የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋሙ: ጨቅላ ልጆቻችኹን አታቍርቡ እያለን ይኾን? ሥነ ምግብ እና ሥጋወደሙ ምን አገናኛቸው? የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርስ ምን ይላል?

stock-photo-23497940-last-supper-painting-in-ethiopian-monastery

ሐዲስ ኪዳን በምሴተ ኀሙስ

ጌታ መዋዕለ ትምህርቱን ማለት የሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሥራውን ጨርሶ የዕለተ ዓርቡን ተልእኮ የሚፈጽምበት ሰዓቱና ጊዜው ሲደርስ ምሥጢሩን ለሐዋርያት ገለጸላቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት አቆጣጠር አራተኛው የአይሁድ ፋሲካ ሲደርስ ጌታ ለሐዋርያቱ በመጀመሪያ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር በኋላም የሥጋውንና የደሙን ምሥጢር ገልጾላቸዋል፡፡ /ማቴ፲፫÷፲፩፤ ፲፬÷፳፪-፳፬፤ ዮሐ.፲፫÷፩/ ስለ ኃጢአታችን ስርየት በስቅለት ዓርብ ለዓለም ኹሉ መድኃኒት እንዲኾን በመስቀል ላይ ለአንዴ እና ለዘላለም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ሥጋውንና ደሙን ኹልጊዜ እንዲያገኙትና በእውነተኛ የሕይወት ምግብነት እንዲቀበሉት ሕግና ሥርዐት ሠርቶላቸዋል፡፡

እንደ አይሁድ ሰዓት አቆጣጠር በዕለተ ዓርብ የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ማለት በእኛ አቆጣጠር በስቅለት ዋዜማ በጸሎተ ኀሙስ ማታ ሥጋውን እውነተኛ ምግብ ደሙንም እውነተኛ መጠጥ አድርጎ ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚያች ምሽት የኦሪትን የእንስሳት መሥዋዕት÷ የአይሁድን የፋሲካ ራት ለመጨረሻ ጊዜ ፈጽሞ አማናዊውን፣ ድኅነትንና የዘላለም ሕይወትን ያገኘንበትን መሥዋዕት የራሱን ሥጋና ደም አቅርቦላቸዋል፡፡ ይህንንም ታላቅ ሥራ ያከናወነው ኅብስቱን አንሥቶ ባርኮ ቆርሶ፣ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው ብሉ፤ ጽዋውንም እንደዚኹ አንሥቶ ባርኮ ይህ በመስቀል ላይ ለኃጢአት ስርየት የሚፈሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ ኹላችኁም ከዚኽ ጠጡ ባላቸው ጊዜ ነበር፡፡››/ማቴ.፳፮÷፲፱-፳፤ ፩ቆሮ.፲፩÷፳፫-፳፭/

ሐዋርያትም ‹‹መታሰቢያዬን እንደዚኽ አድርጉ›› ብሎ ስለ አዘዛቸውና ከክርስቶስ የተቀበሉትን ትእዛዝ ለቤተ ክርስቲያን በመስጠታቸው ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን፣ ዳግም ምጽአቱን በልብዋ እያሰበች፣ በአፍዋ እየመሰከረች በሐዲስ ኪዳን ለሐዲስ ሥርዐት የተሰጠውን የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሠርየውን ሥጋ ወልደ እግዚአብሔርን ደመ ወልደ እግዚአብሔርን ስትቀበል ስታቀብል ኖራለች፤ ትኖራለች፡፡ ስለዚኽ ዛሬ ከቤተ ክርስቲያን በአርኣያ ኅብስት የምንቀበለው የክርስቶስ ሥጋ÷ በአርኣያ ወይን የምንቀበለው የክርስቶስ ደም መኾኑን አምነን የመዳናችን ምሥጢር የሚፈጸምበትን አምላካዊ ጸጋ እናገኛለን፡፡

ጸጋ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በሚታይና በሚዳሰስ በሥጋ ሰውነቱ በመምጣቱ ነው፡፡ በሰውነቱ ሕማማትን በመቀበል፣ እኛን በማጽደቅ፣ በቅዱስ ደሙ ፈሳሽነት ከኃጢአታችን በማንጻትና ከእግዚአብሔርም በማስታረቅ በጸጋ ላይ ጸጋ እንድንቀበል አብቅቶናል፡፡ በሚታይና በሚዳሰስ ሰውነቱ የማይታየውን መለኰታዊ ጸጋውን እንዳጎናጸፈን እናስተውል፡፡ እንዲኹም ዛሬ አካሉ በኾነችው ቤተ ክርስቲያን አማካይነት በሚታዩና በሚዳሰሱ ምሥጢራቱ የማይታየውን ረቂቁን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን፡፡ ስለዚኽም ክርስቶስ ሰው ኾኖ ሥጋ ከመልበሱ የተነሣ ጸጋ እግዚአብሔር በሥጋውና በደሙ እንደመጣልን እንረዳለን፡፡

እንግዲኽ ብዙዎቹን ያስጨንቅ የነበረው ከሰማይ የወረደው የሕይወት እንጀራ ምሥጢር በጸሎተ ኀሙስ ማታ በተፈጸመው በቅዱስ ቊርባን ሥርዐት በእምነት ለጸኑት ለዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት ብቻ እንዲታወቅ ኾነ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዕለተ ዓርቡ የማዳን ሥራ በሥጋውና በደሙ ምሥጢር በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ /የሐዋ. ሥራ ፪÷፵፪/ ምእመናንም ንስሐ እየገቡ በመንፈሳዊ ዕውቀት የሚያድጉበትንና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሚበለጽጉበትን የጌታን ሥጋ እየበሉ ደሙን እየጠጡ እንደ ወንጌሉ ቃል የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ፡፡

በሳይንሱ እንደሚነገረው፣ ቤተ ክርስቲያናችንም የምታስተምረው የእናት ጡት ፍጹም ምግብ ነው፡፡ እግዚአብሔር በእናት በኩል ያዘጋጀው ለሕፃኑ ኹለንተናዊ ምግብ ኾኖ የተሰጠው መኾኑን ታምናለች፡፡ እንዲያውም በዘመኑ ጡት አስጥለው ጡጦ ለማስለመድ ሲጥሩ ቤተ ክርስቲያን በትውፊታዊ ትምህርቷ÷ ‹‹መዋዕለ ጥብዕ ሦስት ዓመት ነው፤ ሦስት ዓመት አጥቡ ብላ›› ነው የምታስተምረው፡፡ ይህም ኾኖ የእናቱን ጡት ስድስት ወር የጠባ ሕፃን ጨርሶ አይታመምም የሚል ሳይንስም ሃይማኖትም የለም፤ ሕፃኑ የለበሰው ሥጋ ነውና በተለያዩ ምክንያቶች ይታመማል፤ በብዙ በሽታ እንዳይጠቃ እንጂ በምንም በሽታ እንዳይጠቃ አይደለም፡፡

እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት ብቻ ይመገብ የሚለውስ ምን ያኽል ተግባራዊነት አለው? ከወሊድ በኋላ የኹለት ወራት ዕረፍት ብቻ የሚሰጣት በሥራ ላይ ያለች እናት በሦስት ወራት ውስጥ የቆርቆሮ ወተት ታስጀምረዋለች ወይም ሌላ አማራጭ ትሻለች እንጂ ለስድስት ወራት ጡቷን ብቻ ልትመግበው እንዴት ትችላለች? ሕፃኑ እስከ ስድስት ወር ቢያመው መርፌ አይወጋም ወይ? ክኒን ተፈጭቶ አይጠጣም ወይ? ሐኪም ያዘዘው መድኃኒት የአመጋገቡን ሥርዓት አያፈርስም ከተባለ በአምላክ የታዘዘው ሥጋ ወደሙን ሲቀበል ያፈርሰዋል ማለት ጣልቃ ገብነት አይኾንም ወይ? ኦርቶዶክሳውያን ለጋ ሕፃናት ሥጋወደሙን በመቀበላቸው ሳቢያ ከማይቀበሉት ሕፃናት በተለየ ለጤና እክል የተጋለጡበት ጥናታዊ ማስረጃስ አለ ወይ? እንዲያውም ጨቅላ ልጆቻቸው የታመሙባቸውና ሥጋወደሙ መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ መኾኑን የሚያምኑት እናቶቻችን ‹‹ቆርቦ ተሻለው›› በማለት አቊርበው ድነውላቸው ይመሰክራሉ፡፡

ከኹሉ በፊት የአዳም ዘር ኹሉ መንግሥተ እግዚአብሔርን ይወርስ ዘንድ መንፈሳዊ አምኃ ኾኖ የተሰጠውን የአምላክ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም÷ ‹‹ተጨማሪ›› ወይም ‹‹ምግብ›› ብሎ መጥራት፣ እንደ ምግበ ሥጋ መቁጠር እርግማን ነው፤ በቤተ ክርስቲያናችንም የተወገዘ ነው፡፡ ሐሳቡ ከየትም ይምጣ ከየት፣ የማንም ይኹን የማን ፍጹም የኾነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ በኅቡእ እና በቂ ባልኾነ ምክንያት ለመምታት መቃጣት ነው፡፡ ምእመናንን ከመሠረተ እምነታቸው፣ ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለማራቅ የተወጠነ ሤራ ነው፤ ምክንያቱም በሃይማኖተኝነት ዐይን ብቻ መታየት ያለበት ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ዘላለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ምሥጢራዊ ጸጋ እንጂ አጥኚዎች እንደሚሉት ‹‹ምግብ›› ወይም ‹‹ተጨማሪ›› ከሚባሉት ነገሮች ጋራ ለመነጻጸር የሰማይና የምድር ያኽል ከዚያም የላቀ ርቀት ያለው ነውና!!

በአጠቃላይ ያለቅዱስ ሥጋው ያለክቡር ደሙ ልጆች አደጉ ማለት እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና አቋም ባይወለዱ ይሻል ነበር፡፡ ይሁዳም ይህን ቅዱስ ሥጋ በማቃለሉ ነው ‹‹ባይወለድ፣ በእናቱ ማሕፀን ውኃ ኾኖ በቀረ የተሻለ ነበር›› የተባለው፡፡ ከቅዱስ ሥጋው ከክቡር ደሙ ሌላ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሕይወት የለንም፡፡ መዳናችን በጌታ ሥጋ ነው፤ ምክንያቱም ይህ አካላዊ ቃልን የተዋሐደ ሥጋ ነው የኃጢአታችንን የሞት ቅጣት የወሰደው፡፡ ይህ የጌታ ሥጋ ነው ሞትን ሽሮ ከመቃብር የተነሣው፡፡ ታዲያ ከዚኽ ከመለኰታዊ ሥጋ ጋራ አንድነት ከሌለን አንድንም!! ስለዚኽ በጥምቀት ከጌታ ጋራ አንድ ኾነናል፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልም የሞቱና የትንሣኤው ተካፋይ ለመኾን እንድንችል ተፈቅዶልናል፡፡ እንደዚኹም በቅዱስ ቊርባን ከእርሱ ጋራ አንድነታችንን በማጽናት ሕይወትንና ትንሣኤ ዘለክብርን በማግኘት ከእርሱ ጋራ እንኖራለን፡፡

የሕፃናትን የሕመምና የሞት መጠን ከሥነ ምግብ አንጻር ሲመረምሩ፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያኑን ማገናዘብ አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘ ተቀባይነት የሚኖረው የተግባቦት መንገድ፣ የሚመለከታቸውን አባቶች በተገቢው መድረክ ጠርቶ ማወያየት እንጂ ቀጥታ በመረጃ መሰብሰቢያ መጠይቅ ውስጥ አካትቶ ለመረጃ ሰብሳቢዎች ሥልጠና መስጠት ሊኾን አይገባውም ነበር፡፡ ይልቁንም ይህ ዓይነቱ አካሔድ ኦርቶዶክሳውያን ባለሞያዎቹ በውል እንደገለጹት÷ የሃይማኖት ነጻነትን መጋፋት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ እና የምእመኑን የእምነት ሕይወት ለማጥፋትና ለመደምሰስ መቃጣት ነው፤ በሳይንሳዊነት ስም የእምነታችንን አክሊልና ፍጻሜ መናቅ፣ ሕዝባዊ ሓላፊነትን ለመወጣት በአግባቡ አለማሰብ እና አለመጠንቀቅ ከመኾኑም በላይ ለባዕዳን አስተሳሰብም አሳልፎ የሚሰጥ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ላይ ሃይማኖታዊ እና ርእዮታዊ ጥላቻ ያላቸውና በዓላማ የተሰለፉ የማያምኑ ኃይሎች ነገ ከነገ ወዲያ ማንኛውንም አጋጣሚ ተጠቅመው ከዚኽም በላይ ሊያስቡ፣ ሊናገሩ፣ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ አዲሱን ትውልድ ለመውረስ እና ሃይማኖተኝነትን ለማጥፋት እንዲኽ ያሉ ብዙ መስኮቶችን መክፈት ስለሚያስፈልጋቸው ይኽን ቢያደርጉ አይደንቅምና ምእመናን አባቶችና እናቶች በአግባቡ ነቅተውና ተግተው ሊከላከሉ ይገባል፡፡

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፭ ቁጥር ፯፻፺፬፤ ቅዳሜ መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

ከውልደታቸው እስከ ስድስት ወራት ዕድሜአቸው ድረስ ያሉ የአገሪቱ ሕፃናት፣ ከእናቶቻቸው ጡት ወተት ውጭ ተጨማሪ ነገር ስለመውሰዳቸው የዳሰሳ ጥናት ለማካሔድ በሚል ለመረጃ ሰብሳቢዎች የተሰጠው ሥልጠና፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሕፃናት ከሚፈጸመው ሥርዐተ ቊርባን አኳያ የሥነ ምግብ ባለሞያዎችን ማከራከሩ ተገለጸ፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ዲፓርትመንት ባለፈው የካቲት ወር፣ የሕፃናት ጥቃቅን ንጥረ ምግብ(micro nutrients) እና ተያያዥ የጤና ችግሮችን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚሰበሰቡ መረጃዎች ለሦስት ሳምንት የዘለቀ ሥልጠና በሰጠበት ወቅት፣ ‹አንድ ሕፃን እስከ ስድስት ወር ዕድሜው ድረስ ሥጋወደሙን ወይም ቁርባን ከተቀበለ የእናቱን ጡት ወተት ብቻ እንደተመገበ (exclusive breast feeding) አንቆጥረውም፤ እንደ ተጨማሪ ምግብ ነው የምናየው፤›› በሚል በጥናቱ አስተባባሪ የተነሣው ሐሳብ ብዙዎቹን አጥኚዎች ክፉኛ እንዳከራከረ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ይናገራሉ፡፡

አንድ ሕፃን ከልደቱ እስከ ስድስት ወር ድረስ መመገብ ያለበት በበቂ ንጥረ ነገሮች የበለጸገውንና በተስማሚነቱ መተኪያ የሌለውን የእናት ጡት ብቻ እንደኾነ በሕክምና ሳይንሱ ይመከራል፤ ይህም ተጨማሪ ምግብና ፈሳሽ ለመውሰድ የሕፃኑ ጨጓራና አንጀት ዝግጁ ባለመኾኑና ለጤና እክልም እንዳይጋለጥ በሚል እንደኾነ የሚያስረዱት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ተከታይ ባለሞያዎቹ፣ በሥርዓተ እምነታቸው ዕድሜ እና ጾታ ሳይለይ የአምላክ አማናዊ ሥጋ እና አማናዊ ደም እንደኾነ አምነው የሚቀበሉት ቅዱስ ቊርባን፤ ‹‹ተጨማሪ›› በሚል በሚሰበሰበው መረጃ ለማካተት መታሰቡንና ከሥነ ምግብ አንጻር መታየቱን በጥብቅ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡

በሕክምናው ስድስት ወራት ያልሞላቸው ሕፃናት ሲታመሙ ሽሮፕ ወይም ክኒን እንዲሟሟ ተደርጎ ለተወሰነ ጊዜ መድኃኒት እንደሚሰጣቸውና ይህም ለመዋዕለ ዘመናቸው የተወሰነውን የእናት ጡት ወተት ብቻ የመመገብ ሥርዓት ያፈርሰው እንደኾነ ለአስተባባሪው ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ባለሞያዎቹ፣ ‹‹በሐኪም ትእዛዝ ከኾነ ችግር የለውም፤ ሥርዐተ ምግቡን አያፈርሰውም ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ቁርባን ከወሰደ ግን ያፈርሰዋል›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ይህም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚታመንበት የሥርዐተ አመጋገቡ መግለጫ እንደኾነ ተነግሮናል የሚሉት ባለሞያዎቹ፣ ከሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ አካላት ለማረጋገጥ ሲጠይቁ ግን ‹‹በዚኽ ጉዳይ መልስ መስጠት አልፈልግም›› እንደተባሉ ተናግረዋል፡፡

DEC29-ETHIOPIAN-ORTHODOX-CHURCH-06_17205218

ቅርንጫፍ ከግንዱ እስካልተለየ ድረስ ልምላሜ፣ ጽጌ እና ፍሬ ሕይወት ዘለዓለም እንዲኖረው ኹሉ ክርስቲያኖችም ጒንደ ሐረገ ወይን ከኾነው ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አለመለየታችንና በሕይወት መኖራችንን ቅዱስ ቁርባን ስንቀበል እናረጋግጣለን፤ ሕያው የሚያደርገንም በውስጣችን የተዋሐደው ሥጋ ክርስቶስ እና ደመ ክርስቶስ ነው፡፡ያለቅዱስ ሥጋው ያለክቡር ደሙ ልጆች አደጉ ማለት እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና አቋም ባይወለዱ ይሻል ነበር፡፡ ይሁዳም ይህን ቅዱስ ሥጋ በማቃለሉ ነው ‹‹ባይወለድ፣ በእናቱ ማሕፀን ውኃ ኾኖ በቀረ የተሻለ ነበር›› የተባለው፡፡ ከቅዱስ ሥጋው ከክቡር ደሙ ሌላ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሕይወት የለንም፡፡

ኢትዮጵያ በሕፃናት ጤና አጠባበቅ ከአህጉሩ በቀዳሚነት ለምትጠቀስበት ስኬቷ፣ በሥርዓተ ሃይማኖቱ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሕፃናት የሚፈጸመው ቊርባን ዕንቅፋት ይኾናል ብለው እንደማያምኑ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡ በእምነቱ የተቀደሰ ትውፊት ከስድስት ወራት በፊት ያሉ ሕፃናትንም ቢኾን ማቁረብ ለመንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ዕድገታቸው የመጨነቅ የጥሩ እናትነት ምልክት መኾኑን የሚያስረዱት ባለሞያዎቹ፣ በብዙ ሚልዮን የሚገመቱት ክርስቲያን ሕፃናት እስከ ስድስት ወራቸው ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ የማይመገቡበት አንዱ ምክንያት ‹‹ስለሚቆርቡ ነው›› የሚል ድምዳሜ በዳሰሳ ጥናቱ እንደ አንድ ነጥብ ቢቀመጥ ለአገር የሚያሰጠው ገጽታ ከወዲኹ መጤን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሥርዓተ ቊርባን፣ ሕፃናት በተወለዱ ከ40 እና ከ80 ቀናቸው ጀምሮ የሚቀበሉትና ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን አንድነት የሚያረጋግጡበት የእምነታቸው አክሊልና ፍጻሜ ነው ያሉት ባለሞያዎቹ፣ ከስድስት ወራት በፊት ያሉ ሕፃናትን አመጋገብ ያፈርሳል የሚለው የጥናቱ ውጤት በሒደት የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት መርሐ ግብር አካል ተደርጎ ሊሠራበት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡ ይህም የሃይማኖት ነጻነትን የሚጋፋ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ የምእመናኑን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያጠፋና የሚደመስስ፣ እንዲኹም ለባዕድ አስተሳሰብም አሳልፎ የሚሰጥ በመኾኑ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረውና በጽኑ እንደሚያወግዙት ገልጸዋል፡፡

‹‹መረጃውን ለእናንተ ከነገሯችኹ ሰዎች በላይ ለምንሠራው ሥራ ሓላፊነት ይሰማናል›› ያሉት በኢንስቲትዩቱ የሥነ ምግብ ዲፓርትመንት የሥልጠናው አስተባባሪ ለአዲስ አድማስ በስልክ እንደተናገሩት፣ ጥናቱ የተወሰነ ሃይማኖትን የሚመለከት አይደለም፤ ዓላማውም ምን ያኽል ሕፃናት እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻ ወስደዋል የሚለውን ለማወቅ ብቻ በመኾኑ ከሃይማኖት ጋራ የሚያያዝ ትንታኔ የሚሰጠበት አይደለም፡፡

‹‹ለሕፃኑ ከውልደቱ ጀምሮ እስከ ስድስት ወሩ ድረስ ከእናት ጡት ውጭ የተሰጠው ማንኛውም ነገር አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ‹‹በሃይማኖት ሥርዓትም ቢኾን›› በመረጃ ሰብሳቢዎቹ መጠየቅ እንዳለበት በሥልጠናው ላይ በአጽንዖት መነገሩን የሚጠቁሙት አስተባባሪው፤ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ለሕፃናት ከሚፈጸመው ቁርባን ከተሳታፊዎች ጥያቄ መነሣቱን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹በሃይማኖት ሥርዓትም ቢኾን ብለን ጥያቄ ስንጠይቅ ኦርቶዶክስ ሊኾን ይችላል፤ ሙስሊም ሊኾን ይችላል፤ ባዕድ አምልኮ የሚከተል ሊኾን ይችላል፤ እኛ እርሱ አይደለም የሚያሳስበን፤ በሃይማኖታዊ ሥርዓትኮ ሥጋወደሙ ብቻ አይደለም፤ ልጆች ሲታመሙ ጠበልም ምንም በተከታታይ አብዝቶ ይሰጣል፤ ይህም ኾኖ ወላጆች የእናት ጡት ብቻ ነው የመገብነው ይላሉ፤ ጤና አዳም ውኃ ውስጥ አድርገው ይሰጡና ምንም አልሰጠንም ይላሉ፡፡ በዚኽ ኹኔታ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው ሕፃናት ይኖራሉ፤ ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ነገሩ ተገቢው ግምት ስለማይሰጠው በየትኛውም ሃይማኖት የሰጣችኹት ነገር አለ ወይ? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄው እንዲኽ ያሉ ነገሮችን ለማስተካከል ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱ የሕፃናት ሕመምና ሞት መጠንን ማሻሻል ብትችልም የሚፈለገውን ያኽል መሔድ አልተቻለም፡፡ ስለዚኽ በሃይማኖታዊ ሥርዓትስ የሰጣችኹት ነገር የለም ወይ? ምን? የሚል ጥያቄ በመጠይቁ ተካትቷል፤›› ሲሉ አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡

*             *            *

ethipoian-crucifixion-painting

ቅዱስ ቊርባን÷ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ኹሉ የበላያቸው፣ መክብባቸውና መፈጸሚያቸው ነው ስንል፣ ጌታ የሰውን ልጆች ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ቅዱስ ሥጋውን በመቁረስ ክቡር ደሙን በማፍሰስ ካሳ የከፈለበትን፣ የማዳን ሥራውን የፈጸመበትን ኹኔታ የሚያረጋግጥና የሚመሰክር ከመኾኑ ጋራ አማኞች ከሥጋውና ከደሙ ተካፋይ እንዲኾኑ በማብቃት የሕይወትን ጸጋ እንዲቀበሉ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ሌሎች ምሥጢራትም የምሥጢራቸውን ትርጉም እና ፍጻሜ የሚያገኙት በቅዱስ ቊርባን አማካይነት ነው፡፡

የምሥጢረ ቊርባን ትርጉም

ቊርባን ቃሉ የሱርስት እና የግሪክ ሲኾን ትርጉሙ መንፈሳዊ አምኃ(ስጦታ)፣ መሥዋዕት፣ መባዕ ማለት ነው፡፡ ግብጾች ኤውክሪስት ይሉታል፡፡ ቃሉ የግሪክ ሲኾን ትርጓሜው ምስጋና ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ከዚኽ በተጨማሪ የጌታ ራት፤ ምሥጢራዊው ራት፤ አንድ የመኾን ምሥጢር እያሉ ይጠሩታል፡፡ ቅዱስ ቊርባን ስንል ግን ስለ አማናዊው ስጦታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ማመልከታችን ነው፡፡ ይህም ምሥጢረ ቊርባን በመባል ይታወቃል፡፡

የቅዱስ ቊርባን መሥራቹ ራሱ ባለቤቱ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲኾን በስቅለቱ ዋዜማ በዕለተ ኀሙስ ምሽት ታላቁን ስጦታውን ለሰው ልጆች ሰጥቷል፡፡ መሥዋዕተ ኦሪት አልፎ መሥዋዕተ ሐዲስ በመተካት ምሥጢረ ቊርባን በምሴተ ኀሙስ በጌታችን አማካይነት ተመሥርቷል፡፡ ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችኁ ብሉ÷ ይህ ሥጋዬ ነው፡፡ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው÷ እንዲኽም አለ፡- ኹላችኁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው አለ፡፡››/ማቴ.፳፮÷ ፳፮ – ፳፱/ ይህም መሥዋዕተ ወንጌል ይባላል፡፡

በጌታ ትእዛዝ በስቅለት ዓርብ ዋዜማ በጸሎተ ኀሙስ ማታ የተመሠረተው ቅዱስ ቊርባን፣ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ኹሉ የበላያቸው፣ መክብባቸውና መፈጸሚያቸው ነው፡፡ ይኸውም ጌታ የሰውን ልጆች ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ቅዱስ ሥጋውን በመቁረስ ክቡር ደሙን በማፍሰስ ካሳ የከፈለበትን፣ የማዳን ሥራውን የፈጸመበትን ኹኔታ የሚያረጋግጥ እና የሚመሰክር ከመኾኑ ጋራ አማኞች ከሥጋውና ከደሙ ተካፋይ እንዲኾኑ በማብቃት የሕይወትን ጸጋ እንዲቀበሉ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚኽም ሌሎች ምሥጢራት በቅዱስ ቊርባን አማካይነት የምሥጢራቸውን ትርጉም እና ፍጻሜ ያገኛሉ፡፡ ምሥጢረ ቊርባን የሚከናወንበት ጸሎተ ቅዳሴ እጅግ የከበረና ለክርስቲያኖች ኹሉ ጸጋና በረከትን የሚያሰጥ ነው፡፡

ጌታችን ሥርዐተ ቊርባንን ካቋቋመበት ከስቅለት ዓርብ ዋዜማ ከምሴተ ኀሙስ በፊት ኹለት ዓመት ያኽል ቀደም ብሎ ከሰማይ ስለወረደው የሕይወት እንጀራ÷ ስለ ቅዱስ ሥጋው እና ስለ ክብር ደሙ ምሥጢር ጌታ በሰፊው ለሕዝቡ አስተምሯል፡፡ ይህም በወንጌለ ዮሐንስ ምዕራፍ ስድስት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ጌታችን በትምህርቱ ከሰማይ የወረደው የሕይወት እንጀራ እርሱ ራሱ እንደኾነና እርሱንም ካመኑት እርሱ ከሚሰጣቸው የሕይወት እንጀራ ከበሉ እንደማይራቡና እንደማይጠሙ በወቅቱ ለተገኙት አይሁድ አስተምሯቸዋል፡፡ አይሁድ ምግበ ነፍስን ትተው ምግበ ሥጋን ብቻ እንደሚፈልጉ ገና ከመጀመሪያው ያውቅ ነበርና ለነፍሳቸውና ለዘላለማዊ ሕይወታቸው የሚያገኙበትን መንገድ በግልጽ ነግሯቸዋል፡፡

ይኸውም በመጀመሪያ የእርሱን ማንነት ዐውቆ ማመንና ለቃሉም መታዘዝ፣ ከዚያም የዘላለም ሕይወት የሚሰጠውን እንጀራ አምኖ መቀበል ነበር፡፡ እነርሱ ግን ‹‹ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ›› እንጂ አልተቀበሉትም፡፡ ጌታም በተከራካሪዎቹና በተቃዋሚዎቹ መካከል ትምህርቱን በማጠናከር ‹‹የሕይወት እንጀራ›› የተባለው ምን እንደኾነ በስውር /በምሳሌ/ ሳይኾን በግልጽ እየደጋገመ አስረድቷቸዋል – ‹‹እኔም ክርስቶስ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡…የወልደ እጓለ እመ ሕያው ክርስቶስን ሥጋ ካልበላችኹ ደሙንም ካልጠጣችኹ በራሳችኹ ሕይወት የላችኹም፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለኹ፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለኹ፡፡ ሕያው አብ እንደላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምኾን እንዲኹ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይኾናል፡፡ ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችኹ መና በልተው እንደሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል፡፡››/ዮሐ.፮ ÷ ፶፩ – ፶፰/ በማለት የተቀደሰውን ምሥጢር በማያሻማ ቋንቋ ገልጾላቸዋል፡፡

የቅዱስ ቊርባን አፈጻጸም ሥርዐት

ለመሥዋዕት የሚኾነው ኅብስት የሚዘጋጀው በወራቱ ከደረሰ፣ ዋግ(የሰብል በሽታ) ካልመታው እንክርዳድ ከሌለበት(ተረለቀመ) ንጹሕ ስንዴ ነው፡፡/ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፫ ረስጠጅ ፫/ ኅብስቱም ሲዘጋጅ ነቅዕ የሌለበት፣ ያላረረ፣ ያልጠቆረ መኾን ይኖርበታል፡፡ በምሴተ ኀሙስ ለሐዋርያት የሰጣቸው ለበረከት ከመጣለት ኅብስት ያላረረውን፣ ያልጠቆረውን፣ ነቅዕ ነውር የሌለበትን አንሥቶ ነውና፡፡

ለመሥዋዕት የሚገባው ወይን፣ ወፍ ያልመጠጠው አይጥ ያልቆረጠመው መጀመሪያ የደረሰው ወይን ሊኾን ይገባል፡፡ ወይኑን ሲሠሩ ጥሩ መኾኑን ተመልክቶ መሥራት ይገባል፡፡ ንጹሕ ጽሩይ ካልኾነ ለመሥዋዕት አይገባም፡፡ ዓመት ያለፈውና መዓዛው የለወጠ ወይን ለመሥዋዕት ሊቀርብ አይገባም፡፡/ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፫ ረስጠጅ ፫፤ በስ.102/

መሥዋዕቱ የሚዘጋጀው በቤተ ክርስቲያን ቅጽር(አጥር) ውስጥ በስተምሥራቅ በኩል(ችግር ካልኾነ በሌላ አቅጣጫ አይሠራም) በሚገኘው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህም ቤት ቤተ ልሔም ይባላል፡፡ ይህም ጌታችን በተወለደባት ከተማ ስም የተሰየመ ሲኾን ቤተ መቅደሱ ደግሞ አምሳለ ቀራንዮ ነው፤ ምክንያቱም ጌታችን የማዳን ሥራውን ከቤተ ልሔም ጀምሮ በቀራንዮ ዐደባባይ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ‹‹ተፈጸመ›› ብሏልና ነው፡፡

በካህኑ በኩል ለቅዱስ ቊርባን ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች ውስጥ÷ ካህን በሚቀድስበት ቀን ዕንቅፋት ቢያገኘው ማለት ነስር፣ ትውኪያ/አንቃር/፣ ብስና፣ ማንኛውም የአካል መድማት መቁሰል፣ ወደ አፍ የሚገባ እንደ ትንኝ ዝምብ ይህን የመሰለው ኹሉ ቢያጋጥመው በዚያው ዕለት መቀደስ፣ መቊረብ አይገባውም፡፡ ይህም ለካህን ብቻ ሳይኾን ምእመንንም የሚመለከት ነው፡፡ ካህን በሥርዐተ ቅዳሴው መጀመሪያና በፍሬ ቅዳሴ መጀመሪያ ኹለት ጊዜ እጁን ይታጠባል፡፡ እንዲኹም ሌሎች ካህናትና ዲያቆናት ከቊርባን አስቀድሞ እጃቸውን ይታጠባሉ፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት የሃይማኖታቸው ጽናት የሚደነቀው ኅብስቱን ‹‹ሥጋዬ ነው›› ወይኑን እያዩት ‹‹ደሜ ነው›› ቢላቸው የሚሳነው ነገር እንደሌለና በግብር አምላካዊ አማናዊ ሥጋ እና አማናዊ ደም እንደሚኾን ያለጥርጥር መቀበላቸው ነው፡፡ ‹‹ለመታሰቢያ አድርጉት›› መባሉ አማናዊነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሳይኾን ቅዱስ ቊርባን ለመቀበል ዘወትር በተሰበሰብን ጊዜ ሞቱን፣ ግርፋቱን፣ ትንሣኤውን እና ዕርገቱን እንዲያስታውሱ ለማሳሰብ ነው፡፡ መታሰቢያ ብቻ ቢኾን ኖሮ ‹‹ሳይገባው የተቀበለ ኹሉ ዕዳ አለበት›› ባልተባለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቊርባን÷ የጌታን የሐዋርያትን፣ ከዚያም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያቆዩትን ሥርዐት መሠረት በማድረግ ይፈጸማል፡፡

ሥርዐተ ቅዱስ ቊርባን

ቅዱስ ቊርባንን ካህናት፣ ሕፃናት፣ ደናግል፣ ሕዝባውያንና ምእመናን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሠራችላቸውን ቅደም ተከተል ጠብቀው ይቆርባሉ፡፡ ሥጋውን ቄሱ በእጁ ሲያቀብል፣ ደሙን ንፍቅ ቄሱ በዕርፈ መስቀል ለካህናት እንዲኹም ዲያቆኑ ለምእመናን በዕርፈ መስቀል ያቀብላል፡፡ ንፍቅ ቄስ ሥጋውን አያቀብልም፡፡ ንፍቅ ዲያቆንም ደሙን ለማቀበል አይችልም፡፡ የአቆራረብ ቅደም ተከተላቸውም፡-
በቅድሚያ መቅደስ ውስጥ በየማዕርጋቸው የሚቀበሉ፤
ሀ) ሊቃነ ጳጳሳት
ለ) ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት
ሐ) ቆሞሳት
መ) ቀሳውስት
ሠ) ዲያቆናት ናቸው፡፡
ዲያቆናት በመቅደስ ይቆርባሉ፡፡
ረ) ከንፍቅ ዲያቆናት ጀምሮ ኹሉም በየማዕርጋቸው በቆሙበት በቅድስት ይቀበላሉ፡፡
ሰ) ከበር ከፋቾች(ከዐጸውተ ኅዋኅው) በኋላ በዕለቱ ክርስትና የተነሡ ይቀበላሉ፡፡ ከእነርሱም በኋላ ቅድሚያ የሚሰጠው ለ40 እና ለ80 ቀን ሕፃናት ሲኾን ለመውሰድ በሚችሉበት መጠን ይቀበላሉ፡፡
ሸ) ከሕፃናት ቀጥሎ ደናግል
ቀ) የቀሳውስት ሚስቶች
በ) የዲያቆናት ሚስቶች
ተ) መነኰሳት ምእመናን
ቸ) መነኰዪያት
ነ). ምእመናን ወንዶች እና ሴቶች ተራቸውን ጠብቀው በየማዕርጋቸው ይቆርባሉ፡፡

ከካህናት ቀጥሎ አዲስ የተጠመቁ ሕፃናት እንዲቆርቡ የተደረገበት ምክንያት፣ ጌታ የተወለደ ዕለት በመጀመሪያ ያመሰገኑ መላእክት ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የእነርሱን ዜና ሰምተው ኖሎት/እረኞች/ ናቸው፡፡ ቊርባን ለተቀበሉ ከሐዳፌ ነፍስ በኋላ ማየ መቊረር/የቅዳሴ ጠበል/ ይሰጣል፡፡/ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ ፲፫፣ ረስጣ ፷፭/

በቅዱስ ቊርባን የሚገኝ ጸጋ

ቅርንጫፍ ከግንዱ እስካልተለየ ድረስ ልምላሜ፣ ጽጌ እና ፍሬ ሕይወት ዘለዓለም እንዲኖረው ኹሉ ክርስቲያኖችም ጒንደ ሐረገ ወይን ከኾነው ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አለመለየታችንና በሕይወት መኖራችንን ቅዱስ ቁርባን ስንቀበል እናረጋግጣለን፤ ሕያው የሚያደርገንም በውስጣችን የተዋሐደው ሥጋ ክርስቶስ እና ደመ ክርስቶስ ነው፡፡ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል የምናገኘው በረከት እና ጸጋ ስፍር ቁጥር ባይኖረውም በዋናነት ግን፡-

 • የዘለዓለም ሕይወትን ያሰጠናል/ዮሐ.፮÷፶፫ – ፶፮፤ ሮሜ፲፩÷፳፩-፳፬/
 • ስርየተ ኃጢአትን ያስገኝልናል/ማቴ.፳፮÷፳፯/ 
 • የኃጢአት ልጓም ኾኖ ያገለግለናል፤ ለጽድቅ ያተጋናል/ዮሐ.፮÷፴፭፤፶፭/

ምንጭ፡-

 • ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን 
 • ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
 • ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት
Advertisements

15 thoughts on “የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋሙ: ጨቅላ ልጆቻችኹን አታቍርቡ እያለን ይኾን? ሥነ ምግብ እና ሥጋወደሙ ምን አገናኛቸው? የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርስ ምን ይላል?

 1. Anonymous April 5, 2015 at 3:42 pm Reply

  ላለፉት 23 ዓመታት የመንግስት ካድሬ በዝህች ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ላይ ምን ያላሉት፣ ምን የጥፋት አዋጀት ያላወጁት፣ ምን የጥፋት ሸንጎ ያልሰበሰቡት … አለና፡-
  – ኦርቶዶክስ የነፍጠኞች ኃይማኖት ነው፡፡
  – ነጭ መልበስም የነፍጠኝነት መገለጫ ነው፣ የመጤዎች ነው፣ …
  – ግዕዝ የሞተ የነፍጠኞች ቋንቋ ነው፤
  – ለዚች ሀገር ድህነት ዋነኛዋ ተጠያቂ የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ናት፤ የስራ ፈት መናህሪ፣ የድህነት ምንጭ ናት፤
  – ይህች ቤተክርስቲያን የልማት ዕንቅፋት ናት፡፡
  – የአብነት ት/ቤቶች ዜጎች ወደ ትምህርት እንዳይሄዱ እንቅፋት ሆኗል፣ ህገ-መንግስቱን ይጻረራል… ፤
  – ማህተም ማድረግም ቢሆን የጥቂት ጊዜያት ጉዳይ ነው፣ ይወልቃል፣ ይበጠሳል፤ ታዩታላችሁ… <br

  ….
  ….. የህትመቱ፣ በየሚዲያው፣ በየመድረኩ በዚች ቤተክርስቲያን ላይ የታወጀው፣ … ስንቱ ተዘርዝሮ ሊያልቅ…
  ….

  – አሁን ደግሞ… ቅዱስ ቁርባን ለህጻናት ማቁረብ ለህጻናት ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለዚህ ቤተመቅደስ ተገብቶ መጠናትና .. ቀጥሎስ … ብሎ አውጇል
  …. ግን እስከ መቼ ይህችን ቤተክርስቲያንን የመንግስት ካድሬ ካለፈረስኩ እያለ፣ እያቅራራ ይዘልቃል? እስከ መቼ …. ?

 2. TIRSIT WUBIE April 6, 2015 at 6:47 am Reply

  ህፃናቱ ስጋ ወደሙን ከበሉና ከጠጡ እና ከተጠመቁ በኋላ በተለይ እንቅልፍ ላይ የሚያሳዩትን ተጨባጭ ለውጥስ እንዴት
  ያዩታል?

 3. Anonymous April 6, 2015 at 7:12 am Reply

  1. አንዳንድ ዜናዎች የሚሰሩት ትክክለኛ መነሻና መድረሻ ኖሯቸው አይደለም፡፡መነሻቸውና መድረሻቸው የሰውን ስሜት ምን ያህል የመቆንጠጥ ኃይል አላቸው ተብሎ ነው፡፡እንዲያ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ይሕ ርእሰ – ጉዳይ ለአቅመ – ዜና ለመድረስ ገና ነው፡፡ ጽንስ እንኳን ለመሰኘት ወሬው ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አልተሸራሸም፡፡ ብቻ በመንግሥትና በኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ውጥረት ያለ ለማስመሰል ስለሚረዳና የአንባቢን ቀልብ ስለሚገዛ ሽሉን ወሬ ለአደባባይ አበቁት፡፡ እንዲህ ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ ከሆነም ቢቻል የቤተ ክርስቲያን አካላትን ማናገር፣ ካልተቻለም በተናጠል ሊቃውንትን ወይም በቤ/ክ አስተምህሮ ግንዛቤ ያላቸውን የቤ/ክ ልጆች ስለጉዳዩ ያለውን የቤ/ክ አተያይ ማካተት የተገባ ነበር፡፡እሱ አልተደረገም፡፡

  2. ጉዳዩ ታላቅ ምስጢረ – ቤ/ክ (ምስጢረ-ሥጋዌ፣ ምስጢረ-ቁርባን)በውስጡ ያለበት እንደመሆኑ፣ ክሕነት ባላቸው ዲያቆናትና ቀሳውስት ብቻ ተጠብቆ የሚያዝ ሆኖ ሳለ እንዳሻን በአደባባይ ለመወያየት የማንችልበትን ርእስ ያለምንም ተጨማሪ ማብራሪያ ከጋዜጣ ገልብጦ በብሎጉ ማቅረብ ስሕተት ይመስለኛል፡፡ እንዲህ አጋጣሚ ሲገኝ ከዜናው ጋር ስለ ምስጢረ – ቁርባን እና ስለ አፈጻጸሙ (ወሰን ሳታልፉ) በተገቢው መንገድ መልእክት ብታስተላልፉ መልካም ነበር፡፡ ይሕን ለማድረግ ብዙ መድከም አይጠይቅም፡፡ የነፍሰ – ኄር ሊቀ ካሕናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን ስርዓተ-ቤተ ክርስቲያን 2ኛ መጽሐፍ ከገጽ 37 እስከ 61 ድረስ ጥቂት ማገላበጥ በቂ ነበር፡፡

  3. ለጤና ሚኒስቴር ያለኝ መልእክት፡- ሀሳብ አይግባችሁ፡፡ ቤ/ክ የመዳን ቤት ናት፡፡ የቁርባኑ አፈጻጸም በትውፊታችን መሰረት የህጻናትን የውስጥ አቅም በሚፈታተን መልኩ አይደለም፡፡ሺህ ዘመናት ሲፈጸም የኖረው ሥርዓት በአንዳችም ህጻን ላይ የብሩህነት እንጅ የጉዳት ምንጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ቤ/ክ ስለልጆቿ እናንተ ከምታስቡት ያነሰ አታስብም፡፡ የበለጠ ታስባለች፡፡ ቁርባንን ለወንዶች ከ40 ቀን፣ ለሴቶች ከ80 ቀን ጥምቀታቸው ጀምሮ ማቁረብ እስከእለተ – ምጽአት የሚቀጥል ነው፡፡ ቁርባን ዶግማ ነው፡፡ አይሻሻልም፡፡ ስለዚህ የተባለው ወሬ እውነት ከሆነ ታላቅ ስህተት ፈጽማችኋልና አባባሉን ከዳታችሁ/ከኩዌሽነራችሁ ሰርዙት፡፡ ፈጽሞ ቁርባን በመንግሥታዊ መዝገባችሁ አይግባ፡፡ ዜናው ውሸት ከሆነ ስለ ህጻናትና እናቶች ሞት መቀነስ የምታደርጉትን ጥረት አድንቀን እንሰነባበት፡፡

  4. ለአንባብያን፡- እባካችሁ መንግሥትንና ቤ/ክንን የሚያገናኝ ርእስ በተፈጠረ ቁጥር ዘለን መንግሥት አናት ላይ ፊጥ አንበል፡፡ በተለይ መንግሥት/ኢህአዴግ ላይ ያለንን ቂም ቤ/ክ በመታከክ ለመወጣት ለመሞከር የምንታገል ሰዎች እውነተኛ የቤ/ክ በደሎችን የሚናገሩ የቤ/ክ አንደበቶችም ጭምር በመንግሥት ተደርበው እንዲታፈኑ በር ስለምንከፍት ጥንቃቄ ቢደረግ አይከፋም፡፡ያላዋቂ ሳሚ አንሁን፡፡ቤ/ክ የዚህ ወይም የዚያ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አይደለችም፡፡ እሷ የክርስቶስ ሙሽራ ናት፡፡ ስለሆነም ዶግማና ቀኖናዋን ለተቀበለ ሁሉ ወገን፣ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር፣ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ እድሜ፣ ጾታ፣ የኑሮ ደረጃ ሳትለይ ሁሉን ትቀበላለች፡፡የአይዲዎሎጂ አጥር በቅጽራችን የለም፡፡ ማመን፤ መጠመቅ!!በቃ!!ትምክህታችንም ትምህርታችንም ይኸው ነው፡፡

  • Anonymous April 6, 2015 at 2:36 pm Reply

   Egziabhare yebarkhe

  • nehmiashishay April 7, 2015 at 5:58 am Reply

   መረጃ ማቅረባችሁ ወድጄዋለሁ፡፡ ዘገባው መልካም ቢሆንም በፎቶ ላይ ያለው ጥሰት ነው፤ ስለዚህ እሱን ሰርዙትና ቀጥሉበት፡፡ ከላይ ከተሰጠው አስተያየት ደስ ያለኝን ደግሜዋለሁ፡፡

   3. ለጤና ሚኒስቴር ያለኝ መልእክት፡- ሀሳብ አይግባችሁ፡፡ ቤ/ክ የመዳን ቤት ናት፡፡ የቁርባኑ አፈጻጸም በትውፊታችን መሰረት የህጻናትን የውስጥ አቅም በሚፈታተን መልኩ አይደለም፡፡ሺህ ዘመናት ሲፈጸም የኖረው ሥርዓት በአንዳችም ህጻን ላይ የብሩህነት እንጅ የጉዳት ምንጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ቤ/ክ ስለልጆቿ እናንተ ከምታስቡት ያነሰ አታስብም፡፡ የበለጠ ታስባለች፡፡ ቁርባንን ለወንዶች ከ40 ቀን፣ ለሴቶች ከ80 ቀን ጥምቀታቸው ጀምሮ ማቁረብ እስከእለተ – ምጽአት የሚቀጥል ነው፡፡ ቁርባን ዶግማ ነው፡፡ አይሻሻልም፡፡ ስለዚህ የተባለው ወሬ እውነት ከሆነ ታላቅ ስህተት ፈጽማችኋልና አባባሉን ከዳታችሁ/ከኩዌሽነራችሁ ሰርዙት፡፡ ፈጽሞ ቁርባን በመንግሥታዊ መዝገባችሁ አይግባ፡፡ ዜናው ውሸት ከሆነ ስለ ህጻናትና እናቶች ሞት መቀነስ የምታደርጉትን ጥረት አድንቀን እንሰነባበት፡፡

   4. ለአንባብያን፡- እባካችሁ መንግሥትንና ቤ/ክንን የሚያገናኝ ርእስ በተፈጠረ ቁጥር ዘለን መንግሥት አናት ላይ ፊጥ አንበል፡፡ በተለይ መንግሥት/ኢህአዴግ ላይ ያለንን ቂም ቤ/ክ በመታከክ ለመወጣት ለመሞከር የምንታገል ሰዎች እውነተኛ የቤ/ክ በደሎችን የሚናገሩ የቤ/ክ አንደበቶችም ጭምር በመንግሥት ተደርበው እንዲታፈኑ በር ስለምንከፍት ጥንቃቄ ቢደረግ አይከፋም፡፡ያላዋቂ ሳሚ አንሁን፡፡ቤ/ክ የዚህ ወይም የዚያ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አይደለችም፡፡ እሷ የክርስቶስ ሙሽራ ናት፡፡ ስለሆነም ዶግማና ቀኖናዋን ለተቀበለ ሁሉ ወገን፣ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር፣ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ እድሜ፣ ጾታ፣ የኑሮ ደረጃ ሳትለይ ሁሉን ትቀበላለች፡፡የአይዲዎሎጂ አጥር በቅጽራችን የለም፡፡ ማመን፤ መጠመቅ!!በቃ!!ትምክህታችንም ትምህርታችንም ይኸው ነው፡፡

  • Anonymous April 7, 2015 at 7:59 am Reply

   Anonymous April 6, 2015 at 7:12 am ‹‹ዜናው መነሻና መድረሻ የለውም፤ ርዕሱ ለአቅመ ዜና አልደረሰም፤ ጭራሽ ለፅንስ አልበቃም፤ በደንብ አልተንሸራሸም፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪ ስለዚህ የውስጥ አዋቂ አስተያየትና ጥቆማስ ምን ይላሉ?

   በእውነቱ ችግርን ሳያድግ በእንጭጩ መግታት በጣም አስፈላጊ ነው…………………….አንድ ጥናት ሲጠና አላማው መደርደሪያ ላይ መቀመጥ አይደለም………………ለእንደዚህ አይነት ጥናት በሚሊዮኖች የሚገመት ወጭም መውጣት አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ ይህ ጥናት ሲጠና አላማው በሀገራችን ያለው ማይክሮ ኒውትሬት እጥረት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ፣ ለማይክሮ ኒውትሬት እጥረት የሚጋልጡ መንስኤዎች(አመጋገብ፣ጤና፣ወ.ዘ.ተ) ለማወቅ፣ እንዲሁም ለተገኙት ችግሮች መፍትሄ ለማስቀመጥ ነው፡፡

   ስለዚህ እንደዚህ አላማ ያለው ጥናት ከ 5 አመት በታች ለሚገኙ ህፃናት በሚጠይቀው መጠይቅ ላይ ህፃኑ ከእናት ጡት ወተት ውጭ ከስድስት ወር በፊት ወስዶ ነበር ወይ (ማንኛውም ምግብ በሃይማኖት ደረጃ የሚሰጠውን ጨምሮ በቅንፍ ውስጥ (holy water፣ ሥጋወደሙ ጨምሮ) ……………አሁን ነው ማጤን የሚያስፈልገው………….እግዚአብሄር በሚያውቀው መረጃ ክተሰበሰበባቸው ህፃናት ውስጥ አብዛኛዎቹ ማይክሮ ኒውትሬት እጥረት ቢኖርባቸው እንዲሁም እኒሁ ህፃናት በሃይማኖታቸው ስርዓት መሰረት ምሥጢረ ቁርባንን የፈፀሙ ቢሆን ሁለቱም ዝምድናቸው ቢጠና አንዱ ላአንዱ ምክንያት ሆነ ማለት ነው………..ሌሎች መንስዔዎች እንዳሉ ሆኖ …….እነዲህ አይነት ዝምድና ጥናቱ አይስራም ከተባለ መጀመሪያውኑ ጥያቄውን መጠየቅ ለምን አስፈለገ!?………… እንበልና ጥናቱ ሲጠናቀቅ የህፃናት መቁረብ ለማይክሮ ኒውትሬት እጥረት መንስኤ ነው የሚል አንድምታ ቢገኝ መፍትሄው ምንድን ነው???……………..ከዚህ ላይ ነው ትልቁ ምስጢር………..

   እንደ ሃገርስ ቢሆን exclusive breast feeding የት ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ነው??? ሲሰራ የነበረው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር እምርታ ውጤት የት ገባ ሊባል ነው???

   This is the objective of the survey w/c is directly taken from the institute

   GENERAL OBJECTIVE
   To assess the national micro nutrient status of the Ethiopian population
   1.1. Specific Objectives

   The specific objectives of the survey are:
   1) To estimate the prevalence of anemia in Ethiopia.
   2) To estimate the prevalence of iron deficiency in Ethiopia.
   3) To estimate the prevalence of vitamin A deficiency in Ethiopia.
   4) To estimate the prevalence of iodine deficiency in Ethiopia.
   5) To estimate the prevalence of zinc deficiency in Ethiopia.
   6) To estimate the prevalence of vitamin B12 and folate deficiency in Ethiopia.
   7) To estimate the proportion of households with adequately iodized salt in Ethiopia.
   8) To estimate the prevalence of infection (malaria, intestinal parasites, schistosomiasis) in Ethiopia.
   9) To determine the prevalence of wasting, stunting and underweight among children and body mass index (BMI) of school age children, women and men in Ethiopia.

   ርዕሱ ከመንሸራሸት አልፎ በአሳሳቢ ደረጃ እንዳለ አያነቃዎትም ወይ? በእንጭጩ እንዲታሰብበት ካልተደረገ ከዚህ በላይ ምን እስኪሆን እንጠብቅ ነው የሚሉት?

   ለመንግሥት/ለግንባሩ ያሳዩት ተቆርቆሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ዜና ባህርያትና ፋይዳ ያልዎትን ግንዛቤ ቢከልሱት መልካም ነው፤ ዜና ጥቋሚም አንቂም ነው፤ መቼም ‹‹አልተንሸራሸም፤ ለፅንስ አልበቃም›› ሲሉም ኦርቶዶክሳውያን ባለሞያዎቹ ከእርስ በርስ እሰጥ አገባ አልፈው እስከ ጤና ጥበቃ የተጠያየቁበት ጉዳይ ቋንጣ እስኪሆን አልያም ችግሩ ሥር እስኪሰድ እንተኛ እያሉን አይመስለኝምና ፕሬሱ እንደ ሴኩላር ሚዲያ የሚጠበቅበትን ሰርቷል፤ በብሎጉ የተጦመረውም በጥያቄአዊ ምንገድና ለቤተ ክርስቲያን በመወገን መሆኑን አይሳቱት እንጂ!

   ብቻ ወሬው እርስዎ እንዳሉት ሽል አለመሆኑን፣ እውነትም መሆኑን ይመኑ፤ ውጥረት መፍጠር፣ ቂምን ለመወጣት… ገለመሌ እርስዎ የሚሉት ነው፡፡ ይልቁስ መረጃው መንግስታዊ ሃላፊነትንና የመንግስትን መዋቅር ተገን አድርጎ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም አንድ ማሳያ ነውና እርስዎም በመድረክዎ ሃላፊነትዎን እንዲወጡ አሳስብዎታለሁ፡፡

 4. fire April 6, 2015 at 8:50 am Reply

  Addis Admas’s subtle contents are anti Orthodox Tewahido, it promotes indirectly dangerous issues and the motive behind it’s all religious issues is devilish. Take care of
  this wicked agenda setter and don’t fall in their trap, instead directly investigate the issue from the source. As to the real issue we must not be surprised by directives and so-called studies against our faith; from every direction of our daily life our Tewhido religion will be attacked further. We must keep our faith in an integrated manner not by responding for every issue.

 5. . April 7, 2015 at 4:43 am Reply

  በእውነቱ ችግርን ሳያድግ በእንጭጩ መግታት በጣም አስፈላጊ ነው…………………….አንድ ጥናት ሲጠና አላማው መደርደሪያ ላይ መቀመጥ አይደለም………………ለእንደዚህ አይነት ጥናት በሚሊዮኖች የሚገመት ወጭም መውጣት አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ ይህ ጥናት ሲጠና አላማው በሀገራችን ያለው ማይክሮ ኒውትሬት እጥረት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ፣ ለማይክሮ ኒውትሬት እጥረት የሚጋልጡ መንስኤዎች(አመጋገብ፣ጤና፣ወ.ዘ.ተ) ለማወቅ፣ እንዲሁም ለተገኙት ችግሮች መፍትሄ ለማስቀመጥ ነው፡፡

  ስለዚህ እንደዚህ አላማ ያለው ጥናት ከ 5 አመት በታች ለሚገኙ ህፃናት በሚጠይቀው መጠይቅ ላይ ህፃኑ ከእናት ጡት ወተት ውጭ ከስድስት ወር በፊት ወስዶ ነበር ወይ (ማንኛውም ምግብ በሃይማኖት ደረጃ የሚሰጠውን ጨምሮ በቅንፍ ውስጥ (holy water፣ ሥጋወደሙ ጨምሮ) ……………አሁን ነው ማጤን የሚያስፈልገው………….እግዚአብሄር በሚያውቀው መረጃ ክተሰበሰበባቸው ህፃናት ውስጥ አብዛኛዎቹ ማይክሮ ኒውትሬት እጥረት ቢኖርባቸው እንዲሁም እኒሁ ህፃናት በሃይማኖታቸው ስርዓት መሰረት ምሥጢረ ቁርባንን የፈፀሙ ቢሆን ሁለቱም ዝምድናቸው ቢጠና አንዱ ላአንዱ ምክንያት ሆነ ማለት ነው………..ሌሎች መንስዔዎች እንዳሉ ሆኖ …….እነዲህ አይነት ዝምድና ጥናቱ አይስራም ከተባለ መጀመሪያውኑ ጥያቄውን መጠየቅ ለምን አስፈለገ!?………… እንበልና ጥናቱ ሲጠናቀቅ የህፃናት መቁረብ ለማይክሮ ኒውትሬት እጥረት መንስኤ ነው የሚል አንድምታ ቢገኝ መፍትሄው ምንድን ነው???……………..ከዚህ ላይ ነው ትልቁ ምስጢር………..

  እንደ ሃገርስ ቢሆን exclusive breast feeding የት ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ነው??? ሲሰራ የነበረው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር እምርታ ውጤት የት ገባ ሊባል ነው???

  This is the objective of the survey w/c is directly taken from the institute

  GENERAL OBJECTIVE
  To assess the national micro nutrient status of the Ethiopian population
  1.1. Specific Objectives

  The specific objectives of the survey are:
  1) To estimate the prevalence of anemia in Ethiopia.
  2) To estimate the prevalence of iron deficiency in Ethiopia.
  3) To estimate the prevalence of vitamin A deficiency in Ethiopia.
  4) To estimate the prevalence of iodine deficiency in Ethiopia.
  5) To estimate the prevalence of zinc deficiency in Ethiopia.
  6) To estimate the prevalence of vitamin B12 and folate deficiency in Ethiopia.
  7) To estimate the proportion of households with adequately iodized salt in Ethiopia.
  8) To estimate the prevalence of infection (malaria, intestinal parasites, schistosomiasis) in Ethiopia.
  9) To determine the prevalence of wasting, stunting and underweight among children and body mass index (BMI) of school age children, women and men in Ethiopia.

 6. Anonymous April 7, 2015 at 6:28 am Reply

  አሁን-አሁን አማረ…እኸ…አሁን አማረ….
  አማን በአማን ሐራ ዘተዋሕዶ!!አጠገባችሁን፡፡ቁስለ – ነፍሳችንን ፈወሳችሁት፡፡ኦርቶዶክሳዊ ውትድርና እንዲህ ነው፡፡ጥቃትን ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን ጥቃትን መመከት፡፡ይልመድባችሁ፡፡ይሕን የመሰለ የቃለ – እግዚአብሔር ትጥቅ ይዛችሁ አንድ አይነት ቅኝት ብቻ ይዛችሁ ከመሄድ አንድ የትምሕርተ – ሃይማኖት ገጽ እዚሁ ላይ ከጎን ጨምሩ፡፡መክሊታችሁን አትቅበሩ፡፡የቺን መስህት-ዘእምስሑታን ዜና ያከማችሁበት መንገድ ግን እንዴት ደስ እንዳለኝ!!እሰይ የኔ ወንድሞች/እኅቶች!!
  አያችሁ፡- እናንተ ይሕን ቀድማችሁ ካላከማችሁ እነ አጅሬ ታዲያ ምን ይገርማል፤ትክክል ነው፤ሥጋ ወ ደሙ ምግብ ነው እያሉ ሊፏልሉብን ነው፡፡አሁን ግን ከነብያኔው ስለጻፋችሁት እንዲያ አይሆንም፡፡ቢሆንም ባስታጠቃችሁን ትጥቅ እንመክተዋለን፡፡
  እስኩ ድግሙ-ድግሙ….እስኩ ድግሙ….

 7. Anonymous April 7, 2015 at 1:07 pm Reply

  so what? truly u r soldiers,

 8. Anonymous April 8, 2015 at 7:01 am Reply

  መርፊ አስተካክሎ መውጋት የማይችል የኛ ሀገር ሐኪም ስለ ክርስቶስ ስጋና ደም እንዴት ሊያወራ ይችላል?

 9. birhan April 8, 2015 at 7:03 am Reply

  leakime ziena alederesem maletlemin tolo tenekabign yasimesilal.endewum Ministry of Health yihen guday sayigebaw bemansatu hizibun talaq yikirita meteyek alebet

 10. Anonymous April 14, 2015 at 9:20 am Reply

  ORTHODOX YEHON HULU YEHNEN TINAT ALMESATEF NEW ATNI TEBYEWECH SIMETU MELSE ALEMESTET .LENEZIH KEHADIWECH TLIK MELSE NEW

 11. Addisalme Asfaw February 9, 2016 at 10:28 am Reply

  ክርስትና መስቀል ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: