የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት: ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ ለግለሰቦች ትርፍ ይሠራል የተባለውን የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አስተዳደር አስጠነቀቀ

Gerji Debra Genet St. George church02

በደብሩ አስተዳደር እና በሕገ ወጥ ነጋዴዎች የጥቅም ትስስር የቤተ ክርስቲያንን መብትና ምጣኔ ሀብት በሚጎዳ አኳኋን የውል ግዴታዎችን በማፍረስ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው በተጋነነ ዋጋ የተከራዩት የደብሩ መጋዘኖች/ቦታዎች/ በከፊል

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃቀምና የኪራይ ተመን ጉዳዮችን በመፈተሽ የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ፖሊሲ ለማውጣት የሚያስችል ዝርዝር የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በቋሚ ሲኖዶስ ተወስኖ በፓትርያርኩ በተሰጠው መመሪያ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ በወርኃ ታኅሣሥ መባቻ የጀመረውን ጥናት እንደቀጠለ ነው፡፡

ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ እና ከሀገረ ስብከቱ በተውጣጡ አምስት የሥራ ሓላፊዎች የተቋቋመው ኮሚቴው በድርጊት መርሐ ግብሩ መሠረት ለጥናቱ ከለያቸው 69 የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት መካከል በሦስት ወራት ቆይታው ከግማሽ በላይ የኾኑትን ሸፍኗል፤ ለተልእኮው ግብዓት ሊኾኑ የሚችሉ መረጃዎችንም በበቂ ኹኔታ እያሰባሰበና እያደራጀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

መረጃዎቹ ገዳማቱና አድባራቱ የአምልኮ፣ የመካነ መቃብር እና የልማት በሚል ከተረጋገጡላቸው ይዞታዎቻቸው መካከል በልማት ቦታቸው ውስጥ የተገነቡ የገቢ ማስገኛ ተቋማት የተከራዩበትን ዋጋና የተከራዩበትን ዘመን ጨምሮ የኪራይ ውሎችን አግባብነት በሰነዶች ምርመራና በግምገማ ስልቶች በመፈተሽ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በዘላቂነት የሚደግፉበትን አሠራር ለመቀየስ እንደሚያገለግሉ አመልክቷል፡፡

ኮሚቴው እስከ አኹን ከአደረገው ማጣራት የተገኙት መረጃዎች፣ የኪራይ ውሎች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለግለሰቦች የተጋነነ ትርፍ በሚያመች መልኩ በጥቅም ትስስር እንደሚዘጋጁና በዚኽም ሳቢያ በከፋ መልኩ ለምዝበራ የተጋለጠው የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት በአሳዛኝ አደጋ ላይ እንደኾነ እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡ ከእኒኽም የኪራይ ውሎች ጥቂት የማይባሉት ከሀገረ ስብከቱና ከሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አካላት ዕውቅና እና የወሳኝነት ሚና ውጭ የተፈጸሙ እንደኾኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሰንደቅ ጋዜጣ በዛሬ ዕትሙ፣ በደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በአስተዳደሩና በሕገ ወጥ ነጋዴዎች መካከል መኖሩ በተረጋገጠው ግልጽ የጥቅም ግንኙነት ምክንያት የውል ግዴታዎችን በመጣስ ለሦስተኛ ወገን እየተላለፉ እጅግ በተጋነነ ዋጋ የተከራዩት የደብሩ ይዞታዎች በአደጋ ውስጥ እንደሚገኙ ያስነበበው ዘገባ አንድ ተጨማሪ አስረጅ ነው፡፡

ለራስ አገዝ ልማት እንዲውል ከታሰበው 65‚000 ካሬ ሜትር ይዞታ ውስጥ ከ500 – 1000 ካሬ የሚኾኑ በርካታ ቦታዎች ከአካባቢው የገበያ ዋጋ በታች በካሬ ሜትር ብር 2 – 10 ሒሳብ ለመጋዘን፣ ለወፍጮ ቤት፣ ለጋራዥ፣ ለብሎኬት ማምረቻና ለሌሎችም የንግድ ተቋማት ያለጨረታ እንደተከራዩ በኮሚቴው ተገልጧል፡፡ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ግለሰቦች ሀብት የሚያፈሩበትና መሬቱን ለግላቸው ማድረግ የሚችሉበት ኹኔታ ተፈጥሯል፤›› ያለው ኮሚቴው፣ አንዳንዶችም የንግድ ዘርፋቸውን በመቀየር ወደ ኢንዱስትሪነት የሚስፋፉበት ኹኔታ እንደሚስተዋል አስታውቋል፡፡

የደብሩ አስተዳደር ሸንሽኖ ያከራያቸውን ቦታዎች መከታተልና መቆጣጠር እንዳልቻለ ኮሚቴው ጠቅሶ፣ ግለሰብ ነጋዴዎች እጅግ የተጋነነ ትርፍ ሲያገኙ ዝም ብሎ የሚመለከት ሓላፊ ቅን ነው ብሎ ለመገመት እንደማይቻል አሳስቧል፡፡ ቀደም ሲል በስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ላይ እንደ አደረገው ኹሉ፣ የጥናቱን መጠናቀቅ ሳይጠብቅ ከወዲኹ በአፋጣኝ ሊታረሙ ይገባል ባላቸው ጉዳዮችም ‹‹በሕጋዊ ሽፋን በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየፈጸመ ነው፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ ለግለሰብ ነጋዴዎች ትርፋማነት ሌት ተቀን እየሠራ መኾኑን አረጋግጫለኹ›› ያለው የገርጂ ደ/ገነት ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአ/አበባ ሀ/ስብከት በኩል ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው አድርጓል፡፡ /ሙሉ ዜናውን ይመልከቱ/


  • በሕገ ወጥ የኪራይ ውሎች የደብሩ 65‚000 ካሬ ሜትር ይዞታ ለአደጋ ተጋልጧል
  • የሦስተኛ ወገን ተከራዮች ለግለሰቦች የሚከፍሉትን ለደብሩ እየከፈሉ እንዲሠሩ ታዝዟል
  • አለቃው እና ጸሐፊው የቤተ ክህነቱን ልኡካን ‹‹በማንቋሸሽና በመሳደብ ለዱላ ተጋብዘዋል››
  • በጥናት ኮሚቴው አመልካችነትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት አሳሳቢነት በሀገረ ስብከቱ የእርምት መመሪያና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የአጥቢያ አስተዳደሮች ሰባት ደርሰዋል

(ሰንደቅ፤፲ኛ ዓመት ቁጥር ፬፻፺፮፤ ረቡዕ መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

Gerji Debra Genet St. George church side view

‹‹ከቤተ ክርስቲያን መብትና ጥቅም መከበር ይልቅ ለግለሰቦች ትርፋማነት ሌት ተቀን ይሠራል›› በተባለው በደብሩ አስተዳደር ያለጨረታ እየተሸነሸኑ ከአካባቢው ዋጋ በታች በሚከራዩ ቦታዎቹ 65‚000 ካሬ ሜትር የልማት ይዞታው በአደጋ ውስጥ የሚገኘው የገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ በቤተ ክርስቲያን ንብረት በሕገ ወጥ አሠራር ለመክበር ለሚሯሯጡ ግለሰቦች ከለላ ሰጥቷል የተባለው የገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱና አስቸኳይ የእርምት/ማስተካከያ መመሪያዎችን ማስተላለፉ ተገለጸ፡፡

ደብሩ ከጠቅላላ ይዞታው ላይ 65‚000 ካሬ ሜትር ቦታውን ለልዩ ልዩ የልማት ሥራ እንዲውል በሚል በውል ማከራየቱን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጠቅሷል፡፡ ይኹን እንጂ ጥቂት የማይባሉት ተከራዮች ከደብሩ ጋራ የገቡትን የውል ስምምነት በመጣስ እጅግ በተጋነነ ዋጋ ለሦስተኛ ወገን በማስተላለፍ በቤተ ክርስቲያን ቦታ ሕገ ወጥ ትርፍ እያጋበሱበት እንደሚገኙ ገልጧል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ አፋጣኝ ማስተካከያ ያስፈልጋቸዋል በሚል በሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ ከተጠቀሱት የኪራይ ውሎች መካከል÷ አቶ ወንድሙ ቢያድግልኝ እና ወ/ሮ ፀሐይ ምትኩ የተባሉ ኹለት ግለሰቦች፣ ከደብሩ የተከራዩዋቸውን መጋዘኖች የአከራይ ተከራይ የውል ስምምነት በመጣስ የሄኒከን ኩባንያ ወኪል ለኾነው ናዩ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በማስተላለፍ ከአራት እስከ ስምንት ዕጥፍ በኾነ ወርኃዊ ክፍያ እጅግ የተጋነነ ትርፍ እያገኙበት እንዳለ ተመልክቷል፡፡

አቶ ወንድሙ የደብሩን 1000 ካሬ ሜትር ቦታ/መጋዘን/ በካሬ ብር 6.00 ሒሳብ ለዘጠኝ ዓመት የተከራዩት በሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም. ሲኾን ያለአከራዩ የጽሑፍ ፈቃድ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠትንና ማከራየትን የሚከለክለውን የደብሩን የአከራይና ተከራይ ውል በመጣስ ለናዩ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በካሬ ብር 2500 በማከራየት በወር ብር 30‚000 የሚያገኙበትን የውል ስምምነት በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ፈጽመዋል፡፡ ይህም በወር የብር 24‚000 ገቢ ባለቤት እንደሚያደርጋቸው ታውቋል፤ በዚኹ ሕገ ወጥ የመጋዘን ኪራይ ውልም የስድስት ወራት ብር 180‚000 ቅድመ ክፍያ እንደተቀበሉበት ተረጋግጧል፡፡

ኹለተኛው ተከራይ ወ/ሮ ፀሐይ ምትኩ ከደብሩ በብር 6.00 ሒሳብ ለዘጠኝ ዓመት በውል የተከራዩትን 1000 ካሬ ሜትር ቦታ/መጋዘን/ ለተጠቀሰው ኩባንያ ወኪል ናዩ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በካሬ ብር 4‚583 ሒሳብ በሕገ ወጥ መንገድ በማስተላለፍ በወር ብር 55‚000 ገቢ የሚያገኙ ሲኾን ይህም የብር 49‚000 ወርኃዊ ገቢ ባለቤት እንደሚያደርጋቸው ተረጋግጧል፡፡

ይኸው የውል ግዴታዎችን የሚጥስ አሠራር ‹‹በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ በደል ነው›› ያለው ሀገረ ስብከቱ፣ የደብሩ አስተዳደር ዝም ብሎ መመልከቱ አግባብነት እንደሌለው በመግለጽ ለአስተዳደሩ የተለያዩ መመሪያዎችን አስተላልፏል፡፡

ኹለቱ ተከራዮች ከደብሩ ጋራ የገቡትን የውል ስምምነት ለሦስተኛ ወገን በማከራየት የጣሱ በመኾናቸው ውላቸው እንዲቋረጥ ሀገረ ስብከቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ በምትኩ ለአንዱ መጋዘን ብር 30‚000፣ ለሌላኛው መጋዘን ብር 55‚000 ለተከራዮቹ ሲከፍል የቆየው ናዩ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ከደብሩ ጋራ በቀጥታ ውል እንዲገባ ተደርጎ ለግለሰቦቹ ሲፈጽም የቆየውን ክፍያ ለደብሩ እየከፈለ ሥራውን እንዲቀጥል በማድረግ ማስተካከያ እንዲሰጥበት አዝዟል፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን ሌሎች በሦስተኛ ወገን የተከራዩ ካሉም ማስረጃዎቻቸውን እያቀረቡ ከደብሩ ጋራ ውል በመግባት ለአከራዮቻቸው የሚከፍሉትን ለደብሩ እየከፈሉ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ እንዲደረግ የደብሩን አስተዳደር አሳስቦታል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ‹‹እጅግ በጣም በአስቸኳይ›› ተፈጻሚ እንዲኾኑ ለደብሩ ያስተላለፋቸው መመሪያዎች፣ የሀገረ ስብከቱን ገዳማትና አድባራት የመሬት፣ የሕንጻና የመካነ መቃብር ኪራይ ጉዳዮችን በማጥናት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ የተቋቋመው ኮሚቴ ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ያቀረበውን ማሳሰቢያ መነሻ ያደረገ እንደኾነ ታውቋል፡፡

ኮሚቴው፣ የጥናቱን ውጤት ተከትሎ የሚደረገውን የአሠራር ለውጥ ሳይጠብቅ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት የሚያረጋግጥ አፋጣኝ ምላሽ›› እንደሚሻ በመግለጽ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባቀረበው ማሳሰቢያው፣ ለኹለት ተከታታይ ቀናት የማጣራት ተግባሩን በሚያከናውንበት ወቅት የደብሩ አለቃና ጸሐፊ ስለተጋነነ ኪራይና የቦታ ሽያጭ ለሚጠየቁት ጥያቄ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ‹‹በማንአለብኝነት መንፈስ ልኡኩን ሲያንቋሽሹ፣ ሲሳደቡና ለዱላ ሲጋበዙ›› እንደነበር ጠቅሷል፡፡ አለቃውና ጸሐፊው በዚኽ ድርጊታቸው በገሃድ የሚታይ አሠራራቸውን በመካድ ከሓላፊዎች የማይጠበቅ ተግባር እንደፈጸሙ የገለጸው ኮሚቴው አክሎም፣ በአጥኚ ኮሚቴው ስም በበላይ አካላት አመራር እንደተሰጠው በማስመሰል በደብሩ አስተዳደር ያለአግባብ ተጽፏል ስላለው ደብዳቤም አውስቷል፡፡

በኮሚቴው እንደተገለጸው ደብዳቤው በይዘቱ፣ ቡድኑ በደብሩ ያካሔደውን ማጣራት አጠናቅቆ በተመለሰ ማግሥት የተጻፈ ሲኾን ከደብሩ ካሬውን በብር 6.00 ሒሳብ በመከራየት በብር 2‚500 እያከራዩ ለሚጠቀሙት ግለሰብ ‹‹የውል ግዴታ እንዲከበር ስለማስጠንቀቅ›› በሚል ሽፋን መጋዘኑን ለሦስተኛ ወገን ማከራየታቸውን የበላይ አካል ስለደረሰበትና ደብሩ ውሎችን እያስከበረ ስላልኾነ ውሎችን እንዲያስከብር መመሪያ እንደተሰጠው በማስመሰል የሚያስጠነቅቅ ነበር፡፡

ደብዳቤው፣ የሦስተኛ ወገን ተከራዮች ለኮሚቴው ግልጽ መረጃ በመስጠታቸው ምንም ዐይነት ጫና በደብሩ አስተዳደር ይኹን በአከራዮቻቸው እንዳይደርስባቸው የደብሩ አለቃና ሌሎች ሓላፊዎች በተገኙበት የተላለፈውን መመሪያ የሚጥስ እንደኾነ ኮሚቴው አመልክቷል፤ አያይዞም በደብሩና በሕገ ወጥ ነጋዴዎቹ መካከል ያለውን ግልጽ የጥቅም ግንኙነት የሚያረጋግጥ በመኾኑ ‹‹ተከራዩ ግለሰብ ለናዩ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ለኹለት ዓመት ያከራዩትን ውል ለማፍረስ የሚያስችል ትልቅ ማስረጃም ነው፤›› ብሏል፡፡ በበላይ አካል ስም የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ እንዲሻርና የደብሩ አስተዳደር ዳግመኛ መሰል ሕገ ወጥ ደብዳቤ በመጻፍ በቤተ ክርስቲያን ንብረት ለመክበር የሚሯሯጡ ወገኖችን ከመጥቀም እንዲታቀብ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በኩል ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ጠቅላይ ጽ/ቤቱን ጠይቋል፡፡

Gerji St George church
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በሀገረ ስብከቱ ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በቀን 26/6/07 በቁጥር 2896/357/2007 በጻፈው ማሳሰቢያ÷ የደብሩ ደብዳቤ ለሕገ ወጥ አከራዩ ከለላ የሚሰጥ እንደኾነ በመጥቀስ አስተዳደሩ ያለአገባብ በጻፈው ደብዳቤና ‹‹ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ ለግለሰብ ነጋዴዎች ትርፋማነት ሌት ተቀን ይሠራል›› በሚል ለተዘረዘሩት ሕገ ወጥ ግንኙነቶቹ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠውና አፈጻጸሙ እንዲገለጽለት አስታውቋል፤ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም በማሳሰቢያው መሠረት ለደብሩ አስተዳደር የማስተካከያ መመሪያዎቹን ያስተላለፈ ሲኾን ተገቢ አይደሉም ለተባሉት አካሔዶቹም ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ታውቋል፡፡

Gerji Debra Genet St. George church04
በታኅሣሥ ወር መባቻ የተጀመረው የሥራ ሓላፊዎቹ ኮሚቴ ጥናት፣ በእስከአኹኑ ክንውኑ ለተልእኮው ከለያቸው 69 ገዳማት እና አድባራት መካከል 37ቱን የሸፈነ ሲኾን አብዛኞቹ ለማለት በሚያስችል አኳኋን በመሬት፣ በሕንጻ እና በመካነ መቃብር አጠቃቀም እንዲኹም ኪራይ የቤተ ክርስቲያኒቷን ጥቅምና መብት አሳልፎ የሚሰጥ አሠራር እንደተስተዋለባቸውና ከሰባት ለማያንሱትም አስቸኳይ የማስተካከያ መመሪያ እንዲሰጣቸው ማድረጉ ተገልጧል፡፡ ጥቅል ውጤቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንደሚቀርብ የሚጠበቀው የኮሚቴው ጥናት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የመሬት ይዞታ አጠቃቀምና የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ተመን ፖሊሲ ለማውጣት እንደ ግብዓት እንደሚያገለግል ተመልክቷል፡፡

Advertisements

5 thoughts on “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት: ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ ለግለሰቦች ትርፍ ይሠራል የተባለውን የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አስተዳደር አስጠነቀቀ

  1. sim March 19, 2015 at 10:15 am Reply

    የቤተክርስቲያንን ጥቅም አሳልፈዉ ለሚሰጡ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች እስከመቸ ነዉ ማስጠንቀቂያ ምናምን እየተባለ ጊዜ የሚሰጣቸዉ; ለምን የማባረር ርምጃ አይወድባቸዉም እስከመቸስ ነዉ ከላይ እስከታች ተደራጅተዉ ቤተክርስቲያኑዋን የሚግጡዋት; ይህ ማናለብኝነትና ትዕቢት ከየት የመጣ ነዉ፤፤ እነዚህስ ናቸዉ ቤተክርስቲያኑዋን መርተዉ በአርአያነት ምዕመኑን ወደ ቅድስና የሚያደርሱት፤፤ ዉስጥን ያደማል

  2. Anonymous September 21, 2015 at 5:24 pm Reply

    we understand our church problems very well now a days .

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: