ትምህርት ቤቱን ወደ ጋራዥ የለወጠው የቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

  • የወቅቱ ሰበካ ጉባኤ የኹለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመገንባት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቅቋል
  • የቦታ፣ የሕንፃ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ማጣራት በመገባደድ ላይ ነው
  • የሊ/ን የማነ፣ የዋና ጸሐፊነትም የሥ/አስኪያጅነትም ሥልጣን የተጠያቂነት ዕንቅፋት ፈጥሯል

Debra Gelila St. Amanuel Cathedral00
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት÷ የመሬት እና የሕንፃ ኪራይ፣ የመካነ መቃብር አጠቃቀም እና የመኪና ሽልማት ጉዳዮችን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እና ከሀገረ ስብከቱ በተውጣጡ የሥራ ሓላፊዎች ኮሚቴ ሲካሔድ የቆየው የማጣራት ተግባር በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ በተመረጡ 69 ገዳማት እና አድባራት የታቀደው ማጣራት ከ85 በመቶ በላይ የተከናወነ ሲኾን ተፈላጊ መረጃዎችም በበቂ ኹኔታ መሰብሰባቸው እና መደራጀታቸው ተገልጧል፡፡ ኮሚቴው ጥናታዊ ሪፖርቱን ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ ካቀረበ በኋላ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የሚሰጥበት ሲኾን ለቤተ ክርስቲያን ወጥ የቦታ እና የቤት የኪራይ ተመን መመሪያ ዝግጅት በመነሻነት እንደሚያገለግል ይጠበቃል፡፡

የሚበዙት ገዳማት እና አድባራት የመሬት አጠቃቀም፤ የቦታ፣ የሕንፃ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ቤተ ክርስቲያንን በሚጠቅምና ሀብቷን በሚያስጠብቅ አኳኋን እየተፈጸመ እንዳልኾነ ከታኅሣሥ ወር መጀመሪያ አንሥቶ በውል ሰነዶች ምርመራ እና በግምገማ ስልት ሲካሔድ የቆየው የማጣራቱ ሒደት በግልጽ አሳይቷል፡፡ ተቋማቱ መሠረታዊውን ሐዋርያ ተልእኮዋን ለማጠናከርና ለማስፋፋት እንዲኹም የላቁ የማኅበራዊ ልማት አስተዋፅኦዎችን ለማበርከት እንድትችል አቅም ሊፈጥሩላት ሲገባ የአስተዳደር ሓላፊዎች እና ሠራተኞች ከጥቅመኛ ግለሰቦች ጋራ በኪራይ ውል አሰጣጥ እየተመሳጠሩ ሕገ ወጥ ጥቅም እንደሚያካብቱባቸው የአጥቢያዎቹ አለቆች፣ ዋና ጸሐፊዎች እና የሰበካ ጉባኤ አባላት በተገኙበት ተረጋግጧል፡፡

ከሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያት የወሳኝነት ሚና እና ከሚመለከታቸው የሀገረ ስብከቱ አካላት ዕውቅና ውጭ በልማታዊ አባት ስም በሚያጭበረብሩ የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ ቤተ ክርስቲያንን የሀብት ዋስትና በሚያሳጣ አኳኋን የሰፈኑት ችግሮች የጥናቱን ውጤት ተከትሎ የሚመጣውን የአሠራር ለውጥ የማይጠብቁና አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ኮሚቴው በተከታታይ የጥናቱ ዙሮች ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ያቀረባቸው ማሳሰቢያዎች ያስረዳሉ፡፡ በማጣራቱ ሦስተኛ ዙር ማጠቃለያ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቀረበው የኮሚቴው ማሳሰቢያ÷የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስን፣ የሰሚት ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረትን እና የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል አብያተ ክርስቲያንን ይመለከታል፡፡

የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ ከመንግሥት የሕጋዊ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማግኘት እጅግ በጣም ከፍተኛ ተጋድሎ የተደረገበት መኾኑን ኮሚቴው አስታውሷል፡፡ ይዞታው ያለበትን ኹኔታ ለማረጋገጥ በደብሩ በመገኘት ባደረገው እንቅስቃሴም አስተዳደሩ ከመመሪያ ውጭ ቦታ ለማከራየት ተዘጋጅቶ ተገኝቷል፡፡ ይኹንና እንቅስቃሴውን እንዲያቆም የተሰጠውን ማሳሰቢያ በመጣስ ግልጽነት በጎደለው የጨረታ ሥርዐት የማከራየት ሥራውን በመቀጠሉ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው፤ የአሠራር ማስተካከያ ተደርጎ ተለዋጭ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስም የማከራየት እንቅስቃሴውን እንዲያቆም ይደረግ ዘንድ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

የሰሚት ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ 28‚500 ካሬ ሜትር በካርታ የተረጋገጠ ይዞታ ያላት ናት፡፡ ከዚኽም ውስጥ 19‚904 ካሬ ሜትር ቦታ ከአካባቢ ዋጋ በታች በካሬ ብር 3.00 ዋጋ መከራየታቸው ተጠቅሷል፡፡ የኪራይ ውሎቹ የደብሩ አስተዳደር ለአምስት ዓመታት ውል የገባባቸው፣ በውል እና ማስረጃ የተረጋገጡ ሲኾኑ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለተከራዮች ዕድል የሚሰጡ በመኾናቸው ቀሪው 8‚000 ካሬ ሜትር ይዞታ ለአደጋ መጋለጡን እንደሚያሳይ ኮሚቴው በማሳሰቢያው አመልክቷል፡፡ ስለዚኽም የአሠራር ማስተካከያ ተደርጎ ተለዋጭ መመሪያ እስኪሰጥ ድረስ የደብሩ አስተዳደር ምንም ዐይነት የቦታ ኪራይ እንዳያካሒድ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ኮሚቴው፣ በገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ኹለት ግለሰቦች በብር 6 ሺሕ በነፍስ ወከፍ የተከራዩትን መጋዘንና ቦታ በብር 33‚000 እና በብር 55‚000 ለሦስተኛ ወገን በማከራየት እጅግ የተጋነነ ትርፍ በማግኘት ላይ መኾናቸውን በማጋለጥ በደብሩ ሓላፊዎች እና በግለሰቦች መካከል የቆየው ጥቅም እንዲቋረጥ አድርጓል፤ የሦስተኛ ወገን ተከራዮችም ከደብሩ ጋራ ቀጥተኛ ውል በመግባት ግለሰቦች በልዩነት የሚጠቀሙበት ብር 76‚000 አጠቃላይ ወርኃዊ ክፍያ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ እንዲደረግ ኾኗል፡፡ በአንጻሩ በማጋለጡና በማስተካከያው ያዘኑ የሚመስሉት የደብሩ የሥራ ሓላፊዎች፣ የአጥኚ ኮሚቴውን አባላት ስም የሚያጠፋ ደብዳቤ ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ ለበላይ አካል መጻፋቸው አግባብነት እንደሌለው ተጠቅሷል፡፡ ቅሬታቸውን ሰንሰለቱን ጠብቀው በሥርዐቱ ማቅረብ እንደሚችሉና ለሚያናፍሱት አሉባልታ ግን አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው ይገለጽላቸው ዘንድ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል በአጥኚ ኮሚቴው ሦስተኛ ዙር ማጣራት ከተካሔደባቸው አድባራት አንዱ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሲኾን የቃለ ዐዋዲ ደንቡን እና የኮንስትራክሽን ሕጉን በመጣስ በተፈጸሙ የኪራይ እና የግንባታ ውሎች በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለብክነት እና ለሙስና መጋለጡን አጥኚ ኮሚቴው በተጨባጭ አረጋግጧል፡፡ ብክነቱና ሙስናው መጋለጡን ተከትሎ አጥኚ ቡድኑን የረዱት የደብሩ ዋና ተቆጣጣሪ በአለቃው በኃይሌ ኣብርሃ ታግደው ምክትላቸው ተተክተዋል፡፡ ከዚኹ ጋራ በተያያዘ የቀንደኛው አማሳኝ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ አስተዳደር አፋጣኝ የአሠራር እርምት የሚያደርግበት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደሚጻፍለት ቢጠበቅም አልኾነም፡፡ የዚኽም ምክንያቱ ካለፈው መስከረም ጀምሮ ከአለቃው መመደብ ጋራ የደብሩ ዋና ጸሐፊ የኾኑት ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅም መኾናቸው በአጥኚ ቡድኑ አባላት መካከል ፈጥሮታል የሚባለው ተጽዕኖ ነው፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቀና የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና የሚጋፋ በመኾኑ የተቃወሙት የሊቀ ማእምራን የማነ አሿሿም፣ የሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ከደብር ዋና ጸሐፊነት ተደርቦ የተያዘበት ግራ አጋቢ ብቻ ሳይኾን አጥፊዎች ከመጠየቅ እና ከመቀጣት ይልቅ በሹመት እና በዝውውር ለሚበረታቱበት አሠራር ዐይነተኛ መገለጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ከሊቀ ጳጳሱ መመሪያ ሳይቀበሉ የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት ተገን በማድረግ በሚፈጽሟቸው ዝውውሮች በሞያዊነት የሚገዳደሯቸውን ሓላፊዎች ከማራቅ አልፈው፣ ቀድሞ በእነኃይሌ ኣብርሃ በተመዘበረውና አኹን ደግሞ ወላጅ አባታቸው በሚያስተዳድሩት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ‹‹የአባቴ ተቀናቃኞች›› ያሏቸውን ተቆርቋሪ ካህናትና ሠራተኞች እየተበቀሉ ይገኛሉ፡፡

በዋና ጸሐፊነታቸው የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ት/ቤቶች አመራሮችን ‹‹ከመዘመር ውጭ ምን ታውቃላችኹ?›› እንዳሏቸው ኹሉ፣ በዋና ሥራ አስኪያጅነታቸውም ተቃውሟቸውን ለፓትርያርኩ በመዝሙር የገለጹ የመካነ ሰላም ሰሚት መድኃኔዓለም ፍኖተ ሰላም ሰንበት ት/ቤት አመራር ያለደንቡ እንዲቀየር የአለቃውን ዓምባገነንነት በመደገፍ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱ የምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ሰልፍ በመውጣት የፀረ ኑፋቄ እና ፀረ ሙስና ንቅናቄአቸውን ያጠናከሩ የሀገረ ስብከቱን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር ለማገድ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ጋርም እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በዚኽም የሀገረ ስብከቱ የሙስና እና የምዝበራ ቴክኒሻኖች የሚባሉት የበጀትና ፋይናንስ ዋና ክፍል እና የቁጥጥር አገልግሎቱ ሓላፊዎች የሚተባበሯቸው ሲኾን እነኃይሌ ኣብርሃምም ‹‹ተሐድሶ የለም›› ከሚሉ ሌሎች መሰሎቻቸው ጋር በመኾን የሰንበት ት/ቤት አመራሮችን ለመከፋፈል እየተፍጨረጨሩ መኾኑ ተዘግቧል፡፡ የመንግሥት እንጂ የቤተ ክህነት ሹም እንዳልኾኑ መናገር የሚቀናቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ይህን ኹሉ የሚያደርጉት ‹‹የሀገረ ስብከቱን ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እና ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት ፖሊሲ እንድትቃኝ›› በሚል መኾኑ የጉዳዩን ተከታታዮች በእጅጉ እያሳዘነ ይገኛል፡፡

በአጥኚ ኮሚቴው የተጠቀሰው ሌላው ደብር፣ የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ነው፡፡ በካቴድራሉ ይዞታ የሚገኙት እንደ ወፍጮ ቤት፣ ኢንተርኔት ካፌ፣ ማተሚያ ቤት እና የንዋያተ ቅድሳት መሸጫዎች ያሉ የንግድ ቤቶች ከጨረታ እና ሕጋዊ አሠራር ውጭ እንደሚሰጡ ኮሚቴው ገልጧል፡፡ የሚሰበሰበው የኪራይ ገቢ በቦታው ላይ ያመጣው ለውጥ ብዙም በማይስተዋልበት ደብር፣ ከፋይናንስ እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ ምእመናኑ እና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ከሰኔ ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ ያደረጉት ተጋድሎ የሚታወስ ነው፡፡

ፖሊቲከኛነት የሚጫናቸው የዛሬው የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን ዘመንፈስ በእልቅና የነበሩበት ይህ ወቅት፣ የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ መመሪያው እንዲከበር የጠየቁ የሰበካ ጉባኤ አባላት ከምክትል ሊቀ መንበሩ ጀምሮ የተባረሩበት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት አባላት ለቀናት የታሰሩበት በአጠቃላይ በካቴድራሉ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ ይቋቋም እስከማለት የተደረሰበት የሠቆቃ ጊዜ ነበር፡፡ በኮሚቴው ማሳሰቢያ እንደተጠቀሰውም፣ ከ፲፱፻፸፰ ዓ.ም. ጀምሮ ከዘመናዊ ትምህርት አገልግሎቱ ባሻገር ለሰንበት ት/ቤቱ በኮርስ መስጫነት ሲያገለግል የቆየው የዐማኑኤል ካቴድራል አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ከ፳፻፪ ዓ.ም. ጀምሮ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጋራዥነት የተለወጠበት ነበር፡፡ የትላንት ረቡዕ ሰንደቅ ጋዜጣ ዝርዝሩን ይዟል፡፡

(ሰንደቅ፤፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፯፤ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

Debra Gelila St Amanuel Cathedral
ለረጅም ዓመታት የመማር ማስተማር አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ጋራዥነት በመለወጥ የግለሰብ መጠቀሚያ አድርጓል የተባለው የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል አስተዳደር የጋራዥነት ይዞታውን በማስለቀቅ ወደ ቀደመ አገልግሎቱ እንዲመልስ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጠው መታዘዙ ተገለጸ፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በጻፈው ደብዳቤ፣ የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ይዞታ የነበረውን 3000 ካሬ ሜትር ቦታ ወደ ጋራዥነት በመለወጥ ግለሰብ ነጋዴዎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ የተደረገበት አግባብ ተቋርጦ ትምህርት ቤቱ አገልግሎቱን ይቀጥል ዘንድ ለካቴድራሉ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጠው አዝዟል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ የ69 ገዳማት እና አድባራት የመሬት፣ የሕንፃ እና የመካነ መቃብር ኪራይ ችግሮችን እንዲያጠና የተቋቋመው ኮሚቴ ‹‹አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥበት የሚገባ›› በሚል ያቀረበውን ማሳሰቢያ መነሻ ያደረገው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ ካሬውን በብር 5.83 ሒሳብ በመከራየት ለካቴድራሉ ብር 17‚500 ወርኃዊ ክፍያ የሚከፍሉት ተከራይ ለሌሎች ተከራዮችም ሸንሸነው በማከራየት ያልተገባ ጥቅም እያገኙበት እንደኾነ በአጥኚ ቡድኑ መረጋገጡን ጠቅሷል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ለማኅበረሰቡ ከምትሰጠው የላቀ አገልግሎት አንጻር ይዞታው ወደ ጋራዥነት መዛወሩ አግባብ አለመኾኑን ጽ/ቤቱ በደብዳቤው ተችቷል፡፡ በመኾኑም ወደ ትምህርት ቤት አገልግሎቱ ስለሚመለስበት ኹኔታ የካቴድራሉ አስተዳደር በዝርዝር አጥንቶ ተገቢውን እንዲፈጽም፣ አፈጻጸሙም በሪፖርት እንዲገለጽለት ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ማሳሰቢያ መስጠቱ ታውቋል፡፡

አጥኚ ኮሚቴው እንዳረጋገጠው በካቴድራሉ የንግድ ቤቶች ከጨረታና ሕጋዊ አሠራር ውጭ ለተከራዮች ይሰጣሉ፤ የንግድ ተቋማቱ ስላሉበት ዝርዝር ኹኔታና ታሪክም የተደራጀ የሰነድ አያያዝ ችግር አለ፡፡ ከ፲፱፻፸፰ – ፳፻፪ ዓ.ም. ለኻያ አራት ዓመታት ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ታላላቅ ሰዎች የወጡበት የካቴድራሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ጋራዥነት የተለወጠውም ከትምህርት ሚኒስቴር የመጣ ደብዳቤ በወቅቱ ለሰበካ ጉባኤው ደርሶ ውሳኔ ካለማግኘቱ ጋራ በተያያዘ መኾኑን የካቴድራሉ ምእመናን ለሰንደቅ ተናግረዋል፡፡

ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ሲያስተምር የቆየው ት/ቤቱ፣ በአዲስ አሠራር ወደ አራተኛ አልያም ወደ ስምንተኛ ክፍል ተሻሽሎ ከፖሊሲው ጋራ መጣጣም እንደሚገባው በ፳፻፩ ዓ.ም. ጥቅምት የተጻፈው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ በካቴድራሉ የታወቀው በእጅጉ ዘግይቶ በነሐሴ ነበር፡፡ ተማሪዎችን መቀበል እንደማይችልና ሥራውን እንዲያቆም በድንገት ሲታዘዝ ከኻያ ያላነሱ መምህራንና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ችግር ላይ በመውደቃቸው ደመወዛቸውን ለመክፈል ሲባል ለጋራዥነት እንዲከራይ መደረጉን ምእመናኑ አስታውሰዋል፡፡

የጋራዡ የኪራይ ውል ባለፈው ታኅሣሥ ወር የተጠናቀቀ ቢኾንም ያለውል እስከ መጪው ሰኔ ፴ ቀን መራዘሙ ተጠቅሷል፡፡ በቅርቡ የተመረጠውና በሥራ ላይ የሚገኘው የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር፣ በመመሪያው መሠረት ጋራዡን ለማስለቀቅ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ የተገለጸ ሲኾን የኹለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመገንባት የልማት እና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተቋቁመው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገልጧል፡፡ የግንባታ ወጪውን ለመሸፈን ከኅብረተሰቡ እና ከበጎ አድራጊ አካላት ጋራ የተደረገው ውይይትም ‹‹ጀምሩት እንጂ እንተባበራለን›› የሚል ተስፋ ሰጪ ድጋፍና አስተያየት እንደተገኘበት ታውቋል፡፡

የዐማኑኤል ካቴድራል አንደኛ ደረጃ ት/ቤትን ወደ ኹለተኛ ደረጃ ለማሳደግ በቀድሞው ፓትርያርክ የሕንፃው ዕብነ መሠረት የተጣለው በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ነበር፡፡

Advertisements

One thought on “ትምህርት ቤቱን ወደ ጋራዥ የለወጠው የቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: