በአቃቂ ቃሊቲ: ለ52 ዓመታት ያገለገለው የባሕረ ጥምቀት ቦታ ለመናፈሻ በሚል ቀንና ሌሊት እየተቆፈረ ነው

  • “ክ/ከተማው ቦታው አይነካባችኹም ብሎ አዘናግቶናል፤ ለሌላ ዓላማ መዋሉ አሳዝኖናል” /ምእመናን/
  • “ለሌላ ዓላማ ሳይውል አጥቢያዎቹ በዕቅዳቸው እንዲያለሙት አመራር ይሰጥላቸው” /ቅ/ሲኖዶስ/
  • “ልማቱ በዓለ ጥምቀቱን ታሳቢ ያደረገ ነው፤ ቦታው በታቦት ማደርያነቱ ይቀጥላል” /ክ/ከተማው/
Akaki Kaliti Bahire Timket

ባሕረ ጥምቀቱን የሚያስከብር የልማት ፕሮጀክት ለማከናወን ከማንም በፊት ዐቅደን ፈቃድ እየጠየቅን ባለንበት፣ መናፈሻ ይሠራል በሚል የተሰጠው ሌላ አካል ፓውዛ ተክሎ፣ ኤክስካቫተር አስገብቶና የሰው ኃይል ጨምሮ ቀንና ሌሊት እየቆፈረና ከአርባ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸውን ዛፎች እያወደመ ይገኛል፤ ይህም ሕዝቡንና ቤተ ክርስቲያንን አሳዝኗል፤” /የምእመናኑ ኮሚቴ/

(አዲስ አድማስ፤ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ቅዳሜ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

ላለፉት 52 ዓመታት በበዓለ ጥምቀት ማክበርያነት እና በታቦት ማደርያነት ሲያገለግል የነበረው የባሕረ ጥምቀት ቦታ ለሌላ አገልግሎት መዋሉ እንዳሳዘናቸው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የዘጠኙ አድባራት አስተዳዳሪዎች እና ምእመናን ገለጹ፡፡

ቦታውን በዘመናዊ መንገድ አልምተው፣ ለምእመናን ማንበቢያ እና ለአረጋውያን ማረፊያ ለማድረግ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን የፕሮጀክት ምክር ሐሳብ ለክፍለ ከተማው አስገብታ ስትጠይቅ መቆየቷን የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች እና የምእመናን ተወካይ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል፡፡

የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኮት ይኄይስ እንደተናገሩት፤ ይህ ጉዳይ እልባት አግኝቶ ቦታው ለባሕረ ጥምቀቱ አገልግሎት እንዲውል በየደረጃው ደብዳቤ ቢያስገቡም ሰሚ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉነህ ፈይሳ በበኩላቸው፤ አኹን ቦታውን እያለማ ያለው የአዲስ አበባ ውበት መናፈሻ እና ዘላቂ ማረፊያ ኤጀንሲ እንደኾነ ጠቅሰው፣ በሚከናወነው ልማት ቦታው ባሕረ ጥምቀት እና የታቦት ማደርያ መኾኑን ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ተዘጋጅቶ የሕዝብ መናፈሻ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራበት መኾኑን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

“ላለፉት 52 ዓመታት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የተከሏቸው እና ያለሟቸው ዛፎች እየተገነደሱ ቦታው ወደ በረሓማነት ሊቀየር ነው፤” ያሉት የኮሚቴው አባላት፤ “እየተሠራ ያለው ሥራ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ጋር ፍጹም የሚቃረን በመኾኑ እንቃወመዋለን፤” ብለዋል፡፡

ለክፍለ ከተማው ያስገቡት የልማት ፕሮጀክት ምክረ ሐሳብ ወደሚመለከተው አካል መምራቱን ምእመናኑ አስታውሰው፣ ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር የሥራ መጀመሪያ ገንዘብ እንዲያሳዩ ተጠይቀው፤ 2.1 ሚሊዮን ብር የልማት በጀት እንዳላቸው ቢያሳዩም ልማቱ ዛሬ ነገ እየተባለ ሳይፈቀድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ 

“በዓለ ጥምቀት ስታከብሩበት የኖራችኹበትን ቦታ ማንም አይነካባችኹም፤ ይህን ለምእመናኑም አሳውቁ፤” በማለት ክፍለ ከተማው እንዳዘናጋቸው የኮሚቴው ሰብሳቢ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኰት ይገልጻሉ፤ አያይዘውም፣ “ባሕረ ጥምቀቱን የሚያስከብር የልማት ፕሮጀክት ለማከናወን ከማንም በፊት ዐቅደን ፈቃድ እየጠየቅን ባለንበት፣ መናፈሻ ይሠራል በሚል የተሰጠው ሌላ አካል ፓውዛ ተክሎ፣ ኤክስካቫተር አስገብቶና የሰው ኃይል ጨምሮ ቀንና ሌሊት እየቆፈረና ከአርባ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸውን ዛፎች እያወደመ ይገኛል፤ ይህም ሕዝቡንና ቤተ ክርስቲያንን አሳዝኗል፤” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፤ ቦታው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ይዞታ እንደ ኾነ ጠቁመው፣ ቤተ ክርስቲያን በቦታው ላይ የይዞታ መብት ሳይኖራት እንዴት ቦታውን ላልማ ትላለች፤ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን ይበሉ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ለወቅቱ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ በጻፈው ደብዳቤ፤ የከተማዋን ልማት ቤተ ክርስቲያን እንደምትደግፍ ገልጾ፣ የአቃቂ ቃሊቲ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከ41 ዓመታት በላይ ለባሕረ ጥምቀት እየተገለገሉ ያቆዩት ቦታ ለሌላ አገልግሎት ከመዋሉ በፊት አብያተ ክርስቲያናቱ በቦታው ላይ ሊሠሩት ያቀዱትን የልማት ሥራ ማከናወን እንዲችሉ አመራር እንዲሰጥላቸው አሳስቦ ነበር፡፡

የኮሚቴው ተወካዮችም፣ ይህንኑ የቅዱስ ሲኖዶሱን የማሳሰቢያ ደብዳቤ ከፕሮጀክት ምክረ ሐሳቡ ጋር አያይዘው ለክፍለ ከተማው ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ኀሙስ በቦታው ተገኝተን እንደታዘብነው፤ ቦታው እየተቆፈረ የግንባታ ሠራተኞች ሥራውን የቀጠሉ ሲኾን በርካታ የግራር ዛፎችም ተቆርጠው ተከምረዋል፡፡ በሥፍራው በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ከምእመናን ኮሚቴ አባላት ጋር በመነጋገር፣ የተሰበሰበው ሰው እንዲበተን ያዘዙ ሲኾን አባቶችም በጸሎት አሳርገው ሕዝቡን አረጋግተው ወደየመጣበት መልሰዋል፡፡

“እኛ ጠብ እና ግርግር አንፈልግም፤ መንግሥት ችግራችንን ያውቀዋል ብለንም አንገምትም፤” ያሉት የኮሚቴው አባላት፣ “እስከ አኹን መልስ ለማግኘት ያንኳኳናቸው በሮች ስላልተከፈቱልን ጉዳዩን በብዙኃን መገናኛ በኩል ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለማሰማት ተገድደናል፤” ብለዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፤ “ቦታው በታቦት መግቢያነቱ እና መውጫነቱ ይቀጥላል፤ ይህን የከለከለ የለም፤ የመናፈሻው ዲዛይንም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው፤” ሲሉ ተቃውሞውን አስተባብለዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አምኃ መኳንንትን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ዝግ በመኾኑ ሐሳባቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡ የኮሚቴው አስተባባሪዎችና ምእመናኑ ግን፣ አማራጭ የባሕረ ጥምቀት ቦታ ባለመኖሩና በዓሉን እዚያው ለማክበር የሚገደዱ በመኾኑ የሚመለከተው አካል አስቸኳይ እልባት እንዲሰጣቸው በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡   

Akaki Kaliti Bahire Timket01
ላለፉት 52 ዓመታት ወደ አቃቂ ቃሊቲ ባሕረ ጥምቀት በመውረድ፣ ከጥር ፲፩ እስከ ፲፫ ቀን በዓለ ጥምቀትን ሲያከብሩ የቆዩት አድባራት ጠቅላላ ቁጥር 25 ሲኾን ከእነርሱም፤ ደብረ ሰላም ቱሉ ዲምቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም፣ ሳሎ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጃቲ መካነ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት፣ ቃሊቲ መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል፣ ፈንታ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ፈጬ ቅድስት ማርያም፣ ቀርሳ ቅድስት ልደታ እና ሰርቲ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ይገኙበታል፡፡

  

Advertisements

3 thoughts on “በአቃቂ ቃሊቲ: ለ52 ዓመታት ያገለገለው የባሕረ ጥምቀት ቦታ ለመናፈሻ በሚል ቀንና ሌሊት እየተቆፈረ ነው

  1. Anonymous November 7, 2015 at 2:10 pm Reply

    ይህ መንግስት በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ይዞታ በመዳፈር ከደርግም በላይ እየሆነ ነው፡፡ ዝምታችን ለምን ይሆን ሆ ብለን ልንወጣ ያስፈልጋል የጀመሩትን ማቁዋረጥ አለባቸው ፡፡ መናፍቃንንና እምነት የለሽን እየመደበ ያሰድበናል ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ በቦታው ባለቤትም ብትሆን አይደል ከ 50 ዐመት በላይ ዛፍ እየተከለች ቦታውን ስትንከባከብ የኖረችው፡፡ ዛሬ ተወልደው እናስተምራትስ እያሉ አይደል እነዚህ ያልተማሩ ፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ አስተዳዳሪዎችና ካህናት ምዕመኑን በመቀስቀስ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣ ማድረግ አለባቸው እነዚህን ሰዎች ንቀታቸውን በህብረታችን ልናሳይ ይገባናል፡፡ አንድ አንድ አስተዳዳሪዎችም የውስጥ ስራ ሊሰሩ ስለሚችሉ ልንነቃባቸው ይገባል፡፡ የይሁዳ ቢጤዎች አይጠፉምና፡፡ በአስቸኩዋይ መልስ ካልሰጡ ህዝቡን ሰብስበው ለሰላማዊ ሰልፍ ካልጋበዙ ተጠያቂ እንደሚሆኑና ትውልድ ሲፋረዳቸው እንደሚኖር ሊያውቁ ይገባል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ደብዳቤ እንደጻፉት ሁሉ አቡነ ማትያስም ያንን ደብዳቤ መሰረት አድርገው ለሚመለከተው በአስቸኩዋይ ጉዳዩን እንዲያውና እንዲያስቆም መመሪያ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባቸዋል ያለበለዚያ በፕትርክና ዘመናቸው ቤተክርስቲያን ይዞታዋን ያጣችበት ተብሎ ከወቀሳ እራሳቸውን ማዳን አለባቸው፡፡

  2. Anonymous November 18, 2015 at 12:28 pm Reply

    እግዚአብሔር ኃይልና ሥልጣኑን ያሳያል ብለን እናስባለን፡፡ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆነ ሁሉ በፀሎት ጉዳዩን እንዲይዘው ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ ድንግል ማርያም ከልጃ ጋር ሆና ትርዳን፡፡ አሜን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: