ቅ/ሲኖዶስ: አራት ዓይናውን ብፁዕ አቡነ እንድርያስን በሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢነት መደበ፤ “በጥራት እንዲጠናከር ያደርገዋል”

 • የሊቃውንት ጉባኤው፣ በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ ከተደረጉ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች አንዱ ነው
 • ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከትን፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከትን ደርበው ይመራሉ

*           *          *

His Grace Abune Endriyasየጥቅምት ፳፻፰ ዓ.ም. የመጀመሪያውን የምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን እያጠናቀቀ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በትላንት ጠዋት ዘጠነኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው፣ የሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ እና ዝውውር አድርጓል፡፡

የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዛውረው በመምሪያ የበላይ ሓላፊ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ኾነው እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡

የብፁዕነታቸው ዝውውር በሀገረ ስብከታቸው ተፈጥሮ ከቆየው አስተዳደራዊ አለመግባባት ጋር የተያያዘ ይኹን እንጂ የሊቃውንት ጉባኤውን በጥራት እንዲጠናከር እንደሚያደርገው ታምኖበታል፡፡

በማእከል ይኹን በአህጉረ ስብከት ደረጃ ያልተመረመሩና ያልተፈቀደላቸው ጽሑፎች፣ የድምፅና የድምፅ ወምስል ኅትመቶች በምእመናን አእምሮ የሚዘሩት ኑፋቄና ስሕተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣበት በአኹኑ ወቅት፤ የሊቃውንት ጉባኤው ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት፣ የሕዝቡን ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ሊመልስ በሚችል መልኩ እያደራጀ ታትመው እንዲሠራጩ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደረጃ ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ የኾኑ ስምንት ድርጅቶችንና 16 ግለሰቦችን ባወገዘበት የግንቦት 2004 ዓ.ም. ውሳኔው፤ ምእመናንና ከስሕተት ለመጠበቅ፣ በማንኛውም አካል በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰነዘረውን ሃይማኖትን የሚያጎድፍ ክብረ ነክ ጽሑፍ ተከታትሎ በጊዜው በቂ ምላሽ ለመስጠት የሊቃውንት ጉባኤው በጥራትና በስፋት እንዲጠናከር ይደረግ ዘንድ አሳስቦ ነበር፡፡

ከአጠቃላይ ጉባኤው ጥያቄና ከቅዱስ ሲኖዶስ ተደጋጋሚ ውሳኔ በተፃራሪ፣ የሊቃውንት ጉባኤው እንደ ጡረታ መውጫና የተቃዋሚዎች ማግለያ መስሎ ሲታይ በቆየበት ተጨባጭ ኹኔታ፣ የአራት ዓይናው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ መመደብ÷ ሃይማኖታዊ ሕጸጽን ለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከሚጠነቀቅ ብስለትና ቀናዒነት አንጻር በመመርመርና ለጥያቄዎች ብቁ ምላሽ በመስጠት ጥራቱን እንደሚያጠናክረው ታምኖበታል፡፡

በ2007 ዓ.ም. ተሻሽሎ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፳፪/፩ መሠረት÷ ለቅዱስ ሲኖዶስ አመራር፣ አስተዳደር፣ ቁጥጥርና ውሳኔ አሰጣጥ የሚያግዙና አሠራሩ ቅንጅትና ጥንካሬ እንዲኖረው ለማስቻል ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲኾን ከተደረጉት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች መካከል በመምሪያ ደረጃ የተዋቀረው የሊቃውንት ጉባኤው ይገኝበታል፡፡


በመንበረ ፓትርያርክ የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ 34ኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በቀረበው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሪፖርት፣ ባለፈው በጀት ዓመት የሊቃውንት ጉባኤው፡-

 • የግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ እንዲወጣ፣ የግእዙ ሐዲስ ኪዳን ኹለተኛ ማጣራት ተደርጎለት ለኅትመት ዝግጁ ተደርገዋል፡፡
 • ስለ ጠበል እና ኤች.አይ.ቪ፤ ስለፅንስ ማቋረጥና ወሊድ መቆጣጠርያ፤ ስለደም መስጠትና መቀበል፤ የዐይን ብሌንና ኩላሊት ስለመለገስ ለቀረቡ ጥያቄዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በሚገልጽ አኳኋን ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
 • በቅድስት ሥላሴ እና በቅዱስ ፍሬምናጦስ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጆች በትምህርት ላይ ካሉት ደቀ መዛሙርት መካከል በመናፍቅነት ተጠርጥረው እንዲኹም በሦስት አብያተ ክርስቲያን ተመድበው የሚያገለግሉ ኹለት መምህራንና አንድ ሰባኬ ወንጌል ኢ-ክርስቲያናዊ ትምህርት አስተምረዋል ተብሎ የቀረበውን መረጃ በጥንቃቄ ተመልክቶ ተገቢውን የውሳኔ ሐሳብና አስተያየት አቅርቧል፡፡
 • በተጨማሪም ከልዩ ልዩ ደራስያንና ግለሰቦች ቀርበው የተመሩ ጽሑፎችን መርምሮ፣ ካሴቶችን አዳምጦ የሚስተካከለውን አስተካክሎ ተገቢውን የውሳኔ ሐሳብ በማስተላለፍ የተጣለበትን ሓላፊነት ተወጥቷል፡፡
 • በተመሳሳይ መልኩ በ2006 ዓ.ም. ካከናወናቸው ተግባራት መካከል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ምሥጢራተ ቀንዲልና ቄደርን አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ እንዲኹም ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና ቀዳማዊነት ተጠንቶ እንዲቀርብ በታዘዘው መሠረት ጥናታዊ ዘገባ አቅርቧል፡፡
 • ከምዕራብ ጀርመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ በቀሲስ ገዳሙ ደምሳሽ ላይ የቀረበውን ሃይማኖታዊ ሕጸጽ፤ የቅዱስ ያሬድን ዜና መዋዕል አስመልክቶ ከማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የቀረበውን ጽሑፍ መርምሮ አስተያየትና የውሳኔ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡

በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ከታላቁ ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኰንን ወንበር ተምረው አኽለውና መስለው የወጡት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና ተጠያቂ ሊቅ በመኾናቸው በአዲሱ የበላይ ሓላፊነት ምደባቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአመራሩና ለቁጥጥሩ የሚያግዙትን ጥልቅና በሳል የውሳኔ ሐሳቦችና አስተያየቶች እንደሚያገኝ እርግጥ ነው፡፡

Abune Endriyas

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ

በተለይም ምልዓተ ጉባኤው፣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶውን አድማሳዊ ተጋድሎ በማእከል የሚያስተባብርና መዋቅሩ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚወርድ ዐቢይ ቋሚ ኮሚቴ በሠየመበት ወቅት፣ አራት ዓይናውን ሊቀ ጳጳስ በሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢነት መመደቡ ውጊያው በኹለንተናዊ አቅሞች ከሚጠይቀው ቅንጅትና መደጋገፍ አኳያ እጅግ አስተዋይነት ነው፡፡

በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው ስብሰባ፣ የኮፕት እና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትን ግንኙነት ጨምሮ በሌሎችም አጀንዳዎች አጋጣሚ ለተነሡ ዶግማ እና ቀኖና ነክ ጉዳዮች ከአንድ ሊቅ የሚጠበቁና ለውሳኔ የማያሻሙ ጥልቅ ትንታኔዎችን በማቅረብ ምልዓተ ጉባኤውን ማስደመማቸውን የጠቀሱ አንድ አባት፣ ብፁዕነታቸው፤ “የሲኖዶሱ ዓይንና ተጠያቂ” እንደኾኑ ይናገራሉ፡፡

ሌላውም መምህር ተጠያቂነታቸውን በማረጋገጥ፣ “እዚያም ሳሉ እዚህም መጥተው በማረፊያቸው አትሮኖሳቸውን ዘርግተው ሊቃውንቱን፣ ሐዲሳቱን በጎንና በጎን ዘርግተው ኑሯቸውን ከመጻሕፍት ጋር ያደረጉ ናቸው፤ በእጃቸው የጻፉት የቄርሎስ፣ የፍትሐ ነገሥቱ እና የሃይማኖተ አበው ብራናዎች ለመሸከም እንኳ ያስቸግራሉ፤ ፍላጎታቸው ከአስተዳደሩ ይልቅ ወደ ማስተማሩና ከሊቃውንቱ ጋር እየተጠያየቁ ስለ መኖር ነው፤ በግልጽ የሚታየውም ክፍተት ይኸው ነው፤” ብለዋል፡፡

his-grace-abune-elsae

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ

በ1991 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ኤጴስ ቆጶስነት ሲሾሙ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ በ2001 ዓ.ም. ወደ ደቡብ ጎንደር ተዛውረው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በብፁዕነታቸው ቦታ በአኹኑ ወቅት የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እስከ መጪው ግንቦት ርክበ ካህናት ድረስ ደርበው እንዲመሩ ተመድበዋል፡፡

his grace abune estifanos

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ

በተያያዘ ዜና፣ ስለ ጋምቤላ እና ኢሉባቦር አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ኹኔታ የተወያየው ምልዓተ ጉባኤው፣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ባለፈው ዓመት በሞተ ዕረፍት በመለየታቸው፣ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ደርበው እንዲመሩ መድቧቸዋል፡፡

ለኹሉም ብፁዓን አባቶች መልካም የሥራ ጊዜ እንመኝላቸዋለን፡፡

Advertisements

9 thoughts on “ቅ/ሲኖዶስ: አራት ዓይናውን ብፁዕ አቡነ እንድርያስን በሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢነት መደበ፤ “በጥራት እንዲጠናከር ያደርገዋል”

 1. መለሠ November 1, 2015 at 10:02 pm Reply

  God may give strength and power to led all holy thing

 2. Alemu November 2, 2015 at 8:02 am Reply

  ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በግጥም አንቱ የተባሉ የአባቶቻችን ተረፈ አካል ወደ ሰማይ እስክ ጠፈር ወደ ታች እስከ ከርሰ ምድር የተራቀቁ ሊቅ ናቸው፤ ሌላ ማን አለና። ብቻ የሰውነታችው መድከም ዘወትር ያሳስበኛል። ምደባው የሊቃውንት ጉባዔ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ተብሎ ይታረም። አመሰግናለሁ።

 3. Anonymous November 2, 2015 at 3:40 pm Reply

  ENKUAN WODE HAGERE SEBEKETEWO BESELAM METU ENILALEN DES SILLLLLLLLL

 4. Anonymous November 3, 2015 at 7:48 am Reply

  የቅዱሳን አምላክ እድሜን ከጤና ጋር ያድልልን።

 5. Anonymous November 3, 2015 at 9:45 am Reply

  the right position for right bishop.

 6. senu November 6, 2015 at 9:01 pm Reply

  ARAT AYNA ??

  ahun yehe ababal Gatewetnet aydelem ?? Hara ye Durye sebesib !! kkkkkkkkk

 7. Anonymous November 9, 2015 at 9:40 am Reply

  correct match!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: