ስለምእመናን ፍልሰትና ጥበቃ: የፓትርያርኩ ጥያቄና የአህጉረ ስብከት ምላሽ፤በ2007 ከ36‚800 በላይ ወገኖች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተደምረዋል

His Holiness and the gambela dio

ከጋምቤላ ሀገረ ስብከት ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት በ2007 ዓ.ም. ከተደመሩት 138 ምእመናን የክልሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይገኙበታል፤ በስብሰባው መክፈቻ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አማካይነት ወደ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርበው ቡራኬ ሲቀበሉ ይታያሉ

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፡-

 • ቤተ ክርስቲያናችንን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በቊጥር እጅግ የላቀ የውሉደ ክህነት ብዝኅነት ያላት ስትኾን ስብከተ ወንጌልን ለውሉደ ሰብእ በማዳረስ ረገድ ያለን ውጤት ግን አናሳ ነው ማለት ይቻላል
 • ባሕርን አቋርጦ፣ ድንበርን ተሻግሮ እስከ ጽንፈ ምድር ተጉዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረጉ ይቅርና በሀገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምእመናንን ማብዛት ብዙ ያልተሔደበት እንደኾነ ማወቅ አለብን
 • በዚኽ ዙሪያ የሚታየው ክፍተት ፈጣን ምላሽ በመስጠት መግቻ ካላበጀንለት ነገ ከባድ የሃይማኖት እና የታሪክ ወቀሳ ማስከተሉ እንደማይቀር ልብ እንበል

*                *                 *

 • ለተደራጀ እና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤ የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ኅሊና ዕንቅፋት እየኾነ ነውና የሃይማኖቱን መርሕ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኵራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን

*                *                 *

የአህጉረ ስብከት ሪፖርት፡-

 • በ2007 ዓ.ም. ከ36‚874 በላይ ወገኖች አምነውና ተጠምቀው ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተደምረዋል፤ ከእኒህም ውስጥ 13‚776 ጥሙቃን፣ ከማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ጋር በመተባበር በተፈጸመ የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት የተገኙ ናቸው
 • የተጠቀሰው ቁጥር፣ በሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ብቻ የተገለጹትን የሚያካትት ሲኾን ከእነርሱም 16ቱ የቻይናን ጨምሮ የተለያዩ ሀገሮች ዜጎች ይገኙበታል

Publication4

፴፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ በመካሔድ ላይ

ትላንት የተጀመረው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር 34ኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ጨምሮ የየአህጉረ ስብከቱን የሥራ ክንውን ሪፖርት በማዳመጥ ላይ ይገኛል፡፡

ሪፖርቶቹ÷ ሰበካ ጉባኤያትንና የሰንበት ት/ቤቶችን በማደራጀትና በማጠናከር፤ አብያተ ክርስቲያናትን በመትከልና የአብነት ት/ቤቶችን በመርዳት፤ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና የራስ አገዝ ልማትን በማጎልበት ዐበይት ጉዳዮች ዙሪያ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐዋርያዊ ጉዞዎች እና በጽ/ቤቶቹ የተከናወኑ ተግባራትንና ያጋጠሙ ችግሮችን ያካተቱ ሲኾኑ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትንና ማጠናከርን ማእከል ያደረጉ ናቸው፡፡

ዓመታዊ ስብሰባውን በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በመክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ለመላው ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን ስታበረክት የኖረችው ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሉዓላዊት ቤተ ክርስቲያናችን፤ የነገው ትውልድ ሊረከበው የሚችለውን ተጨማሪ ዕሴት ለማመቻቸት የሰበካ ጉባኤ መቋቋምና መጠናከር ወሳኝነት እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

በዓለም ውስጥ እጅግ ሀብታምና ኃያል የኾነ ማን ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ትክክለኛ መልስ ሊኾን የሚችለው፣ “ቤተ ክርስቲያን ናት” የሚለው ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥራ የምናከናውንበት ዋነኛ መሣርያችን ሰበካ ጉባኤ÷ የቤተ ክርስቲያናችን ጉልበት የሚለካበት፣ የአባልነት ህልውና የሚገለጽበት በመኾኑ የሥራ እንቅስቃሴን ለመግታት ምክንያት የሚኾኑትን በማስወገድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን በርቀት እና በሪፖርት ብቻ መከታተል በቂ እንዳልኾነ በመጥቀስ፣ በአካል ቀርቦ ሥራቸውን መከታተል፣ የአባላቱን ብቃት እና ጥራት ማየት እና መመዝገብ፤ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸውን አመለካከት በትኩረት መከታተልና መገምገም፣ ችግራቸውን ፍትሕ ርትዕ ባልተለየው መንገድ በፍጥነት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአኹኑ ዘመን ከፍተኛ መሥዋዕትነትን እየጠየቀን ያለው የደምና የሕይወት መሥዋዕትነት ሳይኾን ራስን የመካድ ወይም ያልተገባ ጥቅምን የመጸየፍና ሓላፊነትን በሚገባ ለመወጣት የመነሣሣት ጉዳይ እንደኾነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፤ ካለፈው ዓመት ይልቅ ለበለጠ ዕድል ለመዘጋጀት የመልካም አስተዳደርንና የአመራር ስልትን አስፈላጊነት ጠቁመዋል፡፡

ተልእኮአችን ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳይደለና ተልእኳችንን ለመወጣት ከኅሊና መቆርቆር ጀምሮ የሕይወት መሥዋዕትነትን መክፈል፣ ብዙዎቹ የሃይማኖት መስተጋድላን አባቶቻችን ያለፉበት በመኾኑ አዲሳችን እንዳልኾነ ቅዱስነታቸው አውስተዋል፡፡ በዚኽ ረገድ የቤተ ክርስቲያናችን ካህናት(ውሉደ ክህነት) ቁጥር ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር እጅግ የላቀ ቢኾንም ስብከተ ወንጌልን÷ ባሕር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ፣ እስከ ጽንፈ ምድር ተጉዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረግ ይቅርና በሀገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምእመናንን ማብዛት ብዙ እንዳልሔደበት አስረድተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በሰበካ ጉባኤ መደራጀት ስትጀምር፣ በመቶ ሺሕ ብር ደረጃ የነበረው ገቢዋ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ቢልዮን መድረሱ ትልቅ ዕድገት በኾንም፤ “የምእመናን ዕድገትስ የት ነው ያለው የሚለውን አይተነዋል ወይ? በዚኽ በኩል ያለው ዕድገት የኋልዮሽ መኾኑን የማያውቅስ በመካከላችን ይኖር ይኾን? ይህን ችግር በሚገባ ተገንዝበንና በቁጭት ተነሣሥተን ነገሩን ለመቀልበስ ያደረግነው ሙከራስ ይኖር ይኾን? ሲሉም ጠይቀዋል፤ ምላሹንም ከምልአተ ጉባኤውን እንደሚሹ አመልክተዋል፡፡

የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት ካልተቻለ ነገ ከባድ የታሪክ እና የሃይማኖት ወቀሳ ማስከተሉ እንደማይቀር ያስገነዘቡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ዐቢይ ጉባኤው÷ ለተደራጀ እና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ስለ መነሣት፤ የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተኣማኒነትንና ተጠያቂነትን ያሰፈነ፣ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኵራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ስለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እንዲመክር አሳስበዋል – “ሰበካ ጉባኤ ተጨባጭ ለውጥ የሚያስመዘግበውና ዓላማው ግቡን የሚመታው ይህ ሲኾን ነው፡፡”

IMG_7754የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ የጥንታዊቷንና ታሪካዊቷን ቤተ ክርስቲያን ህልውና በመጠበቅ ኹለንተናዊ ተልእኮዋን ለመወጣት፣ የሰበካ ጉባኤን በመልካም አስተዳደር በማጠናከር ልማቷንና ዕድገቷን ማፋጠን እንደሚገባ መክረዋል፡፡ አያይዘውም፣ የፍትሕ መጓደል፣ የጥላቻ ስሜትና የሥነ ምግባር ጉድለት የሚታይበትን ችግር አርመን መልካም አስተዳደርን ማስፈን አለብን፤ ምእመናን የመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥ እንዲያገኙ ማበረታታትን፣ ሰላምንና ፍቅርን የሚሰብከውን ወንጌልን በጊዜውም አለጊዜውም በትጋት መስበክ እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን÷ የካህናት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት መኾኗን በመጥቀስ ኅብረቱ ተመሥርቶ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ኹለንተናዊ አስተዋፅኦ ማበርከት ከጀመረ አርባ ኹለት ዓመታት መቆጠራቸውን ያስታወሱት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፤ ዛሬ በየዕለቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚጎርፈውን ምእመን ስናይ በእጅጉ እንደሚያስደስት ገልጸዋል፡፡ ይኹን እንጂ፣ አገልጋይ ካህናትም ኾኑ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ከሚጎርፈው ምእመን ጋር አንድ ልብ ነን ወይ? የሚለው ሊያስጨንቀን የሚገባ ጥያቄ ነው፤ ብለዋል፡፡ሊቀ ማእምራን ፋንታኹን ሙጩ Lique Maemeran Fantahun Muchie Head of Parish Council Organizing Dept.

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን እንዳሉት÷ የካህናት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች በአንድ ልብ እና ሐሳብ መቆም የቤተ ክርስቲያንን ዕድገቷን ያፋጥናል፤ በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊ እና በልማታዊ መስኮች ያላትን ተደራሽነትም ያጎላዋል፤ የእነርሱ አንድ ልብ አለመኾን ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ዕድገትም ኾነ የአገልግሎቷ ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥም ይኹን በውጭ አህጉረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ እና በልማት ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መመዝገቡን ዋና ሓላፊው ገልጸው፤ ይህም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየቀረቡና ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እየተወጡ (ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን እየከፈሉ) እንዳለ ቢያሳይም፣ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ጊዜው የሚጠይቃቸው ሥራዎች ሊሠሩ የሚችሉት፤ ድርሻችንን ጠብቀን በፍቅር ኾነን በአንድ ልብ ለቤተ ክርስቲያን ስንቆም ነውና፣ በአንድነት እንሠራ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ምእመናንን በማትረፍ የአህጉረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ፍሬ በጥቅል፡-

ምሥራቅ ጎጃም 35፣ ምዕራብ ጎጃም 99፣ ባሌ 8፣ ቄለም ወለጋ 7‚752፣ መተከል 2‚854፣ ሐዲያ እና ስልጤ 1‚127፣ ሸካ ቤንች ማጂ ዞን 712፣ ጋሞጎፋ 747፣ አሶሳ 3‚665፣ ደቡብ ወሎ 300፣ ጉራጌ 400፣ ሶማሌ 97፣ ምዕራብ ወለጋ 1‚758፣ ጉጂ ቦረናና ሊበን ዞን 2‚459፣ ምዕራብ ሸዋ 8‚000፣ ሰሜን ወሎ 352፣ ሰሜን ሸዋ 115፣ ጋምቤላ 138፣ ምሥራቅ ሸዋ 1‚443፣ ኢሉ አባቦራ 2‚227፣ ካፋ 2‚315፣ ሑመራ 42፣ ምሥራቅ ወለጋ 93፣ ሀላባ ከምባታ እና ጠምባሮ 136፤ ጠቅላላ  ድምር 36,874፡፡

ምእመናንን በማትረፍ የአህጉረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ፍሬ በዝርዝር፡-

ምሥራቅ ጎጃም፤- በበጀት ዓመቱ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሀገረ ስብከቱ በተመደቡ መምህራን ከ75 ጊዜ በላይ ታላላቅ መንፈሳዊ ጉባኤያት ተዘጋጅተው ሰፊ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በዚኽም አገልግሎት 30 የፕሮቴስታንት እና 5 የእስልምና እምነቶች ተከታዮች በድምሩ 35 ወገኖች አምነው ተጠምቀው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባል ኾነዋል፡፡

ምዕራብ ሐረርጌ፤- በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት 188 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት የተካሔዱ ሲኾን 10 ከካቶሊክ፣ 32 ከፕሮቴስታንት፣ 52 ከእስልምና እና 3 ከባዕድ አምልኮ በድምሩ 97 ነፍሳት ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን አባላት ኾነዋል፡፡

በባዕድ አምልኮ መንፈስ፣ በጥንቆላ እና በቃልቻነት ለብዙ ጊዜያት ሕዝቡን በቤታቸው ሰብስበው ሲያሰግዱና ዲቤ ሲያስደበድቡ የነበሩ 2 ጠንቋዮች በሥራቸው ተጸጽተው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን በንስሐ ተመልሰዋል፡፡

ባሌ፡- በበጀት ዓመቱ በ14 ወረዳዎች በ84 አብያተ ክርስቲያናት ከመንበረ ፓትርያርክ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተጋበዙ መምህራንና በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ መምህራን ጋር በመኾን ለኹለት ቀናት የቆየ ጉባኤ ተካሒዷል፡፡ በጎባ ወረዳ በደብረ መደኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወ/ሮ አይሻ አሕመድ የተባሉ እናት ከሰባት ቤተ ሰዎቻቸው ጋር በብፁዕነታቸው ተምረው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና እንዲያገኙ አድርገዋል፤ ለመቋቋሚያም የሚኾን ብር 5‚000.00 ርዳታ አድርገዋል፡፡

ቄለም ወለጋ፡- በኹሉም ወረዳዎች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሀገረ ስብከቱ ባሉ ሰባክያነ ወንጌል እና ዘማርያን ጉባኤያት የተካሔዱ ሲኾን በተሰጠው ትምህርተ ወንጌል ብዙ ምእመናን ለሥጋ ወደሙ በቅተዋል፤ ለቤተ ከመናፍቃን 7500፣ ከእስልምና 252 በድምሩ 7752 ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል፤ ከፍተኛ የገንዘብ ገቢም ተሰብስቧል፤ በጋብቻ ምክንያት ስምንት ምእመናን ከእኛ ተለይተዋል፤ እነርሱንና ሌሎች ብዙዎችን ለመመለስ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡

በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ተመድበው እየሠሩ የነበሩ፣ ከመንፈሳዊ ኪሌጅ ተመርቀው ቃለ መሐላ የፈጸሙለትን ዶግማ እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጠብቀው ከማስጠበቅ ይልቅ የተሐድሶ መናፍቃንን ስውር ዓላማ በማስፋፋት ዶግማዋንና ሥርዐቷን ለመናድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ሠራተኞች፤ ሕዝቡን ግራ ያጋቡ ቆይተዋል፡፡ ግለሰቦቹ ከተሳሳተ ትምህርት ተመልሰው ንስሐ እንዲገቡ ጊዜ ተሰጥቷቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመኾናቸውና በክሕደታቸው በመቀጠላቸው ከክህነት አገልግሎት እና ከሥራ እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም፣ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ውጭ፣ ጎጆ ሠርተው “መንፈስ ወረደብን” እያሉ ሕዝቡን ሲያወናብዱና ሕገ ወጥ ገቢ(ዐሥራት፣ በኵራት፣ ስእለት) ሲሰበስቡ፤ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ከመንግሥት አካላት ጭምር ብዙ ጊዜ ቢመከሩም ሊመለሱ አልፈቀዱም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ከሰኔ 8 – 9/2007 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ኄኖክ ሊቀ ጳጳስ፣ የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት፣ የጊዳሚ ወረዳ የመንግሥት ጽ/ቤት ሓላፊዎች በተገኙበት በተሰጠው ትምህርት እና መመሪያ ለ23 ዓመታት ለአምልኮ ሲጠቀሙበት የነበረው ኹለት ጎጆዎቸቭ እንዲፈርሱ ሲደረግ በዋናነት “መንፈስ እናወርዳለን” በማለት ሲያወናብዱ በነበሩ ኹለቱ ግለሰቦች ላይ ርምጃ ተወስዷል፡፡ በዚኽ ሥራችን ለቄለም ወለጋ የዞን አስተዳዳሪና የጽ/ቤቱ ሓላፊዎች እስከ ቀበሌው ድረስ የፖሊስ ኃይል በመመደብ ላደረጉልን እገዛ ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን፡፡

መተከል፡- በበጀት ዓመቱ በሰባቱም ወረዳዎች ታላላቅ መንፈሳውያን ጉባኤያት ተካሒደዋል፡፡ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ለ30 የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የ15 ቀን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ 57 የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል፡፡ 7 የእስልምና እምነት ተከታዮች ክርስትና ተነሥተው ከማኅበረ ምእመናን ተደምረዋል፡፡ 2790 የጉምዝ ብሔረሰቦች በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በድባጢ እና በማንዱራ ወረዳዎች ተጠምቀዋል፤ በኹለቱ ወረዳዎች ለተጠመቁት የጉምዝ ብሔረሰቦች በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት 3 አብያተ ክርስቲያናት እየተሠሩላቸው ነው፡፡

ሐዲያ እና ስልጤ፡- በበጀት ዓመቱ በተደረገው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከተለያዩ አብያተ እምነቶች ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተመለሱ፡- ወንድ 651፤ ሴት 476 በጠቅላላ ድምር 1127 ተጠምቀዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሌላ ቤተ እምነት የሔዱ በቁጥር ወ3ንድ 51 ሴት 33 በድምሩ 84 ናቸው፡፡ በ20/11 የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር በ10 ወረዳዎች 10 አብያተ ክርስቲያናት 10 ጉባኤያት ተካሒደዋል፤ ለካህናቱም ሥልና ተሰጥቷል፡፡

ሸካ ቤንች ማጂ ዞን፡- በበጀት ዓመቱ ከገጠር እስኪ ከተማ ባሉን አብያተ ክርስቲያናት 83 ያኽል የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተካሒደዋል፡፡ በዚኽም በተገኘው ውጤት፤ ወንድ እና ሴት በድምሩ 712 ሰዎች ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ኾነዋል፡፡

ጋሞጎፋ፡- ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ጥቅምት 28 እና 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በኮንሶ ወረዳ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ለማኅበረ ካህናት ወምእመናን ትምህርት እና ቡራኬ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ፤ በአካባቢው የሚገኙ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች፤ በቁጥር 747 ሰዎች ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ጥምቀተ ክርስትናን ተቀብለዋል፤ ወደፊትም በወረዳው ውስጥ ያሉ ኢአማንያን በተመሳሳይ ኹኔታ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት እንደሚመለሱ በየጊዜው ከሚያቀርቡት ጥያቄ ለመረዳት ተችሏል፡፡

the convert fathfuls being baptized

ጥምቀተ ክርስትና በደቡብ ኦሞ

አሶሳ፡-
ስብከተ ወንጌልን ለማጠናከር እና ለማስፋፋት በተሠራው ሥራ፣ ከተለያዩ እምነት ተከታዮች በበጀት ዓመቱ ከ3‚665 በላይ ሰዎችን ማስጠመቁና እስከ አኹን በጥቅሉ ከ40‚900 በላይ አዲስ አማንያን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ተመልሰዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ፣ የአብያተ ክርስቲያናቱን ስብከተ ወንጌልንና ልማትን አጣምሮ እየሠራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶችን የማደራጀትና የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል፡፡ ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚቃጣውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እና የመናፍቃን ድብቅ ሤራ ለመከላከል የሚያስችለው ዕውቀት ለማስጨበጥ ስፖንሰር እያፈላለገ አሠልጥኗል፤ የመማርያ መጻሕፍትን እያሟላ ከመኾኑም በላይ ድርሻውን ተገንዝቦ በኹለንተናዊ አቅሙ የልማት ተሰታፊ እንዲኾን እየተደረገ ነው፡፡

ደቡብ ወሎ፡- ስብከተ ወንጌል በማስፋፋታችን ከእስልማ ወደ ክርስትና አምነውና ተጠምቀው የተመለሱ ምእመናን ከ300 በላይ መኾናቸውን ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በሕጋዊ መንገድ መመሪያውን ተከትለው በመጡ ሰባክያንና ዘማርያን በደሴ ከተማ እና በኻያውም ወረዳዎች በሚገኙ ከተሞች 33 ዐበይት ጉባኤያት ተካሒደዋል፡፡

ጉራጌ፡- በበጀት ዓመቱ በተሰጠው ውጤታማ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ ከ400 በላይ ኢአማንያን ወደ ቀናች ሃይማኖት ተመልሰዋል፡፡ የሶዶ ወረዳ ምእመናን ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በወረዳው በተመቻቹ ሦስት የሥልጠና ማእከላት ከ500 በላይ ካህናትና ተተኪ ሰባክያን በማሠልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡

ሶማሌ፡- የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ካለፉት ዓመታት በተሻለ ኹኔታ በ2007 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ተጠናክሮ የተከናወነበት ዓመት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ 72 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተካሒደዋል፡፡ ወደ ፕሮቴስታንት ገብተው የነበሩ 45 ምእመናን ተመልሰው የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ኾነዋል፡፡ የእስልም እና የተለያየ እምነት ይከተሉ የነበሩ 52 ሰዎችም ተምረውና ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ኾነዋል፡፡ ከዚኽም መካከል አንዲት ሴት ተምራና ተጠምቃ የቤተ ክርስቲያናችን አባል ከመኾኗም በላይ ሥርዐተ ምንኵስና ፈጽማ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለች ትገኛለች፡፡

ምዕራብ ወለጋ፡- በተለያዩ ወረዳዎች ላይ 39 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተዘጋጅተው ምእመናን ትምህርተ ወንጌል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚኽም በተገኘው ውጤት፣ ከተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ሴት 1068፣ ወንድ 690 በድምሩ 1‚758 ነፍሳት ወደ አቤተ ክርስቲያናችን ሲመለሱ በተለያየ ምክንያት ደግሞ ሴት 200 ወንድ 137 በድምሩ 337 ወጥተው ሔደዋል፡፡ በተለያዩ አድባራትና አጥቢያዎች ተከታታይ ትምህርት የሚሰጥ ሲኾን በዚኽም ሴት 14‚320 ወንድ 4‚545 በድምሩ 18‚865 ሰዎች ንስሐ ገብተው ለሥጋ ወደሙ በቅተዋል፡፡

ጉጂ ቦረናና ሊበን ዞን፡- በበጀት ዓመቱ በሀገረ ስብከቱ ከ34 በላይ ጉባኤያት እንዲካሔዱ ተደርጓል፡፡ በተሰጠው ትምህርተ ወንጌል ከ694 በላይ ኢአማንያን በጥምቀት እና በተለያዩ በዓላት ላይ ተጠምቀው የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ከኮንሶ ብሔረሰብ 1‚365 የተጠመቁ ሲኾን በድምሩ 2‚059 ሰዎች ተከታታይ የማጽናት ትምህርት እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ በመማር ላይ ያሉ 400 ሰዎች በጥምቀተ ክርስትና የሥላሴን ልጅነት ለማግኘት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

በሀገረ ስብከት ደረጃ በኹሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ የተለያዩ ትምህርቶችን በማዘጋጀት ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ምዕራብ ሸዋ፡- በየአድባራቱ እና በየገዳማቱ በየጊዜው በሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል፣ በታላላቅ የጥምቀት ማእከላት በሚደረገው ፈውስ እና ገቢራተ ተኣምራት እየተጸጸቱ፣ ከ8‚000 በላይ ወገኖች ካለማመንና ከባዕድ አምልኮ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል፡፡

ሰሜን ወሎ፡- በሀገረ ስብከቱ በአጠቃላይ ከ550 በላይ ሰባክያነ ወንጌል አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በትምህርተ ወንጌል አገልግሎት የተገኘው ውጤት፡- ከእስልም 299፣ ከመናፍቃን 39፣ ከውጭ ዜጋ 14 በድምሩ 352 ሰዎች በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት አምነው ተጠምቀዋል፡፡

ሰሜን ሸዋ፡- ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ በርእሰ ከተማችን 11 ታላላቅ ጉባኤያት፣ በየወረዳዎቹ 133 ዐበይት ጉባኤያት ሲካሔዱ በውጤቱም 115 የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ኾነዋል፤ 23 ሰዎች ከእኛ ወደ ሌላ እምነት ሔደዋል፡፡

ጋምቤላ፡- በጋምቤላ ክልል እና በደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት እና አዲስ አማንያንን አሳምኖ በማስጠመቅ ረገድ በተደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ፣ በጋምቤላ ከሚገኙት አምስቱ ብሔሮች፣ ከዞን፣ ከወረዳ፤ ከቀበሌ 138 የክልሉ ተወላጆች፣ በመንግሥት መዋቅር ያሉ አመራሮች ተጠምቀው የተዋሕዶ ልጆች ኾነዋል፡፡ በሀገረ ስብከታችን ከሚገኙ 67 አብያተ ክርስቲያናት መካከል በ65ቱ ሰንበት ት/ቤቶች ተቋቁመዋል፤ ወንድ 4‚800 ሴት 7‚700 በጠቅላላ 12‚500 አባላት በተደራጀ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ምሥራቅ ሸዋ፡- በስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴአችን፣ ከመናፍቃን 928፣ ከእስልምና 515 በድምሩ 1‚443 ቁጥር ወገኖች በጥምቀት የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ለማድረግ ተችሏል፡፡ ከእኒህ ጥሙቃን ኹለቱ ቻይናውያን ናቸው፡፡

ኢሉ አባቦራ፡- የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በኹሉም ወረዳዎቻችን ከምንጊዜውም በላይ በአካባቢው ቋንቋ እየተሰጠ በመጠናከሩ 2‚227 ሰዎች ተጠምቀው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ኾነዋል፡፡

ካፋ፡- በጨና ወረዳ ውስጥ ከሕዝቡ ተገልለው የሚኖሩት የሜንጃ ጎሳ አባላት፣ ዓ.ም. ከሕዝቡ ጋር በማስማማትና በማስታረቅ እንዲኹም በአርኣያ ሥላሴ የተፈጠሩ መኾናቸውን በስፋት በማስተማር፣ እነርሱንም በማሳመንና በማጥመቅ ሰፊ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በዚኽም 640ዎቹ ሚያዝያ 18 ቀን 2007 ተጠምቀውና የቅድስት ሥላሴን ልጅነት አግኝተው የቤተ ክርስቲያናችን አባልና አካል ኾነዋል፡፡

ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ጨታ ወረዳ ቀሽ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በተለያየ ምክንያት ከእናት ቤተ ክርስቲያን የተለዩትንና በአምልኮ ጣዖት የሚገኙትን ንስሐ ገብተው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

በዴቻ ወረዳ ውስጥ በኦሞ ወንዝ አካባቢ በዕንጨት እና በድንጋይ ሲያምኑ ከነበሩት ከጫራ እና ከሜዕንት ብሔረሰብ መካከል ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት ያገኙ 945፣ ከሜንጃ ጎሳ 640፣ ከሙስሊም፣ ከፕሮቴስታንት፣ ከካቶሊክ እና ከቃልቻ 730 በድምሩ 2‚315 ወገኖች የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ኾነዋል፡፡

ሑመራ፡- በሀገረ ስብከታችን በሚካሔደው ስብከተ ወንጌል አገልግሎት፤ ከሙስሊም 5፣ ከካቶሊክ 7 አባወራዎች ከሚስቶቻቸው እና ከልጆቻቸው ጋር በድምሩ 39፤ ከፕሮቴስታንት 3 በአጠቃላይ 42 ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተመልሰውና በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጠምቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን ኾነዋል፡፡

ምሥራቅ ወለጋ፡- በአካባቢው ቋንቋ እና ባለው የሰው ኃይል በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን በማዳረስ፤ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ በማድረግ፣ በአራት ወረዳዎች 84 የፕሮቴስታንት እና 9 የእስልምና እምነቶች ተከታዮች አምነው ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ኾነዋል፡፡ 800 አባወራዎችን ከሌሎች የሃይማኖት ወረራ ለማዳን ተችሏል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳንና በሀገረ ስብከቱ የጋራ ጥረት በተከናወኑ 26 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት 11‚413 ሰዎችን በእምነታቸው ለማጽናት ተችሏል፡፡

ሕገ ወጥ ሰባክያንን በመቆጣጠር 84 ታላላቅ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ተካሒዷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል መዋጮ 1 በመቶ በገጠር ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ሰባክያነ ወንጌል በመመደብ ጉባአቼ ተካሒዷል፡፡ ከርእሰ ከተማው እስከ ወረዳ ከተማ ድረስ በድምሩ 2‚380 ሰዎች በተምሮ ማስተማር ኮርስ ተመርቀዋል፡፡

አፋር፡- በብፁዕነታቸው አቡነ ዮናስ የተመራ ከጽ/ቤቱ 150 – 250 ኪ.ሜ. ላይ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ለአንዳንድ ሳምንት የቆየ ሐዋርያ ጉዞ በማድረግ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ታላላቅ የሥብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮች ተካሒደዋል፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ ቁጥር ወድ 32 ደርሷል፤ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ግንባታቸው በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ በአዋሽ ፈንታሌ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ፣ በአርጎባ ወረዳ የቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ሥራ በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡

በአሳይታ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከኬጂ 1 – 3 ዘመናዊ ት/ቤት፤ በሎጊያ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከኬጂ 4ኛ ክፍል ዘመናዊ ት/ቤት በመገንባት ዘመናዊ ትምህርት እየተሰጠ በመኾኑ በአካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የእምነትና የባህል ወረራ ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ሀላባ ከምባታ እና ጠምባሮ፡- በበጀት ዓመቱ 42 ታላላቅ ጉባኤያትን በማዘጋጀት፣ ቤተ ክርስቲያን በፕሮቴስታንቱም በሙስሊሙም ዘንድ አድናቆትን ከማትረፏም በላይ መስብሕ ኾናለች፤ በውጤቱም 136 ሰዎች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተጠምቀው ሲመለሱ በአንጻሩ አራት ምእመናን ሔደውብናል፤ በዚኽም ሀገረ ስብከቱ በጣም ሐዘን ተሰምቶታል፡፡

በአካባቢያአችን ቤተ ክርስቲያን መልእክቷን በሐዘን ቦታዎች በማስተላለፍ በምእመናን ደካማ ጎን እየመጡ ሃይማኖታቸውን የሚያስክዱትን ለመከላከል ተችሏል፡፡ በብፁዕ አባታችን ጠንካራ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ሥራ፤ በዞኑ በአንጋጫ ወረዳ አባ ሠሬቾ እና በሀደሮ ወረዳ ባዕድ አምልኮ የሚያስፈጽሙና የሀናሳራ አባት የሚባሉ ኹለት ጠንቋዮች ከነቤተሰቦቻቸው ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን አባላት ኾነዋል፡፡

ቀደም ሲል ከሌሎች አካባቢ ፈልሰው በሚመጡ አገልጋዮች ሲያስገለግል ከነበረበት በአኹኑ ጊዜ በራሱ ወይም በአካባቢው ቋንቋ የሚቀድሱ፣ የሚሰብኩና የሚዘምሩ አገልጋዮችን አፍርቷል፡፡ በዚኹ ዘርፍ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በተደረገው የበጀት ድጋፍና በሀገረ ስብከቱ ጥረት በጥቅሉ 501 ቋሚ የአብነት ተማሪዎች አፍርቷል፡፡

Advertisements

11 thoughts on “ስለምእመናን ፍልሰትና ጥበቃ: የፓትርያርኩ ጥያቄና የአህጉረ ስብከት ምላሽ፤በ2007 ከ36‚800 በላይ ወገኖች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተደምረዋል

 1. abebaw October 20, 2015 at 3:13 pm Reply

  የተጠማቂዎችን ቁጥር ስናይ ደስ ይላል፡፡ ነግር ግን ከዚህ በላይ በተሀድሶ መናፍቃን እያስወሰድን መሆኑን አባቶች ሊያውቁ ይገባል

 2. dagmay October 20, 2015 at 3:43 pm Reply

  Kebetu wede adarash yegebutis? Musinaw? Yetehadiso protestant guday beyeahugure sibiketu mindinew ? Reports yetal?

 3. Anonymous October 20, 2015 at 5:59 pm Reply

  ኪሳራውና ትርፉ ፥ከወጭ ቀሪው ታስቧል ? ማለት ከእኛው ቤተ ዕምነት ወደ ሌላው በምርኮ የሄዱት ምን ያህል እንደሆኑ ለምን በሪፖርቱ አልተጠቃለለም?

 4. Mar October 20, 2015 at 6:06 pm Reply

  Any report on South Africa …?

 5. Tsmuna Melkamu October 20, 2015 at 9:21 pm Reply

  በእውነት ቤተክርስቲያን ስትበረታ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ሲሰፋ እንደማየት የሚያስደስት ነገር ከወዴት ይገኛል? ይህንን ዜና ስላደረሳችሁን አብዝተን እናመሰግናችኋለን፡፡ ሪፖርት ተጠናቅሮ መቅረቡም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ገና ብዙ የሚሠራ አለ፡፡ የሚያኩራራ ምንም ነገርም አልሠራንም፡፡ 36 ሺሕ ሰዎች መጡ፡፡ ጥሩ! ግን በውስጥ ያሉት 40 ሚሊየን እንዴት እየኖሩ ነው ብለን ስንጠይቅ መልሱ አስፈሪ ይመስለኛል፡፡

  ክርስትናም የሰው ቁጥር ከመጨመር በላይ ጉዳዮች አሉት፡፡ ለምሳሌ፣ ቤተክርስቲያናችን ዛሬ በሙሰኛ ካህናት ተጥለቅልቃለች፡፡ መንፈሳዊነት የራቃቸው ካህናትን ማየት በጣም ከመልመዳችን የተነሣ አሁን አሁን መንፈሳዊ ካህን ማየት ብርቅ ሆኖብናል፡፡ በጣም ብዙው ምእመንም ክርስትናው ትዝ የሚለው ቤተክርስቲያን ሲሄድ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሲወጣ እግዚአብሔርን “በተመሳሳይ ጊዜ ጧፍ እና ዕጣን ይዤ መጥቼ እስክንገናኝ ደኅና ሁን!” ብሎ ነው ወደ ኑሮው የሚመለስ ነው የሚመስለው፡፡ ኑሮው ውስጥም ኢፍትሐዊነት፣ ከእኔ በላይ ላሣር ባይነት፣ ኩራት እንጂ ክርስቶስ ማዕከል ሆኖ አይገኝም፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ግን “የክርስትና ማዕከሉ ክርስቶስ ነው፡፡” ይሉ ነበር፡፡ ክርስቲያን መሆን ማለትም እግዚአብሔርን የኑሮ ማዕከል፣ የእይታ አንጻር አድርጎ መኖር ማለት እንጂ እሑድ እሑድ ቤተክርስቲያን እየሄዱ ሌሎቹን የሳምንቱን ቀናት ራስን ማዕከል አድርጎ መኖር ማለት አይደለም፡፡ ክርስትና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መገንባት አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ ማካሄድ አይደለም፡፡ እገሌ የሚባል ማኅበር ማቋቋም አይደለም፡፡ የመዝሙር ሲዲ ማሳተም አይደለም፡፡ ጥምቀት ሲሆን ታቦት ማጀብ አይደለም፡፡ ነጠላ ለብሶ መታየት አይደለም፡፡ ቀሚስ ማስረዘም አይደለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ገንዘብ መስጠት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ የክርስትና ትውፊትና ትሩፋት እንጂ ክርስትና አይደሉም፡፡ ክርስትና እንደ እመቤታችን እግዚአብሔር የሕይወቴ ጌታ ነው፤ እኔም የእግዚአብሔር ባርያው ነኝ ብሎ እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ኑሮ መምራት ነው፡፡ እመቤታችንን እንወዳለን እንላለን፡፡ የእመቤታችን ሕይወት ግን ፈጽሞ በእኛ ዘንድ የለም፡፡ የእመቤታችን ስሟ እንኳ ትዝ የሚለን ወይ ችግር ሲያጋጥመን አለበለዚያ በዓል ሲሆን ነው፡፡ ወይም ደግሞ ለመሓላ፡፡

  ኩራት፣ ስስታምነት፣ ጭካኔ ልቦቻችንን ሞልቷል፡፡ እነዚህ ዛሬ መጡ ያልናቸው 36 000 ሰዎች ከኑሯችን ክርስቶስን አግኝተው በመንፈሳዊ ሕይወት በልጽገው ይኖራሉ ወይስ በውጪ አማንያን በሥራችን ግን ኢአማንያን ከሆንነው ከእኛ ክፋትን፣ መለያየትን ተምረው፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላም ከእኛ ብሰው የኢአማኒ ሥራ ይሠሩ ይሆን? ጌታችን “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፡፡” ያለው በእውነት ዛሬ በእኛ ላይ ይታያል፡፡ ሁላችንም በልቦቻችን ቄሣሮች ነን- ዓለምን በሙሉ በእኛ ማዕከልነት ማሽከርከር የምንፈልግ ኩራተኞች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ሲልኮ መፎከሩ አልነበረም- ቄሣር ጌታ አይደለም ማለቱ እንጂ፡፡ አዳም አምላክነትን ፈልጎ እንደወደቀ ሁላችንም እግዚአብሔርን የአምላክነቱን የማዕከልነቱን ስፍራ ነፍገነዋልና ወድቀናል፡፡ ልክ አይሁድ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን” ይሉ እንደነበረው እኛም ክርስቲያኖች ነን እንላለን፡፡ ሕይወታችን ግን ክርስቶስ የሌለበት ሆኖ ይታያል፡፡ ክርስቲያኖች ከሆንን ከራሳችን ጋርም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በፍቅር፣ በተስፋና በርኅራኄ ክርስቶስ የሚነግሥበት ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ የእኛ ግን እንዲህ አይደለም፡፡

  እነሆ! በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ጨዋታው “ጥሎ ማለፍ” ነው፡፡ ነጋዴው ሱቁ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሰቅሎ ገበያተኞቹን አለአግባብ ሲዘርፍ፣ ሲዋሽ ይውላል፡፡ የቢሮ ሠራተኛዋ ጠረጴዛዋና ኮምፒውተሯ ላይ ቅዱሳት ሥዕላትን ደርድራ ባለጉዳዮችን ስታጉላላ፣ ስትገላምጥ ትውላለች፡፡ አስተማሪው፣ አንገቱ ላይ ትልቅ መስቀል አንጠልጥሎ ተማሪዎቹን ሲሳደብ፣ ሲያንጓጥጥ ይውላል፡፡ ባለሥልጣን በሥልጣኑ ተመክቶ የሰው ሚስት ሲቀማ፣ በሚስቱ ላይ ሲወሽም ያድራል፡፡ ሁሉም ራሱን ማዕከል አድርጎ ይሮጣል፡፡ እንግዲህ፣ እግዚአብሔር የነገሠበት የክርስቲያን ሕይወት ወደየት ይገኝ? የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ ይህንን ነው “ከንቱ! ከንቱ! የከንቱ ከንቱ!… ነፋስንም መከተል” ብሎ የገለጸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣቱ ከዚህ የከንቱና ትርጉም አልባ ኑሮ ሊያላቅቀን ነበር፡፡ እርሱ አባቱን ማዕከል አድርጎ እንደኖረ እኛም እርሱን ማዕከል አድርገን እንድንኖር አስተማረን፡፡ አሳየን፡፡ ያውም እስከ መስቀል ሞት ድረስ!

  ጸሐፍት ፈሪሳውያን ራሳቸውን “የአብርሃም ልጆች” ይሉ ነበር- ልክ እኛ ዛሬ ራሳችንን የሥላሴ ልጆች እንደምንለው፡፡ አብርሃም ግን የእግዚአብሔር ወዳጅ የተባለው እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ በማመኑ ነበር፡፡ እነርሱ የአብርሃም ልጆች ነን ያሉት ግን ቤተመቅደስ ስለገነቡ፤ የአባቶቻቸውን ባህልና ትውፊት ይጠብቁ ስለነበር ነው፡፡ ባህሉን ያዙትና የባህሉን መነሻ የነበረውን እግዚአብሔርን የሕይወታቸው ጌታ አድርጎ ማመንን ግን ዘነጉት፡፡ እግዚአብሔርን በምሕረትና በፍትሕ ሳይሆን በመሥዋዕትና በሥጦታ ሊገለገሉበት እየሞከሩ ነበር፡፡ የመንገዳቸውን ትክክለኛነትም አይጠራጠሩም ነበር- ኃጢኣት ሲለመድ ጽድቅ ይመስላል እንዲሉ አበው፡፡

  ምናልባትም ጌታችን “እናንተ አንድ ሰው ለማሳመን በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፣ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት ዕጥፍ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፣ ወዮላችሁ!” (ማቴ 23፣ 13) ያለው ተግሣፅ እንዳይደርስብን ማስተዋል መልካም ነው፡፡

 6. yoseph October 21, 2015 at 8:39 am Reply

  እግዚአብሄር ይመስገን ይህንን መስማት ታላቅ ነዉ፡፡ እኔ ጠንካራ ነኝ ብዩ የማስበዉ ሰዉ ቤተክርሰትያን ዉስጥ ተሰግስገዉ ያሉ አማኝ መስለዉ በህዝብ እንባ የመጣዉን ገንዘብ ሙልጭ አርገዉ ሲበሉ ሳይ፤ ከተማ ዉስጥ “ቆብ” አጥልቀዉ ዘመናዊ መኪና የሚያሽከረክሩ አለቆች ሳይ፤ ጉቦ በህገ እግዚአብሄር የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ዉስጡ ሆኜ ስቃጠል ሳይ ገና ገና ገና ብዙ ስራ የጠብቀናል፤፤ አማሳኞቹ ካልተወገዱ እና በህግ ካልተጠየቁ ምንም ያህል ቁጥር ቢጠመቁ በእኔ እምነት እነዚህ ወገኖቻችን እንኩዋን ለእግዚአብሄር መንግስት አበቃቸዉ ከማለት ዉጪ ምን እንላለን፤፤

 7. Anonymous October 22, 2015 at 12:31 pm Reply

  የቀለም ወለጋ ርፖርት ከእዉነት የራቀ ነዉ:: ምክንያቱም Salem International Christian Revewal Church ብቻ ከ1200 በላይ ህዝብን ከኦርቶዶክስ ሰብስቧል:: ለሎች የፕሮተስታንት church እንደዚሁ ሰብስቧል:: የሀገረ ስብከቱ ስራአስኪያጅ ለምን የተደባለቀ ርፖርት ያቀርባል:: አባረርኩ የምላቸዉ አገልጋዮች እንኩአ 87 ናቸዉ:: አንድ ቤ/ክርስቲያን ተዘግቷል:: ኤረ ይጣራ!

 8. Anonymous October 22, 2015 at 5:25 pm Reply

  ሙሰኞች እና ሀራ ጥቃ ተሀድሶ ከቤተክርስቲያን በጊዜ ካልተወገዱ እስከዛሬ አመት በ3 እጥፍ ጨምረው እንደሚታዩ ጥርጥር የለኝም ምክንያቱም የአባቶች ዝምታ ከመጠን ያለፈ ይመስለኛል ቢቻል መክሮ መመለስ ካልተቻለ ግን ማውገዝ ለምንፍቅና ጊዜ መስጠቱ የሚያዋጣ አይመስለኝም እኔ በበኩሌ ተቃጥዬ መሞቴ ነው ቤተክርስትያናችንን እግዚአብሔር ይጠብቅልን አሜን

 9. workineh semma November 12, 2015 at 9:58 am Reply

  ዘግይተናል ቢሆንም ዛሬ ፈጥነናልና በጉባኤያችን ላይ እግዚአብሄር ይጨመርበት፡፡ ለሰው ዘላለማዊ ሂወትን ከማውረስ ውጭ ምን ደስታ አለ???

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: