የደቀ መዛሙርት ምረቃ ሳምንት ነው – አህጉረ ስብከት እና ኮሌጆች በደቀ መዛሙርት ምልመላ፣ ቅበላ እና የትምህርት ዝግጅት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔዎች ያስከብሩ!

 • ‹‹ደቀ መዛሙርቱ ከየአህጉረ ስብከቱ ተመርጠው ሲላኩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መኾናቸው እና የሃይማኖታቸው ጥንካሬ ታይቶ እንዲመለመሉ አህጉረ ስብከት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡››
 • ‹‹ወደ ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎች እና የሚያስተምሩ መምህራን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀታቸው እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እየታየ ወደ ኮሌጁ ገብተው እንዲማሩ እና እንዲያስተምሩ  ይደረግ፡፡››

/የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም. ውሳኔ/

 • ‹‹የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛየትምህርት ተቋማት እና ማሠልጠኛዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያደርጉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ኾኖ ደቀ መዛሙርት ምልመላ፣ በቅበላ እና በትምህርት ዝግጅት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ በታከለበት ኹኔታ እንዲሠሩ፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይደርስ ዘንድ ተግተን እንሠራለን፡፡››

  /የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ፳፻፯ ዓ.ም. የአቋም መግለጫ/

Logos of the three EOTC theological colleges
ትምህርተ ሃይማኖት ዘኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ድኅነትን ያስገኛል፤ በረከትንም ያሰጣል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ለወደፊቱም የሚኖረውን እውነተኛ አስተምህሮዋን ጠብቃ ካኖረችበት መንገድ አንዱ የትምህርት መስጫ ተቋማትን መመሥረቷ ነው፡፡

የበርካታ የአብነት ት/ቤቶች እና የካህናት ማሠልጠኛዎች ባለቤት የኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ነባሩን አስተምህሮዋን በዘመናዊ አቀራረብ አስፋፍታ እና አጠናክራ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሦስት መንፈሳዊ ኮሌጆችንም ለማቋቋም ችላለች፡፡

ለሦስቱ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዛሬ ቅዳሜ ሰኔ ፳ ቀን ጀምሮ ያለው አንድ ሳምንት የደቀ መዛሙርት የምረቃ ሳምንት ነው፡፡ ከሦስቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች በአጠቃላይ ከ647 በላይ ደቀ መዛሙርት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ይመረቃሉ፡፡

EOTC St.Trinity College Logoከዛሬ 54 ዓመታት በፊት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፋኩልቲዎች እንደ አንዱ በመኾን መንፈሳዊው ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር በከፍተኛ ደረጃ የሚሰጥበት የመጀመሪያው መካነ ጥበብየቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ – በተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲያስተምራቸው የቆዩትን 303 ደቀ መዛሙርት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ያስመርቃል፡፡

በዛሬው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በሚከናወነው የምረቃ መርሐ ግብር÷ በመደበኛ የድኅረ ምረቃ ሲስተማቲክ ቴዎሎጂ 9፣ በቀን መደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ 43፣ በማታ ተከታታይ የመጀመሪያ ዲግሪ 68፣ በማታ ተከታታይ ዲፕሎማ 101፣ በግእዝ ቋንቋ ዲፕሎማ 7 እና በርቀት ትምህርት ሰርተፊኬት 84 ደቀ መዛሙርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ሓላፊነት በታማኝነት ለመወጣት ቃል ኪዳን በመግባት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ይመረቃሉ፤ መመሪያም ይቀበላሉ፡፡

St.Paul collegeየብሉያት እና የሐዲሳት ትርጓሜ ቤት እንዲኹም የአንደኛ ደረጃ ዘመናዊ የአዳሪ ትምህርት ቤት ኾኖ በ፲፱፻፴፮ ዓ.ም. የተቋቋመው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መምህራን ማሠልጠኛ፣ ወደ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ተሸጋግሮ የሰሚነሪ(የአራት ዓመት ኮርስ) የጀመረው በ፲፱፻፸፬ ዓ.ም. ሲኾን ወደ ኮሌጅነት ያደገው ደግሞ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ነው፡፡

ኮሌጁ በዘንድሮው ዓመት 218 ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ ያቀርባል፡፡ በቀጣዩ ሳምንት ኀሙስ፣ ሰኔ ፳፭ ቀን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ የሚመረቁት ደቀ መዛሙርት፡- በቀኑ መደበኛ እና ተመላላሽ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ 16፣ በብሉይ ኪዳን አንድ፣ በቀን መደበኛ እና ተመላላሽ የሰሚናር ዲፕሎማ 21፣ በማታ ተከታታይ የሰሚናር ዲፕሎማ 180 ናቸው፡፡

St Fremnatos Abba Selama Collegeየመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የተቋቋመው በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ወደ ኮሌጅ ደረጃ አድጎ በመደበኛ የዲግሪ መርሐ ግብር ማስተማር የጀመረው በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ነው፡፡ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የተከታታይ ትምህርት መርሐ ግብር በመዘርጋት በማታው ክፍለ ጊዜ ማሠልጠን ጀምሯል፡፡

በቴዎሎጂ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ለሦስተኛ ጊዜ 16 ደቀ መዛሙርትን በማሠልጠን ላይ የሚገኘው ኮሌጁ፣ በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፯ ቀን 126 ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ የሚያበቃ ሲኾን ከእኒኽም 7ቱ በዲግሪ፣ 12ቱ በዲፕሎማ፣ 11 በድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ እና 96 በአጭር ጊዜ ኮርስ በሰርተፊኬት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

Advertisements

3 thoughts on “የደቀ መዛሙርት ምረቃ ሳምንት ነው – አህጉረ ስብከት እና ኮሌጆች በደቀ መዛሙርት ምልመላ፣ ቅበላ እና የትምህርት ዝግጅት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔዎች ያስከብሩ!

 1. ታዛቢው June 29, 2015 at 9:11 am Reply

  በመልካም ምኞት እንጀምር!ውድ ደቀመዛሙርት የዓመታት ልፋታችሁን ውጠየት በመዐርግና በአበው ቡራኬ ለማጠናቀቅ እንኳን አበቃችሁ!ከራሳቸው አልፈው ለሌላ የሚተርፉ ተብላችሁ በአደባባይ በሰውና በእ/ሄር ፊት የድካማችሁ ፍሬ ስለታየ ደስታችሁ ደስታችን ነው!ደስታችሁ የቅድስት ቤ/ክ ደስታ ነው!ደስታውን ያካፈለችንና የራሷን ምልከታ ያንጸበረቀችው ሐራ ብሎግም ለዚህ ገንቢ አቀራረቧና አዘጋገቧ ምስጋናችን ይድረሳት ብለን ጥቂት አስተያየቶችን እንሰንዝር!

  1. መንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ባለፉት አመታት የማታ ስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተቀርጾለት በመላ ሐገሪቱ የቤ/ክ አጥቢያዎች እንዲስፋፋ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በብዙኃን አይዘመርለት እንጅ እጅግ አስመስጋኝ ነው!ከምዕመንነት ባለፈ በአስተዳደሩና በውዳሴ-ቅዳሴው ጉልህ ተሳትፎ ያልነ በራቸውን ብሔሮች ኦርቶደክሳዊነታቸው መንፈሳዊ እውቀትን ታክሎበት የራሳቸውን አጥቢያ በራሳቸው ተወላጆች እንዲመሩ በማብቃት ረገድም ከፍ ያለና ደስ የሚያሰኝ ጎዳና ፈጥረዋል–መንፈሳዊ ኮሌጆቹ፡፡ በጠቅላይ ቤ/ክሕነት፣ በአህጉረ ስብከቶች፣ በወረዳ ቤተ ክሕነቶች እና በአጥቢያዎች በአንጻራዊነት ከቀደመው ጊዜ በተሻለ መልኩ ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የፈለቁ ካሕናትንና የአስተዳደር ሰራተኞችን እንድናይ ኮሌጆቾና የካሕናት ማሰልጠኛ ማዕከላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በልቤ ታላቅ ስፍራ አለው፡፡ የማታ መርሐ ግብሮች በስፋት መሰጠት፣ የሴቶች ተሳትፎ፣ የሌሎችን ሃይማኖታዊ ብሂል ክኛ የሚለይበትን አጥርቶ ሃይማኖትን በማስጠበቅ፣ የውስጥና የውጭ መናፍቃንን በመዋጋት ያደረጉት አስተዋጽኦ ባይዘመርለትም በእኔ ዘንድ ክብር አለው!

  2. ያም ሆኖ በደቀ መዛሙርቱ በኩል በቃል እንጅ በሕይወት ለመስበክ አለመሞከር፣ ከነባሩ ትውፊት ተገናዝቦ ከመራመድ ይልቅ አብነቱን ትምህርት ችላ ብሎ ወደ ዓለማዊነት የተጠጋና ሕዝቡ የሚወደው ይሄ ነው በሚል ሰበብ ሕዝቡ መስማት የሚፈልገውን ብቻ የመናገር ተግሳጽ አልባ ስብከት፣ ጥናቶችንና መጻሕፍትን የማቅረብ የ1980ዎቹ መጨረሻና የ1990ዎቹ መጀመሪያ በጎ ጅምር መደብዘዝ፣ ደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ጊዜ መብት ለማስከበር የሚያነሱዋቸውን ጥያቄዎች ከማቅረብ ያለፈና ለማኅበረ-ምዕመናን የሚደርስ አገልግሎትን ለመስጠት ያለመ ካውንስል(የደቀ መዛሙርት መማከርት) አለመታየቱና እና የመሳሰሉት ከደቀ መዛሙርቱ ስጠብቅ ያላገኘኋቸው ናቸው፡፡

  3. በኮሌጆቹ አስተዳደርም በኩል ካምፓስ የመክፈት፣ የደቀ መዛሙርቱን የተመረጡ የምረቃ ጽሑፎች አለማተም፣ የሚጠቀስ አመታዊም ሆነ ክፍለ-አመታዊ የጥናት መጽሔት ከማውጣት መስነፍ፣ የትምህርት አይነቶችን ለማብዛት ዳተኛ መሆን፣ አሁን ቢሻሻልም የምልመላው መቅለል፣ መጽሄትም ሆነ ጋዜጣ ወይም ወቅታዊ መረጃ በተፋጥኖ የሚሰጥ ዌብ ሳይት አለመኖር፣ የርስበርስም ተቋማዎም ሆነ የተቋማዊ-አጥቢያ ወይም ሀ/ስብከት ትስስር መላላት፣ የደቀ መዛሙርቱንና የተቋሙን አካዴሚካዊ ነጻነት ለማስጠበቅ ያለው ተጋድሎ ማነስ፣ የደቀ መዛሙርቱ መለያ የሆነው ቀሚስ ባልተገቡ ሰዎች እንዳይለበስ የሚደነግግ መመሪያ እንኳ ማስወጣት አቅቶት በፍሬ-ጻማ ሊገኝ እና ሊለበስ የሚገባው ቀሚስ ሁሉም በዘፈቀደ እየተነሳ እያሰፋ መዐርጋቸውን ማሳነሱ፣ የግሬድ አሰጣጥ ልል መሆን፤ በተለይ የቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማታ መርሐ ግብር ብዙኃን ካሕናት አማናውያን ኖሎተ-አባግዕ እንዲሆኑ የፈጠረው እድል አስመስጋኝ ቢሆንም የተማሪ ክትትሉ ማነስና (በተለይ አለቆች ላይ) ያልበቃውን ሁሉ እንደበቃ አድርጎ በልበ-ሰፊነት አግበስብሶ ወደ ምረቃ መንጎዱ ቢታሰብበት ጥሩ ነው፡፡

  4. ለበላይ አካላት(ቅ/ሲኖዶስን ጨምሮ) ትሁት አስተያየቴን ልናገር፡- አሁን ቤ/ክ ለደረሰችበት አገልግሎት እነዚህ በጣት(ያውም በ3 ጣት!) የሚቆጠሩ ኮሌጆች ብቻ መሆናቸው ያውም ገና በቅጡ መንበረ-ፓትርያርክ ተደላድሎ ራሳችንን ከመቻላችን በፊት በጃንሆይ ዘመን በተወጠኑ ኮሌጆች ብቻ ተወስኖ መቅረት፣ እነሱንም ለማስፋፋትና በሰው ኃይል ለማጠናከር የሚካሄደው ጥረት ያለው ተነሳሽነት በእውነቱ የልብ የሚያደርስ አይደለም፡፡ ገቢ የሚያስገኙ ዘመናዊ ት/ቤቶችንና ኮሌጆችን የማስፋፋቱ እንቅስቃሴ ሰፊውን ማኅበረሰብ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ላይ የራሳችንን መንፈሳዊ ኮሌጆችም ማስፋፋት ቢታከልበት መልካም ነው፡፡ በአንዳንድ አባቶችና የአስተዳደር ሰራተኞች ቅድስት ቤ/ክ በስንት ሚሊዮናት እያወጣችና በታላላቆቹ አባቶች በእነ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስና አቡነ ጳውሎስ አርቆ አስተዋይነት ለወደፊቷ ቤ/ክ ተብሎ የተተለመውን የቴዎሎጂ ትምህርት እንደ አብነት ትምህርት አቆርቋዥና እንደ የመናፍቅ በትር እያዩ የምሩቃኑን ሞራል መንካት፣ ወደ አስተዳደር አለማስጠጋት፣ አልፎ ተርፎም ‹‹ይሄ ኮሌጅ ተዘግቶ ክሊኒክ ቢሆን ይሻላል›› እስከ ማለት የደረሱ ዘለፋዎች ሲኖዶሳዊ ልጓም ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ ኋላ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ እንዳይሆን! አመላመሉን በሚመለከትም የተገናዘበና ግልጽ መመሪያ ወጥቶ በጽሑፍም ሆነ በኮሌጆቹ ዌብ ሳይቶች በቀላሉ እንዲደርሱ ቢሆንና ከአጥቢያ እስከ ሀ/ስብከት የተጠናከረ ሥርዓት ቢበጅለት የተመቸ ነው፡፡ እርግጥ ከአብነት ትምህርት የመጋለጥ እድል ያላቸውን የሌላቸውን እኩል የሚያወዳድር መስፈርት መቅረጽ ጥንቃቄ እንደሚሻ ይገባኛል!

  5. በምዕመኑ በኩል በተለይ ራሱን የተዋሕዶ ብቸኛ አርበኛ አድርጎ ማኅበራዊ ሚዲያውንና የቤ/ክ የወጣት ክንፉን በሚቆጣጠረው አካል በኩል፡- አብዛኞቹ ምሩቃን ከእናንተ መካከል የወጡ መሆኑን ዘንግታችሁ ማሳደዱን ሙያ ባታደርጉት፣ ገና ለገና በጣት የሚቆጠሩ ተሐድሶዎች በኮሌጁ ስላለፉ ኮሌጅ ብሎ ነገር አያስፈልግም እያላችሁ የኮሌጅ ጥገኛ የሆነችውን የግብፅ ቤ/ክ መናፈቅ ራስን መቃረን መሆኑን ብትገነዘቡ፣ የቅ/ሥላሴን ምሩቃን ብንወስድ እንኳ ከ2487 ተመራቂ ውስጥ እስካሁን በውግዘት የተለዩ መናፍቃን 5ትም የማይሞሉ ሆነው ሳለ ኮሌጁ ይዘጋ ማለት ‹‹የጎንደር ጉባኤ መናፍቁ አለቃ ታየ እና ፅጌ ስጦታው ስለወጡበት ይዘጋ፤ ወይም የጎጃም ጉባኤ መናፍቁ መሰረት ስብሐት ለአብና መሪጌታ ሙሴ ስለወጡበት ይዘጋ፤ ወይም አንድ ወቅት ከልደታ ቤ/ክ ብዙ ተሐድሶዎች ስለወጡ ሰ/ት/ቤቱ ይዘጋ እንደማለት እንደሆነ ቁጠሩት፣ ምሩቃኑ በ20 አመት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ባይጨመርበት ኖሮ ዛሬ ከምንጸጸትበት 10 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ልናጣ እንችል እንደነበር በማሰብ ከስስት የራቀ እውቅና እንስጣቸው(የሌሎቹን የቤ/ክ ሚና አሳንሶ ተዋሕዶ ከተሐድሶ ጎርፍ የተረፈችው በማኅበረቅዱሳንና በሰ/ት/ቤት ብርታት ብቻ እንደሆነ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ማስተጋባት ተገቢ አይደለም!)፣ እነ የኔታ ደጉ እና እነ የኔታ ገሥላሴ ከቀደምቶቹ፤ እነ የኔታ እሸቱ እነ ወጣቱ መምህር ሮዳስ ካዳዲሶቹ ያሉበትን ተቋም እንደ ተሐድሶ መፈልያ ቆጥሮ ልጆቹን ማሸማቀቅ ርስትን መልቀቅ ነው! በተግባር እንደምናየውም ተሐድሶዎች የእኛን ልጆቹን ማቀፍ ስንፈት በማየት ሁልጊዜም በስመ-ደቀመዛሙርት ለመነገድ እንደተጉ ነው፡፡ ጥንቃቄ!

  6. የኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ወንድሞቻችንንም ሆነ ተቋማቱን የምናይበት ዐይን ኃላፊነትና ወንድማዊነት የተሞላበት ይሁን! ቤ/ክ በፌስቡክ ግድግዳና በብሎግ በሚቀርብ የተቆርቋሪነት ዲስኩር ብቻ አልቆመችም፡፡ ከገጠር ወረዳ ከተማ እስከ ጠ/ቤ/ክሕነት ቅድስት ቤ/ክ አስተምራ ለወግ ማዕረግ ባበቃቻቸው ደቀ መዛሙርት ጭምር እንጅ! ይሄ ርቱዕ ኦርቶዶክሳዊ ለመሰኘት ሲባል ከቅ/ሲኖዶስ በፊት ሰባክያንን እያወገዙ የተማሩትን ገፍቶ አማተሪዝምን ማንገስ የሚሆን አይደለም፡፡ በኮሌጁ ውስጥ እንደ ትምህርት ተቋም የሚኖሩ ውይይቶችንና ጽሑፋዊ ምይይጦችን ሁሉ እየጠለፉ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ማጮኽ ሊኖር ሚገባውን አካዴሚያዊ ነጻነት እንዳይጋፋ ብርቱ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ቤ/ክ ተዋሕዶውን ከንስጥሮሳዊው ወይም ከልዮናዊው ወይም ከሉተራዊው አስተሳሰብ ለይቶ የሚያውቅ ደቀ መዝሙር ለማፍራት በምታደርገው ጥረት ከኮሌጅ አጥር ውጭ ሆኖ ኮርሶቹን እየጠለፉ ከራስ የተዛባ አመለካከት በመግመድ መፈትፈት ነውር ነው፡፡ እየተገናዘብን!!!

  በድጋሚ ምሩቃን፡- አኃው ወ አኃት እንኳን ለዚህ በቃችሁ!!!

 2. Anonymous June 30, 2015 at 3:46 pm Reply

  betikikil tazibewal kale hiwot yasemalin!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: