የአንዳንድ አለቆች የመኪና ሽልማት በካህናትና በምእመናን ስም በሐሰት የተደረገ እንደነበር ጠቅ/ቤተ ክህነት አረጋገጠ

 • የቀድሞው የብሥራተ ገብርኤል፣ የመካኒሳ ሚካኤል እና የገርጂ ጊዮርጊስ አለቆች ተጠቅሰዋል
 • ከግለሰቦች ጋር የሕገ ወጥ ጥቅም ተጋሪ በመኾን አድባራቱን ለዕዳ የዳረጉ አለቆች ይገኙበታል
 • የመኪና እና የኮንዶሚኒየም ቤት ቁልፍ ሽልማት በፓትርያርኩ ሳይፈቀድ እንዳይሰጥ ተወስኗል
 • ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ጥንተ ክብሯ የሚመልስ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ይደረጋል ተብሏል

the corrupt Haile Abreha
በጥናታዊ ሪፖርቱ፣ ‹‹አስገራሚ እና ለምዝበራ የተመቸ›› በተባለ አሠራር፣ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ሳያውቁት፣ የልማት አርበኛ በመባል እና በስማቸው በማጭበርበር ጳጉሜን 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ዶልፊን መኪና የተሸለመው ቀንደኛው እና ልማደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ

በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት በቆየባቸው ዓመታት (ከ2002 – 2005 ዓ.ም.) ያለሀገረ ስብከቱ እና ያለ ሰበካ ጉባኤው ዕውቅና እና ፈቃድ ከጥቅመኛ ግለሰቦች ጋር በፈጸማቸው የብድር፣ የግንባታ እና የኪራይ ውሎች፣ ደብሩን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የባንክ እና ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የግለሰብ ባለዕዳ አድርጎታል፡፡

በአንጻሩ የብሥራተ ገብርኤል ኢንተርናሽናል ት/ቤት የተገነባበት ቦታ የተገዛበት የ12 ሚሊዮን ብር የሊዝ ክፍያ ባለመጠናቀቁ ደብሩ፣ በከተማው የመሬት ባንክ አስተዳደር ተጠያቂ ተደርጓል፡፡ ጥናታዊ ሪፖርቱ እንደሚለው፣ ‹‹የመሬት ባንክ አስተዳደሩ ደብሩን ለመክሠሥ በዝግጅት ላይ በመኾኑ የቦታው የይዞታ ዋስትና አሳሳቢ ነው፡፡››

ኹኔታውን በእጅጉ ምጸታዊ የሚያደርገው ግን፣ ግለሰቡ ያለተጠያቂነት ወደ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከተዛወረ በኋላም፣ የሀገረ ስብከቱም ዋና ሥራ አስኪያጅ ከኾነው ዋና ጸሐፊው ጋር ደብሩን ለብክነት እና ለዕዳ በሚዳርግ ተመሰሳሳይ የምዝበራ አሠራር ራሱን እያበለጸገ መኾኑ ነው!!!


(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ቅጽ 03 ቁጥር 117፤ ቅዳሜ ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2007 ዓ.ም.)

በአንዳንድ አድባራት እንደ ፋሽን የተያዘው የአለቆች የመኪና ሽልማትየቤተ ክርስቲያኒቱን ሰፋፊ መሬቶች እና የንግድ ተቋማት ከሕጋዊ አሠራር ውጭ በተቀራመቱ ግለሰቦች እና በአስተዳዳሪዎቹ መካከል በተፈጠረ የጥቅም ትስስር የተገኘ እንጂ የካህናትና የምእመናን ይኹንታ የተሰጠበት አለመኾኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አረጋገጠ፡፡

ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አመራር፣ የገንዘብና ንብረት አስተዳደር የበላይ ሓላፊ የኾነው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሀብት አላግባብ የበለጸጉ አለቆችን፣ ያለተጠያቂነት ከደብር ወደ ደብር ከማዘዋወርና በ‹ልማት አርበኝነት› ከመሸለም ይልቅ ችግራቸው ባሉበት ተረጋግጦ አስተዳዳራዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸውና በሕግም እንዲጠየቁ ወስኗል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት ለታለመለት ዓላማ ከማዋል ይልቅ ዘረፋ እና ምዝበራ ሲጧጧፍ በነበረባቸው አድባራት የሚሠሩ አለቆች÷ ምስጉን፣ ጠንካሮች፣ የልማት አርበኞች ተብለው እንደሚሸለሙ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የአስተዳደር ጉባኤ የተቋቋመውና በመኪና ሽልማት ችግሮች ዙሪያ ማጣራት ያካሔደው ኮሚቴ ባረቀበው ጥናታዊ ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

ለብልሹ አሠራር በር የሚከፍት የሽልማት ሥነ ሥርዐት እንዲቆም በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የተሰጠውን መመሪያ ያስታወሰው ኮሚቴው፣ በመኪና ሽልማቱ ወቅት የተሸላሚው አካል ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም ተገምግሞ፣ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና በፓትርያርኩ ተወስኖ እና ታምኖበት የተከናወነ ሽልማት ነው ወይ? የሽልማቱ ወጪ ከየት ተገኘ የሚሉት ነጥቦች መፈተሻቸውን ገልጧል፡፡

ኮሚቴው እንደታዘበው፣ በጥናቱ ከተዳሰሱት ከ58 ያላነሱ አድባራት እና ገዳማት ጥቂት በማይባሉት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ለሀገረ ስብከቱ የተላለፈው፣ የመኪና ሽልማትን የሚመለከተው የፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ አልተጠበቀም፡፡

እንደ ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ ከሙዳየ ምጽዋት ለመላቀቅ እና የካህናትን ሕይወት ለመቀየር ተብለው የተገነቡ ሱቆች፣ ሕንጻዎች እና የተከራዩ መሬቶች፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ በማያደርግ መልኩ ለሦስተኛ ወገን እየተከራዩና እየተሸጡ ጥቂት ግለሰቦች የአትራፊ አትራፊ ኾነውባቸዋል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰፋፊ መሬቶች እና የንግድ ተቋማት ያለጨረታ በተቀራመቷቸው ‹‹ስግብግብ ነጋዴዎች እና ነጋዴዎች በጥቅም በያዟቸው የአድባራት አለቆች እና የአስተዳደር ሠራተኞች እጅ ወድቀዋል፡፡›› መኪና ሽልማቱም ግለሰቦቹ ከእኒኽ የአድባራት ሓላፊዎች ጋር ከፈጠሩት የጥቅም ትስስር ጋር የተቆራኘ እንደኾነ ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

‹‹ለሽልማት በሚል ከአድባራቱ ሠራተኞች የወር ደመወዝ የሚሰበሰበው ለስሙ እንጂ መኪናው የሚገዛው በቅናሽ እና ከጨረታ ውጭ መሬት ወይም ሱቅ በተሰጠው ባለሀብት ገንዘብ ነው፤›› ያለው ሪፖርቱ፣ ‹‹በባለሀብት ገንዘብ በተገዛ መኪና ‹ካህናት እና ምእመናን ለበጎ ሥራቸውና ለልማት አርበኝነታቸው ሸልመዋቸዋል› ተብሎ ተሸላሚዎች ይኾናሉ›› ብሏል፡፡

የቦሌ ገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

በዚኽ ረገድ በኮሚቴው ጥናታዊ ሪፖርት ከተጠቀሱትና በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ከተገለጹት ሦስት አድባራት መካከል፣ የቦሌ ገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ ደብሩ 65 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሸንሽኖ በካሬ ሜትር ከብር 2 – 10 ድረስ ከጨረታ ውጭ ያከራየ ሲኾን የውል ዘመናቸውም ከሦስት እስከ ዘጠኝ ዓመት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ በቅናሽ ዋጋ የተከራዩ ሰዎች ለሦስተኛ ወገን በከፍተኛ ዋጋ በማከራየት ተጠቃሚዎች ከመኾናቸውም በላይ በተለያየ መንገድ መሬቱን በስማቸው የሚያዞሩበት አካሔድ ሊኖር እንደሚችልና ልዩ ክትትል እንደሚያሻው ተመልክቷል፡፡

የደብሩ አለቃ የመኪና ሽልማት የተሰጣቸው ሲኾን መኪናውን ለመሸለም ካህናቱና ሠራተኞቹ ገንዘብ ማዋጣታቸው በሓላፊው ቢገለጽም ካህናቱና ሠራተኞቹ ገንዘቡን ስለማዋጣታቸው በማስረጃ የተደገፈ ሰነድ ማቅረብ እንዳልቻሉ በሪፖርቱ ሰፍሯል፡፡ በማጣራቱ ሒደት እንደታወቀው፣ ለአለቃው የመኪና ሽልማቱን የሰጧቸው በደብሩ ክልል ሰፋፊ መሬት በአነስተኛ ዋጋ የተከራዩት ጥቂት ባለሀብቶች ሲኾኑ፣ ሽልማቱ አለቃው የሠሩት ሥራ ተመዝኖ፣ በሀገረ ስብከቱ ዕውቅና አግኝቶ በክብር የተሰጠ ሽልማት እንዳልኾነ ተገንዝቤአለኹ፤ ብሏል – ኮሚቴው፡፡

የመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ሌላው የመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሲኾን፣ ደብሩ ሠርቶ ከሚያከራያቸው 55 ሱቆች 50 ያኽሉ ቁልፋቸው የተሸጠ መኾኑን፤ 10 ያኽል ቦታዎች ለጋራዥ፣ ለብሎኬት ማምረቻ እና ለሌሎች አገልግሎቶች በካሬ ሜትር ከብር 10 – 25 ከጨረታ ውጭ በማመልከቻ መከራየታቸውን የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቀ መንበሩ እና ዋና ጸሐፊው በተገኙበት መረጋገጡን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ በካቴድራሉ ቀድሞ ለነበሩት አስተዳዳሪ፣ የመኪና ሽልማት የተሰጠ ሲኾን ለመኪናው ሽልማት አንድ በጎ አድራጊ ግለሰብ የሰጡት ገንዘብ ለመኪና ግዥ መዋሉ ተገልጧል፡፡

በሌላ በኩል ለሽልማቱ ከደብሩ ሠራተኞችና ካህናት መዋጮ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡ መኪናው በአንድ በጎ አድራጊ ምእመን ሲገዛ፣ ከካህናቱና ከሠራተኞቹ የተዋጣው ገንዘብ ለአለቃው ነዳጅ መሙያ በሚል በግል አካውንታቸው ገቢ ሲደረግ፣ ከዚኹ መዋጮ ላይም ለደብሩ ጸሐፊ ብር 20,000 ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ የቀድሞው አስተዳዳሪ የመኪና ሽልማት ሒደት፣ በካቴድራሉ የተሠሩ የልማት ሥራዎች በአግባቡ ተመዝነው፣ በማበረታቻነት መሰጠት ይገባዋል ተብሎ ታምኖበት፣ በምእመናን ፍላጎት፣ በፓትርያርኩ ፈቃድ እና ይኹንታ የተደረገ ባለመኾኑ ተገቢነት ያለው ኾኖ አልተገኘም ብሏል – ጥናታዊ ሪፖርቱ፡፡

የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

በሪፖርቱ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ከተጠቀሱት 15 አድባራት ተርታ በሚገኘው በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንየተሠሩ የልማት ሥራዎች ከደብሩ ይልቅ በሕገ ወጥነት ግለሰቦችን ለመጥቀም እና ሀብት እንዲያፈሩ በማድረግ የጥቅም ተጋሪ ለመኾን እንዲቻል ታስቦ የተሠራ መኾኑን ኮሚቴው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ኾኖም የደብሩ ትምህርት ቤት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ሕንጻዎች በተመረቀበት ዕለት ለቀድሞው አስተዳዳሪ የመኪና ሽልማት በአጥቢያው ምእመናን ስም ተሰጥቶ እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

በማጣራቱ ወቅት ያነጋገራቸው የሰበካ ጉባኤ አባላት ግን ሽልማቱን በተመለከተ የሚያውቁት እንደሌለና የአጥቢያው ምእመናን ለደብሩ አለቃ የመኪና ሽልማት ብለው ያዋጡትም ገንዘብ እንደሌለ መግለጻቸውን ጠቅሷል፡፡ እንደ ሪፖርቱ፣ የመኪና ሽልማቱ ለአለቃው የተሰጠው ወዳጃቸው በኾኑ ግለሰቦች ኾኖ ሳለ የአጥቢያው ምእመናን እንደሸለሟቸው ተደርጎ መገለጹ የሰበካ ጉባኤውን አባላት በእጅጉ አሳዘኗቸዋል፤ በሐሰት በምእመናን ስም የተደረገ ሽልማት በመኾኑም እንደሚቃወሙት አስታውቀዋል፡፡ ሽልማቱ በደብሩ ተሠራ የተባለው ሥራ ባልተገመገመበት፤ በካህናቱም ኾነ በምእመናኑ ይኹንታ ባልተሰጠበት የተደረገ በመኾኑ ብዙዎችን ቅር እንዳሰኘ ተወካዮቹ ለአጥኚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡

Bisrate Gabriel Int School
በደብሩ ከመንግሥት 10 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በብር 12 ሚሊዮን የሊዝ ክፍያ ተገዝቶ ትምህርት ቤት ቢገነባም በአኹኑ ጊዜ ለስድስት ዓመታት በውል ተከራይቷል፤ ውሉም ቀጣይነት ያለውና 95 በመቶ ለተከራዩ የሚወግን ነው፤ ብሏል ሪፖርቱ፡፡

በት/ቤቱ ኪራይ የሚገኘው ገቢ ቀደም ሲል ከተከራዩዋ ደብሩ የወሰደው ብድር እስከሚመለስ የሚታሰብ ኾኖ በውሉ ላይ ለመማር ማስተማር አስፈላጊ የኾኑ የማስፋፊያ ሥራዎች ሲሠሩ ከኪራይ የሚቀነስበት ውለታ በመኖሩ ተከራዮች የሚያከናውኑት የግንባታ ሥራ ኹሉ ተጨማሪ ዕዳ በመኾን ደብሩን ጥቅም አልባ አደርጎታል፡፡ በሌላ በኩል፣ መንግሥት ደብሩ ት/ቤት የገነባበትን ቦታ የገዛበትን ብር 12 ሚሊየን የሊዝ ክፍያ ተጠያቂ እያደረገውና የከተማዋ አስተዳደር የመሬት ባንክ አገልግሎት ደብሩን ለመክሠሥ በዝግጅት ላይ መኾኑ የቦታውን ይዞታ አሳሳቢ እንዳደረገው ተገልጧል፡፡

ቀደም ሲል ደብሩ የትምህርት ቤቱን ሥራ ለማስጨረስና ለማከራየት ብር 3 ሚሊዮን ከባንክ መበደሩን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ዕዳውን ለመክፈልም በወር ብር 107 ሺሕ ለባንክ እየከፈለ፣ ት/ቤቱን ከተከራዩት ግለሰብ ደግሞ የ1.5 ሚሊየን ብር ብድር በመውሰዱ ለተጨማሪ ዕዳ መዳረጉን አስታውቋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. ነሐሴ ወር መጨረሻ ተከራይዋ ከደብሩ ጋር በፈጸሙት ውል፣ በጨረታው ግዴታ መሠረት የ6 ወር ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው መግባት ሲገባቸው የ3 ወር ብቻ ከፍለው እንዲገቡ መደረጉን አውስቶ፣ ውሉም አጠራጣሪ ከመኾኑም በላይ በመዝገብ ቤት ተያይዞ የሚገኘው ፎቶ ኮፒው ነው፤ ብሏል፡፡

ተከራይዋ ት/ቤቱን ተከራይቼበታለኹ ብለው ያቀረቡት ውል እርሳቸው እና በወቅቱ የነበሩት የደብሩ ሓላፊ የፈረሙት ካልኾነ በቀር፣ የምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት እና የካህናት ተወካዮች ያልፈረሙበት ከመኾኑም በላይ በደብሩ መዝገብ ቤት አለመገኘቱ፤ ከዚኽ በፊት የተገባው ውልም በነበሩት የደብሩ ሓላፊ ቲተር እንጂ በደብሩ ክብ ማኅተም ያልተረጋገጠ መኾኑ ተደማምሮ ከት/ቤቱ ጋር ተያይዞ ያለው የኪራይ፣ የብድር እና የውል ስምምነት ኹኔታ በእጅጉ አጠራጣሪ እንደሚያደርገው፤ ደብሩም በችግር ውስጥ መኖሩን እንደሚያመላክት ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ለት/ቤት ግንባታ ማስፈጸሚያ በሚል ከባንክ በሚበደርበት ወቅት ሀገረ ስብከቱ እንዲያውቀው አለመደረጉም አግባብነት እንደሌለው አስቀምጧል፡፡

Bisrate Gabriel bld00
በደብሩ የተገነባው ባለሦስት ፎቅ ሕንጻ የግንባታ ሥራው ሳይጠናቀቅ፣ የወጣው ወጪ እና አጠቃላይ የግንባታ ሥራው በባለሞያ ታይቶ ሳይረጋገጥ በብር 25 ሺሕ ከ6 እስከ 10 ዓመትና ከ10 ዓመት በኋላ እስከ 50 ሺሕ ብር እንዲከራይ መደረጉ በጣም የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ነው፤ ያለው ሪፖርቱ፣ ብሥራተ ገብርኤልን በመሰለ ቦታ ይህን ያኽል ሕንጻ በዚኽ ዋጋ መከራየቱ ተገቢ እንዳልኾነ ተችቷል፡፡ ከኹሉ የሚገርመው ይላል ሪፖርቱ፣ ‹‹ሕንጻውን የተከራዩት ግለሰብ ምድር ቤቱን ብቻ ለባንክ 400 ብር ለማከራየት በመደራደር ላይ መኾናቸው ነው፡፡››

ሕንጻው የተከራየበት ዋጋ ያልተዋጠላቸው በአገልግሎት ላይ ያለው የሰበካ ጉባኤ አባላት ተከራዩን በማግባባት ኪራዩን ወደ ብር 50 ሺሕ ከፍ እንዲል ማድረጋቸውን ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ ‹‹ከዚኽ በላይ እንዳይኬድ በወቅቱ የተሰጠው ውል ግለሰቡን እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚጠቅም ባለመኾኑ ምንም ማድረግ አልተቻለም›› ብሏል፡፡

በአጠቃላዩም፤ በደብሩ የተሠሩ የልማት ሥራዎች በሕጋዊ መንገድ ደብሩን ሊጠቅሙበት በሚችሉበት አኳኋን እንዳልኾነ ገልጾ፣ በሕገ ወጥነት ግለሰቦችን ለመጥቀምና ሀብት እንዲያፈሩ በማድረግ በዚኽ የጥቅም ተጋሪ መኾን እንዲቻል ታስቦ የተሠራ መኾኑን ኮሚቴው መታዘቡን በከፍተኛ አጽንዖት አስቀምጧል፡፡

መልካም የሠራውን መሾሙና መሸለሙ ተገቢና ትክክለኛ ቢኾንም፣ በሀገረ ስብከቱ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት የሚከናወነው የመኪና ሽልማት፥ ግልጽ መመሪያ በሌለበት፣ የሥራ ውጤታቸው ያልተረጋገጠ ግለሰቦችን ከለላ የሚሰጥና ለብልሹ አሠራር በር የሚከፍት እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ በመኾኑም እንደ ፋሽን የተያዘው የመኪና፣ የኮንዶሚኒየም ቤት ቁልፍ እና የሌሎች ሽልማቶች ጉዳይ በሕግና በሥርዐት እንዲመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ጥናታዊ ሪፖርቱ፤ መኪናም ኾነ የኮንዶሚኒየም ቤት ቁልፍ ሽልማት ከመሰጠቱ በፊት የተሸላሚው እያንዳንዱ ሥራዎቹ ተገምግመውና ሽልማት የሚገባው መኾኑ ሲታመንበት ከሽልማቱ ጊዜ በፊት በቅዱስ ፓትርያርኩ ሲፈቀድ ከሚሰጥ ውጭ መሸለም እንደማይገባ ዘርዝሯል፡፡

ፓትርያርኩ ለሐዋርያዊ አገልግሎትና ለአብያተ ክርስቲያናት ምረቃ በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ከዕውቅናቸው እና ከፈቃዳቸው ውጭ እንዲሰጡ የሚቀርቡ የመኪናም ኾነ የኮንዶሚኒየም ቤት ቁልፍ ሽልማት ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ በጥናታዊ ሪፖርቱ የቀረበውን ሐሳብ በሙሉ ድምፅ የተቀበለው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የአስተዳደር ጉባኤ፣ የሽልማቱ አካሔድ፣ የአጥቢያዎችን ጥያቄና ስለ ሽልማቱ አግባብነት ለሀገረ ስብከቱ የሚያቀርቡትን የአለቃውን የክንውን ሪፖርት መነሻ አድርጎ በአስተዳደር ጉባኤው ሲጸድቅ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲቀርብ እና ቅዱስ ፓትርያርኩ ሲያምኑበት ብቻ ተፈጻሚ እንዲኾን መወሰኑ ታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤው፣ በኮሚቴው የቀረበውን ጥናታዊ ሪፖርት መነሻ ያደረገ ጠንካራ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ወደ ጥንቱ ጊዜ ለመመለስ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጎን በመቆም እና ተናቦ በመሥራት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ለመኾን ወስኗል፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ ሀብት አላግባብ የበለጸጉ የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ‹‹የወረደ ዋጋ ለቤተ ክርስቲያን እንዲከፈል እያደረጉ ዘመናዊ መኪና፣ ዘመናዊ ቤትና ፋሽን አመጣሽ ልብስ ለብሰው ሲሽከርከሩ፣ ሆቴል አማርጠው ሲዝናኑ መመልከት የከተማዋ የዘወትር የውሎ ገጽታ ኾኗል›› ሲል የኹኔታውን አሳሳቢነት ጠቅሷል፡፡ ከደብር ደብር ያለተጠያቂነት ሊዘዋወሩ እንደማይገባ የተወያየው አስተዳደር ጉባኤው፣ ሓላፊዎቹ እና ሠራተኞቹ ችግራቸው ባሉበት ተረጋግጦ አስተዳደራዊ ርምጃ ሊወሰድባቸው በሕግም ሊጠየቁ ያስፈልጋል የሚሉ መደምደሚያዎች ላይ መደረሱ ተገልጧል፡፡

Advertisements

4 thoughts on “የአንዳንድ አለቆች የመኪና ሽልማት በካህናትና በምእመናን ስም በሐሰት የተደረገ እንደነበር ጠቅ/ቤተ ክህነት አረጋገጠ

 1. kibrekdusa22w@gmail.com August 21, 2015 at 1:38 am Reply

  ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ለማስጠበቅ የበኩላችን አሰtዋጽዖ ለማድረግ እንረባረብ ::
  ስለመረጃችሁ እውነታነት አንደኛው ምስክር እኔ ነኝ ባለሁበት ደብር የተደረገውን በትክክል መረጃውን ማውጣታችሁ ልቤ እንዲተነፍስ አድርጋችኃልና ቀጥሉበት የዕውነት ባለቤት ፈጣሪ ይርችሁ፡፡

 2. sss August 21, 2015 at 1:47 pm Reply

  Ewunete tanagerachihu mutu

 3. sss August 21, 2015 at 1:48 pm Reply

  Lehulum ekule hunu

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: