ከብር 6 ሚልዮን በላይ የተመዘበረበት የደ/ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሒሳብ እንዲመረመር ተጠየቀ፤ ‹‹የበጀት ዓመቱን ሒሳብ ዘግቼ ለመመርመር ሰባት ቀን ሲቀረኝ ተዘዋውሬአለኹ››/ሒሳብ ሹሟ/

 • በኹለት ዓመት ውስጥ ለደብሩ ከብር 18 ሚልዮን በላይ ተቀማጭ አስመዝግቤአለኹ
 • የተነሣሁት ሕገ ወጥ ክፍያዎችን በመቃወሜ እና ምዝበራዎችን ለመሸፋፈን ሲባል ነው
 • ሕገ ወጥ አሠራር ቢረጋገጥም ውሳኔ አያገኝም፤ በአጥፊዎችም ላይ ርምጃ አይወሰድም
 • የሰነዶቹ ደኅንነት ታይቶ ቢሮዬ ይታሸግልኝመንግሥት ኦዲተሮችን መድቦ ያጣራልኝ
 • በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሚፈጸሙ አደገኛ አሠራሮች ቀርቤ በቃል እንዳስረዳ ይመቻችልኝ

*         *         *

 • የሀገር ሀብት በባለሥልጣናት በሚያስፈራሩት ዋ/ሥ/አስኪያጁ ሲዘረፍ ማየቱ አደጋ ያስከትላል
 • በመላዋ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኩን እንዲያማክሩ በመንግሥት ትእዛዝ እንደተሾሙም ይናገራሉ
 • የሊ/ማዕ. የማነ ቢሮ የንግድ ማስታወቂያ አልተለጠፈበትም እንጂ የሰው ዘር መሸጫ መደብር ኾኗል
 • አላግባብ በማዘዋወር የሚንገላቷቸውን ሠራተኞች ‹‹ምንም አታመጡም›› በማለት ያንኳስሷቸዋል
 • ፓትርያርኩ ሙስና ይጥፋ ቢሉም ከሚዲያ አላለፈም፤ በሥራ እንጂ በሚዲያ አይጠፋም

/ሒሳብ ሹሟ ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም/

(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ቅጽ ፫ ቁጥር ፻፲፬፤ ቅዳሜ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

st-urael-church

የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን

ከብዙኃን ምእመናን የተሰበሰበ በብዙ ሚልዮን ብር የሚገመት የቤተ ክርስቲያን ሀብት እና ንብረት አላግባብ ተመዝብሮበታል የተባለው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሒሳብ፣ በገለልተኛ እና ሕጋዊ አካል በይፋ እንዲመረመር ተጠየቀ፡፡

ሓላፊነትን አላግባብ በመጠቀም እና የሒሳብ አያያዝ እና የንብረት አጠባበቅ ድንጋጌዎችን በመጣስ በደብሩ አስተዳደር ተፈጽሟል በተባለው ምዝበራ እና ብክነት÷ ጥናት እና ጥራት ለጎደላቸው ሥራዎች ከፍተኛ ወጪዎች ይታዘዛሉ፤ ከተመደበው እና ከተወሰነው ውጭ በሕገ ወጥ ትእዛዝ የደብሩን ካፒታል የሚንዱ የተለያዩ ክፍያዎች ይፈጸማሉ፤ ለተከራይ በሚያደሉ እና የደብሩን ጥቅም በሚጎዱ የሕንፃ ኪራይ ውሎች ግለሰቦች መቶ ሺሕዎችንና ሚልዮን ብሮችን ያካብታሉ፤ በዐውደ ምሕረት በምንጣፍ አና በስእለት የተሰበሰበ ገንዘብ በአግባቡ ሳይቆጠር እና በሞዴል ገቢ ሳይኾን እየተወሰደ የገባበት አልታወቀም፡፡

ከኹለት ዓመታት በላይ የደብሩ ሒሳብ ሹም ኾነው ሲሠሩ የቆዩት ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም÷ የተሰበሰበው ገንዘብ የት ገባ ብለው በመጠየቃቸው ያለምንም ማጣራት እና ቅድመ ኹኔታ፣ ንብረት እና መዛግብት አስረክበው ወደ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው እንዲሠሩ ባለፈው ሰኔ 22 ቀን ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መታዘዛቸውን ይናገራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት በመኾኗ በተዛወሩበት ደብር ለመሥራት ፈቃደኛ ቢኾኑም፣ የ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሊዘጋ ሰባት ቀናት ሲቀሩት ዝውውር የተደረገበትን አሠራር ግን እንደሚቃወሙት ገልጸዋል፡፡

የሒሳብ ሠራተኛ የተመረመረ ሰነድ ማስረከብ እንዳለበት ሒሳብ ሹሟ ጠቅሰው፣ ከመጋቢት/2005 ዓ.ም. ጀምሮ እስከተዘዋወሩበት ሰኔ 22/2007 ዓ.ም. ድረስ በደብሩ በቆዩባቸው 27 ወራት ከብር 54 ሚልዮን በላይ ገቢ እና ወጪ የሠሩባቸው፤ ከብር 18 ሚልዮን በላይ ተቀማጭ ያስመዘገቡባቸው የሒሳብ ሰነዶች እና መዛግብት በይፋ እንዲመረመሩ በአድራሻ÷ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በሀገረ ስብከቱ ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና ለዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በጻፉትና በግልባጭ ደግሞ ለሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ለመንግሥት የደኅንነት አካላት ባደረሱት ሰፊ ጽሑፍ ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ መና እንደሚሉት፣ ሰነዶቹ እና መዛግብቱ ያልተመረመሩ ብቻ አይደሉም፡፡ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመጣስ ተፈጽሟል የሚሉት የአስተዳደርና የፋይናንስ አሠራር ችግር እንዲጣራ ለፓትርያርኩ ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት ያለአግባብ የባከነውና የተመዘበረው የብዙኃን ምእመናን ገንዘብ በሀ/ስብከቱ በሚመደቡ ሠራተኞች ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርብ በቋሚ ሲኖዶስ መመሪያ የተሰጠበት ከፍተኛ ክሥ ያለባቸው ሰነዶች እና መዛግብትም ናቸው፡፡ ይህንንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ከመሾማቸውም በፊት እንደሚያውቁት ያወሱት ሒሳብ ሹሟ፣ ሳይመረመሩ ከብር 54 ሚልዮን በላይ ገቢና ወጪ የሠራኹባቸውን ሰነዶች እና መዛግብት እንደ ቀላል ወረቀት አስረክበው ይውጡ ማለት ‹‹ከአንድ ተቋም ሓላፊ የሚጠበቅ አይመስለኝም፤ አጥፊዎቹ ወገኖቼ ናቸውና ተደብስብሶ እንዲቀርላቸው በማሰብ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት የሒሳብ ብክነቱን ለማጣራት፣ የሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር ዋና ክፍል ሓላፊ ባሉበት ልኡክ በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ምርመራ ቢካሔድም ውጤቱ የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ሒሳብ ሹሟ ይገልጻሉ፡፡ ሓላፊው እንኳንስ በደብዳቤ ለምርመራ ተልከው ገንዘብ ጠፋ፤ ንብረት ባከነ ሲባል አጣርተው ለውሳኔ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዘቡት ሒሳብ ሹሟ፣ ‹‹ቁጥጥር ሳይኾን ቁጥርጥር ነው የያዙት›› ሲሉ ይወቅሷቸዋል፡፡

ውሳኔን በውሳኔ በመሻር ከደብሩ የሕንፃ ገቢ ላይ ከብር ስድስት ሚልዮን በላይ ወደ ግለሰቦች ኪስ መግባቱ፤ በውል ላይ ውል በመዋዋል ከአንድ የሕንፃ ኪራይ ብቻ ብር 487,869.32 መመዝበሩ ለቋሚ ሲኖዶሱ ካቀረቧቸው አቤቱታዎች እንደሚገኙበት ሒሳብ ሹሟ ይዘረዝራሉ፡፡ ይህንንም የሕንፃ አጣሪ በሚል ተሠይሞ በደብሩ ጽ/ቤት ለተገኘ ሌላ ኮሚቴ ከመዝገብ ቤት ፋይል እያስቀረቡ በጋራ በማየት መተማመን ላይ ቢደርሱም ‹‹እስከ አኹን ውጤቱ የት እንደደረሰ አይታወቅም›› ይላሉ፡፡

ሒሳብ ሹሟ በስፋት ከዘረዘሯቸውና በየጊዜው በሚካሔዱ ማጣራቶች ቢረጋገጡም ውጤት ላይ አልተደረሰባቸውም ካሏቸው ሕገ ወጥ አሠራሮች መካከል፡- የቀድሞው አስተዳዳሪ ባልተሾሙበት ዘመን ወደ ኋላ እየተመላለሱ አግባብነት የሌለው ወጭ አድርገዋል፤ በአንድ ወር ከአበልና ከነዳጅ ውጭ እስከ ብር 8,000 በሠንጠረዥ እየፈረሙ ወስደዋል፤ ለአንድ የሰበካ ጉባኤ አባል በወር እስከ ብር 30,000 ወጪ ተደርጓል፤ የበዓል መዋያ ድጎማ ተከፍሏል፤ በሰበካ ጉባኤው የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ውጭ ቅጥረኛ ተደርገዋል፡፡

ጥራት ለሌለው የሕንፃ ጠርዝ መሠረት ሥራ፣ ጄኔሬተር ለማዘዋወር፣ ለመኪና እድሳት፣ ለካህናት ጊዜያዊ ቤት ሥራ ጥናት የጎደላቸው ወጭዎች ተደርገዋል፤ በሰኔ 2006 ለኹለት የሰበካ ጉባኤ አባላት ብር 250,000 በአስቸኳይ ወጭ ኾኖ ያለደረሰኝ በሞዴል 6 እንዲከፈል ሕገ ወጥ ትእዛዝ በማዘዝ፤ በነሐሴ 2006 ለደመወዝ ከተወሰነው በላይ በልዩነት ከብር 236,000 በላይ ወጭ በማድረግ የደብሩ ካፒታል ተንዷል፤ የደብሩ ጠበቃ በፍርድ ቤት የተከሰሱ ተከራዮች ውዝፍ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ለማድረግ ሲዳረስ ክሡን በይቅርታ በማንሣት በምትኩ የደብሩ ገቢ ለግል ጥቅም ውሏል፤ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ወ/ሮ መና እንደሚገልጹት፣ የተጣሩት ሕገ ወጥ አሠራሮች ውሳኔ ሳያገኙ በመቅረታቸው እና ርምጃ ባለመወሰዱ ‹‹ያለፉት አጥፊዎች ምን ተደረጉ?›› በማለት በወቅቱ የደብሩ እና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ የተለቀቀ ሱቅ በጨረታ ማከራየት ሲገባቸው ሽያጭ አካሒደዋል፤ ቤተሰቦቻቸውን አስቀጥረዋል፡፡ በሚያዝያ 22 እና ግንቦት 22 የቅዱስ ዑራኤል ክብረ በዓል በዐውደ ምሕረት አስተዳዳሪው በተቀመጡበት ምንጣፍ እና በስእለት ከምእመናን የተሰበሰበ ገንዘብ ሳይቆጠርና በደረሰኝ(በሞዴል 30) ገቢ ሳይደረግ በሻንጣዎች ተሞልቶ ተወስዷል፤ የት እንደገባም አይታወቅም፡፡

የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራው በባንክ የመቁጠሪያ ማሽን እንዲከናወን የወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በየስብስባው መመሪያ እንደሚሰጡ የጠቀሱት ሒሳብ ሹሟ፣ በዐውደ ምሕረት በምንጣፍ እና በጥላ ስለተሰበሰበው ገንዘብ ቢጠየቅም ሀገረ ስብከቱ እንኳ እንዲያጣራ አለመፈለጉን ይገልጻሉ፡፡ ሒሳብ ሹሟ ለምን በማለት ይጠይቁና ምላሹን ራሳቸው ሲሰጡ ‹‹ፈቃጁ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በመኾናቸውና አያገባችኹም ስላሉ›› ብለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ መና፣ በማጣራት የተረጋገጡ ጥፋቶች ተገቢው ርምጃ የማይወሰድባቸው፣ የደብሩ የአስተዳደር ሓላፊዎች ለበላይ አካል ያለትእዛዝ በሚያቀርቧቸው ማባበያዎች ስለሚሸፋፈኑ ነው፡፡ የደብሩ ሒሳብ ክፍል ሳያውቀው፣ ገንዘብ ከባንክ ሳይወጣ በዋና ተቆጣጣሪው አማካይነት ከዕለት ገንዘብ ተቀባዮች በብድር በተወሰደ ብር 430,000 ለፓትርያርኩ ቢሮ በስጦታ የተበረከተው ሶፋ፣ ሒሳብ ሹሟ በጽሑፉ ካሰፈሯቸው ኹለት ማባበያዎች የመጀመሪያው ሲኾን የቅዱስ ዑራኤል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በማይመለከተው እና ባልታዘዘበት በቀድሞው አለቃ የሥራ ዘመን የተፈጸመ ነው፡፡

‹‹ለአባቶች ራት ግብዣ›› በሚል በሰበካ ጉባኤው የተወሰነውን ብር ስድሳ ሺሕ ወጪ ከማወራረድ ጋር በተያያዘ ከወቅቱ የደብሩ አለቃ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ወ/ሮ መና በጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ እንደ እርሳቸው፣ መስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በፓትርያርኩ ቢሮ ለተደረገው የመስተንግዶ ወጭ የሚያስፈልገው ብር 38,611.66 ሲኾን አስተዳዳሪው፣ ‹‹ለምግብ ማስገቢያ የኮቴ የከፈልኩትን አብረሽ አወራርጂ፤ ገንዘቡ ተወስኖና ተፈቅዶ ከባንክ ወጪ ኾኗል›› በማለት እንዳዘዟቸው ጠቅሰዋል፡፡

ሒሳብ ሹሟ አክለውም ‹‹ደረሰኝ የሌለው የኮቴ ወጪ አላወራርድም ብዬ ስላልተግባባን ሕጋዊው ሰነድ ሳይወራረድ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ለዘጠኝ ወራት ከቆየ በኋላ ተወራርዷል፤›› ካሉ በኋላ ‹‹የኮቴ ክፍያውም በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ተፈጻሚ ይኾናል› ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቷ በዚኽ መልክ ያለደረሰኝ ወይም ያለሞዴል 6 እየተመዘበረች እንደምትገኝ ያስታወቁት ወ/ሮ መና፣ ‹‹ሕገ ወጥ ኾኖ አላወራርድም ያልኩት የፓትርያርኩን መመሪያ ወደ ተግባር የለወጥኩ መስሎኝ የነበረ ቢኾንም በእንደራሴ ነን ባዮች የሚፈጸምብኝን ደባ አላሰብኩትም ነበር፤›› በማለት በደብሩ የፋይናንስ አሠራር ላይ ያቀረቧቸው አቤቱታዎች በዝውውር ሽፋን ተድበስብሰው እንዳይቀሩ ተማፅነዋል – ‹‹ምርመራው በቤተ ክህነቱ ሳይኾን መንግሥት በሚመድባቸው ኦዲተሮች ከመሠረቱ ከመጋቢት 2005 እስከ ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ እንዲደረግልኝ እፈልጋለኹ፤ ቢሮዬም ተሰብሮ ሰነድ እንዳይወጣ ሕጋዊ የመንግሥት አካል ባለበት እስከ አኹን ያለው ደኅንነት ታይቶ እስኪመረመር ድረስ እንዲታሸግልኝ፤ ለማሳያነት ካቀረብኋቸው ጉዳዮች ባሻገርም በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሚፈጸሙ አደገኛ አሠራሮች በአካል ቀርቤ በቃል ለማስረዳት እንድችል ይደረግልኝ ዘንድ እጠይቃለኹ፡፡››

በወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ‹‹እንደራሴ ነን ባዮች›› የተባሉት፣ በቤተ ክህነቱንም ኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር ፓትርያርኩን በወሳኝነት ያማክራሉ የተባሉ ሦስት የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን (መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ፣ መልአከ ብርሃናት ዘካርያስ ሓዲስ እና መልአከ ገነት ተስፋ ፍሥሓ) እንደኾነ በጽሑፋቸው ተመልክቷል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ሹመታቸው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ቢኾንም ‹‹በምስጢር ለመላው ኢትዮጵያ ነው›› እንዳሏቸው ወ/ሮ መና ጠቁመው፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና እንደራሴ ነን ባዮቹ በሚሏቸው ብቻ እንዲሠሩ ለፓትርያርኩ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጣቸው በሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ‹‹በዘመናዊ የሙስና አደረጃጀት›› እየተመራ እንዳለ ገልጸው፣ ከዝውውር አሠራር ጋር በተያያዘ በአንድ አካባቢ ተወላጅ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ባለው የአስተዳደር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት የዋና ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ‹‹የሰው ዘር መሸጫ መደብር ኾኗል›› ይላሉ፡፡ የፓትርያርኩ የፀረ – ሙስና ዐዋጅ ከሚዲያ ፍጆታነት እንዳላለፈ ተችተው፣ ሙስና በሥራ እንጂ በሚዲያ እንደማይጠፋ የሚገልጹት ሒሳብ ሹሟ፣ ችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው ወደፊት ቤተ ክርስቲያኒቷን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላት አሳስበዋል፡፡

ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ተዛውረው በተመደቡበት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሒሳብ ሹም የነበሩት ሠራተኛ፣ በሰነድ ማጭበርበር በተፈጸመ ከፍተኛ የእምነት ማጉደል ወንጀል ተከሠው በሰኔ ወር መጨረሻ የተላለፈባቸውን የአንድ ዓመት ከስምንት ወራት የእስር ቅጣት በመፈጸም ላይ እንዳሉ ተገልጧል፡፡

Advertisements

13 thoughts on “ከብር 6 ሚልዮን በላይ የተመዘበረበት የደ/ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሒሳብ እንዲመረመር ተጠየቀ፤ ‹‹የበጀት ዓመቱን ሒሳብ ዘግቼ ለመመርመር ሰባት ቀን ሲቀረኝ ተዘዋውሬአለኹ››/ሒሳብ ሹሟ/

 1. […] በኹለት ዓመት ውስጥ ለደብሩ ከብር 18 ሚልዮን በላይ ተቀማጭ አስመዝግቤአለኹ የተነሣሁት ሕገ ወጥ ክፍያዎችን በመቃወሜ እና ምዝበራዎችን ለመሸፋፈን ሲባል ነው ሕገ ወጥ አሠራር ቢረጋገጥም ውሳኔ አያገኝም፤ በአጥፊዎችም ላይ ርምጃ አይወሰድም የሰነዶቹ ደኅንነት ታይቶ ቢሮዬ ይታሸግልኝ፤ መንግሥት ኦዲተሮችን መድቦ    … ሙሉውን ጽሁፍ ለማየት እዚህ ላይ ይጫኑ። […]

 2. ታረቀኝ August 1, 2015 at 9:34 am Reply

  አረ የደብረ ብስራት ቅ/ገብርኤል ቢታይልን ተዘረፍን በሀይማኖት ሽፋን

  • Anonymous August 2, 2015 at 5:50 am Reply

   ወዳጄ እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ያመጣው ቅጣት ስለሆነ አጥብቆ መጸለይ ነው ምክንያቱም ክፉ ለሆኑ ለመንጋው የማይራሩ ለአባትና ልጅ ለፓትርያርክ ለሊቃነ ጳጳሳት ተላልፈን ተሰጥተናል እግዚኦ እግዚኦ እግዚኦ ማለት.

  • Anonymous August 2, 2015 at 6:51 am Reply

   Pls pray pray pray…..

 3. እንቧይ August 1, 2015 at 9:42 am Reply

  አረ መቼ ነው ወያኔ እጅን ከሀይማኖት የሚያነሣው

 4. Anonymous August 2, 2015 at 2:02 am Reply

  በእውነት ስለቅዱስ ዑራኤል ቤተክረስቲያን በወ/ሮ መና የቀረበውን አጠቃላይ መግለጫ ቀደም ሲል በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ በመቀጠለም በዚህ ድሕረ ገጽ ሳነብ ብዙ ነገሮች በህሊናየ ተመላለሰ፤ ጀግንነት ራስን በመግዛት ለእውነት መታገልና እውነትን መጋፈጥ እንደሆነም ተምሬአለሁ፡፡ በትእቢት ከመወጠርና ከመታበይ ጉዳዩ ምን ያክል እውነትነት አለው ብሎ መመርመርና መፍትሄ መስጠት የተሻለ ነው፡፡

  እንደኔ ወ/ሮ መና ካስተላለፉት አሳሳቢ መልእክት ውስጥ አንድም መሬት የሚወድቅ የለውም፡፡ ጉዳዩን እኔም የማነም ስንወያይበት የነበረ በመሆኑና ወደ ኋላ ከተሔደም የየማነ ጉድ አለበት፡፡ መረጃ ለማጥፋት የተሰራ ስራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የልደታው ጉዳይ ላይ የማነም ተከሳሽና ጉዳዩ ገና ያልተቋጨ ነው፡፡ የአራዳው ጊዮርጊስ 175 ሚሊዮን ብሩን ለማድበስበስና የተዘረፈውን ዘረፋ ሕጋዊ ለማድረግ በድፍረት ያቀረበውን አጀንዳ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ተጥሎበታል(ውድቅ ተደርጓል)፡፡ እንዴት የአንድን ደብር ጉዳይ ራሱ ጸሃፊ የሀ/ስብከት ስራ አስኪያጅ እራሱ በዘራፊነት ተጠያቂ መሆኑ እየታወቀ መረጃ ለማጥፋት መሞከር በራሱ አስደናቂ ድፍረትና ገራሚ ነው፡፡ ነገሩ ቁማርተኛ ምን ጊዜም ደፋር ነው፡፡ ለማንኛውም ወንዝ ያፈራሽ ዳግማዊት ጣይቱ (ምንም እንኳን የእናት ሆድ ዝጉርጉር ነው ቢባልም) ወ/ሮ መና ጀግና ነሽ፡፡

  ይህ በእንዲህ እያለ በአዕምሮዬ ከሚመላለሱት አሳሳቢ ጥያቄዎች መካከል፡-
  1. እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች በቤተ ክርሲቲያኗ ኣስተዳደር ውስጥ እስከ መቼ ድረስ ነው የሚቀጥለው ?
  2. ግለሰቦችስ ቡድናዊ ዘረፋንና የዘረኝነትን አመለካከት ይዘው የሚቀጥሉት እስከመቼ ነው?
  3. መንግስትስ ጣልቃ ገብነቱን በትክክል ሀገራዊ ደህንነትን ባስጠበቀ መልኩ ቤተክርሲቲያኗን የሚጠቅመው መቼ ነው?
  4. የቤተ ክርስቲያኗ የበላይ ኃላፊዎች ከፓትርያርክ እሰከ ስር ያሉ ሰራተኞች ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ፤የእምነት ተቆርቋሪነት ያለው፤ በመንፈሳዊነትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዳደርን የሚያመጡት መቼ ነው?
  5. ፓትርያርክስ ሁሉን አቀፍ የሆነ፤ ከዘረኝነት የጸዳ፤ ለቤተክርስቲያኗ መሰረታዊ ሕግና እምነት ያደላና ተቆርቋሪ የሆነ፤ በስነ ምግባር የታጠረ፤ የሁሉም እኩል አባትና የእምነት አባት የሚሆኑት መቼ ነው?
  6. ቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልናወን አስጠብቆ በግርማ ሞገስ ስለ እውነት የሚመሰክረው፤ ከተራ አሉባልታ ወጥቶ ሕጋዊ መሰረት የሌለውን አጀንዳ ከህጋዊው አጀንዳ እየለየ በእውቀትና በመንፈስ የሚሰራው መቼ ነው
  7. ግለሰቦችስ በመንግስት ስም በመነገድ እያደረጉ ያሉትን የተደራጀ ምዝበራ የሚያቆሙት መቼ ነው?
  8. ምዕመኑና ካህናቱ እየተደረገ ያለውን ግፍ ተቀናጅተው የሚመክቱትና የሚፈቱት መቼ ነው?

  ዞሮ ዞሮ የነአቶ የማነና የአጋሮቹ ተግባር ተራ ውንብድና ነው፡፡ ምክንያቱም መርሃቸው መዝረፍ ፤መዝረፍ፤መዝረፍ ነው፡፡ እያንዳንዱ እርምጃቸውም የጋለሞታይቱን ስርዓት መተግበር ነው፡፡ ባቢሎኖች(ዝሙት የተስፋፋበት ስርቆት የነገሰበት እግዚአብሔር የማይፈራበት አለቆች የረከሱበት ከተማ)፡፡ እኔ በትንሹ የማነን አውቀዋለው፤ አብረንም ሰርተናል፤ አድገናል፤ የቤተ ክርስቲያኑ ትምህርት የማይገባው ሃይ ስኩል እያለንም ለቋንቋ እንጂ ለሌሎች መሰረታዊ ትምህርቶች ቦታ የሌለው(ትግርኛ ለመልመድ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር)፤ በጣም ስለሚያወራ BBC እንለው ነበር፤ ምክንያቱም ስለ ሚትርዮሎጂ ስለ ጦርነት ስለ ስፖርት ወዘተ. ማሰሪያ ነጥብና ጭብጥ የሌለው ነገር ያወራል፡፡

  በማታው ክፍለ ጊዜ 6ኪሎ ዬኒቭርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ ዲፓርትመንት በኢሀዴግ/ሕወሀት/ የደብዳቤ ድጋፍ ተመዘገበ፤ ምክንያቱም ድርጅቱን አማላይ በሆነ ቃል አሳክሮት ነበር፡፡ እውነታው ግን ሕወሀት ለትግል ጫካ በገባበት ወቅት አባቱ ለትግል ልጄን በረሃ ይወስዱብኛል በማለት በልጅነቱ አሽሽተው ወደ አ.አ አመጡት፡፡ በሌሎች ሰማእትነት ለመክበር ታስቦ፡፡ ሆኖም ይህንን እውነታ በማጣመም ደርግን እየሰለልን መረጃ እንድናቀብል ተብሎ የተላክን ነን ይላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም እያመለጠው ጫካ እንደታገለም ያወራል፤ ነገር ግን የትግሉ ዓላማ ምን እንደሆነ መተንተን ያቅተዋል፤ ነገሩ በሚስቱ ታግሏለል፡፡

  ፖለቲካ ሳይንስ ዲፓርትመንት የገባው ሲጨርስ ለትግራይ ክልል ርዕሰ ብሔርነት እንደሚሾም በተደጋጋሚ ያወራ ነበር፡፡ ሕውሀት ሴንጪው ሰርስሮ ገብቶ መረመረውና ከኢቲቪ በፐርፎርማንስ ማነስ አባረረው፡፡ እንኳን ለትልቅ ስልጣን ሊታጭ ለምንጣፍ አንጣፊም ብቁና ታማኝ አለመሆኑን አብጠርጥረው ደረሱበት፡፡ የማን ዘር ጎመን ዘር በአንድ ወቅት አባቱ ከልዋጭ ስራቸው አረፍ ብለው ታማኝ መስለው የአንድ ደብር መገበሪያ አክባሪ ነበሩ፡፡ የመገበሪያ ስንዴ ለግል ጥቅም በማዋላቸው ታግደው ነበር፡፡ በኋላም ምንጣፍ አንጣፊ ተቀጥረው የአንድ ምእመንን የተረሳ ንብረት ወስደው ስለተገኙ ይህም ተደርሶባቸው ለረጅም ጊዜ ታግደው ነበር፡፡ ደፋሮች! ለዚህ ነው ልጁም ያደገበትንና ከአባቱ የወረሰውን ተግባር እያከናወነ ያለው፡፡ ብቻ እንተወው፡፡

  አሁን ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ፖለቲካ ሳይንስ አስፈላጊ እንደሆነ በመኩራራትና በድፍረት መንግስትም እሱን መርጦ ከቤተ መንግስት እንደላከው ይናገራል፡፡ እረ መንግስት የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስት ነው….. በአጠቃላይ ኦና/ባዶ ቤት ሲገኝ እንዲህ ነው፡፡ ትክክል ነው፤ በአሁኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ መሪዎች የሆኑ በአጠቃላይ ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፤ በአብሮ መብላትና መጠጣት ይልኙታ ባይጠፈነጉ የተሻለ ነው፡፡ ይሄ ውርደት ነው፤ ነገር ግን ለማስተካከል ቀላል ነው፤ የሀይማኖት ቁርጠኝነቱ ካለ ታራዎችን ዞር በሉ አይመለከታችሁም የከዚህ በፊቱ መጭበርበርና መሸወድ ይበቃል ቢባሉ ይቆማል፡፡ ነገር ግን ማን ይጀግን፤ ማን ሰማእትነት ይቀበል፤ ያሳዝናል ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስም በሕግ የተሰጣቸውን ስልጣንና አደራ ለመተግበር የስነ ልቦና ጥንካሬና የሓይማኖት ቁርጠኝነት አጡ፤ እንዳውም አንድ ጊዜ ማን ይበላል ብለው ተናግረዋል ይባላል፡፡ ለቸልተኝነታቸው ምክንያቱ ፍርሃት ብቻ ነው እሳቸው በትንሹ እንዴት የሐንስን ፈሩ??????፡፡ ሆድ ይፍጀው፡፡

  እነዚህንና ሌሎችን ጉዳዮች ባሰብኩ ጊዜ ህሊናዬ ከአየራት አየራት ወደላይ መጥቆ በመጓዝ እውነትን በመናፈቅና በመሻት ይዋትታል፤ ይፈልጋል ነገር ግን ሁሉ ነገር ተስፋ አስቆራጭና አሳዛኝ ይሆንበትና በመቆዘም ለጥያቄዎቹም መልስ ያጣና ይመለሳል፡፡ አሳዛኝ ነው ቤተ ክርስቲያኗ ባሳለፈችው ዘመን ንጽጽራዊ በሆነ በዓለም እይታ በዘመናዊ ዕውቀትና ጥበብ እንደ አቡነ ጳውሎስ ያለ ፓትርያርክ ተገኝቶ አያውቅም ይላሉ ነገር ግን በዘረኝነት፤ በቤተሰባዊ አስተዳደርና በአንባገነንነት ላይመለሱ በድለው አለፉ፡፡ ለዚህ ነው በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ታላቁን አባት የማስታወስና በሞታቸው እንኳን የማዘን ሁኔታ የሌለው፡፡ ያረፉበት ቀን እንኳን ከመታወስ ይልቅ የጠፋው ምን አልባት የሚያስታውሷቸው ዘመዶቻቸውና ጥቅመኞቹ ናቸው ያሳዝናል፡፡

  ያገሬ ሰው ሆድ ሲብሰው ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባው ይላል፤ በአቡነ ጳውሎስ እረፍት ቤተ ክርሲቲያኗ ታርፋለች ሲባል የባሰውና ቤተ ክርሲቲያኗን ወደ ከፋ ምዝበራና በዘረኝነት ተገን የሌቦች ቡድን የተዋቀረበት ሆነ ሊቃነ ጳጳሳቱም ለቤተ ክርስቲያን የሚበጀውንባወ ጡት ሕግ መሰረት ከመስራትና ከመቆርቆር ይልቅ የየትኛው ቡድን አባልና ደጋፊ ብሆን ጥቅሜ ይከበርልኛል ዘመዶቼ ያልፍላቸዋል በሚል ከንቱ እሳቤ በመተብተብ በእምነት ዛሉ ለተጠሩበት ዓላማና ለተለዬለት የእምነት ተልእኮ ታማኝ መሆን አቅቶአቸዋል፤ ያሳዝናል ምን ለማግኘት የት ለመድረስ እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡

  ራቁትነት ከዚህ በላይ ምን አለ፤ እግዚአብሔርም ወዴት ናችሁ ብሎ ለመጠየቅና ለመፈለግ በሰሩት ስራ የሚጸጸት የተዘጋጀ ልብ ጠፍቶኣል፡፡ የመንግስትም ሆኔታ ግራ ያጋባል፡፡ የሚገርመው እንዴት ዶ/ር ሽፈራውና ሌሎች አካላት ለቤተ ክርስቲያኗ መፍትሄ ይሰጣሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ እነሱማ ራቁቷን ስትንከራተት አገኟት፡፡ በጦር ሜዳ መካከል እንደ ተገኘ ጠላት ተረባረቡባት፤ ምክንያቱም እንኳንም እናቴ ሞታ እንዲሁም እልቅስ አልቅስ ይለኛል እንዲሉ አሳፋሪ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ጭራሽ አባበሱት፤ ከመፍትሄው ይልቅ ስልጠና የግንዛቤ ማስጨበጫ በሚል ሰበብ ከዘራፊዎቹና ከተከሳሾች ጋር በመጎዳኘት የተከሰሱበትን ጉዳይ ከማጣራትና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ አድበሰበሱት አሁንማ ጓደኛ ነን አብረን እንሰራለን እየተባለም ነው መደናነቅ ተጀምሯል፡፡

  ወይ ዶ/ር ሽፈራውና የፌደራል ጉዳዮች ሰራተኞች፤ ከዚህ በፊት በሸዋ ተወላጅነትና በኦሮሞነት ብቻ ለበቂ ምክንያት ከህጋዊ አሰራር ውጪ ተበድለናል ይታይልን የሚሉ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰራተኞች አቤቱታ ለፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ምርጫው ይለቅና በጥልቀት ተወያይተን መፍትሔ እንሰጣለን ተባለ፡፡ ወይ ዶ/ር ሽፈራው ታሪክና እውነት ይፍረድ፤ ፍርዱ ይህ ከሆነ የት ይኬድ፤ ስራው ይገርማል(ፍትህ በነዶ/ር ስትከሳና ስትጎሳቆል ትዕቢት በልበ ሙሉነት ሲንጎባለል ተመለከትን) ይሁና…

  ቤተ ክርስቲያኗ የተዋረደችው እኮ በአንድ ተራ ዲያቆን ለዛውም ዲቁናውን እንኳን በቅጥ ያላደራጀና ያላደላደለ ውዳሴ ማርያም መድገም የማይችል በማንኛውም መመዘኛ ለስራ አስኪያጅነት የማይበቃና የማይመጥን በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጦ በፓትርያሪክ የተሾመን ሊቀ ጳጳስ ከመንበሩ አፈናቅሎ እንደዚያ ያለ ዘግናኝ ስህተት ሲፈጸም ቆሞ መመልከት ትክክል ነው? ጉዳዩስ የግለሰብ ጉዳይ ነው? ዝምታው ምን ያመላክታል? ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያኗ በእምነቱ የቆረጠ ኣባት በማጣቷ ለራቁትነት የተዳረገችው፡፡ ለተራና ለምናምንቴ ሰዎች ተላልፋ የተሰጠችው፡፡ እባካችሁ አባቶች ከዘረኝነትና ከወገንተኝነት ጸድታችሁ ቤተ ክርስቲያንን ነጻ ሊያወጣ በሚችል መልኩ ተቀናጁ ነገሮች ይፈተሹ መበታተንና በተለያየ ጎራ መሮጡ ይቅርባችሁ፡፡ ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ፡፡

  በአንድ ወቅት አንድ ሊቀ ጳጳስ ለአንድ የወንዛቸው ልጅ በላኩት መልዕክት ላይ፣ የአካባቢህን ሰውና ያገርህን ሰው እየጠከምክ እራስህን ጥቀም፣ ጥቅምም ከሆነ ከነሱ ተጠቀም፤ በማለት ሰው እየሰማቸው በድፍረት ተናግረዋል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ምን አልባት አገር ወዳድነት? ቂቂቂ ዝቅጠትና ራቁትነት፡፡ ከዚክ በላይ ምን አለ? ሌሎቹስ ምን እያደረጉ ነው? በእውነት ለእምነታቸው ተለይተው ቆርጠዋል ያሳዝናል…

  …ሞት ላይቀር ምንድነው ማንቋረር እንዲሉ አበው ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አምባገነንነትና ዘረኝነት ለታላቁ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም አልበጀ ይልቅስ ታሪክ የጣለብዎትን የቤተ ክርስቲያን ስልጣንና አደራ ሁሉን አቀፋ አባት ሆነው ቢያሳልፉት ይሻላል፡፡ በተለያየ ነገር ተተብትበው ሌትና ቀን ለሚወተውትዎት ጥቅመኞች ብቻ ጆሮዎን ከመስጠት ተቆጥበው በሃይማኖት ከበቁትና አጠገብዎ ካሉት ጳጳሳት ጋር ቆም ብለው ቢያሰላስሉ ይሻላል፡፡ በጸሎት ቢተጉ ይሻላል፡፡

  እነዚህ በዙሪያዎት ለአደን እንዳደባ ተኩላ የሚያንዣብቡትን የተደራጁ ሌቦችና አማካሪዎች ከቤተ ክርስቲያንዎና በመንፈስ ቅዱስ ከተሰጠዎ ስልጣን አይበልጡም፡፡ ሕጉ አለልዎ መንፈሳዊና ቁጥብ የሆኑ ጳጳሳት አሉልዎ በጸሎት የሚያግዙዎ አበው በየገዳሙ አሉልዎ እባክዎ ያስቡበት፤ ቤተ ክርስቲያኗን አያስበሏት፤ በተወራልዎና በተደረገልዎ መጠን ሳይሆን ማሰብ ያለብዎ በህጋዊነት
  ይመኑ፤ ለሲኖዶሱም ክብር ይስጡ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ይፍሩ? ምክር አይደለም የመረረ ማስጠንቀቂያና ላለመፈረካከስ መድሃኒት ነው ብለን ነው አስተዳደርዎ ዘቅጧል ተበላስቷል ዘረኝነት አይኑን አፍጥጦ ተጋኖብዎታል በኃላ የተቋጠረው ውል እንዳይጠፋና መመለሻው እንዳይቸግር ትህትናን በመላበስ ቢያስቡበት ይሻላል እርስዎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና የሁሉም አባት መሆንዎን አይዘንጉት እኛ አምነናል እስርዎም ይመኑበት

  ሞት ላይቀር .. ካለፉት አባቶች ደጉንና ክፉውን መመርመርና መማር ይበጃል፡፡ ይህ ካልሆነ የመረረው ይመጣል፡፡ አቡነ ማቴዎስም ከተደበቁበት ዋሻ ይውጡና እውነትን ይጋፈጡ!!!

  • Anonymous August 2, 2015 at 5:40 am Reply

   ወንድሜ የአቶ የማነ ጓደኛ በእርግጠኝነት በቤተክርስቲያን ጉዳይ ታመሃል ጓደኛህ እንደዚህ ያለ ድፍረትን ያገኘው ለቤክርስቲያኗ ትኩረት ከማይሰጡ መሪዎችና የጥቅም ተጋሪዎች ነው፡፡ የሰጠኸው የተብራራ ገለጻ አሳዛኝና የሚያስለቅስ ነው ለሌቦቱና ለታወሩት ግን ድንጋጤና በምን መንገድ እናድበስብሰው ነው፡፡

   መንግስት በእርግጠኝነት ለህዝብና ለቤተክርስቲን በመቆም ጣልቃ መግባት አለበት፡፡ በግፍ የተባረሩትና የታገዱት የሀገረ ስብከቱም ሰራተኞች ትኩረት ተሰጥቶት መመለስና መፈተሸ አለበት፡፡ የሊቀ ጳጳሱም ከስልጣን መታገድና ዝም መባሉ የተቋሟ ውርደት ነው፡፡ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በፍጥነት መጠገን ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ካልሆነ መገነጣጠሉና መለያየቱ የማይቀር ነው፡፡ ቃለ ህይወት ያሰማል ዶ/ር ሽፈራው እባክዎት አይመጥንዎትም ከሀገር ከህዝብ እንዲሁም ከእውነት ጋር ቢቆሙ የታሪክ ጀግና ያስብልዎታል፡፡ የተባረሩትንና የታገዱትን የሀ/ቱን ሠራተኞች ከፍትሃዊነት አንጻር መድረክ ተዘጋጅቶ የማነም ባለበት ይነጋገሩ፡፡ ቦታና መድረክ ይመቻችላቸው፡፡ ባይናቁ ይበጃል በኃላ….፡፡

  • Anonymous August 2, 2015 at 5:57 am Reply

   ለማንኛውም ወንዝ ያፈራሽ ዳግማዊት ጣይቱ (ምንም እንኳን የእናት ሆድ ዝጉርጉር ነው ቢባልም) ወ/ሮ መና ጀግና ነሽ፡፡ ነገር ግን ወንድምሽ አቡ(የሌብነት ስሙ ሩፋኤል ሞት የሌለና ጊዜ የማይለወጥ ይመስለዋል የዘረፈውን ብር ሳይበላው ይሞታል እግዚአብሔር ይቀጣል) አሑንም እያሳየው ነው ከያዘው ህመም መማር ነበረበት፡፡ .

  • Anonymous August 2, 2015 at 6:04 am Reply

   The church should think over it thoroughly, and correct her admin, wipe out the plunderer and give position to the scholars. This should be a strict motto for the church.
   Mena is Hero of the church Among woman of the church member.

 5. Anonymous August 6, 2015 at 3:57 pm Reply

  በቤተክርስቲያናችን በሰማዕትነት ባለፉ ድንቅ የተዋህዶ ፈርጦች፤ ለዕምነታቸውና ለምዕመኖቻቸው ሲሉ ሂወታቸውን መሰዋት ባደረጉ የዕምነረትና የሀገር ምርጥ አባቶች ቦታ በዘመናችን የተቀመጡ የቤተክርስቲያኒቷ የጊዜው አለቃዎች ይህን ሰማያዊ የቅድስና የአገልግሎት ቦታ ለመቀራመትና ለመዝረፍ ለአንድ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪ ለመሆን መነሻ ብር 50 ሺህ፣ ድቁና ለመቀበል መነሻ ብር 35 ሺህ፣ ለዝውውር መነሻ ብር 30 ሺህ፣ ለጵጵስና መነሻ ብር 300 ሺህ፣ ለዋና ጸሐፊነት መነሻ ብር 80 ሺህ፣ ለኮቴ እንደ ቦታው ገበያ ሁኔታ በአደባባይ ተመን አስቀምጠው ቤተክርስቲያኒቷን እንደ አልባሌ ሸቀጥ ሲቀራመቷትና ሲሻሻጡባት ማየትና መስማት የእኛ ትውልድ እጣ ፈንታ ለመሆኑ ምን ይሆን የቃሉ ፍጻሜ ይሆን እንዴ በጣም በጣም በጣም ግራ ያጋባል፡፡
  በቀጥታ የመንግስት እጅም በእያንዳንዱ የዝውውር፣ የሹመት፣ የሽያጭ ተግባር እጁ እንዳለበት ማየት መስማት ለስልጣንም ለሀገርም አይበጅም፡፡ የቁልቢን ገቢ የሚቀራመተው መከላከያው ነው ሲባል ቀልድ ይመስለን ነበር፡፡ ለካስ እውነታው ግልጽ የሆነልን እዚሁ ርዕሰ ከተማው በሚደረገው በህጋዊው የመንግስት አስተዳደር መዋቅር የቤተክርስቲያኒቱን የሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅነትና ጵጵስና ሹመት መደብ ደልደላ መሆኑ ነው፡፡ ከሰባት አመት በፊት ከክፍለ ሀገር የመጣ አንድ ቄስ አሁን እዚህ አዲስ አበባ በዶልፊን ገበያ ሲደራደር ያየ ደላላ ሰውዬው ቀጥሎ በጉልላቱ ሊደራደር ተመልሶ እንደሚመጣ አትጠራጠሩ ያለው ለካ የወደፊቱ ታይቶት ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: