የዴንቨር መድኃኔዓለም ካህናትንና ምእመናንን ባሰብኩ ጊዜ: በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መኾን ማለት መከራ መቀበል እና መሥዋዕትነት መክፈል ነው – ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

 • አባቶቻችን ‹‹እስክንድርያ እናታችን፣ ማርቆስ አባታችን›› ብለው ለ1600 ዓመታት ሲኖሩ በመንበረ ማርቆስ የተቀመጡት አበው ኹሉም አስደስተዋቸው፣ የእስክንድርያው ቤተ ክህነት ሥራ አርክቷቸው አልነበረም፡፡ እንደዚያም ኾኖ ግን አባቶቻችን መንበሩንና ርእሰ መንበሩን አክብረው ኖረዋል፡፡
 • ዛሬም ‹‹እናት ቤተ ክርስቲያን›› ስንል አቡነ ጳውሎስ ወይም አቡነ ማትያስ ማለታችን አይደለም፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ከእነርሱ ብቻ ሳይኾን ከድምራቸውም በላይ ናት፡፡ እነርሱ ያልፋሉ፤ እርሷ ግን ኹሉን ታሳልፋለች፡፡ እነርሱ ይቀራሉ፤ እርሷ ግን ትሻገራለች፡፡
 • እናት ቤተ ክርስቲያን ስንል መንበሯ ከርእሰ መንበሯ በላይ ነው፤ ሲኖዶሷም ከአባላቷ በላይ ነው፡፡ መንበሯ የታሪኳ፣ የቀኖናዋ፣ የትምህርተ ሃይማኖቷ፣ የቅርሷ፣ የባህሏ፣ የስብከተ ወንጌሏ፣ የፈተናዋ፣ የምእመናኗ፣ የአጥቢያዎቿ፣ የአህጉረ ስብከቷ፣ የገዳማቷ፣ የመናንያኗ የአንድነታቸው መገለጫ (ትእምርተ አሐተኔ)፣ አንዲት ጉባኤ የመኾናቸው አይከን ማለታችን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከባለሥልጣኖቿ ኹሉ በላይ ነው፡፡ እርሷ መልዕልተ ኵሉ ናትና፡፡
 • የምንኖረው በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የምንሠራው ለዚኽች ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የምንሞተውም በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የምንታመነውም ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እንዳትገነጠል፣ እንዳትከፋፈል የምንታገለው ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

*           *          *

ሰሞኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በዴንቨር ከተማ ተገኝተው፣ የዴንቨር መድኃኔዓለምን በተመለከተ፣ ‹‹ከእናት ቤተ ክርስቲያን ወጥቷል›› ብለው መናገራቸውን ስሰማ÷ “የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ያዕቆብ መንበር ሥር መኾን የለባትም/አለባት” በሚል ከኃምሳ ዓመታት በፊት በፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግ አንድ ሕንዳዊ አባት የሰጡት ምስክርነት ትዝ አለኝ፡፡

በሕንድ ፍርድ ቤት የሕንድን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለማየት ከኃምሳ ዓመታት በፊት ክርክር በተደረገ ጊዜ፣ የሶርያውን መንበር የተቀበሉ ምእመናን ከባድ ፈተና ላይ ወድቀው ነበር፡፡ በአንድ በኩል፣ በሶርያ መንበር የነበሩ አበው ለሕንድ ቤተ ክርስቲያን ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው ምእመናኑ ይማረራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከመንበሩ መነጠሉ ጥንታዊውን መንገድ እና ሥርዐት አዛብቶ ለተኩላ ስለሚዳርግ ያስጨንቃቸዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት አባ ያዕቆብ የተባሉ ሕንዳዊ መነኰስ፡-

እኔ መንበረ ያዕቆብ ስል ስለ እምነቴ እና ስለ ሥርዓቴ እየተናገርኩ እንጂ በቦታው ዛሬ ስለተቀመጡት አባቶች አይደለም፡፡ እነርሱ እንደ ሰውነታቸው ይበረታሉ ወይም ይደክማሉ፤ ይሠራሉ ወይም ይሰንፋሉ፡፡ ያቺ የተቀደሰቺው የያዕቆብ መንበር ግን ምን ጊዜም ቅድስት ናት፡፡ እኔ ያቺን መንበር ሳስብ ለእምነታቸው የታገሉትን ቅዱሳን አበው፣ ለመንጎቻቸው የሞቱትን ሰማዕታት እረኞች፣ በአሕዛብ ተከብበው በየዘመናቱ የደረሰባቸውን መከራ አሳልፈው በእምነታቸው የጸኑትን ጠንካሮቹን አበው ነው የማስበው፡፡ መንበሪቱ ማንም ቢቀመጥባት የማትረክስ ናት፡፡ ወርቅ ላይ ምንም ዓይነት ጭቃ ቢቀመጥ የወርቁን ክብር አይቀንሰውም፤ እንዲያውም ወርቁ የጭቃውን ክብር ይጨምረዋል፡፡ ለእነዚያ አበው የተሰጠው ቃል ኪዳን እንዲኹ የሚጠፋ አይደለም፡፡ እኔ ከመንበረ ያዕቆብ አልለይም ስል ለዘመናት ከተከፈለው መሥዋዕትነት አልለይም፤ በሐዋርያዊት ትውፊት ከምትኖረው ቤተ ክርስቲያን አንድነት አልለይም፤ እነዚያ ብርቱዎች የታገሉለትን ዓላማ ለደካሞች ብዬ አላፈርስም ማለቴ ነው፤

ብለው ነበር ምስክርነታቸው የሰጡት፡፡


Dn Daniel Kibret at Den Med

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት(በዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን)

በዚኽ ዘመን በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙ አበው እና ምእመናንም ተመሳሳይ ፈተና ነው የሚገጥማቸው፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መሆን ማለት ድሎት እና ምቾት አይደለም፡፡ የአባቶችን ጥበቃ እና እረኝነት ማግኘትም አይደለም፡፡ መከራ መቀበል እና መሥዋዕትነት መክፈል እንጂ፡፡ ‹‹በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መሆን›› ሲባል ምን ማለት እንደኾነ ያልገባው ኦርቶዶክሳዊ ፈተናው ከባድ ይኾንበታል፡፡ መንበሩን ከሰዎቹ፣ እምነቱን ከፖሊቲከኞቹ፣ ሥርዐቱን ከጎጠኞቹ መለየት ካልቻለ ፈተናውን አይቋቋመውም፡፡ ይሁዳን ብቻ የሚያይ ከኾነ ሐዋርያነትን ይጠላል፡፡

አባቶቻችን ‹‹እስክንድርያ እናታችን፣ ማርቆስ አባታችን›› ብለው ለ1600 ዓመታት ሲኖሩ በመንበረ ማርቆስ የተቀመጡት አበው ኹሉም አስደስተዋቸው፣ የእስክንድርያው ቤተ ክህነት ሥራ አርክቷቸው አልነበረም፡፡ ለመንጋው የማይራሩ፣ በሲሞናዊነት የዘቀጡ፣ ከግብጽ መሪዎች ጋር ተመሳጥረው እረኝነታቸውን ለፖለቲካ የሸጡ አበው ነበሩበት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት 111 ጳጳሳት ሁሉ ደጋጎች፣ ሊቃውንት፣ ብርቱዎች እና መንጋውን በትጋት የሚጠብቁ አልነበሩም፡፡ ሙስሊሞች ጳጳሳት ኾነው መጥተው ያውቃሉ፡፡ የግብጽ መሪዎችን ፈቃድ ለመፈጸም መስጊድ የሠሩ ግብጻውያን ጳጳሳት ነበሩ፡፡ ምንም ያልተማሩና ከምእመናኑ በዕውቀት ያነሱ ጳጳሳት ተልከው ያውቃሉ፡፡ እንደዚያም ኾኖ ግን አባቶቻችን መንበሩንና ርእሰ መንበሩን አክብረው ኖረዋል፡፡ ለምን?

አባቶቻችን ‹‹እስክንድርያ እናታችን›› ሲሉ እስክንድርያ የምትወክለውን የአትናቴዎስ እና የቄርሎስ፣ የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ እና የዲዮስቆሮስ እምነት ማለታቸው ነው፡፡ እስክንድርያ ሲሉ ወልድ ዋሕድ የሚለውን የማይናወጽ ትምህርተ ሃይማኖት ማለታቸው ነው፡፡ እስክንድርያ ሲሉ በኒቂያ፣ በቁስጥንጥንያ እና በኤፌሶን የተወሰነውን የተዋሕዶ ትምህርተ ሃይማኖት ያገኙባትን መንበር ማለታቸው ነው፡፡ ለእነርሱ ‹‹ማርቆስ አባታችን›› ማለት ከማርቆስ ጀምሮ ሳይቋረጥ የኖረውን ሐዋርያዊ የክህነት ቅብብል ያገኙበትን ቅዱስ መንበር ነው፡፡ መንበሩን ለማጽናት ከአረማውያን፣ ከአርዮሳውያን፣ ከንስጥሮሳውያን፣ ከልዮናውያንና ከሙስሊሞች ጋር የተደረገውን መሥዋዕትነት ነው፡፡ እነርሱ ታማኝ ኾነው የኖሩት ለዚህ ጽኑዕ እምነት እና ሐሳብ ነው፡፡ ለዚኽም ነው በዘመናት መካከል ዓላማው ያልገባቸው ሰዎች ሲነሡና በመንበሩ ላይ ሲቀመጡ፤ ሓላፊነታቸውን ትተው የንጉሥ ፈቃድ ፈጻሚዎች ሲሆኑ፤ መንጋውን ረስተው ለግል ጥቅማቸው ሲያደሉ የአባቶቻችን ሐሳብ ያልተቀየረው፡፡

ዛሬም ‹‹እናት ቤተ ክርስቲያን›› ስንል አቡነ ጳውሎስ ወይም አቡነ ማትያስ ማለታችን አይደለም፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ስል አቡነ ዳንኤል ወይም አቡነ አትናቴዎስ ማለታችን አይደለም፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ስንል ንቡረ እድ እንትና ወይም ሥራ አስኪያጅ እንቶኔ ማለታችን አይደለም፡፡ እነዚኽ ኹሉም በእርሷ ሥር ኾነው የሚሠሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶች የሚጠበቅባቸውን አንዳንዶችም የማይጠበቅባቸውን የሚያደርጉ ተላላኪዎቿ ናቸው፡፡ አንዳንዶች መጥተውላታል፤ አንዳንዶችም መጥተውባታል፡፡ አንዳንዶች ተነሥተውላታል፤ አንዳንዶችም ተነሥተውባታል፡፡ አንዳንዶች ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ ይጽፋሉ፤ አንዳንዶችም በሞት መጽሐፍ ይመዘገባሉ፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ግን ከእነርሱ ብቻ ሳይኾን ከድምራቸውም በላይ ናት፡፡ እነርሱ ያልፋሉ፤ እርሷ ግን ኹሉን ታሳልፋለች፡፡ እነርሱ ይቀራሉ፤ እርሷ ግን ትሻገራለች፡፡

Denver Med10
እናት ቤተ ክርስቲያን ስንል
40 ሺሕ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፣ 400 ሺሕ ካህናትን፣ 1‚100 ገዳማትን፣ 50 ሚሊዮን ምእመናንን፣ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ የዘለቀውን ታሪክ የጠበቀች ብሔራዊት ቤትን፣ እልፍ ቅዱሳንን ወደ መንግሥተ ሰማያት ያሻገረች ሰማያዊት መሰላልን፣ ከ200ሺሕ በላይ የሚደርሱ መጻሕፍትን ለትውልድ ያቆየች መዝገብ ቤትን ማለታችን ነው፡፡ ዮዲትን ያለፈቺውን፣ ግራኝን የተሻገረቺውን፣ ድርቡሽ አቃጥሎ፣ ጣልያን መዝብሮ ድል ሊያደርጋት ያልቻለቺውን ቤተ ክርስቲያን ማለታችን ነው፡፡ መንበሯ ከርእሰ መንበሯ በላይ ነው፡፡ ሲኖዶሷም ከአባላቷ በላይ ነው፡፡ ለእኛ መንበሯ የታሪኳ፣ የቀኖናዋ፣ የትምህርተ ሃይማኖቷ፣ የቅርሷ፣ የባህሏ፣ የስብከተ ወንጌሏ፣ የፈተናዋ፣ የምእመናኗ፣ የአጥቢያዎቿ፣ የአህጉረ ስብከቶቿ፣ የገዳማቷ፣ የመናንያኗ የአንድነታቸው መገለጫ (ትእምርተ አሐተኒ)፣ አንዲት ጉባኤ የመኾናቸው አይከን ማለታችን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከባለሥልጣኖቿ ኹሉ በላይ ነው፡፡ እርሷ መልዕልተ ኵሉ ናትና፡፡

ባለሥልጣኖቿ የሚሠሩት ስሕተት እና ጥፋት ያሳዝነናል፣ ነገር ግን ተስፋ አያስቆርጠንም፤ ያስለቅሰናል፣ ግን ከመንገድ አያስቀረንም፡፡ ከጥፋታቸው እንጂ ከአንድነቷ አያስወጣንም፤ እንደ ሸረሪት ቤታችን ሲቃጠል ትተን የምንጠፋ ሞኞች አይደለንም፡፡ ልጆቿ ነንና መከራዋን አብረን እንሳተፋለን፤ እንደ ባዕድ ባወጣ ያውጣሽ አንላትም፡፡ ድግስ እንደተጠራ ሰው፣ ሲስተካከል ጥሩን ብለን ትተን አንሔድም፤ እንዲስተካከል በኣት አጽንተን እንጋደላለን እንጂ፡፡

Den Med13
የቤተ ክርስቲያን ልጅነትን ማንም እንኩ ብሎ የሚሰጠን፣ ወይም ማንም አትችሉም ብሎ የሚከለክለን አይደለም፡፡ በዐርባ በሰማንያ ያገኘነው፣ በእምነት እና በምግባር ተግተን፣ በመዋቅር እና በሥርዓት ኖረን ያጸናነው ጸጋችን ነው፡፡ እኛ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስንል አባ ጊዮርጊስ እንዳስተማረን መስቀላዊቷን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች ከፓትርያርክ እስከ ምእመን፤ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ከአሶሳ እስከ ቶጎ ጫሌ፤ ከዛላምበሳ እስከ ሞያሌ ያለቺውን ቤተ ክርስቲያን፡፡ ከላይ እስከ ታች – ከዐጸደ ነፍስ እስከ ዐጸደ ሥጋ፤ ከግራ ወደ ቀኝ – ከቶኪዮ እስከ ሎስ አንጀለስ፣ ከሜልቦርን እስከ ጃማይካ ያለቺውን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች ከአርእስተ አበው እስከ ዓለም መጨረሻ የሚነሡ ክርስቲያኖች፤ ከግራ ወደ ቀኝ – ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የተበተኑ የእግዚአብሔር ልጆች ያሉባትን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

የምንኖረው በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የምንሠራው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የምንሞተውም በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የምንታመነውም ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እንዳትገነጠል፣ እንዳትከፋፈል የምንታገለው ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እኛ ቅዱስ ሲኖዶስ ስንል አባቶቻችን የራሳችን ጳጳሳት እንዲኖሩን ያደረጉትን ተጋድሎ እናስባለን፡፡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ብለው፣ ክብራቸውንም ትተው የአንበሳ ደቦል፣ የዝሆን ግልገል፣ የወርቅ እንከብል ይዘው እስክንድርያ ድረስ ጳጳስ ለማምጣት የደከሙትን ድካም እናስባለን፡፡ አኹን ያሉት አባቶች ቢያቀሉትም ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን ለማግኘት፣ አዲስ አበባ ላይ መንበረ ፕትርክና ለመመሥረት ሺሕ ዓመታትን የፈጀ ተጋድሎ ተደርጓል፡፡ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አስጠብቆ፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን እረኞች እንዲያገኙ እየታገሉ ያለፉትን አበው እናስባለን፡፡

Lik Kah Hail Den Med02

ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ

ቀራንዮ ላይ ዮሐንስን መስሎ የመቆምን ያህል ከባድ ነገር የለም፡፡ ባልንጀሮቹ በሙሉ ሔደዋል፡፡ የሚወደው መምህሩ ራቁቱን ተሰቅሏል፡፡ ሽፍቶች እና አልፎ ሒያጆች ይዘብቱበታል፡፡ ቀያፋ እና ሐና ድል አደረግን ብለዋል፡፡ ያን ጌታ፣ ያን ራቁቱን የተሰቀለ ጌታ፣ ተጠማኹ የሚል ጌታ፣ ልብሶቹን ዕጣ የሚጣጣሉበትን ጌታ፣ በደም አበላ የተዋጠውን ጌታ – ጌታ ነው ብሎ እንደማመንና፣ ባመኑትም እንደ መጽናት ያለ ምን ከባድ ነገር አለ? ጌታን ዓይን ሲያበራ፣ ጎባጣ ሲያቀና፣ ኅብስት ሲያበረክት፣ ሙት ሲያስነሣ፣ ማዕበል ጸጥ ሲያደርግ ማመን ቀላል ነው፡፡ ጌታን ተሰቅሎ ማመን ግን ከባድ ነው፡፡ ያ ቀን እውነት የተሰቀለችበት ቀን ነውና፡፡

ይህ ዘመን እውነት የተሰቀለችበት ዘመን ነው፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ አንዳንድ አባቶች እና አገልጋዮች ራሳቸው አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን ሊያፈርሱ ሲሠሩ፤ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ከሚጋደሉት ይልቅ አፍራሾቹ የቤት ልጆች ሲኾኑ፣ ከአማኞቹ ይልቅ ከሐዲዎቹ፣ ከጽኑዓኑ ይልቅ መናፍቃኑ በር ሲከፈትላቸው፣ ከልጆቿ ይልቅ ጠላቶቿ ሲሾሙ ‹‹እናት ቤተ ክርስቲያን›› ብሎ መጋደል በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ እንደተገኘው እንደ ዮሐንስ መኾን ነው፡፡ እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር መቆም፡፡

ዕለተ ዓርብ ያልፋል፡፡ የቀያፋ ድንፋታ፣ የሐናም ኩራት ያከትማል፡፡ የተቀበረው እውነት ይነሣል፡፡ የሄሮድስ እና የጲላጦስ ማኅተም ይፈታል፡፡ የሸሹ ሐዋርያት ይመለሳሉ፤ የካደው ጴጥሮስ ንስሐ ገብቶ ይመጣል፡፡ የሸጠው ይሁዳም ተቀስፎ ይሞታል፡፡ ያን ጊዜ በመስቀሉ ግርጌ እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር የቆመው ዮሐንስ ‹‹ሞትን ከማይቀምሱት ወገን›› ይኾናል፡፡ የዓርብን ግርግር፣ የቅዳሜን ጸጥታ በትዕግሥት እና በጽናት የሚያልፍ ዮሐንስ ከተገኘ – አላውቅም ካለው ከጴጥሮስ ጋር ኹኖ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ይጠራል፡፡

እስከዚያ ግን እውነት ትሰቀላለች፤ ልጆቿም ራሳቸው ለማዳንና መከራውን ላለመቀበል ሲሉ ትተዋት ይሔዳሉ፡፡ እውነት ያለብትን ትተው ገንዘብ ያለበትን ይመርጣሉ፤ ምቾት ያለበትን ይፈልጋሉ፡፡ በዚኽ ጊዜ እንደ ዮሐንስ የሚጸና ብፁዕ ነው፡፡

Advertisements

19 thoughts on “የዴንቨር መድኃኔዓለም ካህናትንና ምእመናንን ባሰብኩ ጊዜ: በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መኾን ማለት መከራ መቀበል እና መሥዋዕትነት መክፈል ነው – ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

 1. dagmay January 4, 2016 at 10:35 pm Reply

  God be Bless u!!

 2. HG January 4, 2016 at 11:38 pm Reply

  የአንድ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሁሉ አባት ነው መሆን ያለበት። ስህተትም ካለ ትዕግስት ማድረግ መምከር። መለያየት መፍጠሩና መነቃቀፉ ለቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ፡ መንፈሳዊ ዓላማ ሳይኖራቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን መጉዳት ለሚፈልጉት መሣሪያ ከማቀበል ውጭ አይበጅም። መካሪ የሌለው ንጉስ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ የሚለውን መረዳት ጥሩ ነው። መንፈሳዊ ያውም አረጋዊ አባት በወቅታዊው የሀገር ጉዳይ ቢናገር፡ ስለ ድርቁና ሰላም መታጣቱ እንጸልይ ሲል፡ የራቁትን ቅረቡ የጠፋችሁት ተመለሱ ቢል ነው የሚሻለው ።

 3. Anonymous January 5, 2016 at 4:11 am Reply

  በዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን ፈተና በዝቷል ፈተናው እንዲበዛ ካደረጉ ምክንየያት አንዱና ዋነኛው በቤተክርስትያን ውስጥ እናገለግላለን የሚሉ ካህናትና ሌሎች አገልጋዮች ቅንጡ ኑሮ መልመድ ነው ይህን ስል ለራሳቸው በጋን እየዘረፉ ለሌለች በማንኪያ መስጠታቸው አሁን ለምናየው የቤተክርስቲያን ችግር መንሰሄ ዋንኘው ነው እንጂ ብቻ ግን አይደለም ይህን ያልኩት ማንም በጥቀሙ ሲመጡበት ሐሰት መናገር ትንሹ ነው ለርሱ እሰከ ሞት ሊደርሱ ይችላሉ ህልውናቸው ነውና ነገር ግን በቅንነት የሚያገለግሉ ግን የሉም ማለት አይደለም ጌታ በቃሉ ታያላችሁ አትመለከቱም፣መስማትን ትሰማላችሁ ግን አታስተውሉም ያለው አውነት ነው ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ስንት የገጠር አበያተክርሰቲያናት በእርጂና ብዛት ፈርሰው የህምነቱ ተከታዮች በአህዛብና በምነፍቅና እተወስዱ በአመት አንድ ግዜ በሚመጣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ይህን ያክል ምህመን ጠፍቱአል ማለት ለሪፖርት ካለሆነ ምን ደደርጋል ??????? ይህ ሁሉ እያለ በትልልቅ ከተሞች የንግድ ማህከላት ይስፋፋሉ መሆኑ ባልከፋ ግን ለወንጌል ስብከት ምን አገለገሉ????????????? ምንድነው ሃይማኖት ነግዶ ማትረፍ?????? ገንዘብ መሰብስብ????????? ከዚያ የደብር ሃለፊዎችና የቤተክህነት ሹማምንት እንደፈለጉ አንዲሆኑበት ???????? ዛሬ ዛሬማ እንደሚሰማው እግዚያበሔርንም ህዝቡንም በቅንነት ያገለግላል ሳይሆን ስልጣን የሚሰጠው ለእኔ የሚታዘዝ መስፈርትሆኗል ግን እስከመቼ ???? እራስን እያታለሉ መኖር ይቻላል አንድ ቀን በምድራዊው ማበድ ይመጣል አባቶችም ባላችሁ ስልጣን ከህዝቡ አጠገብ ሆናችሁ ማለት በአገረስብከታችሁ ሆናችሁ ለምን አትባረኩትም፣አታሰስተምሩትም እንደው ድፈረት አይሁንብኝና የናንተ ጸሎት ለህዝቡ ካለ አዲስአበባ አልሰማችሁም ብሉአል እግዚአብሄር ወይስ እንደሚባለው ነው????? በአንድ ወቅት የሰው ያለህ የሚል መጸሀፍ አንብቤ ስለነበረ ነው አስካሁንም በዚያ ላይካየሁት ከማየውና ከምሰማው ሥለተመሳሰለብኝ ነው ደግሞም በመጽሃፉ ምላሸ የሰጠም ስላላየሁ እናም አባቶች ሁሉም ነገር ያልፋል የማያልፈውን የሕግዚአብሔርን ቃል እያወቃችሀ ለምን ምዕመኑን አንደ አድረጎ በመመልከት በእምነቱ እንዲጽና አታደረጉትም ???? የናንታ አንድ አለመሆን ለዚህ ሁሉ ምክንየት ነውና ፈጥናችሁ መልሰ ብትሰጡት የሚሻል እረሱ ነው????

  ሕግዚአብሔር ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን

 4. ታዛቢው January 5, 2016 at 6:47 am Reply

  ዲያቆን ዳንኤል ከአንተ የሚጠበቀው ችግሩን ብቻ ማውራት አይደለም፡፡የተወሰኑ አካላትና ግለሰቦች ላይ ብቻ ተጠያቂነቱን መደፍደፍም አይደለም፡፡መፍትሔውንና በጉዳዩ እንደ ግለሰብም እንደ ቡድንም ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ከሁሉም ወገን አካትተህ ካላቀረብክ ጥቅም የለውም፡፡አንድ ጽንፍ ይዘህ በአንድ ረድፍ ጉዞህ ተደመደመ፡፡በቤተክርስቲያን ጉዳይ ያገባናል ስንል ለመብት ብቻ አይደለም፤በተጠያቂነቱም እንደየድርሻችን ተጠያቂ ነን፡፡ኃላፊነትን ሁሉ ለአንድ ወገን የመስጠት ያህል ተጠያቂነትንም ለአንድ ወገን መስጠት ጉዳት አለው፡፡

  ለችግሮች መወሳሰብ በሚዲያው ተሰሚነት ያላችሁ የቤተክርስቲያን ልጆች የምትከተሉት በአመራሩ አካባቢ ያሉ አባቶችንና ተቋሙን በፍቅርና በገንቢ ሂስ ከማገዝ ይልቅ ዘወትር ህጸጽ ብቻ ነቃሽ ሆኖ መቅረብም የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡በዚህ አካሄዳችሁ የተነሳ በሂደት ያላችሁ ተሰሚነትና ሚና እየቀነሰ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡በእናንተ ረድፍ ያለው ተሰላፊ ወደ ትችት አዘንብሏል፡፡ስለቤተክሕነት ደግ ማውራት እርሙ ነው፡፡አንተ ራስህ ዝቋላ ላይ ኤሬቻ ሊከበር ነው ብለህ ጥሩ ጽሑፍ ጻፍክ፡፡ቤተክሕነቱ በጻፈው ደብዳቤ መነሻነት የበዓሉ አከባበር በዝቋላ ሳይሆን በተለዋጭ ቦታ እንዲደረግ ሲሆን የአንድ ዐረፍተ ነገር እውቅና እንኳ መስጠት ተሳነህ፡፡ፍጻሜው ገና ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ የ24 ሰዓት ቴሌቪዥን ለመጀመር ውሳኔ ሲያሳልፍ ምንም ማለት አልፈለክም፡፡ህጸጽ ለመንቀስ ሲሆን ግን ከፊት ትሰለፋለህ፡፡አየህ፡- በቤተክሕነት ያሉ መሪዎች ሰዎች ናቸው፡፡ለእርግማንና ለዘለፋ ብቻ ስማቸውን የሚያነሳ ሰው ለመስማት ኅሊናቸው ይተናነቃቸዋል፡፡ሲጀመር ላይሰሙህ ይችላሉ፤ቢሰሙህም በቸልታ ነው፤ልብ አይሰጡህም፡፡

  ቅኝትህ አንድ አይነት ሆኗል፡፡ምን ቢሳሳቱ የማትወቅሳቸው ወገኖች አሉ፤ምን ደግ ቢሰሩ እውቅና የማትሰጣቸው ሰዎች አሉ፡፡ጉዞአቸውን ሁሉ የጽድቅ፣ንግግራቸውን ሁሉ ክርስቶሳዊ፣የጻፉትን ሁሉ ቄርሎሳዊ የምታደርግላቸው ወገኖች አሉ፡፡ያለመግባባት ሲፈጠር አስታራቂ ሐሳብ እንደማቅረብ ቀድመህ የተወሰነውን አካል ሐና እና ቀያፋ ወይም ይሑዳ አድርገህ ታክፋፋዋለህ፤የደገፍከውን አካል ደግሞ ሐዋርያና ክርስቶስ አድርገህ ለሚዛናዊ አቀራረብ ቅንጣት ሳትጨነቅ ትጽፋለህ፡፡እንደዚህ ሲሆን በቅኝትህ የታቀኙና ስለሌላው ስሕተት በማውራት ራሳቸውን ያጸደቁ ወገኖችን ታስደስት ይሆናል፤ልክ ልካቸውን ነገረልን የሚል ሙገሳ ታገኝ ይሆናል፡፡ለቤተክርስቲያን ግን አትጠቅማትም፡፡ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ችግር ምንጩ አንድ አካል ብቻ አይደለም፡፡መፍትሔውም እንደዛው፡፡ከዚህ አንጻር ቅንጣት መነሻ ስታገኝ የኖረ ቂምህን ሁሉ ከግብጽ የድሮ ጳጳሳት እስከ ቅርብ ዘመኑ አቡነ ጳውሎስ በመጥቀስ ማዥጎድጎድ ብቻ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡እንዲህ አለ ለመባል ካልሆነ በቀር!

  በስክነት፣በሚዛናዊነት፣በመፍትሔ ተቋሚነት፣የራስንና ቡድናዊ ፍላጎትን ብቻ ተገን አድርጎ ባለመንቀሳቀስ፣በቤተክሕነቱ ውስጥ ከነቀዙ ግለሰቦች በተጓዳኝ አያሌ ቅን አባቶች ስላሉ ለእነሱ በመጨነቅ፣በንግግር ሊፈቱ የሚችሉና የመፈታት እድላቸው ተሟጡዋል ለማለት እጅግ ገና ብዙ የሚቀራቸውን ከላይ የጠቀስከውን ደብር አለመግባባት አይነት ገጠመኞች ባለማባባስ በኃላፊነት መንፈስ ብትጽፍ ደስ ይለኛል፡፡ችግር በማራገብና አንዱን አካል ብቻ ነጥሎ በመውቀስ ቤተክሕነቱ የሚቃና ቢሆን ኖሮ የአንተን ብሎግ ጨምሮ ፕሬሱና ማኅበራዊ ሚዲያው ለሁለት ዐሰርት ዓመታት የሰነዘሩት ወቀሳ ብቻ ለቤተክሕነት ክንፍ ያበቅልለት ነበር፡፡ስለዚህ ስንተች በስክነትና በሚዛናዊነት ቢሆን ደስ ይለኛል፤ያለበለዚያ አድማጩም ልማዱ ነው ብሎ በግራው ሰምቶ በቀኙ ያፈሰዋል፡፡እውነትም በቤተክሕነት እንደተሰቀለች ዳግም በቨርጊኒያ ትሰቀላለች፤ምክንያቱም ግራቀኝ አይቶ ፍርድ የሚሰጥ የለም፤ሁሉም የፈረጀውን አካል ለመስቀል ሚስማርና መዶሻ ይዞ ነው የሚጓዝ፡፡

  መፍትሄ ሳይሆን መርዶ ነጋሪ በዛ፡፡ለተፈጠረው ችግር አረጋጊ ሳይሆን አረግራጊ በረከተ፡፡አፈ-ሊቃውንት በዙ፡፡የሁሉም ማጠንጠኛ እኛ ያልነው ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን ትፈርሳለች፤ፈርሳለች ነው፡፡መፍትሄ ጥቆማ የተለየው እሮሮ ይሰለቻል፡፡እሹሩሩ በሉኝ፤እኔ ብቻ ጻድቅ ብሂል ይጎመዝዛል፡፡የሰላም ተስፋው ያልተሟጠጠ የአንድ አጥቢያ ችግርን ተጠቅሞ በዚህ መጠን ሀገራዊ ሟርት መጥራት ያሳዝናል፡፡ደብሩ በውግዘት አልተለየ፤የአገልጋዮቹ የቤተክርስቲያን ልጅነት አልተገፈፈ፤ክሕነታቸው አልተነካ፤ይሄ ሁሉ የተጋነነ ምላሽ ከየት መጣ!ወይስ የተወሰኑ ስብስቦች ያሉበት አጥቢያ ከሌላው አጥቢየ የተለየ ጥበቃ ይደረግለታል!ወይስ ዲያቆን ዳንኤል ለጉባኤ በየዓመቱ የሚጠራበት ደብር ስለሆነ ጉዳዩ በተለየ ዐይን መታየት አለበት!ተው እንጂ ጎበዝ፤ሚዲያውን ተቆጣጥራችሁ በአንድ አይነት ቅኝት እየቃኛችሁ እውነትን ዳግም በድምጽ ብልጫ አትስቀሏት፡፡ተሸቀዳድሞ ራስን ክርስቶስ ማድረግ ያስተዛዝባል፡፡ሊፈታ የሚችልን የአንድ የዲያስፖራ ቤተክርስቲያን አጥቢያ አለመግባባት በዚህ ልክ አስፋፍቶ ሀገራዊ መከራ መጥራት መሰለ፤የተቀናጀ አካሄዳችሁ፡፡ደስ አይልም፡፡ዝግ በሉ፤መፋጠን ሲበዛ መፍትሄ ትቀጥናለች፡፡የቤተክርስቲያንን ክፉ አያሰማን፤አሜን፡፡

  • ዳሞት January 9, 2016 at 5:49 pm Reply

   ለታዛቢ
   ለጡመራ(አሥተያየት) ከምትጠቀምበት ሥም ጀምሮ ግንዛቤህ በጣም ግርም ይለኛል። በመጀመሪያ በክርስትና ታዛቢ መሆን አይደለም የሚያስፈልገው። እውነት የሆነውን እውነት፣ ውሸት የሆነውን ደግሞ ሐሰት በማለት አቋምን ማጥራት ነው የሚፈለገው። ክርስትና የመንግስ ወይም የቀበሌ ምርጫ አይደለምና ታዛቢ አያስፈልገውም ። ይህን ካልኩኝ ክስ ወደ ሆነው ዝብርቅርቅ አሥተያየትህ ላምራ።
   ታዛቢው፦ ችግር ማውራት ብቻ አይደለም ትላለህ። ደግሞም ችግር እንዳለ ለመናገርም ዳር ዳር ትላለህ። ችግር መኖሩ ካልተነገረ የችግሩ ፈፃሚ እንዴት ይወቀስ ከስተቱ ይመለሳል? በደል ሲፈፀም ዝም ማለት እየተፈፀመ ያለውን ችግርና ስህተት አሜን ብሎ መቀበል ትክክል ነው ብሎ ማመን ነው። በወንጌል የተነገረን ፍርድ ተጓደለ ድሀ ተበደለ፣ ስርዓት ህግ ተጣሰ፣ እምነት ተበረዘ፤ ኤዌነት በሐሰት ተቀበረ እንድንል እንጂ ምንም የሌለ በማስመሰል አፋችንን እንድንለጉም አይደለም። ትሁት ካህን ነኝ ብለሀል ከዚህ ቀደምና ካህን ሆነህ ኤሊ የተገሰፀበትን ምክንያት አታውቅምን? በቡድንም በግልም በግለሰብም ተጠያቂ የሆነ አካላት አሉስትል ጽፈሐልና ለመሆኑ እነማን ናቸው? አንድ ጽንፍ ይዘህም ስትል ወቀሳና ክስ ገልፀሐል። ለአንተ አንድ ጽንፍ በእምነት ምን ማለት ነው? ለእውነትና በእምነት ከፀኑት ጋር መቆም ፅንፍ ነውን? አንተም አልተባልህ በዘረኝነት ፅንፍ ሰጥመህ እየተንቦጫረቅ ያለኸው። የተጻፈው እኮ ታሪክን አስተውለው ተለይታችኋል ያሏቸውን አባት አባታችን ከማለት እንዳይወጡና በቤተክርስቲያኗ መዋቅርና ህግ እንዳይወጡ የተሰጠ ምክርና ማጽናናት እንጂ ሌላ አይደለም።
   ታዛቢው፦ መብትንም ጠቀስ አድርገሃልና ለመሆኑ መብትን በሀይማኖት እንዴት ነው የምትመለከተው? ሁላችንም መብት አለን ሲባል በእምነት ተቋም እንዴት ነው የምትገነዘበው። በሀይማኖ ከስርዓት ከህግ ውጭ እንደፈለቁ በሞቅታ በሚመስል መንፈስ የፈለጉትን መናገር መለየት ነውን? የቤተክርስቲያኗን እምነትና አሥተምሮ እየተፃረሩ ሌላ እንግዳ ትምህርትና ጩኸት በአውደምህረት ማራመድ ነውን? እረ ተው ትሁቱ ካህ አቶ ታዛቢው። መጽሐፉ የሚያስተምረን እኮ ውሃና እሳት በፊታችን ቀርቧልና ወደ መረጥነው እጃችንን እንድንልክ እንጂ ሁለቱም ጋ እንድናደርገው አይደለም። የማይገባ ንግግርና ምንፍቅና እያራመዱ ባለመብ ማድረግ ሐጢያት ነው። የቤተክርስቲያንን እምነት፣ ፀሎት ሥርዓ፣ ህግና የወንጌል አሥተምሮ የማይቀበልና የማያከብር በመንግስተሰማይ እንድል ፈንታ የለውም ተብሏልና በቤተክርስቲያንም የፈለግሁትን መሆንና ማድረግ መብት አለኝ ማለት አይችልም። መብቱ ወደ አመነበትና ወደ ወደደው መሔድና መቀላቀል ነው።
   ታዛቢው፦ ሁላችንም ተጠያቂነንም ትላለህ። እውነት ሲነገር ደግሞ ማውራት አይደለም ተለጎሙ ትላለህ። ለመሆኑ ከወደየት ነህ? እንዲሁ በሥጋ ቄናትና ምቀኝነት ላቅ ሲልም በይሁዳነት መንፈስ እየተናጥ ወደዛ ወደዚህ ትዛመማለህና አንዱን ምረጥ።
   ታዛቢው፦ ስትፈልግ ችግር የሌለ ለማስመሰል ትዳክራለህ። መለስትልና ችግር አለ ያወሳሰባችሁት ግን በሚዲያ ተሰሚነት ያላችሁ ናችሁ በማለት የእንናን ለእንት አይነት ዝብርቅርቅ ትዘባርቃለህ። ለመሆኑ በመንፈሳዊ አይን ነው ወይስ በስጋዊ አይን ነው ነገሮችን የምትመለከታቸው። ነው ሥትጽፍ በሞቅታ ባለማስተዋል በስጋ ስሜት ነው። ለዚህ ነው መንፈሳዊ ቅናት ሳይሆን ሥጋዊ ቅናትና ምቀኝነት የተጠናወተህ ትመስላለህ የምለው። ትቀጥልና ተሰሚነት አጣችሁ ትላለህ። ትሁቱ ካህ፦ ሲጀመር ችግር አለ ተብሎም ይሁን ሌላ በየተኛውም መንገድ የሚነገረው የእራስን ተሰሚነት ለመገንባት አይደለም። ችግሩን ገልጦ በማሳየት ለእውነትና ለሀይማኖት የቆሙት እርምት እንዲያደርጉና ትክክለኛውን መንገድ እንዲያስፈፅሙ ለማድረግና ችግር መኖሩን የማያውቁ ካለሙ አውቀው ለችግሩ ሰለባ ከመሆን እንዲነቁ ነው። ኤሊ ልጆቹ በደል ሲያደርጉ በእግዚአብሔር የተገሰፀው እሱ ልጆቹን ባለመገሰፁ የችግሩ ተባባሪ በመሆኑ መሆኑን ተገንዝበኸው ይሆንን። ወረድ ትልና 24 ሰዓት የቴሌቪዠን ብሮግራም ሊጀመር ነው ትላለህ ሚዲያን እየተቃወምህ። ነገርህ ሁሉ ለእግዚአብሔር መንግስት መቅናት ሳይሆን ያንድ ጎጥ ምድራዊ ዝናና የጊነስ ቡክ ዶሴ ይመስላል። ለመሆኑ በቴሌቪዠኑ ዘረኝነት፣ የዘረፋ ስልት፤ ተለይቷል ተለይተዋል የሚል ፅድቅ ነው እየተባለ ይሆን የሚሰበክበት ወይስ እምነት መልካም አስተዳደር?
   ታዛቢ፦ የሚሰሙህም በቸልታና ልብም አይሰጡት ስትልም ሀይማኖታዊና አስተዳደራዊ ስህተት እየፈፀሙ ያሉትን የማይሰሙና ልብ የሌላቸው፤ ከፍ ሲልም ለመንጋውና ለእግዚአብሔር መንግስት ግድ የሌላቸው ቸለልተኛ ናቸው ሥትል በዘወርዋራ ትናገር ትነግራቸዋለህ። ሆኖም የተፃፈው ችግረ ሳይኖርባቸው ተለይተዋል ለተባሉት ምክር ነው። ተለልበኛና ልብ አይሰጡም የምትላቸውም ቢሰሙ ተጠቀሙ። የሚሰማ ይሰማል ፤ ባይኖርም ምድር ትሰማለች።
   ታዛቢው ቅኝት ቅኝት እያልክም ደጋግመህ ፅፈሐል። ምን አይነት ቅኝት ነው? ለምን እውነት ተነረ ነው ቅኝት ቅኝት ኤያልክ የምትከስ? ምንም ጥሩ ቢሰሩ የማትናገርላቸው የማትጽፍላቸው አሉ ስትል ትወቅሳለህ። በቤተክርስቲያን ኀላፊነት የተሰጣቸው መልካም እንዲሰሩ ነው ። መልካም መሥራትና ማድረግ የእምነት ግዴታቸው ነው። የሚሰሩት እንዲወራላቸው ጠብቀው መሆን የለበትም። አንተ ነገርህ ሁሉ ከላይ እንደገለጽሑት ሥጋዊ የአይን ምልከታና ሙገሳ ነው። ቼግሩ የአንድ አካል አይደለም ትላለህ። ሌላው ከመተቸትና የችግሩን አካላት ካወቅህ ለምን በዝርዝር አትገልጣቸውም? ነው እንደ ከዚህ ቀደሙ ንፁሐኑን አሸባሪ ለማለት ዳርዳር እያለክ ነው?ነው በጎቸን ጠብቅ የተባለው አባት ከመቶዎቹ አንዱን መለየቱ ትክክል ነው ለማለት ነው ይህ ሁሉ ልፈፋ? ለአንተ ዘጠና ዘጠኙን በጎች ትቶ አንዱ ለመፈለግ ሔደ ባገኘውም ጊዜ ታላቅ ደስታ ሆነ የሚለው አምላካዊ ቃል ተረት ተረት ነውን? ምነው እንደይሁዳ ገኔዘብን፤ ኤንደ ዴማስም አለምን አታጣጥምም እውነትንና አርነትን ከጠላህ። ወረድ ብለህም አንተ እራስህን ትሑቱ ካህን እያል ማንቆለጳጰስህን ዘንግተህ እንደ ክርስቶስ ፣ ቄርሎስ የምታደርጋቸው አሉ እያልክ ያልተፃፈ ያልተባለ ትላለህ።
   ታዛቢው ክፉ ነገርህና ክፋትህ ብዙ ነው። እኔ ግን የካህን ሳይሆን የሰይጣንና ማን መሆንህን ፅፌ ላብቃ።
   የአንድ ዲያስፖራ ቤተክርስቲያን ስትል ጽፈሐል። ምን ማለት ነው? ለመሆኑ ቤተክርስቲያን የክርስቶስና ለአመኑበት የፀሎት ቤት መሆኗን አታውቅምን? ወይስ የቤተክርስቲያን እራስ ክርስቶስ መሆኑን አልተማርህምን? ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተመሰረተች የሚመለክበት ስሙ የሚቀደስባት ናት እኮ! ነው ዲያስፖራ ለአንተ ከሌላው ህዝ የተለየ ህዝብ ነውን? አንድ የተባለውስ ማን ነው? አለመግባባት የምትለውስ የት ሆነህ ያወያየኸውን ነው? ሥለ ቤተክርስቲያኑም የምታውቀው እንደሌለ ፅፈሐልና አለመግባባቱን ከየት አገኘኸው ምንስ ነው? የጥቂቶች ስብስብና በአመት አንድ ጊዜ ለአገልግሎት የሚጠራበት ስለሆነ የተለየ ጥበቃ ሊደረግለት ነውን የምትለው ማን የተለየ ጥበቃ ጠየቀ? ቤተክርስቲያንን በማንም በላይ ከነ ልጆቿ የሚጠብቃት በደሙ የመሰረታት ክርስቶስ ነው። የጥቂቶች ስብስብ እያል ቤተክርስቲያንን የምትዘልፍና ጥላቻን የምትረጭ አንተ ክፉ አወዴት ነህ? የቤተክርስቲያ አባት ተብለው የተሾሙት ቤተክርስቲያንን አንድ አድርገው እንዲጠብቁ ነውና ባቢሎናዊያን ከበለያዩበት የዘር ቋንቋና አድሎ ወጥተው እውነተኛ የበጎች እረኛ ይሁኑ ተባለ እንጂ ሌላ ምን ተባለና ነው ይህን ሁሉ የጥላቻና የመለያያ ሰይጣናዊ ቋንቋ የሚያስቀባጥርህ።ምናልባት ትሁቱ ካህን የጠመጠምኸው የካህንነት ጥምጥም ካለ አውልቅና ወደ አዳራሽህ። መንፈስህ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሳይሆን ሌላ ነውና።ማንነትህ ከክርስቶስ ወገን ሳይሆን ከሚለያይ ነውና። በሥጋዊ ቅናት፣ በምቀኝነት፣ በዘረኝነትና በክህደት መንፈስ እየተናጥ ለእውነትና ለአርነት ታውረሃልና እግዚአብሔር ልብህን ያብራልህ።

   • ታዛቢው January 11, 2016 at 8:47 am

    ዲያቆን ዳንኤልና ቀሲስ ደጀኔ ለቤተክርስቲያን የዋላችሁት ውለታ አይታበልም፡፡ከተቀበላችሁት በላይ ሰጥታችኋል፡፡በአብነት ት/ቤት እና በኮሌጅ ሳታልፉ ካለፉበት የተሻለ አበርክታችኋል፡፡ችግራችሁ ለዚህ አበርክቶ የተሰጣችሁትን እውቅናና ክብር መንበረ-ፓትርያርኩን፣ጳጳሳቱንና ቤተክሕነቱን ለማጣጣል የተሰጠ የይለፍ ቃል አደረጋችሁት፡፡ቤተክሕነት የሚለው ቃል ኑፋቄ እስኪመስል ድረስ በትውልዱ እዝነ-ልቦና ቀረጻችሁት፡፡‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በሚል ድምጸት ራሳችሁን የቤተክርስቲያን ዐርበኛ አድርጋችሁ እሮሮና እዬዬ ማብዛት መለያችሁ ሆነ፡፡በተለይ ማኅበረቅዱሳንን የተዐብዮኣችሁ መሸፈኛ አድርጋችሁ በማኅበሩ ሰበብ ገጽ የሚያጣብብ የአባቶች ዘለፋ መጻፍ መለያችሁ ሆነ፡፡ለማኅበሩ ያልተገዛ ቤተክሕነት ማየት አንሻም የሚመስል ጎዟችሁ የመዋቅሩ ሥልጣን በእጁ ቢገባ ምን ሊሠራ እንደሚችል በቨርጂኒያ ታዬ፤በየብሎጉ ተንፀባረቀ፡፡የሚፈነገል መንበርና ተቋም፣የሚፈነቅል አቅም ቢኖራችሁ ምን ልታደርጉ እንደምትችሉ እያየን ነው፡፡ደግነቱ ቤተክሕነቱ በጠዋቱ አውቋችኋል፤ ራሱን ለእናንተ አያስገዛም፤ባልተሰጠ ሥልጣን ስታንቧትሩና ለፌ ወለፌ ስታጣቅሱ ተጠባብቆ በቦታችሁ ያስቀምጣችኋል፡፡የውጩም የውስጡም የቤተክሕነት ክንፍ ‹‹የእኛ መንገድ ብቻ ቅዱስ›› ይትበሀላችሁንና ለቤተክርስቲያን በመቆርቆር ስም ማኅበሩን ሽፋን አድርጋችሁ ቢቻል በአመራሩ መፈናጠጥ፤ካልተቻለ አመራሩን ማጣጣል፤ያም ካልሆነ ጥቂት ምልምሎችን በመጠቀም ጉድለቶችን ብቻ በማራገብ ማዕከላዊነትን የመጻረር ዐላማችሁን የተረዳው ይመስላል፡፡ጥሩ ነው፤ሰነፉ እረኛ ከቅርብ መመለስ መጀመሩ ያስመሰግነዋል፡፡እኛም ቤተክሕነቱንና መሪዎቹን ዘወትር በማጣጣል ረዝመው ለመታየት የሚቃጣቸውን የብሎጎቹን ስዩማን ዲ/ዳንኤል ክብረት እና መልአከ ሰላም ደጀኔ ሽፈራው ላይ ቅሬታችንን ለመግለጽ የሚከተለውን ዋዜማ እንቀኝባቸዋለን፡፡

    ዳንኤል፡ወደጀኔ፤
    ስዩማኒሃ፡ለብሎግ፡ዘጳጳሳተ፡ሠዐሩ፣
    ሰቀልዎ፡ለቤተክሕነት፡ከመ-ይጥፋዕ፡ዝክሩ፣
    እስመ-ቤተክሕነት፡ብሉይ፡ዘኢይቴሐት፡መንበሩ፣
    ኢይትቀነይ፡ወትረ፡በማኅበሩ፣
    ለዘቀርበ፡ወርህቀ፡ሐገሩ፡፡

    ወንድም ዳ-ሞት ዘለፋህን፣የተለመደውን ቅዱስ ማኅበሬን የነካ ሁሉ መናፍቅ ነው የሚል ግዝትህን እና ፍረጃህን ካቆምክበት መቀጠል ትችላለህ፤መልስ ልሰጥህ ባለመቻሌ ግን አትቀዬመኝ፤ጊዜና ገጽ ቢያጥረኝ ነው፡፡

  • Bereket January 18, 2016 at 8:57 am Reply

   ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ እንዲህ ያለ አስተዋይ ሰው አያሳጣን፡፡

 5. Anonymous January 5, 2016 at 10:26 am Reply

  ወንድምዬ ጽሑፉ መልካም ነበር ወርቁ ግን ለአንተም በቅጡ አልገባህም ገብቶህማ ቢኾን

  ጽሑፉን በተግባርም በገለጽከው ነበር አንድ ነገር ብቻ ላስታውስህ

  ይህ ዘመን እውነት የተሰቀለችበት ዘመን ነው፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ አንዳንድ

  አባቶች እና አገልጋዮች ራሳቸው አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን ሊያፈርሱ ሲሠሩ፤ ለአንዲት ቤተ

  ክርስቲያን ከሚጋደሉት ይልቅ አፍራሾቹ የቤት ልጆች ሲኾኑ፣ ከአማኞቹ ይልቅ ከሐዲዎቹ፣

  ከጽኑዓኑ ይልቅ መናፍቃኑ በር ሲከፈትላቸው፣ ከልጆቿ ይልቅ ጠላቶቿ ሲሾሙ ‹‹እናት ቤተ

  ክርስቲያን›› ብሎ መጋደል በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ እንደተገኘው እንደ ዮሐንስ መኾን ነው፡፡

  እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር መቆም ነው

  ያልከው ውስጥ እራስህን ፈልግ መልሱን እንደምታገኘው አልጠራጠርም ስለ ዴንቨር ብዙ

  አላውቅም ግን አንድ ነገር አውቃለሁ ርሱም ፍጹም ኢትዮጵያዊውን ሊቀ ካህናት

  ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በወርቃማ ደሙ ለዋጃት ቅድስት ቤተ ክርስቲያኑ

  የትንሣኤዋን ቀን ያቅርብልን

  ቅዱስ ሲኖዶስን ይፈጠርልን

  ቸር ኖላዊ ያስነሣልን

 6. Anonymous January 5, 2016 at 12:48 pm Reply

  “ዕለተ ዓርብ ያልፋል፡፡ የቀያፋ ድንፋታ፣ የሐናም ኩራት ያከትማል፡፡ የተቀበረው እውነት ይነሣል፡፡ የሄሮድስ እና የጲላጦስ ማኅተም ይፈታል፡፡ የሸሹ ሐዋርያት ይመለሳሉ፤ የካደው ጴጥሮስ ንስሐ ገብቶ ይመጣል፡፡ የሸጠው ይሁዳም ተቀስፎ ይሞታል፡፡ ያን ጊዜ በመስቀሉ ግርጌ እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር የቆመው ዮሐንስ ‹‹ሞትን ከማይቀምሱት ወገን›› ይኾናል፡፡ የዓርብን ግርግር፣ የቅዳሜን ጸጥታ በትዕግሥት እና በጽናት የሚያልፍ ዮሐንስ ከተገኘ – አላውቅም ካለው ከጴጥሮስ ጋር ኹኖ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ይጠራል፡፡
  እስከዚያ ግን እውነት ትሰቀላለች፤ ልጆቿም ራሳቸው ለማዳንና መከራውን ላለመቀበል ሲሉ ትተዋት ይሔዳሉ፡፡ እውነት ያለብትን ትተው ገንዘብ ያለበትን ይመርጣሉ፤ ምቾት ያለበትን ይፈልጋሉ፡፡ በዚኽ ጊዜ እንደ ዮሐንስ የሚጸና ብፁዕ ነው፡፡”

 7. Bayable January 5, 2016 at 12:51 pm Reply

  God bless you.

 8. Wubshet January 5, 2016 at 2:23 pm Reply

  ዕለተ ዓርብ ያልፋል፡፡ የቀያፋ ድንፋታ፣ የሐናም ኩራት ያከትማል፡፡ የተቀበረው እውነት ይነሣል፡፡ የሄሮድስ እና የጲላጦስ ማኅተም ይፈታል፡፡ የሸሹ ሐዋርያት ይመለሳሉ፤ የካደው ጴጥሮስ ንስሐ ገብቶ ይመጣል፡፡ የሸጠው ይሁዳም ተቀስፎ ይሞታል፡፡ ያን ጊዜ በመስቀሉ ግርጌ እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር የቆመው ዮሐንስ ‹‹ሞትን ከማይቀምሱት ወገን›› ይኾናል፡፡ የዓርብን ግርግር፣ የቅዳሜን ጸጥታ በትዕግሥት እና በጽናት የሚያልፍ ዮሐንስ ከተገኘ – አላውቅም ካለው ከጴጥሮስ ጋር ኹኖ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ይጠራል፡፡

 9. dagmay January 5, 2016 at 5:03 pm Reply

  Dani ; sile tehadsona nigus Armah guday zim Alik? Ene entone nigus Armah Muslim honoal bilew Tarik gelbitewal? Yetarik muhuran teteyaki nachew!! Dani ante gin bezih zemen lebetekiristian lehagerim tebeka adrgohal !! Ewinetun asawikun?

 10. ዳሞት January 5, 2016 at 6:13 pm Reply

  የሚያጽናና፣ የሚመክር፣ የሚያረጋጋና የሚያፀና አሥተማሪ መልእክት ነውና እግዚአብነብሔር ይባርክህ ፣ በእውነተኛው አገልግሎትህ ያጽናህ፤ ያቆይልን።
  የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም አባቶች አገልጋዮችና ምእመናን እናንተን እኔ ማሳሰብ ባይገባኝ የተሰጣችሁን ምክር ተቀብላችሁ በመንበሯ ሳትለቁ በእምነታችሁ ፀንታችሁ ቁሙ። እኔ እናንተን የማውቃችሁ የዛሬ ገ 8 ዓመትና ለዴንቨር አዲስ ሆኘ ነው። አገልግሎታችሁንና እምነታችሁን ከመፈፀማችሁ ሌላ የሰራችሁት የለምና የሆነው ልብን የሚሰብር ቢሆንም በመስቀልሞቶ ያዳነን ከዚህ በላይ ተቀብሎ ነውና ተጽናኑ።
  ለአባ ማትያስ፦ ለመሆኑ ምን ይሆን ጥፋታቸው አባ እረኛ
  ተብለው ከመንጋው ለይተው ለተኩላ ለመስጠት ያስጨከነዎት? ለአዳናቸው ጌታ ታምነው ስላገለገሉ? የህይወትን ቃል እውነተኛውን የቤተክርስቲያኗን እምነት ስላስተማሩ? እኛ ከክርስቶስ ነን እንጂ ከንትና ዘር ከሚባል አይደለንም ስላሉ? በባእዳን አገር እንቅልፍ እረፍት አጥተው ያገኟትን ለእምነታችን ፤
  ለቤተክርስቲያናችን ብለው በመስጠታቸው? የቤተክርስቲያኗ አባቶችና አገልጋዮች ወገናቸውን በሰው አገር በቃሉና በአገልግሎት እያረሰረሱ በማጽናናታቸው? ላጡ ለተቸገሩ ቤተክርስቲያ እንዳስተማረቻቸው ያቅማቸውን በሠርዳታቸው? የቤተክርስቲያኗን ህንፃ ከእዳ በማውጣታቸው? እረ ምን ይሆን ንገሩ አባ? የያዙት መስቀል የተመረኮዙት በትር ምን ይሆነ የተፈፀመበት ለእርስዎ?
  አባ፦ አሳምመውን ብቻ አይደለም የሔዱት አድምተውን እንጂ። የውሃ እንባ አይደለም ያስነቡን የደም እንባ ጭምር እንጂ። ያባረሩትና የገፉት ልጆችዎን ብቻ አይደለም የሞተለወትን መድኀኔዓለምን ጭምርእንጂ። እኔስ ለሥራ በመድኀኒዓለም ደጅ ባለፍ ቁጥ እንባየ ይቀድመኛል። የቤተክርስቲያንና የእውነተኞች መከራ እየታሰበኝ። እውነት ህሊናዎ እረፍት አግኝቶ ይሆን? የአገር ቤቱ ድጊትዎ ቁሥል ሳይሽር ሌላ ሁለተኛ የሚያቆስልና የቆሰለውን የሚመረቅዝ ሥራ ሰሩ። እውነት የተጠሩለት አላማ ምድራዊ ነው ወይስ ሰማያዊ። ገንዘብ በዶላር ቀይረው ላኩልን ብለው አላስጨነቁዎት ፤ ለምን ገፈተሯቸው?

 11. ሳሙኤል January 6, 2016 at 1:50 am Reply

  ቃለህይወት ያሰማልን ዳን ነገር ሁሉ ለበጎ ሆነ የዴንቨሩ ክስተት ባይፈጠር እንዲህ ያለ የብርታት ሀይለቃል ባላገኘን።

 12. Anonymous January 7, 2016 at 7:10 am Reply

  very sad to hear what happened. From what I have heard the Patriarch was misguided. He should have been patient and investigated more before makeing such a comment. For a person who once resided in US. He should know better on how things work.

  I hope he takes his word back.

 13. ዳሞት January 13, 2016 at 7:00 pm Reply

  ለታዛቢው
  ታዛቢው፦ የበሰበሰ ምን አይፈራም እንዲሉ አንዴ ሐሜተኛና ከሳሽ፣ ውሸታምና እምነት የለሽ፣ ዘረኛና መንደርተኛ ሆኛለሁና ለይቶልኛል ብለህ የነቀያፋ ልጅነትህ አጎላኸው አይደል። እንሿንም ጊዜ አጠረህ ገጽም አጣህ። ጊዜ ኖሮህ ፤ገጽም አግኝተህ ቢሆኖን ንሮ ህይወትን ሊሰጠን የተወለደውን ጌታችንንና መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ካለበደሉ በደለኛ፤ ካለ ወንጀሉ ወንጀለኛ፤ ያላለውን ብሏል ብለው ሰቅለው የገደሉትን ምንኛ ካስቦረቅኀቸው በላይ ባስፈነጠዝሀየቸው ነበር። ጊዜ ኖሮህ፤ ገጽም አግኝተህ ቢሆን ኖሮ በንፁሐን ደም ሰክረህ ያልሰሩ፣ ያላሉትን ሰሩና አሉ እያልክ በሐሜትና በጥላቻ ሰይፍ በመቅላትህ ሞቶ ያዳነህን፤ ለእውነት አርነት ያወጣህን፤ ከኀጢያት ሰንሰለት የፈታህን ክርስቶስን ካሳዘንኸው በላይ ባሳዘንኸው ነበር። ሆኖም ያንተ ክፋትና ጥላቻ ሞልቶ ቢተርፍም ዛሬም መሐሪው ጌታ ተመለስ እያለ በንስሐ ይጠብቅሐል። ተጠቀምበት ነገ ያንተ ላትሆን ትችላለች። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። እድሜ ዘመናችንም በእሱ(በእግዚአብሔር) የተወሰነች ናትና ዛሬ ወደ እውነት ቅረብ። ሥማቸውን ጠቅሰህ በጥላቻ፣ በሐሜትና ያላሉትን አሉ ብለህ የከሰስሐቸውም ጥላቻ ክስና ሐሜት የማ እንደሆኑ ያውቃሉና ላንተ ይቅርታን እያደረጉ ይፀልያሉ።
  ታዛቢው፦ ቤተክህነት የሚለውና የሚባለው ለአንተ እንዴት እንደሆነ ባላውቅም ቤተክህነት አንተና አንተ እንደሆንህ አድርገህ ቤተክህነቱም አውቋችኋል ሥትል አሉባልታህንና ውሸትህን ሳታፍርና ሳታገናዝብ ጽፈሐል። ለመሆኑ ቤተክህነት አንድ ግለሰብ ነውን? ነው ለአንተ ውክልና ተሰጦኀልን? አንተንስ ፈራጅና ዳኛ ማን አደረገህ? በመዘላበድ ምድራዊ ሹመትና ተድላ ታገኝ ይሆናል ነገር ግን በውሸት መንግስተሰማይ የለም።
  ታዛቢው፦ ፓትራሪኩ የፈፀሙትንና እየፈፀሙ ያለትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን የአምላክ ትዛዝን መተላለፍና ታሪካዊ ስህተትን ለማደባበስና ለእውነት ላለመቆም “ፓትራሪኩን፣ ጳጳሳቱን ለማጣጣል የይለፍ ቃል አደረጋችሁት” ስትል ክስ ሰንዝረኀል። ይህን ውሸትህን እውነት ነው ብሎ የሚቀበልህ አባትም ሆነ እውነተኛ ክርስቲያን ባይኖርም አንተ ግን ከሰይጣን እየተቀበልህ ቀባጥረሐል። ፓትራሪኩ የሌሎችን ክስአሉባልታ ለመስማት ጀሮ ከሰጡ የኛንም ስሙንና አባትነትዎ፤ የቤተክርስቲንና ለመንጋው እረኛነትዎ ለሁሉም በጎች ከሆነ መልስ ስጡን ተባሉ ተባለ እንጂ ሌላ ምን ተባሉ? ታዛቢው ወንጌልና እውነት ሳይሆን ክስ፣ ሐሜት፣ ጥላቻና አሉባልታ ብቻ ነው ሥትጽፍ ስትለፍፍ የሰማሁህና ለመሆኑ በመጽሐፍ ያችን ዘማዊ ሴት አይሁድ በክርስቶስ ፊት አቅርበው ሲከሷት ምን ይሆን ያላቸው? እንደ ህጋችሁ አድርጉባት ነውን? እረ አይደለም! ከእናንተ ንፁህ የሆነ ይውገራት አላቸው፤ ጥለዋትም ሸሹ ነው የሚው። ታዲያ ፓትራሪኩ የሌቦችን ጩኸት ሰምተው የተጠሩለትን አላማ መዘንጋታቸው መነገሩ ምኑ ነው ማጣጣል? ታዛቢው፦ በእግዚአብሔር የሆነ እምነትና እውነት ቢኖርህ ኖሮ ይህን የፈተና ዘመን ለሀይማኖትና ለእውነት በተጋፈጥህ ነበር። ሆኖም አምላክ እንደ አምላክነቱ መመለኩ ፣ መመስገኑ ቀርቶ እንዲሰደብና ቤተክርስቲያን ተበታትና እንድትጠፋ ከሚሰሩት ወገን ነህና በስወር ከምትሰራው በዚህ ጽሑፍህም እውነትን ለመቅበር ትታትራለህ አይሆንልህም እንጂ።
  ታዛቢው፦ አንተ የምታምንበትና ታምነህ እየሰራህ ያለህበት እምነት የተለየ ሆነና ማህበረ ቅዱሳንን ሳታውቅ ሳይሆን እያወቅህ ትከስ ትወነጅላለህ። ማህበሩ አንተ ምንም አወራህ ምንም በአምላካቸውን ከማምለክና ለቤተክርስቲያን እምነት፣ ስርዓት፣ ትውፊት፣ ቀኖናና ህግጋት ተጠበቀው እንዲተገበሩና ለትውልድ እንዲተላለፉ ከመሥራት ውጭ ሌላ አላማ የለውም። አንተ በውስጥህ ሌላ መንፈስና አላማ ባይኖርህ ኖሮ ማህበሩንም ሆነ ሌሎችን እውነተኛ የቤተክርስቲያኗ ልጆችን ባበረታታህና በደገፍህ ነበር። በወንጌል የተነገረውን የእውነት ተቃዋሚ ፤ ወንጌል አጣማሚ፤ እንክርዳድ ዘሪ፤ ሐሰተኛ አስተማሪ ወዘተ መኖር መምጣቱን ሁሉም ትክክል ነው የሚመስል ብሒል ድምዳሜ ይዘህ የኛ “መንገድ ብቻ ቅዱስ” ይላሉ አያልክ ትከስ ታናንቃለህ። ለአንተ ወንጌልን መረዳትና ማመን ማለት የሉተር መንገድ ነው። የጥላቻህ መላቅ ደግሞ ለእውነት የቆሙትንና መናፍቅነትን የተቃወሙትን ሁሉ ከማህበሩ ማገናኘትህ ነው።
  ታዛቢው፦ የካህን ሳይሆን የሌላ ቋንቋዎችህ ብዙ ናቸው። እንሿንም ጊዜ አጣህ፣ ገጽም አጠረኸ። ለእኔም እንሿን አልመለስህልኝ። ምክንያቱም ከተጠቀምሁት ገጽ የበለጠ ገጽ ተጠቅሜ እመልስልህ ነበርና። ግና አንተ ዘሬን አትንኩ እያልክ ዘራፍ እንደምትለው ምንም እንሿን በማህበሩ አገልግሎት እንቅስቃሴ የምደሰትና የማምን ብሆንም እኔ የማህበሩ አባል አይደለሁም። እኔ ማህበሩን በሥራውና አገልግሎቱ አውቀዋለሁ እንጂ እኔን አያውቀኝም። የቤተክርስቲያን ጠላት ለቤተክርስቲያኗ ልጆች አይተኛምና ጠላት ስለሆንህ ማህበሩ ላይ ዘለህ ሔድህ። እኔ የጻፍኩትም ሆነ ያልኩህ የእኔ እንጂ ሌላ ማንም የለበትም።
  ታዛቢው፦ ህንፃ መገንባት ዛሬ አይደለም የተጀመረው። ግንብ ሥለ ተገነባም ብቻውን እምነትና ምግባር አይሆንም። አንተን አይንህን ያወረህ በምድር የሚቀረው በምድር የምታየው ምድራዊው ነው። ለሰማያዊው ህንፃ ብትቆምና ብትሰራ መልካም ነው። እውነት እንደሆነች አትደበቅም። ሐዋርያት እንደ ሻማ እየቀለጡ ያበሯት ናት። ቤተክርስቲያንም አትጠፋም አትፈርስም። በአለት ላይ የተመሰረተች ናትና። ክርስቶስ የነበረባት መርከብ በማዕበል ተናውጣለች። ግን አልሰጠመችም። ክርስቶስ ማዕበሉን ፀጥ አድርጎ የተጨነቁትን ሐዋርያትን ከጭንቀት እንዳወጣና መርከቧንም እንዳትሰጥም እንዳደረገ ዛሬም ቤተክርስቲያንን የሚያናውጣትን ወጀብ ማዕበል ፀጥ እያደረገና ልጆቿንም የወጀብ የማዕበሉ አስጨናቂ ፈተና እያሻገረ እስከ ምፅዓት ይጠብቃት፤ ያድናቸዋል።
  ትሁቱ ካህን አቶ ታዛቢው፦ በእኔ በደካማው ፀሎት ሳይሆን በቅዱሳኑ ፀሎት ከሐሜተኛነት፣ ከሳሽነት፣ ከአሉባልተኛነት፣ ከጥላቻና ከክህደት ነፃ ያውጣህ።

 14. Bereket January 18, 2016 at 8:59 am Reply

  ጩኸት ብቻ

  • ዳሞት January 19, 2016 at 4:54 pm Reply

   To bereket
   ተግባሩ እንሿን ከጩኸት ነፃ አወጣህ። ራሔል ሥለ ልጆቿ ጮሀለችና እኛም ሥለ እውነትና ሀይማኖታችን እንጮሀለን። ለአንተ አለሙ ከሆነ እምነትህ ጩኸቱ ላንተ ምንም አይደለምና በተለመደው የአለምና የሐሰት አጃቢነት ተግባርህን ተግብር ብቻ። ጩኸት የምትለውን ምንነትም የገባህ ያወቅኸው አይመስለኝም። የበለጠ ቅኔውን በግዕዝ እንዲዘርፍልህ እራሱን እኔ ትሁቱ ካህን የሚለውን አቶ ታዛቢውን እንዳንተ ያለ አያሳጣን በል አብዝተህ። ደግሞ ጠላት ሰይጣን ለዚህ ማን ብሎት ያግተለትልልሀል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: