አለቃው በምእመኑ ተቃውሞ በተባረሩበት የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን: የአስተዳደር ክፍተት ተፈጥሯል

  • ካህናቱ እና ምእመናኑ ሀገረ ስብከቱን በሰልፍ ለመጠየቅ እየመከሩ ነው
  • የአለቃው ጣልቃ ገብነት ሙዳየ ምጽዋቱ በወቅቱ እንዳይቆጠር አድርጓል
  • “ሀገረ ስብከቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ችግር ግድ እንደሌለው አሳይቶናል” /ምእመናኑ/

(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ቅጽ 03 ቁጥር 121፤ ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም.)

Debra Sina EgzeabhareAb Church
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን፤ ከአስተዳደርና ከአሠራር ጋር በተያያዙ ችግሮች ከሓላፊነታቸው ባሰናበቷቸው አለቃ ጣልቃ ገብነት መቸገራቸውን ገለጹ፤ የ“ቀድሞው አስተዳዳሪ” ሲሉ በገለጿቸው አለቃ መሰናበት ሳቢያ የተፈጠረው የአስተዳደር ክፍተትና የአሠራር ችግር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ሀገረ ስብከቱን በሰልፍ እንደሚጠይቁም አስታወቁ፡፡

የሰበካ ጉባኤ አባላቱና ምእመናኑ፣ ከትላንት በስቲያ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፤ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት ከተመረጡበት ከጥቅምት 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ያለው የደብሩ የሙዳየ ምጽዋት ገቢና ወጪ እንዲጣራ በመጠየቃቸውና አስተዳዳሪው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ወዲህ የሙዳየ ምጽዋቱ ገንዘብ ሳይቆጠር ቆይቷል፡፡

የገንዘብና ገንዘብ ነክ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ለሀገረ ስብከቱም ያቀረቧቸው አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ወቅታዊና አጥጋቢ ምላሽ ባለማግኘታቸው፣ ከነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነት በተገለጸበት ተቃውሞ አለቃውን ከሓላፊነታቸው ማሰናበታቸውን ምእመናኑ አስታውሰዋል፡፡

በአስተዳደር ክፍተቱ የተስተጓጎለው የነሐሴ ወር የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ እንዲከናወን፤ በሰበካ ጉባኤው አባላት፣ በምእመናን ተወካዮችና በካህናቱ ውትወታ ለመስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞ የሚመለከታቸው የሀገረ ስብከት፣ የካህናትና የምእመናን ወኪሎች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም በአለቃው ጣልቃ ገብነት ሳይከናወን መቅረቱን በደብዳቤአቸው ጠቅሰዋል፡፡

በዕለቱ ‘‘የቀድሞው’’ አስተዳዳሪ፣ “የቆጠራው መሪ እኔ ነኝ” በሚል በሁለት ፖሊሶች ታጅበው በደብሩ እንደተገኙ የገለጹት ምእመናኑ፤ “ሕዝቡ ይህን ባለመፍቀዱ ቆጠራው ሳይከናወን ቀርቷል፤ የሙዳየ ምጽዋቱም ቁልፍ ለግምጃ ቤቱ ሓላፊ ተሰጥቶ ወደ ቦታው እንዲመለስ አድርገናል፤ የቀድሞው አስተዳዳሪ የሕዝብን ገንዘብ አላስመረምርም ብለው በሰበካ ጉባኤ አባላቱና በሕዝበ ክርስቲያኑ ተቃውሞ ከተሰናበቱ በኋላ ሊቆጥሩና ሊያስቆጥሩ አይገባቸውም፤” ይላሉ፡፡

“ተመዝብሯል፤ ያለአግባብ ባክኗል” በሚሉት የሕዝብ ገንዘብ ዋነኛ ተጠርጣሪና ተጠያቂ የሚያደርጉትም የቀድሞውን አስተዳዳሪ በመሆኑ በእርሳቸው ላይ አመኔታ የሌላቸው በመሆኑና በተጠረጠሩበት ጉዳይም በገለልተኛ አካል ምርመራ እስከሚደረግ ድረስ ወደ ደብሩ መግባት እንደማይገባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡ በፖሊስ ታጅበው መግባታቸውን በመጥቀስም፣ ችግሩ ከተፈጠረበት ካለፈው ዓመት ግንቦት አጋማሽ ጀምሮ የከፋ ሁኔታ እንዳይፈጠር መድረክ እየፈጠረ በማወያየት የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ ለቆየው ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ማስታወቃቸውን ተናግረዋል፡፡

የሙዳየ ምጽዋቱ ገንዘብ የሚቆጠረው÷ የሀገረ ስብከቱ፣ የካህናቱና የምእመናኑ ተወካዮች ባሉበት ብቻ መሆን እንደሚገባው በአጽንዖት ገልጸው፤ ይህ ካልሆነ ግን የሕዝብ ገንዘብ ለአደጋ እንዳይጋለጥና ለአገልጋይ ካህናቱም በወቅቱ ደመወዝ ለመክፈል ሲባል፤ ከማኅበረ ካህናቱ ጋር በመመካከር ለቤተ ክርስቲያኒቱ ይበጃል ባሉት መንገድ ቆጠራውን እንደሚያከናውኑ አሳስበዋል፡፡

ምእመናኑ÷ በቃለ ዐዋዲው ደንብ የመረጧቸውን የሰበካ ጉባኤ አባላት በሕገ ወጥ መንገድ ከማገድ አልፈው ሕዝበ ክርስቲያኑን በመዋሸትና በመዝለፍ ለደብሩ የሰላም ጠንቅ ሆነዋል በሚል ያሰናበቷቸውን አስተዳዳሪ፣ “በብዙ መልኩ እየደገፈ ይገኛል” ያሉትን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትንም “ለቤተ ክርስቲያናችን ችግር ግድ የሌለው” ሲሉ ነው በደብዳቤአቸው የወቀሱት፡፡

የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ተገን በማድረግ አፍራሽ ተግባር ሲፈጽሙ እንደቆዩ የሚጠቀሱት ‘‘ተሰናባቹ’’ አስተዳዳሪ፣ ዕቅዳቸውን የሚያሳካ ሕገ ወጥ ደብዳቤ በማጻፍ በጸጥታና በፍትሕ አካላት በኩል አስገዳጅ ሁኔታ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ እንዳሉም በደብዳቤው ተጠቁሟል፡፡ በአንጻሩ የክፍለ ከተማው ፖሊስና የወረዳው ፍትሕ ጽ/ቤት ላለፉት አራት ወራት የከፋ ችግር እንዳይፈጠር የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው ምእመናኑ የሚገልጹት፡፡ የፍትሕ ጽ/ቤቱ፣ በአካባቢው የተፈጠረው ለሰላም ጠንቅ የሆነ ከፍተኛ ችግር እልባት እንዲሰጠው ለሀ/ስብከቱ በደብዳቤ እንዳሳሰበና የጽ/ቤቱ ሓላፊም የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ድረስ በመሔድ ለሥራ አስኪያጁ የጉዳዩን አስጊነት እንደገለጹላቸው ምእመናኑ አውስተዋል፡፡

ለተከሠተው የአስተዳደር ክፍተት እንዲሁም የአሠራር ችግር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ፤ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤቱን አባላትና በመንፈሳውያን ማኅበራት የታቀፉ የአጥቢያውን ነዋሪዎች በማስተባበር ሀገረ ስብከቱን በሰልፍ ለመጠየቅ መዘጋጀታቸውን ምእመናኑ አስታውቀዋል፡፡

ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ የሰንበት ት/ቤት፣ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴና መንፈሳውያን ማኅበራት የተውጣጡት ምእመናኑ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸመ ያለው ብልሹ አሠራር እንዲወገድ አስተዳዳሪውና በጽ/ቤቱ የሚገኙ ሌሎች ተባባሪዎቻቸው ተነሥተው በአርኣያነት የሚመሯቸው በጎ አባት እንዲመደቡላቸው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን የጠየቁ ሲሆን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርም ከጥቅምት 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ያለውን የደብሩ የፋይናንስ እንቅስቃሴ በገለልተኛ አካል በማስመርመር እንዲያግዛቸው በደብዳቤ እንደጠየቁ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

Advertisements

One thought on “አለቃው በምእመኑ ተቃውሞ በተባረሩበት የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን: የአስተዳደር ክፍተት ተፈጥሯል

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: