በአ/አበባ ሀ/ስብከት: ሰበካ ጉባኤያት በአማሳኝ አለቆች መታገዳቸው አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ ነው፤ “ሚና አልባ እየተደረጉ ነው”

A.A Dio Head Office

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን እና የምእመናንን ፍልሰት የሚያባብስ እንደኾነ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እና በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባዎች በአጽንዖት ተገልጧል፤ መፍትሔውም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዐት እና ትውፊት በመጠበቅ የመልካም አስተዳደርን መርሖዎች ተግቶ እና ነቅቶ ተግባራዊ ማድረግ እንደኾነ በጉባኤያቱ የውሳኔ መግለጫዎች በጉልሕ ተቀምጧል፡፡

ጉባኤተኞች፣ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ በማበልጸግ እና የሙስና ችግርን በማስወገድ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር እና ልዕልና ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚነሡ በጋራ አቋሞቻቸው ያመለከቱ ሲኾን የጥቅምት 2007 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ውሳኔውን አጽድቆ የዓመቱ የሥራ መመሪያ ኾኖ እንዲሠራበት ለመላው አህጉረ ስብከት አስተላልፏል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን አንቀጽ ፲፩ እንደተዘረዘረው፣ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር በዋናነት የሚከተላቸው ዐሥር የመልካም አስተዳደር መርሖዎች፡- መንፈሳዊነት፣ ፍትሐዊነት፣ ሕጋዊነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነት፣ ተደራሽነት፣ ምላሽ ሰጪነት፣ ምሥጢር ጠባቂነት እና ታማኝነት ናቸው፡፡

በሕጉ መሠረት ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል ደረጃው በሚፈቅደለት መጠን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚከናወኑ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት አለው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር አካላት የሚተላለፉትን ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ ትእዛዞች እና ውሳኔዎች የማክበር፤ ራሱን ከሙስናዊ አሠራር ነፃ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን በመንፈሳዊነት፣ በቅንነት እና በታማኝነት የማገልገል ግዴታዎች አሉበት፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከላይ ወደ ታች በተዘረጋው የሥልጣን መዋቅር፣ አብዛኛው የአስተዳደር ሥራ እና የሀብት ምንጭ ያለው በአጥቢያ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በኩል እንደኾነ የታወቀ ነው፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና አስተዳደር ለማጠናከር የወጣው ቃለ ዐዋዲ፣ በመሬት ሥሪት ላይ ተመሥርቶ የቆየው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በካህናት እና በምእመናን ኅብረት የተደራጀበት ነው፡፡ ይኸውም በሀብት እና በንብረት በኩል ራሷን በማስቻል፤ አስተዳደሯን በማሻሻል ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለማስፋፋት እና ለማጠናከር የታሰበበት ነው፡፡

በሳንቲም ደረጃ አስተዋፅኦ በመሰብሰብ የተጀመረው የሰበካ ጉባኤ ገቢ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለማካበት አስችሏል፡፡ ሰበካ ጉባኤ፣ ይህ የእግዚአብሔር ገንዘብ በተገቢው የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት ለሚገባው አገልግሎት እና ልማት እንዲውል የማድረግ ሓላፊነት አለበት፡፡ አገልጋዮቿን ለሐዋርያዊ ተግባር ለማደራጀት እና ችሎታቸውንና ኑሯቸውን ለማሻሻል፤ ምእመናንን ለማብዛት እና በሃይማኖት ለማጽናት ተግቶ መሥራት ይኖርበታል፡፡

የፋይናንስ አቅምን በማሳደግ የተፈጠረው አቅም የማይናቅ ቢኾንም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳሉት፣ “ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ከሚውል ይልቅ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት እንደሚበዛ ፍጹም የማይካድ ሐቅ ነው፡፡” በምእመናን አስተዋፅኦ የተገኘውን የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እና ንብረት ለሚገባው አገልግሎት እና ልማት ለማዋል የሚደረገው ጥረት ሰበካ ጉባኤያቱን ከአባልነት እና ከአገልግሎት እስከ መታገድ እያደረሳቸው ይገኛል፡፡ የገንዘቡን ያኽል ምእመናንን በመጠበቁ እና በማትረፉ በኩል ብዙ እንዳልተሠራና ይልቁንም በልማት ስም ገንዘቡን የሚያባክኑ አማሳኝ ሓላፊዎች፣ ሀብቷንና ንብረቷን ለምዝበራ እንዳጋለጡት በገሐድ እየተረጋገጠ መጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት እና ገዳማት፣ የብዙ ባለሀብት እና ንብረት ባለቤቶች እንደ መኾናቸው የሀገረ ስብከቱ የገቢ ዕድገት በየጊዜው እንደተሻሻለ በሪፖርቶች ቢሰማም፤ እንደ አህጉረ ስብከት ማዕከልነቱ፣ በፋይናንስ አያያዝ እና በመልካም አስተዳደር በሞዴልነት የሚጠቀስ አልኾነም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጀምሮ በአድባራቱ እና በገዳማቱ የሚታየው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሰበካ ጉባኤያት በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ እንዲደራጁ እና እንዲሠሩ አለማድረግ፣ የፐርሰንት ገቢው በየደረጃው በቅጽ ተሞልቶ በጊዜው አለመቅረብ በአጠቃላይ ከሙስና ጋር የተያያዘ ልዩ ልዩ ችግር የቅዱስ ሲኖዶሱ የማያዳግም ሥር ነቀል ውሳኔ እንደሚያሻው በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባዎች ሳይቀር ተጠይቋል፡፡

ጥያቄውን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት እና ትውፊት ጋር በተጣጣመ የመዋቅር፣ የአደረጃጀት እና የአሠራር መመሪያ የመለሰ ጥናት ቢዘጋጅም ትግበራው በአማሳኞች ተንኰል ተሰናክሏል፡፡ በመልካም አስተዳደር እና በፍትሕ አሰጣጥ÷ ከሙስና የጸዳ፣ ግልጽነት ያለው፣ ፍትሐዊ የኾነና በኹሉ መልኩ የመልካም ምሳሌ መነሻ እና መድረሻ የኾነ ተቋም በአርኣያነት የመገንባት ጥረቱ በአማሳኞች እየተፈተነ ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤያት ሕጋዊ እና ፍትሐዊ አመራር የሚሰጥባቸው የአስተዳደር ማእከላት ሳይኾኑ ለአማሳኞች እኩይ ፈቃድ የሚታዘዙ አሻንጉሊቶች ለማድረግ በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ድጋፍ ጭምር በሚወሰድባቸው የማዳከም እና የማፍረስ ርምጃ ሳቢያ በበርካታ አጥቢያዎች የተፈጠረው ውስጣዊ ውጥረትም አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ መጥቷል፡፡

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፭ ቁጥር ፰፻፲፬፤ ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

 • በደ/ገሊላ ዐማኑኤል እና በደ/ከዋክብት አቡነ አረጋዊ፤ አስተዳደሩ እና ሰበካ ጉባኤያት ተፋጠዋል
 • በደ/ገሊላ ቅ/ዐማኑኤል ካቴድራል ምእመናኑ፣ ለአስተዳዳሪው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል
 • በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ፣ ሰበካ ጉባኤውን ያገዱት ብልሹ አስተዳዳሪ በምእመኑ ተባረዋል
  ሀገረ ስብከቱ፣ በታገደው ሰበካ ጉባኤ ምትክ የክፍለ ከተማውን ሥራ አስኪያጅ ፈራሚ አድርጓል
 • ሰበካ ጉባኤው በታገደበት ብሥራተ ገብርኤል፤ የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች ሙዳየ ምጽዋት ቆጥረዋል
  በመ/ፓትርያርኩ ቅ/ማርያም፤ ሕጹጸ ሃይማኖቱ ቄሰ ገበዝ ሰ/ጉባኤውን ተክተው እየፈረሙ ነው
 • በመንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም፣ በአስተዳደሩ አማሳኝነት ሰበካ ጉባኤው ራሱን አግልሏል
  በመዝገበ ምሕረት ቅ/ፋኑኤል፣ ምእመናን አስተዋፅኦ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ አስጠንቅቀዋል

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በርካታ አድባራት፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት በበላይነት ለመምራት እና ለመቆጣጠር ሥልጣንና ተግባር ያላቸው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ አባላት፣ በሙስና እና ብልሹ አሠራር በሚታሙ የአስተዳደር ሓላፊዎች መታገዳቸው አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ መምጣቱ ተገለጸ፤ ሀገረ ስብከቱም ተጣርተው በሚቀርቡለት ሪፖርቶች ላይ አፋጣኝ ውሳኔ አለመስጠቱ “ትክክለኛ መፍትሔ የማግኘት ተስፋችንን አዳክሞታል፤” ይላሉ ምእመናኑ፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ለአዲስ አድማስ የደረሱ ጥቆማዎች እንደሚያስረዱት፤ የሰበካ ጉባኤያቱ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ከሓላፊነት ይታገዳሉ አልያም በአስተዳደር ተግባር የመሳተፍ ድርሻቸው ተዳክሞ ደመወዝ እና ሥራ ማስኬጃ በመፈረም ብቻ ተወስኗል፡፡

የአስተዳደር ሓላፊዎች ከጥፋታቸው እንዲታረሙ የእርምት ሐሳብ የሚያነሡ የማኅበረ ካህናት ተወካዮች፤ በሌለ ልማት “የልማት ዕንቅፋት እና አድመኛ” እየተባሉ ስለሚሸማቀቁ አይተው እንዳላዩ ለመኾን ይገደዳሉ፤ ከሥራ እና ከደመወዝ ይታገዳሉ፤ ሰበካ ጉባኤያትን ከማደራጀት እና ከማጠናከር ይልቅ ለአማሳኝ አለቆች ከሚያደሉ የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ጋር በመመሳጠር ከፈቃዳቸው ውጭ ወደ ሌሎች አድባራት ዝውውር ይጠየቅባቸዋል፡፡

የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራንና የንብረት አመዘጋገብን አጥብቀው የሚቆጣጠሩ የማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች ከአባልነት ይታገዳሉ፤ “በዐውደ ምሕረት ደም ለማፋሰስ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማበጣበጥ እየሠሩ ነው፤ አሸባሪዎች ናቸው” በሚል ለመንግሥታዊ አስተዳደር እና የፍትሕ አካላት ክሥ ይቀርብባቸዋል፡

በደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊ እና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ አስተዳዳሪው ፤ የሰበካ ጉባኤውን ውሳኔ እንደማይተገብሩ የጠቆሙ ምእመናን፤ በምክትል ሊቀ መንበሩ የማይታወቁ የባንክ ሒሳቦችን በደብሩ ስም እንደሚያንቀሳቅሱ፣ አግባብነት የሌለው የሠራተኞች ዕድገት እና ዝውውር በመፈጸም ሰበካ ጉባኤውን ለማዳከም እና ለማፍረስ እየሠሩ እንደሚገኙ ምእመናኑ ይገልጻሉ፡፡

አለቃው መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ኃይለ ማርያም፣ በባሕር ዳር ሽንብጥ ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ Aba Gebra Sellassie Aregawi
በነበሩበት ወቅት በአስነዋሪ ሥራቸው የተባረሩ ቢኾንም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመካኒሳ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል በእልቅና ተመድበው የቤተ ክርስቲያኑን መሬት ለግል ጥቅም በማዋላቸው ለሦስት ዓመት ከሓላፊነት ታግደው እንደነበር ምእመናኑ አስታውሰዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም. በደብራቸው የተመደቡትም በቀንደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ እና መሰሎቹ አጃቢነት እንደኾነ የጠቀሱት ምእመናኑ፣ ለምዝበራ አመቺ የኾነው አሠራር ሲቀየስ እንደሚቆጡ እና ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በምልአት ስትፈጽም ማየት እንደማይሹ ያስረዳሉ፡፡


በሰኔ 2006 ዓ.ም. በካህናት እና ምእመናን ምልአተ ጉባኤ የተመረጠው ሕጋዊው ሰበካ ጉባኤ፣ በቋሚ የስብሰባ ጊዜ እየተገናኘ እና እየተወያየ እንሥራ ብሎ ላቀረበው ሐሳብ ከአለቃው የተሰጠው ዓምባገነናዊ ምላሽ “እኔ ስጠራችኹ ነው የምትመጡት፤ እኔ በምለው መመራት አለባችኹ” የሚል ነበር፡፡ አባላቱን “አያገባችኹም” በሚል ሰበካ ጉባኤው ቋሚ የስብሰባ ጊዜ እንዳይኖረው ያደረጉት አለቃው፤ በምትኩ በሕገ ወጥ እና ቤተ ክርስቲያን በማታውቀው ቡድን ምክር እና ውሳኔ እየሠሩ እንዳሉ ምእመናኑ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ከ2002 – 2006 ዓ.ም. ለሀገረ ስብከቱ የሚገባው የኻያ ፐርሰንት ፈሰስ ሙሉ በሙሉ እንደተከፈለ የቀድሞው የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ሪፖርት ያቀረቡ ቢኾንም ደብሩ ተከፍሏል በሚለውና ሀገረ ስብከቱ እንደተከፈለ በሚገልጸው መካከል ልዩነት በመኖሩ አለቃው ደብሩን ለውዝፍ ዕዳ እንደዳረጉትም አባላቱ ይናገራሉ፡፡ ሰበካ ጉባኤው፣ በማኅበረ ካህናቱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው በተወላጅነት እንደሚከፋፍሉ፤ ካህናቱን ከደመወዝ እና ከሥራ በማገድ፤ የቃል እና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ለችግር እንደሚያጋልጧቸው ምእመናኑ ይገልጻሉ፡፡

የአለመግባባቱ ዐቢይ መንሥኤ፣ የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ የደብሩን የገንዘብ ገቢ እና ወጪ አጥብቀው በመቆጣጠራቸው፤ በየጊዜው የወጣውን ገንዘብ ሪፖርት በመጠየቃቸው እንደኾነ የሚገልጸው የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት፤ አባላቱ፣ ደመወዝ ፈርሞ ከማውጣት ውጭ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ በቃለ ዐዋዲው በተደነገገው ሥልጣናቸው እና ተግባራቸው እየተሳተፉ እንዳልኾነ አረጋግጧል፡፡ የአስተዳዳሪውን፣ አልታዘዝ ባይነት እና ሰበካ ጉባኤውን “አይመለከታችኹም” እንዳሉ የሚገልጸው የክፍለ ከተማው ሪፖርት፣ ለሀገረ ስብከቱ መተላለፉን ቢያውቁም ምንም ዐይነት ምላሽ አለመሰጠቱ ግራ እንዳጋባቸው ምእመናኑ ይናገራሉ፡፡

Debra Gelila St. Amanuel Cathedral00
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በቅርቡ ባካሔደው የሕንጻ እና የመሬት ኪራይ ተመን ጥናታዊ ሪፖርት፣ የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል፣ “በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን”
እንደኾነ ተገልጧል፡፡ ይኸውም የካቴድራሉ የገቢ ማስገኛ ተቋማት፣ ከመርካቶ የመሬት ውድነት በተለይም ከዐማኑኤል አካባቢ የቦታ እና የመጋዘን ፍላጎት አንጻር ለሀብታም ነጋዴዎች የሚያደላ ውል በመፈጸም በእጅጉ በወረደ ዋጋ መከራየታቸው ነው፡፡ የካቴድራሉን ት/ቤት 3000 ካሬ ሜትር ቦታ ወደ ጋራዥ ከቀየሩ በኋላ በካሬ ሜትር 5.38 ሳንቲም ያከራዩት የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ “ዘመናዊ ቤት ሠርተው እና ፋሽን አመጣሽ ልብስ ለብሰው በሞዴል መኪኖች እየተሽከረከሩ ሆቴል አማርጠው ሲዝናኑ መመልከት የከተማዋ የዘወትር ውሏቸው” እንደኾነ በጥናታዊ ሪፖርቱ ሰፍሯል፡፡

የገቢ ማስገኛ ተቋማቱ እንዴት እንደተሠሩ እና እንዴት እንደተከራዩ የሚገልጹ ፋይሎችን በማጥፋት ከበድ ባለ ሙስና የተተቸው የካቴድራሉ አስተዳደር፣ ከሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ፣ ከንብረት አጠባበቅ እና ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከምእመናኑ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሰበካ ጉባኤው፣ የደብሩን የአሠራር ክፍተቶች በመቅረፍ ገቢውን በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠር እና ለማሳደግ በመንቀሳቀሱ አንድ የማኅበረ ካህናት ተወካዩ ከሥራ እና ከደመወዝ፣ ኹለት የምእመናን ተወካዮች ደግሞ ከአባልነት ታግደውበታል፡፡

የእገዳው ደብዳቤ የተሰጠው ነሐሴ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደኾነ የተጠቀሱት ምእመናኑ፣ የካቴድራሉ አለቃ እና የአስተዳደር ሓላፊዎች በማግስቱ በተለጠፈ ማስታወቂያ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ለማድረግ ያደረጉት ሙከራ በማኅበረ ካህናቱ እና በማኅበረ ምእመናኑ ትብብር እንዲቆም መደረጉ ገልጸዋል፡፡ የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ ችግርን ለመፍታት፣ በሰበካ ጉባኤው ውሳኔ የመቁጠርያ ማሽን እንዲገዛ ተወስኖ ፕሮፎርማ ቢሰበሰብም ግዢው እንዳይፈጸም የአስተዳደር ጽ/ቤቱ ዕንቅፋት መኾኑ ተጠቅሷል፡፡

ጥብቅ ቁጥጥር ከተጀመረ በኋላ በተደረገው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ በግንቦቱ ክብረ በዓል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መገኘቱ የተዘገበ ሲኾን በአዘቦትም እስከ ብር 350,000 መሰብሰብ ጀምሯል፡፡ ይህም ቀድሞ ከሚሰበሰበው ገቢ ከብር 200,000 በላይ ልዩነት እንደታየበት መረጋገጡን የገለጹት ምእመናኑ፣ ሰበካ ጉባኤው ከተመረጠበት የካቲት 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ ቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ከሒሳብ ሹሙ እና ከቁጥጥሩ የገንዘብ እና የንብረት ሪፖርት እንዲቀርብ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ አለመሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በተከናወነው ቆጠራም በጸሐፊው እና በቁጥጥሩ ብቻ የታሸጉ ስምንት የሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች ከሕጋዊ አካሔድ ውጭ ተቀምጠው መገኘታቸውም ታውቋል፡፡

እንደ መልአከ ብርሃናት ነአኵቶ ለአብ አያሌው ከመሳሰሉ የብሔረ ጽጌው አማሳኝ አስተዳዳሪ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው የካቴድራሉ አለቃ ሊቀ ብርሃናት አባ ዓይነ ኵሉ ሺበሺ፤ በንብረት ቆጠራ ወቅት ከምእመናን በስእለት የተሰጠ ወርቅ ወደ ቤታቸው ወስደዋል፤ አልተቀበልኩም በማለት ሲከራከሩ ቆይተው በሰበካ ጉባኤው ጫና ወደ ንብረት ክፍሉ መግባቱን ቢገልጹም ስለመግባቱ የቀረበ ማስረጃ ግን አልቀረበም፤ ተብሏል፡፡

በካቴድራሉ በዋና ጸሐፊነት የሠሩት እና ከወቅቱ ሒሳብ ሹም እና ከንብረት ሽያጭ ሠራተኛው ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በሦስት የሰበካ ጉባኤው አባላት ላይ የተጣለው ሕገ ወጥ እገዳ እንዲነሣ፤ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራው በመመሪያው መሠረት እንዲካሔድ በሰበካ ጉባኤው እና በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ቢጠየቁም መፍትሔ ሰጭ ውሳኔ እስከ አኹን አለመስጠታቸው ታውቋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እና ንብረት ለመጠበቅ ሲባል ካህናት እና ምእመናን የሥራ ሓላፊነታቸውንና የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ግዴታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ለሚፈጠርባቸው ችግር እና ዕንቅፋት ሀገረ ስብከቱ ሓላፊነት እንደሚወስድ ቢገልጽም ተጨባጭ መፍትሔ ባለመኖሩ “ትክክለኛ መፍትሔ የማግኘት ተስፋችንን አዳክሞታል፤ ለሚደርሰው ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂዎች አንኾንም” በማለት ምእመናኑ ያስጠነቅቃሉ፡፡

 • በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣
 • በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ፣
 • በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል
 • በቡልቡላ መድኃኔዓለም፣
 • በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል፣
 • መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም፣
 • በመዝገበ ምሕረት ካራ ቆሬ ቅዱስ ፋኑኤል፣
 • በብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም፣
 • በላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል፣
 • በፉሪ ቅዱስ ገብርኤል፣
 • በሰሚት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣
 • በሰሚት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፣
 • በሰሚት ቅዱስ ሩፋኤል፣
 • በጨፌ አያት ቅዱስ ገብርኤል፣
 • በአያት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣
 • በፉሪ ቅዱስ ዑራኤል
 • በፉሪ ቅድስት ሐና፣
 • በቀርሳ ቅድስት ልደታ
 • በሰሚት መድኃኔዓለም

የአድባራት ሓላፊዎቹ፣ ከማኅበረ ካህናት እና ከማኅበረ ምእመናን ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ በመግባታቸው የቤተ ክርስቲያን ሀብት እና ንብረት ያለተጠያቂነት በመዘረፍ ላይ እንዳለ እና የአጥቢያዎቹ ሰላምም መታወኩ ተጠቁሟል፡፡ የሥራ ጊዜአቸውን ባጠናቀቁ የሰበካ ጉባኤ አባላት ምትክ ምርጫ አለመካሔዱ፤ የሰበካ ጉባኤ አባላት በሥልጣናቸው አለመሥራት፤ የአስተዳደር ሓላፊዎች ብቃት ማነስ፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲኹም የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ መዳከም በዐበይት መንሥኤነት ተዘርዝረዋል፡፡ ሰበካ ጉባኤያቱን የማደራጀት እና የማጠናከር ሓላፊነት የተጣለበት የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊነቱን አለመወጣቱ ግን የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡

በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ በሳምንቱ መጀመሪያ በተካሔደ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ ብርሃኑ ጌጡ እና ሌሎች ኹለት ሓላፊዎች በዓምባገነኑ የደብሩ አለቃ መልአከ ብርሃናት ዘመንፈስ ቅዱስ የተበተነውን ሰበካ ጉባኤ ተክተው ሲሳተፉ የሰበካ ጉባኤው ጉዳይ ግን አላሳሰባቸውም፡፡

በፓትርያርኩ መቀመጫ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በሃይማኖት እና በምግባር የታወቀ ሕጸጽ ያለባቸው ቄሰ ገበዙ አባ ሳሙኤል ቀለመ ወርቅ፣ ለሦስተኛ ተከታታይ ወር፣ የታገደውን ሰበካ ጉባኤ ተክተው ፈራሚ ሲኾኑ ሕገ ወጡን አካሔድ ሀገረ ስብከቱ እያጸደቀ ነው፡፡

ለዚኽ ኹሉ ቀውስ እየከፋ እና እየተባባሰ መሔድ ደግሞ፣ ምእመናንን በመናቅ እና በመጸየፍ ሚናቸውን ዜሮ ለማድረግ እና ለምዝበራ የተመቸ አሻንጉሊት ሰበካ ጉባኤ ለመፍጠር የሚሠሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና የአመራራቸው ተጠያቂነት በትኩረት ታይቶ የኾነ እልባት ሊሰጠው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

አለበለዚያ፣ የአስተዳደር በደል፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር በሚፈጥረው የተከማቸ ቅሬታ የተነሣ ቀደም ሲል በቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም፤ ነሐሴ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአማሳኙ እና ምግባረ ብልሹው አለቃ ላይ የወሰዱት ከአጥቢያው የማባረር ርምጃ ለመቀጣጠሉ ልዩ ዐዋቂነትን አይጠይቅም፡፡

Advertisements

2 thoughts on “በአ/አበባ ሀ/ስብከት: ሰበካ ጉባኤያት በአማሳኝ አለቆች መታገዳቸው አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ ነው፤ “ሚና አልባ እየተደረጉ ነው”

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: