በዕቅበተ እምነት እና በመልካም አስተዳደር ንቅናቄአቸው: የአክራሪነት ፍረጃው እንዲታረም የሰንበት ት/ቤቶች ጠየቁ፤‹‹በአጥባቂነት ከተደረገ ፍረጃው ስሕተት ነው››/ፌዴራል ጉዳዮች/

በሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና በሚኒስቴሩ ሓላፊዎች ውይይት፡-

 • በሓላፊዎች የሀብት ምዝገባ የተጠያቂነት ሥርዐት ለመዘርጋት እገዛ እንዲደረግ ተጠይቋል
 • የሰንበት ት/ቤቶች በስልት እና በሰላማዊነት ተጋድሏቸውን እንዲያጠናክሩ ሚኒስቴሩ አሳስቧል
 • መንግሥትም በሙስና ወንጀሎች ተዋረዳዊ መዋቅሩን ጠብቆ ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል

*        *        *

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ተወካዮች፡-

 • የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላም መደፍረስ ዋናው መንሥኤ ነው
 • ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች አፈጻጸም መዋቅሩን በተቆጣጠሩ አማሳኞች ይሰናከላል
 • ስለ ችግሩ ስንጮኽ በአሸባሪነት እንታሰራለን፤ ከሙሰኞች ተጽዕኖ የጸዳ አሠራር ያስፈልገናል
 • ሳይኾኑ መስለው በቤታችን የሚያውኩትን በማጋለጣችን በአክራሪነት መፈረጃችን ስሕተት ነው
 • ግቢ ጉባኤያት በስጋት ሊታዩ አይገባም፤ ነጠላ አትልበሱ፤ የጾም ዳቦ አታውጡ ለምን ይባላል?
 • ለመልሶ ማልማት ተነሺዎች የአምልኮ ቦታ አለመታሰቡ የተሠሩትንም ማፍረሱ ተገቢ አይደለም

*        *        *

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሓላፊዎች፡-

 • አንዱ ሲሰርቅ ሌላውም ልስረቅ ይላል፤ የተሰረቀውም ይታገላል፤ ውስጣዊ ሰላም ይናጋል
 • በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ የምታወጣው ተቋም በሙስና መጐዳቷ ለሀገርም ጉዳት ነው
 • በወንጀል ነክ ጉዳዮች እና በአለመግባባቶች መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገባ አይባልም
 • ሃይማኖትን ማጥበቅ ይደገፋል፤ የሚያጠብቅ ከአክራሪነት ይርቃል፤ ከሙስና ይቆጠባል
 • ተማሪዎች የጾማቸውን ዳቦ እንዳይሰበስቡ አልከለከልንም፤ ነጠላም አይለበስ አላልንም
 • ተነሺዎች÷ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ፤ የተሠራበትም እየታየ እንዲጸና እናደርጋለን

*        *        *

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፭ ቁጥር ፰፻፲፩፤ ቅዳሜ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

eotc ssd pouring out to patriarch palace01
ሃይማኖት እንዲጠበቅ፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ በሚያካሒዱት ንቅናቄ በአክራሪነት እየተፈረጁ እና እንደ ሁከት ፈጣሪ እየተቆጠሩ የሚደርስባቸው እስር እና እንግልት እንዲታረም የሰንበት ት/ቤቶች ጠየቁ፤ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከተጠያቂነት ሥርዐት መጥፋት ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ በሰፈነው ምዝበራ እና ሙስና መዋቅሩን ጠብቆ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ኀሙስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች፣ የክፍላተ ከተማ የአንድነቱ ሥራ አስፈጻሚዎች እና የአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች ሊቃነ መናብርት በተሳተፉበት ውይይት፣ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በሰላም እና በልማት ጉዳዮች አብሮ እንደሚሠራ የጠቀሱት የሚኒስቴሩ ሓላፊዎች፣ ‹‹የሕዝብ ሀብት ለሕዝብ ጥቅም መዋል አለበት፤ በሕዝብ ገንዘብ እንዲቀለድ አንፈልግም፤ መንግሥት ሰላምንና የሕግን የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ደረጃውን ጠብቆ እና የሙስና ወንጀል መፈጸሙን አጣርቶ ርምጃ ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሙዳየ ምጽዋቱን ማን ነው የሚጠቀምበት፤ ሕዝብ ይጥላል፤ ጥቂት ሰዎች መኪና እና ቤት ይሠሩበታል፤›› በማለት በሙስና ሳቢያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የዘረዘሩት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው፣ የሚመዘብሩት ግለሰቦች እና አካላት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ቢኖሩም እምነት የሌላቸው እና በሃይማኖቱ ስም የሚነግዱ በመኾናቸው በጋራ ሊወገዙ እንደሚገባ ገልጸዋል፤ በሚፈጽሟቸው ወንጀል ነክ ጉዳዮችም ‹‹መንግሥት ለምን ጣልቃ ይገባል አይባልም፤ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ኾኖ ይከታተላል፤ ወንጀለኛውን ይይዛል፤ ይቀጣል፤ ያጸዳል›› ብለዋል፡፡

የግልጽነት እና የተጠያቂነት አሠራር ዘመኑ የሚጠይቀው እና መንግሥትም በአቋም ያስቀመጠው መኾኑን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ሃይማኖት እንዲጠበቅ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል፤ ‹‹እንቅስቃሴአችኹን ከሁከት በራቀ፣ ስልታዊ በኾነና በሰላማዊ መንገድ ቀጥሉ፤ መንግሥትም ድጋፍ ያደርግላችኋል፤›› ሲሉም አበረታተዋቸዋል፡፡

የሰንበት ት/ቤት አባላት ሰላም ፈላጊዎች እንደኾኑ የገለጹት የአንድነቱ አመራሮች በበኩላቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምንጩ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ እንደ አመራሮቹ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ብፀዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ እና ተቋማዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በየጊዜው ቢያሳልፉም አስተዳደራዊ መዋቅሩን ከላይ እስከ ታች በኔትወርኪንግ በተቆጣጠሩ አማሳኞች ስለሚታገት ተፈጻሚ ለመኾን አልቻለም፡፡

አማሳኞቹ÷ በሙዳየ ምጽዋት፣ በስእለት እና በስጦታ ምእመኑ የሚሰጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለራሳቸው ዓላማ እና ጥቅም እያዋሉ፤ የገዳማቱንና የአድባራቱን መሬት እና ሕንፃ ከአካባቢ የገበያ ዋጋ በታች በሳንቲም ደረጃ ለ10 እና ለ15 ዓመታት እያከራዩ፤ በልማታዊነት ስም በሚፈጸሙ የግንባታ ውሎች እና ከፍተኛ ግዥዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን መብቶች እና ጥቅሞች አሳልፈው እየሰጡ፤ ከገቢያቸው በላይ ሕገ ወጥ ሀብት ያካብታሉ፤ በሦስት እና በአራት ሺሕ ብር ደመወዝ ኤሮትራከር ይገዛሉ፤ ሕንፃ ይሠራሉ፡፡

ይኹንና የተጠያቂነት እና የግልጽነት አሠራር ባለመኖሩ ሲነቃባቸው እና ተቃውሞ ሲበረታባቸው የበለጠ ወደሚዘርፉበት ቦታ በዕድገት እንደሚዘዋወሩ ጠቅሰው፣ ለዚኽም በጎጠኝነት እና በጥቅም ትስስር የተመላው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ተጠያቂ እንደኾነ አመልክተዋል – ‹‹ሲያዙ በዕድገት ይነሣሉ፤ እነርሱ ከተያዙ የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች በምን ይጠቀማሉ? ችግሩ ከአሿሿማቸው ይጀምራል፤ ያዋጣል አያዋጣም ተብሎ ይህን ያህል ትሰጣለኽ፤ እዚያው ሔደኽ ታገኘዋለኽ ተብለው ይሾማሉ፤ የሒሳብ አሠራሩ ኋላ ቀር ነው፤ ለሌብነት የተመቸ ነው፤ ሀገረ ስብከቱ ሌባን አሳልፎ አይሰጥም፤ በሹመት እና በዝውውር ጉቦ እየተከፈለ አብሮ ይበላል፡፡ የሕዝብ ንብረት እየባከነ ስለኾነ መንግሥት ጣልቃ ይግባልን፤ ሕዝብ እያዘነ እያለቀሰ ነው፤ መንግሥት ለምን ቸል ይላል? ዝም ያለ ነገር አንድ ቀን ይፈነዳል፤ ሲፈነዳ ያስቸግራል፤ ሰላም ይደፈርሳል፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብታቸው ተሰፍሮ ተቆጥሮ ይታወቃል፤ አሠራሩ እዚኽም ይምጣልን፡፡››

ዐምባገነኖችን በመቃወማቸው እና አማሳኞችን በማጋለጣቸው አሸባሪዎች ተብለው ለእስር እንደሚዳረጉ አመራሮቹ ጠቁመው፣ የጸጥታ አካላት ርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ኹኔታቸውን በሚገባ እንዲያጣሩ፤ ከአማሳኞች ተጽዕኖ የተጠበቀ ፍትሐዊ አሠራር እንዲከተሉ ጠይቀዋል፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን በአስተምህሮ የቤተ ክርስቲያን ሳይኾኑ መስለው በውስጥ የሚበጠብጡ ግለሰቦችንና ቡድኖችን የማጋለጥ እና የማስወጣት ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ በዕቅበት እምነት እንቅስቃሴአቸው በአክራሪነት የሚፈረጁበት አካሔድ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል – ‹‹እውነቱን ስንናገር ሽብርተኛ ተብለን እንያዛለን፤ ክቡር ሚኒስትር ይህን ያውቃሉ ወይ? መንግሥት በየአጥቢያው ያሉ ውሾችን መያዝ ያቅተዋል ወይ? … በእምነት የእኛ ያልኾኑ በእኛ ሜዳ ሲጫወቱ እንጮኻለን፤ እነርሱ ሜዳ ላይ አልሔድንም፤ እናንተ አትጮኹም፤ ጮኸን የማስወጣት ድርሻ የእኛ ነው፤ ወደፊትም እንጮኻለን፤ የእኛ ያልኾኑ የእኛ መስለው ሲበጠብጡ በመጮኻችን አክራሪ የሚል ስም ይሰጠናል፤ ልንፈረጅ አይገባም፡፡››

በከተማው የመልሶ ማልማት ተነሺዎች የሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያ ቦታ ችግሮች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች የሃይማኖት ነጻነት መብት ተሳታፊዎቹ ካነሧቸው ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡ የልማት ተነሺዎች በሰፈሩባቸው የከተማዋ አካባቢዎች የቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ አስቀድሞ ተለይቶ አለመሰጠቱ ድክመት እንደኾነና ምእመኑ ሠርቶ ለወራት ሥርዐተ አምልኮ ሲፈጽምበት የቆየውን ቤተ ክርስቲያንም ማፍረስ ስሕተት እንደኾነ በአመራሮቹ ተገልጧል – ‹‹ምእመኑ ማምለክ ስላለበት በሔደበት አካባቢ አብያተ ክርስቲያናትን ይተክላል፤ ዝም ትሉታላችሁ፤ ለወራት ሥርዐተ አምልኮ ከተፈጸመበት በኋላ እናፍርስ ስትሉ ምእመኑ ቤተ ክርስቲያኔ ተነካች ብሎ ይነሣል፤ ይህን አስቀድማችሁ ነው ማሰብ ያለባችሁ፤ በዚኽ ችግሩ የመንግሥትም ነው፤ እዚያ እስኪደርስ መጠበቅ የለበትም፤ መጀመሪያ በመልሶ ማልማት ለሚነሡት በፖሊሲ የሚያመልኩበት ስፍራ ተለይቶ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ከተሠራ በኋላ ደግሞ ፖሊሶች ታቦታትን እየወሰዱ ኮፕሬቲቭስ ውስጥ ያስቀምጣሉ፤ ሥርዐተ አምልኮ የሚፈጽምበት፣ የሚያከብረው ታቦት እንዲኽ ሲደረግ ወጣቱን ያስቆጣዋል፤ ያ እንደ አክራሪነት መገለጫ እየተወሰደ ነው፤ ይህ ትክክል አይደለም፤ መስተካከል አለበት፡፡››

በዕውቀት የታነጸ ትውልድ በሚያወጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሃይማኖቱን የጠነቀቀ ግብረ ገብ ዜጋ ለማበርከት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ግቢ ጉባኤያት እንደ ስጋት ሊታዩ እንደማይገባ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አክራሪነት አለ ብለው እንደማያምኑ የገለጹት አመራሮቹ፣ ‹‹ተማሪዎች የጾማቸውን ዳቦ አሰባስበው ነዳያንን ቢመግቡ መልካምነት ኾኖ ሳለ ለምን ይከለከላሉ? ነጠላ መልበስ በሥርዐተ እምነታችንና በባህላችን ያለ ኾኖ ለምን አትልበሱ ይባላል? ሴቶች ቢቸግራቸው ስካርፍ ለማድረግ ተገደዋል፤ ነጠላ ሲለብሱ በጥበቃዎች ይያዛሉ፤›› ሲሉ የእምነት ነጻነታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

State Minister Ato Mulugeta Wuletaw and Minister Dr Shiferaw
በሴኩላር ሥርዐት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሃይማኖት እንቅስቃሴዎች መፎካከርያ እንዳይኾኑና ተማሪዎች ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጡ በሚል ዕቀባ ቢደረግም በግላቸው ሥርዐተ እምነታቸውን እንዳይፈጽሙ አለመከልከላቸውን ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አስረድተዋል፡፡ በአለባበስ የማይፈቀደው ማንነትን ለመለየት የሚያስቸግረውን እንጂ ነጠላ አትልበሱ አላልንም ያሉት ሚኒስትሩ፣ የጾማቸውንም ዳቦ ሰብስበው እንዳይጠቀሙበት አልተከለከለም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ጥቂት በማይባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በተለይ ሥርዐተ አጽዋምን ለመፈጸም እና የጾማቸውን በጀት ለመጠቀም በእጅጉ ተቸግረው እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ለመልሶ ማልማት ተነሺዎች የቤተ ክርስቲያን መትከያ ቦታ ባለመለየት ስሕተት ሊፈጸም እንደሚችል የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ቦታው ለሌላ ፕሮጀክት ካልተያዘ መንግሥት ፈቃድ ሰጥቶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ እና የተሠራውም እየታየ እንዲጸና ይደረጋል ብለዋል – ‹‹የኾነ ሰዓት ተተክሎ እናገኛለን፤ አፍርሱ ሲባሉ ይጠፋሉ፤ መሬት እየሸጡ መንግሥት ይዞታችንን ወሰደ ብለው ሕዝብ ይቀሰቅሳሉ፤ እርሱ አስቸጋሪ ኾኖብናል፡፡››

አክራሪነት እና ጽንፈኝነት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ መኖሩ የሚያከራክር አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ኾኖም ጥያቄው በሃይማኖት አጥባቂነት እስከተነሣ ድረስ ከአክራሪነት ስለሚያርቅ እና ከሙስና ስለሚጠብቅ የሚደገፍ እንደኾነና ከዚኽም አኳያ የፍረጃው አካሔድ ስሕተት መኾኑን አብራርተዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የማይፈቅደውን የአክራሪነት አስተሳሰብ እና ተግባር በሃይማኖት ሽፋን የሚያራምዱ ግለሰቦች ለተቋሙ ደኅንነት ሲባል መለየት አለባቸው – ‹‹ሰው ጥያቄ በማንሣቱ ሊፈረጅ አይገባውም፤ ጠያቂ ትውልድ መፈጠሩ መልካም ነው፤ የምታነሡት ነገር መልካም እስከኾነ ድረስ የፍረጃው አካሔድ ስሕተት ነው፤ አክራሪነትን እንጂ ሃይማኖትን ማጥበቅ የምንደግፈው ነው፤ የምንጠላው አይደለም፤ ሰው ሃይማኖቱን የሚያጠብቀው ሲያውቅ ነው፤ ሲያውቅ ከአክራሪነት ይርቃል፤ ከሙስና ይቆጠባል፡፡››

ሕዝብ ከተግባር እንደሚማር ዶ/ር ሺፈራው ጠቁመው፣ አትስረቅ እያሉ በሌላቸው ገቢ የሚልዮን ብር መኪኖችን የሚነዱ አካላት ለሀገር መልካም ዜጋ የምታወጣውን ተቋም በማማሰን በሕዝብ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህም ሀገርን የሚጎዳ በመኾኑ በብጥብጥ እና ድንጋይ በመወርወር ሳይኾን በምእመኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጋለጥ እንደሚገባቸው መክረዋል፤ የሰንበት ት/ቤት አባላትም በመዋቅሩ ውስጥ ኾነው ከቤተ ክርስቲያን አልፎ ለሀገር እና ለዓለም የሚበቁ ሊቃውንቷን በማስተባበር ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል – ‹‹በተቋሙ ውስጥ ያሉ እምነቱ ግን የሌላቸው ጭምብል ለባሾች አትስረቅ ይላሉ፤ እነርሱ ግን ይሰርቃሉ፤ ይኼ አብሮ አይሔድም፤ እናንተ ድንጋይ ሳትወረውሩ ሌብነቱን አጋልጡት፤ ሥራቸው ይኼ ስለኾነ የእነርሱን ሌብነት ሳይኾን የእናንተን ተቃውሞ ጉዳይ ያደርጉታል፤ ስለዚኽ በሰላማዊ መንገድ አድርጉት፡፡››

መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ማለት ሰላም ሲደፈርስ እና ወንጀል ሲፈጸም ዝም ይላል ማለት ባለመኾኑም መዋቅሩን ጠብቆ ርምጃ እንደሚወስድ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል – ‹‹አንዱ ሰርቆ ሌላው ዝም አይልም፤ ያልሰረቀ እኔ ልስረቅ ይላል፤ የተሰረቀም ጸጥ አይልም፤ እስከ መጨረሻው ይታገላል፤ ይህ እየቀጠለ ሲሔድ ለቤተ ክርስቲያኗ ውስጣዊ ሰላም ብሎም ለሀገር ሰላም መደፍረስ ምክንያት ይኾናል፡፡ እየተባለ ያለውን ቸል የምንለው ነገር አይደለም፤ መንግሥት መዋቅሩን ጠብቆ በተዋረድ ይገባል፤ ወንጀል የሠሩትን በሕግ ይጠይቃቸዋል፤ አንምርም፤ አንተውም፤ እስከ ላይ እንሔዳለን፤ ከላይ ካሉት ሰዎች ጋር አብረን እንሠራለን፤ በሃይማኖቱ መሸፈን አይችሉም›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው በዚኹ የግማሽ ቀን ምክክር ማጠናቀቂያ÷ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የልማት እና ዕቅድ ዋና ክፍል ሓላፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ ቀሲስ አሉላ ለማ የተገኙ ሲኾን ሚኒስትሩም ‹‹የወጣቶቹን ጥያቄ እንደ ቀላል አትዩት፤ እንደተናገሩት በዝምታ የታለፈ ነገር በኋላ ያስቸግራል፤ በአስቸኳይ ፍቱ›› ሲሏቸው ተደምጠዋል፡፡

ቀደም ሲል ሚኒስቴሩ፣ ከተወሰኑ የሀገረ ስብከቱ የገዳማት እና የአድባራት አለቆች፣ ጥቂት ካህናት እና ሰባክያነ ወንጌል ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ ይኸውም በቅርቡ በሃይማኖት ተቋማት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሰላምን አስጠብቆ መኖርን፤ ጤናማ ግንኙነቶች ማስፈንን በተመለከተ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች በሚገኙበት ለሚካሔደውና የጋራ አቋም ለሚያዝበት የውይይት መድረክ የግብአት ማሰባሰቢያ ቅድመ ዝግጅት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

Advertisements

5 thoughts on “በዕቅበተ እምነት እና በመልካም አስተዳደር ንቅናቄአቸው: የአክራሪነት ፍረጃው እንዲታረም የሰንበት ት/ቤቶች ጠየቁ፤‹‹በአጥባቂነት ከተደረገ ፍረጃው ስሕተት ነው››/ፌዴራል ጉዳዮች/

 1. w/Maryam August 3, 2015 at 7:09 am Reply

  egna barochu tenesten enseralen, yesemay amlak yakenawnilnal endale Nehimiya yesenbet t/bet amerarochim yihin betegbar geltsewalna yilfatachewn waga Er yikifelilin. kefetenam yitebkachew. . dingayochin lemisgana yazegaje,yebelamin ahiya yanagere zarem bemayaminutm ena yebetekrstyan metames bemayasasbachew af hono eyetenagere new. mastewal letesanachew abatochachinina lemd lebsew lemimezebru tekulawech Er amlak ewnetegna frdun ersu yazegajal,simu yetemesegene yihun Amen.

 2. Anonymous August 3, 2015 at 8:53 am Reply

  እግዚአብሔር ይረዳችሁ ከኡነተኛ ጋ ይሁን ሌባ ይውደም

  • ታደሰ August 4, 2015 at 2:39 pm Reply

   ችግሩ እኮ ሁሉም እውነትን ይዘው አለመነሳታቸው ነው ሰንበት ተማሪው እራሱ በዝሙት መርዝ የተወጋ ልክፍተኛ ነው ሰንበት ተማሪውን ያሰለፈው የሰይጣን ማህበር የሆነው ሁከት ፈጥረው ማህበር ነው እኔ ግርም የሚለኝ የኢሃዲግ አጫዋችነት ነው ኢሀዴግ ሁሉንም ያውቀዋል ግን ጨዋታውን ስለሚፈልገው ነው ።

 3. Anonymous August 4, 2015 at 11:31 am Reply

  በአጥባቂነት ከተደረገ ፍረጃው ስሕተት ነው›

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: