የዴንቨር መድኃኔዓለም ካህናትና ምእመናን:“ከእናት ቤተ ክርስቲያን ወጥታችኋል” በሚል በፓትርያርኩ መገፋታቸውን ተቃወሙ፤“ለሕክምና መጥተው የሚያሳምም ሥራ ሠሩ”/ምእመናኑ/

 • “ለጎጠኞች አድልተው ሕዝቡን ከፋፈሉት፤ ትላንት የመሠረቱትን ደብር ዛሬ ካዱት”
 • በፓትርያርኩ አድሏዊ አነጋገር የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ሳይፈጸም ተስተጓጉሏል
 • የኪዳነ ምሕረት ምእመናን ከመድኃኔዓለም ምእመናን ጋር ጮኸዋል፤ አልቅሰዋል
 • በጎጠኞቹ ተበሳጭተው ከቤተ ክርስቲያናቸው የኮበለሉ ምእመናን ጥቂቶች አይደሉም
 • መገፋቱ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ያሉ አድባራትን ዕጣ ፈንታ አጠያያቂ አድርጎታል

*          *          *

Denver colorado Med9

የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን

አንድነት(አሐተኔ) እና ኵላዊነት(ዓለም አቀፋዊነት) ባሕርይዋ ለኾነው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑ እንጂ ሀገሩ የት ነው፤ ቋንቋው ምንድን ነው፤ አይባልም፡፡ በውጭ አገሮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ደግሞ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ መልክ የሚሰጡ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ልዩ ጸጋ ለዓለም የሚናኙ እና ሱታፌም እንዲኖረው የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ከኢየሩሳሌም አንሥቶ በዐሥራ ኹለቱ አህጉረ ስብከትና ከነርሱም ባሻገር አብያተ ክርስቲያናት በቁጥር እንዲበዙ ሲደረግ፣ ይህንኑ ሐዋርያዊ ተልእኳችንን በተለይም በተስፋ ለሚጠብቁን ወገኖች ከማዳረስ እና ከማጠናከር አኳያ ባላቸው አስፈላጊነት ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባዎች ከሚሰሙት ዘገባዎች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ አብያተ ክርስቲያናቱ በመላው ዓለም ተበትነው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያነት ብቻ ሳይወሰኑ “ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቦታዎች” በመኾናቸው፣ ቤተ ክርስቲያናችን “ከሀገር ውጭ ያለች ኢትዮጵያ” ኾና እያገለገለች ትገኛለች፡፡

ከምእመናን ቁጥር መብዛት እና ከአህጉረ ስብከቱ ዕድገት ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያውያን መሰብሰቢያ ማእከል እና መጽናኛ በመኾኗም መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ተልእኮዋን ከመወጣት አንጻር የበለጠ እንድትስፋፋና እንድትጠናከር ይደረግ ዘንድ በተደጋጋሚ እየተጠየቀ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ገለልተኛ ነን የሚሉ አብያተ ክርስቲያናትንም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ማእከላዊነቱን የማስጠበቁ ሥራ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አጠቃላይ ጉባኤው ሳያሳስብ አላለፈም፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገሮች በማስፋፋት ምእመናን እንዲበዙ የማድረግ ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስም፤ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት አድማሳዊ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን በየጊዜው አሳልፏል፡፡ ከዚኽ አኳያ በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤው፣ በጃፓን እና በኮርያ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋምላቸው ጥያቄ ላቀረቡ ዜጎች አብያተ ክርስቲያናት እንዲመሠረቱ፤ መምህራንም እንዲላኩላቸው መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና አገልግሎት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲመራ ማድረግ የሚጠበቅበት ቅዱስ  ሲኖዶሱ፤ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖችም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ በየጊዜው ጥሪውን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚኽም በላይ በስደት ከሚገኙት ብፁዓን አባቶች ጋር የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እስከ አኹን የሚፈለገውን የአንድነት ውጤት አለማስገኘቱን ምልአተ ጉባኤው በየጊዜው ገምግሟል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እና ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችንም ኾነ ለሀገራችን እንዲኹም ለሕዝባችን ያለው ትርጉም የላቀ መኾኑን በመገንዘብም በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ ሒደቱ እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እንዲጠናከር ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡

በሀገር ውስጥ ይኹን በውጭ ቤተ ክርስቲያናችንን ወክለው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ይህን የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ አክብረው መፈጸምና እንዲፈጸምም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በካህናት እና በምእመናን ዘንድ ታማኝነታቸው እና መንፈሳዊ አባትነታቸው ተቀባይነት እንዳያጣ፣ አጠቃላይ አመራራቸው ሕጉን መሠረት ያደረገና ቤተ ክርስቲያንን የማያስነቅፍ መኾን ይገባዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት በመመለስ ረገድ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ከሢመተ ፕትርክናቸው በፊት በሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስናቸው ወቅት፣ የዕርቀ ሰላሙን ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ በተግባርም አዎንታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከሢመተ ፕትርክናቸው በኋላም ባደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉዞዎች ይህንኑ በማጽናት አባታዊ ምክር እና መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይኾን በሀገረ ስብከቱ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን ኑፋቄን ከማጋለጥ ጋር በተያያዘ በቃለ ስብከትም በጽሑፋዊ መግለጫም ጉባኤ ሠርተው ጭምር ዐበይት ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ካለፈው ወር መጨረሻ አንሥቶ፣ ከሕክምና ምርመራ ጋር እንደተያያዘ በተዘገበ ጉዟቸው በዚያው በአሜሪካ የሚገኙት ቅዱስነታቸው፤ በሜኒሶታ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት ወቅትም የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሤራን ለማጋለጥ እና ለማምከን በቅንዓተ ቤተ ክርስቲያን ከተሰብሰበው የጥምረቱ የሰሜን አሜሪካ ቅርንጫፍ የቀረበላቸውን ገለጻ ለማዳመጥ መልካም ፈቃዳቸው ኾኗል፤ ለተጋድሎው ብርታት የኾነ አባታዊ ምክር እና መምሪያም ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ ቆይታቸውን እስከ መጪው ሰኞ አጠናቀው ወደ ሀገር እንደሚመለሱ የሚጠበቁት፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የአሜሪካ ቆይታ ግን ያለነቀፌታ የተጠናቀቀ አልነበረም፡፡ ፓትርያርኩ የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ለማክበር በዴንቨር – ኮሎራዶ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ባሰሙት ንግግራቸው፣ ካህናቱንና ምእመናኑን አሳዝነዋል፡፡ ፓትርያርኩ በንግግራቸው፣ የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ከእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መውጣቱን በመጥቀስ፣ ከዐሥር ዓመት በፊት ባርከው በመክፈታቸው መቆጨታቸውን ተናግረዋል፡፡

የፓትርያርኩ ንግግር ያልተጠበቀ ብቻ ሳይኾን፣ ለአንድ ወገን ሐሳብ የሚያደላና ደብሩን በጎጥ ፖሊቲካ ለመቆጣጠር የቋመጡ ከፋፋዮችን ፍላጎት የሚያስጠብቅ ነው፤ የሚሉት ካህናቱ እና ምእመናኑ፣ በእንባ ጭምር የእነርሱም ጩኸት እንዲሰማ ቢጠይቁም የመደመጥ ዕድል አለማግኘታቸውን ነው፤ የሚያስረዱት፡፡ የበዓሉ አከባበር ማስተዋል እና ምክር በጎደለው የፓትርያርኩ አነጋገር ሳቢያ ሳይፈጸም ቢስተጓጎልም፣ የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ምእመናን ለበዓል ከመጡ የመድኃኔዓለም ምእመናን ጋር አብረው በማልቀስ ተቃውሟቸውን በአንድነት ማሰማታቸው፣ “ለፓትርያርኩ እና ለጎጠኞቹ ውርደት፥ ለመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ክብር ነው፤” ብለዋል።

ጎጠኞቹ እና ፖሊቲከኞቹ፣ ደብሩን እንደ ግል ካምፓኒ በመቁጠር የማያዙበትን ቤተ ክርስቲያን እንዲበተን ማድረጋቸው ልማዳቸው ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን፣ የቤት ልጅ እና የእንጀራ ልጅ ያለ ይመስል፣ ፓትርያርኩም ከእነርሱ ወግነው በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር የኖሩትን ምእመናን በዐደባባይ መግፋታቸው ነው፡፡ በረዳትነት እና በአማካሪነት ስም በፈረጅያቸው ተከልሎ ወደ ሀገር ቤት እየተመላለሰ የሚያጣቅሰውም ግለሰብ፣ ፓትርያርኩን በተንኮል እና በክፋት በማወናበድ ተጠያቂነቱን ይወስዳል፡፡ የሀገረ ስብከት ከፍተኛ ሓላፊነት ይዞ ሲያበቃ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ብሎጎች ጋር ያለው ያልተቀደሰ ግንኙነትም የተነቃበት ነው፡፡ ጠቅላላ አካሔዱም በአሜሪካ ሦስቱም አህጉረ ስብከት በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ያሉትን ከ103 ያላነሱ አድባራት የነገ ዕጣ ፈንታ አጠያያቂ የሚያደርግ በመኾኑ “ከአኹኑ ልትጠነቀቁ ይገባል፤” ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት ተከታትለው ትዝብታቸውን በጽሑፍ ያደረሱን ምእመን፡፡

የጎጠኞቹ ሰለባ ኾኜ ከአንድም አራት ጊዜ ተሰድጃለኹ የሚሉት ታዛቢው÷ የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከመዋቅር አለመውጣቱን፣ እንኳን ጎጠኞቹ ፓትርያርኩም እንደሚያውቁ አረጋግጠው ይናገራሉ። ትላንት ከግል ገንዘባቸው ጭምር አውጥተው የመሠረቱትን ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በመካድ የአባትነታቸውን ድርሻ ባይወጡም፤ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር በመቀጠል የልጅነትን ድርሻ ከመወጣት ውጭ አማራጭ እንደሌለም ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

“ፓትርያርኩ የዴንቨር መድኃኔዓለምን ለማውገዝ ተዘጋጅተው፥ ሕዝቡ አከሸፈባቸው” በሚል ርእስ የደረሰን የታዛቢው ጽሑፍ፣ ለጡመራ መድረኩ እንደሚኾን ተደርጎ ቀርቧል፤ በጥሞና እንዲመለከቱት ተጋብዘዋል፡፡


ፓትርያርኩ የዴንቨር መድኃኔዓለምን ለማውገዝ ተዘጋጅተው፥ ሕዝቡ አከሸፈባቸው

የዛሬ ያ ዓመት ይናል በዴንቨር፣ በድንግል ማርያም ስም የተሰየመች ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ሕዝቡም ሌላውን ነገር ኹሉ ወደ ጐን ትቶ እናታችን÷ አማላጃችን ብሎ ተሰበሰበ። በከተማዋ ሌላ ቤተ ክርስቲያን አልነበረም፡፡ ያን ጊዜ፣ የአኹኑ ብፁዕ፥ የያኔው አባ ማርቆስ ከሌሎች ብዙ ካህናት ጋር በእዚያ ቀዳሽ እና ሰባኪ ነበሩ።

በአንድ የሰንበት ማለዳ፥ “[የእገሌ] ኮሚኒቲ ቤተ ክርስቲያን” የሚል ባነር ተለጥፎ፥ አማርኛ ተናጋሪ ምእመናንና አባ ማርቆስ በፖሊስ ተባረሩ። ወ/ሮ ዓለምነሽ የተባሉ ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊት ምእመንት ብቻ፣ “በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እንዴት የዘር መድልዎ ይደረጋል?” ብለው፥ ሃይማኖታቸውን አስበልጠው አብረው ተሰደዱ – ከዴንቨር ኪዳነ ምሕረት ደብር። በነገራችን ላይ በጊዜው በብስጭት ወደ ፕሮቴስታንቱ ጐራ የገቡ ጥቂቶች አልነበሩም።

በጎጠኞች ደብራቸውን ተቀምተው የተሰደዱት ምእመናንም ተበትነው እንዳይቀሩ፥ እንደገና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን አቋቋሙ። ጎጠኞቹም ልክ እንደ ንግድ ምልክት፡- “ማርያም የሚለው ስም የግል ድርጅታችን ስም ስለነ ይታገድልን፤” ብለው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። ለካስ፥ አምስት ኪሎ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ስትመሠረት፥ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መክሠሥ ነበረባት፤ የመርካቶ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲመሠረት ደብረ ሊባኖስ መክሠሥ ነበረበት፤ አዲስ ዓለም ጽዮን ማርያም ስትመሠረት አኵስም ጽዮን መክሠሥ ነበረባት። አስኮ ቅዱስ ገብርኤል ሲመሠረት መንበረ መንግሥት ግቢ ገብርኤል መክሠሥ ነበረበትii

የዴንቨር ፍርድ ቤትም በነገሩ ዙሪያ ካከራከረ በኋላ ለስደተኞቹ ፈረደላቸው። በስመ ተጋሩ የሚነግዱት ጎጠኞቹም ስማቸውን ወደ ኪዳነ ምሕረት ለወጡ። መንፈሳዊ ስም ቢለዋውጡም የጎጥ ፖሊቲካ አራማጆች መኾናቸው ሊሸፈን የሚችል አልነበረም፤ ካህናቱም የሃይማኖት ዕውቀት እንጂ እምነት ስለሌላቸው ዋና ተዋናይ ነበሩ። በፓርቲ ፖሊቲካ አራማጅነታቸው በሃይማኖት ከማይመስሏቸው ጋር በፍቅር የሚኖሩትን ያኽል በቤተ ክርስቲያን ግን ክርስቶስንና ድንግል ማርያምን፤ በአጠቃላይ ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓታቸውን፣ ትውፊታቸውንና ታሪካቸውን ከሚወዱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች ጋር በፍቅር መኖር አልቻሉም።

ስደተኞቹ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ከመሠረቱ በኋላ፣ “የስደተኞች መድኅን ስደተኛው ሲኖዶስ ነው፤” ብለው እነርሱ ተረከቧቸው፤ ምእመናኑም በመጀመሪያ ተከራይተው ቀጥሎም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገዝተው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም ባዶ መሬት ገዝተው በዓይነቱ ልዩ የኾነ ቤተ ክርስቲያን አነፁ። የሚያሳዝነው ነገር፥ ቤተ ክርስቲያኑ ተሠርቶ አልቆ ሊመረቅ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው የሰንበት ት/ቤቱን አባላት “ማኅበረ ቅዱሳን ናችኹ ብለው አባላቱን በጠቅላላ በፖሊስ አባረሯቸው።

“እኔም ስደተኛ ነኝ፤ የስደተኞችም መድኅን ነኝ፤” ብሎ የነበረው የስደተኛው ሲኖዶስ፥ በሰው ሀገር ራሱ አሳዳጅ ኾነ። “ስደት ሣልሳዊ” ማለት እንዲኽ ነው – በመጀመሪያ ከሀገር ቤት፥ ኹለተኛ ከትግራይ ኮሚዩኒቲ ቤተ ክርስቲያን፤ ሦስተኛ ከጎንደሮች ቤተ ክርስቲያን ተሰደዱ። እኔም ደግሞ የችግሩ ሰለባ ነበርኩኝና በራብዓዊ ስደት ከዴንቨር ተሰድጄ ወደ ሌላ ስቴት ሔድኩኝ። ዴንቨርን በመልቀቄ ለጊዜው እፎይታ ቢሰማኝም፣ ከባለንጀሮቼ ጋር የዕለት ዕለት ግንኙነት ስለነበረን፥ ከዴንቨር ርቄም አልራቅኹኝም።

የሀገር ቤቱ “ተቃዋሚ”፣ የባሕር ማዶው “ወያኔ” – ማኅበረ ቅዱሳን

የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ሕዝቡ ተከትሎአቸው ወጥቶ ስለነበረ የበለጠ ሓላፊነት በትከሻቸው ላይ ወደቀ። ወ/ሮ ዓለምነሽ የተባሉት እናት፥ በጎጠኞቹ ቁጥጥር ሥር ከወደቀው ደብር ከሕዝቡ ጋር አልቅሰው እንደወጡ፥ ከዴንቨር ግሼን ማርያም ቤተ ክርስቲያንም፣ ከማኅበሩ አባላት ጋር ወያኔዎች ተብለው ወጡ። የሚገርመው ነገር፣ የማኅበሩ አባላት፥ በሀገር ቤት፡- አንድ ሰሞን መኢአድ ቀጥሎም ቅንጅት፥ አኹን ደግሞ ግንቦት ሰባት እየተባሉ፥ በቤተ ክህነቱ አማሳኞች እና በአድርባይ ሹመኞች መከራቸውን ያያሉ። በሰሜን አሜሪካ ደግሞ እናት ቤተ ክርስቲያንን የሙጥኝ በማለታቸው ወያኔ ተብለው ይሰደባሉ። ምእመናኑ ከእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በመባረራቸው÷ ከኹሉም በላይ የተደሰቱት የኪዳነ ምሕረት ካህናት እና ምእመናን ነበሩ። እንዲያውም “የተባረሩት ጴንጤዎች ናቸው፤” እያሉም ስም ያጠፉ ነበር።

የማኅበሩ አባላት፣ በየሳምንቱ የአዳራሽ ጉባኤ እያዘጋጁ፥ መምህራንን ከየስቴቱ በመጋበዝ ምእመናኑ እንዳይበተኑ ትልቅ አስተዋፅዖ አደረጉ። ይህ በእንዲኽ እያለ፣ የአባቱን ስም የማላስታውሰው ግርማ የተባለ ወጣት፡- ልጅ ይወልዳል። ክርስትና ለማስነሣት የእናት ቤተ ክርስቲያን ይሻላል ብሎ ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ቢሔድ “አናነሣም” ብለው አባረሩት።

ያን ጊዜ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ባርከው ከፈቱ
Abune Mathias Denver Med

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ጋር

በወቅቱ የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የአኹኑ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስለነበሩ፥ አማላጅ ኹነው ቢለምኑም ሰሚ ዐጡ፡፡ ካህናቱም ሰበካ ጉባኤውም ታዛዥነታቸው ለፖሊቲካ ሹመኞች እንጂ ለሌላ አልነበረም። ያን ጊዜ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፥ አሁን ብፁዕ ወቅዱስ፥ ጎጠኞቹ እየተቃወሟቸውም ቢኾን የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ባርከው ከፈቱ። ገንዘብ ሲሰበሰብም የመጀመሪያውን አንድ ሺሕ ዶላር ከፈሉ፤ እኔም ካለኹበት ሀገር ኹኜ የአቅሜን ረድቻለኹ።

ቤተ ክርስቲያኑ ሲከፈት ተሾመ ከሚባል ዲያቆን በቀር ሌላ ካህን አልነበረም። በየሳምንቱ ከየስቴቱ ካህን እየተለመነ ነበር የሚቀደሰው። በተለይም መምህር ሀብተ ማርያም ተድላ የሚባሉ አዛውንት ካህን ዕርግናቸው ሳያሸንፋቸው ከሳንሆዜ እየተመላለሱ አገልግለዋል። በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን÷ ከኤርትራ እስከ ሞያሌ፤ ከጋምቤላ እስከ ጎዴ ኹሉም አለ። ትክክለኛ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነው። በመጨረሻም ኹለት ካህናት÷ ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ እና መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው÷ በኹለት ወር ልዩነት ተከታትለው ስለመጡላቸው ቤተ ክርስቲያኑ ጥሩ መሠረት ያዘ።

በአኹኑ ጊዜ የባንክ ዕዳ የሌለበት የራሳቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አላቸው። ማሕሌት እና ሰዓታት ይቆማል፤ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ወንጌል በምልዓት ይሰበካል፤ ብዙ ሕዝብ አላቸው። በውጭው ዓለም ምሳሌ የኾነ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ነው። ቤተ ክርስቲያኑ ካሳተመው መጽሔት እንደተረዳኹት፣ በሑዳዴ ጾም ኹለት ወር ሙሉ ስብሐተ ፍቍር ይደርሳል። ፍልሰታን ሰዓታት ይቆማል፤ ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም ይተረጐማል፤ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ የሠርክ ጸሎት መሐረነ አብም አለ።

Denver Colorado Med11
በዋናነት መድኃኔዓለም በዓመት ኹለት ጊዜ ይነግሣል፤ በድርብ ባሉት ቅዱስ ሚካኤል እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓመት ኹለት ኹለት ጊዜ ክብረ በዓል ይደረጋል። በወር አራት ጊዜ፡- ለቅዱስ ሚካኤል፣ ለእመቤታችን፣ ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ለመድኃኔዓለም ኪዳን አይታጐልም። ይህንንም ዌብ ሳይት እና ፌስቡክ የሚከታተሉ ኦርቶዶክሳውያን ያውቁታል። በተለይም የአብርሃም ደምሰውን ፌስቡክ የሚከታተሉ።

ኹለቱ ካህናት ከመጡ በኋላ ግፍ የተፈጸመበት ሕዝብ ቢመርረውም የመድኃኔዓለምንና የኪዳነ ምሕረትን አብያተ ክርስቲያናት አቀራርበው አንድ አደረጓቸው። የተበደሉት ምንም ሳይሉ፣ በኪዳነ ምሕረት በኵል ግን የባለሀብቱ የአቶ ኃይለ ሚካኤል ቡድን ጐመዘዘው። ለኪዳነ ምሕረት ንግሥ የሚሔዱትን ካህናት እና ምእመናን ፊት መንሳት ሥራቸው ኾነ። ካህናቱንም እንደ ቤታቸው ገረድ ስለሚቆጥሯቸው ከፍ ዝቅ አድርገው ይሰድቧቸው ጀመር፤ ካህናቱም ቢኾን በመጀመሪያ የቀረቡት የሊቀ ካህናትን ተወላጅነት አይተው ነበር። በኋላ ላይ ግን ከኢትዮጵያዊነት በቀር ሌላ አልኾን ሲሏቸው ጊዜ ሸሹ።

“ጉድ እና ጅራት ወደ ኋላ ነው” እንደሚባለው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሞቱ ጊዜ ኹሉ ነገር ዐደባባይ ወጣ። እንደ ሰማኹት በወቅቱ፥ ሊቀ ካህናት፣ ለአቡነ ጳውሎስ ቀብር ኢትዮጵያ ነበሩ። የነሐሴ ኪዳነ ምሕረት ዕለት ካህናቱም ሕዝቡም በመመሪያ ጥቁር ለበሱ። የእመቤታችን ንግሥ ተረሳ፤ ከባልንጀሮቼ እንደተረዳኹት “ታቦት ይውጣ አይውጣ” ተጨቃጨቁ። “እኛ ሐዘን ላይ ስለ የምን ንግሥ ነው፤” አሉ። ለፓትርያርኩ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት እንኳ ያን ያኽል አቅላቸውን አልሳቱም።

በዚኹ ሳይበቃቸው በሳምንቱ አዳራሽ ተከራይተው ፍራሽ አንጥፈው ተቀመጡ። ይህ መብታቸው ነው፤ የሚያሳዝነው ነገር የእግዚአብሔርን ቤት የፖለቲካ ድርጅት ጽ/ቤት ማድረጋቸው ነው። በተጨማሪም የመድኃኔዓለሙ ካህን፣ “ለምን ጠጉሩን አልተላጨም? ለምን ጥቍር አልለበሰም? እንደ ሰሙነ ሕማማት ታቦቱን ለምን ጥቍር አላለበሰም? ምእመናኑም ጥቍር እንዲለብሱ ለምን አልገዘተም?” ብለው፣ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤተ ጣዖት ቆጥረው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደጁን አይረግጡም።

ኹለቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መስቀልንና ጥምቀትን በአንድነት ያከብሩ እንደነበረ አውቃ ለሁ። እኔ ብቻ ሳልኾን ፌስቡክ የሚከታተሉ በመላው ዓለም ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ያውቃሉ፤ ነገር ግን፣ ኪዳነ ምሕረቶች፡- ከጥምቀት በዓል ራሳቸውን አገለሉ፤ ቀጥሎም በመስቀል በዓል ላይ የመድኃኔዓለምን ካህናት አግልለው በዓሉን ተቆጣጠሩት፤ በዓሉንም የመስቀል ሳይኾን የፖሊቲካ ፓርቲ በዓል አስመሰሉት።

ፓትርያርኩ ለሕክምና መጥተው የሚያሳምም ሥራ ሠሩ

ጉዳይ ዛሬ ያነሣነት ያለምክንያት አይደለም። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለቼክአፕም ቢሉ ሕመማቸውን ለመታከም መጥተው የሚያሳምም ሥራ መሥራታቸውን ስለ ሰማኹ ነው። እኔ ወደምኖርበት ወደ ሜኒሶታ መጥተው ያ ኹሉ መዓት ሲወርድባቸው አዝኜላቸው ነበር፤ አሁን በሰማኹት ነገር ደግሞ አዘንኩባቸው።

በሥዕል የተቀረፀውን ንግግራቸውን አይቻለኹ፡፡ በዴንቨር ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ የ፪ሺ፰ ዓ.ም. የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ላይ ነው። ፓትርያርኩ ለጎጠኞቹ አድልተው የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ለማውገዝ በንግግር ራሳቸውን ማሟሟቅ ጀመሩ። “ያኔ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ባርኬ በመክፈቴ ይቆጨኛልእንዲኑን ባውቅ ኖሮ አልከፍትም ነበርከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ር ወጥቶአል፤” አሉ። ከዚኽ በኋላ ለመቀጠል ግን አልቻሉም፡፡

ሕዝቡ፣ “ፓትርያርክ እንዴት ይዋሻል?” ብሎ ጮኸ፤ የሚበዛውም አለቀሰ፤ “እኛንም ስሙን” ብሎ ደጋግሞ ጮኸ። የሚሰማው ግን አልነበረም፡፡ በዚኽ ምክንያት ታቦቱ ዑደት ሳያደርግ (ክብረ በዓሉ ሳይፈጸም) ተመለሰ። የሕዝቡ ቍጣ በማየሉም እርሳቸውን በጓሮ በር አሾልከው አስወጥተዋቸዋል። ባልንጀሮቼ እንደነገሩኝ የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ በፈረሰኛ ፖሊስ ታጥሮ ነበር። ደስ የሚለው ነገር፣ የኪዳነ ምሕረት ምእመናንም ለበዓል ከመጡ የመድኃኔዓለም ምእመናን ጋር አብረው ሲጮኹ፣ አብረው ሲያለቅሱ ታይተዋል። ይህም ለፓትርያርኩ እና ለጎጠኞቹ የኪዳነ ምሕረት ካህናት ውርደት፥ ለመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ክብር ነው።

ቅዱስ ፓትርያርኩ፡- ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ የሚታወቁት፥ በሬድዮ፣ በመጽሔት እና በጋዜጣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አስተዳደር በመተቸት ነበር። በመኾኑም የአቡነ ጳውሎስን ስሕተት ይደግማሉ ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም። የኾነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ብዙዎች በመዋል በማደር እንደታዘቡት፣ ከእኚኽ ይልቅ አቡነ ጳውሎስ የተሻሉ ነበሩ። አቡነ ጳውሎስን ይቃወሙ የነበረውም፣ “ለምን እኔ አልተሾምኩም፤” በሚል መንፈስ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን አስበው አልነበረም። በኹለቱም ሢመተ ፕትርክና የቄሣራውያኑ ተጽዕኖ ርግጥ ቢኾንም በእኚህኛው አፍራሽነት ግን በእጅጉ የሚያፍሩባቸው፣ የሚቆጩም ይመስለኛል፡፡

ለመጮኽ እናንተ እስክትነኩ ድረስ መጠበቅ ነበረባችኹ?

Denver Colorado Med0Denver Colorado Med1

ለዴንቨር መድኃኔዓለም ካህናት እና ምእመናን የማስተላልፈው መልእክት አለኝ። ለመኾኑ፣ ለመጮኽ እናንተ እስክትነኩ ድረስ መጠበቅ ነበረባችኹ? ቤተ ክርስቲያኒቱ በአማሳኞች እና በጎጠኞች እጅ ወድቃ ስትማቅቅ ስንት ዓመታት ተቆጠሩ? ማኅበረ ቅዱሳን “አሸባሪ” ተብሎ ሲቀጠቀጥ ዝም አላችሁ፤ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት መከራ ስትቀበል ዝም አላችኹ፤ እንዲያውም እስከ ዛሬ የምትባሉት “የወያኔ ቤተ ክርስቲያን” ነው። እንዳልኾናችኁ እኔ በግሌ አውቃለኹ፤ እንዲኾን የሚፈልጉ በመካከላችኹ የሉም ለማለት ግን እቸገራለኹ። እስከ ዛሬ መድኃኔዓለም ጠብቆአችኋል፡፡ ምናልባት ጎጠኞቹ ከራሳቸው ሊያመሳስሏችኹ ታግለው፣ ታግለው አልሳካ ሲላቸው ይኾናል÷ ለማስወገዝ የሞከሩት፤ ምክንያቱም ከእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር እንዳልወጣችኹ ስንኳን ጎጠኞቹ ፓትርያርኩም ያውቃሉ።

በመጨረሻም በሰሜን አሜሪካ ለምትገኙ አብያተ ክርስቲያናትም መልእክት አለኝ። ከመጀመሪያው ጀምሮ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ከነበሩት ከዴንቨር ቤተ ክርስቲያን ተማሩ። ምን ተጠቀሙ? የቤት ልጅ እና የእንጀራ ልጅ ያለ ይመስል በዐደባባይ ተገፉ። ፓትርያርኩ ለጎጠኞች አድልተው ሕዝቡን ከፋፈሉት፤ ትላንት የመሠረቱትን ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ካዱት። ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ግል ካምፓኒ ስለቆጠሩት÷ ሌላ ሰው ማየት አልፈለጉም። ፖለቲከኞች የማያዙበት ከኾነ÷ ይበትኑታል። የሌሎቻችኹም የነገ ዕጣ ፈንታችኹ ይኸው ስለኾነ÷ ከአኹኑ ልትጠነቀቁ ይገ ባል። የቅዱሳን አምላክ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅ።

በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መቀጠል ወይስ ተገፋኹ ብሎ መውጣት?

EOTC Den.Med01

ለመኾኑ የዴንቨር መድኃኔዓለም ሕዝበ ክርስቲያን ምን ትወስኑ ይኾን? በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መቀጠል ወይስ ተገፋኹ ብሎ መውጣት? እንደ እኔ ከማኅበረ ቅዱሳን ተማሩ። ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያ ኹሉ መከራ ሲወርድበት አንድም ቀን ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ለመውጣት አስቦ አያውቅም። ፓትርያርኩ፡- ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያንና ቤተ ክርስቲያንን ግጠው ግጠው በአጥንት ያስቀሩ ሙሰኞችን በፈረጅያቸው ሸፍነው፣ ማኅበሩን “አሸባሪ” በሚል ለእርድ አሳልፈው ሲሰጡ፣ እነርሱ ግን “ቅዱስ አባታችን” ከማለት አቋርጠው አያውቁም። ይህንንም የሚያደርጉት ከልባቸው ነው። ድሮ ድሮ አድር ባዮች ይመስሉኝ ነበር። ውዬ አድሬ ስመለከተው ግን አይደለም፤ ምክንያቱም ቅዱስነታቸው የአባትነታቸውን ድርሻ ባይወጡም፣ እነርሱ የልጅነታቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው። ያውም ልጆቼ አይደላች እየተባሉ።

“እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳየአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል ይዳል።” ይለዋል ይኼ ነው። ሉቃ. ፩፥፲፯።

Advertisements

15 thoughts on “የዴንቨር መድኃኔዓለም ካህናትና ምእመናን:“ከእናት ቤተ ክርስቲያን ወጥታችኋል” በሚል በፓትርያርኩ መገፋታቸውን ተቃወሙ፤“ለሕክምና መጥተው የሚያሳምም ሥራ ሠሩ”/ምእመናኑ/

 1. Anonymous January 3, 2016 at 12:39 pm Reply

  we don’t know when we pass from this world, the only thing what is better to us praying together begging God to give us peace.

 2. T January 3, 2016 at 11:40 pm Reply

  I would have believed half of your story if you hadn’t falsified what happened in Minnesota (where you claim to be residing currently.) If you falsified facts for which you could have been an eye witness to, your credibility for telling a second-hand story is ZERO.
  For the reader’s information regarding Minnesota: https://www.youtube.com/watch?v=dRTOB7p6Wy4

  • Anonymous January 5, 2016 at 1:38 am Reply

   T, I just want to challenge you with some facts. The writer has pointed out correctly that Abune Matias was confronted with angry protesters. That is what you are trying to cover up. Here is the other side of your graceful reception. You better say now a spread is a spread.The train is leaving you behind. He is what he is and you know it.
   http://quatero.net/ethiopia-tplfs-patriarch-aba-mathias-faced-angry-protesters-in-minnesota/

   • T January 6, 2016 at 7:23 am

    The writer chose to reflect the perspective of 8 people and fail to mention the 1000+ parishioners who were the owners of the Minnesota story. That is the reason for giving the writer ZERO credibility. For your consumption: The chatters of 8 people doesn’t mean diddly-squat to the 1000+ parishioners who welcomed His Holiness Abune Matthias Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church with utmost humility and received countless blessings from His Holiness. That is calling a spade a spade. Take your politics back to Starbucks or your tehadiso-self back to your assembly halls/discothèque. Waste no energy; your venom won’t change our love and respect for our religion, the mother church, the Holy Synod, and the Patriarch. You may wanna be careful not to swallow your own venom. Read and reread Diacon Daniel Kibret’s article: http://www.tewahedo.org/dan_upload/upload/The%20mother%20church%20mean.pdf
    .
    Also, you may want to consider to take part in our joy: https://www.youtube.com/watch?v=Q7MAX6hDNYw

 3. Anonymous January 4, 2016 at 5:08 am Reply

  የምንሰራው ሥራ ሁሉ ስጋዊ እየሆኑ የመጡ ይመስላል ምክንያቱም የሚሰሙት ነገሮች ከመንፈሳዊውም ከምድራዊውም ሰው
  ከማቅረብ ማራቅ
  ከማስታረቅ ማጣላት
  ከመሳመን ማስካድ
  ከማዳን መግደል
  ከማክበር ማቃለል
  ከመስራት ማውራት
  ከእውነት ሐስት
  ከመሞት መግደል
  ከህሊና ሆድ በተለይ በሃይማኖት አባቶች በኩል የሚሰሙት ነገሮች እጅግ የሚያሰሳዝኑ እየሆኑ መጥተዋል እናም ከመለያየት አንድነት ከመገፋፈት መቀራረብ የተጠራነው ለምድራዊ ሳይሆን ለሰማያዊ ርስት ስለሆነ ማንም በምድር ላይ ካለው አትርፎ ይዞት የሄደው ነገር የለም ሊነር የሚችለው ይዞት ሊሄድም ሥራው ነውና ሁላችንም ለሀገር እና ለወገን የሚበጅ ስራ ሰርተን እንለፍ በተላይ የሃይማኖት አባቶች ቆምብለን ህዝቡ የሚያምነንን ከጌታ በተሰጠን ስልጣን በአግባቡ እናገለልግል በአገልግሎታችን እግዚአብሔር እንዲያከብርን.
  እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅልን
  አሜን.

  • Anonymous January 4, 2016 at 6:24 pm Reply

   ቃለ ህይወት ያሰማልን

 4. Anonymous January 4, 2016 at 1:04 pm Reply

  ደብሩ ከፓትርያርኩ ጋር ነው ያልተግባቡት ወይስ ማኅበረቅዱሳን ከፓትርያርኩ ጋር ነው ያልተስማሙት?ደብሩና ማኅበረቅዱሳን አንድ ተደርገው መቅረባቸው ስላልገባኝ ነው፡፡የማኅበረቅዱሳን የሚባል ደብር ያለ አይመስለኝም፡፡ስለዚህ ጉዳዩን ከሀገር አቀፉ ማኅበር ጋር ከማያያዝ አጥቢያው ራሱን ችሎ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ቢፈታው ይሻላል፡፡ሁሉን አጣጥሎ ማኅበረቅዱሳንና አባላቱን ብቻ ንጹሐን አድርጎ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለደጋግ ሰዎች የተነገሩ ጥቅሶችን ሁሉ ለእነሱ አሸክሞ ለግል አጀንዳ ማስፈጸሚያነት መጠቀም ትርጉም የለሽ ነው፡፡ጳጳስ፣ፓትርያርክና ተቋም በጅምላ በማጠልሸት ራሳችሁንና እናንተ የታቀፋችሁበትን ማኅበር ብቻ ጻድቅ የምታደርጉ ጸሐፍያን ትውልዱን ስለማትጠቅሙት ሚዛናዊ ለመሆን ሞክሩ፡፡ጣት መቀሰር ሲበዛ ያስቀይማል፤ያቀያይማል፡፡ሚዛናዊ ሁኑ፡፡

  • Anonymous January 4, 2016 at 4:01 pm Reply

   Damot Eat Dom means blood stop talking false Egziabher Endiferdibh tetenkek Betekrstiyan yemibedl and ken wagawan yagegna Behegeritwa Higiyalyaze poletikegna Mahbere kidusan bicha new Aynhih sebara spokiyonew mayet YEMIGEBAW eyasadegkut aydelme

 5. ዳሞት January 4, 2016 at 2:50 pm Reply

  እኔም በዴንቨር ነዋሪነኝና ሥለእውነት ከሆነ የዴንቨር መድኀኒአለም አገልጋዮችና ምእመናኑ ባይሰየፉም ስለእምነታቸው ሰማእትነትን እየከፈሉ ያሉ ናቸው ማለት ይቻላል። እኔም በርቱ በሀይማኖት ቁሙ እላቸዋለሁ፡

 6. Anonymous January 6, 2016 at 2:18 am Reply

  Egziabeher yemesgen sele hulum neger.

 7. ዘሚካኤል January 9, 2016 at 11:02 pm Reply

  ማኅበረ ቅዱሳን እኮ ብቻውን የቆመ አካል አይደለም፤በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ያለ የአገልግሎት ማኅበር ነው።ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ናት፥ስለዚህ፡-ማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊ ማኅበር በመሆኑ፥ቤተ ክርስቲያን ያለ ጥርጥር የእርሱ ናት ።ለዚህም ነው ተሀድሶዎችና ዘረኞች ሊያፈርሷት ሲታገሉ፥እርሱ ግን እንዳትፈርስ እየታገለ ያለው።የፕሮቴስታንት የጦር አርበኞች ተሀድሶዎች እንደ አባታቸው ሓሳዊ መሲህ፥ዲያብሎስ የሰጣቸውን የስድብ አፍ፡-እንደ መቃብር ቢከፍቱበትም ሥራውን ቀጥሎአል። ዘረኞች ኢትዮጵያን በዘር ሲከፋፍሉ፥ማኅበረ ቅዱሳን ግን ሁሉንም ዘር ሰብስቦ፡-“በክርስቶስ አንድ አካል ነን፤” የሚለውን በተግባር እያሳየን ነው።ተሀድሶዎች፡-የኦርቶዶክስ የሚለውን ፍቀው የመካነ ኢየሱስ ወይም የመሉ ወንጌል ወይም የመሠረተ ክርስቶስ ለማለት ቸኵለዋል።ፕሮቴስታንቱ እንደው እንደ አሜባ ተከፋፍለው ተበታትነዋል፥አንዷን ኦርቶዶክስ ስንት ቦታ ሊከፋፈሏት እንዳሰቡ ሰይ ጣን ብቻ ነው የሚያውቀው።ዘረኞቹም “የኤርትራ ኦርቶዶክስ፤” እንዲል፡-“የትግራይ ኦርቶዶክስ፣የአማራ ኦርቶዶክስ፣የኦሮሞ ኦርቶዶ ክስ፣ የጉራጌ ኦርቶዶክስ፣የካምባታ ኦሮቶዶክስ፣የሀድያ ኦርቶዶክስ፣የወላይታ ኦርቶዶክስ፣ወዘተ…ለማለት ቸኵለዋል።ነገር ግን ለሁለ ቱም የጥፋት መልእክተኞች ማኅበረ ቅዱሳን እንቅፋት ስለሆነባቸው፥ባይዝላቸውም፡-በህልማቸውም በውናቸውም እየረገሙት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ “ጆሮ ዳባ ልበስ፤” ብሎ ገዳማትና ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ት ቤቶች(የሊቃውንት ምንጭ የሆኑ የቆሎ ት/ት ቤቶች) እንዳይዳከሙና እንዳይዘጉ ሃያ አራት ሰዓት እየሠራ ነው።ድሮ ድሮ፥የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን የሚናጠቋቸው መናፍቃን ነበሩ ፥አሁን ግን አርቆ አሳቢ የነበሩት የዝዋዩ አቡነ ጎርጎርዮስ በዘረጉት የወንጌል መረብ፥ሙሉ በሙሉ የኦሮቶዶክሳውያን ሆኖአል።በዚህ ዓመት እንኳ በመላው ሀገሪቱ ባሉ የትምህርት ተቋማት ከሚማሩ ወጣቶች፥ከሦስት መቶ ሃምሣ ሺህ በላይ የሚሆኑትን በየሚቀርባ ቸው ቤተ ክርስቲያን ሰብስቦ መንፈሳዊ ትምህርት እያስተማራቸው ነው።ለዚህም፡-ዘመናዊም መንፈሳዊም ሙያ ባላቸው የቤተ ክርስ ቲያን ልጆች ሥርዓተ ትምህርት አስቀርጾ፥የመማሪያ መጻሕፍትን እና የመምህሩን መምሪያ አዘጋጅቶ ወጥ የሆነ ትምህርት እየሰጠ ነው።ማኅበረ ቅዱሳን፡-ቤተ ክርስቲያንን ግጠው ግጠው በአጥንት ላስቀሩ የደብር አስተዳዳሪዎችና የቢሮ ሠራተኞች(ቀበኞችም) አል ተመቻቸውም።የእግዚአብሔርን ገንዘብ እንዳይዘርፉ የእንቅፋት ደንጊያ ሆኖባቸዋል፥ስለዚህ በፈጠራ ክስ በቤተ ክህነቱም በቤተ መን ግሥቱም ለማስመታት ሃያ አራት ሰዓት እየሠሩ ነው።ማኅበረ ቅዱሳን፡- ከዘረኞች፣ከተሀድሶ ፕሮቴስታንት እና ከሙሰኞች ምርቃት አይጠብቅም፥ተሳስተው ቢመርቁት እንኳ የረገሙት ያህል ያመዋል።አንድ ሰሞን፡-አባይ ፀሐዬ መንበረ ፓትርያርክ ተገኝተው፥ማኅ በረ ቅዱሳንን ሲያስጠነቅቁ በቀጥታ በቴሌቪዢን ተላለፈ፥ጠላቶች እሰይ ስዕለታችን ሠመረ አሉ።በሰሜን አሜሪካም አንድ ቋንቋ ተና ጋሪ የሆኑ ካህናት ቴሌ ኰንፍረንስ አድርገው፡-“ማኅበረ ቅዱሳንን፡- ከውጪዋ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እናጥፋው፤” ተባባሉ። አንድ ሰሞን ደግሞ፡-ሟቹ መለስ ዜናዊ፡-በምክር ቤት ስብሰባ ላይ፥ማኅበረ ቅዱሳንን፡-“የኦርቶዶክስ አልቃይዳ፤” አለው ብለው ሠርግና ምላሽ አደረጉ፤ቅልቅል ግን ያስፈራቸዋል።እነዚህ ሰሜን አሜሪካ የመሸጉ ካህናትም፡-በማኅበረ ካህናት ስም በቴሌ ኰንፍረንስ ምክረ አይሁድ አደረጉ።የተቀዳውንም ድምፅ ደጀ ሰላም አሰማችን።እነርሱም በዚህ ሳያፍሩ በሲያትሉ “አባ” ወልደ ሰማዕት መሪነት ማኅበረ ቅዱሳንን፡-“ውጉዝ ከመ አርዮስ፤” ብለው የተፈራረሙበትን ደብዳቤ፥ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እና ወደ አምስት ኪሎ መን በረ ፓትርያርክ ላኩ።መሪዎቹ የአሜሪካኑ ደብዳቤ ሳይደርሳቸው በፊት የሰማዩ ደብዳቤ ደረሳቸውና ይህችን ዓለም ተሰናበቱ።አዲስ የተተኩት ፓትርያርክም ሰሜን አሜሪካ በነበሩበት ጊዜ፥“የማኅበረ ቅዱሳን የልብ ወዳጅ ነኝ፤”ይሉ እንዳልነበረ፥“ቤተክር ስቲያን በማ ኅበረ ቅዱሳን በቅኝ ግዛት ተይዛለች፤” ሲሉ ሰማናቸውና ጆሮአችንንም ዓይናችንንም ተጠራጠርን።ቀጥለውም ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብ ከት እውቅና ውጪ የአድባራት አለቆችን ሰብስበው፡-ማኅበሩን ሲያወግዙና ሲያስወግዙ ሰማን፥አየን።እኛም ከእንግዲህ ዓይንንም ጆሮንም መጠራጠር አይገባም አልን።ተሀድሶዎችና ዘረኞች ደግሞ “አቡነ ጳውሎስ ለዘብተኛ ነበሩ፥እኚህ ቆራጥ ናቸው፤” አሉ።እርሳ ቸውም፡-“አባይ ፀሐዬ ቆራጥ ኖት፥ብሎ አመስግኖኛል፤” ብለው ሳያፍሩ በስብሰባ ላይ ተናግረዋል።ቆራጥነታቸውንም በአዲስ አበባ እንዳሳዩት ሁሉ በሰሜን አሜሪካም በዴንቨር ኪዳነ ምሕረት አሳይተዋል።

 8. kdste January 14, 2016 at 6:47 am Reply

  28 wyese29 b2008 e.c

 9. Anonymous January 15, 2016 at 5:30 am Reply

  reporter/profet/ Desalagn/in ziway karchele/
  is it z next target will be mahibre kidusan?
  Desu wondimachin Egzabher yifta yitebikhi.
  refer

 10. Anonymous March 4, 2016 at 9:34 pm Reply

  Remember that:
  MONEY, BELLY AND LIE will pass away. TRUTH will not be covered in front of God whats so ever supported by false medias, talkative, propaganda and supporters. God knows who is who of its followers. And the patriarch and the synod and the bishops too. Don’t feel happy by misleading the followers who has no information about your strategic moves to snatch money from the followers in the pretext of helping unknown monasteries and safeguarding the church. Stop your accusation of the innocent.REMEMBER THAT YOU ARE MORTAL AND STAND IN FRONT OF THE HEAVENLY JUDGE AND STICK TO THE TRUTH AND YOUR MIND. FABRICATE NOT FALSE MOVIES, DOCUMENTS AND NEWS.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: