ሰንበት ት/ቤቶች መልካም አስተዳደር እና ፍትሕን የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርጉ ነው

  • ፓትርያርኩ የሀገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎችን ባለማነጋገራቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል
  • ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያከማቹ ሓላፊዎችን በሕግ ለመጠየቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው

(ሰንደቅ፤ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፰፤ ረቡዕ ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

eotc ssd pouring out to patriarch palace01

ቁጥራቸው ከ1500 የማያንስ የ፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የመጨረሻ ቀን ተሳታፊዎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለማሰማት የወሰኑት፣ ፓትርያርኩ በማጠቃለያው ዕለት ተገኝተው እንዲያነጋግሯቸው ለመጠየቅ ከአዳራሹ ወጥተው ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ በዚኽ መልኩ ተሰልፈው እየዘመሩ ከተጠባበቁ በኋላ አባታዊ ምላሽ በማጣታቸው እና በተደጋጋሚ በፓትርያርኩ የደረሰባቸውን መገፋት በተጨባጭ ካረጋገጡ በኋላ ነበር

ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ፣ ሃይማኖት እንዲጠበቅ በተደጋጋሚ ያቀረብነው አቤቱታ መፍትሔ አላገኘም ያሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትሕ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት እና የአስተዳደር መዋቅር እንዲሰፍን የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎችን እንደሚያደርጉ አስታወቁ፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ፣ ጥያቄአችንን ለሕዝብ እና ለመንግሥት እናሰማለን ብለዋል – የሰንበት ት/ቤቶቹ ወጣቶች፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ የወሰኑት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባደረጉት አጠቃላይ ጉባኤ ‹‹ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ ከጎኔ ተሰለፉ›› ያሏቸው ፓትርያርኩ፣ ተገኝተው ስለ ጉዳዩ ሊያነጋግሯቸው ባለመፍቀዳቸው እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ ከ37 አህጉረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍሎች ልኡካን የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ ዓመታዊ ስብሰባ ከግንቦት ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. መካሔዱን የጠቀሱት ወጣቶቹ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የዕቅበተ እምነት ችግሮች እና በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በሰንበት ት/ቤቶቹ አመራሮች እና አባላት ላይ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎች ለአገልግሎታቸው ዋነኛ ዕንቅፋቶች እንደኾኑ ከየአህጉረ ስብከቱ በቀረቡ ሪፖርቶች መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደር በደል ተወግዶ ብልሹ አሠራር የሚታረምበት ሥርዐት እንዲዘረጋ በሚጠይቁ የሰንበት ት/ቤቶች አመራሮች እና አባላት ላይ እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንዲደርስ ምክንያት የኾኑ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች እንዲኹም ከእነርሱ ጋር በመተባበር አባላትን የሚያስሩ እና የሚያንገላቱ የመንግሥት የፍትሕ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ይደረግ ዘንድ በጠቅላላ ጉባኤው የጋራ አቋም መግለጫ ተጠይቋል፡፡

እንደማሳያም በሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሰላም ሰንበት ት/ቤት ላይ በአስተዳደሩ ተፈጽሟል የተባለው በደል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ እንደ ሪፖርቱ፣ የደብሩ አስተዳደር የሰንበት ት/ቤቱን ጽ/ቤት እና አዳራሹን ከማሸጉም በላይ አመራሩን አግዶ በክሥ እና በእስር እንዲንገላቱ እያደረገ (በዛሬው ዕለትም በጎሮ ፖሊስ ጣቢያ ለሰዓታት ታስረው ተለቀዋል) በመኾኑ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡

‹‹ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ልታጠናክር፣ ተሰሚነቷን ልታስከበር ይገባታል›› ያሉት ጉባኤተኞቹ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እና ንብረት ለግል ጥቅማቸው በማዋል የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እየነሱ እና አቅሟን እያዳከሙ ናቸው ያሏቸው አማሳኞች ማስረጃ ተጠናቅሮ በአገሪቱ ሕግ እንዲጠይቁ አመልክተዋል፡፡ ከዚኹ ጋራ በተያያዘ የጠቅላላ ጉባኤው አቋም ኾኖ በተወሰደው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጥያቄ፣ ከገቢያቸው በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት በሕገ ወጥ መንገድ ያካበቱ ከ25 በላይ የአድባራት አለቆች እና ጸሐፊዎች ላይ በቂ ማስረጃ መሰብሰቡ ተጠቅሷል፤ በአገሪቱ ሕግ መሠረትም የሚጠየቁበትን ኹኔታ የሚከታተል የሕግ ባለሞያዎች ቡድን ተቋቁሞ ቅድመ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መኾኑ ታውቋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ እና ልማታዊ ጉዳዮች ከአባቶች ጋራ በመኾን ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ልዕልና የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን በአቋም መግለጫቸው ያመለከቱት ወጣቶቹ፣ ፓትርያርኩ በጉባኤያቸው ማጠቃለያ አባታዊ መመሪያና ቃለ ምዕዳን እንዲሰጧቸው መርሐ ግብር የተያዘላቸው ቢኾንም ተገኝተው ባለማነጋገራቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ከጎኔ እንድትሰለፉ›› በማለት በሰጡት አባታዊ መመሪያ የአስተዳደር በደል የሚያደርሱባቸውን አማሳኛ ሓላፊዎች ለማጋለጥ መነሣታቸውን ወጣቶቹ አስታውሰዋል፡፡

ይኹንና የብዙኃን አባት እንደመኾናቸው በየደረጃው አቅርበው መፍትሔ ያጡለትንና ለሰንበት ት/ቤቶች ኹለንተናዊ ዕድገት ዕንቅፋት የኾነውን የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ዕጦት አቤቱታቸውን በስብሰባቸው ተገኝተው እንዲሰሟቸው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት(የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ የማደራጃ መምሪያው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የምዕራብ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ) እና በሌሎችም ሓላፊዎች መልእክተኛነት ጭምር በወቅቱ ቢያሳውቋቸውም እና ቢያስለምኗቸውም ‹‹የያዝነው መርሐ ግብር የለም›› በሚል በራቸውን እንደዘጉባቸው ተናግረዋል፤ ‹‹እንደማይፈልጉን እና የሰጡንን ቦታ የሚያመለክት ነው›› ይላሉ ወጣቶቹ ቅሬታቸውን ሲገልጹ፡፡

ስለኾነም ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው ሲያቀርቧቸው የቆዩዋቸውንና ምላሽ ያጡላቸውን ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለሕዝብ እና ለመንግሥት ለማሰማት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፤ መላው የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤት አባላትም በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሚካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡

Advertisements

One thought on “ሰንበት ት/ቤቶች መልካም አስተዳደር እና ፍትሕን የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርጉ ነው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: