ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ: ዘመን ለሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ እንዲኾነን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል

His Holines pat Abune Mathias at Zeitun Mariam

የዘመን ሀብት ባይኖር ሰው ምድራዊ ሕይወቱን በትክክል መምራት አይችልም ነበር፡፡ ምድራውያን ፍጥረታት በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ የሰው ልጅ ሥርዐት ባለውና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በዕቅድ ሥራውን በማከናወን ሕይወቱን በትክክል መምራት ይችል ዘንድ ሀብተ ዘመን ያስፈልገዋል፡፡

ዘመን ለተግባር ከሚያበረክተው አገልግሎት በተጨማሪ በትምህርት ሰጪነቱ እጅግ አስፈላጊ በመኾኑ ያለፈውን ዘመን እንድናስታውስ እንጂ እንዳንረሳ፣ የልጅ ልጅ ዘመናትን አስብ ብሎ እግዚአብሔር ይነግረናል፤ ምክንያቱም ለወደፊቱ የተሻለ ሥራ መሥራት የምንችለው ካለፈው ዘመን ትምህርት ቀስመን፣ ልምድ እና ተሞክሮ ወስደን ስለኾነ ነው፤ ሥራን ከዘመን ለይቶ ወይም ነጥሎ ማስቀመጥ በፍጹም አይቻልምና፡፡

ስለኾነም ዘመን ለአጠቃላዩ ሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ ኾኖ እንዲያገለግለን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና አዲሱን ዘመን ሲቀበል፣ ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በበለጸገ የሥራ ባህል በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

የዘመናት ፈጣሪ አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ እንኳን ለአዲሱ የ፳፻፰ ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችኹ!!

በምስሉ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በግብጽ የአምስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ በዘይቱን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴ ላይ እንዳሉ ይታያሉ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ካልዕ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የእስክንድርያ ፻፲፰ኛ ፖፕ እና ፓትርያርክ ዘመንበረ ማርቆስ በአጸፋው፣ ከኹለት ሳምንት በኋላ የመስቀል ደመራን በዓል ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ፡፡

የኮፕት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዓመተ ሰማዕታት (anno martyrum or AM)፣ ከኢትዮጵያውያን ዐውደ ዓመት ጋር የዘመን መለወጫ በዓል እንደሚያከብሩ ይታወቃል፡፡ «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው፤ እርሱም የግብጽ እና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመርያ ነው፡፡ የዚኽ ወር ቀኑ እና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡» /ስንክሳር ዘመስከረም/


ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠር እና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅ እና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ፤
  • በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤
  • የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ፤
    ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የዘመናት ፈጣሪ የኾነው አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ እንኳን ለአዲሱ የ፳፻፰ ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችኹ!!

‹‹ወኀሊ ዓመተ ለትውልደ ትውልድ፤ የብዙ ትውልድን ዓመታት አስብ››(ዘዳ. ፴፪፡፯)፡፡

የኹሉም አስገኝና ፈጣሪ የኾነው እግዚአብሔር አምላካችን ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንድ ስንኳ ጥቅም የለሽ የሆነ ፍጥረት አይገኝም፡፡ ፍጥረታት ኹሉ በእርሱ ዘንድ ውብና የየራሳቸው ዓላማ እና ተግባር ያላቸው ናቸው (ዘፍ.፩፡፳፭)፡፡ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት በፍጡር ዓቅም ሙሉ በሙሉ ተቆጥረው የሚዘለቁ አይደሉም፡፡

ከጥቂቶቹ በስተቀር ኹሉንም በዐይነ ፍጡራን ማየት ስለማይቻል ቅዱስ መጽሐፍ ፍጡራንን ጠቅለል አድርጎ በአጭር ቃል ሲገልጽ፣ ‹‹በሰማይ እና በምድር ያሉት፣ የሚታዩት እና የማይታዩት›› ይላቸዋል፡፡ (ቈላ. ፩፡፲፭)፡፡ በምድር ላይ እያሉ ከማይታዩት መካከል አንዱ ዘመን ወይም ጊዜ ነው፤ ጊዜ በድርጊት ከሚታወቅ በቀር በዐይን የሚታይ ግዙፍ አካል ወይም ልዩ ቀለም ያለው ፍጡር አይደለም፡፡

ይኹን እንጂ ባለመታየቱ ብቻ የለም ብሎ መደምደም ወይም መናገር አይቻልም፤ ምክንያቱም ከድቁቅ ስፍረ ጊዜ አንሥቶ ሰዓታትን በቀናት፣ ቀናትን በሳምንታት፣ ሳምንታትን በወራት፣ ወራትን በዓመታት ከዚያም በልዩ ልዩ አዕዋዳት እየጠቀለለ ሲያሽከረክር በተግባር እናያለንና ነው፡፡ ዘመን የድርጊት መሣሪያ ስለኾነ በአንድ ወቅት በተፈጸመ መልካም ወይም መጥፎ ነገር ይገለጻል፡፡ ከዚኽም የተነሣ ዘመኑ መልካም ነው ወይም መጥፎ ነው ሲባል እንሰማለን፡፡

ይኹንና የእኛ መሠረታዊ ጉዳይ ሊኾን የሚገባው፣ የዘመን መታየትና አለመታየት ሳይኾን ለፍጡራን ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ግንዛቤ ወስደን ተጠቃሚ ለመኾን መንቀሳቀሱ ላይ ነው፡፡ ዘመን ከዓለም መፈጠር በፊት ያልነበረ ከዓለም ጋር አብሮ የተፈጠረ፣ በሰማይ የሌለና ለምድራውያን ፍጡራን ብቻ አገልግሎት ሊሰጥ የተፈጠረ ነው (ዘፍ.፩፡፲፬)፡፡

የዘመን ሀብት ባይኖር ሰው ምድራዊ ሕይወቱን በትክክል መምራት አይችልም ነበር፡፡ በመኾኑም ምድራውያን ፍጥረታት በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ የሰው ልጅ ሥርዐት ባለውና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በዕቅድ ሥራውን በማከናወን ሕይወቱን በትክክል መምራት ይችል ዘንድ ሀብተ ዘመን ያስፈልገዋል፡፡

ዘመን ለተግባር ከሚያበረክተው አገልግሎት በተጨማሪ በትምህርት ሰጪነቱ እጅግ አስፈላጊ በመኾኑ ያለፈውን ዘመን እንድናስታውስ እንጂ እንዳንረሳ፣ የልጅ ልጅ ዘመናትን አስብ ብሎ እግዚአብሔር ይነግረናል፤ ምክንያቱም ለወደፊቱ የተሻለ ሥራ መሥራት የምንችለው ካለፈው ዘመን ትምህርት ቀስመን፣ ልምድ እና ተሞክሮ ወስደን ስለኾነ ነው፤ ሥራን ከዘመን ለይቶ ወይም ነጥሎ ማስቀመጥ በፍጹም አይቻልምና፡፡

ስለኾነም ዘመን ለአጠቃላዩ ሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ ኾኖ እንዲያገለግለን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!

ሀገራችን ኢትዮጵያ ኹሉንም የተፈጥሮ ሀብት ተሟልቶ የተሰጣት፣ ድንቅ እና ውብ ሀገር ናት፡፡
ምድራዊት ገነት በኾነች በዚኽች ሀገር ተቀምጠን ስለ ድህነት ማውራት ከእንግዲኽ ወዲኽ እንዲያከትም ኹሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መረባረብ አለበት፤ ልማታችንን በአስተማማኝ ደረጃ ዘላቂ ለማድረግ የድህነታችን ምሥጢር የት እንዳለ በውል ማወቁ ይጠቅማል፡፡ እንደ እውነቱ ከኾነ የድህነታችን ምሥጢር ተደብቆ ያለው የሥራ ባህልን አዳብሮ፣ የጊዜን ጥቅም ዐውቆና አንዲት ደቂቃ ስንኳ ሳያባክን በሀገሩ ውስጥ ሠርቶ ለመለወጥ ያለን ተነሣሽነት አናሳ መኾኑ ላይ ነው፡፡

በተለይም ወጣቱ ትውልድ ይህን ተገንዝቦ መሠረታዊ የአስተሳሰብ እና በጊዜ ሠርቶ የመለወጥ ባህል ሊያጎለብት ይገባል፡፡ ይህን ክፍተት በውል ስናውቅና በሥራ ስንታገለው ድህነትን ከሥር መሠረቱ ነቅለን መጣል እንችላል፡፡ ዛሬ አደጉ በለጸጉ ተብሎ የሚነገርላቸው ሀብታም ሀገሮች አብዛኛዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለእርሻ እና ለልዩ ልዩ አዝርዕት የተመቸ ለም መሬት፤ ለእንስሳ ርባታ እና ለሰው ኑሮ የተመቸ አየር እና ንጹሕ ውኃ፣ በልዩ ልዩ ማዕድን የተሞላ ነገር ግን ገና ያልተፈተሸ ድንግል መሬት ኖሮአቸው ሳይኾን፣ ያላቸውን ውሱን ሀብት በበለጸገ የሥራ ባህል ማለትም ሥራን ሳያማርጡ፣ ጊዜን በከንቱ ሳያባክኑ ያለዕረፍት ሌት ተቀን በመሥራታቸው ያገኙት ጸጋ እንደኾነ ማስተዋል አለብን፡፡

በመሆኑም ኅብረተሰባችን በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ፤ አዲሱን ዘመን ሲቀበል አዲሱን ዓመት ከሀገራችን የሕዳሴ መርሐ ግብር ጋር በማቀናጀትና ጠንክሮ በመሥራት ግዙፍ የኾነ የልማት እና የዕድገት ስኬት ለማረጋገጥ ከዳር እስከ ዳር ተባብሮ እንዲንቀሳቀስ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

Advertisements

2 thoughts on “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ: ዘመን ለሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ እንዲኾነን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል

  1. Yared Sirak September 14, 2015 at 6:04 am Reply

    መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: