የአ/አበባ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሙሰኛ አስተዳደር የሰንበት ት/ቤቶችን ማሳደዱን ቀጥሎበታል፤በሰሚት መድኃኔዓለም ከአዳራሽ እንዲባረሩ ተደርጓል

የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች÷ በአህጉረ ስብከትና በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንድነት መድረክ በመፍጠር፣ በፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄና በፀረ ሙስና ንቅናቄ፣ ለዕቅበተ እምነትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን በየአጥቢያቸው ተጋድሏቸውን በአቀጣጠሉበት በአሁኑ ወቅት፤ ራሱን ከአማሳኞችና ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ምንደኞች ጎራ በገሃድ አሰልፎ በሥልጣን ለመሰንበትና ምዝበራውን ለማጧጧፍ የሚወራጨው የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ – ኤልያስ ተጫነ የሀገረ ስብከት አስተዳደር ወጣቶቹን በማሳደድና በመበተን እኩይ ግብሩ ቀጥሎበታል፡፡

ገና ከማለዳው ሲገለጽ እንደቆየው፣ በአስተዳደራዊ መዋቅራችን የተሰገሰጉ አማሳኞችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ያላቸው የዓላማም የጥቅምም ትስስር ከሰሞኑም በማያሻማ ሁኔታ በተረጋገጠበት የብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን፤ አጉራ ዘለሉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ምንደኛ በጋሻው ደሳለኝ በዐውደ ምሕረታቸው እንዳይቆም በሰላማዊ መንገድ የተቃወሙ ዐሥር የሰንበት ት/ቤቱ አመራርና አባላት በእስር ተንገላተዋል፡፡

the heretic and the corrupt

የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ምንደኛው በጋሻው ደሳለኝ እና አማሳኙ ነአኵቶ ለአብ አያሌው

ያለአግባብና ከዋጋ በታች በሚፈጸም ኪራይ በሚመዘበረው የደብሩ ቦታ ሳቢያ በገነፈለው የምእመኑ ቁጣ፣ ከሀገረ ስብከቱና ከክፍለ ከተማው ሓላፊዎች ጋር በጥቅም በተቆራኘው በዋልጌው የደብሩ አስተዳዳሪ ነአኵቶ ለአብ አያሌው፣ ‘ሁከት ፈጥረዋል’ በሚል የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮችና አባላቱ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሐሰት ክሥ ቀርቦባቸዋል፡፡ ከዐሥሩ ወጣቶች ስምንቱ በእስር የዋሉ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ አድረው ወጥተዋል፤ ከእስር ሲለቀቁም ፈረመው እንዲወጡ ነው የተደረጉት፡፡

አጉራ ዘለሉ በጋሻው÷ የደብሩ አስተዳዳሪ ባደረገለት ጥሪ ዐውደ ምሕረቱን ለመዳፈር ያደረገው የመጀመሪያ ሙከራ በቀናዒ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ሰላማዊ መከላከል ከተደረገበት በኋላ፣ አለቃው ዳግመኛ ከመጋበዝ እንደማይቆጠብ በይፋ መግለጹን ተከትሎ ሀገረ ስብከቱ ችግሩን ተገንዝቦ ለአጥቢያው ሰላም መጠበቅ የማያዳግም ርምጃ እንዲወስድ ለዋና ሥራ አስኪያጁ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ እንዲነገረው ተደርጓል፡፡

“እኔ በዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም፤ የሰጠነውም ደብዳቤ የለም፤” ያለው ዋና ሥራ አስኪያጁ ጉዳዩን ካወቀውም በኋላ፣ “እሺ ከዚህ በኋላ አስቁምልን” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ የሚጠበቀውን መመሪያ ለደብሩ አስተዳደር ሳያስተላልፍ ቀርቷል፤ “እስኪ እናየዋለን” የሚለው የዕብሪት ምላሹም የፈየደው ነገር ባለመኖሩ፣ አጉራ ዘለሉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ምንደኛ በሁለተኛ ሙከራው በዐውደ ምሕረቱ እንዳሻው በመደንፋት ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያንን ለመዝለፍ አስችሎታል፡፡

ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከቁጥጥር ዋና ክፍሉ፣ ከክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅና የሰው ኃይል አስተዳደር ሓላፊ ጋር በሙስና የተቆራኘው የብሔረ ጽጌው አስተዳዳሪ÷ ከጉባኤው አንድ ቀን በፊት ምንደኞቹ ለጊዜውም ቢሆን በተቆጣጠሩት የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ቅስቀሳ ያካሔደ ሲሆን ለምንደኞቹ እገዛ የሚያደርገው ናሁ ሠናይ ነጋም ያለአጥቢያው ተገኝቶ መርሐ ግብሩን እንዲመራ ተደርጓል፡፡ “የሚገርመውና አሳፋሪው ነገር ምእመን ተብሎ የመጣው ሕዝብ የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍን የሚያውኩና የአካባቢ የፕሮቴስታንት ድርጅት ተከታዮች ያለመደባቸውን ነጠላ ለብሰው መገኘታቸው ነው፤” ይላሉ በፌስ ቡክ ትዝብታቸውን ያሰፈሩ ጸሐፊ፡፡

በተለይም የክፍለ ከተማው የሰው ኃይል አስተዳደር ክፍል ሓላፊና ከየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለው ቅርበት በክፍለ ከተማው አጥቢያዎች ላይ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራትን በተልእኮ እየፈጸመ የሚገኘው ሙሴ ዘነበ፣ “እኔ በዚህ ክፍለ ከተማ እስካለሁ ድረስና እኔ በምመራው ማንኛውም ክፍለ ከተማ በጋሻው እንደሚያስተምር ቃል እገባላችኋለሁ፤” ሲል በመዛት አጋርቱነን መግለጹ ተዘግቧል፡፡

በጃቲ ኪዳነ ምሕረት እና በአቃቂ ቅ/ጊዮርጊስ አጥቢያዎች ምንደኞቹ በሚፈጥሩት ሁከት የሰንበት ት/ቤቶቹን አባላት ጨምሮ ካህናቱና ምእመናኑ ያልተቋረጠ አቤቱታ የሚያሰሙ ቢሆንም ለሙሰኛው የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አስተዳደር የሚገደው አልሆነም፡፡


ስለ ሰንበት ት/ቤቶች አደረጃጀት በቃለ ዐዋዲው የሰፈረውን ድንጋጌ በመተላለፍ፣ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሀብታምና ድኃ ተብለው መከፈላቸውን የተቃወሙት የሰሚት ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አመራሮች እና አባላት በአማሳኙ አለቃ ጥያቄና በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የታገዱ ሲሆን የሰንበት ት/ቤቱም ተበትኖ አመራሮቹ፣ አባላቱና ቤተሰቦቻቸው ሳይቀር ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡

የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ዋና ጸሐፊ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የጥቅም ቀርኝት የፈጠሩት የያኔው የካቴድራሉ ካህን የዛሬው የደብሩ አለቃ፤ በአሁኑ ወቅት በዋና ሥራ አስኪያጁ የቅጥርና ዝውውር የምዝበራ ሰንሰለት ውስጥ ተጠቃሹ የጉቦ አቀባባይ ሲሆኑ ይህንኑም ግንኙነታቸውን በመጠቀም የሰንበት ት/ቤቱን አባላት በማንአለብኝነት ማሳደዳቸውንና መበተናቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ በቃለ ዐዋዲው በተደነገገው ተግባርና ሓላፊነታቸው ክልል ጥያቄ በማንሣታቸው፣ “ሁከት ፈጣሪዎችና አሸባሪዎች” በሚል ተከሰው አምቼ በሚገኘው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዐሥር የሰንበት ት/ቤቱ አመራርና አባላት በአጠቃላይ ለ15 ቀናት በእስር ቆይተዋል፤ ከእነርሱም ጋር አብረው መንገላታታቸው ሳይበቃ በቦሌ ምድብ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የስምንት ወራት እስር የተፈረደባቸው ሁለት ምእመናን በሁለት ዓመት ገደብ ቢለቀቁም አራት የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር አባላት ጉዳይ ሳይዘጋ ለዚህ ዓመት ተላልፎ ለመጪው ኅዳር 14 ተቀጥረዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የአመራር አባላቱ “የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ልጆች” መኾናቸውን መስክሮና ጉዳዩም በውስጥ አሠራር እንደሚፈታ የጻፈው ደብዳቤ ከእስር እንዲፈቱ አስተዋፅኦ የነበረው ቢኾንም የተከፈተባቸው ክሥ ሳይዘጋ በቀጠሮ እንዲራዘም ተደርጓል፤ የሰንበት ት/ቤቱ እንዲበተን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የጻፈው ደብዳቤም ጉዳዩን ለማጠናከርያነት ምክንያት ኾኗል፡፡

የደብሩ አስተዳዳሪ በየማነ ትእዛዝ “ከሠላሳ ዓመት በታች” ባሉ በሚል ሰንበት ት/ቤቱን እንደ አዲስ አቋቋምኩ ቢሉም፣ በአመራርነት የሠየሟቸው የጽ/ቤቱን የአስተዳደር ሠራተኞች መኾኑ ሲታይ ሕገ ወጡ የኃይል ርምጃ፣ ዲስኩረኛው አማሳኝ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሳያባራ እንደሚለፈልፈው፣ እንደ ቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ለማዋቀር ሳይኾን ሕጋዊውንና ጠንካራውን የሰንበት ት/ቤትና አመራሩን ለመበተን ሲባል ብቻ የተደረገ እንደነበር ግልጽ ያደርገዋል፡፡

ጥቂት የማይባሉ የአጥቢያው ምእመናን በልጆቻቸው መንገላታት ተመርረው በሸሹት አጥቢያ፣ እንደ አዲስ ተዋቅሯል የተባለውን የሰንበት ት/ቤት በሊቀ መንበርነት የሚመራው የደብሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊ ሲኾን፤ ጸሐፊው፣ ቁጥጥሩና የሒሳብ ሹሙ ደግሞ በአመራር አባልነት ተካተውበታል፤ ይህም አማሳኙ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከት አስተዳደር የቤተ ክርስቲያን ተተኪዎች ለሚፈሩበት ተቋም ያለውን ሓላፊነት የጎደለው ዓምባገነናዊ አካሔድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

የቱንም ያህል ቢሳደዱም በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ተስፋ ያልቆረጡት የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮችና አባላት፣ በአቅራቢያ የተለያዩ አጥቢያዎች ታቅፈው አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ አስተዳደራዊ ፍትሕ ለማግኘት ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ መስከረም 26 ቀን ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ ጉዳያቸው በሕግ ተይዞ በቀጠሮ ያሉትን፣ ጉዳያቸው በፍርድ ተይዞ በቀጠሮ የተለቀቁትን የሰንበት ት/ቤት አባላት÷ ወደ ሰንበት ት/ቤት እንዳይገቡ፣ እንዳይመዘገቡ እንዲኹም እንዳያገለገሉ ይልቁንም ከሰንበት ት/ቤቱ አዳራሽ በግፍ እንዲባረሩ የተደረጉትን 16 አመራሮችና አባላት በስም በመዘርዘር ድርጊቱን በጥብቅ ተቃውሟል፤ ኹኔታውም ጽ/ቤቱ በ“ሁከት ፈጣሪነት ሥራ ነው” መቀጠሉን እንደሚያሳይ በመግለጽ ችግሩን በአግባቡ በመፍታት የማረጋጋት ሥራ እንዲሠራ አሳስቧል፡፡
eotc ssd on summit med

የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ምእመናንን ማባረርና መበተን ሳይኾን መሰብሰብና ማስተማር እንዲኹም ለአገልግሎት ማብቃት እንደኾነ ማደራጃ መምሪያው ጠቅሶ፤ በቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት መዋቅር ሥር እንዳያገለግሉ የሚያግድ ሕግ እስካልተጣለባቸው ድረስ ገብተው እንዲማሩ፣ በተመረጡበት የአገልግሎት ዘርፍም እንዲያገልግሉ መፈቀዱን በማስታወቅ ሀገረ ስብከቱም ሰንበት ት/ቤቱም አካሔዳቸውን እንዲያርሙ አስታውቆ ነበር፤ ደብዳቤውም በማግስቱ መስከረም 27 ቀን ለደብሩ አስተዳዳሪ መድረሱ ተረጋግጧል፡፡

የደብዳቤው ግልባጭ የደረሳቸው፣ የታገዱት 5 የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮችና 11 አባላት በዚያው ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 29 ቀን ወደ ሰንበት ት/ቤቱ በመግባት ከሌሎች ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ጋር እየተማሩ ባሉበት፣ በሊቀ መንበርነት በተሠየመው የደብሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊ፣ “አስተዳዳሪው አልነገሩንም፤ ውጡልን” በሚል ከአዳራሽ አባሯቸዋል፡፡

Summit Medhanialem ss

የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ጉባኤያቸው ተበትኖ ከአዳራሹ ከተባረሩ በኋላ የማኅበር ጸሎት ሲያደርሱ

ከማዳራጃ መምሪያው የተጻፈውን ደብዳቤ በማሳየት ለማስረዳት ሙከራ ቢደረግም፣ “እንኳን ማደራጃ መምሪያ ፓትርያርኩ ራሳቸው ቢነግሩኝም አባ ገብረ ሥላሴ[አለቃው] ካላዘዙኝ አላስገባችኋም” የሚል ምላሽ ነው ከስብከተ ወንጌል ሓላፊው የተሰጣቸው፡፡ በኹኔታው ያዘኑት ቀሪዎቹ 130 ያኽል የሰንበት ት/ቤቱ አባላት፣ “የወንድሞቻችን መገፋት የእኛም መገፋት ነው፤ እነርሱ ከወጡ እኛም እንወጣለን” ብለው አዳራሹን ለቀው በመውጣታቸው አጠቃላይ መርሐ ግብሩ ተስተጓጎሏል፡፡

summit med ss whole demolished

’ድኃ ልጆች’ በሚል በአማሳኙ የደብሩ ጽ/ቤት የፈራረሰውና የተሰባበረው አዳራሽና የዜማ መሣርያዎች

“አፈንጋጮች ውጡ፤ ተብለን የሀብታም ልጆች የሚማሩበት ነው ካሉት አዳራሽ ካስወጡን በኋላ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠግተን የጉባኤ ጸሎት እያደረሰን ነበር፤” ያለ አንድ የሰንበት ት/ቤቱ አባል፣ ‘የድኃ ልጆች’ የተባለው አዳራሽ ፈራርሶ፣ በውስጡ የነበሩት መቋሚያዎችና ከበሮዎች፤ ጠረጴዛዎችና ወንበሮች ተሰባብረው መመልከቱን ተናግሯል፡፡ አያይዞም፣ “ይህም አስተዳደሩ የማዳራጃ መምሪያውን ማሳሰቢያ እንዳልተቀበለና እንድንመለስም ጨርሶ እንደማይሻ አረጋግጦልናል፤” ብሏል፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብቶችና ጥቅሞች አሳልፈው በመስጠት ራሳቸውን ያበለጸጉ አማሳኞችን በማስተባበር በሥልጣን ለመሰንበት፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በየማረፊያዎቻቸው ደጅ እየጠና ለሚገኘው ለሀገረ ስብከቱ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ – ኤልያስ ተጫነ አስተዳደር በየአጥቢያው የሚሰማው የግፉአን አዳጊዎችና ወጣቶች ድምፅ፣ የውኃ ውስጥ ጩኸት ቢኾንም፤ በፀረ ኑፋቄና ፀረ ሙስና ንቅናቄው ለዕቅበተ እምነት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለፍትሕ የሚደረገውን ንቅናቄ የበለጠ ያጠናክረዋል እንጂ ለአንዳፍታ እንኳ እንደማያዝለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: