ፓትርያርኩ: ‹‹ገለልተኛ ነን በሚል ከእናት ቤተ ክርስቲያን መኮብለል ሊታረም ይገባል››

 • በሊቀ ጳጳስ ሥር የማትመራ ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት ለማለት ያስቸግራል
 • እንደቀደሙ ጠንክረን በማስተማር ወደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ማሰባሰብ ይገባናል
 • ቀኖናን በመጠበቅ ተልእኳቸውን በአንድነት እንዲያጠናክሩ ኹኔታው ሊመቻችላቸው ይገባል
 • ይህን ጊዜያዊ ስሕተት ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ምእመናን ተባባሪ መኾን ይጠበቅባቸዋል

Miyazya 28, 2007 Holy Synodየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤውን፣ ዛሬ ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ጀምሯል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ÷ ለቤተ ክርስቲያችን እና ለአገራችን የሚበጁ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በመፈተሽ እና በመመርመር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ፓትርያርኩ በንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የቅብብሎሽ አገልግሎት በመኾኑ ከአገር ውስጥ አልፎ መላውን ዓለም ባካለለ መልኩ እየተካሔደ እንዳለ የገለጹት ፓትርያርኩ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በኹሉም የዓለም ክልል ፈላጊዋ እየበረከተ መምጣቱን ተናግረዋል፤ ዕድሉ ለቤተ ክርስቲያናችን በጣም ትልቅ ስኬት የሚያስከትል በመኾኑ በሚገባ ልንሠራበትና ልንጠቀምበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከአገር ውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እየበረከቱ መምጣታቸው የቤተ ክርስቲያናችንን መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጪ እንደሚያደርገው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጠቅሰው፣ ‹‹ገለልተኛ ነን›› የሚል ስም በመጠቀም ከእናት ቤተ ክርስቲያን መኮብለል ግን መታረም ይኖርበታል ብለዋል፡፡ እንደ ፓትርያርኩ መግለጫ፣ የገለልተኛነት ስያሜ በቤተ ክርስቲያናችን ይኹን በኦርቶዶክሱ ዓለም በአጠቃላይ የለም፤ እንደ ቤተ ክርስቲያችን ቀኖና ካየነውም፣ በሊቀ ጳጳስ ሥር ኾና የማትመራ ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት ለማለት ያስቸግራል፡፡

ከእናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር በገለልተኛነት ስም መለየቱን ‹‹ባለመጠንቀቅ አልያም ባለማወቅ የተጀመረ ጊዜያዊ ስሕተት›› ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ‹‹ጊዜ ሊሰጠው ስለማይገባ›› እንደ ቀደሙ ጠንክሮ በማስተማርና በማስረዳት ወደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ኦርቶዶክሳዊ ቀኖናን በመጠበቅ የቤተ ክርስቲያናችንን ተልእኮ በውጭ አገር በማስፋፋት እና በማጠናከር ረገድ በውጭ አገሮች ለሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና አገልጋይ ካህናት እንዲኹም መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሙሉ ሓላፊነት፣ በአንድነት እና በኅብረት አብዝተው እንዲሠሩ ኹኔታዎችን ማመቻቸት ከቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚጠበቅ ፓትርያርኩ በመክፈቻ ንግግራቸው አሳስበዋል፤ ጊዜያዊ ስሕተት ሲሉ የገለጹትን የገለልተኛነት ችግር ለማስተካከል እየተደረገ ነው ላሉት ጥረትም ምእመናን እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

*       *       *

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የሚያዝያ ፳፻፯ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር ሙሉ ቃል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ምሕረትና ይቅርታ፣ ትዕግሥት እና ቸርነት የባሕርዩ የኾነ እግዚአብሔር አምላክ ሰፊውን የወርኃ ጾም አገልግሎት በሰላም አስፈጽሞ ብርሃነ ትንሣኤውን በሰላም ስለ አሳየን፣ እንደዚኹም ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና ዓመታዊ ከኾነ ከዚኽ የርክበ ካህናት ጉባኤ በሰላም ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡

‹‹ኀበ ሀለው ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡአን በስምየ አነ እሄሉ ማእከሌሆሙ ህየ፤ ኹለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እኾናለሁ፡፡›› /ማቴ.18፤20/

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከዚኽ በላይ በተጠቀሰው የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ቃል የተመሠረተ እንደኾነ ኹላችንም እናውቃለን፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ጀማሪና ፈጻሚ ራሱ ጌታችን ቢኾንም ሥራው በአጠቃላይ በሰው ልጅ ድኅነት ላይ የሚከናወን ፍጹም እና ምሉዕ ተልእኮ በመኾኑ በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በመኾኑም ተልእኮው እስከ መጨረሻ ለሚነሣው ትውልድ ኹሉ እንዲዳረስ፣ እርሱን ተከትለው የድኅነት አገልግሎት የሚሰጡ ሐዋርያት እንደሚያስፈለጉ ግልጽ ነበረ፡፡

ከዚኽ አንጻር የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የቅብብሎሽ ሥራ በመኾኑ እነኾ አባቶች ሲያልፉ በልጆች እየተተኩ ሥራው እኛ ዘንድ ደርሶአል፡፡ በዚኽም ‹‹ወናሁ አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ኅልቀተ ዓለም፤ እነኾ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ኹልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› /ማቴ. 28፤20/ ብሎ የገባልን ቃል ኪዳን በተግባር እየተፈጸመልን አገልግሎታችንን ከአገር ውስጥ አልፎ መላውን ዓለም ባካለለ መልኩ እያካሔድን እንገኛለን፡፡ በዚኽም እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ቤተ ክርስቲያናችን በኹሉም የዓለም ክልል ፈላጊዋ እየበረከተ መምጣቱ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናችን አማካይነት ሊሠራ ያሰበው ሥራ እንዳለ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ዕድል ለቤተ ክርስቲያናችን በጣም ትልቅ ስኬት የሚያስከትል በመኾኑ በሚገባ ልንሠራበትና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

በመኾኑም በውጭ አገሮች የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና አገልጋይ ካህናት እንዲኹም መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ ኦርቶዶክሳዊ ቀኖናን ከመጠበቅ ጋር በሙሉ ሓላፊነት፣ በአንድነት እና በኅብረት ኾነው በውጭ አገር ያለውን የቤተ ክርስቲያናችንን ተልእኮ በማስፋፋት እና በማጠናከር ረገድ አብዝተው እንዲሠሩ ኹኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅብናል፡፡

ከአገር ውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እየበረከቱ መምጣታቸው በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያናችን መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጪ እንደ ኾነ ሲያመለክት በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክርስቲያችንም ኾነ በአጠቃላይ በኦርቶዶክሱ ዓለም የሌለ ገለልተኛ ነን የሚል ስም በመጠቀም ከእናት ቤተ ክርስቲያን መኮብለል ሊታረም የሚገባ እንደ ኾነ ያመለክታል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያችን ቀኖና ካየነው በሊቀ ጳጳስ ሥር ኾና የማትመራ ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት ለማለት ያስቸግራል፡፡

በመኾኑም ያለጥንቃቄም እንበለው ያለማወቅ በፈጠረው መነሾ የተጀመረው ስሕተት ጊዜ ሊሰጠው ስለማይገባ በዚኽ ዙሪያ እንደ ቀደሙ ጠንክረን በማስተማር እና በማስረዳት ወደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ማሰባሰብ ይገባናል፡፡ምእመናንም ይህን ጊዜያዊ ስሕተት ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲኾኑ በዚኽ አጋጣሚ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከሰበካ ጉባኤ መቋቋም በኋላ ያሳየችው እመርታ በተለይም በትላልቅ ከተሞች እየታየ ያለው፡-

 • በኢኮኖሚ የመለወጥ ኹናቴ፣
 • የትምህርት ቤቶች በብዛት መገንባት፣
 • የጤና ተቋማትና የምግባረ ሠናይ ድርጅቶችን ማቋቋም እየተለመደ መምጣት፣
 • ወጣቶች በየሰንበት ት/ቤቱ ስለ ሃይማታቸው በቂ ዕውቀት መቅሰማቸው፣
 • የስብከተ ወንጌል ሥራ እየሰፋና እየተወደደ መምጣቱ እጅግ ተስፋ ሰጪ ኾኖ ይገኛል፡፡

እነዚኽ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ያላቸውን ክፍተት በመሙላትና በማስተካከል ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብ እና ብልሐት ከሠራንባቸው የዕጥፍ ዕድገትን ማምጣት እንደምንችል ኹኔታዎች ያሳያሉ፡፡ ስለኾነም ለበለጠ ዕድገት የተሻለ አሠራር እና የጋራ ተነሣሽነትን አንግበን በመሥራት ዕድገታችንን በፍጥነት እውን ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀን ሓላፊነት ነው፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ኹላችንም እንደምናውቀው ጥንካሬና ድክመት ምን ጊዜም ቢኾን የማይለያዩ አንጻራዊ ነገሮች ናቸውና በቤተ ክርስቲያችን አሠራር ውስጥም ጥንካሬ እንዳለ ኹሉ ድክመትም እንማይጠፋ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በተለይም ካለፉት ዘመናት ጀምሮ እየተከሠተ ያለው የምእመናን ፍልሰት ወይም የበጎች መነጠቅ እና መኮብለል በመጀመሪያ ሊቀመጥ የሚገባው መሠረታዊ ችግር ኾኖ ይታያል፡፡

ኹኔታው በዚኽ የሚቀጠል ከኾነ ከባድ ጥያቄ ሊያስነሣ የሚችል ጉዳይ መኾኑን ኹላችንም መገንዘብ አለብን፡፡ ስለኾነም ይህን ችግር በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል ጊዜ ሳይወስድ ይህ ቅዱስ ጉባኤ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል፡፡

ሌላ በቤተ ክርስቲያችን ተከታዮች እየተስተዋለ ያለው ችግር በስደት እና በዝርወት የሚከሠት የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የሃይማኖት ነጻነት ዕጦት አልፎ ተርፎም ሕይወትን ማጣት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በእነዚኽ ምክንያቶች የምታጣቸው ልጆች ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም፡፡ ልጆቻችን ለእንጀራ ፍለጋ ሲባል ወደ ባዕድ አገር ሲሔዱ ስመ ክርስትናን ከመለወጥ ጀምሮ ሃይማኖት እስከ መለወጥ የሚደርስ ተጽዕኖ ኹሉ እየገጠማቸው ብዙዎችን እያጣን ነው፡፡

ከዚኽም ጋራ በቅርቡ በሊቢያ እንደተከሠተው ያለ አረመኔያዊ ተግባር ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ የዚኽ ኹሉ ማባባሻ ኾኖ የሚገኘው ጥቅም በአገር ውስጥ ቢገኝ ኖሮ ልጆቻችን ለስደት አይዳረጉም ነበር፤ ካልተሰደዱም ከላይ የተገለጸው ግፍ እና በደል በልጆቻችን እና በቤተ ክርስቲያናችን አይደርስም ነበረና ነው፡፡ ስለኾነም አኹን በአገራችንም ኾነ በቤተ ክርስቲያችን ላይ በአሸባሪዎች እየተፈጸመብን ያለው ተግዳሮት በወሳኝ መልኩ ለመመከት በአገራችን ያለውን የልማት እና የዕድገት መርሐ ግብር ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ በማፋጠን ድህነትን ታሪክ ማድረግ ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያችን ተልእኮ ሊኾን ይገባል፡፡

ኾኖም ለብዙ ዘመናት ሥር ሰዶ የቆየው ድህነት በአንድ ጀምበር ይጠፋል ተብሎ ሰለማይገመት ‹‹ከመሞት መሰንበት›› የሚለውን አባባል በመከተልና አሁን ያለውን ምቹ ኹኔታ በመጠቀም ወጣት ልጆቻችን በአገራቸው ሠርተው እንዲያድጉ ቤተ ክርስቲያችን ያለማቋረጥ አዘውትራ ማስተማር እና መምከር ይገባታል፤ እየመከረችም ትገኛለች፡፡

በመጨረሻም ይህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሚቀርቡ አጀንዳዎች መሠረት ለሰላም፣ ለቤተ ክርስቲያችን እና ለአገራችን የሚበጁ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በመፈተሽ እና በመመረመር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በመወሰን ጉባኤውን እንዲያካሒድ በማሳሰብ የ2007 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም

Advertisements

8 thoughts on “ፓትርያርኩ: ‹‹ገለልተኛ ነን በሚል ከእናት ቤተ ክርስቲያን መኮብለል ሊታረም ይገባል››

 1. ሠይፈ ገብርኤል May 6, 2015 at 2:21 pm Reply

  ከመክፈቻ ንግግሩ ያጣኋቸው፦
  1. የሰንበት ት/ቤቶች ህብረትን ጥያቄዎች እንደሚመለከቷው እንኳን አለመጥቀሳቸው
  2. ውጭ ሀገር ስላሉ ከቤተ ክርስቲያናችን የተለዩ ሊቃነጳጳሳት የዕርቅ ጉዳይ ምንም አለማንሳታቸው
  3. በቤተ ክርስቲያናችን ተንዘራፍቶ ስላለው የገንዘብና የንብረት ዘረፋ ምንም አለማንሳታቸው
  4. ፓትርያርኩ በተለያዩ ጊዜያት “ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያጠፉና እንደሚዋጉ፣ የቤተ ክርስቲያንንም የቀድሞ ቅድስናዋን፣ ልዕልናዋንና ክብርዋን እንዲሚያስመልሱ” ስለትናገሩት ምንም አለማንሳታቸው
  5. “ድህነትን ታሪክ ማድረግ” ከየት የተወሰደች አባባል ናት?

  ቸር ያሰማን!

 2. Anonymous May 6, 2015 at 3:24 pm Reply

  ግንቦት ደረሰ ወሬ ቀንጥሱ፣
  ጥቅምት መጣ ወሬ ቀንጥሱ፣
  ሐራ ሚዛኑ የሲኖዶሱ፡፡
  በሉ እንግዲህ ትንሽ ቀን አናክሱን፡፡የስድብና የፍረጃ ወራት ደረሰ፡፡አባ ማትያስን ያልሰደበ ሁሉ መናፍቅ ይባል ይመስል ሁሉ ለስድብ ይሰለፋል፡፡በስድብና በፍረጃ አዋቂነትና ጽኑ አማኝነቱን ለማስመሰከር እነ ሐራ የከፈቱትን የሐሜት መስኮት ያጨናንቃል፡፡መረጃውን እንወረደ እየተቀበለ በየፌስቡኩ ይዘምታል፡፡ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 15 ቀናት የተለመደው የነአባ ማትያስ የስቅላት ጊዜ ነው፡፡ሁሉም ታጥቦና ተቀሽሮ በሚቀርብለት መረጃ መሰረት እንደየአቅሙ አባቱን ይቸነክራል፡፡ተጀመረ፡፡፡፡

  • Gere May 6, 2015 at 6:36 pm Reply

   አንተ ደሞ የትኛው ዘራፊ ት ሆን እዚህ እንድትጽፍ ስንጽ ተከፈለህ…. ሃሃሃሃሃ ማፈሪያ

  • Anonymous May 6, 2015 at 7:46 pm Reply

   አንተ ደሞ የየት አመላላሽ ነህ ባክህ ቱልቱላ

 3. Gere May 6, 2015 at 5:51 pm Reply

  Always there are such decisions by the Holy Synod, but implementation is zero; much talk but no work towards the decisions. Consistently inconsistent Pope: Aba Matyas

 4. Negash Tesfaye May 6, 2015 at 10:24 pm Reply

  Egziabher lebete krstiyanachin yemitekmewun esu yistat kelib honen entseliy

 5. Belachew May 7, 2015 at 3:50 am Reply

  He is a fake patriarch, weyane appointed cadre. No if or but.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: