ቋሚ ሲኖዶስ ለሰንበት ት/ቤቶች የመልካም አስተዳደር እና የዕቅበተ እምነት ጥያቄዎች ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታወቀ

(ሰንደቅ፤ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፲፤ ረቡዕ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

EOTC SSS

በ፬ኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ፍጻሜ ለዕቅበተ እምነት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለፍትሕ መስፈን ወደ ጽርሐ ጽዮን መንበረ ፓትርያርክ የተደረገው የተሳታፊዎች ሰልፍ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ አስተምህሮ እና ሥርዐት እንዲጠበቅ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ውሳኔ እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡

የሰንበት ት/ቤቶቹ፣ በአማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎች እና በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ኾነው አስተምህሮዋን እና ሥርዐቷን በሚፃረሩ የተሐድሶ መናፍቃን ላይ ያሰባሰቧቸውን ማስረጃዎች አሠራሩን እና መዋቅሩን ተከትለው ሲያቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተገቢ ርምጃ እንደሚወስድ ሰብሳቢው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ገልጸዋል፡፡

ላለፈው አንድ ወር በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ከ160 በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች በማስተባበር÷ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ እና የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩት የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች ትላንት በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጋር ለሰዓታት ተወያይተዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና መጠበቅ እና ቀጣይ ዕድገት በየጊዜው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በየአጥቢያቸው በመተግበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት የሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራሮች፣ በአተገባበሩ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አማሳኝ አለቆች በየአጥቢያው እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ እንደ አመራሮቹ ማብራሪያ፣ አማሳኝ አለቆቹ፥ የአራት ሺሕ ብር ደመወዝተኛ ኾነው የ1ነጥብ8 ሚልዮን ብር መኪና የሚነዱ፣ ቪላ ቤቶችን እና ሕንፃዎችን የሚገነቡ፣ ኤሮትራከር ለማስመጣት የሚፎካከሩ ናቸው፡፡

አማሳኞቹ ሓላፊዎች፣ በአድባራትና በገዳማት አለቆችን እስከ ማሾም እና እስከ ማሻር ድረስ እጃቸውን ያስረዘሙበት የሙስና ሰንሰለት እንዳላቸው አመራሮቹ ጠቅሰው፣ ‹‹ይህም የሚጀምረው በዙሪያዎ ካሉ ሰዎች ነው፤›› በማለት ችግሩ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ዙሪያም ተያያዥነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሰረቁ ጣቶች ባለመቆረጣቸው ሌሎች እንዲሰርቁ በር ከፍቶላቸዋል›› ያሉት አመራሮቹ፣ አብያተ ክርስቲያን ከጠቅላላ ገቢያቸው ለሀገረ ስብከቱ የሚያደርጉት የኻያ በመቶ ፈሰስ ወጪ ከተደረገ በኋላ ወደ አካውንት ሳይገባ አየር ባየር እየተበላ አጥቢያዎቹ ባለዕዳ እየኾኑ እንዳለ፤ የፋይናንስ እንቅሰቃሴውን እና የንብረት አጠባበቁን ለዘረፋ ለማመቻቸት አሠራሩን የሚጥስ አካሔድ እንደሚፈጸም አስቀምጠዋል፡፡

‹‹በሰበካ ጉባኤያት የሰንበት ት/ቤቶች፣ የምእመናን እና የካህናት ተወካዮች ተሟልተው የሚገኙት በስንቶቹ ነው?›› ሲሉ የጠየቁት አመራሮቹ፣ ብልሹ አሠራሮችን በመቃወማቸው እና ጥያቄ በማንሣታቸው ለእስር እንደሚዳረጉ ተናግረው፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥያቄ የታሰሩባቸውን እንደ ቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ያሉ አጥቢያዎችን በስም ዘርዝረዋል፡፡ በአንዳንድ አጥቢያዎች ምእመናን አለቆችን እስከ ማባረር የደረሱት ፍትሕ ስላጡ እንደኾነ ጠቅሰው፣ ‹‹ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያካበቱ አለቆች በሀገሪቱ ሕግ መዳኘት አለባቸው፤ ያለተጠያቂነት እየተዘዋወሩ በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ ለምን ይበረታታሉ? በሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል ይጠየቁልን፤ እኛ ውሳኔ ሰጪዎች አይደለንም፤ በማስረጃ እንርዳችኹ እናንተ ወስኑ›› ሲሉ ቋሚ ሲኖዶሱን ተማፅነዋል፡፡

his-grace-abune-markos-zedebre-markos

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፤ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ከወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አንዱ፣ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ÷ ‹‹አንዳንድ አለቆች ከቤተ ክህነቱ በላይ ኾነዋል፤ ትክክል ነው፤ እውነትም ነው፤ ማን እንደሚያሾም ማን እንደሚያሽር ይታወቃል፤›› በማለት በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እና በፍትሕ ዕጦት ረገድ በአንድነት አመራሮቹ የተሰጠው ማብራሪያ የተዘረዘሩት ችግሮች ሥር መስደዳቸውን እንዳስገነዘባቸው ገልጸዋል፤ አክለውም ‹‹ማስረጃው ይቅረብልን፤ ሒደቱ በእኛ ደረጃ ብቻ የሚያልቅ አይመስለኝም፤ ወደሚቀጥለው አካልም የሚደርስ ነው፤›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በትላንቱ የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ የተገኙት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሰንበት ት/ቤቶቹ በሙስና ረገድ ያነሧቸውን ጥያቄዎች እንደሚደግፉና አብረዋቸው እንደሚሠሩ፤ ስለ ተሐድሶ መናፍቃን ጉዳይም በአቋም እንደሚግባቡ ገልጸዋል፡፡ ይኹንና ባለፉት አንድ ወራት የሰንበት ት/ቤቶቹ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በራሳቸው ከመጓዝ ይልቅ የሀገረ ስብከቱን መዋቅር ሊከተሉ እንደሚገባ፤ የአንድ ሰንበት ት/ቤት ችግር የሀገር መስሎ መቅረቡ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

‹ዩኒፎርም አገልግሎት መስጫ እንጂ አድማ መቅስቀሻ አይደለም›› ሲሉ የተቹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹የአጥቢያ አለቆች የሰንበት ት/ቤቶቹን እንቅስቃሴ አያውቁትም›› ብለዋል፡፡ በካሽ ካውንተር አሠራር በመቶ ሺሕዎች የገቢ ልዩነት እየታዩ ያሉትን ለውጦች መነሻ በማድረግ ችግር ያለባቸውን ሠራተኞች እንዳዘዋወሩ በመጥቀስ፣ ‹‹እኛ ችግር አለባቸው የምንላቸው አለቆች ቲፎዞ አላቸው፤ ለመንካትም ተቸግረናል›› ሲሉ እየተዘመተባቸው እንዳለና ለመሥራት መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

aa ssa rep reading the petiton00

በርክበ ካህናት የቅ/ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት የዕቅበተ እምነት፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ ጥያቄው በቀረበበት ወቅት (ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም.)

የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ‹‹ቅዱስ አባታችንን ላናግር ብላችኹ መች ከለከልኳችኹ?›› ሲሉ አመራሮቹን ጠይቀው፣ ‹‹ተጠሪነታችኹ ለሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤት ዋና ክፍል ነው፤ በዚያ በኩል ኑ›› ሲሉ በአንድነቱ አመራሮች ለተሰነዘረባቸው ተቃውሞ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

መዋቅርን ጠብቆ ጥያቄን ስለማቅረብ በተደጋጋሚ ስለተነሡት ትችቶች የሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራሮች ሲናገሩ፣ ‹‹ደረጃ ጠብቃችኹ ቅረቡ ተብለናል፤ የሙስና ሰንሰለቱ እኮ ከአጥቢያ እስከዚኽ ድረስ ነው፤ ሰንሰለቱን ስንቆርጠውም የሚጠገነው ከዚኹ ነው፤›› በማለት ከወራት በፊት በዐደባባይ ሓላፊነት ወስደው ያቀረቡትን አቤቱታ እንዳላቀረቡ ተደርጎ በተለይ በልዩ ጸሐፊው መጠቀሱ አግባብ እንዳልኾነና ከዚኽም አንጻር የቤቱ አሠራር መፈተሽ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በበኩላቸው፣ ‹‹እዚኽ እንደገባኹ ሙስናን በሕጉ እና በአግባቡ እንድንዋጋው አግዙኝ ብዬ መመሪያ የሰጠኹት እኔው ነኝ፤›› ማለታቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ኹሉም ነገር በአንዴ አይስተካከልም፤ በሙስናም በተሐድሶ ኑፋቄም ያሉትን ማስረጃዎች መዋቅሩን አሠራሩን በጠበቀ መንገድ አምጡ፤ እኛም ርምጃ እንወስዳለን፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ታዲያ ምን ሊሠራ ነው የተቀመጠው? ይህን ሊሠራ አይደለም ወይ?›› ሲሉ የሰንበት ት/ቤቶቹ ጥያቄ ውሳኔ እንደሚሰጠውና ምላሽ እንደሚያገኝ አረጋግጠውላቸዋል፡፡

Advertisements

3 thoughts on “ቋሚ ሲኖዶስ ለሰንበት ት/ቤቶች የመልካም አስተዳደር እና የዕቅበተ እምነት ጥያቄዎች ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታወቀ

  1. ገብረ ማርያም June 18, 2015 at 6:09 am Reply

    ጥብቆ ለባሽ ሁላ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ብትጠየቁ አትመልሱም ለአድማ ሲሆን ግን ጥብቆ ለብሰህ ትሰለፋለህ የእግዚአብሔር ቃል አድመኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ይላል እግዚአብሔር የሚያድሙ ልጆች ያሉትም።።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: