ሰበር ዜና – የመንበረ ፓትርያርኩ መጋቢ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ዐረፉ

 • የቀብር ሥርዐታቸው ነገ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት ይፈጸማል
 • ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የ5 ቀናት የሊባኖስ – ቤሩት ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ይመለሳሉ
His Grace Abune Ermias

በቅዱሳን ፓትርያርኮች መጋቢነታቸው፣ ጸጥታ እና ርጋታ በተመላበት ትሑት ሰብእናቸው እና ረድኤታቸው የሚታወሱት – ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ

በትሑት ሰብእናቸው እና በቅዱሳን ፓትርያርኮች መጋቢነታቸው የሚታወቁት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የበላይ ጠባቂ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ዐረፉ፡፡

ዛሬ፣ ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ገደማ በመንበረ ፓትርያርኩ በሚገኘው መኖርያቸው ያረፉት ብፁዕነታቸው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከኩላሊት ሕመም ጋር በተያያዘ በሕክምና ሲረዱ መቆየታቸው ተገልጧል፡፡

ጸጥታ እና ርጋታ የተመላበት ትሑት ሰብእና የተላበሱት ግብረ ገቡ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ ትምህርታቸው መጻሕፍተ ሐዲሳት እና ቅዳሴ ሲኾን ከመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እስከ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ድረስ በመንበረ ፓትርያርኩ ለረጅም ጊዜ በመጋቢነት አገልግለዋል – ‹‹ቤታቸው ወደ አዋሬ ነበር፤ ጵጵስና እስኪሾሙ ድረስ ከአዋሬ እየተመላለሱ በመንበረ ፓትርያርኩ እንደ ግቢ ሚኒስቴር ነበሩ፤ የፓትርያርኮቹ መጋቢ ነበሩ፡፡››

አሳዳጊ አልባዎችን በአይዞኽታቸው፣ የተቸገሩትን በረድኤታቸው ሲደግፉ የኖሩት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ በስብከተ ወንጌል እና ሰንበት ት/ቤቶችን በማቋቋም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በገንዘባቸው እና ገባሬ ሠናይ ምእመናንን በማስተባበር ችግረኞች የሚማሩበት ዘመናዊ ትምህርት ቤት(በሙከጡሪ የመርጋፋት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበካ) አሠርተዋል፡፡

Beale Simetብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ የአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሰባተኛ ዓመት በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከበረበት ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም.፣ በቅዱስነታቸው አንብሮተ ዕድ ከተሾሙት 16 ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ነበሩ፡፡

በኤጲስ ቆጶሳት ጸሎተ ሥርዐተ ሢመቱ፣ በፊት ስማቸው አባ ገብረ ወልድ ኃይለ ማርያምብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ተብለው የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጳጳስ የኾኑት ብፁዕነታቸው፣ ከ፲፱፻፺፪ – ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ለስድስት ዓመታት በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት ተመርጠው አገልግለዋል፤ በመንበረ ፓትርያርኩ ቤተ መጻሕፍትም በሓላፊነት ሠርተዋል፡፡

His Grace Abune Ermiasየመምህረ ትሕትና እና ረዳኢ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሥርዐተ ቀብር፣ ነገ ሐምሌ ፲፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከጸሎተ ቅዳሴ ፍጻሜ በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ አበው መነኰሳት፣ ካህናት እና ምእመናን በተገኙበት ሥርዐተ ምንኵስና በተቀበሉበት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ይፈጸማል፡፡

በሊባኖስ – ቤሩት ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እና ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጋር ለአምስት ቀናት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያጠናቀቁት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ነገ ጠዋት አዲስ አበባ ደርሰው በብፁዕነታቸው ሥርዐተ ቀብር እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይድረሰን፡፡

4 thoughts on “ሰበር ዜና – የመንበረ ፓትርያርኩ መጋቢ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ዐረፉ

 1. […] Source:: haratewahido […]

 2. ከበደ July 22, 2015 at 12:05 am Reply

  ዜናውን እጥር አደረጋችሁት

 3. ABEBE SEWUNET July 22, 2015 at 4:25 pm Reply

  Egiziabher ybarkachiwu

 4. adis July 22, 2015 at 5:56 pm Reply

  LEABATA CHIN HIYWET YISTACHEW

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: