ፓትርያርኩ፡የማኅበረ ቅዱሳንን ደንባዊ ህልውና የሚክድ የክሥ መመሪያ ለኮሌጆች አስተላለፉ፤ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ቀሰቀሱበት

  • “ቅዱስ ሲኖዶሱን በመጋፋት ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየፈጸመ ነው”   /ፓትርያርኩ/
  • “የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ በመፈጸምና ለአባቶች በመታዘዝ ታሪክ እየሠራ ነው” /የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ/
*               *               *

(ሰንደቅ፤ ረቡዕ፤ ጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም.)(ደብዳቤውን ከዜናው በታች ይመልከቱ)

Aba Mathiasooፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለሚገኙት ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ መቐለ ለሚገኘው ለቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በአድራሻ በጻፉት ደብዳቤ፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ “የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን በመጋፋት እና ቤተ ክርስቲያንን በማተራመስ ቀኖና የለሽ ሥርዓት ሲከተል ይስተዋላል፤ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየፈጸመ ነው፤” ሲሉ ከሠሡ፤ የማኅበሩን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘገባ ሰበብ በማድረግ በኮሌጆቹ አንዳንድ አካላት በማኅበሩ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መመሪያ አስተላለፉ፡፡

ፓትርያርኩ በዚኹ የጽሑፍ መመሪያቸው፣ ማኅበሩ ከኦርቶዶክስ ቀኖና ውጭ በመዋቅር ያልታቀፉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው እና የተበታተኑ ማኅበራት እንዲፈጠሩ እና ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በየመንደሩ እና በየአዳራሹ እንዲሰበሰቡ በማድረግ ኦርቶዶክሳዊ ያልኾነ ባህልን እንዲለማመዱ፣ እንደዚኹም ከኦርቶዶክስ ቀኖና እንዲያፈነግጡ መጥፎ በር በመክፈት የነገዪቱን ቤተ ክርስቲያን ሰው አልባ የሚያደርግ ኹኔታ ፈጥሯል፤ ሲሉ በርካታ ነጥቦችን ያዘለ ጠንከር ያለ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

ፓትርያርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለፌዴራል ፖሊስ እና ለትግራይ ክልላዊ መንግሥታዊ አካላት ጭምር በግልባጭ ባሳወቁት በዚኹ መመሪያ አዘል ደብዳቤአቸው ማሳረጊያ፣ ለኮሌጆቹ ማሳሰቢያ እና መመሪያ ሰጥተዋል፡- “አኹን እየተከሠተ ያለው ኹኔታ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ስለኾነ የኮሌጆቹን ቀጣይ ህልውና በዘላቂነት ለመጠበቅ የተጠናከረ፣ የተደራጀ እና ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሥራት ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያንና በት/ቤቶቿ ላይ የቀሠራቸውን የጥፋት ጣቶቹን መልሶ ወደ ኪሱ እስኪከትና ለቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊ ሕግ ተገዢ እስኪኾን ድረስ የማያቋርጥ ትግል በማድረግ በንቃት መከታተል ይጠበቅባችኋል፡፡ አንድነታችኹን፣ ሃይማኖታችኹንና ሰላማችኹን ከማስጠበቅ ጋር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ ሉዓላዊ ክብር እና ህልውና ለማስጠበቅ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ኹሉ ቤተ ክርስቲያን ምንጊዜም ከጎናችኹ መኾንዋን በዚኽ አጋጣሚ ልናረጋግጥላችኹ እንወዳለን፤”  የተቃውሞ ቅስቀሳ አካሒደውበታል፤ ለእንቅስቃሴውም መጠናከር አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

mahibere-kidusan-logoማኅበረ ቅዱሳን በጉዳዩ ላይ ከሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየቱን ተጠይቆ፣ ዋና ጸሐፊው አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ በሰጡት ምላሽ፤ ፓትርያርኩ ለኮሌጆቹ ጻፉት የተባለው ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ጠቅሰው ነገር ግን በመረጃ ደረጃ ስለ ደብዳቤው መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡

በደብዳቤው ስለ ቀረቡት ክሦችም፣ ፓትርያርኩ ማኅበሩን በየጊዜው በሚከሡባቸው ጉዳዮች አመራሩን አቅርበው እንዲያነጋግሩ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፤ ነገር ግን እኒኽን ክሦች ለተለያዩ አካላት ማቅረባቸውን ከመቀጠላቸውም አልፈው ማኅበሩ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን እንደሚጋፋና ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየፈጸመ እንደሚገኝ፣ መጥቀሳቸው በቅዱስነታቸው ደረጃ የማንጠብቀውና በእጅጉ ያሳዘነን ጉዳይ ነው፤ ብለዋል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ በ1994 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎና ጸድቆ የተሰጠው መተዳደርያ ደንብ እንዲሻሻልለት ማኅበሩ መጠየቁን ያስታወሱት ዋና ጸሐፊው፤ ቅዱስ ሲኖዶስም በግንቦት 2004 ዓ.ም. ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሕግ ባለሞያዎች እና የማኅበሩ ተወካዮች ያሉበት ኮሚቴ በማቋቋም እንዲሻሻል ወስኖ የማሻሻል ሥራው ተሠርቶ በ2006 ዓ.ም. ተጠናቅቆ ነበር፤ ይኹንና የማኅበሩ አባላት ለምን በኮሚቴ ውስጥ ተካተቱ በሚል ረቂቁ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሳይቀርብ በዚኹ ዓመት ሒደቱ እንዲቆም ተደርጎ የማኅበሩ ተወካዮች ያልተካተቱበት ሌላ ኮሚቴ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ተቋቁሞ ማሻሻያውን እየሠራ መኾኑን እንደሚያውቁና መረጃውም እንዳላቸው አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ ደንብ ተሻሽሎ እስኪጸድቅ ድረስ ማኅበሩ ቀደም ብሎ በነበረው ደንብ የመመራት መብት እንዳለውና ግዴታም እንዳለበት አቶ ተስፋዬ አስገንዝበዋል፡፡ አዲስ በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ የማኅበሩ ተወካዮች በሌሉበትና አንዳችም ዕንቅፋት ባልፈጠሩበት ኹኔታ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ማኅበሩ የማሻሻያውን ሒደት ኾን ብሎ ያሰናክላል መባሉ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፤ ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ማኅበሩ፣ የአባላቱንና የበጎ አድራጊዎችን የሞያ እና የገንዘብ አስተዋፅኦ በማስተባበር ቅዱሳት መካናት እና የአብነት ት/ቤቶች እንዲደገፉ የማድረግ ተግባር ተሰጥቶት ሳለ፣ ከቤተ ክርስቲያን ሳይጠየቅ እና ሳይፈቀድለት በጣልቃ ገብነት፣ የአብነት መምህራንን፣ ገዳማውያንንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለድብቅ ዓላማው መሣርያ እንዲኾኑ ያታልላል፤ በሚል በፓትርያርኩ ደብዳቤ የቀረበው ክሥ የማኅበሩን አገልግሎት የሚገልጸው አይደለም፤ በማለት አቶ ተስፋዬ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ፣ በፓትርያርኩ በሥራ አስኪያጅነት በተሾመበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በየሰበቡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያካበተ ይገኛል፤ ልጄን በውጭ ሀገር ለማሳከም በሚል ብቻ እንኳ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ከየአድባራቱ ሰብስቧል፤ ይህንንም እስከ 7 ሚሊዮን ብር የማድረስ ውጥን ይዞ እየሠራ ነው፤ ቀደም ሲል፣ ከሥራ አስኪያጅነቱ ጋር ደርቦ በያዘው የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ዋና ጸሐፊነቱም ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ልዩነት በታየበት የሕንፃ ዲዛይን ማሻሻያ ስም ሚሊዮኖችን መዝብሯል፤ ቋሚ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በመጣስ በደብሩ ከሕንፃ ግንባታ ጋራ በተያያዘ በልማታዊነት ስም የሚፈጽመው አንቃዥነትም በፓትርያርኩ ቡራኬ ጭምር ቀጥሏል፤ ይህም ኾኖ በሀገረ ስብከቱ መልካም አስተዳደር ሰፍኗል በሚል ባለፈው ሰኞ ከፓትርያርኩ ጋራ ተሸላልሟል፤ በዚኹ ዕለትም በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የፓትርያርኩ የክሥ እና የቅስቀሳ መሪያ የተላለፈበትን ደብዳቤ ከኮሌጆቹ ግብረ አበር ሓላፊዎች ጋር አዘጋጅቶ ያቀረበው እርሱ ነው – በተለያዩ ግርዶሾች የከፋ የሙስና ወንጀሉን በመሸፈን የዘረፋና የምዝበራ ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ!


 ከማኅበሩ የንብረት እና የገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ፣ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው ሀብት ያለካርኒ እየሰበሰበና እያደለበ እንደሚገኝ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ተስፋዬ በሰጡት ምላሽ፣ ይህ ክሥ የማኅበሩ የሒሳብ እና የንብረት እንቅስቃሴ ሪፖርት በሚቀርብለት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካል ያልቀረበ፣ ከእውነታው ጋር የሚጋጭ እና ተጨባጭነት የሌለው ነው፤ ብለዋል፡፡ ማኅበሩ በዚኽ ረገድ በሚከተለው ደንባዊ አሠራሩም÷ የአገልግሎት ዕቅዱን በየዓመቱ፣ ክንውኑንም በየመንፈቁ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በማሳወቅ በተሻሻለው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሞዴላሞዴሎች እየተጠቀመ፣ በሕጋዊ ኦዲተር እያስመረመረና ይህንንም ሪፖርት እያደረገ እንደሚገኝ በስፋት አብራርተዋል፡፡ 

ለፓትርያርኩ ክሥ እና መመሪያ በዋናነት መነሻ የኾነው፣ የስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ የኅዳር አጋማሽ 2008 ዓ.ም. እትም ዘገባ ሲኾን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ውስጥ ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ በተፃራሪ የሚካሔዱ የኑፋቄ እንቅስቃሴዎችን በማጋለጥ እና በማሳወቅ ላይ ያተኮረ ዘገባ እንደነበር አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል፡፡

ይህ ዘገባ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባዎች በተላለፉ ውሳኔዎች እና የአቋም መግለጫዎች፣ ለማኅበሩም በደንቡ በተሰጠው ድርሻ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ ሥርዓት እና ትውፊት ለመጠበቅ የቀረበ የዕቅበተ እምነት ተግባር እንጂ ኮሌጆቹን በጅምላ በሃይማኖት ሕጸጽ ለመክሠሥ ያለመ እንዳልኾነ፤ ዋና ጸሐፊው ያስረዳሉ፡፡

ማኅበሩ ከአብዛኞቹ የኮሌጆቹ ሓላፊዎች እና መምህራን ጋር ያለው ተቋማዊ ግንኙነት መልካም እንደኾነ የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ፣ ልዩነትም ካለ በሃይማኖት አቋም ባለ አሰላለፍ እንደኾነ በአጽንዖት አስቀምጠዋል፡፡ በዘገባው የኮሌጆቹን ስም የሚያጠፋው፣ የራሱን ት/ቤት ሊያስፋፋ ነው ለተባለውም፣ ማኅበረ ቅዱሳን ገዳማትንና የአብነት ት/ቤቶችን ባሉበት፣ እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የነፃ ትምህርት ዕድል ያሉ ፐሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን እየቀረጸ ማኅበራዊ ኑሯቸውን ከመደገፍ በስተቀር እነርሱን የሚያስተምረው ትምህርት የለውም፤ ሲሉ ውንጀላውን ተከላክለዋል፡፡

በአጠቃላይ የስምዓ ጽድቅን ዘገባ መነሻ በማድረግ በማኅበሩ ላይ የቀረቡ ክሦች መሠረተ ቢስ ናቸው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ማኅበረ ቅዱሳን፥ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በመፈጸም፣ የአባቶችን መመሪያ በመቀበል እና ለአባቶች በመታዘዝ ፣ ቅዱሳት መካናትንና የአብነት ት/ቤቶችን በመደገፍ እና በመጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን ማእከል ያደረገ ጥናትና ምርምር በማካሔድ፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት እንዲኹም በመንግሥት እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን አሰባስቦ በሃይማኖት በማነፅ እና በሥነ ምግባር በመቅረፅ ለሀገር እና ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ እየሠራ እንጂ በፓትርያርኩ መመሪያ እንደሰፈረው፣ “ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየፈጸመ”  እንዳልኾነ፤ አበክረው ተናግረዋል፡፡

*               *               *
ፓትርያርኩ፥ የማኅበረ ቅዱሳንን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሚዲያዊ ዘገባ ምክንያት በማድረግ የቀረበበት ክሥና ውንጀላ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ደንባዊ ህልውናውን ክደው የቅስቀሳ መመሪያ ያስተላለፉበትና ለእንቀስቃሴውም አጋርነታቸውን ያረጋገጡበት ደብዳቤ

Pat Aba Mathias on MK01 Pat Aba Mathias on MK02 Pat Aba Mathias on MK03

Advertisements

68 thoughts on “ፓትርያርኩ፡የማኅበረ ቅዱሳንን ደንባዊ ህልውና የሚክድ የክሥ መመሪያ ለኮሌጆች አስተላለፉ፤ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ቀሰቀሱበት

  1. Anonymous February 6, 2016 at 2:54 pm Reply

    የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል

  2. Anonymous February 7, 2016 at 9:07 am Reply

    Sew babatu eegefal enji yigefeteral!!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: