የኢትዮጵያ እና የግብጽ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እመርታ

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ርእሰ አንቀጽ፤ ፷፫ ዓመት ቁጥር ፸፤ ጳጉሜን ፳፻፯ ዓ.ም.)

collage-600x300

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ፓትርያርክ ዘግብጽ

የኢትዮጵያ እና የግብጽ ሕዝቦች÷ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ መነሻው ከኢትዮጵያ ምድር በኾነው በዓባይ ውኃ በጋራ ሲጠቀሙ የኖሩና የሚኖሩ ናቸው፡፡ ስለኾነም ይህ በተፈጥሮ ጸጋ የታደላቸው የማኅበራዊ ኑሮ ትስስር ግራም ነፈሰ ቀኝ ዘመን ሳይገድበው እስከ ኅልፈተ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እንደሚዘልቅ ጥርጥር የለውም፡፡ ለአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዘመናት ያህል ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በግብፃውያን አበው ሲባረኩና መንፈሳዊውን ዕሴት ኹሉ ሲያገኙ መኖራቸውም የኹለቱ ሕዝቦች ሃይማኖታዊ ግንኙነት ዋና መሠረት ነው፡፡

ከዚኽም ሌላ፣ በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የኹለቱን አህጉር ሕዝቦች እና አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ይበልጥ ያቀራረበና ያጠናከረ ነው፡፡

የመጨረሻውና የግንኙነታቸው ፍሬያማ ውጤት ደግሞ፤ በጉዳዩ በወቅቱ የነበሩት የኹለቱ አገሮች መንግሥታት መሪዎችም ተጨምረውበት ከብዙ ውይይት እና ምክክር በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል በመደረጉ በ፲፱፻፳፩ እና በ፲፱፻፳፪ ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን አበው በ፲፱ኛው የእስክንድርያ ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሐንስ አንብሮተ እድ መሾማቸው ነው፡፡

በቀጣዩም በ፲፱፻፵ ዓ.ም. የተመረጡ አምስት ኢትዮጵያውያን አበው ካይሮ ወርደው በዚያን ጊዜ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ተቀብተው ሢመተ ጵጵስና መቀበላቸው ግንኙነታቸውን አጠናክሮታል፡፡

በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኾነው በእስክንድርያው ፖፕና በመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ በሚመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሥርዐተ ጸሎት መሾማቸውም የኹለቱን አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት የበለጠ ሊያጠናክረው ችሏል፡፡

አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም.፣ በፖፕ አቡነ ሲኖዳ ሣልሣዊ ጋባዥነት ግብጽን በይፋ የጎበኙ ሲኾን በአጸፋውም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋባዥነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ በ፳፻ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረጋቸው ተቋርጦ የነበረው ዘመናትን ያስቆጠረ የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ግንኙነት በተደረገው የጉብኝት ልውውጥ እንደገና ሊጠናከር ችሏል፡፡ ኹለቱም አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የትብብር ፕሮቶኮል ተፈራርመዋል፡፡

በተፈጠረው የተጠናከረ ግንኙነትም፤ ፻፲፰ኛው የእስክንድርያ ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ባደረጉላቸው የወዳጅነት ጥሪ መሠረት ስድስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በ፳፻፯ ዓ.ም. ከጥር ፩-፯ ቀን ድረስ በግብጽ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የኹለቱም አህጉር ሕዝቦች ከቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ቀጥሎ የክርስትና ሃይማኖትን በመቀበል ረገድ ቀደምት እንደመኾናቸው መጠን ኹለቱም የሃይማኖት መሪዎች፣ የኹለቱን አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ካለፈው በበለጠ አጠናክረው ለመላው የዓለም ኅብረተሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና የተጠሩበትን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ በሰፊው ተወያይተው በበርካታ መንፈሳዊ የሥራ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የጋራ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ይህም የግንኙነታቸው እመርታ የደረሰበትን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ገጽታ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አይ.ኤስ.አይ.ኤስ በተባለው ፀረ ክርስትና ቡድን፣ በክርስትና ሕይወታቸው ምክንያት ለተሠዉት ወጣት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች፣ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ርዳታ ከማድረጓም በላይ ልኡካኗን ልካ የሟች ቤተሰቦች እንዲጽናኑ አድርጋለች፡፡ ቀደም ሲልም በተጠቀሰው ፀረ ክርስትና ቡድን በሊቢያ ለተሠዉት ግብጻውያንና ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የኹለቱም አኃት አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ክርስቲያኖች በመኾናቸው ብቻ የተሠዉት የግራ ቀኙ ወገኖች ሰማዕታት እንዲባሉ መወሰኑ በኹለቱም አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን አንድነት የሚያሳይና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር ነው፡፡

አኹም ደግሞ በታሪካዊው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ በመገኘት ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጎበኙላቸው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ የእስክንድርያን ፖፕና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ዳግማዊን ስለጋበዟቸው ለኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት መጠናከር ታላቅ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል÷ ንግሥት ዕሌኒ ድኅረ ልደተ ክርስቶስ በ፫፳፻፯ ዓ.ም. መጋቢት ፲ ቀን የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስቆፍራ ያስወጣችበትን ዕለት በማዘከር የሚከበር ነው፡፡ ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷ እና ዓለም አቀፋዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም፤ የክርስትና እምነት የሕዝብ እና የመንግሥት ሃይማኖት ኾኖ ከታወጀበት ከ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በብሔራዊ ደረጃ ስታከብራቸው ከኖሩት የሃይማኖት በዓላትም አንዱ ነው፡፡   

በዚኽ መልካም አጋጣሚም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ፣ ታሪካዊው የመስቀል ደመራ በዓል፣ ከመላው ዓለም በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ በታላቅ ክብር በሰፊው እንደሚከበር በበዓለ ሢመታቸው ማግሥት በዓይናቸው አይተው ለመረዳት፣ የመጀመሪያው ዕድለኛ ፓትርያርክ ናቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ከበዓሉ መልስ የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በሚያደርጉት የጋራ ውይይት የተጀመረው አዲስ ግንኙነት የበለጠ ጥንካሬን እንደሚያገኝም ይታመናል፡፡

ይህ ታሪካዊ በዓል በመላው ኢትዮጵያ ዳር እስከ ዳር በታላቅ መንፈሳዊ ስሜትና ዝግጅት ሲከበር ዘመናትን ያስቆጠረ መኾኑ ይታወቃል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የአገሪቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች፣ የውጭ መንግሥታት አምባሳደሮች፣ እንዲኹም በርካታ አገር ጎብኚዎችና ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሚገኙበት በየዓመቱ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ባለው መልኩ በታላቅ ክብርና በከፍተኛ ድምቀት በብሔራዊ ደረጃ የሚከበር መኾኑን መላው ዓለም ያውቀዋል፡፡

የዘንድሮውን የመስቀል በዓል ከምንጊዜውም ለየት የሚያደርገው ግን፣ የሦስቱ ሀገራት ማለት የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን መንግሥታት መሪዎች በዓባይ ወንዝ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከመግባባት ላይ በደረሱበትና የመስቀል በዓል በዩኔስኮ በቅርስነት በተመዘገበበት ማግሥት መከበሩ ነው፡፡ በተለይም የእስክንድርያው ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ በክብር እንግድነት በተገኙበት መከበሩ ለታሪካዊ በዓልነቱ ተጨማሪ ታሪክ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ባለፈው ባደረጉት የጉብኝቱ ልውውጥ ከሃይማኖት ጉዳዮች ባሻገር በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲወያዩ ኢትዮጵያ እና ግብጽ እግዚአብሔር በዓባይ ወንዝ በጋራ እንዲጠቀሙ አድርጎ አያይዞ የፈጠራቸው ሀገራት በመኾናቸው በዓባይ ውኃ በጋራ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳላቸው፣ እግዚአብሔር በተፈጥሮ አንድ ያደረገውንም ማንም ሊለየው እንደማይችል አሥምረውበታል፡፡

ቀደም ሲልም የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ስለ ግንኙነታቸው መጠናከር ባደረጉት የጋራ ውይይት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ዳግማዊ፣ ‹‹እኛ የግብጽ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ አንድ ብርጭቆ ውኃ በጠጣን ቁጥር ኢትዮጵያን እናስታውሳታለን›› ብለው የተናገሩት ቃል መሠረታዊ ግንኙነታቸውንና ሲተሳሰቡ የኖሩ መኾናቸውን በጉልሕ ያስረዳል፡፡

አኹንም ከመስቀል በዓል መልስ ኹለቱ የሃይማኖት መሪዎች የሚያደርጉት ሲኖዶሳዊ ውይይት፣ በሃይማኖት ጉዳዮች ዙሪያ ብቻ የሚያነጣጥር ሳይኾን በኹለቱ አገሮች መካከል ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነት ኹሉ ሊያዳብረው ስለሚችል ለታሪካዊው የመስቀል በዓል አከባበርና ለኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የጋራ ውይይት ደኅንነት ቤተ ክርስቲያን፣ ሕዝብ እና መንግሥት ከፍተኛ ግምት ሊሰጡትና የጋራ ጥንቃቄ ሊያደርጉበት ይገባቸዋል፡፡

Advertisements

One thought on “የኢትዮጵያ እና የግብጽ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እመርታ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: