አማሳኝ ሓላፊዎች በንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከለላነት ያገዱት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ: ፓትርያርኩን ወቀሰ

YeBetekirstian Tser Elias Abreha

 • ገዳሟን ለችግር የዳረጉት ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው፣ ሰበካ ጉባኤው እንዳይሠራ ተደርጓል
 • ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት ለማቅረብ ጽ/ቤቱ ቢጠየቅም ሌላ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ተካሒዷል
 • የገዳሟ ሒሳብ በውጭ ኦዲተር እንዲጣራ በፓትርያርኩ የተሰጠው ትእዛዝ ተግባራዊ አልኾነም
 • ፓትርያርኩ፣ ወደ ተግባራዊ የፀረ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ርምጃ እንዲገቡ ተጠይቋል

*          *          *

 • በ7 ወራት ሒሳብ የቅድመ ኦዲት ዳሰሳ ብቻ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩ ተረጋግጧል
 • ከሰበካ ጉባኤው ጋር የተባበሩ ካህናት በደመወዝ፣ በእገዳና በዝውውር እንግልት ተፈጽሞባቸዋል
 • በመዝባሪነታቸው መጠየቅ የሚገባቸው ሓላፊዎች፣ በሹመት እና ዝውውር እንዲሸፈኑ ተደርጓል
 • ሰበካ ጉባኤው የኹኔታውን ምፀታዊነት፣ “እናቱን በገጀራ የገደለ ጎራዴ ተሸለመ” ሲል ገልጦታል

(ሰንደቅ፤ 11ኛ ዓመት ቅጽ 526፤ ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም.)

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የሚታየውን ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለማስወገድ ጥረት ባደርግም፣ “የፓትርያርኩን አዎንታዊ እገዛና አመራር አላገኘሁም” ያለው የታገደው የገዳሟ ሰበካ ጉባኤ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ወቀሰ፤ “ሙስናን እንታገላለን፤ መልካም አስተዳደርን እናሰፍናለን” ብለው ፓትርያርኩ ለሕዝቡ የገቡት ቃል በተግባር ካልታገዘም “የማዘናጊያ መፈክር እንጂ በራሱ ትግል አይኾንም” ብሏል፤ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፈው ደብዳቤ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መቀመጫ በኾነችው ገዳም፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት በማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጦ በከፊል ወደ ሥራ ገብቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ሰበካ ጉባኤው በደብዳቤው ጠቅሷል፡፡ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊትም፣ በገዳሟ ያለውን ዘረፋ በማስቆም ሒሳቧን በውጭ ኦዲተሮች እንዲያስመረመር እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ እና የሥራ መመሪያ ተቀብሎ እንደነበር አስታውሷል፡፡

በመመሪያው መሠረት በተመረጠ በኹለት ወራት ጊዜ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ የቃለ ዐዋዲ ደንብ ላይ የተመሠረተና ዘመኑን የዋጀ÷ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል፣ የንብረት፣ የግዥ መመሪያዎች፣ የገዳሙ ማኅበረሰብ የሚመራበት መተዳደርያ ደንብ ሰነዶች ረቂቅን በአባላቱ ወጪ ማዘጋጀቱን ሰበካ ጉባኤው ገልጧል፡፡

ለሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሠራር እንዲዘረጋ፣ ቆጠራውም ከባንክ ጋር በትብብር የሚሠራበት መመሪያ አዘጋጅቶ ትግበራውም ተወጥኖ እንደነበር አስቀምጧል፡፡

የሒሳብ ማጣራትን በተመለከተ በገዳሟ ሒሳብ ላይ በተካሔደው የቅድሚያ ዳሰሳ ጥናት፤ ከኹሉም ገቢዎች በአማካይ በወር ብር 300‚000 ወይም በሰባት ወራት ላይ በተደረገው ዳሰሳ ከብር ኹለት ሚሊዮን በላይ መመዝበሩን ተመልክቼአለኹ፤ ብሏል፡፡ የንብረት ምዝገባም ባለመኖሩ ቤተ ክርስቲያንና አገራችን በአጠቃላይ ልታጣ የምትችለውን መገመት እንደማይከብድ ለቅዱስነታቸው አስገንዝቧል፡፡

ለተዘረዘሩት ዘረፋዎች÷ የገዳሟ ገንዘብ አንቀሳቃሽ(ቼክ ፈራሚዎች)፣ የሒሳብ ሹም፣ የቁጥጥር፣ የንብረት አስተዳደር፣ ጸሐፊው እና የገንዘብ ቤት ሓላፊዎች ተጠያቂዎች መኾናቸውን በመግለጽ የገዳሟ ልማት የበላይ ጠባቂ የኾኑት ፓትርያርኩ በደብዳቤ እንዲያውቁት ማድረጉንና ርምጃ ይወሰድም ዘንድ ለሚመለከተው አካል አመራር እንዲሰጥ ከኹለት ጊዜ በላይ በግንባር ቀርቦ ማስረዳቷን ሰበካ ጉባኤው ገልጧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተገቢውን አመራር እንደሚሰጡ በየጊዜው ቃል ቢገቡም ከጽ/ቤታቸው በተላለፉ ትእዛዞች፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለችግር የዳረጉ ኃይሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የተለየ ጥበቃ እና ክብካቤ ሲደረግላቸው በአንጻሩ ሰበካ ጉባኤው እንዳይሠራ መደረጉን አስታውቋል፤ ኹኔታውንም “እናቱን በገጀራ የገደለ ጎራዴ ተሸለመ” ሲል ነው የገለጸው፤ አያይዞም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን መመሪያ ትልቅ አቅም አድርጎ ለመሥራት ቢነሣሣም አዎንታዊ አመራራቸውንና እገዛቸውን ባለማግኘቱም ማዘኑን ገልጧል፡፡

ከፓትርያርኩ ጽ/ቤት በሚተላለፉ ትእዛዞች፣ ሰበካ ጉባኤው ለቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱና ይልቁንም የገዳሟ ችግሩ እየተባባሰ መሔዱ እንዳሳዘነው በደብዳቤው ጠቁሟል፡፡ ይህም በሥራው መጀመሪያ ላይ በፓትርያርኩ ከተሰጠው መመሪያ እና ፓትርያርኩ በየመድረኩ ሙስናን ከሕዝብ እና ከመንግሥት ጋር ኾኖ ለመታገልና ከቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ከገቡት ቃል ጋር እንደሚፃረር አስረድቷል፤ የቅዱስነታቸው ቃል በተግባራዊ እንቅስቃሴ ካልታገዘም “የማዘናጊያ መፈክር እንጂ በራሱ ትግል አይኾንም” ሲል ሰበካ ጉባኤ አሳስቧል፡፡

ይኹንና “የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመኾናችን ተስፋ አንቆርጥም” ያለው ሰበካ ጉባኤው፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመልካም አስተዳደር ማስፈን ርምጃ ውስጥ በተግባር እንዲገቡ ተማፅኗል፤ ለዚኽም ከጎናቸው በመቆም የበኩሉን እገዛ ለማበርከትም ያለውን ዝግጁነት አረጋግጧል፡፡

ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ በአማሳኝ የገዳሟ አስተዳደር ሓላፊዎች በተላለፈ እገዳ እንዳይቀጥል መደረጉ የተመለከተው ሰበካ ጉባኤው፣ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ 12(28) መሠረት ለመረጠው የማኅበረ ካህናት እና የማኅበረ ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ የሥራ ሪፖርት ለማቅረብ በፓትርያርኩ አመራር ይሰጥለት ዘንድ መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቅዱስነታቸው በጻፈው ደብዳቤ ቢጠይቅም ባለፈው ሳምንት እሑድ አዲስ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ መካሔዱ ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት ጥር የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ፣ የሦስት ዓመት የሥራ ዘመን ቢኖረውም መንፈቅ እንኳ በቅጡ ሳይሞላው ከልዩ ጽ/ቤቱ በተላለፈ ትእዛዝ አላግባብ ከሓላፊነቱ ስለታገደበት ኹኔታ ጠቅላላ ጉባኤው በሪፖርት እንኳ እንዲሰማ ሳይደረግ ሌላ ምርጫ መካሔዱ ጥቅመኝነት ያስተሳሰረው አሠራር የሚገኝበትን ደረጃ አመላካች ነው፤ በመንበረ ፓትርያርኩ መፈጸሙም በእጅጉ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡


Qese Gebez Aba Samuel Kelemework Edቄሰ ገበዝ አባ ሳሙኤል ቀለመ ወርቅ ይባላሉ፡፡ በተመደቡባቸው አጥቢያዎች ኹሉ፣ ከአስከፊ የምግባር ብልሽት ባለፈ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በማቃለልና የታቦትን ክብር በመዳፈር በታየባቸው ከፍተኛ የሃይማኖት ሕጸጽ ቀኖናዊ ርምጃ ሲወሰድባቸው ቆይቷል፡፡ ይኹንና ይህ ችግራቸው ላለፉት አራት ወራት የታገደውን ሰበካ ጉባኤ ተክተው የገዳሟን ሒሳብ እንዳያንቀሳቅሱ አልከለከላቸውም – ከለላ በሚሰጧቸው በንቡረ እድ አልያስ እና በሀገረ ስብከቱ ተባባሪዎቻቸው ድጋፍ!!!

Aba Samuel Kelemework's file00


የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያትን የማደራጀትና የማጠናከር ሓላፊነት ያለባቸው የሀገረ ስብከቱ ዋና እና ድጋፍ ሰጭ ክፍሎች፣ ከገዳሟ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በማስወገድ አስተዳደሯን ለማሻሻል ለተፈጸሙ ተጋድሎዎች ያደረጉት ድጋፍ እና ክትትል የለም፤ ይልቁንም፣ የሰበካ ጉባኤው የማኅበረ ካህናት ተወካዮች በጥረቱ ተሳታፊ በመኾናቸው ብቻ ከአስመሳዩ ዋና ሥራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጋር በመመሳጠር ከሥራ እና ከደመወዝ ሲታገዱ፣ ወደ ሌሎች አጥቢያዎች ዝውውር እየተጠየቀባቸው በአቤቱታ ሲንገላቱ ከአለኝታነት ይልቅ ዋነኛ ተባባሪዎች ነበሩ፡፡

nebureed-elias-abrehaቀደም ሲል ስለ ጉዳዩ በተላለፉ ዜናዎች እንደተዘገበው፤ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት አሠራር ውጭ የኾኑት የገዳሟ ታጣቂ አማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎች÷ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሳቢነት በማኅበረ ካህናት፣ በማኅበረ ምእመናን እና በሰንበት ት/ቤት ምልዓተ ጉባኤ የተመረጠውንና ተጠሪነቱ ለአጥቢያው ካህናትና ምእመናን ጠቅላላ ጉባኤ የኾነውን የሰበካ ጉባኤ የማገድ ሥልጣን ባይኖራቸውም ለሕገ ወጥ አካሔዳቸው ዋና መከታ ያደረጉት የፓትርያርኩን ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን ነው፡፡

የሰበካ ጉባኤው በአሠራር እያጠናከረ በመጣው የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ቁጥጥር የተነሣ ከአማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎቹ በኩል የሚቀርብላቸው ፈሰስ የቀረባቸው ንቡረ እዱ፣ የገዳሟ የልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ለፓትርያርኩ የሚቀርቡ የማኅበረ ካህናቱንና የማኅበረ ምእመናኑን አቤቱታ ሲያፍኑ ቆይተዋል፡፡

‹‹የሙስና አባቱ፤ የአማሳኞች ካቢኔ ሊቀ መንበሩ›› ልዩ ጸሐፊው፣ የሀገረ ስብከቱን ግብረ አበሮቻቸውን በመጠቀም ከሰበካ ጉባኤው ጋር ይተባበራሉ የተባሉ የገዳሟ ሊቃውንትና ካህናት ከሥራና ከደመወዝ አሳግደዋል፤ በማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች አሸማቅቀዋል፤ አኹን ደግሞ ጊዜአቸውንና ገንዘባቸውን ሰጥተው በታማኝነት እና በትጋት የሚያገለግሉ የሰበካ ጉባኤው አባላት ‹‹ጃኬት ለባሽ›› ተብለው እንዲታገዱና ጨርሶ በቅጽሩ እንዳይሰበሰቡ አስከልክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው እሑድ ስለተደረገው ምርጫ የወቅቱ የገዳሙ ዋና ጸሐፊ መምህር ምሩፅ ትኵዕ ለዛሬው የሰንደቅ እትም እንደተናገሩት፤ ለምርጫው የኹለት ወራት ቅስቀሳ ሲካሔድ የቆየ ሲኾን በዕለቱም የገዳሙ ማኅበረ ካህናትና ሠራተኞች፤ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት አባላት እንዲኹም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ነው የተከናወነው፡፡

ከቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ወደ ገዳሟ በዝውውር የመጡት በቅርቡ በመኾኑ ስላለፈው ችግር ለማስረዳት እንደማይችሉ፤ ነገር ግን የሰላም እና ዕርቅ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ችግር ቢኖር በአጥቢያ ደረጃ መፍትሔ የሚሰጠው አስተዳደሩና የሰበካ ጉባኤው ስለኾነ መፍትሔ እየሰጠን እንሔዳለን ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፤ ብለዋል፡፡

*          *          *

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጻፈው ደብዳቤ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው፤

መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም.

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ

በቅድሚያ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ፣ ቸሩ እግዚአብሔር ለቅዱስነትዎ ረዥም ዕድሜ እና ጤና እንዲሰጥዎት ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ቅዱስ አባታችን÷ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ፣ በጥር ወር 2007 ዓ.ም. ተመርጦ ሥራውን በየካቲት 2007 ዓ.ም. ለመጀመር ከቅዱስነትዎ ቡራኬ እና የሥራ መመሪያ ለመቀበል ወደ ጽ/ቤትዎ በቀረበ ጊዜ ቅዱስነትዎ አበክረው ከሰጡት ትእዛዝ ውስጥ፤ በዋናነት በገዳሙ ውስጥ ያለውን ዘረፋ የማስቆም፣ ለዚሁም በገለልተኛ የሒሳብ አጣሪዎች የገዳሙ ሒሳብ ማስመርመር እንዲሁም መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አሠራር መዘርጋት የሚሉት ዋነኞቹ እንደነበሩ ሰበካ ጉባኤው ያስታውሳል፡፡

ይህን የቅዱስነትዎን መመሪያ መሠረት በማድረግ ሰበካ ጉባኤው በሳምንት ኹለት እና ሦስት ጊዜ እየተሰበሰበ የገዳሙን መሠረታዊ ችግሮች በመለየትና የቃለ ዐዋዲ ደንቡን መሠረት በማድረግ፤ ዘመኑን የዋጀ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል፣ የንብረት እና የግዥ መመሪያዎች እንዲሁም ለማኅበረ ካህናቱ ለውይይት የሚቀርብ የገዳሙ ማኅበረሰብ የሚመራበት መተዳደርያ ደንብ ሰነዶች ረቂቅ፤ የሰበካ ጉባኤው አባላት ከግል ኪሳቸው ወጪ በማድረግ በኹለት ወራት ጊዜ ውስጥ አዘጋጅተዋል፡፡

St. Marry sebeka gubae letter
የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ላይ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ሊያስከትል የሚችል አሠራር እንዲዘረጋ፣ ቆጠራውም ከባንክ ጋር በትብብር የሚሠራበትን መንገድ ወስኖ ወደ ሥራ እንዲገባ መመሪያ አዘጋጅቷል፤ በከፊልም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

የሒሳብ ማጣራት ሥራን በተመለከተም፣ ሰበካ ጉባኤው የቅድሚያ የዳሰሳ ጥናት አድርጎ የገዳሙ ሒሳብ፣ ከኹሉም ገቢዎች በአማካይ በወር ሦስት መቶ ሺሕ/300‚000/ ወይም በሰባት ወራት ላይ በተደረገው ዳሰሳ ከኹለት ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩን ተመልክቷል፡፡

የገዳሙን ንብረት በተመለከተ፣ ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ የንብረት ምዝገባ የሌላት በመኾኑ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያናችንና አገራችን ያጣችውን፣ የተዘረፈችውን ወይም ልታጣ የምትችለውን መገመት ለቅዱስነትዎ መረዳት አይከብድም፡፡

የዘረፋው ዐይነት እና ምክንያቶች ብዙ ቢኾኑም የሰበካ ጉባኤው ገንዘብ አንቀሳቃሽ ቼክ ፈራሚዎች፤ የሒሳብ ሹም፤ የቁጥጥር፣ የንብረት አስተዳደር፣ ጸሐፊው እና ገንዘብ ቤት ሓላፊዎች በዋናነት ተጠያቂ መኾናቸውን በጽሑፍ ገልጸን ቅዱስነትዎ እንዲያውቁት አድርገናል፡፡ ቅዱስነትዎም በጉዳዩ ላይ ርምጃ እንዲወስዱ፤ ለሚመለከተውም አካል አመራር እንዲሰጡ ከኹለት ጊዜ በላይ በግንባር ቀርቦ አስረድቷል፡፡ ቅዱስነትዎም አመራር እንደሚሰጥ ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡

ይኹን እንጂ ይህን ተከትሎ ከቅዱስነትዎ ጽ/ቤት ተሰጡ በተባሉ ትእዛዞች፣ ቤተ ክርስቲያንን ለችግር የዳረጉትን ኃይሎች ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የተለየ ጥበቃ እና ክብካቤ እንዲደረግላቸውና ይልቁንም ሰበካ ጉባኤውን እንዳይሠራ ማድረግ ተይዟል፤ “እናቱን በገጀራ የገደለ ጎራዴ ተሸለመ” እንዲሉ፡፡

ቅዱስነትዎ ለሰበካ ጉባኤው በግንባር ከሰጡት መመሪያ ባሻገር በተደጋጋሚ በተለያዩ ዐውደ ምሕረት እና የዜና ልሳናት/ማሰራጫዎች፤ ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሕዝብ እና መንግሥት ጋር በመኾን ለመታገል ቃል መግባትዎ ይታወቃል፡፡ በጽ/ቤትዎ በኩል ተሰጡ በተባሉ ትእዛዞች የተወሰዱትን ርምጃዎችንና የሰበካ ጉባኤው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ አለማግኘቱ ሲታይ፣ “ሙስናን እንታገላለን፤ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን” የማዘናጊያ መፈክር እንጂ በራሱ ትግል እንዳልኾነ ቅዱስነትዎ ይረዳል፡፡

ሰበካ ጉባኤው ቀድሞውንም በገዳሟ ውስጥ የሚታየውን የሙስናን መስፋፋትና የመልካም አስተዳደርን ዕጦት የመታገል ጉዳይ የሚያምንበት ቢኾንም በዚኽ ትግል ዙሪያ ቅዱስነትዎ ከሰበካ ጉባኤው ጎን እንደሚቆሙ ያረጋገጡለትን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም የገቡለትን ቃል እንደ ትልቅ አቅም አድርጎ ለመሥራት ተነሥቶ እንደነበር አንሸሽግም፡፡

ይህን አዎንታዊ እገዛም ኾነ አመራር እስከ አኹን ባለማግኘታችን ብቻ ሳይኾን ችግሩ እየተባባሰ መሔዱን ስናስተውል ማዘናችንን ለቅዱስነትዎ አንደብቅም፤ ግን ደግሞ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመኾናችን አኹንም ተስፋ ባለመቁረጥ ቅዱስነትዎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መልካም አስተዳደር የማስፈን ርምጃ ውስጥ እንዲገባ አበክረን እንማጸናለን፡፡ ለዚኽም እንደ ሰበካ ጉባኤ አካል ብቻ ሳይኾን እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንም ከጎንዎ ቆመን ለመሥራት ለማገዝ ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን፡፡

ሰበካ ጉባኤው በማኅበረ ካህናቱ፣ በማኅበረ ምእመናኑና በሰንበት ት/ቤቱ አጠቃላይ ጉባኤ ስብሰባ የተመረጠ እንደመኾኑ፣ በቃለ ዐዋዲውም መሠረት የሥራ ሪፖርቱን ማቅረብ ስለሚኖርበት ለመረጠው ጠቅላላ ጉባኤ ማቅረብ እንዲችል አመራር እንዲሰጥልን በትሕትና እንጠይቃለን፡፡

በዚህ ደብዳቤ ግልባጭ የተደረገላቸው በተለይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደረጃ መምሪያ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው እንደመኾኑ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ተገቢውን ርምጃ እንዲወስድ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር

ሙሉጌታ ቱሉ
የመ/ፓ/ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀ መንበር

ግልባጭ

 • ለብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ
 • ለብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ
 • ለመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ
 • ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
 • ለመ/ፓ/ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም ጽ/ቤት
 • ለመ/ፓ/ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም ማኅበረ ካህናት
 • ለመ/ፓ/ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም ፈለገ ሕይወት ሰንበት ት/ቤት
 • ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
 • በአ/አ ፖሊስ ኮሚሽን ለአራዳ ፖሊስ ጽ/ቤት
  አዲስ አበባ
Advertisements

2 thoughts on “አማሳኝ ሓላፊዎች በንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከለላነት ያገዱት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ: ፓትርያርኩን ወቀሰ

 1. Anonymous October 8, 2015 at 7:46 pm Reply

  ይህንን ሌባ እግዚአብሔር ለምን ዝም አለው። ቤተክህነቱን እያመሰ እስከ መቼ ይሆን የሚኖረው ።እግዚኦ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍረድላት።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: