የአብያተ ክርስቲያን፣ የካህናትና የምእመናን ምዝገባ ሊካሔድ ነው፤ የመላው አገልጋዮችና ምእመናን ንቁ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ ነው

  • የአሠልጣኞች ሥልጠና በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ተሰጥቷል
  • ለማረሚያ ቤቶች፣ ለገዳማትና ለአብነት ት/ቤቶች ትኩረት ይሰጣል
  • የውጭ አህጉረ ስብከት ምዝገባ በመገናኛ ቴክኖሎጂው ይመቻቻል
  • ውጤቱና ትንተናው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ እንደሚታወቅ ይጠበቃል
  • ቤተ ክርስቲያን፣ አገልጋዮቿንና ምእመናኗን የመመዝገብ መብት አላት

*               *               *

(ሰንደቅ፤ 11ኛ ዓመት ቁጥር 545፤ ረቡዕ፣ የካቲት 9 ቀን 2008 ዓ.ም.)

eotc logo
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባራቷን ተኣማኒነትና ተቀባይነት ባላቸው መረጃዎች ላይ ተመሥርታ በዕቅድ በመምራት ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለመወጣት የሚያስችላትን የአብያተ ክርስቲያናት፣ የአገልጋዮች እና የምእመናን ምዝገባ በቀጣዮቹ ኹለት ወራት ውስጥ እንደምታካሒድ አስታወቀች፡፡

ምዝገባው፥ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የአኃዛዊ መረጃ (ስታትስቲክስ) ክፍል አስተባባሪነት፣ ከመጪው መጋቢት መባቻ እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ 2008 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሔድ ታውቋል፤ የምዝገባውን ሒደት በትክክል ለማከናወን ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚሠራባቸው ልዩ ልዩ ቅጾች ተዘጋጅተው የተሠራጩ ሲሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም መሠራታቸውን የመምሪያው ሓላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ምዝገባው ያስፈለገበት ዋና ምክንያት፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን፣ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ወቅታዊና የተሟላ መረጃ ለመስጠት፤ ችግራቸውንና ጉዳታቸውን በዝርዝር በማጥናት የማጠናከርያና የመልሶ ማቋቋሚያ መርሐ ግብር ሥራ ለመሥራት፤ የልማትና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችን ለመቅረፅና ዕቅዶችን ለመንደፍ፤ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችሉ ቀመሮችን ለማዘጋጀት፤ የሕዝበ ክርስቲያኑን ብዛት የወደፊት ትንበያ(population projection) ሳይንሳዊ በማድረግ የት አካባቢ ምን ያስፈልጋል የሚለውን ለመወሰን እንዲያግዝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ይህንኑ የምዝገባ ሥራ በተመለከተ፣ ጥር 30 እና የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ያዘጋጀው የአሠልጣኞች ሥልጠና፥ ከ50 አህጉረ ስብከት ለተውጣጡ ሥራ አስኪያጆች፣ ለሰበካ ጉባኤ ዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ ለሒሳብ ሹሞች፣ ለሦስቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች ዲኖች እና ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የመምሪያ ሓላፊዎች በጽ/ቤቱ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ያላት የበጀት አቅም ከምታከናውነው መጠነ ሰፊ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት አንጻር ሲታይ እጅግ አነስተኛ እንደኾነ በሥልጠናው ተጠቁሟል፡፡ ለሀገራዊ ልማትና ለድህነት ቅነሳው የበለጠ አስተዋፅኦ ማድረግ ስለሚጠበቅባትም፤ ዕቅዶችን በመንደፍና የሥልጠና መርሐ ግብር በመዘርጋት የአፈጻጸም ስልት ቀይሳ ሰፊ ሥራ ማከናወን የምትችለው አብያተ ክርስቲያናቷን፣ አገልጋይ ካህናቷንና ምእመናኗን በሳይንሳዊ የአመዘጋገብ ስልት መዝግባ መያዝ ስትችል ብቻ እንደኾነም አጽንዖት ተሰጥቶበታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ አስተዳደራዊ መዋቅሯ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን በክፍል ደረጃ ማጠናቀር ከጀመረችበት ከ1975 ዓ.ም. ወዲኽ በየአምስት ዓመቱ አጠቃላይ የምእመናን ምዝገባ ስታካሒድ ብትቆይም፣ የሥራ ዘርፉና መረጃው በአንድ ገጽታው የተሻለ ዕድገት ሲገኝበት በሌላ በኩል ጥራትና ብቃት ሲያንሰው እንደሚታይ ለሥልጠናው በቀረበ ሰነድ ተጠቅሷል፡፡

ሥልጠናውን በአባታዊ ቡራኬና መመሪያ የከፈቱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፥ “በተለያየ ደረጃ በሓላፊነት ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት የአገልጋዮቿንና የምእመናኗን ቁጥር ማወቅ አለባቸው፤ ካላወቅን ሥራችንን ማከናወን አንችልም፤” በማለት የምዝገባውን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ በምዝገባው ጥራትና ብቃት ያለው መረጃ እንዲገኝና ሒደቱም ስኬታማ ይኾን ዘንድ፣ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት የየራሱን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው፤ አገልጋዮችና ምእመናንም መረጃ በመስጠትና በመመዝገብ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኹለት የሥነ ሕዝብ እና የአኃዛዊ መረጃ ምሁራን፥ ስለ ምዝገባ አስፈላጊነትና ባሕርያት እንዲኹም የምዝገባው ሒደት ምን መምሰል እንዳለበት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሥልጠና ለተሳታፊዎቹ ሰጥተዋል፡፡ የሥልጠናው ተሳታፊዎች የቡድን ውይይት ያካሔዱ ሲኾን ምዝገባው በአጥቢያ፣ በወረዳ ቤተ ክህነት፣ በሀገረ ስብከት እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በሚፈጸምባቸው በአራት ዓይነት የማስፈጸሚያ ቅጾችና ቁሳቁሶች ልምምድ አድርገዋል፡፡

በየዐሥር ዓመቱ የሚደረገው ሀገራዊ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የማይሸፍናቸው የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች (ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች) መኖራቸው በሥልጠናው ወቅት የተጠቆመ ሲኾን፤ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ በምታከናወነው ምዝገባ፣ በገዳማት ለሚገኙ ማኅበረ መነኮሳትና መናንያን፤ በአብነት ት/ቤቶች ለሚገኙ መምህራንና ደቀ መዛሙርት እንዲኹም ካህናት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡ ቅጾቹ የካህናትንና የምእመናንን ቁጥር ለማወቅ የሚሞላ በመኾኑ፣ ምዝገባው ከሕፃን እስከ ዐዋቂ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮችን ኹሉ የሚያካትት እንጂ የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ የከፈሉትን ብቻ ለይቶ መጻፍ አግባብ እንዳልኾነ የመምሪያው ሓላፊዎች ለሥልጠናው ተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አህጉረ ስብከት የሚኖሩ አገልጋዮችንና ምእመናንን ለመመዝገብ፣ የተለያዩ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ካህናትና ምእመናን ባሉበት መረጃ መስጠት እንዲችሉ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከአህጉረ ስብከት ጋር በመቀናጀት ኹኔታዎችን ያመቻቻል፤ ተብሏል፡፡

ከብር 400 ሺሕ በላይ ወጪ የተደረገበትን የመምሪያውን የኹለት ቀናት የአሠልጣኞች ሥልጠና የተሳተፉት የአህጉረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች፣ በየደረጃው ለሥራው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ለማሠልጠን ዝግጅት እያደረጉ መኾኑ ተገልጿል፡፡ ምዝገባውን ለማከናወን በርካታ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ሲኾን በአጥቢያ ደረጃ የንስሐ አባቶችን፣ የሰንበት ት/ቤቶችን፣ መንፈሳውያን ማኅበራትን፣ የዕድር አባላትን በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት በማስተባበር በማረሚያ ቤቶች፣ በገዳማትና በአብነት ት/ቤቶች…ወዘተ ያሉትን ጨምሮ ኹሉም ምእመናን እንዲመዘገቡ ማድረግ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

የምዝገባውን ዝርዝር አኃዛዊ መረጃዎች በማጠቃለልና የስታቲስቲክስ ውጤቶችን በጥልቀት በመዳሠሥ የመተንተን ሥራ እስከ ግንቦት መጨረሻ የሚጠናቀቅ ሲኾን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የትንተናው ዘገባ ተዘጋጅቶና ታትሞ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግበት ለአፈጻጸሙ ከወጣው የጊዜ ሰሌዳ ለመረዳት ተችሏል፡፡

Picture 069
ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ የመንበረ ፕትርክናውን ነጻነት በመቀዳጀት በራሷ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ፓትርያርክ እየተመራች ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ በሀገር ውስጥ 50፣ ከሀገር ውጪ 12 ያህል አህጉረ ስብከት፤ ከ500 በላይ የወረዳ አብያተ ክህነት፣ ከ35 ሺሕ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ያሏት ሲኾን ከ50 ሚሊዮን በላይ ምእመናንን አቅፋ እንደያዘች የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

Picture 110
ፓትርያርኩ በየጊዜው እንደሚያነሡት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ቁጥር “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣት” ቤተ ክርስቲያን ካጋጠሟት ተግዳሮች ዋነኛው ሲኾን፣ በ1999/2000 ዓ.ም. በሀገሪቱ በተካሔደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃ መሠረት፣ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 43 ነጥብ 5 በመቶ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ መኾኑ ይታወቃል፡፡ ይኸው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፥ በማረሚያ ቤቶች፣ በገዳማትና በአብነት ት/ቤቶች እንዲኹም በተለያዩ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚገኙ አገልጋዮችና ምእመናን አልተካተቱም፤ በሚል ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት ቅሬታ አቅርባ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የአብያተ ክርስቲያን፣ የካህናትና የምእመናን ምዝገባ ሊካሔድ ነው፤ የመላው አገልጋዮችና ምእመናን ንቁ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ ነው

  1. anonymously February 18, 2016 at 8:52 am Reply

    Mekuteruna mekoteru aykefam ; gin mimenun yemiyatsena Abat yifeligal! Menekosatu; kahinatu ; Sebakiyan yet nachew!!??? Be Arsenal maliya le Manchester yemichawetu !!?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: