በደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል: የ6 ሚ. ብር የሕንፃ ገቢ ምዝበራ ጥያቄ ሳይመለስ ሌላ የሕንፃ ዕብነ መሠረት ሊቀመጥ ነው

 • የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር: “ባልተጣራ ሒሳብ እንዴት ሕንፃ ይሠራል?”
 • የግንባታ ጥናቱ ከክፍያ ነፃ እንደተሠራ ቢነገርም የብር 250,000 ክፍያ እያነጋገረ ነው
 • ሕግን መጣስ፣ ያለዕቅድ እና ያለጥናት ከፍተኛ ገንዘብ ማባከን የአስተዳደሩ መገለጫ ነው
 • በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተካሔደው የምዝበራ እና ብክነት ምርመራ ውጤቱ አልታወቀም
 • ነገ ዕብነ መሠረቱን የሚያስቀምጡት ፓትርያርኩ ኹኔታውን እንዲያጤኑት ተጠይቋል

St.Urael church bld complex
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ነገ ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው፣ የሕንፃ መሠረት ደንጊያ እንዲያስቀምጡ በደብሩ አስተዳደር መርሐ ግብር ተይዞላቸዋል፡፡

በቀድሞው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የታቀደው ግንባታው÷ የካህናት ማረፊያ፣ የአብነት ት/ቤት እና የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ እንደሚያካትት ተገልጧል፡፡

የግንባታው ጥናት፣ የምሕንድስና ሞያ ባላቸው በአንድ የቀድሞው የሰንበት ት/ቤቱ አባል እና በሌላ ምእመን ከክፍያ ነፃ በበጎ አድራጎት መሠራቱ ቢነገርም፣ በስማቸው ቃለ ጉባኤ ተሠርቶ ወጪ ለማድረግ የታቀደው ብር 250,000 የወቅቱን የሰበካ ጉባኤ አባላት እያነጋገረ ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት የግንባታ ፕሮጀክት ሰነዱ እና ዝርዝር ወጪው ተሠርቶ ከሀገረ ስብከቱ እና ከሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ እና መመሪያ ባልተገኘበት ኹኔታ ዕብነ መሠረቱን ማስቀመጡ “ልማታዊ” ሳይኾኑ መስሎ ከመታየት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው የደብሩ ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡

በሕንፃ ኪራይ የሚሰበሰበውን ከፍተኛ ገቢ ጨምሮ በሕገ ወጥ አሠራር ለባከነው እና ለተመዘበረው የደብሩ ገንዘብ ይፋዊ የሒሳብ ምርመራ ጥያቄ በቀረበበት፤ በቀጣይም ተገቢ እና ውጤታማ የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዐት ባልተዘረጋበት ኹኔታ ሒሳቡ ያልታወቀ እና እንደ ቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ያልተፈቀደ ሕንፃ መሠረት ማስቀመጥ ጉዳዩን የማድበስበስ አካሔድ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡

“መነሻ እና መድረሻው በማይታወቅ የገንዘብ ወጭ እንዴት ሕንፃው ይሠራል?” ሲሉ የሚጠየቁት ሠራተኞቹ፣ ግንባታው የሚታወቅ የጸደቀ በጀት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

የደብሩ ሒሳብ ሹም፣ የ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሊዘጋ ሰባት ቀናት ሲቀሩት ወደ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራል መዘዋወራቸውን በመቃወም፣ ከመጋቢት/2005 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 22/2007 ዓ.ም. ድረስ ለ27 ወራት ከብር 54 ሚሊዮን በላይ ገቢ እና ወጪ የሠሩባቸው የሒሳብ ሰነዶች እና መዛግብት በገለልተኛ እና ሕጋዊ ኦዲተሮች በይፋ እንዲመረመርላቸው ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ፣ በአጠያያቂ ኹኔታ ላዘዋወራቸው ሒሳብ ሹሟ ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም፣ ነሐሴ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከተዘዋወሩበት ቀን ድረስ የሠሩባቸውን ሕጋዊ ሰነዶች በማቅረብ በተመደቡ ኦዲተሮች አማካይነት እንዲያስመረምሩ እና በእጃቸው የሚገኙ ሰነዶችን እንዲያስረክቡ አስጠንቅቋል፡፡

ሒሳብ ሹሟ ማስጠንቀቂያውን በመቃወም ነሐሴ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በድጋሚ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ፣ በምትካቸው የተመደቡት የሒሳብ ሠራተኛ የዋና ሥራ አስኪያጁ የረጅም ጊዜ ጓደኛ መኾናቸውን ጠቅሰው፣ የሰነድ ርክክብ በጓደኝነት እንደማይደረግና የተፈለገውም ዶክመንት ለማጥፋት መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ አክለውም፣ መመርመር የማይቀር እና አስፈላጊ አሠራር ነው፤ ነገር ግን ምርመራው፣ ለአንድ ዓመት የሠሩበትን ብቻ ሳይኾን ከመጋቢት 2005 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ያለውን እንዲያካተት እና ሕንፃውንም እንዲጨምር ጠይቀዋል፡፡


… ምርመራውን እጅግ በጣም እፈልገዋለኹ፤ ነገር ግን ለአንድ ዓመት የሠራኹበትን ብቻ አይደለም፤ ኹሉም አካል እንዲረዳልኝ እና እንዲያውቀው የምፈልገው፣ ከመጋቢት 2005 ዓ.ም. እስከተዘዋወርኩበት ሰኔ 22/2007 ዓ.ም. የቅዱስ ዑራኤል ገቢ እና ወጪ ሒሳብ፣ ሕንፃው እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታ በአጠቃላይ በይፋ እንዲመረመር እጠይቃለኹ፤ ምክንያቱም የ2005 እና የ2006 ዓ.ም. የሒሳብ ምርመራ ውጤት ለእኔ እንዲደርስ አልተደረገም፤ እንዲደበቅ ተደርጓል፡፡

ስለዚኽ የመንግሥት ኦዲተር፣ የካህናት ተወካይ፣ የሰበካ ጉባኤ ተወካይ፣ የምእመናን ተወካይ፣ የፀረ ሙስና እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ተወካይ፣ የቢሮ ሠራተኞች በአጠቃላይ በታዛቢነት ባሉበት ነው ምርመራው መደረግ ያለበት፡፡ በሞዴል ፷፬ ገባ፤ በሞዴል ፮ ወጣ፤ ከወጪ ቀሪ ይኼ ነው የሚባለውን አልፈልገውም፡፡


በሒሳቡ ሹሟ ጥያቄ መሠረት፣ ሒሳቡ ሳይመረመር እና ሳይጣራ የሌላ ሕንፃ መሠረት መጣሉ አግባብነት እንደሌለው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምእመናን ተችተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ለደብሩ ከፍተኛ ገቢ ለሚያስገኘው ሕንፃ ዕድሳት ባለመደረጉ ይዞታው እየተጎዳ ባለበት የሌላ ሕንፃ መሠረት መጣሉ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ነው፤ ብለዋል፡፡

ምእመናኑ እንደሚናገሩት፣ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘው የወቅቱ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር፣ እውነቱ መውጣቱን እንደሚሹ እና ሒሳቡ ተጣርቶ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ወደ ግንባታው መሔዱን ነው የሚመርጡት፡፡

በደብሩ ስለተፈጸመው የገንዘብ ብክነት እና ምዝበራ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንደሚያውቁ የጠቆሙት ምእመናኑ፣ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ውጭ ስለተፈጸሙ የአስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ችግሮች በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ሀገረ ስብከቱ ማጣራት ቢያካሒድም ውጤቱ እንዳልተገለጸላቸው አስታውሰዋል፤ ቅዱስነታቸው በነገው ዕለት ዕብነ መሠረቱን ከማስቀመጣቸው አስቀድሞም ከግንባታው ጋር በተያያዘ በተጨባጭ ያሉ እውነታዎችንና አግባቦችን በጥንቃቄ እንዲያጤኑት ጠይቀዋል፡፡

በአስተዳደሩ፣ ያለዕቅድ እና ያለጥናት የሚሠሩ ሥራዎች እና የሚፈጸሙ ክፍያዎች፣ የወጣባቸውን ከፍተኛ ገንዘብ ያኽል ጥራት እንደሌላቸው ተነግሯል፡፡ ለካህናት “ጊዜያዊ ቤት” በሚል እስከ ብር 600,000 ወጪ ቢደረግም ያለጥናት በመሠራቱ ክፍቱን መቀመጡ በአብነት ተጠቅሷል፡፡ ለደብሩ ዐይነተኛውን ገቢ ለሚያመነጨው እና በርካታ ሱቆች ላሉት ሕንፃ ጠርዝ የመሠረት ሥራ ከፍተኛ ወጪ ቢወጣም ጥራቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዳልኾነ ተገልጧል፡፡

በአንጸሩ ጥቂት የደብሩ የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ ውሳኔን በውሳኔ በመሻር ከሕንፃው የኪራይ ገቢ ላይ ከብር 6 ሚሊዮን በላይ ወደ ደብሩ ካዝና አለመግባቱን፤ በውል ላይ ውል በመዋዋል ከአንድ የሕንፃ ኪራይ ብቻ ብር 487,869.32 መመዝበሩን፤ የደብሩን የሕንጻ ኪራይ የአፈጻጸም ችግሮች ያጣራው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጥኚ ኮሚቴ በሒሳብ ሹሟ አማካይነት ከመዝገብ ቤት በቀረቡለት ሰነዶች ማረጋገጡ ታውቋል፡፡

በኮሚቴው ጥናታዊ ሪፖርት እንደተዘረዘረው፣ በትክል ዘመኑ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀደምት አብያተ ክርስቲያን አንዱ የኾነው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፡-

 • ሰፋፊ የንግድ ተቋማት ካሏቸው አጥቢያዎች መካከል በርካታ የንግድ ማእከላትን በማቀፍም ተጠቃሽ ቢኾንም አትራፊዎቹ ግን ግለሰብ ነጋዴዎች እና ከእነርሱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ጥቂት የአስተዳደሩ እና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ናቸው፡፡
 • የደብሩ አስተዳደር፣ የንግድ ተቋማቱን የሚያከራየው ከሕጋዊ አሠራር ውጭ ያለጨረታ ነው፡፡ በደብሩ አካባቢ የሚከራዩ የግለሰቦች እና የደብሩ ሱቆች ኪራይ ዋጋ በእጅጉ የሚለያይ በመኾኑ ደብሩ ተጎጂ ኾኗል፡፡
 • ያለጨረታ የተከራዩት የንግድ ቤቶች የውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ውስጥ ለውስጥ ስለሚሸጡ እና በሰፊው ለሦስተኛ ወገን ስለሚተላለፉ፣ ለደብሩ ገቢ መኾን የሚገባው የስም ማዘዋወርያ ብር 50,000 ገቢ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ ይህም ግለሰብ ነጋዴዎች እርስ በርስ እንዲጠቃቀሙ በማድረግ ደብሩን ያለአንዳች ጥቅም እያስቀረው ነው፡፡
 • ግለሰብ ነጋዴዎች ከደብሩ የተከራዩትን ሱቅ ሸንሽነው ለግሰለቦች በማከራየት ተጠቃሚ ሲኾኑ አስተዳደሩ በዝምታ አልፏል፡፡ ተከራዮቹ የኪራይ ውላቸው እንዲጸና በማድረግ እና ውል በመዋዋል ሱቆቹ በጨረታ ቢከራዩ ኖሮ ደብሩ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከፍተኛ ጥቅም አሳጥተውታል፡፡
 • አስተዳደሩ፣ በሕጉ መሠረት በካሬ ሜትር መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ በአግባቡ የማይከፍሉትን በመከታተል እና በመቆጣጠር ማስከፈል አልቻለም፡፡ ለምሳሌ፣ የቅዱስ ዑራኤል ፋርማሲ ብር 167,552 ዕዳ እያለባቸው ተገቢው ክትትል ባለመደረጉና ተከራዮቹ ከአንዳንድ የደብሩ ሓላፊዎች ጋር በመመሳጠራቸው የተጠቀሰውን ገንዘብ ሳይከፍሉ ቤቱን ለቀው በመሔድ ደብሩን ተጎጂ አድርጎታል፡፡
 • በደብሩ ከሦስት እስከ ስምንት ሱቆች በአንድ ግለሰብ ስም ተከራይተው ይገኛሉ፡፡ ይህ በተናጠል ለተለያዩ ግለሰቦች በጨረታ እንዲከራይ ቢደረግ ኖሮ ደብሩ እጅግ በጣም ተጠቃሚ መኾን ይችል ነበር፡፡ ይህ ቀርቶ ተከራዩ ግለሰብ ለሌሎች በማከራየት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርገዋል፡፡
 • የሱቅ ቁጥር 35 ከመስከረም 2006 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. በውል ከተሰጠው በኋላ ከየካቲት 2006 እስነ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. ኹለተኛው ውል ለአቶ ሰሎሞን ገብረ ወልድ በመስጠት የስም ማዘዋወሪያ ብር 50,000 እንዳይከፈል ተደርጓል፡፡
 • ቁጥር 31 ሀሮት ትሬዲንግ ከመጋቢት 27 ቀን 2005 እስከ የካቲት 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ውል የተሰጣቸው ሲኾን የውል ዘመኑ ሳያልቅ ወደ ኋላ ተስቦ ከመስከረም 1 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2010 ዓ.ም. ለ5 ዓመታት ተራዝሟል፡፡
 • የሕንፃው ግራውንድ ቤት፣ በክፍለ ከተማው አስተዳደር ሲከለከል፣ ተከራይቶት የቆየው ግለሰብ ለቆ ሲሔድ መከፈል የሚገባው ክፍያ እንዳይከፈል በመደረጉ ደብሩ ጎጂ ተደርጓል፡፡
 • ሕገ ወጥ ተከራዮችን ለማስለቀቅ የሚደረገውን ጥረት ለማኮላሸት ሀገረ ስብከቱ ለግለሰቦች የሚወግን ደብዳቤ ይጽፋል፤ በተጭበረበረ ውል ምክንያት የሦስት ሚሊዮን ብር ባለዕዳ የኾኑ ግለሰብ በደብሩ ተከሠው ዕዳቸውን እንዲከፍሉ የሚደረገውን ጥረት የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመደገፍ ፈንታ ለሀብታም ግለሰብ ነጋዴ በመወከል፣ በክሥ የሚጠየቁት ሦስት ሚሊዮን ብር እንዳይከፍሉ “ቤተ ክርስቲያን የይቅርታ ቤት ስለኾነች” በሚል ክሡ እንዲቋረጥ ለደብሩ ደብዳቤ ጽፈዋል፤ ቤተ ክርስቲያንም ጉዳዩን በሕግ አግባብ ከሣ ገንዘቧን በተሟላ ኹኔታ እንዳታገኝ ተደርጓል፡፡
 • የደብሩ የሕግ ክፍል፣ ማስታወቂያ ወጥቶ እና ተወዳድረው በሕግ አግባብ ያልተቀጠሩ ከመኾኑም በላይ በወር ከደብሩ ሦስት ሺሕ ብር ደመወዝ ያገኛሉ፤ ክሥ በሚከሥበት ወቅት ደብሩ ተረታም ረታም ከደብሩ በቅጣት ከሚገኘው ገንዘብ በፐርሰንት ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው መኾኑ አግባብነት የለውም፡፡ ይኹንና የሕግ ክፍሉ በዚኽ መልኩ የሚያገኙት ጥቅም ከፍተኛ በመኾኑ፣ ክሦች እንዲበራከቱ በማድረግ ጥቅም የሚጋሩበት እና ክሦችን በማመቻቸት ተጠቃሚ የሚኾንበትን መንገድ ስለሚፈጥር የቅጥር ውሉ እንዲቋረጥ መደረግ ይኖርበታል፡፡

ጥናታዊ ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ የተቀበለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ፣ ካሳለፋቸው ባለዐሥር ነጥብ ውሳኔዎች መካከል፣ “በጥናት ሥራው ወቅት ግንባር ቀደም ተሰላፊ እና በሰነድ በተደገፈ አግባብ በደብሩ የሚታዩ የአሠራር ችግሮችን በማጋለጥ መሥዋዕትነት የከፈሉ” ናቸው ሲል ለጥረታቸው ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ለሚመለከታቸው ኹሉ፣ በደብራቸው የሚታየውን የአሠራር ችግር አስመልክተው አስፈላጊውን መረጃ በሰነድ አስደግፈው ያቀረቡና ያለውን ችግር ለመቅረፍ ፊት ለፊት የተጋፈጡ ቢኾንም ካሉበት ደብር እንዲዘዋወሩ መደረጉ አግባብነት እንደሌለ በመግለጽ ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ በአንድ ድምፅ የወሰነው በሚከተለው መልኩ ነው፡-

ካሉበት ደብር እንዲዘዋወሩ መደረጉ የሥራውን ተኣማኒነት እና የበላይ አካልን ውሳኔ ሰጪነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ተጨማሪ የማጣራት ሥራ መሥራት ቢያስፈልግ እንኳን ጉዳዩን የበለጠ ሊያብራራ እና በሰነድ በተደገፈ መልኩ ሊያቀርብ የሚችል ሰው እንዳይኖር የሚያደርግ ከመኾኑም በላይ በአጥቢያ የሚታዩ የአሠራር ችግሮችን በፊት ለፊት ማቅረብ እንደ ወንጀል እንዲታይ በማድረግ ችግሮችን ለማጋለጥ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ቅስም የሚሠብር ስለኾነ ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ሲል የአስተዳደር ጉባኤው በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡


 

Advertisements

3 thoughts on “በደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል: የ6 ሚ. ብር የሕንፃ ገቢ ምዝበራ ጥያቄ ሳይመለስ ሌላ የሕንፃ ዕብነ መሠረት ሊቀመጥ ነው

  • Anonymous August 29, 2015 at 7:13 am Reply

   የተሃድሶ ምንፍቅና አራማጁ በጋሻው ደሳለኝ በሰሚት ኮንዶሚንየም የተሃድሶ ምንፍቅና አራማጆች በአዲስ አበባ በሰሚት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን (ቦሌ ክፍለ ከተማ) ከነሀሴ 15 እስከ 17 ጉባኤ እናካሂዳለን ብለው ያሰቡት ፕሮግራም በምእመናን እና በሰንበት ትምህርት ቤቱ ብርቱ ጥረት ከሸፈባቸው፡፡ አዲሱ የደብሩ ሰባኪም መ/ር አይምሮ ዋነኛ ተዋናኝ እንደሆኑ ለመረዳት ችለናል፡፡

 1. Anonymous August 29, 2015 at 7:12 am Reply

  የተሃድሶ ምንፍቅና አራማጁ በጋሻው ደሳለኝ በሰሚት ኮንዶሚንየም የተሃድሶ ምንፍቅና አራማጆች በአዲስ አበባ በሰሚት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን (ቦሌ ክፍለ ከተማ) ከነሀሴ 15 እስከ 17 ጉባኤ እናካሂዳለን ብለው ያሰቡት ፕሮግራም በምእመናን እና በሰንበት ትምህርት ቤቱ ብርቱ ጥረት ከሸፈባቸው፡፡ አዲሱ የደብሩ ሰባኪም መ/ር አይምሮ ዋነኛ ተዋናኝ እንደሆኑ ለመረዳት ችለናል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: