የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ተካሔደ፤ “የአዲስ አበባን ጉዳይ በጽሞና መፈተሽ፣ መነጋገር፣ ማረም አለብን” /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

ሲኖዶስ ማለት፡-

 • ሲኖዶስ፣ ቃሉም ሥራውም የምሥራቃውያን ነው
 • ቃሉ ግሪክኛ ኾኖ የአንድነት ስብሰባ ማለት ነው
 • የእኛ ቤተ ክርስቲያን ከምሥራቃውያን አንዷ ነች
 • ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊትና ሲኖዶሳዊት ነች

የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ፡-

 • የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደ ማንኛውም ጉባኤ አይደለም፤ የቤተ ክርስቲያን የበላይ መሪዎች ስብሰባ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ ስለሚመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ተብሎ ነው የሚጠራው፤
 • ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል እንደተባለው፤ መኑ ይብልዎ ሰብእ ለቅዱስ ሲኖዶስ፤ ካህናት እና ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶስን ምን እያሉት ነው፤ እያመሰገኑን ነው? እያሙን ነው?
 • ሰዎች የሚሉን ብዙ ነገር ነው፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀ መንበርነት፣ በጽሞና፣ በሰከነ ኹኔታ በውይይት መፍትሔ መፈለግ፣ ማጽዳት አለብን፤
 • መልካም ነገርም ክፉ ነገርም በአዲስ አበባ ይከሠታል ይባላልና መፈተሸ፣ መነጋገር፣ ማረም አለብን፤ መፈተሽ የሚችል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ ፓትርያርኩ ሊቀ መንበር ስለሆኑ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የኹሉም ድርሻ ነው፡፡ /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

Shashemene faithfuls on the synod opening prayer
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት የሚመራው እና የሚጠብቀው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የመጀመሪያውን ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን ከነገ ጀምሮ ያካሒዳል፤ የጉባኤው የመክፈቻ ጸሎት፣ ዛሬ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ሠርክ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናውኗል፡፡

በመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐቱ፣ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እንደተናገሩት÷ በዓለም በተጋድሎ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ወቅት የደረሱባት ችግሮች እያደር ወደ መጥፎ ሳያመሩ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍቅር፣ በውይይት እና በሰላም ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ በማቴዎስ ወንጌል ፲፮÷፲፫ ላይ በመመሥረት፣ “መኑ ይብልዎ ሰብእ ለቅዱስ ሲኖዶስ” በሚል መነሻ ጭብጥ በሰጡት ትምህርት፣ “ካህናት እና ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶስን ምን እያሉት ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ብዙ እንደሚባልና ይኸውም በኹሉም ልቡና እንደሚታወቅ ጠቅሰው፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት፣ ጸጥ ባለ፣ በሰከነ ኹኔታ፣ በጽሞና ውይይት መፍትሔ በመፈለግ ጉድፉን ማጽዳት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ተኩላ ስላለ፣ ቀበሮ ስላለ በጎች ምእመናንን ማሰማራት እና መጠበቅ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደር ቀላል ባለመኾኑ ችግሮች እንደሚኖሩ ብፁዕነታቸው አስገንዝበው፣ እያደር ወደ መጥፎ ከማምራታቸው በፊት በሰላም እና በውይይት ከተስተካከሉ ከባድ አይኾኑም፤ ብለዋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱን አስቸኳይ ትኩረት ይሻል ካሏቸው ጉዳዮችም፣ የፓትርያርኩን ልዩ ሀገረ ስብከት አዲስ አበባን በስም ጠቅሰዋል፡፡ “መልካም ነገርም ክፉ ነገርም በአዲስ አበባ ይከሠታል” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ እንደ አህጉረ ስብከት ማእከልነቱ መፈተሽ እንዳለበትና መፈተሽ የሚችለውም ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

his-grace-abune-gabrielኵሉ ይወፅዕ ኵሉ ይትከሠት በሀገረ አዲስ አበባ ይላሉ፤ መልካም ነገርም በአዲስ አበባ ይከሠታል፤ ክፉ ነገርም በአዲስ አበባ ይከሠታል፤ በአዲስ አበባ ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን ምን ችግር አለባት ብለን መፈተሽ፣ መነጋገር፣ ችግሩን ማረጋገጥ፣ ማረም አለብን፤ ችግሩ ምን ያህል ጥልቀት እና ውፍረት እንዳለው መፈተሽ የሚችል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ በርግጥ ችግሩ ችግር ነው፤ ከኛ አልፎ ወደ ምእመናን ወርዷል፤ ችግሩ ችግር ነው፤ ከኛ አልፎ መነጋገርያ ኾኗል፤ ነገር ግን መፍታት የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ነው፤ በቅዱስ ሲኖዶስ በፓትርያርኩ አድሮ፡፡ ካልፈታነው ግን አደጋ ነው፤ ከባድ አደጋ አለው፡፡


ሀገረ ስብከቱ በአጠቃላይ ጉባኤው ካቀረበው ፐርሰንቱ ጀምሮ የመልካም ነገሮች ብልጭታዎች እየተሰሙበት ቢኾንም “አይ፣ ግዴለም ሳይባል፤ አዝመራው የአውሬ መናኸርያ ኾኖ ታፍኖ እንዳይቀር” ወደ ምእመናን የወረዱትና በኹሉ ዘንድ የሚታወቁት ችግሮቹ ምን ያህል ውፍረት እንዳላቸው ሊመረመሩና ዳኝነት ሊታይባቸው ሊታረሙም እንደሚገባ ብፁዕነታቸው በትምህርታቸው ጠቁመዋል፤ በዚህም ረገድ ፓትርያርኩ ሊቀ መንበር ቢኾኑም ድርሻው የኹሉም ሥራ እንደኾነ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ባለፈው ምን እንደተሠራ የሚፈተሸውና ለሚመጣው ዕቅድና መርሐ ግብር ወጥቶ ምን መሠራት እንዳለበት የሚታወጀው በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በመኾኑ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊት እንደምትባል ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በስፋት አስረድተዋል፡፡

ሲኖዶስ ሥራውም ቃሉም ምሥራቃዊ ሲኾን በዚህም “የአብያተ ክርስቲያናት ኹሉ መሪ ነኝ፤ ዓለም አቀፋዊት ነኝ” ከምትለዋ የሮም ካቶሊክ እንለያለን፡፡ የአንድነት ስብስባ፣ የአንድነት ምልክት የኾነው ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያን የበላይ መሪዎች ስብሰባ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የብፁዓን አባቶች ጉባኤ እንጂ እንደ ማንኛውም ስብሰባ ባለመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ተብሎ ይጠራል፡፡

እንደ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ማብራሪያ፣ የእስክንድርያ ሲኖዶስ የእኛ ሲኖዶስ ነበር፡፡ ከዚያው እየተሾሙ ሲመጡ የቆዩትን ጳጳሳትም እኛው ነን ያስመጣናቸው፡፡ በቅዱስ ፍሬምናጦስ አማካይነት የቅዱስ አትናቴዎስ፤ በቅዱስ አትናቴዎስ አማካይነት የቅዱስ ማርቆስ፤ በቅዱስ ማርቆስ አማካይነት የሐዋርያት ልጆች ነን፤ የማርቆስ፣ የአትናቴዎስ፣ የቄርሎስ ልጆች በመኾናችን የራሷን ፓትርያርክ መርጣ በነጻነት የምትመራው ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊት ናት፡፡

መልካም ስም እና ዝና የነበራት፣ ያላት ሐዋርያዊት እና ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ በዓለም በተጋድሎ ያለች ቅድስት እና የሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን በመኾኗ፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀ መንበርነት ጉድፉን ለማጽዳት፣ እንክርዳዱን ለመንቀል፤ ከሌለም እንዳይገባ ለመጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ጸጥ ባለ፣ በሰከነ ኹኔታ፣ በጽሞና ውይይት መፍትሔ ይፈልጋል፤ ይህን በማድረግ ተስፋ የሚሰጥ ውሳኔ እንድንወስንና የበለጠ መሥራት እንድንችል ቅድስተ ቅዱሳን ወላዲተ አምላክ እመቤታችን በአማላጅነቷ፣ የቤተ ክርስቲያን አምላክ በቸርነቱ ይርዳን፤ በማለት ትምህርታቸውን አጠቃለዋል፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ የመጠበቅና የማስጠበቅ፤ አገልግሎቷ የተሟላ እንዲኾን የማድረግና ፍትሕ ርትዕን የማስፈን ዓላማዎች ያሉት ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ቀጣይ የህልውና ስጋቶች በኾኑት የመልካም አስተዳደር እና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን ችግሮች ላይ ኹነኛ መፍትሔ እንዲሰጥ ትላንት በተጠናቀቀው 34ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠይቋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በእኒኽና በመሳሰሉት ዐበይትና አንገብጋቢ ጉዳዮች የምልአተ ጉባኤውን የመነጋገርያ አጀንዳዎች በመቅረጽ ይቀጥላል፡፡

Advertisements

6 thoughts on “የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ተካሔደ፤ “የአዲስ አበባን ጉዳይ በጽሞና መፈተሽ፣ መነጋገር፣ ማረም አለብን” /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

 1. Anonymous October 23, 2015 at 6:48 am Reply

  ሲኖዶስ የተለየ(ቅዱስ) ስብሰባ ነው፡፡እውነት ነው፡፡ግን የስብሰባው ቅድስና በእናንተ ምክንያት አደጋ አንዣቦበታል፡፡ስብሰባው ቅድስናውን ጠብቆ በሰከነና በሰለጠነ ውይይት እንዳይካሄድ አባቶችን ገና በስብሰባው ሂደት የተለያየ ስም እየሰጣችሁ ከ‹‹ምን ይሉኝ›› ነጻ ሆነው እንዳይነጋገሩ ታደርጋላችሁ፡፡ወደ ቡድናዊነት እንዲወርዱ ታደርጓቸዋላችሁ፡፡በእናነተ ዐይን ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ማኅበረቅዱሳን በሚል ስለተተካ የአባቶች ምግባርና ድካም ሁሉ ከማኅበሩ ጋር በተገናኝ ብቻ እንዲታይ በሞኖፖል በያዛችሁት ሚዲያ ታርገበግባላችሁ፡፡አልፎ አልፎም ወደ መንደርተኛነት ትዘቅጣላችሁ፡፡ዝቅጠታችሁ ለሲኖዶሱም ይተርፋል፡፡በዚህ ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቅምትና ግንቦት በደረሰ ቁጥር የእናንተ ስብሰባዎችን ሁሉ አጀንዳቸውን ጠልፎ እጅግ በጠባቡ ስለማኅበረቅዱሳን ብቻ እንድንጨነቅ ማድረግ የተነሳ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም፡፡

  ማኅበረቅዱሳንን በብዙ ነገሩ ብውደውም በእናንተ የወረደና ከማኅበር አሻግሮ ስለሁለንታዊ መዋቅር አለመጨነቅ የተነሳ ቅር ይለኛል፡፡እባካችሁ ስብሰባውን የሆነ ግሩፕን ደግፎ ሌላኛውን ለማጥቂያ በሚመስል መልኩ ስላችሁ ውዥንብር ሳትነዙ ሀቁንና አሰራሩን ብቻ ያለምንም ጥላች ስሜት አቅርቡልን፡፡ቤተክርስቲያንን አታጥብቧት፡፡ማኅበረቅዱሳን ቅርንጫፍ ነው፡፡ግንድ አይደለም፡፡ግንዱ ሁሉም የቤተክርስቲያን መዋቅሮች ሲደመሩ የሚገኝ ነው፡፡ከእግዚአብሔር በታች በቅስት ቤተክርስቲያን መዋቅር ከፍተኛው ጫፍ ላይ ያለው ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ብትችሉ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሁሉንም አባላት ክብር ጠብቃችሁ ዘግቡ፡፡ለማኅበርና ለጎጣዊ አስተሳሰብ ብቻ ተሸንፋችሁ አባቶችን አትከፋፍሉብን፡፡ይሄ አካሄዳችሁ ብዙ ተከታይ ሊያስገኝ ቢችልም በፍጻሜው የሚገኘው ፍሬ እጅግ ታናሽ ነው፡፡አይጠቅምም፡፡ቅኝታችሁን ከጀብደኝነት ወደ ገንቢነት ብትቀይሩት ደስ ይለኛል፡፡ከዚህ አንጻር ከአምናው ዘንድሮ ለውጥ አሳይታችኋል፡፡በገንቢነት ቅኝት መሻሻሉን ቀጥሉበት፡፡

 2. TIRSIT WUBIE October 23, 2015 at 7:10 am Reply

  ለቤተ ክርስትያን በጎ በጎውን ያመላክታችሁ አባቶቼ

 3. Anonymous October 23, 2015 at 7:35 am Reply

  በጣም ደስ ይላል እባካችሁ በዚሁ ቀጥሉ አይቁረጥ

  • ተመሥገን October 24, 2015 at 5:17 am Reply

   ጥሩ ሀሣብ ነዉ ማህበረ ቅዱሣ በጣም እያወዛገቡኝ ነው

 4. mamush solomon October 23, 2015 at 11:54 am Reply

  መልካም ንግግርን ብቻ ከአፋችን እንድናወጣ በመጽሐፍ ቅዱስ ታዝዘናል ፡፡ ስለዚህ ተግሳጽም መሥጠት ካለብን በቅድሚያ ጥንካሬዉን በመግለጽ በመቀጠልም ማኅበሩ ያሉበትን ስህተቶች ነቅሰን በመረጃና በማስረጃ አስደግፈን አስተያየት ልንሰጥ ይገባል ፡፡ ከጉባኤ ነቢያት፣ ሐዋርያትና ከሊቃዉነትን ጉባኤ ያለተለየዉ መንፈስ ቅዱስ በአባቶችም ጉባኤ ተገኝቶ ቤተክርስቲያናችን ያሉባትን ችግሮች የምታስወግድበት ፣ ምዕመናኖቿን የምታጸናበትና የጠፉትን የምትሰበስበበት ዉሳኔ የሚተላለፍበት ጉባኤ ያድርግልን ሁላችንም በጸሎት ልናስባቸዉ ይገባል ዓሜን ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: