ክርስትና የየዕለት ሰማዕትነት ነው፤ ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ተነጥሎ ሊታይ አይችልምና

(ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፤ መድሎተ ጽድቅ፤ ሚያዝያ ፳፻፯ ዓ.ም.)

Dn. Yaregal Abegaz

ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ቸርነት የተሰጠን መዳን በመስቀል ላይ የተፈጸመ መኾኑን እንደሚነግረን ኹሉ ያን መዳን ገንዘብ ለማድረግ እያንዳንዱ ሰው ከማመን ጀምሮ በተቻለው መጠን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ ባሳየንና ባስተማረን መጓዝና መጋደል ያለበት መኾኑን ያስተምረናል እንጂ በክርስቶስ ድነናል እንጂ ንጽሕናን ለመጠበቅ መጋደል፣ እንዲኹም ሰውነትን በገድል ማስጨነቅ አያስፈልግም አይልም፡፡ እንዲኽ የሚለው አባባል ጠላት የዘራው እንክርዳድ ብቻ ነው፡፡ እንክርዳድ ደግሞ ከስንዴው ጋራ ስለሚመሳሰል መጠንቀቅና መለየት የእያንዳንዱ ድርሻ ነው፡፡…

በመዳን ትምህርት ዙሪያ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ስሕተቶች እና ችግሮች በጣም ብዙ ቢኾኑም በሦስት ነጥቦች ዙሪያ ሊጠቀለሉ ይችላሉ፡፡ ይህም አንደኛው፣ መዳንን ከኃጢአት ቅጣት ማምለጥ ብቻ አድርጎ የሚወስድና በመካከለኛው ዘመን ከነበረው የወንጀለኞች መቅጫ ሕግ አንጻር የተቃኘና በዚያ የተመሠረተ መኾኑ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ግን መዳን ከዚያ ባለፈ ከመለኰቱ ባሕርይ ተካፋይ እስከ መኾን የሚደርስ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት ‹‹መዳን›› ሲልና ፕሮቴስታንት መራሾቹ ተሐድሶዎች ‹‹መዳን›› ሲሉ በውስጡ ያለው ነገር እጅግ የተለያየ ነው፡፡

በኹለተኛ ነጥብ ደግሞ፣ እያንዳንዱ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች ትምህርት ሰው የሚድነው ‹‹በእምነት ብቻ ነው›› የሚሉ ሲኾን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ግን ሰው ለመዳን እምነት መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ነገር አለመኾኑን ‹‹በእምነት ብቻ መዳን›› የሚል ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለና መናፍቃኑ የፈጠሩት ሰው ሠራሽ ትምህርት መኾኑን፣ እንዲኹም መጀመሪያ ማመን፣ ቀጥሎም መጠመቅ፣ ከዚያም የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነገሮች መኾናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ደጋግሞ በአጽንዖት የሚያሰረዳን መሠረታዊ ትምህርት መኾኑን በስፋት አይተናል፡፡

ከዚኽም በኋላ በአንድ በኩል የተቀበሉትን የመዳን ጸጋ ለመጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ…›› እንደተባለው መዳን ሕያው እንደ መኾኑ በሱታፌ አምላካዊነት ማደግም ስለኾነ በጾም፣ በጸሎት፣ በመንፈሳዊ ትጋት፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሱታፌ መጋደልን ይጠይቃል፡፡ ‹‹እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል›› የተባለውን፣ እንዲኹም ‹‹እስከ ሞት ድረስ የታመንኽ ኹን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለኹ›› የተባለውንና ይህን የመሰሉትን ሌሎችም ብዙ አምላካዊ ቃላት እናምናለንና፡፡

በመጨረሻም ክርስትና የመልካም ምግባር ሕይወትን ለመያዝና በዚያ ለማደግ የሚደረግ የዕድሜ ልክ ሒደት ነው፡፡ ክርስትና ጌታ በወንጌል ‹‹መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፣ ከደስታውም የተነሣ ሔዶ ያለውን ኹሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ›› ብሎ የገለጸው ነው፡፡ የክርስትና እምነት የገባው ሰው በእርሷ ሰው የተሰወረውን ክቡር ነገር ለማግኘት ሲል ደስ እያለው ያለውን ኹሉ እስኪሸጥ ድረስ ይደርሳል፤ ያለውን ኹሉ ሳይሸጥ ግን ያን የተሰወረ መዝገብ መግዛት አይችልም፡፡ ይህም በጥምቀት ተጀምሮ ከዚያ በኋላ በሚደረግ ተጋድሎ በሒደት የሚደረግ መንፈሳዊ ዕድገት ነው፡፡ ግቡም ከእግዚአብሔር ጋራ መኖርና እርሱ ‹‹የሰማዩ አባታችኹ ፍጹም እንደኾነ እናንተም ፍጹማን ኹኑ›› ብሎ የተናገረውን ፍጽምና ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ የክርስትና ሕይወት ዓላማው እግዚአብሔር በባሕርዩ ያሉትን ለእኛ ደግሞ በጸጋ ገንዘብ እናደርጋቸው ዘንድ በቸርነቱ የሰጠንን መልካም ነገሮች ለማግኘት ከሰው የሚጠበቀውን ኹሉ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚኽ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ የቅድስናና የመልካም ምግባር ሕይወትን ገንዘብ ለማድረግ መጋደል መሠረታዊ ነገር ነው፡፡

ስለኾነም ክርስትናን ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ በብሉይ ኪዳን ከግብጽ የወጡት እስራኤላውያን መካከል የተቆጠሩትና ብዛታቸው ይህን ያኽል ተብሎ በቁጥር መጽሐፍ(በኦሪት ዘኍልቁ) የተነገረን ዕድሜአቸው ከኻያ ዓመት በላይ የኾኑ ወንዶች ብቻ፣ ከእነዚያም መካከል ወደ ጦርነት መሔድ ከጠላት ጋራ መዋጋት የሚችሉ ጤነኞችና አካለ ሙሉዎች፣ እንዲኹም ያልሸመገሉና ያልደከሙ ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ በኦሪት ዘኍልቁ በምዕራፍ ኹለት ላይ ‹‹ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤት የተቈጠሩ እነዚኽ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ኹሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ኃምሳ ነበሩ›› ይላል፡፡ ኦ.ዘኍ.፪÷፴፪፡፡ ኾኖም ከግብጽ የወጡት የአጠቃላይ የሕዝቡ ቁጥር ግን ቢያንስ የእነዚያን ያኽል ሴቶች(ሚስቶቻቸውን)፣ ሕፃናትን፣ ሽማግሌዎችንና ደካሞችን ስንጨምርበት ከአንድ ሚልዮን በላይ ይኾናል፡፡ ኾኖም የተቈጠሩት ግን ወደ ጦርነት መዝመትና ከጠላት ጋራ መዋጋት የሚችሉት ብቻ ነበሩ፡፡ ያ ለክርስትና ሕይወት ምሳሌ ነው፡፡

የክርስትና ሕይወትም ከርኩሳን መናፍስት እና ከእኵያት ፍትወታት ጋራ የሚደረግ ረቂቅና መንፈሳዊ ውግያ መኾኑን አመላካች ነበር፡፡ ያን ጊዜ ተቆጥረው በኦሪት ዘኍልቁ የተጻፉት የሚዋጉት ብቻ እንደ ነበሩ ኹሉ ዛሬም በእግዚአብሔር ፊት የሚቆጠሩትና በሕይወት መጽሐፍ የሚጻፉት መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጋደሉ ብቻ ናቸው፡፡ ክርስትና ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ተነጥሎ ሊታይ አይችልምና፡፡

Medlote Tsidik, Dn Yaregal New Book
ክርስትና በየዕለቱ ከክፉ ፍላጎቶች እና ከክፉ መናፍስት ጋራ የሚደረግ የዕድሜ ልክ ተጋድሎ ነውና፡፡ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹ለኹሉም እንዲኽ አላቸው፡- በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› ያለው ለዚኽ ነው፡፡ ሉቃ.፱÷፳፫፡፡ ክርስትና የአንድ ሰሞን ሳይኾን የዕለት ተዕለት መስቀል መሸከም(ተጋድሎ መንፈሳዊ) ነውና፡፡ ክርስትና የየዕለት ሰማዕትነት የሚባለውም ለዚኽ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንዲኽ ሲል የገለጸው ይህንኑ ነው፡-

የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችኹ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ኹሉ ልበሱ፡፡ መጋደላችን ከደም እና ከሥጋ ጋራ አይደለምና፤ ከአለቆች እና ከሥልጣናት ጋራ ከዚኽም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋራ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋራ ነው እንጂ፡፡ ስለዚኽ በክፉው ቀን ለመቃወም፣ ኹሉንም ፈጽማችኹ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ኹሉ አንሡ፡፡ እንግዲኽ ወገባችኹን በእውነት ታጥቃችኹ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችኹ፣ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችኹ ተጫምተው ቁሙ፤ በኹሉም ላይ ጨምራችኹ የሚንበለበሉትን የክፉዎች ፍላጻዎች ኹሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነት ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ኤፌ.፮÷፲፩-፲፯፡፡

ኾኖም ይህ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ሕይወት በመዳን ውስጥ ያለው ሚና በፕሮቴስታንቱ ዓለም አላስፈላጊና ለክርስቶስ የማዳን ጸጋ እንደ ተቃራኒ ተድርጎ በይፋ ይለፈፋል፡፡ በመኾኑም ክርስትናን ከመሠረታዊ ባሕርዩና ማንነቱ ነጥለው ስሙን ብቻ እንደ ማስታወቂያ ይዘው ውስጡን ግን አራቁተውታል፡፡ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች አንደኛው መሠረታዊ ችግራቸው ይህን አለመረዳታቸው ነው፡፡ የዚኽ ዋናውና መሠረታዊው ምክንያትም ከትንሣኤ በኋላ በሚገኘው ዘለዓለማዊ ክብርና ሕይወት በሚገባ አለማመናቸው ነው፡፡ ምዕራባዊው ዓለም የክርስትና መሠረት የኾነውን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና የትንሣኤውን አማናዊነት ለማመን እየተቸገረ ያለበት ኹኔታ በመኾኑ ከሞት በኋላ ስለሚገኘው ሕይወትና ክብር ሲሉ አኹን ባለው ዓለም የሚገኘውን ተድላና ጣዕም ለመተውና ራስን በመግዛት ለመጋደል ፍላጎቱም እምነቱም በእጅጉ እየራቃቸው ሔዷል፡፡

ክርስቲያናዊ ተጋድሎን፣ ለሰማያዊ ክብርና ጸጋ ሲሉ ራስን መግዛትንና ይህን ዓለም መናቅን በተለያዩ መንገዶች የሚያጥላሉትና የሚያቃልሉት ከዚኽ ውስጣዊ የእምነትና የአረዳድ ችግራቸው የተነሣ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ እግዚአብሔር ለሰዎች ተስፋ አድርጎ የሰጠው መልካም ነገር በዚኽ ዓለም በሚደረግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገትና ያ በሚያመጣው የኑሮ መሻሻልና ብልጽግና እውን ሊኾንና ሊፈጸም ይችላል እያሉ እንደ ፍልፈል ምድር ለምድር እየቆፈሩ ይገኛሉ፡፡ ‹‹ሐሳባቸው ምድራዊ ነው›› ተብለው የተገለጹት ዓይነት ናቸው፡፡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች ችግርም ይህን ከክርስትና መንፈስ ባዕድ የኾነ ባህልና ፍልስፍና እንዳለ አፍሰው መጋታቸው ነው፡፡ ከእኒኽም የተወሰኑት በየዋህነት መልካምና እውነት መስሏቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ እያወቁ እንደ ይሁዳ ለጥቂት ገንዘብ ሲሉ ለማጥፋት ነው፡፡(ገጽ 261 – 263፤ ገጽ 421)

Advertisements

3 thoughts on “ክርስትና የየዕለት ሰማዕትነት ነው፤ ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ተነጥሎ ሊታይ አይችልምና

  1. sentalewu January 3, 2017 at 4:31 pm Reply

    እግዚአብሔር ይስጥልን

  2. sentalewu January 3, 2017 at 4:32 pm Reply

    Egziabher yistiln

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: