አመራር አልባው የአ/አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ሕግ አፍራሽ ይኹንታ በተሰጠው የሥራ አስኪያጁ ሕገ ወጥ የሓላፊዎች ዝውውር እና እግድ እየታመሰ ነው፤ ከጠቅ/ቤተ ክህነቱ ጋር ያለው ግንኙነት ተስተጓጉሏል

 • ያለሊቀ ጳጳሱ ዕውቅናና ፈቃድ በአምስት ሓላፊዎች ላይ እግድ እና ዝውውር ተፈጽሟል
 • አካሔዱ በሊቀ ጳጳሱ ሕገ ወጥ ነው በሚል ታግዷል፤ የሊቀ ጳጳሱ እግድ በፓትርያርኩ ተሽሯል
 • የተጠናከረው የሰንበት ት/ቤቶች ፀረ ኑፋቄ እና ፀረ ሙስና መነሣሣት በመንሥኤነት ተጠቅሷል
 • ‹‹ያለአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ እና ያለጥናት የአንድ አካባቢ ሰዎችን በመምረጥ የተፈጸመ ነው፡፡›› /ዋና ሓላፊዎቹ/

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በፓትርያርኩ ብቸኛ ምርጫ ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች መሾማቸውን ተከትሎ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ የተጀመረው ውዝግብ፣ ከሓላፊዎች ሕገ ወጥ ዝውውር እና የእግድ ርምጃ ጋራ በተያያዘ በመባባሱ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደራዊ አንድነት እና ሰላም አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ፡፡

የሥራ አስኪጆቹን ምርጫ እና ሹመት መነሻ በማድረግ ካለፈው መጋቢት አንሥቶ ተፈጥሮ የቆየው የፓትርያርኩ እና የረዳት ሊቀ ጳጳሱ አለመግባባት ዳግም ወደ ዐደባባይ የወጣው፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በአምስት የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች ላይ ሕገ ወጥ ዝውውር በማድረጋቸው እና በዛሬው ዕለት ደግሞ አንድ ሓላፊን ከሥራ እና ከደመወዝ በማገዳቸው እንደኾነ ተገልጧል፡፡

ዝውውሩ የተፈጸመው ዋና ሓላፊዎቹን በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዋና ክፍሎች መካከል በማሸጋሸግ፣ ወደ ክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶች ከደረጃ ዝቅ አድርጎ በመመደብ እንዲኹም ‹‹ለውጡን ተቃውመዋል፤ አሠራሩን አስተጓጉለዋል›› የተባሉ የአስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊውን ከሥራ እና ከደመወዝ በማገድ መኾኑ ተመልክቷል፡፡

በዋና ሥራ አስኪያጁ የተደረገው የዋና ክፍል ሓላፊዎቹ ሕገ ወጥ እና ያልተመከረበት ዝውውር፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው›› የሚለውን የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ድንጋጌ በሰበብነት በመጠቀም ከጅምሩም የሚታወቀውን የፓትርያርኩን ይኹንታና ፈቃድ ማግኘቱን ዛሬ ከቀትር በኋላ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በወጣ ደብዳቤ ተገልጧል፡፡


ፓትርያርኩ፣ በዋና ሥራ አስኪያጁ ለተደረገው የሓላፊዎቹ ዝውውር ይኹንታቸውን መስጠታቸው ይፋ ከመኾኑ አስቀድሞ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ የሕግ ድንጋጌ ውጭ የተፈጸመ መኾኑን በመግለጽ ታግዶ እንደነበር ታውቋል፡፡

Ab Kelementos' letter
በሀገረ ስብከቱም ኾነ በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሚደረጉ የሠራተኞች ዝውውር፣ ዕድገት እና ቅጥር ያለሊቀ ጳጳሱ ዕውቅና እና ፈቃድ መፈጸም እንደማይቻል በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እና በቃለ ዐዋዲ ደንቡ በግልጽ መደንገጉን ረዳት ሊቀ ጳጳሱ በእግድ ደብዳቤአቸው ጠቅሰዋል፡፡ ይኹንና ዝውውሩ እና ሽግሽጉ ከዚኽ መሠረታዊ የሕግ ድንጋጌ ውጭ መፈጸሙን ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አስገንዝበዋል፡፡

አፈጻጸሙ አግባብነት የሌለው ብቻ ሳይኾን ሠራተኞች ባሉበት ቦታ ላይ ተረጋግተው የመሥራት መብታቸውን የሚያሳጣ በመኾኑ በሀገረ ስብከቱ እና በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የተደረገውን ዝውውር እና ሽግሽግ እንዳይፈጸም መሻራቸውን እና ማገዳቸውን ባለፈው ዓርብ ለሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈ ቅዱስ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ ባሉበት ውይይት ተካሒዶ፣ የዝውውሩ እና የሽግሽጉ ጉዳይ ተጠንቶ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስም ሓላፊዎቹ ባሉበት ቦታ ላይ ኾነው ሥራቸውን እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡

ዝውውሩ፣ ‹‹በማናውቀው ጥፋት ከደረጃችን ዝቅ የተደረግንበት እና ሳንጠየቅ በግብታዊነት የተፈጸመ ነው›› ያሉ አምስት የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከትላንት በስቲያ ፓትርያርኩ ዘንድ ቀርበው አካሔዱ እንዲታረም ጠይቀው እንደነበር ታውቋል፡፡

የሠራተኞችን መብት፣ ደረጃ እና ሞራል ጠብቆ ማዘዋወር፣ ብርቱውን ማነቃቃት እና ደካማውን ማረም አግባብ ቢኾንም የአንድ አካባቢ ብቻ ሰዎችን በመምረጥ ያለጥናት እና ያለበቂ ምክንያት የተፈጸመው ከደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ዝውውር ሠራተኞች በሥራ መደባቸው የሥራ ዋስትና እንዳይኖራቸው የሚያደርግ እንደኾነ ሓላፊዎቹ ገልጸዋል፤ ከክርስቶስ፣ ከሐዋርያት እና ከአበው አስተምህሮ ውጭ፣ ‹‹የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው›› በማለት በዘር እና በብሔር ስሜት ተነድቶ የተወሰደ ርምጃ በመኾኑም ያልተለመደ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እና ፓትርያርኩ ለቆሙለት ዓላማም አፍራሽ መኾኑን በማሳሰብ ከፓትርያርኩ ፍትሐዊነትን እና ሚዛናዊነትን የተጎናጸፈ አባታዊ አመራር እና ውሳኔ እንዲሰጣቸውም ተማፅነው ነበር፡፡

ፓትርያርኩ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጋራ ያልተግባቡበት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ሹመት ከመፈጸሙ በፊት፣ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ጭቅጭቅ እና ውዝግብ አንጻር በስፋት እንዲጤን የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት እና ሠራተኞቹን በበላይነት የማስተዳደር ሥልጣን ያለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በቃልም በጽሑፍም ሲያሳስቧቸው ቆይተዋል፡፡

ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የተቃወሙት ሕገ ወጥ ሹመት ከተፈጸመበት ከመጋቢት ወር ወዲኽ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋራ ያለው መዋቅራዊ ግንኙነት የተስተጓጎለ ሲኾን በሀገረ ስብከቱም የሓላፊዎችን የሥራ ዝምድና ከማቃወሱም በላይ የሠራተኞችን እና የምእመናንን አንድነት እና ሰላም አደጋ ውስጥ እንደከተተው እየተገለጸ ይገኛል፡፡

Advertisements

5 thoughts on “አመራር አልባው የአ/አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ሕግ አፍራሽ ይኹንታ በተሰጠው የሥራ አስኪያጁ ሕገ ወጥ የሓላፊዎች ዝውውር እና እግድ እየታመሰ ነው፤ ከጠቅ/ቤተ ክህነቱ ጋር ያለው ግንኙነት ተስተጓጉሏል

 1. ታዛቢው May 13, 2015 at 6:40 am Reply

  ምነው እናንተ እንዲህ ያንድ ብሔር የበላይነት የነገሠበት ሀ/ስብከት ዐይናችሁ ስር ሲገነባ እንዳላየ ስታልፉ የከረማችሁ?የጠቅላይ ቤተክሕነቱ ስ/አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስና የአ/አ/ሀ/ስብከቱ አቡነ ቀሌምንጦስ የተቀናጀ አሰላለፍ በውስጡ ዘረኝነት የለውም ልትሉን ነው?ትግራውያኑ የሀ/ስብከቱ ም/ስ/አስኪያጅና የካሕናት አስተዳደሩ ሲነሱ ምነው ዝም አላችሁ?ወይስ እነሱ የግድ እናተ ሰፈር መወለድ ነበረባቸው?ሚዛናችሁ ግሩም ነው!!
  የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ኃላፊው በብጹዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሳይቀር በሙስና መሳተፉ ተደርሶበት በአስተዳደር ጉባኤ ተግሳጽ ተሰጥቶት ነበር፣የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊው ደብዳቤ በመሰወር ምንዱባን ካሕናትን ሲያስለቅስ የከረመ ነው፡፡ሁለቱም የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው፡፡ከዚህ አንጻር በአስተዳደር ጉባኤው ድምጽ አጥተው ከከረሙት ወገኖች መምህር ጌጡን ከጎንደር፣ከወለየዎች ወልደሰንበትን፣ከጎጃሞች አባ ኅሩይን በመጨመር ሀ/ስብከቱ ሚዛን እንዲኖረው መደረጉ ትክክል ነው፡፡
  በሚነሱትና በሚዘዋወሩት ሰዎች ቦታ እየገባ ያለው የትራይ ተወላጅ ተመርጦ አይደለም፡፡ሌሎቹም በሐውርት በአስተዳደሩ አንጻራዊ ድምጽ እንዲኖራቸው ነው ለማድረግ እየተሞከረ ያለው፡፡ስለዚህ ማን ተነሳና ተዘዋወረ ብቻ ሳይሆን ማን ተተካ በሚለው ነው አካሄዱ መገምገም ያለበት፡፡
  አቡነ ቀሌምንጦስ በደፈናው የጠቀሱት ቃለዐዋዲ አ/አ/ሀ/ስብከት ሀገረስብከትነቱ በግልጽ ለፓትርያርኩ እንደሆነ ስለሚገልጽ አናቅጹ ለሊቀጳጳስ ያስቀመጡት ድንጋጌ ትርጉም የሚሰራው ለፓትርያርኩ እንጅ ለአቡነ ቀሌምንጦስ አይመስለኝም፡፡አቡነ ቀሌምንጦስ አ/አ/ሀ/ስብከት ላይ ያላቸው ስልጣን ረዳት ሊቀ ጳጳስነት ነው፡፡ይህም ዋናው ሊቀጳጳስ ፓትርያርኩ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ስለሆነም ደብዳቤያቸው በፓትርያርኩ መሻሩ ከሕግ አንጻር ክፍተት ያለበት አይመስለኝም፡፡የረዳቱን ደብዳቤ ዋና ኃላፊው መሻሩ የተለመደ አሰራር ነው፡፡
  እኔ የምፈራው በዚህ ሁኔታ ጉዳዩ እየተካረረ ከሄደ ያሰቡትን ከማድረግ ወደኋላ የማይሉት ፓትርያርክ ባለፈው ጊዜ አቡነ አስጢፋኖስን እንዳደረጉት አቡነ ቀሌምንጦስንም እንዳያግዱ ነው፡፡ያ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ ለየለት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሐራዎች ነገር ከማወራከብ ብትችሉ ሚዛናዊ ኹኑ፡፡ በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳትና በፓትርያርኩ መሀል ለተፈጠረው ክፍተት ያላችሁ ድርሻ ቀላል አይምሰላችሁ፡፡

 2. Anonymous May 15, 2015 at 7:24 am Reply

  “…..የአንድ አካባቢ ብቻ ሰዎችን በመምረጥ….” ነው ያላችሁት፡፡ ሐገረ ስብከቱ እኮ 16 ክፍሎች አሉት፡፡ በእናንተ አቆጣጠር ብንሄድ አሁን ያሉትን ጨምሮ አሥር የሚሆኑት የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው፡፡ (ልብ በሉልኝ በእናንተ አቆጣጠር ነው) ታዲያ ይህንን እስከ ዛሬ ለምን አልተቃወማችሁም ? ኦሮሞዎች በሙሉ ፣ የደቡብ ተወላጆች እና እኛ የአዲስ አበባ ቅይጥ ተወላጆች…….. የሸዋ አማራ አይደለንም እኮ ፣ በወዲህ በቤተሰቦቻችን ቋንቋ እና ትውልድ የማናፍር ፣ ከፍ ሲል ኩሩ ኢትዮጵያውያን ነን ዋናው ብሔረ ሙላዳችንም በጥምቀት የከበረው የቤተ ክርስቲያን ልጅነት የመንግሥተ ሰማያት ዜግነት ነው፡፡
  ወደ አነሳችሁት የአንድ አካባቢ ተወላጆች ጨዋታ ልመለስና ፓትርያርኩ አባ ማቴዎስን ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ይሁንታ ሲሰጡ ፣ አባ ቀሌሜንጦስን በራሳቸው አቅራቢነት ለአዲስ አባባ ረዳት ሊቀ ጳጳስነት ሲያቀርቡ አንድ አካባቢን መሰረት አድርገው ነበር አላላችሁም፡፡ በሌላ በኩል ከሁለት ወር በፊት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የካህናት አስተዳደር የነበሩት ሁለት ሰዎች በፓትርያርኩ ደብዳቤና ትዕዛዝ ሲነሱ ትግራውያን ስለሆኑ አልነበረም እናንተም የአንድ አካባቢ ብቻ ሰዎችን በመምረጥ ለማለት ቀርቶ ዜናውንም አላነሳችሁትም፡፡
  አሁን የመጡት ከኦሮሞ ፣ ከወሎ ፣ ከጎንደር ፣ ከጎጃምና ከሸዋ ተወላጆች ናቸው! አንድ ዘር ታስቦ ቢሆን መቀየጥ አያስፈልግም፡፡
  ይልቁንስ እናንተንም ከትዝብት መሪዎችንም ወደ ወከባ እና የከረረ ጥል ከሚከተው አካሄዳችሁ ተመለሱና ፤ በንዝኃተ ደሙ ተረጭታችሁ ወደ ታተማችሁባት የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ተመለሱ፡፡

 3. ነብር፡አየኝ April 26, 2017 at 3:50 am Reply

  መፍትሄው፡ ቀላል፡ ነው፡፡ ኦርቶዶክስ፡ እምነት፡ ተከታዮች፡ እነኝን፡ ቀጣፊዎች፡ እርግፍ፡ አርጎ፡ ቢዘጋቸው፡ እንዲህ፡ አይባልጉም፡ ነበር፡፡ አነኝን፡ ባለጎች፡ አምላካቸውን፡ የናቁ፡ አንዴ፡ ነብስ፡ አባት፡ ( ድንቄም) አነዴ፡ ባርኩ፡ እያልን፡ ገንዘብ፡ እየጠፈጠፍን፡ ያጠገብናቸው፡ እኛ፡ነ ን፡፡

  1. ገነዘብ፡ መስጠት፡ አቁሙ፡
  2. ቤተሰኪያን፡ ቤትዋን፡ እስክታጸዳ፡ መሄድ፡ አቁሙ፡
  3. ቄስ፡ መቀለብ፡ አቁሙ፡፡
  4. ጠይቁ፡ አትፍሩ፡፡ ፍርሀት፡ አሚቀርፁብን፡ ይህን፡ ውንብድናቸውን፡ እንዳንጠይቅ ነው፡
  5. ቤተክርስቲያን፡ ሀብታም፡ ናት፡ ነገር፡ ግን፡ አንድ፡ ቀን፡ ደሀ ስትረዳ፡ አይተን፡ አናውቅም፡፡

  ኢትዬጵያውያን፡ አዬናችሁን፡ ክፈቱ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: