በማኅበረ ቅዱሳን: ሰማዕትነት ለክርስትና በሚል ርእስ ነገ ውይይት ይካሔዳል

on martyrdomበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማእከል÷ ‹‹ሰማዕትነት ለክርስትና› በሚል ርእስ ነገ፣ ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 – 11፡00 ሰዓት በማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት አዳራሽ ጥናታዊ ውይይት ያካሒዳል፡፡

የጥናታዊ ውይይት መርሐ ግብሩ፣ በየኹለት ወሩ (በዓመት ስድስት ጊዜ) በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ የሚዘጋጀው የነገረ ቤተ ክርስቲያን የውይይት መድረክ አካል ቢኾንም የሊቢያ ኦርቶዶክሳውያን ሰማዕታትን በማሰብ እና የኦርቶዶክሳዊ ጽናት ምሳሌነታቸውን በመከተል ከትውልዱ ምን እንደሚጠበቅ አትኩሮ የሚካሔድ መኾኑ በዓይነቱ ልዩ እንደሚያደርገው ከማእከሉ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

Yared Shumete picture of Kirkos mourningከነገው ጥናት አቅራቢዎች አንዱ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የኾኑት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ ሲኾኑ በቂርቆስ የሊቢያ ሰማዕታት ቤተ ሰዎች መካከል በመገኘት በሰጡት የማጽናኛ ትምህርት÷ ሃይማኖታችንን አንክድም፤ ማዕተባችንን አንበጥስም በሚል የተሠዉ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ‹‹የተግባር መምህሮቻችን›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ አክለውም ክርስትና ‹‹የመከራ ሃይማኖት›› መኾኑን የተናገሩት መመህሩ ‹‹መከራ የበለጠ ሊያስተሳስረን ይገባል›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

Medlote Tsidik, Dn Yaregal New Bookሌላው የጥናት አቅራቢ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የኾኑት ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ሲኾኑ በነገረ ሃይማኖት እና በዕቅበተ እምነት ላይ በአተኮሩ የጽሑፍ ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስን እና የቀደምት አበው ሊቃውንት ትምህርትን ሚዛን በማድረግ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዓላውያን ለሚያሰራጩት የስሕተት ትምህርት ምላሽ የሰጡበትን በስድስት ክፍሎች እና በዐሥር ምዕራፎች የተቀመረ ባለ523 ገጾች መጽሐፋቸውን ‹‹መድሎተ ጽድቅ›› በሚል ርእስ በዚኹ በሚያዝያ ወር ፳፻፯ ዓ.ም. ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ቤተ እምነቶች በዋናነት የሚለያት የመዳን ትምህርቷ መኾኑን የሚገልጹት ዲያቆን ያረጋል፣ የክርስትና ሃይማኖት የመዳን ሃይማኖት በመኾኑ የመዳን ትምህርት ከትምህርቶች ኹሉ ዋናውና የመጀመሪያው መኾኑን በመጽሐፋቸው አበክረው ይገልጻሉ፡፡

በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መዳን ስንል የኃጢአት ደመወዝ ከኾነው ከሞትና ከቅጣት መዳን ብቻ፤ ወይም ከኩነኔ መዳንና ማምለጥ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ እጅግ ያለፈ ጥልቅ እና ኹለንተናዊ ነው፡፡ ከኃጢአት ቅጣት መዳናችን አንዱና የመጀመሪያው ደረጃ ብቻ ነው፡፡ ከኃጢአት ቅጣት ነጻ ከመኾን በላይ ግን የእግዚአብሔር የባሕርዩ መገለጫዎች የኾኑትን ነገሮች (ኃይላተ እግዚአብሔር) በጸጋ ገንዘብ ለማድረግ የማያቋርጥ ጉዞ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ሱታፌ አምላካዊ (theosis) ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡

በየጊዜው የሚያድግና የሚበለጽግ ሱታፌያዊ ሒደት እንጂ ቅጽበታዊ አይደለም፡፡ በጥምቀት የክርስቶስ አካል ኾኖ መሠራት የጀመረ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከፍጹምነት ወደ ፍጹምነት፣ ከቅድስና ወደ ቅድስና እየተሸጋገረ ወደ እግዚአብሔር የበለጠ እየቀረበና እየተዋሐደ የሚሔድበት መንፈሳዊ የዕድገት ጉዞ ነው፡፡ ስለዚኽ የሰዎች መዳን ስንል የሰው ባሕርይ መክበር እና የጸጋ አምላክ መኾንንም ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሰው የኾነው እኛ ሰዎች አምላክ እንኾን ዘንድ ነውና›› በማለት በተደጋጋሚ የሚገልጸው ይህን ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው፡፡ በአጠቃላይ በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መዳን በአንድ ቅጽበት ተፈጽሞ ከዚያ በኋላ ‹‹ድኛለኹ›› እያሉ የሚፎከርበት ሳይኾን ሐዋርያው ‹‹ስለዚኽ፣ ወዳጆች ሆይ፣ ኹል ጊዜ እንደ ታዘዛችኹ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችኹን መዳን ፈጽሙ››(ፊልጵ.፪÷፲፪) በማለት እንዳስተማረን በፈሪሃ እግዚአብሔር እና በተጋድሎ እስከ መጨረሻው በመጽናት የሚፈጸም ነው፡፡

‹‹መዳን በእምነት ብቻ››፣ ‹‹ክርስቲያናዊ መልካም ሥራ አያስፈልግም››፣ ‹‹ካመንን በኋላ ኃጢአት ሠርተን ብንገኝ እንኳ አንኰነንም››… የሚለውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የፈጠራ ትምህርት ከተቀረጸበት ነገረ እሳቤያዊ መሠረቱ (The doctrine of satisfaction) ጋራ በንጽጽራዊ ትንተና ያፈለሱት ጸሐፊው፣ አንድ ሰው ለመዳን በእምነት ላይ ኾኖ ክርስቲያናዊ መልካም ሥራ መሥራት እና መጋደል እንዳለበት፣ ተጋድሎው እና ክርስቲያናዊ ምግባሩም በእምነት የተቀበለውንና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በመሳተፍ የራሱ ያደረገውን የመዳን ጸጋ ጠብቆ እና አጽንቶ ወደ ሕይወት ለመግባት እንደሚያበቃው በስፋት አስረድተዋል፡፡

ሰው የሚድነው በእግዚአብሔር ቸርነት የተሰጠውን የመዳን ጸጋ በእምነት ሲቀበል፣ በመቀጠልም ይህን የመዳን ጸጋ በአማናዊ መንገድ የሚያገኝባቸውንና የራሱ የሚያደርግባቸውን ምስጢራት(ጥምቀት፣ ሜሮን፣ ቅዱስ ቁርባን) ሲፈጽም ነው፡፡ ከዚያም ይህን የተቀበለውን የመዳን ጸጋ ለመጠበቅና ወደ ሕይወት ለመግባት መጽናት እና መጋደል፣ እንደዚኹም ክርስቲያናዊ መልካም ሥራ መሥራት ይገባዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እና አበው ቀደምት ኹሉም ተባብረው እና ተስማምተው የሚነግሩን ይህን እውነተኛ የሕይወት መንገድ ነው እንጂ የራሳቸውን መንገድ ፈጥረው የሚጓዙት ተሐድሶዎች እንደሚሉት ‹‹መዳን በእምነት ብቻ ነው›› ብለው አይደለም፡፡ (ገጽ 215)

የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ኹል ጊዜ በመስቀል ላይ በመኾኑ ከብዙ ተጋድሎ ብዙዎችን ስትማርክ እንደኖረች ዲያቆን ያረጋል ነገረ ቅዱሳን – ፫ በተባለውና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ማስተማርያ በተዘጋጀው መጽሐፍ ያብራራሉ፡፡ የተጋድሎ መንገዱ ብዙ ነው፡፡ ስለ ሃይማኖት ሲያስተምሩ በዓላውያን መንገላታት፣ በሐሰተኞች መሠቃየት፣ በከሐድያን እጅ መሞት ተጋድሎ ነው፡፡ አጋንንትን፣ ነፍሳትን የሚወጉ እኵያት ፍትወታትን፣ ኃጣውዕን ለመቋቋም ወስኖ በጽናት መታገል ተጋድሎ ነው፡፡ በሰይፍ የተመተሩ፣ በመጋዝ የተተረተሩ፣ በእሳት የተቃጠሉ፣ ለአናብስት የተጣሉ በአጠቃላይ በብዙ ሥቃያት የተፈተኑ ቅዱሳን ሰማዕታት ይባላሉ፡፡ ሰማዕትነቱም በአፍም በመጽሐፍም፤ በቃልም በተግባርም በማመንና በመታመን ነው፡፡ ሮሜ ፲÷፱-፲፩፤ ፪ቆሮ.፬÷፲፫፤ ያዕ ፪÷፰-፳፮፡፡

ሰማዕትነት በጥንት ትርጉሙ ብዙኀኑ በተሰበሰቡበት ዐደባባይ በገሃድ ስለሚሰጠው ምስክርነት የቅርብ ዕውቀት፣ የዐይን ምስክርነት ያለውን ሰው ያመለክት ነበር፡፡ ‹‹አማን አማን እብለከ በዘነአምር ንነግር÷ ወበዘርኢነ ሰማዕተ ንከውን ወእምዐነሰ ተዐብዩነ ነሢአ = የምናውቀውን እንድናነገር÷ የአየነውንም እንድንመሰክር እውነት እውነት እልሃለኹ፤ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም፡፡››/ዮሐ.፫÷፲፩/ በዚኽም መሠረት ሰማዕት የሚለው መጠሪያ በመጀመሪያ ያመለክት የነበረው ቅዱሳን ሐዋርያት ብቻ ነበር፡፡ የሰማዕትነት መደበኞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፤ ጌታችንም ምስክሮቼ ብሏቸዋል፡፡ ‹‹አላ ሶበ ይወርድ ላዕሌክሙ መንፈስ ቅዱስ ትነስኡ ኃይለ÷ ወትከውኑኒ ሰማዕትየ÷ በኢየሩሳሌም ወበኵሉ ይሁዳ ወሰማርያ ወእስከ አጽናፈ ምድር = መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ችሎታ ታገኛላችኹ፤ በኢየሩሳሌም በይሁዳ በሰማርያ እስከ ምድር ዳርቻ ምስክሮቼ ትኾናላችኹ፡፡››/ግብ.ሐዋ.፩÷፫/

በኋላ ዘመን ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ›› /ማቴ.፲÷፳፰/ ብሎ የተናገረውን አምላካዊ ቃል መመሪያ በማድረግ በአላውያን ነገሥታት እና በመናፍቃን ጳጳሳት ፊት እሳቱንና ስለቱን ሳይፈሩ አንገታቸውን ለስለት፣ ጀርባቸውን ለግርፋት፣ እግራቸውን ለሰንሰለት ሰጥተው ስለ ክርስቶስ ሲሉ በግፍ የሞቱ ቅዱሳን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ዮሐ.፲፰÷፴፯፡፡

እግዚአብሔርም በእነርሱ ኃይሉን ገለጸ፡፡ በእርሱ ታምነው የተሰማሩ ያክል አንበሳ አሰግዶ፣ ነበልባል አብርዶ ተኣምሩን ለአሕዛብ ገለጸላቸው፡፡ ሌሎቹንም በሞታቸው እንዲመሰክሩ አደረጋቸው፡፡ የተቆረጠ ባሕር ዛፍ ከሥሩ ብዙ እንደሚያስገኝ አንድ ሰማዕት ሲሞት ሌሎች ብዙ ሰማዕታትን ያስገኝ ነበር፡፡ ይኸውም የሰማዕታቱን ሃይማኖታዊ ጀግንነት እያዩ ከገዳይ ወታደሮች ሳይቀር ‹‹እኔም በዚያ ሰው አምላክ አምኛለኹ›› እያሉ ወዲያው ሰማዕት ይኾኑ ነበር፡፡

ይህን የሰማዕታትን ተጋድሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲኽ ገልጾታል፡-

የአንበሶችን አፍ ዘጉ÷ የእሳትን ኃይል አጠፉ÷ ከሰይፍ ስለት አመለጡ÷ ከድካማቸው በረቱ… ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ÷ ሌሎችም መዘበቻ በመኾንና በመገረፍ ከዚኽም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ÷ ተፈተኑ፤ በመጋዝ ተሠነጠቁ÷ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ÷ ኹሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ÷ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ፡፡ /ዕብ.፲፩÷፳፭-፴፰/

አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየኹ፤ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ፡- ቅዱስ እና እውነተኛ ጌታ ሆይ÷ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም አሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው÷ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ÷ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው፡፡ /ራእይ፮÷፱-፲፩/

አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም፡፡ ወከዐዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት = ሰማዕታት የዚኽችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ፡፡ /ውዳሴ ማርያም ዘኀሙስ/

ሰማዕታት በደም እና ሰማዕታት ዘእንበለ ክዕወተ ደም(ያለደም መፍሰስ ሰማዕታት) አሉ፡፡ በዚኽ ላይ በመመሥረት ሰማዕትነትን በሦስት ከፍለው የሚያዩ አሉ፡፡ ይኸውም፡-

(፩) አረንጓዴ ሰማዕትነት፡- ውስጣዊ ፈተናን ማለትም ክፋትን፣ ምቀኝነትን፣ ኃጢአትን በዐቂበ ሕዋሳት እና በትጋሃ ሌሊት ለማስወገድ በጽኑ ጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በትኅርምት እና በንስሐ ሕይወት የሚደረግ የገዳማውያን ሰማዕታት ተጋድሎ ነው፡፡

(፪) ነጭ ሰማዕትነት፡- በአጭሩ መንኖ ጥሪት ማለት ነው፡፡ ይኸውም አፍዓዊ/ውጫዊ/ የኾኑ የፈተና ምንጮችን ለመቋቋም በዚኽ ዓለም ሀብትንና ንብረትን በመተው የሚደረገውን የመናንያን ሰማዕታት ተጋድሎ ያጠይቃል፡፡

(፫) ቀይ ሰማዕትነት፡- መስተጋድላን ሰማዕታት ስለ እውነት እና ስለ ክርስትና የአካል እና የአእምሮ ሥቃያትን መቀበላቸው በመጨረሻም የሕይወት መሥዋዕትነት መክፈላቸው ነው፡፡ የሰማዕትነት የመጨረሻ ደረጃ እና ዐይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ ሰውም ቅሉ ወደዚኽ ሊደርስ የሚችለው ውስጣዊ ፍትወቱን ታግሎ ሲያሸንፍ፣ አፍዓዊ ንብረቱን ንቆ ሲተው፣ በፈቃደ ሥጋው ፈቃደ ነፍሱን ሲያሠለጥን በአጠቃላይም ራሱን መግዛት ሲችል ነው፡፡

ደመ ሰማዕታት የክርስቲያኖች ዘር ነው፤ ዕረፍታቸውም እንደ ልደት ቀናቸው ነው፤ በዚያች ዕለት ለዘለዓለማዊ ሕይወት ተወልደዋልና፡፡ የደም ሰማዕትነት የአንድ ጊዜ ሲኾን መንኖ ጥሪት በየዕለቱ ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች አንጻር የሚፈጸም ነው፡፡

በአጠቃላይ ሰማዕትነት÷ በዘወትር ሕይወታችን ውስጥ ነው፤ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለቤዛ ዓለም በተደረገው የጌታችን መከራ፣ ሕማምና ሞት ውስጥ ያለን የማያቋርጥ ሱታፌ ነው፡፡ ሰማዕትነት ለዓለሙ ድኅነት የተሰቀለው፣ የሞተውና የተነሣው መድኃኔዓለም ክርስቶስ በእኛ ሕይወት ግልጥ ኾኖ የሚታይበት አነዋወር ነው፡፡ ‹‹ዓለም ቢጠላችኹ እኔን አስቀድሞ እንደጠላ ዕወቁ፡፡…እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኋል››/ዮሐ. ፲፭÷፲፰/ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ዘወትር የክርስቶስን ሞት በሥጋችን እንሸከማለን፤ የክርስቶስ ሕይወቱ በዚኽ ሟች ሰውነታችን ላይ ይታወቅ ዘንድ፤ በሕይወት የምንኖር እኛም እኮ ዘወትር ስለ ኢየሱስ ብለን ተላልፈን ለሞት እንሰጣለን፤ በመዋቲው ሰውነታችን ላይ የክርስቶስ ሕይወቱ ይታወቅ ዘንድ ነው›› ብሏል፡፡/፪ቆሮ.፬÷፲-፲፩/፤ ‹‹መጽሐፍ እንዳለ÷ አንተን ስለ አመን ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱም በጎች ኾነናል››/ሮሜ፰÷፴፮/ እንዳለ፡፡

ሰማዕትነት ከሰይጣን ጋራ የሚደረግ ፍጹም ተጋድሎ/supreme conflict/ ነው፤ ሰማዕትነት በጥንተ ሕይወት ለታጨንለት ክብር የምንወለድበት የዘላለም ሕይወት መግቢያ በር ነው፡፡ ሰማዕትነት ለክርስትና ከምሥረታውና መስፋፋቱ ጀምሮ ባጋጠሙት የተለያዩ መሰናክሎች ሳቢያ በደም እና እንበለ ደም በተደረጉ ተጋድሎዎች ሲፈጸም የኖረ፣ ዛሬም እንደመሰከርነው ኹሉ እስከ ዕለት ምጽዓትም የሚቀጥል የሱታፌአዊ ሒደቱ አካል ነው፡፡ ክርስትና ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ተነጥሎ ሊታይ የማይችል የየዕለት ሰማዕትነት እና በምድር ላይ ያለችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተጋድሎዋን በመፈጸም ላይ ያለች (church militant) ናትና፡፡

ምንጭ፡-

  • መድሎተ ጽድቅ (፳፻፯ ዓ.ም.)
  • ነገረ ቅዱሳን – ፫ (፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)
  • ፍኖተ ቅዱሳን (፲፱፻፺፫ ዓ.ም.)
Advertisements

2 thoughts on “በማኅበረ ቅዱሳን: ሰማዕትነት ለክርስትና በሚል ርእስ ነገ ውይይት ይካሔዳል

  1. Anonymous May 2, 2015 at 9:41 pm Reply

    You are interested in Unity as same time you are working for dis Unity ..Mahibere Qedusan?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: