ሰበር ዜና – የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ዐረፉ

 • የቀብር ሥነ ሥርዐቱ ነገ በ5፡00 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል
 • በባንክ የተገኘውን ብር 9000 ለሚረዷቸው ልጆች እንዲከፋፈል ዐርብ ዕለት ተናግረው ነበር
 • በአማሳኞች እና በኑሮ ውድነት ለተሠቃየው ሠራተኛ በወሰዱት ተጠቃሽ ርምጃ ይታወሳሉ
 • በግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት ተመድበው ነበር
his-grace-abune-filpos

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፤ የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (፲፱፻፳፰ – ፳፻፯ ዓ.ም.)

“ቅድስና ያላቸው ጸሎተኛ እና ቀናዒ ኦርቶዶክሳዊ፣ ሰባኬ ወንጌል እና መካሪ አባት ነበሩ፡፡አህጉረ ስብከቱን በመሩበት የ፳ ዓመታት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው፣ ከ93 በላይ አብያተ ክርስቲያንን አሳንጸዋል፤ የመቱ ካህናት ማሠልጠኛ ከነበረበት ተሻሽሎ በአካባቢው ቋንቋ አገልጋዮችን ለማፍራት እንዲበቃ አድርገዋል፤ ከተመደቡላቸው የሥራ ሓላፊዎች ጋር ተግባብተው እና በአባትነታቸው በሕዝቡ ተወደው ተልእኳቸውን በታላቅ ትጋት ተወጥተዋል፡፡በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅነታቸው ወቅት፣ በአማሳኝ ሓላፊዎች እና በኑሮ ውድነት ለተሠቃየው ሠራተኛ በወሰዱት ተጠቃሽ ርምጃ ይታወሳሉ፡፡”

በብሕትውናቸው፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው እና ኹሉን በሚያቀርበው ይውህናቸው የሚታወቁት የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ዛሬ፣ ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ማለዳ ላይ ዐረፉ፡፡

የእግራቸው ቁስለት ወደ ካንሰር የተባባሰባቸው ብፁዕነታቸው፣ በደቡብ አፍሪቃ ሕክምና ተደርጎላቸው ከተመለሱ በኋላ በሀገር ውስጥ በናሽናል ሆስፒታል ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ዛሬ፣ ማለዳ 12፡00 ላይ ዐርፈዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ሥርዐተ ምንኵስና የተቀበሉት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከስድሳ ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው የሚነገርላቸው ብፁዕነታቸው፤ በይበልጥ የሚታወቁት በተባሕትዎ ሕይወታቸው፣ ወገን ሳይለይ ኹሉን በሚያቀርበው የዋሃታቸው፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው እና ከደብር እልቅና እስከ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት በሚደርሰው የአስተዳደር ሥራቸው ነው፡፡

በፊት ስማቸው አባ ገብረ ማርያም ፈለቀ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፤ ባዕለጸጎችን አስተባብረው ነዳያንን ሲረዱ የኖሩበትን የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራልን በምእመናን ጥያቄ ተመድበው አስተዳድረዋል፤ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር እንዲኹም ሊቀ ሥልጣናት ተብለው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በእልቅና አገልግለዋል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ እና በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከትም በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሠርተዋል፡፡

ፍቅረ ሢመት የራቀላቸው ብፁዕነታቸው፣ ከሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጀምሮ ለኤጴስ ቆጶስነት ማዕርግ ቢታጩም፣ “ለዚኽ ማዕርግ አልበቃኹም” በሚል ሲሸሹት ቆይተው፣ ከሌሎች ስድስት ብፁዓን አባቶች ጋር ኅዳር ፬ ቀን ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተብለው የኢሉባቦር ጳጳስ ኾነው ተሹመዋል፡፡

አህጉረ ስብከቱን በመሩበት የኻያ ኹለት ዓመታት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው፣ ከ93 በላይ አብያተ ክርስቲያንን አሳንጸዋል፤ የመቱ ካህናት ማሠልጠኛ ከነበረበት ተሻሽሎ በአካባቢው ቋንቋ አገልጋዮችን ለማፍራት እንዲበቃ አድርገዋል፤ ከተመደቡላቸው የሥራ ሓላፊዎች ጋር ተግባብተው እና በአባትነታቸው በሕዝቡ ተወደው ተልእኳቸውን በታላቅ ትጋት ተወጥተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ አህጉረ ስብከታቸውን እንደያዙ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትንና የመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርንም ከከሐምሌ ፲፱፻፺፰ – ፳፻፫ ዓ.ም. በበላይ ሓላፊነት መርተዋል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ምርጫ እና ውሳኔ ከሚያዝያ ፳፻፪ – ፳፻፭ ዓ.ም. ግንቦት ወር ድረስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡ “ቅድስና ያላቸው ጸሎተኛ እና ቀናዒ ኦርቶዶክሳዊ፣ ሰባኬ ወንጌል እና መካሪ አባት ነበሩ፤” ያሉ አንድ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባልደረባ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በዚኽ ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚነት ሓላፊነታቸው ወቅት፣ በአማሳኝ ሓላፊዎች እና በኑሮ ውድነት ለተሠቃየው ሠራተኛ በወሰዱት ተጠቃሽ ርምጃ እንደሚታወሱ ይናገራሉ፡፡

በብፁዕነታቸው አመራር የሠራተኛው ደመወዝ እስከ ኃምሳ በመቶ በልዩ ኹኔታ ተሻሽሏልያለሞያቸው በመምሪያ ሓላፊነት ደረጃ ተቀምጠው ሠራተኛውንና ብፁዓን አባቶችን ሳይቀር በሙስና ሲያሠቃዩ ከነበሩት መካከል፤ የሒሳብ እና በጀት መምሪያ ሓላፊ እንደነበረው ሊቀ ትጉሃን ገብረ መስቀል ድራር ያሉት ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስወግደው የሚመጥናቸውን ቦታ ከማስያዛቸውም በላይ በገንዘብ እና ገንዘብ ነክ ሥራዎች እንዳይመደቡ በቋሚ ሲኖዶስ አስወስነዋል፤ በምትካቸውም ተፈላጊው የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ያላቸው ከፍተኛ ባለሞያዎች እንዲተኩ አድርገዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ከተማሪ ቤት ጀምሮ በእግራቸው ታፋ ላይ ሲያስቸግራቸው የኖረውና ቆይቶም ወደ ነቀርሳነት ለተባባሰው ቁስለት የሕክምና ክትትል ለማድረግ ካልኾነ በቀር በሀገረ ስብከታቸው ጸንተው በመሥራት ይታወቃሉ፤ “የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ካለቀ ለአንድ ቀን ማደር ይከብዳቸዋል” ይላሉ አንድ ወዳጃቸው፡፡

የብፁዕነታቸው ዜና ዕረፍት ዛሬ ማለዳ ከመሰማቱ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ በንግድ ባንክ ብቸኛ ሒሳባቸው ያለውን ብር 9000፣ በሀገረ ስብከታቸው ላሳደጓቸው እና በዚኽ ዓመት ለመሰናዶ እና ለከፍተኛ ትምህርት ላበቋቸው ኹለት ልጆች እኩል እንዲከፋፈል አዝዘው እንደነበር ሲያስታምሟቸው የቆዩት ተናግረዋል፤ “ሌላ ሀብት እና ንብረት የለኝም” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ልጆቹ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱም ረዳት እንዳያጡ አደራ ሰጥተዋል፡፡

የብፁዕነታቸው አስከሬን ካረፉበት ናሽናል ሆስፒታል ዛሬ ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ሊቀ ሥልጣናት ኾነው ወዳገለገሉበት፣ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ታጅቦ ይደርሳል፡፡ ጸሎተ ፍትሐቱ በዚያው ሲከናወን አድሮ በነገው ዕለት ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከታቸው ሓላፊዎች፣ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት ሥርዐተ ቀብሩ እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊልጶስ በረከታቸው ይድረሰን፡፡ አሜን፡፡

Advertisements

11 thoughts on “ሰበር ዜና – የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ዐረፉ

 1. alem August 31, 2015 at 11:16 am Reply

  hope god with him

 2. anonymous August 31, 2015 at 1:38 pm Reply

  bereketachew yideribin!

 3. Anonymous August 31, 2015 at 2:08 pm Reply

  gin egziabher min liadergen new yasebew? minew degag abatochin eyemerete yemiwosdibin?????

 4. fentaw August 31, 2015 at 3:39 pm Reply

  Wedemiwedut amlakachew hedu.

 5. Anonymous August 31, 2015 at 7:42 pm Reply

  Bereketachew yiderbn.

 6. kesis neway kassahun September 1, 2015 at 2:47 am Reply

  አባታችንን ምንም ቃላት አይገልጻቸውም፡፡ ይብላኝ ለኛ ለክፉዎቹ ደግነት ለራቀን ከአንድ ወር በፊት ተሰናብቻቸው ተለያየን፡፡በአጭሩ ይህ ጥቅስ ወደ አእምሮዬ መጣ፡፡
  ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። የሐዋርያት ሥራ
  11፥24

 7. fikre yesus September 1, 2015 at 12:30 pm Reply

  Abatachin, bereketo Yideribin. Timhirto ena hiweto ayiresam, yatsnanal

 8. Anonymous September 1, 2015 at 3:24 pm Reply

  ነፍሣቸውን በገነት ያኑርልን

 9. Anonymous September 2, 2015 at 1:28 pm Reply

  ነፍሣቸዉን ከፃድቃን ጋር በገነት ያኑርልን

 10. Endeg biresaw September 4, 2015 at 3:19 pm Reply

  tiruyyenesew

  abatachin bereket yideribin

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: