ከገቢያቸው በላይ ሀብት ባካበቱ አማሳኞች እና ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር በሰረጉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

aa ssa rep reading the petiton

ፓትርያርኩ፣ ሰንበት ት/ቤቶቹ በጽሑፍ ያዘጋጁትን ጥያቄ እና አቤቱታ ለማዳመጥ ፈቃደኝነት ባለማሳየታቸው ተወካዩ በቃል አሳጥሮ ለማቅረብ ተገዷል

ዛሬ፣ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተካሔደው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ወቅት ከመላው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት የተውጣጡ ከኹለት ሺሕ ያላነሱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች÷በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት እና በግልባጭ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ በሀገረ ስብከቱ ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት ያሳወቁት አምስት ዐበይት እና በርካታ ንዑሳን ነጥቦችን ያካተተው አቤቱታ አንኳር ሐሳቦች

 • ቤተ ክርስቲያን ከዐሥር ሚልዮን በላይ ልጆቿን አጥታለች፤ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብቶቿን በአግባቡ እያስተዳደረች ለተልእኮዋ ማስፈጸሚያ ማዋል ሲገባት ከብክነት፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከተዝረከረከ አሠራር ጋራ ተያይዛ መጠቀሷ በእጅጉ ያሳዝነናል፡፡
 • ፓትርያርኩ ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያጠፉና እንደሚዋጉ፣ የቤተ ክርስቲያንንም የቀድሞ ልዕልናዋንና ክብርዋን እንዲሚያስመልሱ በተደጋጋሚ የገለጡ ቢኾንም እስከ አኹን ምንም የታየ ለውጥ ባለመኖሩ አማሳኞች እየተጠናከሩ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች በመዋቅር እየገቡ፣ ምዝበራ እና የአስተዳደር በደል እየተባባሰ ነው፡፡
 • በፓትርያርኩ ውሳኔ ከልዩ ጽ/ቤት በተጻፉ ደብዳቤዎች፣ በአዲስ አበባሀገረ ስብከት በቅርቡ የተካሔደው የሥራ አስኪያጆች ምደባ እና ሹመት ሕገጋተ ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቁ እና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚጋፉ ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያኗ ህልውና ሲባል መዋቅርን ባልተከተለና ሕገ ቤተ ክርስቲያን ባልጠበቀ መልኩ የሚፈጸሙ አካሔዶች የሚታረሙበት መንገድ እንዲቀየስ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

anti tehadeso and corrupts rally of sss

 • ሙስና እና ኑፋቄን የሚያጋልጡ የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች÷ ‹‹ሽብርተኞች ናቸው፤ መንግሥትን ለመገልበጥ አሲረዋል›› በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች በኑፋቄ እና በሙስና በተዘፈቁ የአስተዳደር ሓላፊዎች እና ሠራተኞች መዋከባቸው እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ከመንፈሳዊ አባትም የሚጠበቅ ባለመኾኑ በእኒኽ ሓላፊዎች ላይ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፡፡
 • በዝርፊያ የተሰማሩ እና በአግባቡ ሥራቸውን የማይሠሩ አንዳንድ የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች እና ተቆጣጣሪዎች ያላቸው ቤት፣ መኪና እና አኗኗር ከሚያገኙት ደመወዝ/ገቢ/ ጋራ የማይመጣጠን በመኾኑ በአቋራጭ ያለአግባብ የበለጸጉ መኾናቸውን በማያሻማ መልኩ የሚያረጋግጥ ነው፤ በዘረፉት ብርም ከግብር አበሮቻቸው ጋራ ቤተ ክርስቲያንን ሰላም እየነሱ ነው፡፡ ያለአግባብ የተያዘ ምንጩ የማይታወቅ ንብረት ማካበት በሕግ የሚያስጠይቅ በመኾኑ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በመንግሥት በኩል ማስረጃ ተጠናክሮ ለፍርድ እንዲቀርቡ በአንድነት እንጠይቃለን፡፡
 • በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩ መናፍቃን መካከል አንዳንዶቹ ባልታወቀ ምክንያት እንዲመለሱ መደረጋቸውና ስም በመቀየር መልሰው ሥራ የተቀጠሩ መኖራቸው በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ ጉዳያቸው በእንጥልል የቀሩት ግለ ሰዎች እና ቡድኖች ከዚኽ ቀደም ባቀረብነው ማስረጃ መሠረት እንዲኹም በሌሎች ቀሳጮች ላይ በቀጣይነት በምናቀርበው ማስረጃ መሠረት ጉዳያቸው ታይቶ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰድ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 • የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመኾናቸው፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና ቃለ ዐዋዲን የሚፃረሩ አፈጻጸሞች እየገዘፉ ለመጡት ችግሮች ዋነኛ መንሥኤ በመኾናቸው አቤቱታዎች ተጠራቅመው አቅጣጫቸውን ስተው ወደአልተፈለገ ደረጃ ከማምራታቸው በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በትኩረት ተመልክተው እልባት የሚሰጥ ውሳኔ ያሳልፉ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

*       *       *

presenting the petiton01
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች በሚያዝያ ፳፻፯ ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ወቅት ያቀረቡት ጥያቄና አቤቱታ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን፡፡

ሚያዚያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊት እና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በክርስቶስ ፈቃድ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እየፈጸመች ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ በእነዚኽ የኹለት ሺሕ ዓመታት ጉዞዋ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ፈተናዎች ገጥመዋታል፡፡ እነዚኽን ፈተናዎች ተቋቁማ ለአገራችን የትምህርት፣ የባህል፣ የሕግ እና ሌሎች አገራዊ ዕሴቶችና ሀብቶች መሠረት በመኾን አገልግላለች፡፡

ለታላቋ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሕግ አውጪ እና ወሳኝ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ከተቋቋመ የአንድ ሰው ዕድሜ እንኳን ኾነው ሊባል የማይችል እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው እና በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያናችን ኹለንተናዊ ዕድገት የሚጠቅሙ አያሌ ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡ ተወስነው ተፈጻሚ የኾኑ ጉዳዮች ከፍተኛ የአገልግሎት ዕድገት አምጥተዋል፡፡ ይህ ፈጽሞ የማይካድ ሐቅ መኾኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ጉዳዮች በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስነው ተፈጻሚ ባለመኾናቸው ምክንያት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አምጥተዋል፤ እያመጡም ይገኛሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የፈተና ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ ከመንበረ ማርቆስ በተሾሙ ግብፃውያን ጳጳሳት፣ አማካይነት በእነርሱም በተሾሙ ኢትዮጵያውያን ካህናትና ሊቃውንት ብሎም ለበርካታ ዓመታት ያለጳጳስ በነበረችበት ዘመን ኹሉ እንኳ ከባድ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ መንፈሳዊ ተልእኮዋን እና አስተዳደራዊ ሥራዎችን በሚገባ ተወጥታለች፡፡ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲፈጠሩ (ሃይማኖታዊ ሕፀፅ፣ ጥርጥር፣ ክሕደት) አባቶች ካህናት፣ ሊቃውንት እና መምህራን የሚመለሰውን መክረው እየመለሱ፣ አልመለስም ያለውን ደግሞ ከመንጋው እየለዩ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት እና ቅርስ ሳይሸራረፍ ምእመናንንም በንቃት በመጠበቅ ለዚኽ ትውልድ አስረክበዋል፡፡

ብዙ ያላመኑ ወገኖችን እያጠመቀች ድኅነት እንዲያገኙ ስታደርግ የነበረች እና ማድረግ ያለባት ቤተ ክርስቲያን አኹን ከዐሥር ሚልዮን በላይ የኾኑ የራሷን ልጆችን አጥታለች፤ ያላትን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብት በአግባቡ እያስተዳደረች ለተልእኮዋ ማስፈጸሚያ ማዋል ሲገባት የብክነት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እና የተዝረከረከ አሠራር ምሳሌ ኾናለች፡፡ ይህ ኹኔታ ደግሞ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ ሲሔድ አላስተዋልንም፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ነገሩ ኹሉ ከድጡ ወደ ማጡ እየኾነባት ይገኛል፡፡

ለመኾኑ ይህ ኹሉ ለምን ኾነ ብለን ስንጠይቅ ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እኛ ልጆቻችኹ ለእነዚኽ ኹሉ ችግሮች መንሥኤዎች ያልናቸውን ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

 1. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመኾናቸው፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና ቃለ ዐዋዲን የሚፃረር አፈጻጸም መኖሩ፡-

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (በረከታቸው ይደርብንና) የኘትርክና ዘመን ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰኑ አንገብጋቢ ውሳኔዎች ፍጻሜ አለማግኘታቸው አኹን ለገዘፈው ችግር መንሥኤ እንደኾነ እናምናለን፡፡ ይህ ኹኔታም የቤተ ክርስቲያናችንን አገልጋዮችና ምእመናን የሚያሳዝን ኾኗል፡፡ እዚኽ ላይ ጥሩ ማሳያ እንዲኾን አንድ ውሳኔ ከዚኽ በፊት ካቀረብነው እንዲኹም ደግሞ በቅርቡ ከተወሰነው ሌላ ጉዳይ እናቀርባለን፡፡ 

ሀ. ከዚህ ቀደም ካቀረብናቸው ጉዳዮች ቅዱስ ሲኖዶስ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን በተመለከተ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም በወሰነው ወሳኔ፡-

 • ጥፋተኛ ተብለው የተገኙ በሕግ እንዲጠየቁ የተወሰነው ውሳኔ ፍጻሜ አለማግኘቱ፣
 • ውሳኔው ለየአህጉረ ስብከቱ ደብዳቤ እንዲላክ ቢወሰንም አለመተግበሩ፣
 • የቤተ ክርስቲያንን የነገረ መለኰት፣ የነገረ ማርያም አስተምህሮ በተፃራሪ መልኩ አስተምረዋል፤
 • መጻሕፍት ጽፈዋል፤ የኑፋቄ ትምህርት አሰራጭተዋል በማለት ማስረጃ ያቀረብንባቸው አካላት ጉዳይ በእንጥልጥል መቅረቱ፣
 • ከላይ የዘረዘርነውን የስሕተት አስተምህሮ ስለሚያራግቡ ማኅበራት፣ ገጸ ድሮች፣ የቴሌቭዥን መርሐ ግብሮች ማስርጃ ብናቀርብም እስከ አኹን መፍትሔ አለመሰጠቱ፤
 • ይህን ውሳኔ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቁጥር 3160/90/03 በቀን 13/07/03 ዓ.ም ለአጥቢያዎች ስለ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና መዘምራን በተጻፈው ደብዳቤ ተግባራዊ ባለመኾኑ ዐውደ ምሕረቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በማይቀበሉና በአስተምህሮዋ ላይ በሚዘባበቱ ሰዎች መያዛቸው፤
 • ራሳቸውን አጥማቂ እያሉ በመሠየም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውጭ ስለሚያጠምቁ ግለሰቦች የቀረበው ማስረጃ እልባት አለማግኝቱ የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእነዚኽ ጉዳዮች ላይ የተወሰነው ውሳኔ ባለመተግበሩ ከተወገዙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ግለሰቦች እና ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎችም የጥፋት ተግባራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡  

ለ. በቅርብ ከተወሰኑ ውሳኔዎች መካከል፡-

ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ በአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ቀርበው ቀኖናዊ ምክር እና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ የወሰነውን ውሳኔ በ30/03/2007 ዓ.ም በቁጥር ል/ጽ/126/300/2007 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ውሳኔው ትግበራ ላይ እንዳይውል መታዘዙ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ ከመኾኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነትን የሚጋፋ ነው፡፡

ሐ. በተጨማሪም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብክት ሥራ አስኪያጆች ሹመት ምክንያት የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ስለ መፈጸሙ የደብዳቤ ልውውጦች ያመለክታሉ፡፡

 • ከልዩ ጽ/ቤት በቁጥር ል/ጽ/301/10/2007 ዓ.ም በቀን 10/07/07 እና በቁጥር 312/10/2007 በቀን 14/07/07ዓ.ም የወጡ ደብዳቤዎች፣
 • ለእኒኽ ደብዳቤዎች ምላሽ ለመስጠት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በቁጥር 3156/357/07 ቀን 14/07/2007ዓ.ም ለልዩ ጽ/ቤቱ የተላከው ደብዳቤ እንዲኹም ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቁጥር 3344/546/07 በቀን 11/07/07 ዓ.ም የተደረጉት የደብዳቤ ልውውጦች፣

ሕገጋተ ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቁና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚጋፉ ነገሮች እንዳሉ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ስለዚኽ ለቤተ ክርስቲያኗ ህልውና ሲባል መዋቅርን ባልተከተለና ሕገ ቤተክርስቲያን ባልጠበቀ መልኩ የሚደረጉ አፈጻጸሞች የሚታረሙበት መንገድ እንዲቀየስ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

2. ራሱን ‹‹የተሐድሶ አራማጅ›› እያለ የሚጠራው ቡድን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኅቡእ በመንቀሳቀስ እና ከውጭ ካሉት መናፍቃን ጋር በመተባበር ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ መኾኑ፤

ሀ. ከዚኽ ቀደም ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ ገብተው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በሚፃረሩ ግለ ሰዎች ላይ ማስረጃ በማጠናከር የአቀረብንባቸው ጉዳዮች ከፊሎቹ እልባት ቢያገኙም ከፊሎቹ ደግሞ ተንጠልጥለው መቅረታቸው በጥፋት ተልእኳቸው ለመግፋት ምቹ ኹኔታ ፈጥሮላቸዋል፤

ለ. በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩ መናፍቃን መካከል አንዳንዶች ባልታወቀ ምክንያት እንዲመለሱ መደረጋቸውና ስም በመቀየር ሥራ የተቀጠሩ መኖራቸው እጅግ አሳሳቢ እየኾነ መጥቶአል፤

ስለዚኽ ጉዳያቸው በእንጥልል የቀሩት ግለሰዎች እና ቡድኖች ከዚኽ ቀደም ባቀረብነው ማስረጃ መሠረት እንዲኹም በሌሎች ቀሳጮች ላይ በምናቀርበው ማስረጃ መሠረት ጉዳያቸው ታይቶ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰድ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡

3. ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በልዩ ልዩ መድረኮች ባደረጓቸው ንግግሮች እና እኛም በኅብረት ከእሳቸው ጋር በተወያየንበት ወቅት ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያጠፉና እንደሚዋጉ፣ የቤተ ክርስቲያንንም የቀድሞ ቅድስናዋን፣ ልዕልናዋንና ክብርዋን እንዲሚያስመልሱ በተደጋጋሚ የገለጡ ቢኾንም እስከ አኹን ምንም የታየ ለውጥ ባለመኖሩና ችግሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መምጣቱ የሚከተሉት ነገሮች ሊከሠቱ ችለዋል፡፡

ሀ. አንዳንድ የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች በጉቦና በዝርፊያ መሰማራታቸው፣ በአግባቡም ሥራቸውን አለመሥራታቸው፣ በሥራ ቦታ አለመገኘታቸው በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ምዝበራ እና የአስተዳደር በደል መኖሩን የሚያረጋግጡ ወይም የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

በዚኽ ክፉ ተግባር የተሠማሩ አካላት/ተቀጣሪዎች/ የሚያገኙት ደመወዝ/ገቢ/ ካላቸው ቤት፣ መኪና እና አኗኗር ጋራ የማይመጣጠን በመኾኑ በአቋራጭ ያለአግባብ የበለጸጉ መኾናቸውን በማያሻማ መልኩ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስለዚኽ እነዚኽ ግለሰቦች በዘረፉት ብር ከግብር አበሮቻቸው ጋራ በመኾን የቤተ ክርስቲያኗን ሰላም የሚነሱ በመኾናቸው ያለአግባብ የተያዘ ምንጩ የማይታወቅ ንብረት ማካበት በኢትዮጵያ ሕግ የሚያስጠይቅ በመኾኑ በመንግሥት ይኹን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ማስረጃ ተጠናክሮ ለፍርድ እንዲቀርቡ በአንድነት እንጠይቃለን፡፡

ለ. በሥራ ቦታቸው የማይገኙ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች፣ ደመወዛቸውን እንኳ በተልእኮ የሚቀበሉ ሓላፊዎች መኖራቸው በየአጥቢያው ላይ ብጥብጥና ችግር እያስከተለ በመኾኑ የእነዚኽ ሰዎች ጉዳይ በጥልቀት እንዲታይና መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡

ሐ. በአንዳንድ አድባራት የሀብታም ልጆች እና የድኻ ልጆች ብለው በመለየት ከፋፍለው ትምህርተ ሃይማኖት እናስተምራለን የሚሉ ግለሰቦች እና ሓላፊዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

4. እውነተኛ ፍትሕ አለመኖሩ፤

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አጥፊው የሚሾምበት፣ መልካም ሠሪው የሚታገድበት፣ በጥፋታቸው የተጐዱት ደግሞ ያለአግባብ የሚመለሱበት የጎጠኘነትና የዘረኝነት አሠራር የመሳሰሉት ነገሮች መንሰራፋታቸው ለአገልግሎት ትልቅ ዕንቅፋት ፈጥሮአል፡፡ በመኾኑም ይህ ተግባር የሚታረምበት አሠራር ይዘረጋ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡

5. አንዳንድ የአጥቢያ አስተዳደር ሓላፊዎች የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ማወከብ፤

አንዳንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች በኑፋቁ እና በሙስና ውስጥ የተዘፈቁ በመኾናቸው ‹‹በዚኽ ጉዳይ ሊያጋልጥን የሚችለው የሰንበት ተማሪ ነው›› ብለው ስለሚያስቡ ከሰንበት ተማሪዎች ጋራ ግጭት በመፍጠር የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን ሰላም በመንሣት አንድነታቸውን እያናጉ ይገኛሉ፡፡

ሓላፊዎቹ በአስተዳዳሪነት የተቀመጡበትን የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችን በማሳሰር ብሎም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ከመንግሥት ጋራ ለማጣላት ‹‹ሽብርተኞች ናቸው፤ መንግሥትን ለመገልበጥ አሲረዋል›› በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች ወጣቶችን በማዋከብ ላይ መገኘታቸው እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር፣ ከመንፈሳዊ አባትም የሚጠበቅ ኾኖ አላገኘነውም፡፡ ስለኾነም በእነዚህ ሓላፊዎች ላይ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡

ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱት በስፋት ተንሰራፍተው የሚገኙ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የማይመጥኑ እና ቅድስናዋን የሚፃረሩ አሳፋሪ ድርጊቶች አንገታችንን እያስደፉና እያሳፈሩን እያለ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን ለማለፍ ሃይማኖታችንም ኾነ ኅሊናችን የማይፈቅድ በመኾኑ፣ በእግዚአብሔር ዘንድም የሚያስጠይቀንና በታሪክ የሚያስወቅሰን ስለኾነ ጥያቄዎቻችንን ለማቅረብ ተገደናል፡፡

በየደረጃው ያሉ ሓላፊዎችም መፍትሔ ለመስጠት የሚቸገሩ መኾናቸውን በየጊዜው ባደረግናቸው ጥረቶች ያረጋገጥን በመኾኑ አቤቱታዎች ተጠራቅመው አቅጣጫቸውን ስተው ወደአልተፈለገ ኹኔታ ከመሔዳቸው በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በትኩረት ተመልክተው እልባት የሚሰጥ ውሳኔ ያሳልፉ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚጋፉ አሠራሮችን እንቃወማለን

የመናፍቃንን ሤራ እናጋልጣለን

 

    ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

   በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት

የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ በመኾን

 

ግልባጭ፡-

 • ለብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የወላይታና ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ
 • ለብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአ/አበባ ሀ/ስብከት የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የከምባታ ሐድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ የበላይ ሓላፊ
 • ለአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
 • በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የደኅንነት አማካሪ
 • ለፊዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
 • ለብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት
 • ለፌዴራል ፖሊስ
 • ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
 • ለአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፤
Advertisements

19 thoughts on “ከገቢያቸው በላይ ሀብት ባካበቱ አማሳኞች እና ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር በሰረጉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

 1. Anonymous May 5, 2015 at 7:23 pm Reply

  we do know you very much who you are. and the one who is behind you please stop bothering the holy church. but I do believe there are many corrupters in the Church. however if your really want to stand against them you have to follow the right way, because your way is not the right way.

  • Anonymous May 6, 2015 at 5:57 am Reply

   ወንድሜ ከዚህ የበለጠ ትክክለኛ መንገድ ምን አለ አባቶች ፊት ሄዶ በትህትና ከመማጸን ውጪ ፣ ለምንድን ነው ነገሮችን ሁሉ ወደ ሆነ ነገር ለመጠምዘዝ ምንሞክረው? እነዚህ ልጆች አብዛኛው ምእመን ተስፋ ቆርጦ ዝም ያለበትን ጉዳይ ነው ዋጋ ከፍለው በስርአት ለመጠየቅ የጣሩት፡፡ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!!!!!!!!!! እኔስ እላለሁ ይህ በትእግስት የሚለምን የሚለማመጥ ሁሉ እምቢ ያለ ለታ (የተቆጣ ለታ) ያኔ መመለሻም የለው፡፡ በቀላሉ እንዲህ የሚያሰቃዩትን የምእመን ገንዘብ ማስቆም እንደሚችልም እንዳይዘነጋ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እነከሌ እንዳይደርሱ ያለ ለታ መመለሻም እንደማይኖረው ማን በነገራቸው? አሁንም ስለምንም ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት ስለተሸሙባት ስልጣን ሲባል በትዕግስት ይለመናሉ

  • Anonymous May 6, 2015 at 6:04 am Reply

   if u believe there is corruption in church What does it mean “follow the right way” is that Anti corruption commission? What a funny is that?

  • Anonymous May 7, 2015 at 12:45 am Reply

   ይሄ ነው ማድረግ የሚገባቸው በዚሁ ይቀጥሉ ሌላውማ መቼ ተቆረቆረ እግዚአብሔር ይርዳችሁና ለዚች ቤተክርስትያን እድሮዋ ቦታ ይመልስልን ።ወንድሜ ትክክል አይደላችሁም አልካቸው ግን ትክክለኛውን መንገድ አልተናገርክም ለመወያየት ካልሆነ ለምን ብቅ አልክ።

 2. gelila May 5, 2015 at 9:51 pm Reply

  Wore wore bicha, and wusane yele!

 3. nehmiashishay May 6, 2015 at 5:48 am Reply

  continue it up and they will be through out of the saint church

 4. Anonymous May 6, 2015 at 6:04 am Reply

  why did you silent during kesis Belay regime, zim bilachihu tigalebalachihu, wefefe hula

 5. ስምዖን May 6, 2015 at 6:41 am Reply

  የጥቅምትና ግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ሲመጣ በብሎግ ተጠራርቶ ራስን እያጸደቁ ሌላውን መወንጀል ከአዲስ አበባ ሰ/ት/ቤት ያልተጻፉ ሕጎች አንዱ ሆነ መሰለኝ፡፡በየሰበካ ጉባኤው የሰ/ት/ቤት ተወካይ አለ፡፡ቅሬታችሁንና ማስረጃችሁን በዛ በኩል ማቅረብ ትችሉ ነበር፡፡አሁን የያዛችሁት የማኅበረቅዱሳን ተላላኪ መሆንን ነው፡፡ያሳፍራል፡፡ከቻላችሁ በራሳችሁ ሳንባ ተንፍሱ፡፡ቢያንስ ደግሞ አሁን ቅሬታ ተብየውን በመነጽር ታግዞ በወጣቶች ሥም ለማቅረብ እንደሚሞክረው እድሜውን ከቤ.ክ ተጠግቶ የቆይታውን ያህል የረባ መንፈሳዊ እውቀት ሳይጨብጥ ከካሕናት በቀሰመው አድማና አሉባልታ ከሚለካ ወመሽ ሸበቶ ሳይሆን በትክክል በቃለዐዋዲው መሰረት 30 አመት ያልሞላው ተወካይ እንዲናገር አድርጉ፡፡መናገር መብት ስለሆነ ማንም አይከለክላቸሁም፡፡የተሞላችሁትን ይዛችሁ ቁረጠው ፍለጠው ስላላችሁ ግን የሚሆን ነገር የለም፡፡በሰልፍና በመንጋ ሆኖ በጮኸ ሳይሆን እውነት የምትቆመው በማስረጃ ነው፡፡ለእያንዳንዷ በቤተክርስቲያን ባለች ድክመት ውስጥ ፓትርያርኩ ብቻ ሳይሆኑ ከሰ/ት/ቤት ጀምሮ ያሉ አካላት ተጠያቂ መሆናቸውን አትዘንጉ፡፡በከዳው ምዕመን፣በጠፋው ሥርዓት፣በጎደለው ገንዘብ ሁሉ ይብዛም ይነስም ሁልሽም እጅሽ አለበት፡፡ወላ ማኅበረቅዱሳን ወላ ሰ/ተማሪ፡፡እንደ ጲላጦስ እጅሽን ቀድመሽ ለመታጠብ አትሽቀዳደሚ፡፡እሱ የቸከና የመነቸከ ከማኅበረቅዱሳን የተዋሳችሁት መፈክር ተነቃበት፡፡ሌላ ሞክሩ፡፡

  • ኀይለገብርኤል May 6, 2015 at 12:44 pm Reply

   እሺ አንተ መናፍቅ እዚህ ምን ትሰራለህ?አዳራሽህ ሄደህ ጩህ

  • Anonymous May 11, 2015 at 1:35 pm Reply

   በፈጠረህ አምላክ የመምታምን ከሆነ ማለቴ ነው፡ ከምትከሳቸው ሰዎች አሻላለሁ ካልክ የስድብ አፍ አይኑርህ፡፡ ተሳደቡ ይላል እንዴ እምነትህ፡፡ ዘመን አያሳየው የለው

 6. Anonymous May 6, 2015 at 12:01 pm Reply

  ግልባጩን ለእነማን እንደጻፋችሁ ሳይ ዘወትር አባቶችን ፖለቲከኞች አድርጋችሁ ለመፈረጅ ከምትጠቀሙበት መረጃ አንዱ ደብዳቤያቸውን ለመንግሥት አካላት ግልባጭ ያደርጋሉ የሚለው ታወሰኝ፡፡ለካ ለመንግሥት ግልባጭ አድርጎ መጻፍ ፖለቲካ የሚሆነው ለፓትርያርኩ ሲሆን ብቻ ነው፡፡በስንቱ እንገረም በማርያም

 7. Abraham May 6, 2015 at 12:22 pm Reply

  ወገን ብናስተውል መልካም ነው፡፡ አካሄዱን ባልደገፋችሁት የሚጠቀሱት ሀሳቦችና ከዚያም በላይ ሳይሞከር ወደዚህ እርምጃ ይኬዳል ብየ አላምንም፡፡ ይህም እርምጃ ሲወሰድ ብዙ ታስቦና ተመክሮበት እንዳማራጭ የተወሰደን ድርጊት ከዚህ ሁሉ ሰው ሀሳብ የኔ ሀሳብ ይበልጣል አይነት ግለፅ አማራጭ የሌለው ድንፋታ ምንም ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡ የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው፣ በአርምሞና በትህትና ቀርበው ጥያቄ ማቅረባቸው ምኑ ላይ ነው ጥፋቱ? ምናልባት ጋሻና ጦር ቢይዙ አለዛም ድንጋይ ቢወረውሩ ይሻል ነበር አይነት ይመስላል ተቃውሟችሁ፡፡
  ማህበረ ቅዱሳንን በተላላኪ የሚመራ፣ ደካማና ፊት ለፊት በአግባቡ ችግሮችን መጋፈጥ የማይችል አካል አድርጋችሁ የምታስቡ ወገኖች ራሳችሁን ብትፈትሹ አለዛም መናፍቅነታችሁን በግልፅ ብታሳዩ ይሻላል፡፡ በጉያዋ ተቀምጣችሁ የወገን አስመስላችሁ የምትሰብቁትን የጠላት መርዘኛ ጦር ልታቆሙ ይገባል፡፡ ከመናፍቃን የምትለቅሙትን ፍርፋሪ ለማራዘም ብላችሁ ህሊናችሁን አትሽጡ፤ ይህ አካሔዳችሁ አንድቀን ሲጋለጥ መደበቂያው እንዳይጠባችሁ አስቡ፡፡

  ሙሰኞችንና አስመሳዮችን እግዚአብሔር ልብ ይስጣቸው!

  ስለ ርትዕት ኦረቶዶክስ እምነት የሚታገሉትን አባቶች፣ ማህበረ ቅዱሳንና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እግዚአብሔር ያበርታልን!

  ኦርቶዶክስትለምልም!

  እግዚአሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

  • ስምዖን May 7, 2015 at 6:22 am Reply

   አማሳኝ ተብለው የሚሳደዱት ሰዎች ማኅበረቅዱሳንን ከመውቀሳቸው በፊት ከነመኖራቸውም የሚያውቃቸው አልነበረም፡፡ከወቀሳው በኋላ ግን ሁሉም ሥራው እነሱን ማላመጥ ነው፡፡ሚዲያው በየሰ/ት/ቤቱ አባላት ጭንቅላት ስማቸውን ነቀሰው፡፡

   የሚገርመው በዋናነት ተፈርጀው የሚሳደዱት መልአከ መንክራት ኃይሌ እና ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ በራሳቸው ደብር ሰ/ት/ቤት ተቃውሞ ሲነሳባቸው አላየንም፡፡ በብሎግ የሚመርሸውና በማኅበረቅዱሳን የሚነዳው የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አመራር ግን ሐሜት እየደረደረ ሥልጣኑን እስከ ሽበት እድሜው ለማራዘም ሲል በዋናነት ሐራ ላይ የወጡ የአንድ ወገን አድሏዊ መረጃዎችን ተሸክሞ እንገፍ-እንገፍ ይላል፡፡ ቀሲስ በላይ የተሸመው በፓትርያርኩ ደብዳቤ ነበር አሁንም የማነ በእሳቸው ደብዳቤ ተሸመ፡፡ሁልሽም ግን ሐራ ያወራውን ይዘሽ በስ/አስኪያጅ ሹመትም ለማዘዝ ያምርሻል፡፡እስኪ ዝምብላችሁ አትነዱ፡፡
   ሰልፉ ላይ ያለው አብዛኛው ተሰላፊ ስለሚቀርበው ጽሑፍ ይዘት ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የጥቂት ሰዎች ሥራ ናት፡፡

   የሱስ ይሁን ፓትርያርክ እየተሳደቡ ጽላት የተቀረጸለት ይመስል ማኅበራችንን ምንም አትተቹብን ብለው የሚያላዝኑትና ሰው ካልተከፈለው ወይም መናፍቅ ካልሆነ በቀር ማኅበረቅዱሳንን አይተችም ብለው የሚያሽቃብጡት ናቸው የሚገርሙት፡፡ወዳጆች እናንተ ፓትርያርኩንና አባ ሰረቀን የምትሞልጩት ማኅበረቅዱሳን እየከፈላችሁ ነው ማለት ነው እንዴ?ትገርማላችሁ፡፡አፈ – ጻድቅ ሁሉ፡፡

 8. ኀይለገብርኤል May 6, 2015 at 12:37 pm Reply

  መናፍቁ ሰረቀ ምን እየሰራ ነው፡አባ ማትያስ ደግሞ አያልቅባቸውም ብለው ብለው በተንቀሳቃሽ ስልክ ምስል አንሽነት ቀጠሩት

 9. Kessis gebrekrstos May 7, 2015 at 7:04 am Reply

  realy it is too late but still Lrefedem.

 10. Anonymous May 7, 2015 at 8:12 am Reply

  ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ-ክርስቲያን አሀቲ ቅድት ጉባዔ (ስለ አንዲቷ የተቀደሰች ቤተ ክርስቲያናችን ሰላም እንጸልይ) በርቱ ወንድሞቻችን፡፡ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!!!!!

 11. Anonymous May 8, 2015 at 10:10 am Reply

  ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ-ክርስቲያን አሀቲ ቅድት ጉባዔ (ስለ አንዲቷ የተቀደሰች ቤተ ክርስቲያናችን ሰላም እንጸልይ) በርቱ ወንድሞቻችን፡፡ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!!!!! እውነት ብለካል ወንድሜ

 12. Anonymous May 22, 2015 at 8:50 am Reply

  ሁሉም ጋር የየራሱ ችግር ይኖራል ሰውም አይደለን ነገር ግን ስለ ቅድስ ቤተክርስቲያ ህልውና እየሆነ ያለውን የምናየውን አንታገስም ማለታቸው ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም እኛም እያየን እየሰማን ነው እና በተለይ ተሀዳሶ የተባሉትን አጥብቀን እንቃወማለን የቅዳስት ቤተክርስቲያን ሥርዓት አይታደሰምና፡፡ ሁላችንንም ልዑል እግዚአብሄር ማስተዋል ያድለን ድግንል ማርያም አሰራት አገርሽን በምልጃሽ አስቢያት አሜን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: