ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ

His Grace Abune Ermias00

ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ
(ከታኅሣሥ 1925 – ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም.)

prayer service aba erm0

ጸሎተ ፍትሐቱ እና ሥርዐተ ቀብሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተከናውኗል(ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን)

ልደት እና ትምህርት

ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ ከአባታቸው ከመምህር ሀብተ ማርያም ደስታ ተክሌ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በስሙ ቸርነት ታኅሣሥ 19 ቀን 1925 ዓ.ም. በድሮው አጠራር ሸዋ ጠቅላይ ግዛት እየተባለ ይጠራ በነበረው እንሳሮ ወረዳ በአኹኑ አጠራር በሰላሌ አውራጃ በውጫሌ ወረዳ ልዩ ስሙ በርጋፈት ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተወለዱ፡፡

ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ በታላቁ ገዳም በጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም ገብተው ከመምህር ደነቀ ወልደ ጊዮርጊስ ከፊደል ጀምሮ የዳዊት ንባብ እና የቃል ትምህርት ተምረዋል፡፡ ከመምህር ገብረ ጊዮርጊስ እንግዳወርቅ መዝገብ ቅዳሴን ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠልም በ1945 ዓ.ም. ወደ ታላቁ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በመሔድ ከአለቃ ዐምደ ሥላሴ ኃይለ ማርያም ቅኔ ከእነአገባቡ እንዲኹም የባሕረ ሐሳብ ትምህርት አጠናቀው ተምረዋል፡፡

በ1950 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ ከመልአከ ገነት አፈወርቅ ገብረ ሥላሴ እና ከአለቃ ታመነ አግደው የብሉያትን ትርጓሜ ተምረዋል፡፡

የአገልግሎት ኹኔታን በተመለከተ

 1. ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቱ በሚያስተዳድራቸው መሥሪያ ቤቶች እየተዘዋወሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በዚኽ መሠረትም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የስብከተ ወንጌል ማኅበር ሲቋቋም የትምህርት ክፍል ሓላፊ በመኾን፤
 2. በጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት በመምህርነት
 3. በኢሉባቦር ሀገረ ስብከት በጎሬ ወረዳ በስብከተ ወንጌል እና የአውራጃው ቤተ ክህነት ሓላፊ በመኾን፤ እንዲኹም በካህናት ማሠልጠኛ በመምህርነት፤ አገልግለዋል፡፡
 4. ከ1953 – 1978 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ የጎሬ አውራጃዎች ወንጌልን በማስተማር አገልግለዋል፡፡
 5. ከ1978 – 1983 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሓላፊ በመኾን ሠርተዋል፡፡
 6. ከ1983 – 1987 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የቅዱስ ፓትርያርክ ግቢ ንብረት ሓላፊ በመኾን ሠርተዋል፡፡
 7. ከ1987 – 1991 ዓ.ም. ድረስ የቅዱስ ሲኖዶስ ማኅበራዊ ኑሮ መጋቢ ኾነው ሠርተዋል፡፡
 8. ሐምሌ 5 ቀን 1991 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አንብሮተ እድ የኤጴስ ቆጶስነት ማዕርግ አግኝተዋል፡፡ እንዲኹም የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የበላይ ሓላፊ ኾነው አገልግለዋል፡፡
 9. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በመኾን ለ6 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

የተለያዩ የትሩፋት ሥራዎችን በተመለከተ

 1. ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ ከራሳቸው እና ከሚረዷቸው ቤተሰቦች ጥቅም ይልቅ የሌሎች ችግረኞችን ጥቅም የሚያስቀድሙ ቸር ሩኅሩኅ አባት እንደመኾናቸው ልማትን ማእከል ያደረገ የተለያዩ የትሩፋት ሥራዎችን አበርክተዋል፤ ለማስረጃም ያኽል፤
 2. በበርጋፈት ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመክፈት ለመምህራንና ደቀ መዛሙርቱ ሠርክ ኅብስት የሚኾን ገንዘብ ከደመወዛቸው በመደጎም የአካባቢው ልጆች ተምረው ሥልጣነ ክህነት ተቀብለው ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲበቁ አድርገዋል፡፡
 3. ብፁዕነታቸው ትምህርት እንዲስፋፋ የቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ምንጭ እንዳይደርቅ ተተኪ ደቀ መዛሙርት እንዲወጡ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሣ በጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም የንባብ መምህር በግል ገንዘባቸው ቀጥረዋል፤ እንዲኹም
 4. ሰው ለሰው እየተባለ ከሚጠራው በጎ አድራጊ ድርጅት ሓላፊዎች ጋር ገጽ ለገጽ በመነጋገር ከበርጋፈት መንፈሳዊ ት/ቤት ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከ1 – 8 እንዲሠራ በመጠየቅ እጅግ ዘመናዊ የኾነ ትምህርት ቤት እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ የመምህራን መኖርያ ቤትም አብሮ እንዲሠራ፣ የሶላር ሲስተም መብራት እንዲገባላቸው በማድረግ ከፍተኛ የኾነ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአኹኑ ወቅትም ከ4,000 ያላነሱ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
 5. ብፁዕነታቸው ድንቁርና ጠፍቶ ዕውቀት እንዲስፋፋ፣ በሽታ ጠፍቶ ጤንነት እንዲረጋገጥ፤ የመኪና መንገድ፣ የጤና ኬላ ተሠርቶ ኅብረተሰቡ እንዲረዳ በማድረግ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አገልግለዋል፡፡

prayer service aba erm
ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በልዩ ልዩ ሆስፒታሎች በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በ82 ዓመታቸው ከዚኽ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሥርዐተ ቀብራቸውም በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች እና ሠራተኞች፤ ወዳጅ ዘመድ የትውልድ አካባቢ ነዋሪዎች በተገኙበት አቶ ጌታቸው ዓለማየሁ የተባሉ የቅርብ ወዳጃቸው በግል ገንዘባቸው ባሠሩላቸው መካነ መቃብር ዛሬ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈጽሟል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ለደጋግ አባቶች ባዘጋጀው መካነ ሕይወት ያሳርፍልን

Advertisements

3 thoughts on “ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ

 1. ተስፋ July 23, 2015 at 4:53 am Reply

  የሞተውን ታንቆለጳጵሳላችሁ በሕይወት ያለውን ትራገማላችሁ ይሄኔ በሕይወት እያሉ አንድ ቀን ስለሳቸው መልካም አውርታችሁ አታውቁም እናንተ የእፉኝት ልጆች የወላጆቻችሁ ገዳዮች ገና የጻድቃን ደም ይፋረዳችኋል የልጅ ልጆቻችሁን ሳይቀር የቅዱሳን ደም የፈረዳችኋል እናንተ በላእተ ሰብእ ኢየሱስን የሚጠላ ሁሉ የተረገመ ይሁን

 2. haile alemu July 24, 2015 at 9:59 pm Reply

  ya ortodxse edzi nwe

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: