ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ: በዓለም ልዩ አድናቆት ላላት ሀገር ባለቤት እንድንኾን ያስቻለን ሃይማኖታችን እንደኾነ ከቶ ሊዘነጋ አይገባም

His Holiness Abune Mathias

በዚኽ የጾም ወቅት ያዘኑትን በማጽናናት፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጎሳቆሉትን በመደገፍ፣ ፍጹም ርኅራኄን ለወገኖቻችን በማሳየት አካሔዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ አለብን፡፡ በአኹኑ ጊዜ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የዝናም እጥረት እንዳለ እየተሰማ ስለኾነ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ሱባዔ በየቤተ ክርስቲያኑ እየተገኘ የምህላ ጸሎት በማድረስ ፈጣሪውን በሐዘንና በጸሎት እንዲለምን፣ ቅድስት ድንግል ማርያምንም እንዲማፀን መልእክታችንን ከአደራ ጭምር እናስተላልፋለን

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጾመ ፍልሰታን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የምትገኙ፣ የእግዚአብሔር እና የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች ምእመናን እና ምእመናት፣ እንኳን ለ፳፻፯ ዓ.ም. የቅድስት ድንግል ማርያም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር = ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች›› (ሉቃ.1፡47)

ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት አካላዊ ቃለ እግዚአብሔርን ከፀነሰች በኋላ ወደ ቅድስት ኤልሳቤጥ ቤት ገብታ ሰላምታ ባቀረበች ጊዜ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ያለው ፅንስ በድንግል ማርያም ማኅፀን ላለው ፅንስ ከመስገዱም በተጨማሪ ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብፅዕና በሰፊው መናገሯ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል (ሉቃ.1፡45)፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር በቅዱስ ገብርኤል እና በቅድስት ኤልሳቤጥ በኩል ያስነገረላትን ታላቅ ክብር እና ሞገስ በማድነቅ እግዚአብሔርን በከፍተኛ ደረጃ አመሰግናለች፤ ደስታዋንም ገልጻለች፡፡

ከዚህ ከቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና የምንማረው ዓቢይ ትምህርት፣ እግዚአብሔር በየጊዜው ያደረገልንን መልካም ነገር ኹሉ በማሰብ ለእርሱ አምልኮ እና ምስጋና ማቅረብ ያለብን መኾኑን ነው፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት በዚህ ክፍል በእርስዋ እና በክርስቲያኖች መካከል ያለው የዘላለም ግንኙነት እና ትስስር ምን ዐይነት ገጽታ እንደሚኖረው በትንቢት ተናግራለች፤ እርሱም ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል›› የሚል ነው (ሉቃ.1፡48)፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

በኹሉም ዘንድ እንደሚታወቅ፣ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ቃለ እግዚአብሔርን መጠበቅ እና ማስጠበቅ እንደኾነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከተናገራቸው ኃይለ ቃላት መካከል፣ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ኹሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ባለሟልነትን አግኝተሻል፤ ጸጋን የተመላሽ ነሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው›› የሚሉት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው፤ (ሉቃ፡ 1፡ 28-30) በተለይም ‹‹ትውልድ ኹሉ ብፅዕት ይሉኛል›› የሚለው ቃል በቅድስት ድንግል ማርያም አንደበት የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

ይህ የእግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምንና ምእመናንን እስከ ወዲያኛው ያስተሳሰረ የቃል ኪዳን ሐብል ነው፡፡ በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አምስት ቀን በጾም፣ በጸሎት፣ በአምልኮ፣ በምስጋና፣ በንሥሐ እና በቊርባን ለእግዚአብሔር መገዛታችንና ቅድስት ድንግል ማርያምን መማፀናችን፣ ባለሟልነትን አግኝተሻል የሚለውን ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ባለሟል ማለት በባለሥልጣን ዘንድ ተሰሚነት፣ ተደማጭነት፣ ተቀባይነት ያለው፣ ቀራቢ ልዩ ወዳጅ ማለት እንደኾነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

በዚኽ መሠረት ቀደምት ቅዱሳን አበው እና ነቢያት በባለሟልነታቸው በሕይወት እያሉም ኾነ ከሞቱ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ኾነው እግዚአብሔርን እየተማፀኑ፣ እየማለዱ እና እየለመኑ ሰውን ያስምሩ እንደነበር ተጽፎአል፤ (ኦ.ዘጸ. 32፡ 11-14፤ መጽ. ኢዮ. 42፡ 7-9፤ ነገ.ቀዳ. 11፡ 10-13)፡፡ እንደዚኹም ኹሉ ቅድስት ድንግል ማርያም በባለሟልነቷ ብቻ ሳይኾን እርሱን ፀንሳ የወለደች እና ያሳደገች የጌታችን እናት እና ልዩ ባለሟል በመኾኗ በጸሎትዋ፣ በልመናዋ እና በአማላጅነቷ አምነን ስንማፀናት እኛን ታስምራለች ብለን እናምናለን፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ልመና ተቀባይነት ያለው ስለመኾኑ በቃና ዘገሊላ የሠርግ ቤት ያቀረበችው ምልጃ እና ልመና በኹኔታውም የተገኘው ውጤት ለእኛ በቂ ማስረጃችን ነው፤ (ዮሐ. 2፡ 1-9)

ከዚኽም ጋር ራሱ ጌታችን በመስቀል ላይ ኾኖ እርስዋን የእኛ እናት አድርጎ፣ እኛንም የእርስዋ ልጆች አድርጎ መስጠቱ ልጅ የሚፈልገውን ነገር ከእናቱ እንደሚሻ ኹሉ እኛም የምንሻውን ነገር ታሰጠን ዘንድ እንድንማፀናት ነው፡፡

እናትም አዛኝ፣ ርኅርኅት፣ ተቆርቋሪ፣ አሳቢ ኾና ለልጇ እንደምትጨነቅ እርስዋም ለእኛ አዛኝ፣ ርኅርኅት እና ተቆርቋሪ በመኾን ዘወትር ስለ እኛ እርሱን እንድትለምንልን ነው፡፡ ከዚኽ ውጭ ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን መሠረታዊ ትምህርት ተገንዝበውና የቅድስት ድንግል ማርያምን እናትነት ተቀብለው እርስዋን ለማግኘት ሲሉ በዚኽ ወር በመጾም እና እርስዋን በመማፀን ልጅነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣውና የተላውያነ ሐዋርያት ትምህርትን በምልአት የተረዳው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሎአል፤ ‹‹ወይብሉ ኵሎሙ ሐዋርያቲሁ ለእግዚእነ ሰአሊ ለነ ማርያም እምነ፤ የጌታችን ሐዋርያት ኹሉ፣ እናታችን ማርያም ሆይ፣ ለምኝልን ይላሉ›› በማለት በድጓው በብዙ ቦታ ላይ ጽፎአል፡፡

ጥንታዊው የሐዋርያት ትምህርት፣ ትውፊት እና ባህል ያልተለያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከጌታችን እና ከሐዋርያት የተቀበለችውን ሁሉ ሳትሸራርፍ እንዳለ ይዛ እነኾ እስከ አኹን ድረስ የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር እና ብፅዕና እንደ ቃሉ ጠብቃ እየተጓዘች ነው፡፡ ለዚኽም ዛሬ የምንጾመው የ፳፻፯ ዓ.ም. የቅድስት ድንግል ማርያም ጾም ምስክር ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

የሀገራችን ታላቅነት እና ነጻነት፣ አንድነት እና ሉዓላዊነት፣ ታሪክ እና ባህል፣ ቅዱስ ሥነ ምግባር እና ሌላውን ጸጋ ኹሉ ጠብቆ በማስጠበቅ ዛሬ በዓለም መካከል ልዩ አድናቆት ላላት ሀገር ባለቤት እንድንኾን ያስቻለን ይህ ሃይማኖታችን እንደኾነ ከቶ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ አኹንም ከአባቶቻችን የወረስነውን መልካም ዕሴት ለቀጣዩ ትውልድ በአስተማማኝ ለማስተላለፍ የሃይማኖታችንን ዕሴቶች ኹሉ በሚገባ መጠበቅ ይገባናል፡፡

‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም›› እንደተባለው ኹሉ ከሃይማኖታችንና ከባህላችን እንደዚኹም ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ እና ከሕገ ተፈጥሮ ውጭ የኾነውን ነውረ ኃጢአት ከሌላው ሀገር ወደ ሀገራችን ለማጋባት የሚደረገው ተጽዕኖ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናንና ኹሉም ኢትዮጵያውያን አምርረው ሊታገሉትና ሊመክቱት ይገባል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ እኛ ‹‹እጆቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ይዘረጋሉ›› ተብሎ የተነገረልን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነን፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ የነውረ ኃጢአት ተገዥ ሊኾን ከቶ አይችልም ብለን በጽናት መቋቋም ይኖርብናል፡፡

ጾም የተፈጠረው ከነውረ ኃጢአት ለመራቅ፣ በንጽሕና እና በቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ለሰው ኹሉ የርኅራኄ እና የፍቅር ሥራ ለመሥራት ነው፡፡

በመኾኑም በዚኽ የጾም ወቅት ያዘኑትን በማጽናናት፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጎሳቆሉትን በመደገፍ፣ ፍጹም ርኅራኄን ለወገኖቻችን በማሳየት አካሔዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ አለብን፡፡

በተለይም በአኹኑ ጊዜ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የዝናም እጥረት እንዳለ እየተሰማ ስለኾነ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ሱባዔ በየቤተ ክርስቲያኑ እየተገኘ የምህላ ጸሎት በማድረስ ፈጣሪውን በሐዘንና በጸሎት እንዲለምን፣ ቅድስት ድንግል ማርያምንም እንዲማፀን መልእክታችንን ከአደራ ጭምር እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን፤
እግዚአብሔር ይባርካችኹ ይቀድሳችኹ፤
አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.

Advertisements

3 thoughts on “ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ: በዓለም ልዩ አድናቆት ላላት ሀገር ባለቤት እንድንኾን ያስቻለን ሃይማኖታችን እንደኾነ ከቶ ሊዘነጋ አይገባም

  1. Anonymous August 7, 2015 at 7:15 am Reply

    Amen

  2. Endeg biresaw August 19, 2015 at 9:01 pm Reply

    amen

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: