አንድ ሺሕ ልኡካን ዛሬ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር ይወያያሉ፤“ከዋነኛ ትኩረቱ የመልካም አስተዳደር ችግር በመነሣት ርምጃ ይወሰዳል”/ሚኒስትሩ/

  • የዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ውይይቱን በቡድናዊ አካሔድ የመቆጣጠር ሙከራ ተነቅቶበታል
  • አማሳኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በመወንጀል መሸፈን እንደማይችሉ ሚኒስትሩ አሳስበዋቸዋል
  • “ምኑን ነው የፈራችሁት? የሙዳየ ምጽዋቱን ሕዝብ ሰምቶታል” በማለት የነገር ጥፊ አልሰዋቸዋል
  • “ስለ መልካም አስተዳደር ከሚደረሰው መግባባት በመነሣት መንግሥት ርምጃ ይወስዳል”

ከአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ከማኅበረ ካህናት፣ ከሰባክያነ ወንጌል፣ ከሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች እና የሀገረ ስብከቱ አንድነት አመራሮች ጋር በተናጠል ሲወያይ የቆየው፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት የማጠቃለያ ውይይት ያካሒዳል፡፡

የመርሐ ግብሩን አስተባባሪዎች ጨምሮ ከ800 – 1000 ያኽል ተወካዮች በውይይቱ እንደሚሳተፉ ተገልጧል፡፡ ከተሳታፊዎቹ የሚበዙት ከ169 የሀገረ ስብከቱ ገዳማት እና አድባራት የተውጣጡ አምስት፣ አምስት ልኡካን ሲኾኑ እነርሱም አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች እና የአንድነቱ ተወካዮች የሚገኙበት ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ሓላፊዎችም በውይይቱ እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል፡፡

ልኡካኑ፣ “ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል” በሚል በሚኒስቴሩ የተለዩ ናቸው ተብሏል፡፡ ይኹንና የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት እና የምእመናን ተወካዮች ቀጥተኛ ተሳታፊ አለመኾናቸው ጥያቄ አስነሥቷል፡፡ የካህናት ተወካዮቹም “የንስሐ ልጆች ያላቸው” ከሚል በስተቀር በአመራረጣቸው በርግጥም ካህናቱን ሊወክሉ የሚችሉ ስለመኾናቸው አለመታወቁ ተመልክቷል፡፡

State Minister Ato Mulugeta Wuletaw and Minister Dr Shiferaw
ከዛሬ ነሐሴ 29 ቀን ጠዋት 2፡00 ጀምሮ ለኹለት ቀናት በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የስብሰባ አዳራሽ የሚካሒደው
ውይይት፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ ጭብጦች የመወያያ ጽሑፎች ይቀርቡበታል፡፡ እነርሱም፡- በሰላም አብሮ የመኖር የቆየ ወርቃማ ተሞክሯችንን እንዴት ማስቀጠል እንችላለን? አክራሪነት እና ጽንፈኝነት በውስጣችን አለ ወይ? እንዴትስ መታገል እንችላለን? የቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ሥርዐት የሚሉ ናቸው፡፡ መድረኩ÷ ባለፉት ጊዜያት በተናጠል ውይይት የተካሔደባቸውን ጉዳዮች በጋራ መግባባት በማጠቃለል እና ሰፊ ጥናት በማድረግ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

የውይይት መርሐ ግብሩን ለማመቻቸት እና አቅጣጫ ለማስያዝ፣ ትላንት ከቀትር በኋላ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና በራሳቸው የመረጧቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሓላፊዎች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡

የማጠቃለያ መድረኩ፣ 1000 ያኽል ተሳታፊ ልኡካኑ በ10 ቡድኖች ተከፍለው በቡድን የሚወያዩበት መርሐ ግብርም እንዳለው ታውቋል፡፡

የውይይት ሒደቱንና የጋራ አቋሞችን ተቆጣጥረው ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያሰቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በትላንቱ የቅድመ ዝግጅት ምክክር፣ እነኃይሌ ኣብርሃንና ዘካርያስ ሐዲስን የመሳሰሉ አማሳኞችን በአካል ይዘው በመቅረብ ጭምር የቡድን ውይይቱ መሪዎች እንዲኾኑ ሐሳብ ከማቅረብ አልፎ ደልዳይም ኾነው ታይተዋል፡፡

“የውይይት መድረኩን የሚበጠብጡ ይኖራሉ፤ ከመሥመር እንዳይወጣ ምን እናድርግ?” በሚል ሰበብ ሚናቸውን ከተሳታፊነት በላይ አድርገው የተወካዮችን ማንነት እና አገባብ ለመቆጣጠር ከጅሏቸዋል የተባሉት አማሳኞቹ፣ “በኛ ተጠርቶ የሚበጠብጥ የለም፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከችግር የምትወጣበት ሐሳብ ያለው ኹሉ ሳይፈራ መናገር ይችላል፤” የሚል ምላሽ ከሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሚኒስትሩ አያይዘውም “ምኑን ነው የፈራችሁት? የሙዳየ ምጽዋቱን እንደኾነ ሕዝብ ሰምቶታል” በማለት የነገር ጥፊ አልሰዋቸዋል፡፡

የቡድን ተወያዮች(በተለይም በአማሳኞቹ አለቆች የቅጣት፣ የእገዳ እና የዝውውር ተጽዕኖ የሚደረግባቸው ካህናት) ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይሰጡ ለማሸማቀቅ የታሰበበት ይኸው ስልት፣ የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚኾን በሚጠበቀው የሙስና ጉዳይም ከአለቆቹ ተጠርጣሪዎች እንዳሉበት በመጠቆም ተቀባይነት እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡

ሚኒስትሩም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማሳሰቢያ ነው የሰጡት፡፡ አማሳኞቹ ስለ አክራሪነት እና ጽንፈኝነት በሚደረገው ውይይት እንደለመዱት ማኅበረ ቅዱሳንን ወንጅለው ራሳቸውን በመሸፈን የውይይቱን ሒደት እና የጋራ አቋም ለመቆጣጠር ተዘጋጅተው ከኾነ፣ “ጊዜአችኹን አታጥፉ” ብለዋቸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ፣ ዋናው የውይይቱ ትኩረት በቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ እንደሚኾንና መንግሥት በቀጣይ የሚወስዳቸው ርምጃዎችም በዚኽ ዋነኛ ነጥብ ላይ በሚያዘው የጉባኤው የጋራ መግባባት ላይ እንደሚመሠረት ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ጥናታዊ ሪፖርት፣ አስከትሎ ባመጣው የአማሳኞቹ የሕግ ተጠያቂነት ጉዳይ ቋሚ ሲኖዶሱ የጋራ አቋም ላይ እንዳይደርስ ብፁዓን አባቶችን በተለያዩ መንገዶች ለመከፋፈል እየጣሩ ለሚገኙትና የቤተ ክርስቲያንን ዐበይት ችግሮች ውጫዊ ለሚያደርጉት እነየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ኃይሌ ኣብርሃ እና መሰሎቻቸው፣ ይህ ዐይነቱ የሚኒስትሩ አቋም በእጅጉ አስከፍቷቸዋል፤ አስደንግጧቸዋልም!!
EOTC SSS
በአንጻሩ በፀረ ሙስና እና በፀረ ኑፋቄ የተጋጋለ ንቅናቄ ለዕቅበተ እምነት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለፍትሕ መስፈን የቆሙ የለውጥ ኃይሎች በጠንካራ የአስተሳሰብ፣ የመረጃ እና የሞራል የበላይነት ቁመና ላይ ይገኛሉ፤ አማሳኞች እና የለውጥ ኃይሎች በትይዩ በሚቆሙበት መድረክ÷ ወይ አማሳኝነት ወይ ተቋማዊ ለውጥ ያሸንፋል፡፡


የሃይማኖት ተቋሞቻችን የተመሠረቱበት ዘመናት እንደተጠበቀ ኾኖ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ሥርዐታቸው፤ ለተከታዩ ሕዝብ ያላቸው ግልጸኝነት እና የተጠያቂነት ጉድለት ለኪራይ ሰብሳቢነት ከፍተኛ ተጋላጭነትን እየፈጠረ የሚገኝ ጉዳይ ነው፡፡ መሪ ተቋማቱ በሕዝብ ዘንድ እምነት እንዲያጡና ከተለያዩ ጫፎች ተነሥተው ተቋሙ እንዲወገዝ ምክንያት የሚኾነው ብልሹ አሠራሮች የሚፈጥሩት የተከማቸ ቅሬታ ነው፡፡

በተለያዩ መንገዶች የሚገኘው ሀብት እና ንብረት ለኪራይ ሰብሳቢነት በስፋት የሚጋለጥበት፣ የሰው ኃይል አስተዳደር በዘመድ አዝማድ፣ በጉቦ እየኾነ የሥራ ብቃት በሌላቸው ሰዎች የሚሠራበት፣ በአጠቃላይ ሀብት እና ንብረት የት እና በማን እጅ እንደሚገኝ የማይታወቅበት ነው፡፡

የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ተከታዮች የሚተቹበት እና አስተያየት የሚሰጡበት መንገድ፤ የሃይማኖቶቹ የልማት ሥራም ይኹን ሌላ ለተከታዩ ቀርቦ ግልጽ ውይይት የሚደረግበት፤ የግልጸኝነት እና የተጠያቂነት አሠራር የሚባል ጉዳይ የተተከለ አይደለም፡፡

ስለዚኽ በውስጣቸው የሥልጣን ሽኩቻ፣ የሙስና እና የአስተዳደር በደሎች ይህንኑ ለመሸፈንና ለመቃወም በሚደረግ ትግል የሚፈጠር ቀውስ ተጋላጭነትን ያስከተለ ነባራዊ ኹኔታ ኾኗል፡፡

አክራሪነት እና ጽንፈኝነት ከሕገ መንግሥታችን ጋር ያለው የማይታረቅ መሠረታዊ ቅራኔና መፍትሔው፤ ገጽ 84 – 85

Advertisements

2 thoughts on “አንድ ሺሕ ልኡካን ዛሬ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር ይወያያሉ፤“ከዋነኛ ትኩረቱ የመልካም አስተዳደር ችግር በመነሣት ርምጃ ይወሰዳል”/ሚኒስትሩ/

  1. Asrate Gebreal September 4, 2015 at 12:21 pm Reply

    Amasagnoche Ye Kirstosin Bete Kirstian Awardachihualna, Bezihu Mekniyat Simachihu Yelem!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: