ሰንበት ት/ቤቶች ከሥራ አስኪያጁ ጋራ ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት ተቋጨ፤ በአማሳኞች እና በተሐድሶ መናፍቃን ላይ በየአጥቢያው የሚወስደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል

 • የታሸገው የሰሚት መድኃኔዓለም ሰንበት ት/ቤት ሳያውል ሳያድር መከፈት፤ የታሰሩት አባላት እና ምእመናን መፈታት በተሰላፊዎቹ ሰንበት ት/ቤቶች እና በዋና ሥራ አስኪያጁ መካከል ወሳኝ ልዩነት የፈጠረ ጉዳይ ኾኗል
 • ‹‹ለማሳሸግ ኹለቴ አላሰብክም፤ ለማስከፈት ለምን ጊዜ ይወስድብኻል? በአንድ ደብዳቤ እንዳዘጋኸው በአንድ ደብዳቤ ዛሬውኑ አስከፍት!›› ለሚለው ግልጽ እና ቀላል ጥያቄ፣ ‹‹እናንተ ስላላችኹኝ አይደለም፤ አታስገድዱኝም፤ ተወካዮቻችኹን ስጡኝና እናጥናው›› በሚለው እልክ የተጋባበት ምላሻቸው የተቆጣው መላው ጉባኤተኛ÷ በዓምባገንነታቸው ገሥጾ፣ የንቅናቄውን ቀጣይነት አስረግጦ እና ውይይቱን በጸሎት አሳርጎ ከአዳራሹ ጥሏቸው ወጥቷል
 • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ውስጥ ለውስጥ በቤተ ክርስቲያን እና በአገልግሎቷ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንዳለ በማመን በትጋት እና በጽናት እንዲሠራበት በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ይፋዊ መግለጫ በተሰጠበት ኹኔታ፣ በንግግር ተንኰል(demagogue) ራሳቸውን በመክበብ አቋማቸውን በተጨባጭ ርምጃ ለማረጋገጥ ሲቸገሩ ተስተውለዋል
 • የሰንበት ት/ቤት ተሰላፊዎች፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እና በሀገረ ስብከቱ አማሳኞች መካከል ስላለው ሥር የሰደደ የጥቅም ግንኙነት ያቀረቧቸውን ማብራሪያዎች ለማስተባበል የሞከሩት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ከጉባኤተኞች በገጥማቸው የከረረ ተቃውሞ አንደበታቸውን ሰብስበዋል
 • በሥራ አስኪያጁ መመሪያ እና በደብሩ አስተዳዳሪ ትእዛዝ ከታሰሩ ሦስተኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩት የሰሚት መድኃኔዓለም ሰንበት ት/ቤት አባላት እና ምእመናን በዛሬው ፪ኛ የፍርድ ቤት ውሏቸው የዋስትና መብት ተነፍገው እስከ ዓርብ ሰኔ ፭ በእስር እንዲቆዩ በችሎቱ ታዝዟል
 • ‹‹የታሰሩትን ልጆች ለመልቀቅ ከፖሊስ የተስፋ ቃል ተሰጥቶናል፤ ችግሩ ያለው ከደብሩ አስተዳዳሪ እና እናንተ ጋራ ነው፤ ወገባቸው ጠንቶ መቆም የማይችል፣ መድኃኒት የሚወስዱ ሕሙማን እና የሚያጠቡ እናቶች አብረው ታስረዋል፤ ስለ መድኃኔዓለም ስለ ወላዲተ አምላክ ፍትሕ ስጡን!!››

/የሰሚት መድኃኔዓለም ሰንበት ት/ቤት አባል ሥራ አስኪያጁን የተማፀነበት ቃል/

aa sun sch demo01ረዓድ እና ድንጋፄ በሚፈጥር ኃያል ንቅናቄ ማልደው ወደ ሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ተንቀሳቅሰው ባስከበሩት የመደመጥ መብት በተዘረጋው መድረክ፣ ወላዋይ እና አማሳኝ ሓላፊዎችን በትንታግ አንደበት ሲያስጨንቁ የዋሉት የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች – የአ/አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች!!!

*       *       *aa sun sch demo0

ሰንበት ት/ቤት የቤተ ክርስቲያን ልጆች እና ቅን አገልጋዮች፣ ተረካቢ አባላት እና ተከላካይ ትኩስ ኃይል መገኛ እንዲኾን በአበው በጥልቅ ታስቦ የተመሠረተ ተቋም መኾኑ ይታወቃል፡፡ ስለኾነም መንፈሳውያን ወጣቶች በትምህርተ ሃይማኖት ታንፀው፣ በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው ያድጉ ዘንድ ተገቢውን ቦታ እና ትኩረት በመስጠት የዕለት ከዕለት ክትትል እናደርጋለን፡፡ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንም አስፈላጊውን ኹሉ እናሟላለን፡፡ ለሰንበት ት/ቤቶች መምህራን፣ አሳራጊዎች እና ጠባቂዎች ካህናት እንዲኖራቸው የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ (የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ፳፻፭ ዓ.ም. የአቋም መግለጫ)
ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በሚሰጡት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መኾኗ እስኪረጋገጥ፣ ሕፃናት እና ወጣቶችን ወደ ቤተ እግዚአብሔር የመጋበዝ፣ ተቀብሎ በሥነ ምግባር ማነፅ እና አገልግሎታቸውን ሊጠቅም በሚችል መልኩ ሥራ ላይ ማዋል ይቻል ዘንድ በሚሰጠን መመሪያ መሠረት በንቃት ለማገልገል ቃል እንገባለን፡፡ ከዚኽም ጋራ ሕገ ወጥ ሰባክያንን በመከላከል፣ ስብከተ ወንጌልን የሚያስፋፉ ሰንበት ት/ቤቶችን በይበልጥ የማደራጀት ሥራ ተግተን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ (የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ፳፻፮ ዓ.ም. የአቋም መግለጫ)

 

Advertisements

6 thoughts on “ሰንበት ት/ቤቶች ከሥራ አስኪያጁ ጋራ ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት ተቋጨ፤ በአማሳኞች እና በተሐድሶ መናፍቃን ላይ በየአጥቢያው የሚወስደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል

 1. ዳሞት June 10, 2015 at 5:09 am Reply

  ንቁ በሀይማኖት ቁሙ
  ሰንበት ተማሪዎች ሆይ እንዲሁም ምዕመናንና ለእምነታችሁ ቀናይ የሆናችሁ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አገልጋዮች ሆይ ንቁና የትኛውም ስጋዊ መደለያ ሳያሸንፋችሁ በሀይማኖት ቁሙ። በተለይ ሰንበት ተማሪዎች ሆይ በቅርቡ ያደረጋችሁትን አመታዊ ስብሰባ አስመልክቶ በአንድ የመናፍቃን ብሎግ በመናጆ የወጡት በሚል መጽሐፍ ቅዱስ እንደማታውቁ ተደርጎ እጅግ ተንቋሻችሁ ተስድባችኋል። መሰደባችሁ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችሁ ስለ ክርስቶስ ነውና እነዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ተሸክመው በልዩ የውሸት ወንጌል የክርስቶስን መንግስት ለሚቃወሙና ሐሰተኛ አስተማሪዎች ዘለፋ ቦታ ሳትሰጡ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ከቅጥሯ እስኪወገዱ በእምነት ፀንታችሁ አንድ ጊዜ ለክርስቲያኖች ስለተሰጠች አንዲቷ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖታችሁ ልትጋዱ ይገባችኋል። በማናቸውም ስለ ሀይማኖታችሁ በምታደርጉት ተጋድሎ የሚደርስባችሁን መከራ እንደ ደስታ ቁጠሩት። ለናንተ ክብር ይሆናልና ነው።
  እግዚአብሔር ልባችሁን ያበርታ።

 2. ቀፀላወርቅ ዓድማሱ June 10, 2015 at 7:28 am Reply

  ውድ ሐራውያን ይህን እንበል!

  1. በሰ/ት/ቤቶች በመሰረታዊነት ተነሱት ምዝበራን የመግታት፣ርትእት ሃይማኖትን ሳትበረዝ ሳትከለስ የማስቀጠል፣የፋይናንስ ሥርዓትን ግልጽነት የማስፈን፣ለወጣቶች ትኩረት የመሻት የመሳሰሉ አጀንዳዎች ቅድስና ያላቸው ተገቢ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከጥያቄዎቹ ጋር ቤ/ክንን ራስ ለማስቻል የሚረዱ የልማት አጀንዳዎችና ለማኅበረ-ምዕመኑ የሚተርፉ ፕሮጀክቶችም ሊቀረጹ ይገባል የሚሉ አጀንዳዎችም ቢካተቱ እንዲሁም አማራጭ የመፍትሄ አቅጣዎችን የሚጠቁሙ ነጥቦች ቢካተቱበት ደግሞ የበለጠ ሳቢ ይሆን ነበር፡፡ሆኖም እነዚህ ነጥቦች ስላልተካተቱ ብሎ መሰረታዊውን የሰ/ት/ቤቶች ጥያቄ ማጣጣል ተገቢ አይሆንምና ጥያቄዎቻቸውን በቅን ልብ መቀበል ግድ ይሆናል፡፡ተገቢም ነው!

  2. ሰ/ተማሪዎቹ ጥያቄዎቻችንን ይሰማናል በሚል እምነት ለሀ/ስብከቱ ማቅረባቸው በራሱ በመካከላቸው ብዙ ቅን አሳቢ ወጣቶች እንዳሉ አመላካች ነው፡፡ይሕ አካሄዳቸው እውቅና ሊቸረው ይገባል፡፡ክብር ያገባናል ለሚል እንቅስቃሴያችሁ!

  3. በሌላ በኩል የተጀመረውን በመንበሩ ከተሰየሙ ኃላፊዎች ጋር በአንድ ቤት ሆኖ የመመካከር በጎ ጅምር እንደማበረታታት ኃላፊው እንዲህ ናቸው፣እንዲህ ተናገሩ፣ ጥለናቸው ወጣን የምትለዋን ጀብደኝነት የገነነባት ድርጊትና ዘገባ ብናቆያት አይከፋም፡፡ ለሁላችንም ስለማትጠቅም!ዛሬ ተነጋግረን ሙሉ ስምምነት ላይ አልደረስንም ማለት ለዘለዓለሙ አንደርስም ማለት አይደለምና ንግግሩን ሚዛን አሳጥቶ ማራገብ ዳግም ንግግር እንዳይኖር በር ይዘጋልና አስቡበት!

  4. ሳያነግሩን ብሎም ጩኸት፤ለንግግር በሩ ሲከፈትም እኛው ያልነው ብቻ ብሎ ጩኸት ቅዱሱን አጀንዳ የሌላ ያስመስልብናልና በቅጡ ብንሆን መልካም ነው፡፡በምክክሩ ሊነሱ የሚገባቸው ሁሉንም ሰ/ት/ቤቶች ታሳቢ ያደረጉና ለቤ/ክ አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎችን ባነገበ መልኩ እንጅ የእገሌና የእገሌ ሰ/ት/ቤት ችግር እየተባለ ነጠላ ድርጊቶችን ሁሉ በማዥጎድጎድ ከሆነማ ሥ/አስኪያጁ የመላው ሀ/ስብከቱን ጉዳይ ትቶ ሰ/ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ ሊሆን ነው፡፡መርህ ይኑረን!!ከዚያ በኋላ ነጠላ ድርጊቶችም በመርሆዎቹ ሊመለሱ ይችላሉ፡፡

  5. የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጥያቄዎቻችንን በምልዐት ስላልመለሰ የራሳችንን እርምጃ በየአጥቢያችን እንወስዳለን የሚለው አካሄድ ስሜታዊነት የተጫነው ይመስለኛል፡፡ በስርቆት የምንጠረጥረው አካል ካለ ማስረጃ መሰብሰብ፣ ስርቆቱን ለመግታት ክትትልና ጥንቃቄ ማድረግ፣ በሰበካ ጉባኤ ውስጥ ባለው ሰ/ት/ቤት ወኪል አማካኝነት አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት ማስወሰድ፣ ካልተቻለም ደረጃውን ጠብቆ ከወረዳ(ክፍለ ከተማ) ቤተ ክሕነት እስከ ቅ/ሲኖዶስ(ቋሚ ሲኖዶስ) ባለው የቤ/ክ መዋቅር ተጠቅሞ መፍትሔ ማፈላለግ ሊቀድም የሚገባው እርምጃ ነው፡፡ ደረቅ ወንጀል ስለመፈጸሙ በቂ የሰውና ሰነድ ማስረጃ ካለን ደግሞ ለአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት በማድረግ ተጠያቂዎቹን ለሕግ ከማቅረብ የሚከለክለን ሕግ የለም፡፡

  ተሐድሶዎችን በሚመለከትም የመፈረጅ ሥልጣኑ በሕገ-ቤተክርስቲያን ተለይቶ የተሰጠው ለቅ/ሲኖዶስ መሆኑን ተገንዝበን ነገር ግን በየአጥቢያችን የሚመጡ ሰባክያን የሚጠበቅባቸውን እውቀትና ሃይማኖት ከአጥቢያችን ስ/ወንጌል ጋር በመሆን ከመደንገግ የሚያግደን ሕግ ያለ አይመስለኝም፡፡ ስብከተ ወንጌሉ የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔን ተጋፍቶ ውጉዝ ሰባኪ በመድረኩ አቁሞ ከሆነ ከአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ጀምሮ ካሉ የቤ/ክ አስተዳር አካላት ጋር በመሆን ጋባዡም ሆነ ውጉዙ ሰባኪ አስፈላጊው መንፈሳዊ ቅጣት እንዲጣልባቸው ማድረግ የተገባ ነው፡፡

  ከዚህ ውጭ በጉልበትና በቁጥር ብዛት ተመክቶና ሥርዓቱን በእጅ አድርጎ ወደ ጉልበት ርምጃ መሄድ በራስ ላይ ሌላ ጉልበተኛ መጋበዝ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ሊጠራ የሚገባው ኃይል የግድ ቢጠራ ሊገርመን አይገባም፡፡ የራሳችንን እርምጃ በመንጋ ሆነን እየወሰድን ሌላ ኃያል ሲመጣ ‹‹ኃይል የእ/ሄር ነው፤ ማዳን የእ/ሄር›› ብንል ዝማሬያችን መንበረ-ጸባኦት መድረሱን እንጃ!

  6. የመኪኖቻቸውን መስታወት የምንሰብረባቸውና ጎማዎቻቸውን የምናተነፍስባቸው፣ከመስመር በወጣ ዘለፋ ሰብአዊ ክብራቸውን የምንነካው፣ማሰረጃ በሌለው ክስ በተቆርቋሪነት ስም ስማቸውን የምናጠፋው፣አካላዊና ሞራላዊ ስብራት በየመድረኩ የምናደርስባቸው የቤ/ክ አገልጋይ ሰራተኞችም እኮ ካሕን ዘለዓለሙን በችጋርና በጉስቁልና ይኑር ካላልን በስተቀር ቢያንስ እንደ ዜጋ መብት አላቸው፡፡ እነዚህ መብቶችን በድምጽ ብልጫ እየወሰንን መግፈፍ አንችልም፡፡ እሱን ማደረግ ስራው የሆነ ኃይል አለ፡፡ ባይሆን ለእሱ ኃይል ጥቆማና ማስረጃ መስጠት የሰመረው መንገድ ነው፡፡ እነዚህን የኃይል ድርጊቶች በራስ ተነሳሽነት በሆታ እየወሰዱ የሕግ ተጠያቂነት ሲመጣ ራስን ሰማዕት ብሎ ለመሰየም መድፈር ግን ክብረ-ሰማዕታትን ማሳነስ ነው፡፡ ውንድብናና የሰማዕታት ተጋድሎ ሊምታታ አይገባውም!በሕግ አምላክ!

  7. አጀንዳው በዘላቂነት ዳር እንዲደርስ ከተፈለገ እንደ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ራስን ወደ ቋሚ ተገዳዳሪነት ቀይሮ በየጊዜ በመሰለፍ ላልሆነ ዒላማ ከመመቻቸት ይልቅ አጀንዳውን በደንብ አጥሩት፣ ከሀ/ስብከቱ ጋር ቋሚ ምክክር የሚያደርግ ተወካይ አስቀምጡ(ለጊዜው ራሱ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አመራርም ተደራዳሪ መሆን ይችላል!)፣ እኛ ያልነው ብቻ ከሚል አባዜ ውጡ፣ በወቅታዊ ኩነቶችና በሚዲያ ተጽእኖ ስር እየወደቃችሁ ትልቁን ምስል(የኢኦተቤክ ከነክብሯና ማዕረጓ ቀኖናዋና ዶግማዋ ሳይነካ በተሸለ አስተዳደር የካሕናትና የምዕመናን ኅብረትነቷ ጸንቶ እንዲቀጥል) አታድበስብሱት፣ ነገሮችን ግለሰባዊ አድርጋችሁ ወደግለሰቦች የግል ጉዳይና በቤተክሕነቱ ሰፍኖ ወደሚያውከን የጎጥ ቆጠራ አትውረዱ፣ ካላስፈላጊ ዘለፋና የኃይል ተግባራት ተቆጠቡ፣ ብዙ ክሶችን በውብ ቃላት ከደረደራችሁ በኋላ ክሶቹ ኃላፊነት የሚወስድና በማስረጃ የሚያነጥር አካል እያጡ በሐሜትነት ስለሚቀሩ ‹‹ልማዳቸው ነው›› የሚል ታርጋ እንዳይለጠፍባችሁ ማስረጃ ሳታስቀድሙ ክስና አሉባልታ አትንዙ፣ ውስጣዊ ስነ-ምግባርና አመራራችሁን በደንብ ፈትሹ፣ካሕናት ላይ ሚደርሰው አስተዳደራዊ በደል ወደ እናንተ አዳራሽ ካልመጣ በቀር አያገባንም በሚል መንፈስ የግፉ ተባባሪ አትሁኑ፣ እንዲሁም በእያንዳንዱ የቤ/ክ አስተዳደራዊ ድክመት እና የኦርቶዶክሳዊ መንጋ ቁጥር መቀነስ ድርሻ እንዳላችሁ አትዘንጉ፣ ከምንም በላይ አጀንዳችሁን የሰ/ት/ቤት ያልሆነ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ አካል ለራሱ ቡድናዊ፣ ግለሰባዊ፣ ብሔረሰባዊ፣ ሃይማኖታዊ(የክሕደት)፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እንዳይጠልፍባችሁ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡

  ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን፤ኅብረተ መንፈስ ቅዱስ ሠናየ ከመ ይፀግወነ!!

 3. Anonymous June 10, 2015 at 10:29 am Reply

  ይህችን ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከውስጥና ከውጭ የሚፋለሟትን የአውሬው ርዝራዦችን ሀይል የእግዚአብሔር ነው ብሎ በዓላማ፣ በብልሀት እና በአንድ ህብረት መዋጋር የዘመኑ የሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ አማኝ ሁሉ ሰማዕትነት ነውና በአንድ ቃል በህብረት መቆም ይጠበቅብናል፡፡
  ዋናው ነገር ግን እነዚህ አሁን በዚህች ቤ/ክ ውስጥ ከፕትርክናው እስከ ታችኛው አስተዳደር የተሰገሰጉት አካላት (‹‹ፓትሪያርኩ፣ ልዩ ዋና ጸሀፊ ኤልያስ አብርሀ፣ የአ/አ ስራ አስኪያጁ፣ …››) እንዴት? በማን? ለምን? … ወደ እዚህ መንበር ተጋዙ የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ ዕምነትና ሥርዓት በአግባቡ በአስተውሎት መረዳት መቻል፤ ለኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ዓላማና ተልዕኮ እንቅፋትና ተግዳሮት የሆኑትን በሙሉ ለማወቅ ያስችለናልና በሂደቶች ሁሉ ፍጹም ብልናት፣ አስተውሎት እና ቁርጠኝነት … ያስፈልገዋል፡፡
  እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡

 4. Anonymous June 11, 2015 at 7:40 am Reply

  ምዕመናን ከሀሰተኛ ሰባኪና ዘማሪ ተጠንቀቁ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ አባቶች እንደተነገረው የበግ ለምድ የለበሱ ሀሰተኛ መምህራንና ዘማሪያን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተሰግስገው የመናፍቅ /የጴንጤ/ ትምህርትና መዝሙር እያስፋፉ እንደሆነ ሲገለፅ ቆይቷል ምዕመናንም ጥንቃቄ ማድረግ ጀምረዋል፣የቀድሞ የዱባይ ዘፋኝ የነበረችው ዘርፌ ጥልቅ የሆነ የመፀሃፍ ቅዱስ እውቀት ሳይኖራት ገንዘብ አምላኪ በሆኑ የሀሰት መምህራን የሚሰጣትን ግጥም በጥንቃቄ ሳትመረምር እየዘመረች ምንፍቅናን እያስፋፋች ትገኛለች ከዚህ በፊት ለቅድስት ድንግል ማሪያም አልዘምርም አንድ መዝሙር ይበዛባታል ብላ ኢንተርቪ ስትደረግ መናገሯ ይታወሳል በዚሁ መሰረት በምታወጣቸው የመዝሙር አልበሞች የእመቤታችንን ምስጋና እንዲሁም የመላዕክትንና የቅዱሳን ሰማእታትን መዝሙር ማካተት አቁማለች ወገኔ ይህ ጤኔኛ አካሄድ ነው እንደ ጴንጤዎቹ እየሱስ ይበቃኛል እያሉ ይገኛሉይህ ከሆነ ደግሞ ወደ ወዳጆቿቸው ጵንጤዎች መሄድ ይኖርባቸዋል በጴንጤዎች መፅሄትም ዘርፌ የጌታናት እያሉ እያሞጋገሱ እያወጧት ይገኛሉ በአዳራሾቻቸው ሄዳችሁ መፅሄቱን ማየት ትችላላችሁ በተለይ በ ebs ቴሌቪዥን የሚተላለፉት ታኦሎገስ እና ቃለአዋዲ የተባሉ ስብከቶች ቤተክርስቲያን ዕውቅና ያልሰጣችውና ዝሙትና መዳራት በተስፋፋባቸው ሆቴሎች መሰሎቻቸውን እየሰበሰቡ ቀርፀው የሚያስተላልፉት ፕሮገራም ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙትም አውሮፓ ከሚገኘው የጵሮቴስታንት/ጵንጤ/ ድርጅት እንደሆነ ታውቋል በተለይ ህሊናውን በመሸጥ ለሆዱ ያደረው አሰግድ ሳህሉ ከመናፍቃን በሚወረወርለት ሳንቲም በመደለል የቅድስት ድንግል ማሪያምና የቅዱሳን ሀዋሪያት፣ሰማዕታት፣ስም እንዳይነሳ የመርዝ ትምህርቱን ቢረጭም ቤቴክርቲያን ከባለፉት ጊዜአቶች በበለጠ የፀጋ ምብጋና እያቀረችቸው ትገኛለች እዚህ መሀይም አጉራ ዘለል ዘማሪንና ሰባኪያን የመፀሃፍ ጥቅስ ከመሸምደድ ያለፈ ዕውቀት የሌላቸው በገንዘብ መውደድ ልቦናቸው የታወረ የተህድሶ ጴንጤ አራማጆች በአብዛኞቹ ቤተክርስቲያናት ድርሽ እንዳይሉ ምዕመኑና የስብከተወንጌል ሃላፊዎች ባደረጉት ርብርብ በአዲስ አበባ አድባራት መንቀሳቀስ አልቻሉም ሆኖም ቅዱስ ዮስፍ እና ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ለስብከተ ወንጌል ሃላፊዎች ጉቦ በመስጠት አልፎአልፎ መድረክ እያገኙ እንደሆነ ታውቋል ነግርግን ሰንበት ትምህርት ቤቱ እንዲታገዱ እስከቤተክነት ድረስ ጥረት እያደረገ ስለሆነ ልንደግፈው ይገባል ጥረታችንም እንደዚህ በፊቱ በጌታችን በኢየሱሰ ድጋፍና በቅድስት ድንግል ማሪም አማላጅነት እንደሚሳካ እርግጠኞች ነን በአጠቃላይ ስሜታዊ ከመሆን ወጥተን የሚሰራጩ የስብክትና የመዝሙር ሲዲዎችን በጥንቃቄ መርምረን መግዛት ይገባናል በዋናነት በጋሻው፣ትዝታው፣ዘርፌ፣ያሬድአደመ፣አሰግድ ሳህሉ፣ጋሽዬመላኩ/ማሜ፣ሀዋዝ፣ሰሞኑን ግብረሰዶማዊ መሆኑ የተጋለጠው ዲያቆን አሸናፊ መኮንን/የዚህ ቡድን ተዋናይ ምንህል የረከሱ መሆናቸውን ልብ በሉ ድሮም ከፍሬአቸው ታወቃሉ አይደል የሚለው መፀሃፉ/ በFacebook ከመናፍቃን ጋር በብዛት የሀሰት ትምህርት ሼር በመደራረግ እያሰነካከሉ የሚገኙት ጋሽዬመላኩ/ማሜ እና በውሸት ቄስ ነኝ የሚለው አሸናፊ ገበረማሪም፣ ያሬድ አደም ለአርቲስት አቦነሽ አድነው በቂ ስንቅ የሌለው ቼክ በመጻፍ በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ተከሶ ቂሊንጦ ለመውረድ ተገድዷል የመናፍቅ አራማጅ መሆናቸው በአደባባይ በሚፈፅሙት ተግባር እየተለዩ ይገኛሉ በተለይ ያሬድ አደመ በደረቅቼክ ማጭበርበር ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ገብቷል ታዲያ በቅዱስ መፀሀፍ እንደተፃፈው ሀሰተኛ መምህራን ከእውነተኛ መምህራን በፍሬአቸው ይለያሉ የተባለው አልተፈፀመም አንድ ዘራፊ ሌባ የሆነ መምህር በምን ሞራል ቤተክርስቲያን አውደምህረት ላይ ቆሞ መስበክ ይችላል ህሊናው ካልታወረና የድፍረት ሀጢያትን ካልተለማመደ በቀር፡፡ እነ ጋሻዬ/ማሜ/ በዱባይ ሀገር በሀሰት የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ብለው በከፈቱት አዳራሽ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ያልሰጠው በራሳቸው ፍላጎትና ማን አለበኝነት ከቤተክርስቲያን ሥርአትና ሕግ ውጪ በመክፈት በዚያ ሀገር የሚገኙ ሁልትና ሶስት ገንዘብ ያለቸውን ሴቶች ቤትለቤት እየሄዱ አጥንቶ በመምረጥ እየወሸሙ አዲስአበባ ያሉ ችግረኛ ቤተሰቦቻቸውን በነዚህ ምስኪን ሴቶች ገንዘብ እያኖሩ ይገኛሉ፣ ሌላው ካልባረከኝ አለቅህም የሚለው መዝሙር ከ10 አመት በፊት በፕሮቴስታንት ዘማሪ የተዘመረ ሲሆን በጋሻው የተባለው የተሀድሶ መሪ ለኦርቶዶክስ ዘማሪዎች የኔ ግጥም ነው በማላት በሀሰት የሌላ ሰው ግጥም ወስዶ እያዘመራቸው ይገኛል የሚያስተምረው ትምህርትም ሆነ መንገዱ/ስታይሉ/ ከጴንጤ ሰባኪዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ስለሆነም አባቶቻችን ሳትበረዝና ሳትከለስ ያቆያትን ቤተክርስቲያን የዛሬ ወጣቶች በንቃት መጠበቅ ይኖርብናል ከቤተክርስትያናችን ስርአት ውጪ የሆኑ ሰባክያንና ዘማሪያንን ከእውነተኛዎቹ በመለየት የራሳችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል፣ እባካችሁ ይህን መልዕከት ኮፒ አድርጎ ለሌሎች በማስተላለፍ ግንዛቤ እንፍጠር፡፡”የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ነጣቅው ተኩላዎች ተጠበቁ ” ያለውን የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ብቻ መጠበቅ ነው አሁን የኛ ሥራችን።

  • Anonymous June 11, 2015 at 11:15 am Reply

   @Anonymous June 11, 2015 at 7:40 am Reply

   እናንተ ልጆች ሰው ከመዘንጠል በቀር ስራ የላችሁም፡፡ሰባኪውንም፣ዘማሪውንም፣አለቃውንም፣ጳጳሳቱንም፣ቅዱስ ፓትርያርኩንም ክርስትና እንደሌላቸው ቆጥራችሁ፤ሁሉንም አውግዛችሁ ጨረሳችሁ፡፡እረ አስተውሉ!ውንጀላ ጀግንነት ሆነ እንዴ!ሁሉን ኮንናችሁ ጨርሳችሁ ጌታ በዳግመ-ምጽአት ሲመጣ ምን ይስራ!የተከበራችሁ የብሎግና የፌስቡክ አነስተኛና ጥቃቅን ሲኖዶሶች በፈጠራችሁ አደብ ግዙ፡፡ስድብ፣ዘለፋ፣ውንጀላ መቼውንም የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ተቆርቋሪነት ምልክት ሊሀን አይችልም፡፡አንድ ተኩላ ለማስወጣት 99 በጎችን ማስበረገግ አዋጭ አይደለምና አካሄዳችሁን ዳግም ገምግሙት፡፡

   ብታውቁ አንድ ሰው ሲወገዝ አንድ ባለማዕተብ ኦርቶዶክሳዊ ወንድማችንን አጣን ማለት ነው፡፡ብዙ ጊዜ ግን መክሮና ገስጾ ከመመለስ ይልቅ ጥቃቅን የቃላት ሐረጋትን እየፈላለጡ ሰዎችን በእልህ መንገድ ለውግዘት ማመቻቸት እንደ ግብ የተያዘ ይመስላል፡፡እነዚህ ስማቸውን በየብሎጉ፣ጋዜጣውና ፌስቡኩ እየቆረጥን የምንጥለው ልጆች ትናንት በየሰ/ት/ቤቶቻችን ከእኛው ጋር የነበሩ ናቸውና የእነሱ ከሥርዓት መዛነፍ ብናስተውል በእኛ ውስጥ ያለውን ድክመት ጠቋሚ ነው፡፡ልጆቹ መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው መንገድ ለመረዳት በሚያደርጉት ጥረት እንደ መናፍቃን በተዓብዮ ተጠልፈው ትርጓሜውን ስሜት-መር እንዳያደርጉት በፍቅር ቀርቦ መመለስ ሲቻል ከንግግሮቻቸው መሐል ቃላት ሰንጥቆ ከባዕድ ለማዋደድ መሞከር የራሳችንን ስንፍና እና ለመንጋው ኅብረት ያለንን ደንታ ቢስነት ነው የሚያሳየው፡፡እየተስተዋለ!!ማስወገዝ መርህ መሆን የለበትም–ልዩና ከአቅም በላይ በሆነ አጋጣሚ የሚሆን እንጅ!እሱም ደግሞ ሥልጣኑ ባለው የሊቃውንት ጉባኤና በቅዱስ ሲኖዶስ፡፡

   እየተስተዋለ!ያላሰራችሁትን ማዕተብ ለማስበጠስ በመሯሯጥ ቀናኢ ኦርቶዶክስ የመሰኘት ካባን ለመደረብ የምትሯሯጡ ወንድም/እኅቶች አካሄዳችሁን መርምሩ–ኋላ በተዘዋዋሪ የተሐድሶ መሳሪያ መሆናችሁ ሲገባችሁ እንዳትጸጸቱ፡፡ተሐድሶ እንደሆነ እንኳንስ እከሌ ያንተ ነው ተብሎ የእሱ ያልሆነውን ሃይማኖ አበው እና የቅ/ያሬድ ድርሰቶችንም ከመቆንጸል አይቦዝንም፡፡እየተስተዋለ!ያን ያህል የረቀቀ እውቀትና የጠለቀ መንፈሳዊነት የሌላቸው ዘማርያንን ከቅድስት ቤተክርስቲያንን በየሰበብ አስባቡ በገፋናቸው ቁጥር ድምጽና ትርጓሜያቸውም የዚያኑ ያህል ቢርቅ ተጠያቂዎቹ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛ ገፊዎቹም ጭምር ነን፡፡እየተስተዋለ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: