የአድባራት ሠራተኞች: በሙስና እና በአድልዎ ላይ የተመሠረተው የሀገረ ስብከቱ የዝውውር አሠራር እንዳሳሰባቸው ገለጹ

 • በእገሌ ቦታ በጀትና መደብ በሚል ተገቢ ያልኾነ ጥቅም ይሰጣል፤ ተገቢ የኾነ ጥቅም ይነፈጋል
 • የሒሳብ ሹሞችያለወቅቱ ዝውውር አጥፊዎችን በመከላከል ተጠያቂነትን እንዳያዳፍን ተሰግቷል
 • በግንኙነቱ መስተጓጎል ጠቅ/ቤተ ክህነቱ ለሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች አቤቱታ ምላሽ አይሰጥም
 • ‹‹አቤቱታችንን የት እና ለማን እንደምናሰማ ግራ ተጋብተናል››/የአጥቢያ ሠራተኞች/

(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ በበርካታ አድባራት የጽ/ቤት ሠራተኞች ላይ እያካሔደ የሚገኘው ዝውውር ‹‹አንዱን በመጥቀም እና ሌላውን በመጉዳት ላይ ያተኮረ ነው›› ያሉ አገልጋዮች አሠራሩ እና አፈጻጸሙ እንዳሳሰባቸው ገለጹ፡፡

በሀገረ ስብከቱ ገዳማት እና አድባራት የሥራ ዕድገት እና ዝውውር የሚጠይቁ በርካታ ሠራተኞች እንዳሉ የገለጹት አገልጋዮቹ÷ የዝውውር አሠራሩ የሥራ መዋቅርን፣ ዕውቀትን፣ ልምድንና በጀትን ያማከለ ሒደት መኾን ሲገባው በግለሰብ ቦታ እና በጀት ላይ ያነጣጠረ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

የሠራተኞች ጥያቄ በአመዛኙ ‹‹በእገሌ ቦታ በጀት እና መደብ አዛውሩኝ ወይም ለእገሌ የተመደበው ቦታ እና በጀት ይሰጠኝ›› እየተባለ እንደሚቀርብ አገልጋዮቹ ጠቅሰው፣ ይህም ተገቢ ያልኾነ ጥቅም የሚሰጥበትንና ተገቢ የኾነ ጥቅም ደግሞ የሚከለከልበትን፣ ሰብአዊ መብቶች የሚረገጡበትን አሳሳቢ የዝውውር አሠራር እያሰፈነ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ሲያዘዋውር የሠራተኛው ደመወዝ እና ለቦታው የተመደበው አበል እንዲጠበቅ ቢያዝም ብዙውን ጊዜ ከአድባራቱ ደረጃ እና የመክፈል አቅም አንጻር ተፈጻሚ ባለመኾኑ አገልጋዮቹ ለረጅም ጊዜ በአቤቱታ እንደሚጉላሉ ገልጸዋል፡፡ በሚከፈላቸው ደመወዝ እና አበል፤ በልዩ ልዩ ገቢዎች የሚገኙ ሕጋዊ ጥቅማጥቅሞች እንዲኹም በትራንስፖርት እና መሰል ወጪዎች በአድባራት መካከል ያለው ልዩነት በአግባቡ ባለመመዘኑ የዝውውር አሠራሩ የኑሮ አቅማቸውን እየተፈታተነው እና ሞራላቸውን እየጎዳው መኾኑን አብራርተዋል፡፡

በአድባራት የአገልግሎት እና የአስተዳደር ክፍሎች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት፣ ግጭትን ለማስወገድ እና ለማረጋጋት በሚል በሀገረ ስብከቱ ዝውውር እንደሚፈጸም አገልጋዮቹ ጠቁመዋል፡፡ ይኹንና ለአለመግባባቱ በመንሥኤነት የቀረቡ አቤቱታዎች ታይተው ውሳኔ ሳያገኙ ዝውውር እንደሚፈጸም፤ ይህም ለሥራው ከመቆርቆር ሳይኾን በማስረጃ እና በማጣራት የተረጋገጠውን አቤቱታ በማዳፈን አንዱን ለመጥቀምና ሌላውን ለመጉዳት የታሰበ እንደሚያስመስለው፤ ጥቂት በማይባሉ አጋጣሚዎችም የአንድ አካባቢ ተወላጆች እየተለዩ በደል የሚፈጸምበት እንደኾነ አልሸሸጉም፡፡

በዝውውሩ አፈጻጸም ከሒሳብ ሹሞች እና ከቁጥጥሮች አንጻር እየተካሔደ ያለው ዝውውር ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው አገልጋዮቹ ይጠቁማሉ፡፡ የዝውውሩ አፈጻጸም በተለይ ሒሳብ ሹሞች ኦዲት ሳይደረጉና አስፈላጊውን ክሊራንስ ለሀገረ ስብከቱ ሳያቀርቡ ያለወቅቱ እንዳይዘዋወሩ በሚያዝያ አጋማሽ ከተላለፈው የአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ጋር ያልተግባባና የአስተዳደር ጉባኤውም የማያውቀው ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ የበጀት ካሌንደር፣ ከሰኔ ፴ እስከ ሐምሌ መጨረሻ የዓመታዊ ሒሳብ ምርመራ ወቅት ሲኾን ከሐምሌ አንድ ጀምሮ በኹሉም አድባራት 52 ያህል ኦዲተሮች ተመድበዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ደረጃ የነጠላ ሒሳብ አያያዙ የተሟሉ የሒሳብ መግለጫዎች ያልተዘጋጁበት እና ለውስጥ ምርመራ የማያመች በመኾኑ የሒሳብ ምርመራ ለማካሔድ እና አስተያየት ለመስጠት የማያስችል(Disclaimer) እንደኾነ በሪፖርቶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

‹‹የነጠላ የሒሳብ ምዘገባ መርሕ እየተከተልን የሒሳብ ሥርዐቱ ግለሰብ እና ሰነድ ነጻ ኾነው እንዲሔዱ የሚያደርግ ሥርዐት አለው ወይ?›› በማለት አገልጋዮቹ ይጠይቃሉ፡፡ በአሠራሩ፣ ገቢው ለምን እንደገባ ወጪው ለምን እንደወጣ የሚያውቀው የሠራው ሰው በመኾኑ ሥርዐቱ ግለሰብን መሠረት ያደረገ እንደኾነና በምርመራ ወቅት እንደ ኹለትዮሽ የሒሳብ ምዘገባ መርሕ፣ ሰነድ ብቻ ስለ ገቢ እና ወጪ በበቂ ሊያስረዳ የማይችልበት ኹኔታ እንዳለ ያትታሉ፡፡ ከዚኽ አንጻር በአኹኑ ወቅት የአድባራት ሒሳብ ሹሞች ዝውውር ትዕግሥት ሊደረግበት ሲገባ በብዛት መፈጸሙ፣ ማስረጃን በማጥፋት እና ተጠያቂነትን በማዳፈን አጥፊዎችን ለመከላከል እና ንጹሐንን ለመጉዳት የታሰበበት ያስመስለዋል፡፡

በተለይ ሀገረ ስብከቱ በመደባቸው ልኡካን በአለቆች ላይ የቀረቡ ጥፋቶች በማስረጃ እና በማጣራት በተረጋገጠባቸው አንዳንድ አድባራት (እንደ ብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም) አቤቱታ አቅራቢ ሒሳብ ሹሞች በዝውውር እንዲነሡ መደረጉ የዝውውሩ አፈጻጸም፣ ‹‹ከአገልግሎቱ ይልቅ ጥቅምንና ግለሰቦችን መሠረት ያደረገና ተጠያቂነትን የሚያዳፍን መኾኑን የሚያረጋግጥ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ ሕገ ወጥ ጥቅሞችን በማስቀረት ሠራተኛው የሥራ ዋስትናው ተጠብቆ እና ተረጋግቶ ይሠራ ዘንድ ከአስገዳጅ ኹኔታዎች ውጭ ዝውውር እንዳይፈጸም በሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ በተደጋጋሚ የተላለፉ ውሳኔዎች መጣሳቸውን አገልጋዮቹ ይናገራሉ፡፡ ከዝውውር እና አዲስ ቅጥር ይልቅ ሀገረ ስብከቱ በየአድባራቱ እና በየገዳማቱ ያሉትን የአስተዳደር ሥራዎች በመገምገም እና እንዲሻሻል ድጋፍ እየሰጠ በዋናነት የልማት ፕሮጀክቶችን እየነደፈ በማልማት ላይ እንደሚያተኩር የወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሥራቸው መጀመሪያ የሰጡትን ቃላቸውንም ያጠፉበት ነው  ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ መሾማቸውን ተከትሎ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር ያለው ግንኙነት መስተጓጎሉን ያወሱት አገልጋዮቹ፣ በአኹኑ ወቅት አቤቱታቸውን የት እና ለማን ማሰማት እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸውን በምሬት ተናግረዋል፡፡

በፓትርያርኩ የተመደቡት÷ ‹‹ሙስና እንዲወገድ፣ ፍትሕ ርትዕ እንዲሰፍን፣ መልካም አስተዳደር እንዲነግሥ›› እንደኾነ ቀደም ሲል ለኢትዮ-ምኅዳር  የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ለሌላ ሰው ዕድገት ለማስገኘት ሲባል የደመወዝ ቅናሽ እየተደረገባቸው ወደ ሩቅ ቦታዎች ጭምር የተዘዋወሩ እንዳሉ ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ዝውውር መደበኛ አሠራር እንደኾነና እርሳቸውም ከ15 ጊዜ በላይ ተዘዋውረው መሥራታቸውን ያወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹አጥፊ ሲገኝ እንደ ርምጃ የሚወሰደው ማዘዋወር ነው፤ ሰውዬውም ስለማያርመው ከፍተኛ የሰው ኃይል ዝውውር በሀገረ ስብከቱ ይካሔዳል፤በዚኽ የተነሣ ሠራተኛውም የተረጋጋ አይደለም፤ በመኾኑም አስፈላጊነቱ ካልታመነበት በቀር ዝውውርን በከፍተኛ ደረጃ ለማቆም ወስነናል፡፡ ዝውውሩ ታምኖበት ሲፈጸመም የሚነሣው፣ የሚዘዋወረው ሠራተኛው እንጂ ብሔሩ አይደለም፡፡›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

 

Advertisements

4 thoughts on “የአድባራት ሠራተኞች: በሙስና እና በአድልዎ ላይ የተመሠረተው የሀገረ ስብከቱ የዝውውር አሠራር እንዳሳሰባቸው ገለጹ

 1. Anonymous July 13, 2015 at 5:20 am Reply

  በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶስ በክብሩና በሉአላዊነቱ አለ ማለት ያስቸግራል አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ነው ነገሩ፡፡
  በጣም ተደራጅተዋል ወንጀሉን እየፈጸሙ ያሉት በእቅድና በቅንጅት ነው መንግስትም ሳያውቀው የቀረ አይመስልም ነገር ግን የመንግስት ቸልተኝነት ሆን ተብሎ የታሰበበት ይሆናል፡፡ ምክንያቱስ መንግስትስ ማን ሆነና ባለስልጣናቱ የሚውሉት የሚበሉት የሚጠጡት ከማን ጋር ሆነና ደ/ር ሽፈራው የሰራተኞችን አቤቱታ ወደጎን በመተው ተስማምቶ እየሰራ ያለው ከማን ጋር ነው በአጠቃላይ እውነት የለም ታጋይ የነበረችው የአቶ የማነ ባለቤት እኮ ልክ እንደ አዜብ መስፍን ያደርጋታል ብቻ ይቅር ፡፡

 2. Anonymous July 13, 2015 at 11:57 am Reply

  የብሔረፅጌ ማርያሙ ነአኵቶ ለአብና የላፍቶ ሚካኤሉ ተክለማርያም በተለየ መልኩ የቤተክርስቲያን ቦታ እየሸነሸኑ የማከራየት መብት የተሰጣቸው ናቸው፡፡ነአኵቶ መመሪያ ከወጣ በኋላ ወደወንዙ(ወደ አቃቂ) ያለውን ይዞታ ቀኑን መመሪያው ከመውጣቱ በፊት(back-date) በማድረግ የቦሌ ቡልቡላን ይዞታ ለጋራዥነት ከያዘው ግለሰብ ጋር የጋራዥ የኪራይ ውል የተዋወለ ሲሆን ተክለማርያም በበኵሉ የቅ/ገብርኤልን ጸበል ይዞታ ቆርጦ እንዲሁ በ19ሺህ ብር አከራይቷል፡፡የመቃብርና የሐውልት ብር የቢሮ ሰራተኞችና የአለቆቹ መክበሪያ ነው፡፡

  ሁለቱም አለቆች ሲበዛ እልኸኞች፣ቂመኞች፣ተገለባባጮች፣በአንድ ብሔር ጥላቻ የተለከፉ፣በግልጽ ጸጥታ ሲነግሥ ይጨንቀናል የሚሉ፣በራሳቸው ስልጣን ባልተገባ መንገድ በሰፊው የሰራተኛ ቅጥር የሚፈጽሙ፣ሰ/ተማሪና ካሕን ሰው የማይመስላቸው፣ከምዕመን አስከ ሊቃውንት ርስበርስ በመከፋፈል የሚያናክሱ፣አንደበታቸውን የማይቆጣጠሩ፣በየፍርድ ቤቱና በየፖሊስ ጣቢያው ከዘበኛ እስከ ጸሐፊ እየተካሰሱ በቤተክርስቲያን ብር መቀለዳቸው ሳያንስ እከሌ የተባለውን ቄስ በፍርድ ቤት ስላሸነፍነው እልል በሉ የሚሉ በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን ለዛ የሌላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡

  ሆኖም ማሙየ የክፍለከተማው ስራ አስኪያጅ እያለ እሱን እየተንከባከቡ፣ሊቀአእላፍ በላይ ሲመጣ እግር ለግር እየተከተሉ አሁን እነ የማነ ሲሾሙ ደግሞ ለሦስት አመታት ከአድማ እና ተራ ካሕናትን ከማስለቀስ በቀር የረባ ስራ ያልሰሩበትን ደብር እነ ተክለማርያም ደርሰው የልማት አርበኛ ለመባል እነ የማነን ጋብዘው ዜናውን በሀገረስብከቱ ዌብሳይት አስወጥተዋል፡፡ብቻ ያሳዝናል፡፡የተገፉ ካሕናትና ሰ/ተማሪዎች ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ቅዱስ ፓትርያርኩ አጣሪ የላኩበት ደብር የአጣሪው ሪፖርት ሳይሰማ ካሕናቱ የአማሳኞች በትር ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ጥቆማዎችና ማስረጃዎች የሀገረስብከቱ መዝገብ ቤት ውጡዋቸው ይቀራሉ፡፡ከዛ ያ ፍትሕ አገኛለሁ ብሎ የተነሣ ካሕን በላተኛውን አለቃ ይማጸናል፡፡ ደሃ ተበድሎም ይቅርታ ይለምናል፡፡ መቆርቆር ሞኝነት ይሆናል፡፡ ዝምታ ወርቅ ይሏት ብሂል ትነግሣለች፡፡

  አንድ አለቃ የልጆች አባት የሆነና ከቤተክርስቲያን ውጭ ትም ሄዶ ሰርቶ ለመብላት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት የሌለውን ካሕን/መሪጌታ አባሮ ለአንድና ለሁለት አመት ቢያንገለታ ትልቁ ቅጣት ሰራተኛውን ወደ ስራው መልስ የሚል ነው፡፡ ላንገላታበትና ለተሳሰተ አስተዳደራዊ ውሳኔው አይጠየቅም፡፡ ስለዚህ የካሕናት እጣ ፈንታ በአንድ አለቃና ፀሐፊ እጅ ነው፡፡ በስንት ጉባኤ የዋሉ መምህራንም እንዲሁ በእንደነ ለአኵቶ እና ተክለማርያም ባሉ ወፈፌዎች እየተሸማቀቁ እጣቸው አንድም አንገት ደፍቶ መኖር ያ ካልሆነም ከስራና ደሞዝ ታግዶ በ31 ቁጥር አውቶብስ ከለገሀር 4 ኪሎ እየተመላለሱ አዳዲስ ሹማምንትን ደጅ መጥናት ሆኗል፡፡ ይሄ ያሳዝናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየጉባኤው የደከሙላትን ገፍታ ብልጣብልጦችን አንግሣ ልጆቿ በቤታቸው ባይተዋር ሲሆኑ ማየት ያማል፡፡

  እነ የማነ እና በጉባኤ ቤት ያለፈው ሊቁ መጋቤ ብሉይ አእመረ ወደ መንበሩ ሲመጡ እንዲህ አይነት በካሕናትና በሊቃውንት ላይ የሚደርስ አስተዳደራዊ በደል ይረግባል ብለን ጓጉተን ነበር፡፡ የተስፋችንን ፍጻሜ ለማየት አልታደልንም መሰል፡፡ ዛሬም እነዚህ ሰዎች አንድ ሰሞን በተፈጠረው በሰንበት ትምህርት ቤቶችና ሀገረ ስብከቱ ጊዜያዊ አለመግባባት ሽፋን የሀገረ ስብከቱ ቀራቢ መስለውና በአስተዳደሩ ተመክተው የቀደመ አስጸያፊ እና ብሔር ተኮር የሆነ ዘመቻቸውን እንዲሁም ከገንዘብ ያዥ፣ ከሂሳብ ሹም፣ ከቁጥጥርና ከጸሐፊ ጋር የተቀናጀ ስልታዊ ዘረፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከስራ ያስቀየሩትም እንደተቀየረ፣ ያባረሩትም እንደተባረረ፣ ከደረጃ ያወረዱትም እንደወረደ፣ ያጎደሉትም ሂሳብ በፓትርያርኩ እንዲጣራ ቢታዘዝም ምርመራው በሀገረ ስብከቱ እንደተዳፈነ የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ሁኖ ይቅር ተብሏል፡፡

  የነ የማነና የነአእመረ የአጥቢያ ጉብኝት ካሕናትንና ሰንበት ተማሪዎችን እንዲሁም ምዕመናን ሳይሆን አለቆችንና የቢሮ ሰራተኞችን ብቻ እያነጋገሩ ካንድ ወገን የሚመነጭ መረጃን ይዞ ለመሄድ ከሆነ ባይደረግ ይሻላል፡፡ ስራ አስኪያጁ በእጄ ስለሆነ ወላ ሰንበት ተማሪ፤ ወላ ተራ ሰራተኛ ለጥ ሰጥ ብለሽ ተገዢ ለሚሉ እንደ ተክለ ማርያም አይነት ግብዝ አለቆች የልብ ልብ ሰጥቶ የካሕናትንና ሰንበት ት/ቤትን ሰቆቃ ማራዘም ተገቢ አይደለም፡፡

  ይባስ ተብሎ ነአኵቶለአብ የፈለገውን የሚያስቀይርበት፣ ተክለማርያም ያላግባብ ያባረረውን ሰራተኛ መልስ ተብሎም በግልጽ አልመልስም እያለ በሦስት አመታት ቆይታው የረባ ስራ ሳይሰራ እንደ ልማት አርበኛ የሚታይበትና በሀገረ ስብከቱ በይፋ እውቅና እንዲያገኝ የሆነበት አካሄድ አሳዛኝ ነው፡፡ ሰውን ባልዋለበት ማመስገን ደግ አይደለም፡፡ የሁለቱ አለቆች ሪከርድ በክፍለ ከተማው ሀገረ ስብከት ሳይቀር ይታወቃል፡፡ ይሁንእንጅ አዲሱ የሀገረ ስብከት አስተዳደርም ሰዎቹን እንኳን ሊያርማቸው ጭራሽ የሞራል ድጋፍ እየሰጣቸው ይመስላል፡፡ ያሳዝናል፡፡ እድሜያቸውን ባለሙት ልማትና ባሰፈኑት አስተዳደራዊ ሰላም ሳይሆን ባስከፈቱት የወንጀልና የአሰሪና ሰራተኛ የክስ መዝገብ የሚለኩ ሰዎች ያሻቸውን የሚያስቀይሩበት፤ ያሻቸውን ከስራ አፈናቅለው በስዕለት ብር በተገዛ ጠበቃ እያንከራተቱ ምስኪን ካሕናትን በረሀብ አለንጋ መቅጣታቸው የልማት አርበኛ ሲየሰኛቸው ማየት ያሳዝናል፡፡

  • adis July 15, 2015 at 8:29 pm Reply

   TEW MEAZA DEG AYDELEM KANTE BELAY LEBANA AMASAGN
   BEBETEKRISTIYANAWA YELEME ERASH DELALA HUNEH SHENSHINEH YECHERSKEW BOTA BENEAKUTO MAMEKAGNET ATCHILM LIDETAWOCH YISKUBIHAL AWKENBACHUL YELEBNET PATENT YENANTE NEBERENA ZARE BIZUWOCHIN LEBOCH PATENTU SIWESDU MEBTMESLOACHU TICHOHALACHIHU BEBETEKIRSTIYANITWA AYDELM BEALEM YENANTE YAH I’LL LEBA YELEM MERKATOM A
   LATER
   CHIM

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: