ፓትርያርኩ: አዲሱ ዓመት ቤተ ክርስቲያን በፀረ ሙስና እንቅስቃሴዋ ልዕልናዋን የምታስመልስበት ይኾናል

 • በአ/አበባ ሀ/ስብከት በየዓመቱ ከ1.5 ቢልዮን ብር በላይ የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ይመዘበራል
 • የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማዳከም “የተለያዩ ነፋሳት እየነፈሱ” መኾኑን ፓትርያርኩ ጠቁመዋል
 • የሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ሙስና ንቅናቄውን በማጠናከር በጋራ አብረዋቸው እንዲሠሩ ጠይቀዋል

*         *         *

 • የሰንበት ት/ቤት አንድነት አመራሮቹ ‹‹በሚያስፈልገው ነገር ኹሉ ከጎንዎት ነን›› ብለዋቸዋል
 • በደመራ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ለሀ/ስብከቱ ዋ/ሥ/አስኪያጅ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ ተጠይቋል
 • ከ3000 በላይ የሀ/ስብከቱ ወጣቶች እና ሕፃናት ቅድመ ዝግጅታቸውን ነሐሴ ፳፬ ይጀምራሉ
 • የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮውስ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

*          *        *

(ሰንደቅ፤ ረቡዕ ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

His Holiness patriarch Abune Mathias

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ

መጪው ፳፻፰ ዓ.ም.፣ ቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ችግሮቿን አስተካክላ ልዕልናዋን የምታስመልስበት እንደሚኾን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡

ከቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ የሙስና እና የሥነ ምግባር ብልሽቶችን ለማስወገድ የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ “ጭላንጭል እየታየበት ነው” ያሉት ፓትርያርኩ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቷ ልዕልና እና ሕይወት እስኪመለስ በሰላማዊ መንገድ እና በአቋም መታገላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፓትርያርክነት በተመረጡበት በዓለ ሢመት፣ በቆራጥ የለውጥ ርምጃዎች የፀረ ሙስና ሥርዐት ለመደንገግ የገቡትን ቃል መነሻ በማድረግ ስለተከናወኑ እንቅስቃሴዎች ከሰንበት ት/ቤቶች ሥራ አመራር አባላት ጋር ባለፈው ሰኞ ከቀትር በኋላ በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የሥራ አመራር ጉባኤያት ተወካዮች በተገኙበት ውይይት፤ “ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለማረም እና ለማስወገድ በሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ከጎኔ እንድትቆሙ”  በሚል ፓትርያርኩ የሰጡት አባታዊ መመሪያ ምእመኑን ያስደሰተ እና ወጣቱን ያነቃቃ መኾኑ በተወካዮቹ ተገልጧል፡፡

መመሪያውን ለማስፈጸም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንዳሉ የተናገሩት የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ፣ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዳይገኝለት የሚጥሩ ኃይሎች ፓትርያርኩ ከወጣቶች እንዳይገናኙ የፈጠሩትን ዕንቅፋት አስረድተዋል፤ ዕንቅፋቶቹን በመቋቋም በተሠሩ ሥራዎች ወጣቶቹን እንዲያበረታቷቸውም ቅዱስነታቸውን ጠይቀዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እና ሰፊ የመሬት ይዞታ ቢኖሯትም የሚገባውን ያኽል ተጠቃሚ እንዳልኾነች ሰሞኑን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ የቀረበው የአዲስ አበባ አድባራት የመሬት እና የሕንፃዎች ኪራይ ተመን ጥናታዊ ሪፖርት ማረጋገጡን የፓትርያርኩ ጽ/ቤት ሓላፊ በውይይቱ ወቅት ጠቅሰዋል፡፡

የንግድ ተቋማቱ የሚያመነጩት ገቢ የግለሰቦች መጠቀሚያ ከመኾኑ ባሻገር፣ በሀገረ ስብከቱ የቃለ ዐዋዲውን ሕግ እና መመሪያ ተደግፎ በታማኝነት ባለመሠራቱ በየወሩ ብር 100 ሚሊዮን፣ በዓመት ብር 1 ነጥብ 5 ቢልዮን ለራስ አገዝ ልማት መሰብሰብ ሲቻል እንደሚመዘበር ሓላፊው ገልጸዋል፡፡

በአማሳኝ ሓላፊዎች ላይ አስተማሪ እና ሕጋዊ ርምጃ በመውሰድ ብልሹ አሠራርን በወሳኝ መልኩ ለማረም እና ለማስወገድ፤ በመሪ ዕቅድ የሚመራ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው፣ ለለውጥ የተዘጋጀ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማደራጀት፤ ዘመኑን የዋጀ እና ወጥነት ያለው የፋይናንስ አያያዝ እና አጠቃቀም ሥርዐት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት በፓትርያርኩ የተጀመረው ጥረት በቅርቡ በተሳካ መልኩ ከዳር እንደሚደርስ ሓላፊው አብራርተዋል፡፡

“የጠቅላይ ቤተክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ ብዙ ከደከመበት ጥናታዊ ሪፖርት ጋር ተያያዞ በቅርቡ ኹላችንም በጉጉት የምንጠብቀውን ነገር እናያለን፤” ያሉት የጽ/ቤቱ ሓላፊ፣ “በአዲስ ዘመን፣ በአዲስ መንፈስ ቤተ ክርስቲያናችን የተሳካ አስተዳደራዊ የለውጥ ኹኔታ ይኖራታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ እናንተ ወጣቶች ስለኾናችኹ በሩ ክፍት ነው፤ ቅዱስነታቸውን አግዟቸው፤” ብለዋል፡፡

የተጀመረውን የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ለማዳከም እና ተቋማዊ ለውጡን ለማስቀረት “የተለያዩ ነፋሳት እየነፈሱ” እንዳሉ ያመለከቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች “ሕይወት የሚሰጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ነፋስ (መልእክት)” ብቻ ማድመጥ እና መከተል እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የካህናትም የምእመናንም መኾኗንና ልዩነቱ የሓላፊነት ድርሻ ብቻ እንደኾነ ያስረዱት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹ትውልዱ ዛሬ በሚሠራው ሥራ የታሪክ ተጠያቂም ተመስጋኝም በመኾኑ ወጣቶች አያገባችኹም አይባልም፤ የነገ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ናችኹ፤ በሞያችኹ፣ በዕውቀታችኹ የበለጸጋችኹ ስለኾናችኁ ትልቅ ሚና አላችኹ፤ ይኼን ጸያፍ ነገር አስወግደን የቤተ ክርስቲያንን ሕይወቷን፣ ልዕልናዋን እስክናስመልስ አብረን በጋራ መንቀሳቀስ አለብን፤›› በማለት የሰንበት ት/ቤቶቹን የሥራ አመራሮች አሳስበዋል፡፡

ፓትርያርኩ፣ ጭላንጭል ታይቶበታል ባሉት የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብቶች እና ጥቅሞች አሳልፎ በመስጠት አላግባብ የበለጸጉ የአድባራት ሓላፊዎች፣ ጥፋታቸው በሕግ አግባብ እየተመዘነ ክሥ እንዲመሠረትባቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ለሀገር አቀፉ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መቋቋም ሐሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት የቆየው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር÷ ሃይማኖት እንዲጠበቅ፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራር ተወግዶ ፍትሕ እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በየአጥቢያው በመደረግ ላይ ያለውን ንቅናቄ በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡ 

በቅርቡ የተካሔደው የሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፬ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የሀገረ ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጥያቄ የጋራ አቋሙ በማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን ንብረት ለምዝበራ በማጋለጥ ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያካበቱ አማሳኝ የአድባራት ሓላፊዎች በሀገሪቱ ሕግ እንዲጠየቁ ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ በውይይቱም ‹‹ባስፈለገው መንገድ ብንታዘዝ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ፈቃደኞች ነን፤ በሚያስፈልገው ነገር ኹሉ ከጎንዎት ነን፤›› በማለት ነው ያለውን ዝግጁነትና ጽናት ያረጋገጠው፡፡

SSS Demera
በተያያዘ ዜና፣
በውይይቱ ላይ ስለ ቀጣዩ ዓመት የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር በሰንበት ት/ቤቶች ስለሚቀርበው ዐውደ ትርኢት በስላይድ የተደገፈ ማብራሪያ የሰጡት የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ፣ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥላቸው ፓትርያርኩን ጠይቀዋል፡፡

የዋና ሓላፊው አቤቱታ መነሻ፣ ከነሐሴ ፳፬ ቀን ጀምሮ በአምስት ምድቦች ተከፍለው የቅድመ ዝግጅት ሥልጠና ለሚያካሔዱት ከ3000 በላይ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የሀገረ ስብከቱ አድባራት እና ገዳማት ተገቢውን የትራንስፖርት አበል እንዲመድቡ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለመጻፍ ዋና ሥራ አስኪያጁ እስከ አኹን ፈቃደኛ አለመኾናቸው ነው፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን የፀረ ሙስና አቋሞች በማራመድ እና የሀገረ ስብከቱንና የአጥቢያ አማሳኝ ሓላፊዎችን ፈቃድ በማስፈጸም መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የፀረ ሙስና ተጋድሏቸውን በአጥቢያው ካቀጣጠሉት ሰንበት ት/ቤቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት በውጥረት እና ግጭት የተሞላ ነው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የራሱ ቢሮ ላለው ለአንድነት አመራሩም ከሚሰጡት ድጋፍ ይልቅ በከንቱ ማስፈራሪያ እና መሠረተ ቢስ ክሥ የሚፈጥሩበት ዕንቅፋት ጎልቶ ይታያል፡፡

በመጪው ዓመት መስከረም አጋማሽ የግብጽ – ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ፣ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጎበኙ ሲኾን በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይም እንደሚታደሙ ተገልጧል፡፡ በበዓሉ ላይ ከሚቀርቡ ትዕይንቶች መካከል፣ በሊቢያ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ የተገደሉ ግብጻውያንና ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ሰማዕታትን በመዘከር እስከ 500 የሚደርሱ ሕፃናት የሚያሳዩት ዐውደ ትርኢት እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡

 

Advertisements

8 thoughts on “ፓትርያርኩ: አዲሱ ዓመት ቤተ ክርስቲያን በፀረ ሙስና እንቅስቃሴዋ ልዕልናዋን የምታስመልስበት ይኾናል

 1. Abebe beyene August 21, 2015 at 7:45 pm Reply

  በገጠር አቢያተክርስቲያናት ፈርሰው፣ተዘግተው ሙሰኛች ደግሞ በቤተክርስቲያኒቱ ገንዘብ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር ስትነግሩን ውስጣችን አዝኖ ነበር፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው እንደባለ እግዚአብሔር እያደረገልን ያለውን ነገር ስትግሩን በጣም ታላቅ ደስታ ነው፡፡ የቤተክርስቲያንን ትንሳዔ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብየም አሰብኩ፡፡
  ገ/ሥላሴ

 2. ኀይለገብርኤል August 21, 2015 at 7:48 pm Reply

  ዛሬም ህዝበ ክርስትያኑን ያታልላሉ እንዴ?

 3. Anonymous August 24, 2015 at 5:59 am Reply

  Really keep up our right wing !!!

 4. admasu August 25, 2015 at 12:33 pm Reply

  des bilonal abatachin lihonunew be ewonet des yilal endihi kehone

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: