“የሊቀ ጳጳሱ ልጅ ነኝ” በሚል የቀረበን ጥያቄ ፍ/ቤቱ ውድቅ አደረገ

  • የፍትሐ ብሔር ክርክሩ ከአራት ዓመታት በላይ ፈጅቷል

*           *          *

  • በሥር ፍ/ቤት የተሰጠው ቃል በጥናት እና ለመረዳዳት ታስቦ የተሰጠ ቃል ነው ከሚባል በቀር፣ በአቤቱታው የተገለጸው ስለ መፈጸሙ ተገቢው ማጣሪያ ተደርጎበት ቢኾን ማረጋገጥ ቀርቶ ለጥርጣሬ የሚያበቃ ፍንጭ የማይሰጥ ኾኖ ተገኝቷል፡፡(ፍ/ቤቱ)

*          *          *

(አዲስ አድማስ፤ ማኅሌት ኪዳነ ወልድ፤ ቅዳሜ፣ ኅዳር ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

Federal high court 2008A
የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፤ በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ ነው – “የሊቀ ጳጳሱ ልጅ ነኝ” የሚል የወራሽነት አቤቱታ ለፍ/ቤት ቀርቦ የፍትሐ ብሔር ክርክር ሲደረግበት የቆየው፡፡

“የሟች ልጅ ነኝ” የሚል አቤቱታ ያቀረቡት አቶ ዮሐንስ ተክለ ሚካኤል፤ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል (በቀድሞ ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ ተክለ ሚካኤል ዓባይ) እንዳሳደጓቸው በመግለጽ እና ተወላጅነቴን ያስረዱልኛል ያሏቸውን ሰነዶች በማያያዝ፣ የሰዎችን ምስክርነት ለፍ/ቤት አሰምተዋል፤ ፍ/ቤቱም ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም የልጅነት ማረጋገጫ ውሳኔውን አሳወቀ፡፡ ጉዳዩ ግን በዚሁ አልተቋጨም፡፡ የሊቀ ጳጳሱ እኅት፤ የፍ/ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ጠይቀዋል፡፡

በአቶ ዮሐንስ የቀረበው የልደት እና የጥምቀት ምስክር ወረቀቶች በአግባቡ የተረጋገጡ አይደሉም፤ ልጅነቱ በሳይንሳዊ መንገድ በዲ.ኤን.ኤ መረጋገጥ አለበት በማለት መቃወሚያ አቅርበዋል – የጳጳሱ እኅት ወ/ሮ በላይነሽ ዓባይ፡፡ “ሊቀ ጳጳሱ አሳድገውኛል ከማለት ውጭ፣ ሊቀ ጳጳሱ በልጅነት እንደተቀበሉት የሚያሳይ ማስረጃ አልቀረበም፤” ያሉት ወ/ሮ በላይነሽ፤ “በተጨማሪም በቀረበው የጥምቀት እና የልደት ካርድ ላይ የአባት ስም የተቀየረው ሊቀ ጳጳሱ ከሞቱ በኋላ ነው፤” ብለዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ በሰጡት መልስ፣ “ወ/ሮ በላይነሽ የጳጳሱ እኅት መኾናቸውን አላውቅም፡፡ በሕይወት እያሉ እኅት አለኝ አላሉኝም፤” ብለዋል፡፡ “የአባቱን ስም ቀይሯል” ለሚለው ተቃውሞ አቶ ዮሐንስ ምላሽ ሲሰጡም፤ በሟች አባቴ እና በእናቴ ስምምነት፤ እናቴ ቤተሰቦችጋ ነው ያደግኹት፡፡ በዚኽ ምክንያት፣ በእናቴ አባት ስም ስጠራ ቆይቻለኹ፤” ብለዋል፡፡ “ከልደት እና ከጥምቀት ወረቀት ውጭ፤ የሰው ምስክሮች አስደምጫለኹ፡፡ ከምስክሮቹ አንዷም እናቴ ናት፤” በማለትም ተከራክረዋል፡፡

የይግባኝ ክርክሩን የዳኘው ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ በአቶ ዮሐንስ የቀረበው የልደት የምስክር ወረቀት ሕጋዊነት እንደሌለው ገልጾ፤ በክሊኒክ የተመዘገበ የወሊድ መረጃዎችንም ጠቅሷል፡፡ በክሊኒኩ የተመዘገበው የወላጅ እናት አድራሻ የተሳሳተ እንደ ኾነ ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፤ የወላጅ እናት ዕድሜ ተብሎ የተመዘገበው መረጃም፤ ከዮሐንስ እናት ዕድሜ ጋር በሰፊው ይራራቃል፤ ብሏል፡፡

Federal high court 2008
ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስከ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም
ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ በሰጠው ውሳኔ፣ “አቶ ዮሐንስ የሊቀ ጳጳሱ ልጅ አይደሉም፤” በማለት የሥር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሽሯል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. መጀመሪያ አንሥቶ ሲደረግ ለቆየው የፍትሐ ብሔር ክርክር በተሰጠው ፍርድ፣ በሥር ፍ/ቤት የተላለፈ እግድ መነሣቱን ጨምሮ ልዩ ልዩ ትእዛዞች በችሎቱ መሰጠታቸው ታውቋል፡፡

His Grace Abune Mikael

ብፁዕ አቡነ ሚካኤል (ከ1942 – 2003 ዓ.ም.)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ ለማዕርገ ጵጵስና የሚመረጡት፣ በሥርዓተ ምንኵስና በድንግልና መንኵሰው በክህነት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያገለግሉ ሲኾኑ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በመጥቀስ በጣልቃ ገብ መከራከሯን የፍርድ ሐተታው ያመለክታል፡፡

በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ፣ ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም. ከተሾሙት 17 ብፁዓን አባቶች አንዱ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣ ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ – ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ባሻገር ለተወሰኑ ወራት የወላይታ፣ ዳውሮና ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው አገልግለዋል።

ከሐሞት ጠጠር የተነሣ ሕመም የነበረባቸው ብፁዕነታቸው፣ የቀዶ ጥገና ሕክምናቸውን በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በመከታተል ላይ ሳሉ ነበር ከሰመመን መንቃት ሳይችሉ ሕይወታቸው ያለፈው፡፡

ሥርዐተ ቀብራቸው ነሐሴ 10 ቀን 2003 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተፈጸመበት ወቅት በተሰማው ዜና ሕይወታቸው፤

በቀድሞው ዐድዋ አውራጃ በዕምባ ሰነይቲ ወረዳ በላውሳ ቅዱስ ገብርኤል አካባቢ ከአለቃ ዓባይ ወልደ ገብርኤል እና ከወ/ሮ ታደለች ንጉሤ በ1942 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

በኤጲስ ቆጶስነት ከመሾማቸው በፊት በተለያዩ ጊዜያት፡- በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስኮላር ሽፕ ዋና ክፍል ሓላፊ፤ የገዳማት መምሪያ ሓላፊ፤ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ፣ የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ፤ የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ዲን፤ በቀድሞው የኤርትራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የዕቅድ እና ጥናት መምሪያ ሓላፊ፤ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ሓላፊ እና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት በመኾን አገልግለዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያንና በዘመናዊ ትምህርት ዝግጅታቸውም፡- በታላቁ በደብረ ዓባይ ገዳም ከመምህር አበራ እና ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ከመሠረተ ትምህርት እስከ ጸዋትወ ዜማ፣ ከመምህር የኔታ የኋላ እሸት መዝገበ ቅዳሴ ጠንቅቀው ከተማሩ በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

መዓርገ ምንኵስናን በዋልድባ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ በጎንደር ክፍለ ሀገር በወገራ አውራጃ በጉንተር አቦ ከመሪጌታ ሐረገ ወይን፣ ጎንደር ከተማ ከመምህር ዕፁብ ቅኔ ተምረው ተቀኝተዋል፡፡ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እያገለገሉ የአንደኛ እና መለስተኛ ኹለተኛ ደረጃ ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት በአዳሪነት ገብተው የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በእንግሊዝ ለንደን ሴንት ኤድዋርድስ ኮሌጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለአንድ ዓመት፤ በግሪክ የአቴንስ ዩኒቨርስቲ ለስድስት ዓመታት ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር በቴዎሎጂ የማስትሬት ዲግሪ፤ በአሜሪካ ሆሊ ክሮስ በተባለው የግሪክ ሴሚነሪ በሲስተማቲክ ቴዎሎጂ ዲፕሎማ፤ በቦስተን ዩኒቨርስቲ የኤስ.ቲ.ኤም ወይም በፓስተራል ካውንስሊንግ/ሳይኮሎጂ/ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

Advertisements

3 thoughts on ““የሊቀ ጳጳሱ ልጅ ነኝ” በሚል የቀረበን ጥያቄ ፍ/ቤቱ ውድቅ አደረገ

  1. Anonymous December 5, 2015 at 4:02 pm Reply

    No need to write all this about his education.

  2. Anonymous March 23, 2016 at 10:58 am Reply

    yemane is leading the corrupt practice in the church system. this could further be exemplifed by the situation in SAMiITst. Giorgis church which is managed only by the administrator, secretary, casher and accountant without involving any representative from the community. the complain of the public about this dangerous situation in the face of Yemane was rejected because of the huge amount of money deliveded to Yemane as tangible information reveal

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: