ቅ/ሲኖዶስ: ከብር 159 ሚሊዮን በላይ ዓመታዊ በጀት አጸደቀ፤ ስብሰባው ተጠናቋል፤ መግለጫም ይሰጣል

Holy Synod Tik2008

  • ለመሪ ዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ ከኹለት ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቧል
  • የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ ችግር የሚያጠና ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሟል
  • የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት በኮሚቴው ጥናት ተካተዋል
  • የጥናቱ ግኝትና መፍትሔ ተቋማዊ ህልውናዋንና አቅጣጫዋን ይወስና

የ፳፻፰ ዓ.ም. የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፪ ቀን ከቀትር በፊት ያጠናቀቀው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለመንበረ ፓትርያርኩ የብር 159,316.269.22 ዓመታዊ በጀት አጸደቀ፡፡

በጸደቀው በጀት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መደበኛ ወጪዎች ብር 39,548,583.24፤ ለአህጉረ ስብከት ድጎማ ብር 14,497,309.45 ተመድቧል፡፡ ምልዓተ ጉባኤው፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ በአጀንዳው ይዞ ባካሔደው ውይይት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ማስፈጸሚያ ብር 1,054,200 የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ወስኗል፡፡

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ተጨማሪ የካህናት ማሠልጠኛዎች የሚቋቋሙ ሲኾን በእነርሱና በሌሎችም አህጉረ ስብከት ሥር ለሚገኙት ማሠልጠኛዎች ብር 4,417,129 ወጪ ተመድቧል፡፡

ለከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን የደቀ መዛሙርት ምልመላና ቅበላ እንዲኹም የሥርዐተ ትምህርት ጥራት ከፍተኛ የድጋፍና ክትትል ሥራ እንዲሠራ በማሳሰብ፤ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ለቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በአጠቃላይ ብር 13,827,160.78 በጀት ተወስኗል፡፡

ለአብነት ት/ቤቶች ማጠናከርያ፣ ለጥንታውያን ገዳማት መደጎሚያ፣ ለ18 የንባብና ቅዳሴ ቤቶች እንዲኹም ለአንድነት ገዳማት መንፈሳዊ ት/ቤቶች ማቋቋሚያ በድምሩ የብር 9,397,799 ድጋፍና እገዛ ይደረጋል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻ ንግግር እንደተመለከተው፣ ጥናቱ ለተጠናቀቀው የቤተ ክርስቲያን የመሪ ዕቅድ ጥናት የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት ትግበራ ሥራዎች ብር 2,500,000 በቅዱስ ሲኖዶሱ ተመድቧል፡፡

መሪ ዕቅዱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ሥራዎች በመምራት፣ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ ለመቅረፍ እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡

በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በሙስና መስፋፋት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች አስፈጻሚ ማጣት እና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታዎች የተነጋገረው ምልዓተ ጉባኤው፤ የኹለንተናዊ ችግሮችን መሠረታዊ መንሥኤዎች አጥንቶ መፍትሔ የሚያቀርብ ዘጠኝ አባላት ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡

ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ አቡነ ሳሙኤል፣ አቡነ ጎርጎሬዎስ እና አቡነ ሳሙኤል ለዐቢይ ኮሚቴው የተወከሉ ሲኾን የተቀሩት ስድስቱ ከተቆርቋሪ ምእመናን የሚመረጡ ከፍተኛ ባለሞያዎች እንደኾኑ ተገልጧል፡፡

በትግበራው፣ በቀደሙት እልክ አስጨራሽ ሙከራዎች እንደታየው፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ለውጥና ዕድገት የማይሹ አማሳኞች፣ ጎጠኞች፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንና አድርባይ ፖሊቲከኞች ለሚፈጥሩት አሻጥር፣ ዕድል የማይሰጥበትና ምሕረት የማይደረግበት እንደኾነም ተጠቁሟል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው፣ ለዐሥራ ኹለት ቀናት ያካሔደውን ስብሰባ ዛሬ፣ ከቀትር በፊት ያጠናቀቀ ሲኾን ተሲዓት በኋላ በ9፡00 በስብሰባው አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
******************

እርማት፡- የመሪ ዕቅድ በጀቱ “ከአምስት ሚሊዮን በላይ” በሚል በመጠቆሚያው የተጠቀሰው፣ ከኹለት ሚሊዮን በላይ ተብሎ እንዲታረም ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Advertisements

2 thoughts on “ቅ/ሲኖዶስ: ከብር 159 ሚሊዮን በላይ ዓመታዊ በጀት አጸደቀ፤ ስብሰባው ተጠናቋል፤ መግለጫም ይሰጣል

  1. Jigsa November 3, 2015 at 3:05 am Reply

    Wanaw tegibaru new!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: