በላእተ-ሰብእ ድኅረ-ጥረሲሁ አፍለሱ ማኅበረ-ቅዱሳን ሣዕረ፡
   አብልእዎ ከመይብልእዎ ከዊኖ እሡረ፡፡
   እስመ እንድርያስ ሊቅ በክነፈ-ነፋስ ዘበረ፡
   ሎቱ በጺሐ አስተደኀረ:
   ወእመሎቱ ይበጽሕ በዊኦ ማኅደረ፡
   እምአንቅዐ ዘምስጢር ባሕረ፡፡
   ሃ/ማርያም

 2. Anonymous March 25, 2016 at 8:52 am Reply

  ስለነገስታት እንማልዳለን ስለሃይማኖት አባቶቻችን እንማልዳለን የሚባለውን የቤተክርስያን ጸሎት የሚመለከታቸው ለበረከት ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው፡፡ ማህበሩን መናፍቃን፤ ሃራጥቃ ተሃድሶዎች፤ ሙሰኛ የቤተክርስቲያን አካላት ይፍሩት እንጂ መንግስት ለምን እንደሚፈራው አይገባኝም፡፡ ለነገሩ በመንግስት ውስጥም የተሰገሰጉ ከላይ የጠቀስናቸው አካላት አባላት አሉና ልንጠብቅ ግድ ነው ለምን ቢሉ የኦርቶዶክስ ምዕመና ስለቤተክርስቲያናቸው ሲያውቁ በአዲስ መንፈስና መነሳሳት ለቅድስት ቤተክርስቲያናቸው የድርሻቸውን ለመወጣት ግንዛቤ የሚያገኙበት ስለሆነ እነዚህ አካላት መቃወም አለባቸው፡፡ በጣም የማዝነው አቡኑ በዚህ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከተገኙ ነው፡፡ ከተገኙ ግን ማህበሩን ሳይሆን ያስደፈሩት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ነውና እናዝናለን፡፡

 3. Anonymous March 25, 2016 at 12:34 pm Reply

  ማህበሩን መናፍቃን፤ ሃራጥቃ ተሃድሶዎች፤ ሙሰኛ የቤተክርስቲያን አካላት ይፍሩት እንጂ መንግስት ለምን እንደሚፈራው አይገባኝም፡፡ ለነገሩ በመንግስት ውስጥም የተሰገሰጉ ከላይ የጠቀስናቸው አካላት አባላት አሉና ልንጠብቅ ግድ ነው…..

  • annonimous March 25, 2016 at 2:07 pm Reply

   ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፡- ፓትሪያሪኩ ቢያውቁትና ይህንን መረጃ የሚያገኙበት ሁኔታ ቢፈጠር ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸው ነበር ቃል አቃባዮቻቸውም ይህንን ገልብጠው ነው የሚነግሯቸው፤ እሳቸው ደግሞ እንደ አባት ሰከን ያሉ ሳይሆኑ ስሜታዊ ናቸው፤ አግድልኝ፤ ግደልልኝ፤ አስወጣልኝ፤ የሚሉ ብቻ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለዚህ የዋህና አማኝ ምዕመን ለበጎቹ የሚራራና ተላልፎ የሚሰጥ አባት ይሹምለትና እርፍ ይበል፡፡

   በሥራው ተጨንቆ በኑሮው ተጨንቆ ቤተ ክርስቲያን ከጭንቀቴ ታሳርፈኛለች ብሎ ሲመጣ እዛም አባቶቹ ያስጨንቁታል፤ የት ሔዶ ይረፍ፤ እረ እባካች፣ አባቶች ለህዝቡ ራሩለት፤ ከላይ እስከ ታች ያላችሁ መልካም አባቶች ሆይ፣ ጥሩ ላልሆኑትና ለመንጋው ለማይራሩ አባቶች ፀልዩላቸው አእምሮውን ማስተዋሉን ይሰጣቸው ዘንድ፡፡

 4. Sami March 25, 2016 at 6:23 pm Reply

  Ene, MK saykotaterew sayfekdelet lemahberu ye gelibach debdabe tsefo ke and betekerestian gar tenegagro talak ketema akef gubae miazegaj ye university gebi gubae endeLeLe akalew. Mahberu le senbet temert bet maderaja mamria yeglebach debdabe leko ke menbere patriark office yefekad debdabe mawtat hegawi new beye alamnm. Maderaja memriaw memratena mekotater alebet endezi aynet gubae. Endene endene…..Egziabher selalfekede tekelekele. Akahedum serawem hege wet neber.

  • Anonymous March 26, 2016 at 9:41 pm Reply

   Tultula kaderea

 5. Aregawi March 26, 2016 at 6:52 am Reply

  የቤተ ክርስቲያን መሪ ካልከለከሉ ደግሞ መንግስት ምን አገባው፧ እግዚአብሔር የነገስታትና የመናፍቃን አፍ ይዝጋልን።

 6. Anonymous March 26, 2016 at 10:03 am Reply

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ምን አሰማኸን!!! እረ የዛሬውስ እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው!! ፓትሪያርኩ የቤተክርስቲያ መሪ ወይስ የዚህ አለም አስተዳዳሪ? ለነገሩማ የማን ዘር ጎመን ዘር ተብሎ የለ፡፡ አቡነ ፓውሎስ የዋልድባ ገዳምን ከመለስ ጋር ተመሳጥረው ሲያስፈርሱ መነኮሳት አባቶችን ሲያስደበድቡና ሲያሳስሩ ዘላለም እኖርበታለሁ ብለው በደካማው ሰውነታቸው ሲያስቧት የነበረችውን ምድር ለቤተክርስቲያን አድም በጎ ነገር ሳይሰሩ የቀደሙ አባቶች ያቆየቱን እንኳ ማስቀጠል ተስኗቸው ላይመለሱ ምድርን እየጓጓት ተሰናበቱ ከግብረአበራቸው ጋር አብረው ፈረሱ ፡፡ አባ ማቲያስ ደግሞ ከዚህ መማር ይኖርባቸዋል ፡፡ በቀደሙ ብፁአን አባቶች በነ አቡነ ጴጥሮስ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ና በሌሎችም አባቶች ቦታ ላይ የተቀመጡ ናቸውና ሲሾሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለትም የእምነቱ ተከታዮች ብዙ ተስፋ ጠብቀን ነበር ፡፡ እሳቸውም ብዙ ለውጥ እንደሚያመጡ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ታዲያ ምን ወሰደው ያንን ንግር እና ወኔ? ይች ቤተ ክርስቲያን እደሆነች ዝም ስትል እግዚአብሔር እንደረሳት የሚያስቡ ሞኞች አሉ ፡፡ ሊያጠፏት የሚያስቡትን ታጠፋለች እንጅ እንደማትጠፋ ማወቅ አለባቸው፡፡ እነ ዮዲት ጉዲት እነ ግራኝ ሙሃመድ የጣሊያን ጦር ባድዋ ላይ የተመታው አባቶች የቅ/ጊዮርጊስን ጽላት በመያዛቸው ሃይልና ጽናትን ሰጥቷቸው እንደሆነ ማስታወስ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው እንደነዚህ ያሉ ደጋግ ሰዎች ተገኝተው ስለሃይማኖታቸው እናስተምር ሲሉ አይዟችሁ ከጎናችሁ ነኝ ምን ላግዛችሁ ማለት ሲገባ በተለያየ ምክንያት ማህበሩን ለመበተን ሲፈታተኑ ይታያል ይልቁንም ስለፖለቲካ ከሚሰብኩ የሃይማኖት መሪ ስለሆኑ እግዚአብሔር ስለሰጣጨው ስለ ሃይማኖታችን መስበክና ማስተማር እና የበጎቹን አደራ መወጣት ይገባቸው ነበር ፡፡እኛ እምናውቀውና የሃይማኖታችን አስተምሮ የሚመክረን በሃይማኖቱ የታነፀ ትውልድ ለመንግስት ታዛዥና ተገዠ አባቶቹን አክባሪ ይሆናል ነው፡፡ ስለዚህ አማኙ ስለ ሃይማኖቱ ይበልጥ በተረዳ ቁጥር ፍሪሃ እግዚአብሔር እያደረበት ምቹ የሆነ ማህበረሰብ ይፈጠራል፡፡ ይህንን መጠቀም ያልፈለጉት ከላይ እንደተጠቀሰው ምንአልባትም ሰይጣን ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
  መንግስትም ቢሆን በሰሙ የሚነግዱትን ወሮ በሎች ማጥራት አለበት የሚል አምነት አለኝ፡፡ በመንግስት መዋቅር ተሰግስገው የህዝብ ሃብት እየመዘበሩና ህዝቡን በመልካም አስተዳደር እጦት እያንገላቱ መኖራቸው አለበቃ ብሏቸው በቤተክርስቲያን ውስጥ ጣልቃ እየገቡ እየፈተፈቱ የጥቅማቸው ማካበቻ ያደረጉትን አመራሮቹን ማሳረፍ ይገባዋል፡፡
  በመጨረሻ ቅዱስ ጳትሪሪካችን ከዚህ ብልሹ አሰራራቸው ወጥተው ቤተክርስቲያኗን ቢመሯት መልካም ነው እላለሁ ፡፡
  እኔ የማህበሩ አባል አይደለሁም ነገር ግን የምትሰሩት ስራ ሁሉ በጣም ያረካኛል፡፡ በርቱ እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ፡፡ አመጸኞችን እግዚአብሔር ያስታግሳቸው፡፡

  • Anonymous March 26, 2016 at 4:52 pm Reply

   The heart of Amorewon and the heart of MK is the same. Please repent and retun back to the truth

  • Anonymous March 26, 2016 at 6:15 pm Reply

   That is great point!!!

 7. ትዕግስቱ መገራ March 27, 2016 at 1:49 pm Reply

  ማቲያስ ይበቃሃል፤፤አቁም ልንለዉ ይገባል፤፤ወሬ ብቻ ፤፤ዘረኛ ካድሬ ነው፤፤ማንን ሊመራ እንዳሰበ እናያለን፤፤

 8. getachew March 28, 2016 at 2:42 pm Reply

  በእግዚብሽን ማእከል እዉነት ዳግም ተሰቀለ
  ይህ ማእከል ከስሙ ብንጀምር ኢትዮጵያዊነትን የረሳ የsንs ባንዳዎች አዉቀዉ የተኙበት ይመስላል፤ ምክኒያቱም ስለ ሀገር ባህል፤ ታሪክ፤ ትዉፊት እና የገቢ ምንጭ የሚሰራ ማእከል ቢያንስ በአንዱ ሀገራዊ sንs‹ን መጠራት ይችል ነበር፤ ቢያንስ ከ2000 ዓ.ም ላይ አዉደ ርዕይ የሚል ምርጥ ስም ኢግዚብሽን የሚለዉን ባእድ ቃል ተክቶ በይፋ መጥቶ ነበር፤ ለዚህም ባህረ ጥበባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልትመሰገን ይገባታል፤ ማኅበረ ቅዱሳን ታዲያ ይህንን እና መሰል ሀገራዊ እና ቤተ ክርስቲያናዊ ጉዳዮች ከመሰረቱ ሳይከለሱ ለመጭዉ ትዉልድ እንድተላለፉ እየሰራ ያለ ትዉልድ አዳኝ የዘመኑ ወሳኝ ትዉልድ ስብስብ ነዉ፡፡ አሁን ስለ ማኅበሩ ልተርክ ሳይሆን እዉነት ግን እያለቀሰች ነዉና ህሊናየ የሚከነክነኝ ነገር ልተንፍስ፤ እዉነት ቦታ እና ጊዜ አጥታ ዉሸት እና አስመሳይነት ዓለምን ሞልተዉ እየፈሰሱ ነዉ፡፡
  ትናንት በጉጉት ይጠበቅ የነበረዉ የእዉነት ምስክርነት አዉደ ርይ ዘቤ/ክን ታግዶ በእምነት ብቻ አየነዉ፦
  በዚህ ድራማ ተዋናያን እነማን ናቸዉ
  ሀ/ ኤግዚብሽን ማእከሉ
  1. የሙዚቃ ድግስ ያዉም በተቀደሱ በዓላት በማዘጋጀት
  ይህ ፕሮግራም በቤተ ክርስቲያን ስም ለረጅም ዘመናት ሲነገድበት ብቻ ሳይሆን ሲቀለድበት ማለት በራሳችን የተከበሩ በዓላት ልዩ ዝግጅት እያሉ ሲጭፍሩ ሲያስጨፍሩ ኖሩ፤ ነገም ሳንባቸዉ ነዉና ይቀጥላል፡፡ ማንኛዉም ሰዉ የመጨፈር ብሎም የፈለገዉ የማመን እና የመግለጽ መብት ቢኖረዉም (በተግባር ሳይሆን በህልም) የሌሎችን መብት ግን ማክበር ግደታዉ ነዉ፤ የሆነዉ ግን በተገላቢጦሽነዉ፤ ለምን በሌላ ዕለት የሙዚቃ ድግስ አታዘጋጁም፤ ለምን በቤተ ክርስቲያን ስም ትነግዳላችሁ፤ ለነገሩ የዛፎች ጠላት በዛፎች መካከል የሞኖር ጠማማ እንጨት ዛቢያ በመሆኑ ማለቴ ደንበኞቻችሁ እኛዉ ኦርቶዶክሳዊያን ስለሆን ነዉ ይገባናል፡፡ ነገር ግን ሁለት ስህተቶች በግልጽ ይታያሉ አንድ የሙዚቃዉ ጩኸት በበዓላት ዕለት ሌላዉ አብዛኛዉ የንግድ እና ባዛራችሁ ደንበኞች የቁም ነገር ጊዜ ግን ባእዳኖች እኛዉ መሆናችን፡፡ ሁለቱም ግን ለቅድስት ቤተ ክርስጢያን አላማ የማይመጥኑ የዲያብለስን ተልእኮ የሚያፋጥኑ ናቸዉ፤ ለዚህ ርካሽ ተግባር ያሰለፋችሁት የዋህ ህዝብ ነፍስ ጥፋት ግን እግዚአብሔር ከእጃችሁ ላይ ይቀበላል፤ በኃጢዓት የተሰበሰቡ የይሁዳ ብርም የደም መሬት ይገዛ እንደሁ እንጅ ለመቃብር እንኳን አይሆንም፡፡
  2. የቤተ ክርስቲያንን ክብር የተዳፈሩ በርካታ የፕሮቴስታንት መርሃ ግብራት ፈቅዶ ማካሄዱ
  ሌሎች ለምን አካሄዱ የሚል ቅናት የለኝም፤ ለምን ቤተ ክርስቲያንን ተሳደቡ የሚል ቁጭት ግን አንጀቴን አቁስሎታል፡፡ በሙዚቃ ሰበብ በደስታ በዓላችን ሁሉ ልባችንን ስታደሙ የምትኖሩ እናንተ የማእከሉ ባለጊዜዎች እና ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣናት ወይም የቤተ ክህነቱ ፖለቲከኛች ሌላዉ ጉዳችሁ ደግሞ ባለፈዉ ተደጋጋሚ ጊዜ ለመፕሮቴስታንት መጨፈሪያ ፈቀዳችሁ፤ ይሁን ይህም ተመሳሳይነት ስላለዉ መብታቸዉ ነገር ግን በተለይ በ1990 ዓ.ም በተደረገዉ ኮንፈረንስ ቤተ ክርስቲያንን የስድብ መዓት ሲያወርዱባት፤ አሮጊት ሳራ ብለዉ እራሳቸዉን ግን ሰማይ ድረስ በትዕቢት ወጥረዉ ያካሄዱትን ጉባኤ እኛ ስለተወጋን አንረሳዉም፡፡ ይህ አዉደ ርዕይም ያንን ለመበቀል አይደለም፤ ለማስተማር እንጅ፤ እናንተ ግን ክፋትን ለሚዘራ፤ በጦር እና በብር ለሚያስብ እንጅ በእዉቀት እና በእምነት ለመጣባችሁ እንደት ሞት ሞት አላችሁ፤ በሰከነ መንፈስ፤ በፍቅር አይን እያዩ ለለመናችሁ ማኅበር እንደት ልባችሁ ደነደነ? ምክኒያት ይኖራል? ልበል ግን ምክኒያቱ ወቅታዊም በቂም እዉነትም ለመሆኑ ማረጋገጫ ለምን አጣችሁ፤ ይህ ደግሞ የከፋ ስህተት ሆነ፡፡ ስለዚህ እስካሁን ያቀሰላችሁነት ምእመናን በምን ልትክሱት ይሆን በቃ ወረቀት ላይ ባለ ይቅርታ? ይህማ ሌላ የባሰ ቀልድ እና ታሪካዊ በደል ነዉ፤ ተግባራዊ ምላሽ እና ካሳ አሁንም እንፈልጋለን፡፡
  3. ለመጀመሪያ ጊዜ ኦርቶዶክሳዊያን አዉደ ርዕይ ብንጠይቅ በአሳዛኝ ጊዜ እና ሁኔታ ተከለከልን
  በጣም የሚገርመዉ ደግሞ ይህ ነዉ፤ በዓላትን በማራከስ፤ የጭፈራ መድረክ በማድረግ በንፁህ ህዝብ ላይ ስትቀልድ ዝም ስለተባላችሁ በመቀጠል ደግሞ የስድብ አፍ በማዘጋጀት ክብራችንን ነካችሁ፤ አሁንም ዝም የልብ ልብ ተሰማችሁ፡፡ ስለዚህ ለዚህ በሰላም እና በፍቅር ለሚያምን ለጠላቱ የሚጸልይ ህዝብ ላይ ግፍ መስራቱን ቀጠላችሁ፤ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሌሎች ሁሉ እኛም ኢትዮጵያዊ ነን ብለን ኮርተን ነገር ግን አስፈላጊዉን ቅድመ ሁኔታ ሁሉ ጨርሰን፤ ብራችሁን ከፍለን፤ አንድ አመት ደክመን ተመላልሰን፤ ባለቀ ስዓት ፊት ነሳቹሁን፤ የበላይ ትእዛዝ ከማለት ዉጭ አብራችሁን የመፍትሔዉ አካል ለመሆን ያደረጋችሁት ጥረት ምን ነበር እንስማ ካለ ከሌለ ተዉት አንስማ፤ ምንም አንጠብቅም፤ ከማን ምን ይጠበቃልና፤ ስለዚሀም እወነት ተሰቅላ በማእከላችሁ ግቢ ታለቅሳለች፡፡ እዉነት ማን ናት ካላችሁ፤ ቅድስት ቤ/ክን፤ ወንጌል ናት፤ ከሁሉም በላይ ጌታዩ ፈጣሪየ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ፡፡
  4. ነገ ምን እንጠብቅ
  ምንም አንጠብቅም፤ ከማን ምን ይጠበቃልና፤
  ለ/ መንግስት
  እናንተ ባለጊዜዎች በቃላት ብቻ የሚገለጽ ስቅላት የለም፤ ሁሉም ነገር ከቃላት በላይ እየሆነ ነዉና፤ ገና በረሃ ሳላችሁ በቤተ ክረስቲያን ላይ ያላችሁ ጥላቻ እና ᎂርት ከየት አንደመጣ በዉል ባይገባኝም መሰረታዊ ሀሳብ ግን ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ የመጀመሪያ መሰረታዊ የሆነ ሀገራዊ የሆነ እሴት አትፈልጉም፤ በዚህም የአዉነት ሰቃይ ናችሁ፤ ገና ከጅምሩ የምትፈልጉት ፓትሪያሪክ አመጣችሁ በወንበር ላይ ተቀመጡ አቡነ ጳዉሎስ፤ በዚህም ህገ ወጥ አሰራር የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለሁለት ከፍሎ በማዳከም ህልማችሁ ተሳካ፤ በመቀጠል እናንተ 20 ዓመት አደስ ሀገር ስትገነቡ እኒህ አባት ለእናንተ ድንጋይ ከማቀበል ዉጭ አንድ የሚጠቅም ስራ ሳይሰሩ እንዲያዉም አላሰራ ብለዉ ባለህበት እርገጥ ስልጥከ17 ሚሊዮች ምእመናን በላይ በጎች በተኩላ አስበሉ፤ እርሳቸዉ ወደ እዉነቱ ቦታ ሲሄዱ አሁንም በለመደ ስልታችሁ ሌላ እንዲያዉም የበለጠ አቡነ ወያኔ አመጣችሁ ግን መሸወድ ትችላላችሁ፤ ነጻ ምርጫ እንደነበር ታወራላችሁ፤ ታስወራላችሁ፤ በዚህም አሁን በቅድስት ቤ/ከንን ደመወዝ እና ስም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ ለእናንተ የሚሰራ አባ አገኛችሁ፤ እርሳቸዉ ደግሞ በርካታ ቡችሎችን እንደጫጩት በየዕለቱ በመፈልፈል በዙ አሁን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆናችሁ፤ ሽታቸዉም መልካቸዉም ንግግራቸዉም፤ ዉሳኔያቸዉም ሁለንተናቸዉ በሙሉ የመለስን ለጋሲ ለማስቀጠል የተቀረጹ ሀዉልት ሆኑ፤ ግን ጎበዝ አናጺ ናቸሁ ወያኔዎች፤ በርቱ እስከ ትንሳኤ ተንፍሱ፡፡
  ሐ/ ቤተ ክህነት ያለዉ ጉድ
  በዚህ መዋቅር ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሚደክሙ በርካታ አባቶች እና ምእመናን እንዳሉ ቢሰማኝም የጋን መብራት ጨለማን ማሻገር አይችልምና ሆድ ይፍጀዉ፡፡ በተለይ ስድስተኛዉ ወያኔ አቡነ እና ጽ/ቤታቸዉ በአደስ አበባ ታሪክ ይቅር የማይለዉ የምንፍቅና ስራ በመስራት ዲያብሎስ ራሱ ገርሞት ራሳቸዉ ላይ ቆሞ እየተማረ ነዉ፡፡ እኒህ አባ እንደ ይሁዳ የሚመሳሰሉባቸዉ ነጥቦች ትንሽ ላንሳ
  1. በስም ደረጃ ሁቱም የተከበረ ስም ነበራዉ፤ ይሁዳ የእግዚአብሔር ህዝብ እንደማለት ነዉ፤ ፓትሪያሪኩም በአጸደ ስጋ ቅዱስ ተብለዉ የተጠሩ ብቸኛ ሰዉ ናቸዉ፤ ቤ/ከንን እንድህ አክብራቸዉ ነበር ግን……
  2. ሁለቱም የሐዋርያት አባላት ወይም የጌታ ደቀ ምርጦች ነበሩ፤ ልዩነቱ ይሁዳ በዘመኑ አይቶ ሰምቶ ተመርጦ ነበር፤ አባ ደግሞ በእምነት ምክኒያቱም ቤ/ከንን ሐዋርያዊት ናትና በትዉፊት ክህነቱ አስካሁን አለና፤ ያዉም ከይሁዳ የበለጠ ስልጣን፤ ታላቅ አባት እና ቅዱስ ነበሩ፡፡
  3. ሁለቱም በልባቸዉ ተንኮል አዝለዉ በአንደበታቸዉ ግን እባብ ናቸዉ፤ እባብ ለአላማዉ ብልነ ነዉ፤ ሄዋንን ሲያስት ተመልከቱ በአንደበቱ ሄዋን መረዳት የምትችለዉ ክፉ ነገር አልወጣዉም፤ ይሁዳ እኮ ጌታዉን በ30 ብር ሽጦ እርሱ ግን ሰላማዊ መስሎ ጌታዉን በመሳም አሳልፎ ሰጠ፡፡ አቡነ ወያኔም ገና ከሹመት ቀናቸዉ ጀምሮ በየአጋጣሚዉ የሰጡን ተስፋ ለካ እንደ ሄዋን ሰክረን የሰማነዉ እና እጸ በለስን ያስበላን ነበር፤ ዛሬ እዉነት ስትሰቀል ገባኝ፤ ስለዚህ በዉሸት ያወራሉ በእዉነት ቤ/ክንን ቁልቁል ይቀብራሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ሆይ ኢትዮጵያ ሆይ ትንሳኤሽን ማየት ናፈቀኝ፡፡
  4. ሁለቱም ገንዘብ ወዳጆች ናቸዉ፤ ለይሀዳ 30 ብር አባ 30*2008 ዛሬ 60240 በቀን ደረሰ፡፡ ሁለቱም ግን አይበሉትም፤ እዉነት እንዲሰቀል ግን ያደርጉበታል፡፡ ዛሬ ቤ/ክንን በነጻ ለመርዳት የተሰበሰበን ትዉልድ በዚህ ክፋት ብር ኃይል ለመምታት እና ለመቅበር እንቅል የላቸዉም፤ እስከሞት ድረስ ገና ይዋጋሉ፤ ተዋጊ ጦረኛ አባ እንደት ይርማሉ፤ ምናለ የጣሊያን ጦርነትጊዜ ቢኖረ ኖሮ አንሸነፍም ነበር፤ አይ ይህስ አይሁን አቡነ ወያኔ ብቻ አይደሉም ለካስ አቡነ ቫቲካንም ናቸዉ፤ እኛ እና ካቶሊክ አንድ ነን፤ የቀድሞ ፍቅራችን ይመለስ ያሉ አባ ያኔ ቢኖሩማ ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት፡፡
  5. ሁለቱም እዉነትን ሰቅለዋል፤ ይሁዳ አንድ ጊዜ አባ ማትያስ ግን ሽ ጊዜ እስከሞት ድረስ ደጋግመዉ ደጋግመዉ ክርስቶስን እያሳደዱ እየሰቀሉ ነዉ፤ ምእመናን ክርስቲያኖችን ማሳደድ መቼም ክርስቶስ ማሳደድ መሆኑ ግልጽ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነዉ፡፡
  6. ሁለቱም የሰይጣን እና ተሀድሶዉ አቀንቃኝ እና ተላላኪ ናቸዉ
  ተሀድሶ መናፍቃን ከቤተ መንግስት እስከ ቤተ ክህነት የተሳካላችሁ ነዉ የምትመስሉት፤ የሁሉም ችግሮች እና የሀሰት አባት ግን እናንተ መሆናችሁን ሳልጠቁም አላልፍም፡፡ ነገን ለእዉነት ትንሳኤ በእምነት ሆነን እንጠብቃለን፡፡
  መፍትሔ
   ነፍስ ይማር ለአባ ማትያስ ዘኢትዮጵያ፤ ትንሳኤ እና ድኅነት ለቤ/ክን፡፡
   ግብአተ መሬት ለወያኔ፤ ትንሳኤ ለኢትዮጵያ
   ትንሳኤ ልቡና ለእኔ እና ለመሰሎቼ ኦርቶዶክሳዊያን በሙሉ፤ በተለይ በየበዓላቱ በኤግዚብሽን ማእከል በመገኘት በጭፈራ እና ሸቀጥ በመሸጥ በመግዛት ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የችቃ እሾህ አንሁን ይቅርብን፤ ቤተ ክርስቲያንን ባንጠቅምም እንኳን ጠላት ወይም የጠላት ተባባሪ አንሁን፡፡
   ኤግዚቢሽን ማእከል በኦርቶዶክሳዊያ የሰራዉ ግፍ ካሳ ይክፈል፤ በራሱ ወጭ ለ14 ቀን አወደ ርዕዩን ያሳይ፤ ለሚቀጥለዉም በእኛ መቀለዱ ይብቃዉ፤ መብት የሚከበረዉ የግድ በጦርነት ብቻ ነዉ?
   ቅር ያለዉ ኤግዚብሽን ማእከል ይሂድ፤ በክህደት ተደስቶ ይመጣል፡፡

 9. tewodros March 30, 2016 at 8:36 am Reply

  አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይስጥልኝ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: