የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዐሥር ዐበይት: ጠንካራ ጎኖች፣ ድክመቶች እና የስጋት አቅጣጫዎች በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እይታ

holy-trinity-theological-college-logoየቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የጥናት እና ምርምር ክፍል የወሩን ኹለተኛ ጥናታዊ ውይይት መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በኮሌጁ አዳራሽ አካሔዷል፡፡ ከግማሽ ምእት በላይ የምሥረታ ዘመን ባስቆጠረው መንፈሳዊ ኮሌጅ ከዐሥር ዓመት በፊት የተጀመረው የውይይት መድረኩ፣ እንዳስፈላጊነቱ የሚጋበዙ የአገር ውስጥ እና የውጭ ምሁራንና ሊቃውንት ጥናታቸውን ሲያቀርቡበት ቆይተዋል፡፡ ከስድስት ዓመት ወዲኽ ደግሞ መርሐ ግብሩ ራሱን የቻለ አስተባባሪ ተመድቦለት በየሳምንቱ ረቡዕ ከቀኑ 10፡00 – 12፡00 በደቀ መዛሙርት ጸሎት ቤት እየተካሔደ ይገኛል፡፡

በነገረ ቤተ ክርስቲያንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚቀርቡት ሐሳቦች፣ ኮሌጁ ለሚያቅደው የጥናት መጽሔት(ጆርናል) ዝግጅት በግብዓት እንደሚያገለግሉ የተጠቆመ ሲኾን ለቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ችግሮች እና ውጫዊ ተግዳሮቶች መፍትሔዎችን በመጠቆም ተቋማዊ ሚናውን የሚጫወትበት፣ ደቀ መዛሙርቱም በጥናትና ምርምር ሥራና አቀራረብ ልምዶችን ለመቅሰም የሚረዳቸው እንደኾነም ተመልክቷል፡፡ በያዝነው ዓመት መርሐ ግብሩ ከመስከረም እስከ የካቲት ወር ድረስ ተቋርጦ ቆይቶ በዚኽ ወር ሲቀጥል የወሩ ኹለተኛ መድረክም ባለፈው ረቡዕ ከቀኑ 10፡00 – ምሽቱ 12፡15 በኮሌጁ አዳራሽ ተከናውኗል፡፡

3

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በተገኙበት የዕለቱን ተጋባዥ ተናጋሪ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በማስተዋወቅ ውይይቱን የመሩት አካዳሚክ ዲኑ መ/ር ግርማ ባቱ፣ ርእሰ ጉዳዩ እና የአቅራቢው ማንነት የሳምንቱን መርሐ ግብር ከቀደሙት የተለየ እንደሚያደርገው ለታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲኹም የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ስጋቶች›› በሚል ርእስ የዳሰሷቸው ነጥቦች፣ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ በአግባቡ ነቅሶ አውጥቶ ለመፍትሔ በሚጋብዝ መልኩ በመቅረባቸው ብፁዕነታቸውን አመስግነዋቸዋል፡፡

ተከታታዮች በጥያቄ እና አስተያየት በነጻነት የተሳተፉበት ውይይቱ፣ ‹‹የቅርብ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች በእንጥልጥል እንዳሉ አሳይቷል›› ያሉት አካዳሚክ ዲኑ፣ ‹‹ለአካሔዱም ፈር ቀዳጅ›› እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ችግሮች እየተለዩ ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸው የሚቀጥል ሲኾን ‹‹እንወያያለን፤ ማንንም ተጠያቂ ሳናደርግ እኛው መፍትሔ እንፈልጋቸዋለን›› ብለዋል፡፡ የበላይ ሓላፊው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በማጠቃለያ ምዕዳናቸው÷ ‹‹የቀረበው፣ የተጠየቀው፣ የተመለሰው ኹሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን በመኾኑ ፍርዱን መስጠት የኹላችን የእያንዳንዳችን ነው፤›› ሲሉ መክረዋል፡፡

የኮሌጅ መንፈስ የሚታየው መድረክ ተከፍቶ ሐሳቦች ሲወጡ መኾኑን የጠቀሱ አንድ ተሳታፊ÷ የጥናትና ምርምር ክፍሉ መርሐ ግብር፣ መንፈሳዊ ኮሌጁ ከአርባ ዓመት በፊት ገና በከፍተኛ ኹለተኛ ደረጃ ሳለ ተስፋፍቶበት የነበረውን የውይይት መንፈስ እንዳስታወሳቸውና ያን ለመመለስ የታሰበበት እንደሚመስል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከውይይቱ ተከታታዮች የአብዛኞቹ ጥያቄና አስተያየት፣ በብፁዕነታቸው የቀረቡት ሐሳቦች የቅዱስ ሲኖዶሱን ትኩረት እንዲያገኙ በተማፅኖ የቀረቡ ናቸው፡፡ ዘወትር ውስጣችንን የሚነኩና ዕረፍት የሚነሡን በመኾኑ ታች ካለው አስፈጻሚ አካል ይልቅ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲታሰብባቸው ተጠይቋል፡፡ ‹‹መምህራን ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ደቀ መዛሙርትም መመረቂያቸውን እንዲሠሩ ዕድል የሚጋብዝ፣ የጥሪ ደወል የሚያሰማው አቀራረብ ነው›› ያሉ አንድ ተሳታፊ፣ ‹‹ለቤተ ክርስቲያኗ ራስ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያቀርቡልን በአበው አምላክ እንማፀንዎታለን፤ ለእርስዎም የድርሻዎን የሚወጡበት ይኾናል›› ሲሉ አሳስበዋል፤ ሌሎች መሰል ድምፆችም በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡

ይህም ኾኖ በውይይቱ ኹለተኛ ዙር የጥያቄ ክፍለ ጊዜ፣ ችግሮቹን ለመፍታት እና ስጋቶቹን ለማስቀረት የቅዱስ ሲኖዶሱ አወቃቀር እና አሳታፊነት በራሱ እንዲፈተሽ የሚያሳስብ ጥያቄ ተሰንዝሯል፡፡ ለዘመናት ያለሲኖዶስ በጉባኤ ሊቃውንት ስትመራ እንደኖረች የተናገሩት መምህሩ፣ ‹‹ከሲኖዶስ መመሥረት አርባና ኃምሳ ዓመታት ወዲኽ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመወደቅ መፍገምገም ጀምራለች›› ብለዋል፡፡ ይህም በቅዱስ ሲኖዶሱ የአወቃቀር ችግር ሳቢያ እንደኾነ ሲያብራሩ፣ ‹‹ኹሉንም የመወሰን ኹኔታ በሊቃነ ጳጳሳት ተይዟል፤ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ፣ ሕግ ተርጓሚ ኾነው ለምእመናን የተሰጠ ሥልጣን የለም፤›› ብለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስን በማማከር እና መረጃ በመስጠት የሚያገለግል የሊቃውንት አካል ማቋቋም የአወቃቀር ብቃት ክፍተቱን እንደሚያስወግድ የተናገሩት መምህሩ፣ ‹‹ጥቁር ራስን ወደ ጵጵስና እስከማምጣት ድረስ መሔድ አለበት፤›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ የቅዱስ ሲኖዶስ አወቃቀር ሳይኾን የአካሔድ እና የአፈጻጸም እንደኾነ አስተያየት የሰጡት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ከእኔ ጀምሮ አልሠራንም፤ አልፈጸምንም፤›› ብለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጭ ነው፤ ውሳኔዎችን በሕጉ መሠረት በማስፈጸም በኩል ግን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ ወረዳ ቤተ ክህነት አለመሠራቱን አበክረው ተናግረዋል፡፡ ተጠያቂነት የሌለበት ሓላፊነት መስጠት እየተለመደ መምጣቱን ብፁዕነታቸው አስታውቀው፣ ይህም በአስፈጻሚው አካል የሚመራውን አስተዳደር ወደ ቤተሰባዊነት እየወሰደው እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቤተሰባዊነት ከገባበት ተጠያቂነት የለም፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው÷ ቀኖና፣ ሥርዐት ሲጣስ በግልጽ ከማረም ይልቅ በዝምታ እየታየ እንዳለ፤ ከአስፈጻሚው አካል ይልቅ ምእመናን ሃይማኖታችን በሚል የበለጠ መቆርቆር እንደሚያሳዩ አልሸሸጉም፤ ‹‹ይህ ሊቃነ ጳጳሳትንም ይጨምራል፤ እየተኮራረፍን ሥራው እየሞተ እየተማማን ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚኽ ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመቀነስና ቤተ ክርስቲያኗን ለማዳን ሲባልም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ራሳቸውን በመስጠት እና ወቅቱን በዋጀ አካሔድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጠቅላላ እንቅስቃሴ እንዲፈጽሙና እንዲያስፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት በነበረበት ዘመን የአስተዳዳሪዎች ሹመት እና የሊቃውንቱ ምደባ በነገሥታቱ የሚወሰን እንደነበርና የመንግሥት ሕግ የበላይነት እንደነበረው የገለጹት ብፁዕነታቸው፣ መንግሥት እና ሃይማኖት መለያየታቸው ከታወጀ በኋላ የተከተልነው አደረጃጀት በባሕርይው የማን(የአኃት አብያተ ክርስቲያን) እንደኾነም ችግሩ በውል ሊፈተሽና ውስንነቱ ሊታወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን÷ በመንፈሳዊውም ኾነ በዘመናዊው መስክ፣ በዓለም አቀፍም ኾነ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሁራን እናት እንደኾነች ብፁዕነታቸው በጥንካሬ ቢያስቀምጡም፣ ‹‹ካሉ የት ገቡ? ልዕልናዋ እና ክብሯ በጥራዝ ነጠቆች ሲደፈር ያለፉትን ሊቃውንት ሥራዎች ከመጥቀስ ውጭ የታየ ነገር የለም፤ በዕቅድ እንመራ ከማለታችን በፊት የሰው ሀብታችን በአግባቡ እናውቃለን ወይ? ይቅርና የተማረውን ኃይላችንን የአብያተ ክርስቲያን፣ የካህናት እና የምእመናን ብዛት እንኳ በግምት እየተነገረ የውጭ አካላት ለሚያወጧቸው የተዛቡ መረጃዎች ምክንያት እየኾነ ነው፤ ዘመናዊውን ዕውቀት ከቤተ ክርስቲያን ጋራ አዛምዶ የመምራት ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል ተቋም አለን ወይ? ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ዝግጁነቱ አለን ወይ? የምሁራኑ እና የትምህርት ተቋሞቻችን ብዛት ከሕዝቡ ብዛት ጋራ የተመጣጠነ ነው ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ተነሥቶባቸዋል፡፡

በአስፈጻሚው አካል የሰው ኃይል አመዳደብ ‹‹በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ እና የራስን ምሩቃን አለመጠቀም›› በብፁዕነታቸው ከዋነኛ አስተዳደራዊ ድክመቶች እንደ አንዱ የተነሣ ነው፡፡ ዕቅድ መሠረቱ የቤተ ክርስቲያን ቢኾንም እንዳልተሠራበትና እንዳልተመራንበት፤ ወቅቱን የዋጁ፣ የተሟሉና በተግባር የሚተረጎሙ የተዘረዘሩ ሕገጋትና ደንቦች አለመኖራቸው በብፁዕነታቸው ታምኖበታል፡፡ ዘመናዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት እንዳይኖር ከሚታየው የመቃወም አመለካከት የተነሣ፣ ደካማ አመራር እና አንዱ ከአንዱ የሚጣረስ የሥራ ሓላፊነት፣ መሥመር የለቀቀ ዘረኝነት፣ ልቅ ሙስናና ዝርፊያ መስፈኑን ገልጸዋል፡፡ በረጅምና በአጭር ጊዜ ዕቅድ መመራት፣ የተሟላ የሰው ኃይል አስተዳደር ማንዋል መቅረጽ፣ በተወሰነ ጊዜ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን፣ ውጤታማነትንና ቀልጣፋነትን የሚያረጋግጥ ከአድልዎ የጸዳ ተቋማዊ ግምገማ ማካሔድ ችግሮቹን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ብፁዕነታቸው፣ በየአድባራቱ ከእግዚአብሔር ዋጋ እናገኝበታለን በሚል ሃይማኖተኝነት ሳይኾን ደመወዝ ስለሚከፈል ብቻ ክህነታዊ አገልግሎትን መፈጸም የቤተ ክርስቲያናችን የውድቀት አደጋ ማሳያ ነው፤ በክህነቱም ለሕፃናቱ እና ወጣቶቹ የተተኪነት ዕድል ጠፍቶ እስከ አርባ ዓመት ዕድሜአቸው ዲያቆን እየተባሉ በሚቀመጡ አገልጋዮች ባለቤት የኾነና ያልኾነ የተለየበት፣ በደጀ ጥናትና ጥቅም በመስጠት ላይ በተመሠረተ ግንኙነት መንፈሳዊነት የተሟጠጠበት፣ ቀድሞ የቀረው ቶፋነት በሌላ መልኩ የቀጠለበት ቅኝ ገዥነት ይታያል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በረጅም እና በአጭር ጊዜ ዕቅዶች የሥራ ዕድል በምትፈጥርባቸው አቅሞች፣ በሰው ኃይል አጠቃቀሟ ረገድ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ እንደሚጠበቅባት አስገንዝበዋል፡፡

የኮሌጆቻችን ምሩቃን በውጤታቸው እየሠለጠኑ እና በክህሎታቸው እየተለዩ ቢሠለጥኑና ቢመደቡ አስተዳደሩን እንደሚለውጡ ብፁዕነታቸው ያምናሉ፤ ሰው ‹‹ባልተሰጠበት/ባልሠለጠነበት›› በሓላፊነት ሊጠየቅ ስለማይችል ያስተማርነውን የሰው ኃይል አቅም ለመገንባትና ለመጠቀም፣ ሠራተኛውን ከሥራው ጋራ ለማገናኘት ሥልጠና ያስፈልጋል፤ ለዚኽም በቴዎሎጂው ብቻ የተወሰነውን የኮሌጆቻችንን መርሐ ግብር በሌሎች መስኮችም ማስፋፋት አልያም ሥርዓተ ትምህርታቸውን መፈተሽ ይገባል፡፡ ምሩቃን ደቀ መዛሙርትን እንደ ውጤታቸውና እንደ ብቃታቸው ለማሠማራት በቅዱስ ሲኖዶስ የተያዘ ዕቅድ መኖሩንና ከኮሌጆቹ ጋራ ውይይት እንደሚካሔድበት ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል፡፡

በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሁራን አሉን ስንል ዘመናዊዎቹን ኮሌጆች ብቻ ሳይኾን በዘመናት የሚቀድሟቸውን የአብነት ት/ቤቶችና ከውዳሴ ከንቱ ሸሽተው ራሳቸውን የደበቁ ሊቃውንትን መመልከት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ብፁዕነታቸው፡- ‹‹ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሊቃውንት በትክክል አሉን፤ ምሁራን የሉንም ካልን ትምህርት የለም ማለት ነው፤ እናንተም እየደከማችኹ ያላችኹት ምሁራን ስላሉና በእነርሱ እግር ለመተካት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይኹንና ከዘመኑ ጋራ እየተራመዱ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ከምዕራባውያን ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የሚወዳደሩና የሚልቁ የአብነት ት/ቤቶቻችን ነባር አስተዋፅኦ አስጠብቆ ለመቀጠል፣ ሥርዐተ ትምህርታቸውን በወጥነት በማደራጀትና በማዘጋጀት በየአህጉረ ስብከቱ ማስፋፋት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

የሥራና ሠራተኛው አለመገናኘት በሀገር ውስጥና በውጩ ሐዋርያዊ ተልእኮም ጭምር እንደሚንጸባረቅ ተገልጧል፡፡ በተስፋ ለሚጠባበቁን በተለይም ድረሱልን ለሚሉ አፍሪቃዊ ወገኖች ጥሪ ምላሽ በመስጠት በኩል የተገኘው ውጤት ‹‹ዲያቆን እንኳ ያላወጣንበት›› አሳፋሪ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ እንግሊዝኛውን ‹አጥምቀው› ከግእዙ ጋራ አስማምተው ዶግማውንና ቀኖናውን በቋንቋው ለማስተማርና ለማሳመን ለሚጥሩ ሰባክያነ ወንጌል ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ በመንደርተኝነት መሳሳብ እና ሀብት ለማፍራት መሯሯጥ ፈጦ የወጣበት ኾኗል፡፡ በደቡብ አፍሪቃውያኑ ‹‹በአፍሪቃ ቀንድ የተቀመጣችኹት የአፍሪቃ ብርሃን፣ የአፍሪቃ አለኝታ እንድትኾኑ ነው›› የምንባለውን ያኽል አለመሥራታችን ራስ ወዳድነታችን እያጋለጠው ነው፡፡ የሓላፊነቱ ክብደት ሩቅ ሳይኬድ በአገራችን ጠረፋማ አካባቢዎችና ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትን እንሻለን›› በሚሉት በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ስለሚታይ የራሳችንን ወገኖች ከማጽናት ጋራ ‹‹ለአፍሪቃውያን ነፍስ መጥፋትም›› የታሪክ ተጠያቂ እንዳንኾን ትክክለኛውን አገልጋይ በትክክለኛው ቦታ በዕቅድ ላይ ተመሥርቶ ማሰማራት ግድ ይለናል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በከተማ ይኹን በገጠር ሰፊ የማይንቀሳቀስ መሬት ባለቤትና በገቢ መጠኗ ተወዳዳሪ የሌለው የገቢ መጠን ያላት መኾኗ በብፁዕነታቸው ንግግር በጥንካሬ መገለጫነት ቀርቧል፡፡ በአንጻሩ፣ ‹‹እውን ቤተ ክርስቲያን ባለሀብት ናት ወይ?››በማለት የጠየቁ ተሳታፊ ሀብቱ ለመዝባሪዎች የተጋለጠ መኾኑንና የግለሰቦች ብልጽግና ቤተ ክርስቲያኗን እንደማይወክል ሞግተዋል፡፡ ምእመኑን በአግባቡ ለማስተባበር ቢቻል ራስ አገዝ አቅም የሚፈጥሩ፤ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎትን የምናስፋፋባቸው ተቋማት(የኒቨርስቲዎች፣ ሆስፒታሎች…) ለማቋቋም ቢቻልም በአድባራት ዙሪያ የሚታዩት ግንባታዎች ኹሉ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዘዋል ለማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ የሚገነቡት ሕንፃዎች ልመናን እያስፋፉ፣ የምእመናን ልማትን ወደ ጎን የተዉ በመኾናቸው አለ የሚባለውን ልማት ያኽል የምእመናን ቁጥር ሲጨምር እንደማይታይ የሚጠቅሱ አስተያየቶችም ተደምጠዋል፡፡

በገጠር አብያተ ክርስቲያን በነባር አድባራትና ገዳማት ሰፋፊ የመሬት ይዞታ ያለን ቢኾንም እየተጠቀምንባቸው እንዳልኾነና ከአየአስተዳደሩ ጋራ በመመካከር በአካባቢ ጥበቃ ያለንን መልካም ልምድ የሚያስቀጥል ዕቅድ አውጥቶ፣ አቅምን አስተባብሮ መሥራት እንደሚገባ ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡ የከተማ መሬት ባለይዞታ የኾኑት የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት በአብዛኛው ወቅቱን የዋጀ ልማት ሲያካሒዱ ታጥረው የተቀመጡም እንዳሉና በዚኹ ኹኔታ ሳይሠራባቸው ከቆዩ ለነገ ሊቆዩን ስለማይችሉ በአግባቡ ሊለሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በበላይ ሓላፊነት በሚመሩት የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በኩል በሦስት ቢልዮን ብር ጠቅላላ ወጪ መንበረ ፓትርያርኩ የሚገኝበትን የአራት ኪሎ ዙሪያ ከ3 – 5 ዓመት በመኖርያ ቤቶችና በኹለገብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ የማልማት ዕቅድ መያዙን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ኋላ ቀር የፋይናንስ ሥርዐት እና የንብረት አያያዝ ከዋና ዋና አስተዳደራዊ ድክመቶች አንዱ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ የተሟላ የፋይናንስ እና የንብረት አጠባበቅ ሥርዐት ማዘጋጀት የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ዋስትና አደጋ የኾነውን ልቅ ዝርፊያና ሙስና ለመግታት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ሙስና በባሕርይው፣ በይዘቱ ገንዘብ መቀበልና ማቀበል ብቻ ሳይኾን አእምሯዊ ኹኔታንም የሚያመለክት ሰፊ ትርጉም ስላለው ከመሠረቱ ማድረቅ አይቻልም ተብሎ እንደሚታሰብ ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ ጋር ግን ይቻላል›› በማለት መቀነስ ብቻ ሳይኾን ማስወገድ እንደሚቻልም አረጋግጠዋል‹‹በሲቪክ ያለውን እንተወውና የኛ ሃይማኖታዊ ተቋምና አሠራር ነው፤ የሌላውን ገንዘብ አትመኝ ነው ትምህርታችን፤ ሃይማኖት ነው፤ ይህን የማይቀበልና የማይተገብር የሃይማኖቱ ተከታይ አይደለም፤ የሥነ ምግባር ምንጮች ነን እያልን ጫማ፣ ወርቅ፣ ሰዓት፣ ሞባይል የሚጠፋው ከመስጊድ ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ነው፤ ማንን ነው መስበክ የምንችለው? በአርኣያነት ልንታይ፣ ሕይወታችን ሊሰብክ ሲገባ በእኛ አካሔድና ኹኔታ ሕዝቡ እየተበከለ ነው፤ የአባቶቻችንን ተኣምኖና ቅድስና መመለስ ካልቻልን አደጋው የከፋ ይኾናል፡፡››

‹‹ሕዝቡ ያውቃል፤ ሳይጠየቅ የሚሰጥ ነው›› ያሉት ብፁዕነታቸው፣ በልመናው አኳኋን ግን እየተሰላቸ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአንድ ቤተ ክርስቲያን ፍጡር ከፈጣሪ እየተዳበለ እስከ 12 ታቦት አለ፤ በየወሩ ይነግሣል፤ ቀኖናዊ ግን አይደለም፤›› በማለት የተቹት ብፁዕነታቸው፣ ቤተ ክርስቲያንን የቢዝነስ ተቋም በማስመሰልና አጉል ፉክክር በመግባት ገጽታዋን እንደሚያበላሽ አስጠንቅቀዋል፡፡ በምትኩ አስተዳደሩና ስብከተ ወንጌሉ፣ ሃይማኖቱን በፍቅር የሚወድ ራሱን የገዛ ምእመን በማፍራትና በማብዛት ላይ ቢያተኩር የተፈለገው ድጋፍ ሊገኝ እንደሚችል መክረዋል፡፡ የምእመኑ ቁጥር ለመቀነሱ ይኹን ለመጨመሩ ማሳያው በየአጥቢያው ያለው አያያዝ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ከልማቱ ጋራ ቁጥሩ አልጨመረም፤ ቀንሷል›› ከተባለም የቀነሰበት ምክንያት በዝርዝር ተነቅሶ፣ የአገልጋዩም የምእመኑም ድካም ተለይቶና ተመዝኖ ቢያንስ የመቀነሱን ፍጥነት በመግታትና ያለውን በማጽናት ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዚኽ ረገድ የልማት ኮሚሽኑ የራሱ ዕቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን እያደገ በመጣው በቱሪዝም መስክ ያልተነካ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ከአገሪቱ የቱሪስት ሀብቶች ከፊሉ የቤተ ክርስቲያኗ ኾነው ሳለ የተጠቀመችው ምንድን ነው ሲሉ የጠየቁት ብፁዕነታቸው፣ የቱሪዝም ገቢው ለሌላ አሳልፋ መስጠቷን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ/እስከ ኹለት ቢልዮን ዶላር/ በቱሪዝሙ ማግኘቱን የሚናገረው ገቢውን የሚሰበስብበት ሥርዐት ዘርግቶ መኾኑን ብፁዕነታቸው ጠቅሰዋል፤ ቤተ ክርስቲያንም የአሠራር ችግሮቿን ፈትሻ በዕቅድ ብትሠራና አገልጋዮቿን በሥልጠና ብታበቃ፣ ለሰው ኃይሏ የሥራ ዕድል የምትፈጥርበትና ተጠቃሚ የምታደርግበት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሙዝየሞችን ከመገንባት ጀምሮ ቅርሷቿን የምትከባከብበት አቅም መፍጠር እንደሚቻላት አረጋግጠዋል፡፡

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስ እንደምትመራ በንግግራቸው መግቢያ ያወሱት ብፁዕነታቸው፣ አስተዳደራዊ መዋቅሯ በሰው የተገነባ ነውና ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደማያጡት ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው፣ ዋናው ነገር ጠንካራውን አጎልብቶ ደካማውን አስወግዶ ለመራመድ መቻል ነው፡፡ የወደፊት ጉዞዋን በተሟላ መልኩ ለመቀጠል ትችል ዘንድ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ኹኔታው ያለበትን ጥንካሬና ድክመት በትክክል በመለየት የወደፊቱን አቅጣጫ መተለም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልኾነ ግን፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት በቀጠለው ውዝግብ ሳቢያ የቤተ ክርስቲያኗ አንድነት ሲናጋ የውስጥና የውጭ ጠላቶች እንደሚበረቱና በመጨረሻም መከፋፈልና መበታተን እንደሚከተል ብፁዕነታቸው በስጋት አቅጣጫቸው አሳስበዋል፡፡ /በጥናታዊ መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው የቀረበውን የውይይት መነሻ ሓሳብ ሙሉ ይዘት ይመልከቱ፡፡/

*        *        *

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ስጋቶች
ab-samuel

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ጉዞዋን በተሟላ ሁኔታ መቀጠል ትችል ዘንድ እና አሁን የምትገኝበትን ሁኔታ ማወቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

በዚህ ምድር የሚገኝ ፍጡር በሙሉ ጠንካራ እና ደካማ ጎን እንዳለው ይታወቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ቢሆንም አስተዳደሩ በሰው የተገነባ ነውና ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደማያጣ ይገመታል፡፡ ዋናው ነገር ግን ጠንካራውን አጎልብቶ ደካማውን አስወግዶ ለመራመድ መቻሉ ነው፡፡

በዚህም መሠረት አሁን የምንገኝበትን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በትክክል ከለየን የወደፊት አቅጣጫችንን መገመት የምንችልበት ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ /1ኛ ቆሮ. 12፤12፣ ኤፌ. 1፤23/

በአሁኑ ወቅት የሚታዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ዋናዎቹ ጠንካራ ጎኖች ከዚህ ቀጥለን እናያለን

፩ኛ. ሃይማኖታዊም ሆነ ታሪካዊ ይዞታዋ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በጎ ገፅታ አላት፡፡
፪ኛ. ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት /WCC/ መሥራች በመሆኗ ከለጋሽ ድርጅቶች ጋርም የተፈጠረ መልካም ትስስር አላት፡፡
፫ኛ. በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ምሁራን አሏት፡፡
፬ኛ. በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያተረፉ የዜማና የቅኔ እንዲሁም መንፈሳዊ ኮሌጆች የምርምርና የጥናት መጻሕፍቶች አሏት፡፡
፭ኛ. በመንፈሳዊውም ሆነ በዘመናዊውም መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባለቤት እና የምሁራን እናትም ናት፡፡
፮ኛ. በከተማም ሆነ በገጠር ሰፊ የማይንቀሳቀስ መሬት ባለቤት ናት፡፡
፯ኛ. በገቢ መጠኗ ተወዳዳሪ የሌለው የገቢ መጠን ያላት ናት፡፡
፰ኛ. በቱሪዝም መስክ ያልተነካ ሀብት ባለቤት ናት፡፡
፱ኛ. በአካባቢ ጥበቃ እና ነባር የአድባራትና የገዳማት አፀዶችን በመትከልና በመንከባከብ በኩል መልካም ልምድ አላት፡፡
፲ኛ. በዩኔስኮ የተመዘገቡ እና ወደፊት የሚመዘገቡ ቅርሶችና ጥበባት ባለቤት ናት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ዋና አስተዳደራዊ ድክመቶችን እናያለን

፩ኛ. በረጅም እና በአጭር ዕቅዶች አለመመራት
፪ኛ. የተሟሉና ወቅቱን የዋጁ ደንቦችና ሕገጋት አለመኖር ወይም በተግባር አለመተርጎም
፫ኛ. ዕውቀትን መሠረት ያደረገ የሰው ኃይል አመዳደብ፤ የራስን ምሩቃንም አለመጠቀም
፬ኛ. ደካማ አመራር እና አንዱ ከአንዱ የሚጣረስ የሥራ ኃላፊነት
፭ኛ. የዕለት ተዕለት የእርስ በእርስ ግጭት እና አለመግባባት
፮ኛ. ኋላቀር የፋይናንስ ሥርዓት
፯ኛ. ልቅ የኾነ ሙስና እና ዝርፊያ
፰ኛ. ኋላቀር የንብረት አያያዝ
፱ኛ. ዘመናዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት እንዳይኖር መቃወም
፲ኛ. መንፈሳዊነትና ሰብአዊነት የሌለው መሥመር የለቀቀ ዘረኝነት

ወደፊት ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሥጋት አቅጣጫዎች፤
የተሟላ የገንዘብ እና የሰው ኃይል አጠቃቀም እንዲሁም መልካም አስተዳደር ባለመኖሩ ምክንያት በየጊዜው በሚፈጠረው ውዝግብ የተነሣ፡-

፩. የቤተ ክርስቲያኒቱ ገጽታ ይዳከማል
፪. የእርስ በእርስ ግጭቶች ይስፋፋሉ
፫. ሙስና እና ዝርፊያ ይንሰራፋል
፬. የሕዝብ ድጋፍ ይጠፋል
፭. የኢኮኖሚ አቅም ይቀንሳል
፮. የቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ቀኖናዊ ሥርዓቶች ቀስ በቀስ ይጣሳሉ
፯. ምግባረ ብልሹነት ሲሰፍን የሕዝብ እምነት ይቀንሳል የሕዝብ እምነት ሲቀንስ የውጭ ዕውቅናም ኾነ ድጋፍ ይጠፋል
፰. የቤተ ክርስቲያኗ አንድነት ሲናጋ ልዩ ልዩ እምነቶች በየመንደሩ ይፈጠራሉ
፱. የቤተ ክርስቲያኒቱም የውስጥና የውጭ ጠላቶች ይበረታሉ
፲. በመጨረሻም መከፋፈል እና መበታተን ያስከትላል

ከላይ የተጠቀሱትን መረጃዎች ተመርኩዘን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከዚህ የሚከተሉትን ስድስት ዋና ዋና ነጥቦች ወደ ተግባር ብትለውጥ አሁን በመታየት ላይ ያሉትን ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ትቀንሳለች ተብሎ ይታመናል፡፡

፩ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቤተ ክርስቲያኗን ለማዳን ሲባል ራሳቸውን በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን ጠቅላላ እንቅስቃሴ ወቅቱን በዋጀ አካሔድ ሥራውን ሁሉ መፈጸም ማስፈጸም
፪ኛ. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መምሪያዎችንና አገልግሎቶችን በተሟላ የሰው ኃይል በማጠናከር እና አስፈላጊውን የሥራ ዝርዝር በማውጣት ሥራውን በኃላፊነት እንዲያከናውኑ ማድረግ
፫ኛ. የተሟላ የሰው ኃይል አስተዳደር ማኑዋል መቅረጽ
፬ኛ. የተሟላ የፋይናንስ ሥርዓት ማዘጋጀት
፭ኛ. በየመስኩ ተገቢውን ባለሞያ መመደብ እና ሥልጠና መስጠት
፮ኛ. ቤተ ክርስቲያኗ አሠራሯ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ውጤታማና ቀልጣፋነትን በጠቅላላው የሥራው ሒደት በየሦስት ወሩ ባልተወሳሰቡ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጭምር ያለአድልዎ በተቋማዊ መንገድ መገምገም፡፡

አባ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ
አዲስ አበባ
መጋቢት 23/2007 ዓ.ም

Advertisements

9 thoughts on “የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዐሥር ዐበይት: ጠንካራ ጎኖች፣ ድክመቶች እና የስጋት አቅጣጫዎች በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እይታ

 1. Anonymous April 5, 2015 at 10:01 am Reply

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ኢሀዲግ ለ23 ዓመታት እየፈጸመ ያለው መሰሪ ተግባር፡-
  • እቺ ነፍጠኛ ቤተክርስቲያን
  • የድህነት ፊት አውራሪ
  • ማህተሙም ቢሆን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይወልቃል! ይወልቃል!
  • ለህጻናት የሚሰጠው ቁርባን ለህጻናት የጤና ጠንቅ ነው፤
  • …..
  • …..

 2. Anonymous April 6, 2015 at 6:09 am Reply

  ሄ አስተያየት ሰጪው ምንምን ብታጉሮመርም ያው ያንተ አይደለች ስለዚህ አንገትህን አቀርቅርህ አልቅስ እንጂ ይህች ቤተ ክርስትያን የሁሉ ባለ ቤት ነው የሚቀራት የአሰራር ክፍተት ነው የህም በመልካም አባቶች አሰተዳደር እና በየቤተክርስትያኒቱ ምሁራን እና ጀግና ማህበራት በቅርብ ግዜ ለውጡ ይታል አንተ ግን አንገትህን አቀርቅረህ አልቅስ

 3. nehmiashishay April 6, 2015 at 6:12 am Reply

  ሄይ አሰተያየት ሰጪው አንገትህን አቀርቅረህ አልቅስ ቤተ ክርስትያኒቱ ግን ባላት የበለፀገ የሰው ሃይል እና የአማኞችዋ መልካም ፍቃደኝነት ከቅርብ ግዜ ሁሉ ይከናወናል እንበረታለን አንተ እና መሳዮችህ ግን አንገታችሁ አቀርቅራችሁ አልቅሱ
  በአሁኑ ወቅት የሚታዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ዋናዎቹ ጠንካራ ጎኖች ከዚህ ቀጥለን እናያለን፤

  ፩ኛ. ሃይማኖታዊም ሆነ ታሪካዊ ይዞታዋ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በጎ ገፅታ አላት፡፡
  ፪ኛ. ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት /WCC/ መሥራች በመሆኗ ከለጋሽ ድርጅቶች ጋርም የተፈጠረ መልካም ትስስር አላት፡፡
  ፫ኛ. በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ምሁራን አሏት፡፡
  ፬ኛ. በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያተረፉ የዜማና የቅኔ እንዲሁም መንፈሳዊ ኮሌጆች የምርምርና የጥናት መጻሕፍቶች አሏት፡፡
  ፭ኛ. በመንፈሳዊውም ሆነ በዘመናዊውም መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባለቤት እና የምሁራን እናትም ናት፡፡
  ፮ኛ. በከተማም ሆነ በገጠር ሰፊ የማይንቀሳቀስ መሬት ባለቤት ናት፡፡
  ፯ኛ. በገቢ መጠኗ ተወዳዳሪ የሌለው የገቢ መጠን ያላት ናት፡፡
  ፰ኛ. በቱሪዝም መስክ ያልተነካ ሀብት ባለቤት ናት፡፡
  ፱ኛ. በአካባቢ ጥበቃ እና ነባር የአድባራትና የገዳማት አፀዶችን በመትከልና በመንከባከብ በኩል መልካም ልምድ አላት፡፡
  ፲ኛ. በዩኔስኮ የተመዘገቡ እና ወደፊት የሚመዘገቡ ቅርሶችና ጥበባት ባለቤት ናት፡፡

 4. Anonymous April 6, 2015 at 11:01 am Reply

  እውነት ነው፡፡

 5. Anonymous April 6, 2015 at 1:36 pm Reply

  አሏት ፣ አሏት፣ አሏት፣ ..ናት፣ ናት ፣ ናት፣ . . . . ነገ ነበሯት ነበሯት ነበሯት . . . ነበረች ነበረች ነበረች . . . ይቺ ቤተ ክርስቲያን ሚያወራላት መች አጣችና ስለ ድፍረቴ ይቅርታና አሳቸውስ ቢሆን ለዚህ ችግር አንዱ ተጠያቂ አይደሉም ወይ? አፍንጫቸው ስር እየሆነ ስላለው ጉድ ምን የሚታይ ነገር ተናግረው እንደሳቸው እንድንል አደረጉን፤ ዝምታን ከመምረጥ ውጭ ምን ጠብ የሚል ስራን ሰሩ??? የአዲስ አበባ ሀገረስብከትን አሰራር ለማጠናከር የተደከመበት ጥናት እሳቸው ላነሷቸው አብዛኞቹ ችግሮች መፍትሔ አይሆንም ነበር ወይ? እንደቀልድ ተኮላሽቶ ሲቀር እሳቸው ምን አደረጉ?
  ‹‹እኛ ጋር ግን ሙስናን መቀነስ ብቻ ሳይኾን ማስወገድ እንደሚቻልም አረጋግጠዋል›› በእውነት በፉከራ የጠፋ ሙስና አለ ወይ? ሚቻል ከሆነ ለማጥፋት ምን ተሰራ?
  ‹‹የአራት ኪሎ ዙሪያ ከ3 – 5 ዓመት በመኖርያ ቤቶችና በኹለገብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ የማልማት ዕቅድ መያዙን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡›› አሁን የቤተ ክርስቲያን አንገብጋቢ ችግር ህንጻ ነው ወይ? ይህስ እንደ ትልቅ ስኬት ይጠቀሳል ወይ? ሰው ላይ ካተሰራ በዚህ ህንጻ ግንባታ እና ገቢ ቤ/ክ እንዴት ነው ልትጠቀም ምትችለው? ስንቶች ከሱ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ለመቆራመት ቤተ ክህነት ውስጥ አሰፍስፈው እየገቡ፤ እየተደላደሉስ አይደለም ወይ?
  <> እሳቸው እና ጓደኞቻቸው አይደሉም ወይ ሲኖዶሱ ? ታዲያ እርሳቸው በተግባር ያልጀመሩትን ራስን መስጠት የትኛው የሲኖዶስ አባል እንዲጀምር ነው ሚጠብቁት?
  ይልቅስ ወገኔ ከዚህ አይነቱ አቃቃ ጨዋታ ወተን ከኛ ሚጠበቀውን ትንሽ ነገር ብቻ እንስራ ከኛ በላይ ስለሆነው ደግሞ እንፀልይ ‹‹እርሱ በጉድለቶች ላይ ነቀፌታ አልሰነዘረም ቤተክርስቲያን የሚጎድሏትን ነገሮች ለማቅረብ ሥራ ሠራ እንጂ፡፡›› ከተባለለት የለውጥ ሀዋርያ ሐቢብ ጊዮርጊስ እንማር እርሱ ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን መምህር ሆኗታል፣ አስተዳደር ሆኗታል፣ ጸሐፊ ሆኗታል ሌላም ሌላም እኛስ ለዚች አደጋ ላይ ላለች ቤተ ክርስቲያን ምን ሆናት? ማነው ልጁን ዲያቆን ሊያደርግ ሚወድ? እሱ ቀርቶ ማነው ራሱን በንጽሕና ሕይወት እየመራ አርዐያ መሆን የቻለ? ኡፍ !!!!! ሌሎች ስንት እጥፍ ይቺን ቤ/ክ ለማጥፋት እየደገሱ እንደሆነ ማሰብ እና መረዳት እንዴት ተሳነን? ብቻ ሁላችን ከወሬ ወተን እኔ ለቤተ ክርስቲያኔ ምን ሰራሁ??????????????????????????????
  ለማለት ያብቃን

  • Anonymous April 11, 2015 at 5:23 am Reply

   Great View

 6. Anonymous April 7, 2015 at 7:38 am Reply

  አሁን አሁን በአባቶች ላይ በተናጠልም ሆነ እንደተቋም የማየው ጥሩ ነገር አለ፡፡አንደኛ በቤ/ክ ያለውን ችግር አንጥሮ ለማወቅና ችግሩን ለማመን አለማመንታታቸው ነው፡፡ሁለተኛ መፍትሔ የሚሉትን ነገር ለመናገርና ለመጻፍ በየአደባባዩ መድፈራቸው ነው፡፡እነዚህ 2 ነገሮች የመፍትሔው መቅድም ናቸው፡፡ብቻቸውን ግን መፍትሑ አይደሉም፡፡ምክንያቱም መፍትሔ በአንድ ወገን መልካም ፍላጎት ብቻ አይመጣም፡፡ቤ/ክ የአንድ ወገን ስላይደለች፡፡

  ስለዚህ ቀጣዩን መፍተሄ ለመሻት መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር የሚሉት ቃላት ያስፈልጉናል፡፡በብዛት ያስፈልጉናል፡፡እየተደማመጥን አይመስለኝም፡፡የሚያደማምጠም ሚዲያ የለንም፡፡የሚያራርቅ ግን ሞልቶናል፡፡የማያደማምጥ ብዙ አለን፡፡ሚዲያችን አባትን ከልጅ ለማቀራረብ፣ለማናበብ፣ለማስተማመን፣ለማከባበር፣ለማፋቀር የሚጥር አይደለም፡፡የአንድ ወገንን (የአባቶችንና የቤተክሕነትን) ድክመት ብቻ በማጉላት የተጠመደ ነው፡፡እንደ እውነቱ ግን የቤ/ክ ጥንካሬዎች ሁሉ ከቤተክሕነት እንዳልመነጩት ሁሉ ድክመቱም ከቤተክሕነትና ከሊቃነ – ጳጳሳት ብቻ እንደሚመነጭ አድርገን ማሰባችን ስህተት ነው፡፡(ውስጣዊ) ድክመቱ፡-

  ከምዕመኑም፣ከሰ/ተማሪውም፣ከማኅበራትም፣ከካሕናትም፣ከቤተክሕነትም፣ከሊቃነ – ጳጳሳትም፣ከሊቃውንትም፣ከኦርቶደክሳዊ ዓለማዊ ምሁራንም ከሁሉም ነው፡፡ስለዚህ ሁሉም ተባብሮ ካልተነሳና የራሱን ኃላፊነት በየፊናው ለመወጣት ካልጣረ በቀር መፍትሄ ከላይ ብቻ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋሕነት ነው፡፡

  ሚዲያችን ሐራን ጨምሮ በዚህ ረገድ ተጫወቱት ሚና በዋናነት ወጣቱ ወደ አንድ ወገን ብቻ ጣት ቀሳሪ እንዲሆንና የቤተክሕነትን ድክመት በመዘርዘር ለራሱ ቅድስና እንዲሰማው ማድረግን ነው፡፡ወጣቱን እጓለማውታ የመሆን ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ የሚካሄደው ዘመቻ ከቶም ገንቢነቱ አይታየኝም፡፡

  የባለፈው ጥናት ያልተተገበረው በሌላ በማንም አይደለም፡፡በራሳችን አጥኚው ወገንን ነን በምንል ሰዎች ድክመት ነው፡፡የጥናቱ ሂደትም ሆነ የሥልጠናው አሰጣጥ መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር የሚሉ ሐሳቦችን ቁብ አልሰጣቸውም፡፡በውድም በግድም ይተገበራል የሚል እጅግ መሳጭ ያልሆነ አቀራረብ ነው የነበረው፡፡ጥናቱ አሳታፊ አልነበረም፡፡እርግጥ ነው ምዕመናንንም ሆነ ማኅበራት በቤ/ክ ያላቸው ድርሻና ወሳኝነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ያ ማለት ግን ካሕናት አይመለከታቸውም ማለት አይደለም፡፡አንድ ተቀጣሪ ብቻ ላመል ጣል አድርጎ የካሕናትና የሥራ ድርሻ የሚገለባብጠውን ጥናት ካልተቀበላችሁ በቃ ሙሰኛ ናችሁ ብሎ ያን ሁሉ ውርጅብኝ ማውረድ ጥናቱን ይበልጥ ጎዳው እንጅ አላሳካውም፡፡ምክንያቱም ከጥንስሱ መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር የሚሉ ቃላት አልነበሩም፡፡ካሕናትን የመናቅ ቢጤም ይመስል ነበር፡፡ራስን አንጽቶ የተለየ ሀሳብ ያሰማውን ሁሉ የማርከስ ዘመቻ ነበር፡፡ጥያቄ ያነሱትን ለይቶ የማሳደድ ዘመቻ ነበር፡፡ሱ ማሳደድ ግን ሌላ መልሶ የሚያሳድድ ግሩፕ ፈጥሮ ምን ያህል ወደ እርስ በርስ መሳደድ እንደሄድን ያለፈው አመት ከ6 ወር ምስክር ነው፡፡

  ስለሆነም በእርምጃችን ሁሉ፡- መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር የሚሉት ሐሳቦች አይለዩን፡፡በባዶው የራሳችንን ቡድናዊ ፍላጎት በጉያችን ሸሽገን፣በማን አለብኝነትና ከእኔ በላይ ለቤ/ክ አሳቢ ለሳር ብሂል ታጅረን መታበይ ወርቃማ ጊዜያችንን እየበላው መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር የሚሉ ሐሳቦች ተዘነጉ፡፡በተለይ ዘመናዊ ትምህርት ተማርን የምንል የቤ/ክ ልጆች የካሕናትንና የጳጳሳትን በደል በመዘርዘር ብቻ ራሳችንን ለማጽደቅ የምናደርገው ሩጫ አትራፊ አይደለም፡፡ይበልጥ ከካሕናቱም ከተቋሙም እያራራቀን ነው፡፡መማራችንን ለበጎ እናውለው፡፡ጣት ለመቀሰርማ፤ለማስተሀቀርማ ከዚያኛው ወገንም(ከእነ ስም አይጠሬ) ሞልተዋል፡፡
  መረጃን እንደወረደ እየተቀበልን በአካልም በሥራም የማናውቃቸውን ሰዎች ማሳደዱ ቢበቃ መልካም ነው፡፡ምክንያቱም አትራፊ አይደለም፡፡ለመፍቴው ግን አልመሽም፡፡ደግሞም አይመሽም፡፡መቼውኑም!!ምክንያቱም የቤ/ክ መስራች የማይመሽበት ነው!!

  • Anonymous April 11, 2015 at 6:59 am Reply

   ሰላም ወንድሜ አንዳንድ ሀሳቦችህ ላይ ብስማማም ያልተዋጡልኝን ላንሳ በጽሁፍህ ላይ ካነሳህው ሀሳብ አንዱ
   ‹‹የባለፈው ጥናት ያልተተገበረው በሌላ በማንም አይደለም፡፡በራሳችን አጥኚው ወገንን ነን በምንል ሰዎች ድክመት ነው፡፡የጥናቱ ሂደትም ሆነ የሥልጠናው አሰጣጥ መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር የሚሉ ሐሳቦችን ቁብ አልሰጣቸውም፡፡በውድም በግድም ይተገበራል የሚል እጅግ መሳጭ ያልሆነ አቀራረብ ነው የነበረው፡፡ጥናቱ አሳታፊ አልነበረም፡፡›› የሚለው ሲሆን የመጀመርያው ‹‹ያጥኚው ወገን ነን የምንል ሰዎች›› ስትል ምን ለማለት ፈልገህ እንደሆነ ብታብራራው መልካም ነበር ምክንያቱም ወረድ ሲል ያለው ሀሳብ ከዛ ስለሚለይ ነው፡፡

   ሁለተኛው መቀራረብ፣ መተማመን …ቁብ አልሰጣቸውም ላልከው ከማን ጋር? ብዬ ልጠይቅህ ወደድኩ በርግጠኝነት ልነግርህ ምፈልገው ግን ጥቅማችን ይነካብናል ብለው ካሰቡ ሰዎች ጋር አይነካባችሁም ብሎ መተማመን ከባድ ነው ከሌሎቹ ማለትም ውስጣቸው ችግር ከሌለባቸው ምዕመናን እና ካህናት ጋር ግን ይህ ችግር እንዳልነበረ አስረግጬ ልነግርህ እወዳለሁ ምክንያቱም በአንዱ የገለጻ መርሀግብር ላይ እያነቡ በእድሜያቸው ይህን የቤተክርስቲያን ትንሣኤ ለማየት በመብቃታቸው መደሰታቸውን የገለጹ ነበሩ ይሄ ታሪክ የሚያወጣው የተቀረፀ ሰነድ ነው፡፡

   ሌላው ‹‹ጥናቱ አሳታፊ አልነበረም›› ላልከው አበክሬ ልነግርህ ምፈልገው ነገር ቢኖር እንደውም ከሚገባው በላይ ወርዶ ያሳተፈ ጥናት እንደሆነ በማስረጃ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ 1ኛ/ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት አጥኚዎቹን የተመረጠው አጥቢያ ላይ ካሉ የሰበካ ጉባኤ አባላት ነው ይህም አጥኚዎቹ የጉዳዩ ባለቤቶች ናቸው ማለት ነው ስለዚህ ከውጪ እንደመጣ አጥኚ አካል ሳይሆን ሲኖሩበት ያዩትን ችግር ነው መፍትሄ ያቀረኑት 2ኛ አንድ ተቋም ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ነክ ጉዳዮችን ሲያጠናም ሲያስተገብርም አስተዳደር ላይ ያሉ አካላት በሙያ አማካሪዎቻቸው (Technical Advisors)ተጠንቶ ያመኑበትን በቀጥታ ይተገብራሉ እንጂ እታች ላይ ያለውን የመጨረሻ ሰራተኛ እንዲህ ላደርግ ነው እንዴት ይመስልሀል እያሉ አያማክሩም የድርጅቱ አስተዳደሮች (management Level) ከታመነበት ይተገበራል!! ይሔኛው ምንም እንኳ በላይኛው የቤተ ክርስቲያኗ አስተደዳደር ቢታመንበትም በጣም አሳታፊ ከመሆኑ የተነሳ እታች ያሉ አካላትን ሁሉ ለማወያየት ወርዷል በዚህ ብቻ አልበቃም ጥናቱ ከተሳታፊዎቹ የተሰጡትን ገንቢ አሰተያየቶች ጨምሮ ተሻሽሎ ነው በሰነድ ለሀገረ ስብከቱ ያስረከቡት ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አይነት አሳታፊነት ይኑር?

   ‹‹የካሕናትና የሥራ ድርሻ የሚገለባብጠውን ጥናት. . . ›› ‹‹ካሕናትን የመናቅ ቢጤም ይመስል ነበር›› ላልከው ይሄ ያንተ አመለካከት የቱጋ እንዳለ ሚያሳይ ነው፡፡ ወይ ጥናቱ አልገባህም፤ ወይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወቅታዊ ሁኔታ አታውቅም ፤ ወይም ስለ ጥናቱ የደረሰህ መረጃ ሆን ብለው ሊያፈናቅሏቹህ ነው አይነት መረጃ ሲበትኑ ከነበሩ አካላት ነው፤ አልያም ደግሞ አውቀህ የተሳሳተ መረጃን ለማድረስ ፈልገህ ነው ይህን ህሊናህ እና ስለ ጥናቱ ገለጻ ሲደረግ የነበሩ አካላት እንዲፈርዱት እተወዋለሁ፡፡

   በመጨረሻም ልልህ ምወደው ግን ‹‹መቀራረብ፣መናበብ፣መተራረም፣መማማር፣መከባበር፣መተማመን ፣መፋቀር›› እያልክ ደጋግመህ ላነሳህው ግን አዎ ያስፈልጉናል ግን እነዚህ ሚያስፈልጉት ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን በቅን ከሚያስቡ ሰዎች ጋር መሆኑን ልነግርህ እወዳለሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን በአላማ ለማጥፋት ከሚሰሩ ሰዎች ጋር ግን እንዴት መናበብ እና መቀራረብ እንደሚቻል አይገባኝም መስመራችን የተለያየ ነውና ሌላው ደግሞ እነዚህ በተግባር የሚኖሩ እንጂ እንደመፈክር ስለተጻፉ የሚመጡ አይደሉም መፋቀር አለብን እያለ የሚሰብክ ሰው በጽሑፉ አንድ ጥግ ይዞ ፀብን ከሰበከ መፈክር ብቻ ይሆኑበታል፡፡

   ከዛ በተረፈ ስለምንም ሳይሆን ነገ ለልጆቻችን ስለምናስረክባት ስለ ቤተ ክርስቲያን ጥቅም ብለህ ፃፍ ፣ አገልግል፣ ስራ እንከሌን ለመደገፍም ሆነ እነከሌን ለመቃወም አይሁን ያኔ ማንም ሁን ከየትም ና አንድ አላማ ባንድ መስመር ያስጉዘናል ፡፡ ስለሁሉም ሳላውቅህ በመጻፌ ይቅርታ ስለየዋሀን ምዕመናን ግን ሚዛናው መረጃ እንዲኖር ስል ብቻ ጻፍኩ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: