በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአ/አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደር: የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ስለምን ውኃ በላው?

 • የመሬትና የገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ውሳኔው አልተተገበረም፤ የጥናቱም ሒደት ታጉሏል
 • የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም የማያስከብሩ ውሎች በወጥነት መስተካከል ነበረባቸው
 • በጥናቱ የታዩ ጥፋቶች እንዲቀጥሉና አድባራቱ ተገቢ ጥቅማቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል
 • በፍጻሜው፥ ቤተ ክርስቲያን የመሬትና የሕንፃ ኪራይ ፖሊሲ እንዲኖራት አስተዋፅኦ ነበረው

*          *          *

 • የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ውሳኔውን ወደ አጥቢያዎቹ ባለማስተላለፉ ለውጤታማነቱ ተግዳሮት ኾኗል፡፡ ይህም ለቀጣዩ ጥናት ዕንቅፋት በመኾኑ ሒደቱ እንዲስተጓጎል አድርጎታል፡፡
 • የሕግ አውጭና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የኾነውን የበላይ አካል ውሳኔ አለማክበርና አለማስከበር ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያለን ንቀት ከሚያመለክት በቀር ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡
 • ብዙ የተደከመበት እና የውጤት ጭላንጭል የታየበት ጥናት በከንቱ እንዳይቀር፣ የሚመለከተው አካል በትኩረት ሊከታተለው ይገባል፡፡
 • ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የመሪነት ሚናውን በማስከበር ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ብሎ የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲኾን ሓላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

  /የአጥኚ ኮሚቴው ጸሐፊ ለዜና ቤተ ክርስቲያን ከጻፉት/

*          *          *

Yemane with parish heads

ዜና ቤተ ክርስቲያን በዚኽ ወር እትሙ በርእሰ አንቀጽ ደረጃ እንደነገረን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ ሙስናን አዳክመናል፤ መልካም አስተዳደርን አስፍነናል በሚል ራስን በራስ ለማስመስገን የሚካሔደው መሸላለም ድራማዊና የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ በሥራ አስኪያጁ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስና የምዝበራ ሰንሰለቱ እየተደረሰና እየተዘጋጀ በአማሳኞቹ የሚተወነው ድራማ በዚኹ ሳያበቃ፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስም በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ ቀጥሎ ውሏል፡፡

ቀንደኞቹ አማሳኞች(ሃይሌ ኣብርሃ፣ ዘካርያስ ሐዲስ፣ ነአኵቶ ለአብ አያሌው፣ ተስፋ ፍሥሓ)፤ የተሐድሶ ኑፋቄን በኅቡእ ከሚያቀነቅኑ ስመ ሰባክያንና እንደ አፈ ወርቅ ካሉ የክፍለ ከተማ ምግባረ ብልሹ ሓላፊዎች ጋር በመሪነት በተወኑበት ድራማ፥ ነውረኛ ሙስናቸውን ጽድቅ አስመስለው ሲያቀርቡ፤ ለዕቅበተ እምነት፣ ለሙስና መወገድ፣ ለመልካም አስተዳደርና ለፍትሕ መስፈን በየአጥቢያው የሚጋደሉ የምእመናን ማኅበራትን ግን በሁከት ፈጣሪነት፣ በፖሊቲከኛነትና በጥቅመኛነት ሥለዋል፤ ማኅበረ ቅዱሳንም ተመልሰው ባደሩ ጥያቄዎች ጭምር የተወነጀለ ሲኾን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አጸድቆና ፈቃድ አግኝቶ በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ ለማሳየት እያዘጋጀው የሚገኘው ዐውደ ርእይም፣ “ቅዱስ ሲኖዶስና ቅዱስ ፓትርያርኩ አያውቁትም” በሚል እንዲታገድ ተጠይቋል፡፡

ድራማውን በአንክሮ ሲከታተሉ የነበሩ ታዳሚዎች እንደተናገሩት፥ “ሲኖዶሳዊት ፓትርያርካዊት ቤተ ክርስቲያንን መፈታተን”፤ “የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን መቀናቀን”፤ “ከቅዱስ ሲኖዶስና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር መገዳደር”፤ “የቤተ ክርስቲያንን ቀኖናዊ አሠራርና መዋቅራዊ ሉዓላዊነት መፈታተን” የሚሉ ሐረጋተ ተውኔት ከድራማቲስቱ ሥራ አስኪያጅ በተደጋጋሚ መደመጣቸው መድረኩን ይበልጥ አስደናቂ (dramatic irony) አድርጎታል፡፡ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነትም በደብር ዋና ጸሐፊነትም አጃምሎ በያዘው ኢ-ሕገ ቤተ ክርስቲያናዊ ሥልጣን፣ የተጠያቂነትን መርሕ በመፃረር ቆዳውን ለማዳንና የበለጠ ለመጠቀም እየሠራ ባለበት ተጨባጭ ኹኔታ፤ ለመዋቅራዊ ሉዓላዊነት ጠበቃ መስሎ ሲኖዶሳዊነትንና ፓትርያርካዊነትን ሲደሰኩር መዋሉ(እያምታታም ቢኾን)፤ ድራማዊውን መድረክ በርግጥም በእጅጉ ምፀታዊ ያደርገዋል፡፡

በድራማዊ ስብሰባው ማግሥት ለንባብ የበቃው ዜና ቤተ ክርስቲያን በተመሳሳይ እትሙ፣ ይኸው የየማነ ዲስኩር ከንግግር ያለፈ አንዳችም ፋይዳ የሌለው መኾኑን በማሳያ አስነብቦናል፡፡ ጋዜጣው ከርእሰ አንቀጹ ባሻገር፣ “ንገሩን እንንገራችኹ” በተሰኘው ዓምዱ፣ “የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ስለምን ውኃ በላው?” በሚል ርእስ እንዳስነበበን፣ ቤተ ክርስቲያን የራሱዋ የገቢ ማስገኛ ተቋማትና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እንዲኖራት ታስቦ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በናሙናነት የቀረበው ጥናት፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስተዳደር ጉባኤ ተቀባይነት አግኝቶ ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ በሸፈናቸው 48 የሀገረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት እንዲተገበር መመሪያ ከተላለፈ ወራትን ቢያስቆጥርም፣ አፈጻጸሙ በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ቢሮ ታፍኗል፤ ጥናቱ፣ ባልሸፈናቸው አጥቢያዎችም እንዲቀጥል በቋሚ ሲኖዶሱ ቢወሰንም ሒደቱ በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አልታዘዝ ባይነት ተስተጓጉሏል፡፡

በዚኽም ሳቢያ ሀገረ ስብከቱ፣ የአጥቢያ አማሳኞች ከጥቅመኛ አካላት ጋር ተቆራኝተው የአድባራቱን መብትና ጥቅም በማሳጣት በገቢ ማስገኛ ተቋማቱ ላይ የሚፈጽሟቸው ምዝበራዎች ሳይታረሙ እንዲቀጥሉ ከማድረጉም በላይ በተገቢ የኪራይ ውሎች ቤተ ክርስቲያን ልታገኝ ይገባት የነበረውን ጥቅም እንዳታገኝም አድርጓል፡፡ የሕግ አውጭና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የኾነውን የበላይ አካል ውሳኔ አለማክበርና አለማስከበር ለቤተ ክርስቲያን ያለን ንቀት ከሚያመለክት በቀር ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፤” ያለው ጽሑፉ፤ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በአልታዘዝ ባይነት የተስተጓጎለውን ውሳኔውን በማስፈጸምና የጥናቱን ቀጣይነት በማረጋገጥ ችግሩን ከመሠረቱ የሚፈታ ርምጃ እንዲወስድና የመሪነት ሚናውን እንዲያስከብር በአጽንዖት ጠይቋል፡፡

Haile and Yemaneየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አፈጻጸሙን ያፈነበትና ሒደቱን ያስተጓጎለበት ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ በዋና ጸሐፊነት በሚሠራበት ደብር፣ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ልዩነት በታየበት የሕንፃ ዲዛይን ክለሳ ሰበብ ቃለ ዐዋዲውን በመተላለፍ ከፍተኛ ምዝበራ መፈጸሙን ጥናታዊ ሪፖርቱ አረጋግጧል፤ በዚኽ ረገድ የሚጠብቀውን የተጠያቂነት ዳና አጥፍቶ ሕገ ወጥ አካሔዱን ሕጋዊ ለማስመሰል፣ የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣኑን ተጠቅሞ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ለማጸደቅ ያደረገው ሙከራ ታዲያ ከሽፎበታል፤ መሰል ግንባታዎችንም በቋሚ ሲኖዶሱ ከተላለፈው ውሳኔና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከተሰጠው መመሪያ ውጭ በደብሩ እያስፈጸመ ይገኛል፡፡

በዚኽም ሳይገታ እንደ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያሉ ሌሎች አጥቢያዎችም ይዞታዎቻቸውን በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ለማልማት እየጠየቁ ባለበት ኹኔታ፣ “ከባለሀብት ጋር አልሙ” በሚል ግልጽ የጥቅም ትስስር ያለበትን ጫና ለመፍጠርም ሞክሯል፡፡ “የቅዱስነትዎንና የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ ማስፈጸም ሲገባቸው፣ አባቶቻችን ያቆዩትን መሬትና ሀብት በሕገ ወጥ መንገድ ለግለሰብ ለመዳረግ ከሀገረ ስብከቱ የመጣ መመሪያ ነው በሚል የሚንቀሳቀሱትን ዋና አስተዳዳሪውንና ጸሐፊውን እንዲያስጠነቅቁልን፤ ቢቻልም በመንፈሳዊ ትጋታቸው የሚታወቁ፣ የቤተ ክርስቲያንን ጥቅም አሳልፈው የማይሰጡ መሪዎችን እንዲመድቡልን እንጠይቃለን፤” ይላል – የደብሩ ልማት ኮሚቴ አባላት በኅዳር ወር ለፓትርያርኩ የጻፉት የተማጥኖ ደብዳቤ፡፡

ድራማቲስቱ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስና አማሳኝ ተዋንያኑ፣ የሰንበት ት/ቤቶችና የምእመናን ማኅበራት በዚኽ መልኩ እየታሰሩና በሐሰተኛ ክሥ እየተንገላቱ ለዕቅበተ እምነት፣ ለሙስና መወገድ፣ ለመልካም አስተዳደርና ለፍትሕ መስፈን በየአጥቢያው ያቀጣጠሉትን ንቅናቄ በፀረ ሰላምነትና ፖሊቲከኛነት ፈርጀው ራሳቸውን የሰላም ሐዋርያ አድርገው ከመተወናቸው በፊት ከበላይ አካል የታዘዙትን ሊፈጽሙ ይገባቸዋል፤ ማኅበረ ቅዱሳን፥ ለዘመናዊ የሒሳብ አመዘጋገብ አመቺ ኾኖ በተሻሻለው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሞዴላሞዴል እየተጠቀመ አሠራሩን ለተጠያቂነት ግልጽ ያደረገበትን ኹኔታ ክደው የተመለሱ ጥያቄዎችን እያመነዠኩ ከማላዘን ይልቅ ራሳቸውን ለመሰል አሠራር ዝግጁ ማድረጉ ይበጃቸዋል፡፡ ማኅበሩ፣ መድረክ አጥቶና ፍትሕ ተነፍጎ ለተበደለበት ጉዳይ እንደ ልጅነቱ ደብዳቤ በመጻፉ የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይነትና ቅዱስ ፓትርያርኩን እንደተገዳደረ እያደረጉ ከማወራከባቸው በፊት፣ የሚመሯቸውን አድባራት መብትና ጥቅም አሳልፎ ከመስጠትና ራሳቸውን በሕገ ወጥ መንገድ ከማበልጸግ ታቅበው በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተቀባይነት ያገኘውንና በቋሚ ሲኖዶሱ የጸደቀውን የገቢ ማስገኛና የመሬት አጠቃቀም መመሪያ መተግበር፤ ለጥናቱም ቀጣይነት ኹኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡

ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሀገረ ስብከቱ በተውጣጡ የሥራ ሓላፊዎች የተቋቋመው የመሬት፣ የሕንፃዎችና የገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ አጥኚ ኮሚቴ ጸሐፊ የኾኑትና ድራማቲስቱ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በመራው ስብሰባ የአማሳኞቹ ጥቃት አንዱ ዒላማ የነበሩት የዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ በጉዳዩ ላይ በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ያቀረቡት ጽሑፍ እንደሚከተለው ተስተናግዷል፡፡


የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ስለምን ውኃ በላው?

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ንገሩን እንንገራችኹ፤ ጥር እና የካቲት ፳፻፰ ዓ.ም.)

                                                                                                     እስክንድር ገብረ ክርስቶስ 

eskinder-gebre-kirstos-head-of-pd(የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ሓላፊ)

በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የመሬት፣ የሕንፃዎች፣ የሱቆችና የመካነ መቃብር ጉዳዮችን በዝርዝር በማጥናት፥ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ጥቅምና ጉዳት፤ የሚከራዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ኹኔታ በዝርዝር ተጠንቶ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በይቀጥላልም ለቅዱስ ሲኖዶስ በመቅረብ መፍትሔ እንዲፈለግለት ለማድረግ ይቻል ዘንድ በቀረበው ጥናታዊ ማስታዎሻ መነሻነት፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ የመምሪያና የክፍል ሓላፊዎችን ያቀፈ ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራው እንዲጀመር ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመምሪያና የክፍል ሓላፊዎች ተውጣጥቶ የተቋቋመው ይህ ኮሚቴ በወቅቱ ሥራውን የሚያከናውንበት የመስፈጸሚያ ዕቅድና የድርጊት መርሐ ግብር በመንደፍ፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁና በወቅቱ ሀገረ ስብከቱን ይመሩ በነበሩ ሊቀ ጳጳስ በማስገምገምና በማጸደቅ ወደ ሥራ ሲገባ በየሦስት ቀኑ አፈጻጸሙን፣ ያጋጠመውን ችግርና መፍትሔዎችን በመጠቆም ቅዱስ ፓትርያርኩና የሚመለከታቸው የሥራ ሓላፊዎች በተገኙበት የዕቅድ ክንውኑ እንዲገመገም ያደርግም ነበር፡፡

በዚኽ ግምገማ ላይም ለነዳጅ፣ ለትራንስፖርት ወዘተ… በሚል የኮሚቴ አባላቱን ለመደለል የሞከሩ የአድባራትና ገዳማት የሥራ ሓላፊዎች የስም ዝርዝር ሳይቀር በመግለጽ የግምገማው አካል እንዲኾን በማድረግ ሥራውን በግልጽነት ለማከናወን ተሞክሯል፡፡

በኹሉም የሥራ ክንውን ግምገማ ወቅትም፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ተጨማሪ የሥራ መመሪያን በመስጠት ለጥናቱ ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን ኹሉ በተግባር ተወጥተዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና የወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚደነቅና የሚመሰገን ብቻ ሳይኾን ሙስና ከቤተ ክርስቲያን እንዲጠፋ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም ያሳዩበት ጭምር ነበር፡፡

ጥናቱ በሚከናወንበት ወቅት ይህን ሓላፊነት ተቀብለው በጥናት ሥራው ላይ የተሠማሩ ሓላፊዎች በእጅጉ የተፈተኑበት ወቅት እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ተግዳሮቱ የጀመረውም፤ የአጥኚ ቡድኑን አባላት ስም በማጥፋት፣ በሙስና ለመደለል በመሞከርና እርስ በርስ እንዳይተማመኑ ለማድረግ በመሞከር ጭምር ነበር፡፡ የጥናት ቡድኑ ግን ጥናቱን በሚያካሒድበት ወቅት በሙሉ የርስበርስ ግምገማና የሥራ ግምገማ በማድረግ ችግሮችን ለመፍታትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ሥራዎቹን ያከናውን ስለነበረ ያጋጠሙትን እጅግ ፈታኝና እልክ አስጨራሽ ፈተናዎችን ኹሉ በጽናት ተወጥቷቸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ታላቅ አደጋ ኾኖ የሚታየው የፈጠራ ወሬና አሉባልታ፣ እርሱን ተከትሎ በተለያየ መልኩ የሚፈጠር ትንኰሳም የኮሚቴ አባላቱን በብርቱ የፈተነ ብቻ ሳይኾን አንዳንድ ሓላፊዎች ጭምር ከኮሚቴ አባላቱ ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ አደገኛ ኹኔታም ተፈጥሮ ነበር፤ ችግሩ በውይይትና በሥራ ግምገማ ሲታይ የተለመደ ተራ አሉባልታ ኾኖ ቢገኝም የኮሚቴ አባላቱን ትዕግሥትና የሥራ ተነሣሽነት በእጅጉ የፈተነ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በጥናቱ ወቅት ያጋጠውመውን ተግዳሮት ያኽልም በአንዳንድ አድባራት የገጠመው አዎንታዊ ምላሽና በአድባራቱ የተከናወኑ በጎ ሥራዎች፣ የኮሚቴውን ሞራል የገነቡና ሥራውን በተረጋጋ ኹኔታ እንዲቀጥል ያደረጉ ክሥተቶችም በጥናቱ ወቅት ተስተውለዋል፡፡ ይበልጡኑ የኮሚቴ አባላቱን ሞራል በእጅጉ ይገነባ የነበረው ግን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ የወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅርብ ክትትል እንዲኹም ሥራው በተገቢው መንገድ እንዲከናወንና እንዲጠናቀቅ የነበራቸው ብርቱ ጉጉት ነበር፡፡

በተቃራኒው አማሳኞች፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት ለመክበር በተለያየ መንገድ የተሠማሩ ጥቂት ወገኖችም፣ የአጥኚ ኮሚቴውን አባላት በማጣጣል፣ ስም በማጥፋትና በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በርካታ የትችት ጽሑፎችን በመልቀቅ የጥናት ሥራው ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት የበሬ ወለደ አሉባልታቸውን ሲነዙ ቆይተዋል፤ በተደራራቢ ሥራ ምክንያት የጥናት ሥራው ሲቀዛቀዝ የኮሚቴ አባላቱ ከእነእገሌ ረብጣ ብር በኪሳቸው ስለገባ ጥናቱን አቆሙት፤ በማለትና በማስወራት የጥናት ሥራው ውጤታማ እንዳይኾን ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡

ኮሚቴው ይህንና ይህን የመሳሰሉ ታላላቅ ፈተናዎችን አልፎ በግል ሰብእናውና በእያንዳንዱ የኮሚቴ አባላት ማንነት ላይ የተነጣጠሩ ፈተናዎችንና አደጋዎችን በመቋቋም በፍጹም ቁርጠኝነትና በፍጹም ቅንነት የመጀመሪያ ዙር የጥናት ሪፖርቱን አቀረበ፡፡

የመጀመሪያው ዙር ሪፖርት

ኮሚቴው የመጀመሪያውን ዙር ጥናታዊ ሪፖርት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ሲያቀርብ፣ የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ ጥናታዊ ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ ጥናቱ እንዲከናወን ለላኩት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በማቅረብ በቅዱስነታቸው በኩል እንዲታይ አድርጓል፡፡ በመቀጠልም ቅዱስነታቸው፣ ቋሚ ሲኖዶስ ጥናታዊ ሪፖርቱን እንዲመለከተው በማድረግ በሰነዱ ላይ የተቀመጡ አሳሳቢ ኹኔታዎች እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

ሰነዱ በአስተዳደር ጉባኤ ላይም ኾነ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሰብሳቢነት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ ሓላፊዎች በተገኙበት ውይይት ሲደረግበት፤ የሰነዱ ትክክለኛነት፣ ቤተ ክርስቲያን ያለችበት አሳሳቢ ኹኔታና ችግሩ ለዘለቄታው በሚፈታበት ኹኔታ፣ በጥናቱ ሰነድ ላይ የቀረበው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳገኘ ተረጋግጦ ጥናት ባልተደረገባቸው አድባራትና ገዳማት እንዲቀጥል የሚል የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦም ነበር፡፡

Quwami Synod Nehasse2007
ቤተ ክርስቲያን የራሱዋ የመሬትና የሱቅ ኪራይ ፖሊሲ እንዲኖራት በማድረግ ታላቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክተው የጥናት ሰነድ፣ ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየና ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በአስተዳደር ጉባኤው አባላት ያገኘውን ተቀባይነት በቋሚ ሲኖዶሱም በማግኘቱ ቋሚ ሲኖዶሱ የሚከተሉትን ዓበይት ነጥቦች የያዘ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

እነርሱም፡-

 • አጥኚ ቡድኑ ያቀረበውን ጥናት ቋሚ ሲኖዶሱ ሙሉ በሙሉ መቀበሉን፤
 • ጥናቱ በቀሩት አድባራትና ገዳማት እንዲቀጥል መወሰኑ፤
 • በጥናት ሰነዱ ላይ የቀረበው የማጠቃለያ ሐሳብ ማለትም ከቤተ ክርስቲያን ተከራይተው ለሦስተኛ ወገን የሚያከራዩ ወገኖች የሚያገኙት ጥቅም ተገቢነት የሌለው ስለኾነ የሦስተኛ ወገን ተከራዮች ለአከራዮቻቸው ይከፍሉት የነበረውን ክፍያ ለቤተ ክርስቲያን እንዲከፍሉ በማድረግ ውላቸውን ከቤተ ክርስቲያን ጋር እንዲያደርጉ፤
 • በየአድባራቱ ያለው ውል ወጥነት የሌለውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም የሚያስከብር ስላልኾነ ውሎች በሙሉ ወጥነት ባላቸውና ለአንድ ዓመት ብቻ የሚያገለግሉ ኾነው እንዲዘጋጁ፤
 • አጥኚ ቡድኑ ኹለተኛውን ዙር የጥናት ሥራውን መቀጠል ይችል ዘንድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለኮሚቴ አባላቱ አበልና ትራንስፖርት እንዲያዘጋጅ ወዘተ… የሚሉ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና ተጫውቷል፡፡

የውሳኔው ትክክለኛ ቅጂም በቁጥር 4949/22/07 በቀን 6/13/2007 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ በሸኚ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በተግባር ላይ ይውል ዘንድ ካስተላለፉት ወራት ተቆጥሯል፡፡
patriarchate head office to A.A Dio

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

መዋቅር ወይም የዕዝ ሰንሰለት ለአንድ ተቋም የህልውና መሠረት ነው፤ ነገር ግን መዋቅር ወይም የዕዝ ሰንሰለት ለአንድ ተቋም ህልውና መሠረት ሊኾን የሚችለው በየደረጃው የተቀመጡ የመዋቅር አካላት የዕዝ ሰንሰለታቸውን በሚያከብር መልኩ ሥራቸውን መሥራት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

ቋሚ ሲኖዶስ፣ የምልዓተ ጉባኤውን ውክልና ያገኘና በምልዓተ ጉባኤው መራጭነት የተሠየመ በመኾኑ የራሱ ኃይልና ሥልጣን ያለው መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ማክበርና ማስከበርም የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአህጉረ ስብከት ሚና መኾኑም ርግጥ ነው፡፡ የሕግ አውጭና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የኾነውን የበላይ አካል ውሳኔ አለማክበርና አለማስከበር ግን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያለን ንቀት ከሚያመለክት በቀር ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡

ከላይ እንደተገለጸው፣ በአዲስ አበባ አንዳንድ ገዳማትና አድባራት የተደረገውን የገቢ ማስገኛ ተቋማት ጥናት ተከትሎ የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠውን ውሳኔ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሓላፊነቱን ከላይ በጠቀስነው ቀንና ቁጥር በተጻፈ ደብዳቤ ተግባራዊ ሲያደርግ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ግን ውሳኔውን ማስፈጸም ተስኖት ሲታይ ያስገርማል፡፡

ከፍ ብሎ ከተራ ቁጥር1 እስከ 5 የተጠቀሱና መሰልነት ያላቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲያደርግ ትእዛዝ የተሰጠው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ውሳኔውን ወደ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ማስተላለፍ ባለመቻሉም በጥናቱ ወቅት የታዩና በሪፖርቱ የተካተቱ ጥፋቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልታገኝ ይገባት የነበረው ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓል፡፡

የጥናት ቡድኑ አባላትም ጥናታቸውን በኹለተኛው ዙር አጠናክረው በመቀጠል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን የገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃላይ ችግር ሊፈታ የሚችል ጠቋሚ ሰነድ በማዘጋጀት፣ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ፖሊሲ እንዲኖራት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መሥራት እንዳይችሉ ዕንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ስለኾነም ሀገረ ስብከቱ ለዚኽ ሥራ መቋረጥ ዋና ተጠያቂ መኾኑ አይቀርም፡፡

በጥናቱ የተገኙ አዎንታዊ ውጤቶች

ገርጂ ቅ/ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

Gerji Debra Genet St. George church02በገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከደብሩ በብር 6‚000 ተከራይተው ለአንዱ በብር 30‚000 ለሌላው በብር 55‚000 ሲያከራዩ የነበሩ ሰዎች ውላቸው ተቋርጦ ሦስተኛ ወገን ተከራዮች ለአከራዮቻቸው የሚከፍሉትን ክፍያ ለደብሩ በመክፈል ውል እንዲዋዋሉ በጥናቱ ወቅት ሐሳብ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የውሳኔ ሐሳቡን በማጽደቅ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተጽፎ፣ ደብሩ በሀገረ ስብከቱ የቀድሞው አስተዳደር በኩል የተሰጠውን ትእዛዝ በመቀበል ተግባራዊ በማድረጉ በየወሩ ግለሰቦች ኪስ ይገባ የነበረው ከብር 85‚000 በላይ ወደ ደብሩ ገቢ መኾን ጀምሯል፡፡

በመሠረቱ ለደብሩ የተሰጠውን ትእዛዝ በወቅቱ በመጻፍ ውሳኔውን ያስተላለፈው አካል ቀደም ሲል የነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር አካል በመኾኑ እንጂ በአኹኑ ቢኾን የውኃ ሽታ ኾኖ መቅረቱ አያጠራጥርም፡፡ ደብሩ በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረጉንም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በጻፋቸው ደብዳቤዎች አስታውቋል፡፡ ሌላው ቢቀር ቡድኑ በጥናቱ ወቅት በደብሩ በተገኘበት ወቅት የጠቋቆማቸውን የልማት ሥራዎችንም በአፋጣኝ ተግባራዊ በማድረግ የሚመሰገን ሥራ ሠርቷል፡፡

ከዚኹ ከተከራይ አከራይ ጋር በተያያዘም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ በሚሞክርበት ወቅት የገጠመውን ችግር በፍርድ ቤት በመጋፈጥ ጠንካራ ውሳኔዎችን በማስወሰንና የደብሩን ገቢ ለማሳደግ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሶ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ በማድረግ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ደብሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተሰጠውን ትእዛዝ በማክበር፣ የተጋነነ ዋጋ በማከራየት ይጠቀሙ የነበሩ ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ በመውሰድና ርምጃ በመውሰዱም ግለሰቦቹ በፍ/ቤት ክሥ ሲመሠርቱበት ጠንካራ ጠበቆችን በማቆምና በመሞገት ከሣሾች ላይ እንዲፈረድ በማድረግ የበላይ አካልን መመሪያ ጠብቆ ለማስጠበቅ የከፈለው መሥዋዕትነት ያስመሰግነዋል፤ መመሪያን በማስከበር የቱን ያኽል መሥዋዕትነት መክፈል እንደሚገባ አሳይቷልና በአርኣያነት ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡

ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን

በቤተ ክርስቲያኑ በሦስተኛ ወገን ተከራይነት የሚታወቁ ነጋዴዎች ቀደም ሲል በተሰጠው የውሳኔ ሐሳብ መነሻነት ቀጥታ ከደብሩ ጋር እንዲዋዋሉ ትእዛዝ ቢሰጥም ደብሪ ተግባራዊ ሳያደርገው ቆይቶ በቦታው ክሥና ንትርክ እንዲነግሥ አድርጎ ሰንብቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔውን ካስተላለፈ በኋላም፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ለሀገረ ስብከት የተጻፈውና ወደ አድባራት እንዲሠራጭ የታዘዘው ወረቀት እንደሌሎቹ ኹሉ ለደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንም ስላልደረሰው/በሀገረ ስብከቱ ታፍኖ ስለቀረ/ ቀድሞም ተግባራዊ ያላደረገውን መመሪያ በአስገዳጅነት ተግባራዊ እንዳያደርግ ኾኖ ቆይቷል፡፡

patriarchate office on Yoh Wolde Negod
በደብሩ ያሉ የሦስተኛ ወገን ተከራይ ነጋዴዎችም ስለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሰሙትን መነሻ በማድረግ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዘንድ በተደጋጋሚ አመልክተዋል፡፡ በዚኽም ምክንያት በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ ቅዱስ ፓትርያርኩ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ደብዳቤ በመጻፍ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ግን ቀድሞውኑም የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳላደረገ ኹሉ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጠውን ኹለተኛ ውሳኔና መመሪያም ተግባራዊ ሳያደርገው ቀረ፡፡ ይኹንና ደብዳቤው ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሲጻፍ ለደብሩ በግልባጭ ስለደረሰው፣ ውሳኔውንና ትእዛዙን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የደብሩ ሓላፊዎች በሀገረ ስብከቱ ሊደርስባቸው የሚችለውን ተጽዕኖ ተቋቁመው የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና የቅዱስ ፓትርያርኩን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰኑት ውሳኔ ለበላይ አካል መታዘዝን ለሀገረ ስብከቱ ያስተማረ አፈጻጸም በመኾኑ የሚደነቅ ነው፡፡

በገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ አድባራት የታየው አዎንታዊ ኹኔታ በጥናቱ ከተጠቀሱት በጎ ጎኖች ጋር ተዳምሮ የጥናቱን ትክክለኛነት በማሳየት ረገድ ጉልሕ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡ የውሳኔ አፈጻጸም ሒደቶቹ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አልታዘዝ ባይነት ባይሰናከሉ ኖሮ ለቤተ ክርስቲያን የቱን ያኽል ይጠቅም እንደነበር በማጋለጥ ረገድ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡ እዚኽ ላይ፣ ጥናቱን መነሻ በማድረግ የማስተካከያ ሥራ እንዲሠሩ ታዘው በማን አለብኝነት ሳይፈጽሙ የቀሩና በሕገ ወጥ መንገዳቸው የቀጠሉ አድባራት መኖሯቸውንም ልብ ይሏል፡፡

ለማጠቃለል ያኽል፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ ታምኖበት፣ በአስተዳደር ጉባኤ ጸድቆ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተውጣጡ ሓላፊዎች የተጀመረው የጥናት ሥራ የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ ችግር በማመላከት ረገድ ታላቅ አስተዋፅኦን አበርክቷል ተብሎ ይታመናል፡፡ ችግሩ የተጨበጠና በእውነት ላይ የተመረኮዘ በመኾኑም በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስተዳደር ጉባኤ፤ በቅዱስነታቸውና በአስተዳደር ጉባኤ እንዲኹም በቋሚ ሲኖዶሱ በኩል ተቀባይነት ያገኘ ሰነድ ለመኾን በቅቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ችግር እንደሚቀርፍ ታምኖበት የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ የሚኾነውና ለውጥ ማምጣት አለማምጣቱ የሚታወቀውም፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ጥናቱ በሸፈናቸው አድባራት ተፈጻሚ ሲኾን ነው፡፡ ይኹንና የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ውሳኔውን ወደ አጥቢያዎቹ ባለማስተላለፉ ለውጤታማነቱ ተግዳሮት ኾኗል፡፡ ይህም ለቀጣዩ ጥናት ዕንቅፋት በመኾኑ ሒደቱ እንዲስተጓጎል አድርጎታል፡፡

የጥናቱ ዋነኛ ዓላማ ችግሮችን መለየት፣ ለተለዩት ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከትና ችግሮቹን እስከወዲያኛው ለማስወገድ ሕጋዊ መመሪያ እንዲዘጋጅ መጠቆም ነው፡፡ ይኸውም በሰነዱ እንደተመለከተው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ያሉበትን ዝርዝር ኹኔታ ማጥናትና ቤተ ክርስቲያን ጥናቱን መነሻ ያደረገ የገቢ ማስገኛ ተቋማትና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እንዲኖራት ማድረግ ነው፡፡ በዚኽ መሠረት ኮሚቴው የተጣለበትን ሓላፊነት በሚገባ ተወጥቷል፡፡

በግሌ ጥናቱ ተጠናክሮ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብዙ የተደከመበትና የውጤት ጭላንጭል የታየበት ጥናት በከንቱ እንዳይቀር የሚመለከተው አካል በትኩረት ሊከታተለው ይገባል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የመሪነት ሚናውን በማስከበር ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ብሎ የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲኾን ሓላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ውሳኔ መስጠት ብቻውን ውጤት ስለማያመጣ አስፈጻሚዎቹን መፈተሽና ችግሩን ከመሠረቱ መፍታት ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬም ጥናቱ የቆመው በአጥኚው ቡድን ችግር መስሎ የሚታያቸው ወገኖችም፣ በዚኽ ማስታወሻ መጠነኛ ግንዛቤ ይጨብጣሉ ብዬ አምናለኹ፡፡ ይቆየን፡፡

Advertisements

9 thoughts on “በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአ/አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደር: የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ስለምን ውኃ በላው?

 1. asefa February 29, 2016 at 10:25 am Reply

  ortodox kurat new!!!!!!!!!

 2. fesha negash February 29, 2016 at 12:55 pm Reply

  እሱ ባለ ጊዜ አንተ ባለ ሥጋት፣
  ምን አገባህና ወደ ማታ ቅናት፣
  እንኳን የእጅ ሰዓት የወርቅ ሐብላት ትልቁ ብራስሌት፣
  አንተ ምን አገባህ ለሚስቱ ቢሰጣት፣
  ይሁነ በጊዚያቸው ቶሎ ቶሎ ይሙሉት፣
  ደግሞ የተራበ እስከሚተካበት፡፡
  በባዶ ኪስ ነበር በርግደው ሲገቡ፣
  ጳጳሱን ሲገፉ ምስኪኑን ሲሰድቡ፣
  እኮ ምን ይደረግ ባለጊዜ ናቸው፣
  የሰቀለው እርሱ እስከሚያወርዳቸው፡፡

 3. Anonymous February 29, 2016 at 3:04 pm Reply

  ሀቁን ለማወቅ ለሚፈልጉ ቅን አንባቢዎች የምመክረው ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣን ካለበት ፈልገው እንዲያነቡ ነው፡፡ጋዜጣው የሚገኝበትን የዌብ ሳይት አድራሻ በወላዲተ አምላክ ስም እለምናችኋለሁ አውጡልኝ፡፡ከምንደባበቅ ሰው አይቶ እና አመዛዝኖ ፍርድ ይስጥ፡፡የሚችል ጋዜጣውን ይግዛ የማይችል ጭኖ ያንብበው፡፡ http://eotcssd.org/images/stories/PDF/zenabet.pdf

 4. Anonymous March 1, 2016 at 5:01 pm Reply

  ማህበረ ቅዱሳን ለቅዱስ ፓትሪያሪኩ ደብዳቤ ሲፅፍ በግልባጭ ለትግራይ መንግሰት፣ ለትግራይ ደህንነት ቢሮ እና ለትግራይ ፓሊስ ኮሚሽን አሳዉቋል፡፡
  ለምን ለኦሮሚያ መንግስት አላሳወቀም፣ ለምን ለኦሮሚያ የደህንነት ቢሮ አላሳወቀም፣ ለምን ለአፋር መንግስት፣ ለደቡብ መንግስት፣ እና የመሳሰሉት በግልባጭ አላሳወቀም?
  ማህበረ ቅዱሳን አላማዉ ትግሬን መቃወም ነዉ?
  ይህ የማህበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴ ትግሬዎችን ለማስጠላትና በስንት ወንድሞቻችን ደም የመሰረትነዉን መንግስት መናድ ነዉ፡፡
  ማህበረ ቅዱሳን ዋጋዉን ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በአስቸኳይ፡፡

  • Anonymous March 1, 2016 at 9:57 pm Reply

   Miskin Anonymous. Debdabe melse sitsaf yetsafew akal teketilo new. Ahun ante kemengist gar lemagachet memokerih new? Ante erasih tiris wusit eyegebah mohonun alemawekih yasafiral.

 5. Anonymous March 1, 2016 at 5:03 pm Reply

  ማህበረ ቅዱሳን ‹‹ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል›› የሚባለዉ ዓይነት ስለሆነ ለቤተክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ መፍረስ ይገባዋል፡፡ ፓትርያሪኩም ይህንን የማህበረ ቅዱሳንን መፍረስ በተግባር እንደሚያሳዩ እርግጠኞች ነን፡፡

 6. Anonymous March 2, 2016 at 9:55 am Reply

  በእውነቱ ሃይማኖት ያለው ሰው እውነቱን ይረዳል ቤተክርስቲያንን ልንጠብቅ ይገባል ተወደደም ተጠላ እኛ የናቡቴ ልጆቸ ቤተክርስቲያንን እናስከብራለ

 7. tadi wolde March 7, 2016 at 12:06 pm Reply

  ትክክለኛ የቤተክርስትያን ተቆርቋሪ ሳትሆን የምታልባት ላም ወተቷን እንድትከለክል ስለታሰበ ጉዳዩ ስላንገበገበህ ነው። የኢትዮፒያዊነት ደም የሌለህ ሆዳም ሁላ በፍርድ ቀን ምን ይውጠሃል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: