የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ምእመናን አስተዳዳሪውን አስጠነቀቁ፤ በሀገረ ስብከቱ ዳተኛነት ተመርረዋል

Debra Sina EgzeabhareAb Church

በመሠራት ላይ የሚገኘው የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን

 • አስተዳዳሪው ለጥያቄዎቻቸው በሳምንት ውስጥ ምላሽ ካልሰጡ ችግሩ እንደሚባባስ አሳስበዋል
 • ሰበካ ጉባኤው ጥያቄ በማንሣቱ በአለቃው ተበትኗል፤ ምክትል ሊቀ መንበሩንም አግደዋል
 • የክ/ከተማው ፖሊስ አስተዳደሩን ከሰበካ ጉባኤውና ከምእመናኑ ጋር እንደሚያወያይ ተጠቁሟል

(ሰንደቅ፤ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፲፯፤ ሐምሌ ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

በመንፈሳዊ እና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ነን ያሉ የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ ለደብራችን ግልጽ የሰላም ዕጦት አፋጣኝ መፍትሔ አልሰጠንም ባሉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዳተኛነት መማረራቸውን ገለጹ፤ የደብሩን መንፈሳዊ አገልግሎት እና ልማታዊ ሥራዎች እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ከመባባሳቸው በፊት ለአስተዳዳሪው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጡ፤ ጥያቄዎቻቸውን በሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲመልሱላቸውም አሳሰቡ፡፡

የተለያየ መጠሪያ ባላቸው ዘጠኝ የጽዋ እና የሰንበቴ ማኅበራት በርካታ ምእመናንን በማቀፍ ደብሩን በበላይነት ከሚያስተዳድረው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መመሪያ እየተቀበሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን በማገልገል ላይ እንዳሉ የገለጹት ጠያቂዎቹ፣ ዕንቅፋቶቹ በግልጽ መከሠት ከጀመሩበት ካለፈው ግንቦት አጋማሽ አንሥቶ ከኹለት ወራት በላይ ትልቁን ሓላፊነት ወስዷል ላሉት ለሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ሲያሳስቡ መቆየታቸውን አውስተዋል፤ ይኹንና የተስፋ ቃላት ከመመገብ በቀር አፋጣኝ ርምጃ ባለመወሰዱ ‹‹የደብራችን ችግር እየተባባሰ እና ምእመናንንም ግራ እያጋባን ይገኛል፤›› ሲሉ ወቅሰውታል፡፡

የምእመናን ማኅበራቱ፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ለደብሩ አስተዳደሪ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ (ultimatum) የሰጡባቸው ባለሰባት ነጥብ ጥያቄዎቻቸው÷ አስተዳደርን፣ የገንዘብ ፍሰትን፣ የይዞታ ማስከበርንና የአጥማቂዎች ሥነ ምግባርን የተመለከቱ ሲኾኑ እኒኽም ከሰበካ ጉባኤው ሥልጣንና ሓላፊነት፣ ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው እንቅስቃሴ እና ከሰንበት ት/ቤቱ አገልግሎት ጋር የተያያዙ የግልጽነት እና የተጠያቂነት ጉዳዮች እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡

Egziabehar AB letterበጥያቄዎቹ እንደተመለከተው፣ በማኅበረ ካህናት እና በማኅበረ ምእመናን ምልአተ ጉባኤ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር የተመረጠው እና ደብሩን በበላይነት የሚመራው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በአስተዳዳሪው መልአከ ሰላም አባ ገብረ ሚካኤል ወልደ ሳሙኤል እንዲበተን የተደረገ ሲኾን ምክትል ሊቀ መንበሩም ያለምእመናን ዕውቅና እንዲሰናበቱ ተደርገዋል፡፡ ይኸውም አስተዳዳሪው፣ ለአዲሱ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥራ ከአንዲት በጎ አድራጊ በተለያዩ ጊዜያት የተሰጧቸውን ከሩብ ሚልዮን በላይ ገንዘብ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሒሳብ ገቢ ባለማድረጋቸው ቃለ ዐዋዲውን በመፃረር በሌላቸው ሥልጣን የወሰዱት ሕገ ወጥ ርምጃ መኾኑ ተገልጧል፡፡

የደብሩ ዋና የገቢ ምንጭ የሙዳየ ምጽዋት አስተዋፅኦ መኾኑን ምእመናኑ ጠቅሰው፣ አለመግባባቱን ተከትሎ ሰበካ ጉባኤው የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ የተያዘበትን ቃለ ጉባኤ ከባንክ መግለጫ ጋር በማነፃፀር የገንዘብ እንቅስቃሴውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ቃለ ጉባኤዎቹ እንዲቀርቡለት ቢጠይቅም በአስተዳዳሪው ተከልክሏል ብለዋል፡፡

ለአዲሱ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የውስጥ ግድግዳ ሥዕሎችን ለማሣል ጨረታ በይፋ ወጥቶና አሸናፊው ሠዓሊ በዐውደ ምሕረት ተገልጾ ለክፍያው በምዝገባ የገንዘብ አስተዋፅኦ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ሒደቱ መቋረጡን ምእመናኑ ጠቁመው፣ በምን ምክንያት እና እንዴት ተቋረጠ ሲሉ ምክንያቱን ማወቅ እንደሚሹ ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ግን፣ ሠዓሊው ባሸነፈው ጨረታ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአለቃው እስከ ብር 200,000 ጉቦ እንዲከፍል መጠየቁንና ፈቃደኛ ባለመኾኑ በውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብ በመንሥኤነት ይጠቅሳሉ፡፡

የደብሩ እግዚአብሔር አብ አንደኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት የጎደሉትን ነገሮች ለማሟላት ዘጠኙ የጽዋ እና የሰንበቴ ማኅበራት እያንዳንዳቸው ብር 11,000 ቢከፍሉም፣ ‹‹አንድም ሥራ ግን በአግባቡ አልተሠራም›› ያሉት ምእመናኑ፣ ያዋጡት አንድ መቶ ሺሕ ያኽል ገንዘብ ምን ላይ እንደዋለና ሥራውም ለምን እንዳልተሠራ ይገለጽልን ሲሉ ነው የጠየቁት፡፡

ከቤተ ክርስቲያኑ ቤተ ልሔም ጀርባ በሚገኝ የደብሩ ይዞታ ላይ ግለሰቦች ቤት ሠርተው፣ መጸደጃ ቤትም አስቆፍረው እንዲኖሩ መደረጉ ሥርዐተ እምነቱን እያወከ እና በቀጣይም የይዞታ ማስከበር ችግር እንደሚፈጥር ያሰፈሩት ምእመናኑ፣ ስለተፈጸመው ድርጊት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በደብሩ የጠበል ማጥመቅ አገልግሎት ሴት ምእመናት ችግር እየገጠማቸው እንዳለና መፍትሔ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም አስተዳደሩ ተገቢ ርምጃ አለመውሰዱ ሌላው የምእመናኑ ጥያቄ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተተከለበት ከ፲፱፻፷፱ ዓ.ም. ጀምሮ የተመሠረተው የደብሩ ሰንበት ት/ቤት፣ ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ጋር ተግባብቶ እንደሚያገለግል ምእመናኑ አውስተዋል፡፡ ይኹንና ‹‹ሰበካ ጉባኤው ተበትኖና እንዳይሠራ ተደርጎ የነገ ተተኪና ተረካቢ የኾኑት ልጆቻችን በሃይማኖታቸውና በሥነ ምግባራቸው ጠንክረው የሚወጡበት ተቋም እንዴት በአስተዳዳሪው ብቻ ሊጎለብት እና ሊሻሻል ይችላል?›› በማለት ስጋታቸውን አመልክተዋል፡፡

በሐምሌ ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ተመርጦ ለሦስት ዓመት ካገለገለ በኋላ በአስተዳዳሪው እና በሰበካ ጉባኤው ጥያቄ ለኹለተኛ ጊዜ እንዲቀጥል የተፈቀደለት የሰንበት ት/ቤቱ አመራር፣ አስተዳዳሪው ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው እና ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ጋር ውዝግብ ውስጥ ከመግባታቸው ጋር በተያያዘ ከመተዳደርያ ደንቡ በተፃራሪ ያለወቅቱ በአዲስ ምርጫ ለመቀየር በአለቃው እየተፈጸመ ነው ባሉት የአፈርሳለኹ ድርጊት ላይ አስተዳደሩ ማብራሪያ እንዲሰጥበትም አመልክተዋል፡፡

የደብሩ የአስተዳደር እና የአገልግሎት መዋቅሮች ከምእመናንም የተውጣጡ የምእመናን አካላት እንደ መኾናቸው ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉት የምእመናኑ የጽዋ እና የሰንበቴ ማኅበራት፣ የደብሩ ሰላም ተመልሶ መንፈሳዊ አገልግሎቱንና ልማታዊ ሥራውን በተረጋጋ መልኩ ለመቀጠል ይችል ዘንድ አስተዳዳሪው እስከ ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ባለው የሳምንት ጊዜ ውስጥ ለጥያቄዎቻቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጧቸው አስጠንቅቀዋል፤ ‹‹ጥያቄአችን በበጎ ታይቶ ምላሽ ካልተሰጠን የደብሩ ችግር አኹን ካለበት ወደባሰ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለን፤›› ሲሉም አስተዳዳሪውን አሳስበዋቸዋል፡፡

የማኅበራቱ ጥያቄ በግልባጭ ከደረሳቸው አካላትና የችግሮቹ ወቅታዊ መፍትሔ አለማግኘት አሳስቦታል የተባለው የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ፣ የሀገረ ስብከቱ ልኡክ በተገኙበት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን፣ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን የሰንበት ት/ቤቱን ከደብሩ አስተዳደር ጋር ለማግባባት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጧል፤ ከአካባቢው ሰላም አኳያ በነገውም ዕለት የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ውይይት እንደሚያካሒድ ተጠቁሟል፡፡

ከ38 ዓመት በፊት በድርብ ከነበረበት የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መጥቶ የተተከለው የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ፣ ከ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ መልክ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በሙዳየ ምጽዋት የሚሰበሰበውን ገንዘብ በአግባቡ በመጠቀም እና የራሳቸውን አስተዋፅኦ በማከል ሥራው አኹን ለሚገኝበት ደረጃ ያበቁት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው አባላት ትጋት እና ታማኝነት በአጥቢያው ምእመናን የሚጠቀስ ነው፡፡

ይኹንና በሰላማዊነቱ የሚታወቀው አጥቢያ በተለይ ካለፈው ግንቦት አጋማሽ ወዲኽ ሰላም እና መረጋጋት ተስተጓጉሎ ‹‹በፖሊስና በጸጥታ አካላት እየተጠበቀ ነው›› የሚሉት ማኅበራቱ፣ ምእመናንንና ካህናትን ከሀገረ ስብከት እና ከፖሊስ ጋር በበሬ ወለደ ቅጥፈት በማጋጨት የተጠመዱትን አስተዳዳሪውን ዋነኛ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

አንዱን ከሌላው በማበጣበጥ ድርጊታቸው ከተጠያቂነት ለመሸሽ እየሞከሩ ያሉት ምግባረ ብልሹው አስተዳዳሪ፣ ‹‹አይነካኝም›› በሚሉት በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ትምክህታቸውን አድርገዋል፡፡ የሙስናንና የኑፋቄን ትስስር በሚያረጋግጥ መልኩ በሃይማኖት ሕጸጽ ጥያቄ የሚነሣባቸውንና ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በአጋርነት ያሰለፉ ሲኾን ከጽ/ቤታቸው የሚወጡ ደብዳቤዎች በመጠቀም በሰበካ ጉባኤው፣ በሰንበት ት/ቤቱ እና በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በመልካም ሥራቸው የሚታወቁ ምእመናንን ስም በማጥፋት ተጠምደዋል፡፡

ከሰበካ ጉባኤው ዕውቅናና ከበላይ አካላት መመሪያ ውጭ በሌለ በጀት ‹‹ደመወዝ አስጨምራለኹ፤ አስቀጥራለኹ›› እያሉ ጉቦ በመቀበል የሚያንገላቷቸውን ማኅበረ ካህናት በተደጋጋሚ በመሰብሰብ፣ ‹‹ሰበካ ጉባኤው እንዲወርድ ቃለ ጉባኤ ይያዝ›› ቢሉም ካህናቱ፣ ‹‹ሰበካ ጉባኤው በሕዝብም የተመረጠ ነው፤ እኛ ብቻችንን ማፍረስ አንችልም፤ ሕንፃ አሠሪዎቹም ደጋግ ሥራ እየሠሩ ያሉ ናቸው›› ብለው በመቃወማቸው አልተሳካላቸውም፡፡

በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌዎች መሠረት ሰበካ ጉባኤው የተጠያቂነት ጉዳዮችን በማንሣቱ የተጠናከረው እንቅስቃሴ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ ቀጥሎ ከጸሎተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ አስተዳዳሪው በጽሑፍ ለደረሷቸው የምእመናኑ ጥያቄዎች በዐውደ ምሕረት ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠበቁም አልተገኙም፡፡ በማኅበራቱ በተመረጡ ሽማግሌዎች መሪነት በተካሔደ ውይይት አስተዳዳሪው እስከ መጪው እሑድ በምእመኑ ፊት ቀርበው ምላሽ የሚሰጡበት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል – ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን ሰላሟ ተመልሶ መንፈሳዊ አገልግሎቱ እና ልማታዊ ሥራዎች በተረጋጋ መልኩ መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለን በማመን የደብሩ አስተዳዳሪ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡባቸውን ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡ ጥያቄአችን በበጎ ታይቶ በጠየቅነው ጊዜ ምላሽ ካልተሰጠን የደብሩ ችግር አኹን ካለበት ወደባሰ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ያለን መኾኑን አበክረን እንገልጻለን፡፡››

6 thoughts on “የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ምእመናን አስተዳዳሪውን አስጠነቀቁ፤ በሀገረ ስብከቱ ዳተኛነት ተመርረዋል

 1. Tazabi August 6, 2015 at 12:35 pm Reply

  The biggist treat to development in Ethiopia is religion-especially the orthodox church. Money is the one only thing that drives the adminstrators no matter who they are. One advice to all orthodox, DO NOT GIVE MONEY TO THE CHURCH !!!!!!!

 2. getachew August 6, 2015 at 2:27 pm Reply

  This is quite right and fact news. i am a witness and i know this debr and Sunday school before 10 years ago. i live in outside addis now but i am member of the Sunday school. i was in addis three weeks ago and i shocked by the issues i have seen during sunday school elections and conflict between members and the leader, who have many illegal practice in the church and i have evidence.

 3. Anonymous August 6, 2015 at 3:59 pm Reply

  በቤተክርስቲያናችን በሰማዕትነት ባለፉ ድንቅ የተዋህዶ ፈርጦች፤ ለዕምነታቸውና ለምዕመኖቻቸው ሲሉ ሂወታቸውን መሰዋት ባደረጉ የዕምነትና የሀገር ምርጥ አባቶች ቦታ በዘመናችን የተቀመጡ የቤተክርስቲያኒቷ የጊዜው አለቃዎች ይህን ሰማያዊ የቅድስና የአገልግሎት ቦታ ለመቀራመትና ለመዝረፍ ለአንድ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪ ለመሆን መነሻ ብር 50 ሺህ፣ ድቁና ለመቀበል መነሻ ብር 35 ሺህ፣ ለዝውውር መነሻ ብር 30 ሺህ፣ ለጵጵስና መነሻ ብር 300 ሺህ፣ ለዋና ጸሐፊነት መነሻ ብር 80 ሺህ፣ ለኮቴ እንደ ቦታው ገበያ ሁኔታ በአደባባይ ተመን አስቀምጠው ቤተክርስቲያኒቷን እንደ አልባሌ ሸቀጥ ሲቀራመቷትና ሲሻሻጡባት ማየትና መስማት የእኛ ትውልድ እጣ ፈንታ ለመሆኑ ምን ይሆን የቃሉ ፍጻሜ ይሆን እንዴ በጣም በጣም በጣም ግራ ያጋባል፡፡

  በቀጥታ የመንግስት እጅም በእያንዳንዱ የዝውውር፣ የሹመት፣ የሽያጭ ተግባር እጁ እንዳለበት ማየት መስማት ለስልጣንም ለሀገርም አይበጅም፡፡ የቁልቢን ገቢ የሚቀራመተው መከላከያው ነው ሲባል ቀልድ ይመስለን ነበር፡፡ ለካስ እውነታው ግልጽ የሆነልን እዚሁ ርዕሰ ከተማው በሚደረገው በህጋዊው የመንግስት አስተዳደር መዋቅር የቤተክርስቲያኒቱን የሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅነትና ጵጵስና ሹመት መደብ ደልደላ መሆኑ ነው፡፡ ከሰባት አመት በፊት ከክፍለ ሀገር የመጣ አንድ ቄስ አሁን እዚህ አዲስ አበባ በዶልፊን ገበያ ሲደራደር ያየ ደላላ ሰውዬው ቀጥሎ በጉልላቱ ሊደራደር ተመልሶ እንደሚመጣ አትጠራጠሩ ያለው ለካ የወደፊቱ ታይቶት ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: