ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅምና በሚያስተች አኳኋን ለሦስተኛ ወገን የሚተላለፉ የአድባራት የንግድ ማዕከላት ኪራይ አሳሳቢ ኾኗል

Beauty Salon at the gate of Bole Bulbula Medhanialem churchgoceries at the gate of Bole Bulbula Medhanialem churchBar and Resturant around St. Rufael Churchበምስሉ የሚታዩት የቢራ ማስታወቂያዎችን የያዙ የመጠጥ ግሮሰሪዎች፣ የውበት ሳሎን፣ ባርና ሬስቶራንት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለምንና የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል አብያተ ክርስቲያንን ደጀ ሰላም፣ ቅጥርና ገረገራ ይዘው የሚታዩ የንግድ ማዕከላት ናቸው፡፡

በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ፲፪ ንኡስ አንቀጽ (፯) እና (፰) በቤተ ክርስቲያን ስም ውል ስለመዋዋል በተለይም በቋሚ ንብረቶችና ግምታቸው ከፍተኛ ስለኾኑ የኪራይ ውሎች የተደነገገውን በመተላለፍ የቦታውን ዋጋ በአገናዘበ አኳኋን በሕጋዊ መንገድ ከአለመከራየታቸውም በላይ በተከራይ አከራይ ለሦስተኛ ወገን በከፍተኛ ጥቅም የተላለፉት እኒኽ የንግድ ማዕከላት፣ በቤተ ክርስቲያን መሳለሚያና መዳረሻ በሮች ለአገልግሎት መዋላቸው ምእመኑን እያሳዘነውና እያስቆጣው ይገኛል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ውስጥና ዙሪያ የሚተከሉ የልማት ተቋማትና የንግድ ማእከላት÷ ሐዋርያዊ አገልግሎትዋን በዘላቂነት የሚደግፍ ቋሚ የገቢ ምንጭ የመፍጠር፣ የካህናቷን የኑሮ ኹኔታ የማሻሻል፣ የምግባረ ሠናይ ተግባራትን በስፋት የማከናወንና ከልመና የምንወጣበትን ስልት የመቀየስ፤ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችንን የፋይናንስ አቅም በማሳደግ በራሷ ምእመናን ልማት ላይ የተመሠረተ ሉዓላዊ ክብሯን ለመጠበቅ ተግቶ የመሥራት ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የፕሮጀክቶቹ መርሖዎችም፡- ሥርዐትና ትውፊት የጠበቁ ንዋያተ ቅድሳትን፣ የኅትመትና የጥበበ እድ ውጤቶችን፣ የስጦታና የግንባታ ዕቃዎችን ለማምረትና ለማከፋፈል፣ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን በዕውቀት የበለጸገና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ቅድሚያ መስጠት፤ የማኅበረሰቡን ጥቅምና ሀገራዊ ማንነት ታሳቢ ማድረግ፤ ለብዝሐ ሕይወት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከት፤ የምርትና የአገልግሎት ዋጋ ፍትሐዊነትና ምክንያታዊነት ሊኾን ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ደጅ፣ ቅጥርና ገረገራ÷ የሰላም ደጅ፣ የሰላም በር – ደጀ ሰላም ነውና፡፡


(ሰንደቅ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፬፻፺፪፤ የካቲት ፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት ለግለሰቦች የሚያከራዩዋቸው በርካታ የንግድ ማዕከላት/ሱቆች/ ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅምና በሚያስተች አኳኋን ለሦስተኛ ወገን በከፍተኛ ጥቅም እየተላለፉ (ቁልፋቸው እየተሸጠ) እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

በሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት ይዞታ ውስጥ የሚገኙ መሬቶችንና ሕንፃዎችን ኪራይና አጠቃቀም በመፈተሽ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ጥቅም የሚሰጡባቸውን መንገዶች የሚያመቻች ጥናት ለማቅረብ የተቋቋመው ኮሚቴ እያካሔደ ባለው የማጣራት ሥራ፣ ግለሰቦች ከአድባራቱ የሚከራዩዋቸው አብዛኛዎቹ የንግድ ማእከላት/ሱቆች/ ‹‹እጅግ በጣም አሳዛኝ በኾነ መንገድ የተከራዩና ለሦስተኛ ወገን የተሸጡ›› ሲኾን የመካነ መቃብር ይዞታም እየተቆረሰ ከዓላማው ውጭ መዋሉ እንደተረጋገጠ ተመልክቷል፡፡

በተመረጡ 69 አድባራትና ገዳማት ላይ የጀመረውን ጥናት በድርጊት መርሐ ግብሩ መሠረት እያከናወነና ግብዓት ሊኾኑ የሚችሉ መረጃዎችንም እያሰባሰበና እያደራጀ እንደሚገኝ የገለጸው ኮሚቴው፣ ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአቀረበው ማሳሰቢያ÷ አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ያላቸው አሳሳቢ ችግሮች በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኩል መመሪያና ማስተካከያ እንዲሰጥባቸው ጠይቋል፡፡

የጥናቱን ውጤት ተከትሎ የሚመጣውን የአሠራር ለውጥና ማስተካከያ ሳይጠብቁ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር አፋጣኝ መመሪያ ሊሰጣቸው ይገባል ከተባሉት አድባራት መካከል የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሚሳለምበት የደብሩ ዋና መግቢያ በር ግራና ቀኝ፣ የመጠጥ ግሮሰሪዎችና የሴቶች የውበት ሳሎን ተከፍተው የተከራዩ ሲኾኑ ተከራዩ ደግሞ ለሦስተኛ ወገን በከፍተኛ ጥቅም አከራይቷቸዋል፡፡ ይህም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ሥርዐት አንጻር የማይደገፍና እምነቱን የሚያስተች ከመኾኑም በላይ ምእመኑን ለቁጣ እንዳነሣሣው ተገልጧል፡፡

የሱቆቹ ውሎች ተቋርጦ ቦታው ነጻ ይደረግ ዘንድ መመሪያ እንዲሰጥ የጠየቀው ኮሚቴው፣ ደብሩ ባለው ሰፊ ይዞታ ውስጥ የሚገኙ ባዶ ቦታዎች ሕጋዊ ባልኾነ አግባብ ሊከራዩ የሚችልበት ዕድል እንደሚኖር በማሳሰብ ጥናቱ እስኪጠናቀቅና ተለዋጭ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ የደብሩ አስተዳደር ምንም ዓይነት የኪራይ ውል እንዳይዋዋል ጥብቅ መመሪያ እንዲተላለፍለት አመልክቷል፡፡

ደብሩ ለመካነ መቃብር አገልግሎት የተሰጠው ቦታ ተቆራርሶ ለሌሎች አገልግሎቶች የተከራየ ሲኾን ይህም ‹‹ያለጨረታ፣ በጣም አሳዛኝ በኾነ ዋጋ›› መፈጸሙን ኮሚቴው በጥናቱ አጣርቷል፡፡ ቦታው ከአገልግሎቱ ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ ለመኪና ማቆሚያና ለጋራዥ መዋሉ ይዞታውን እንደሚያጣብበና በመንግሥት ሊያስነጥቅ እንደሚችል የጠቆመው ኮሚቴው፣ ተከራዮች እንዲለቁና ቦታው በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ይውል ዘንድ ጥብቅ መመሪያ እንዲተላለፍ አሳስቧል፡፡

Bole Saint Michael Churchበቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን 17 ሱቆች በብር 1500 ለአንዲት ግለሰብ የተከራዩ ሲኾን ግለሰቧም ለሌሎች በማከራየት በወር ከብር 30‚000 በላይ በማግኘት እንደሚጠቀሙ ተገልጧል፡፡ የደብሩ አስተዳደር ኹኔታውን በመቃወም ውላቸው እንዲቋረጥ ለማድረግ በክሥ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ሀገረ ስብከቱ ውሉ እንዲታደስ የሚያስገድድ ደብዳቤ ለደብሩ መጻፉ ለውዝግብ መንሥኤ እንደኾነና ለማጣራት ሥራውም ዕንቅፋት መፍጠሩን ኮሚቴው ያስረዳል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለግለሰብ በማድላት ደብሩ ውል እንዲዋዋል የሚያስገድደው የሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ እንዲነሣና ደብሩ ይዞታውን እንዲያስከብር መመሪያ እንዲሰጥ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
trade centers at the gate of Debra Negodguwad St Jhon churchበመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል፣ በጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል እና በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ አብያተ ክርስቲያን የተሠሩ የንግድ ሱቆች ለተከራይ አከራይ ወይም ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የተከራዩ (ቁልፋቸው የተሸጠ) መኾኑን የየአድባራቱ ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤያቱ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ዋና ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮችና ሒሳብ ሹሞች በተገኙበት መረጋገጡ ታውቋል፡፡
Mekanisa Debra Genet Saint Michael Churchበመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ለኪራይ ከዋሉት 55 ሱቆች ውስጥ 50ዎቹ ለሦስተኛ ወገን ተከራይተዋል(ቁልፋቸው ተሽጠዋል)፡፡ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ኹለት ታላላቅና 13 ታናናሽ ሱቆች ያሉት ሲኾን አብዛኞቹ ከ5 – 10 ለሚኾኑ ዓመታት ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የተከራዩ ናቸው፡፡ ለመኪና መመርመሪያ በሚል ከደብሩ በካሬ ብር 6.00 ሒሳብ ለዐሥር ዓመት የተከራየው ግለሰብ ብር 18‚000 ወርኃዊ ኪራይ ለደብሩ የሚከፍል ቢኾንም ተከራዩ መጋዘን ሠርቶበት ለሦስተኛ ወገን በማከራየት በወር ከብር 50‚000 በላይ ያገኛል፡፡

ከመሬት ኪራይ፣ ከሱቅ ኪራይና ከመካነ መቃብር ጋራ በተያያዘ በርካታ ችግሮች የታዩበት የደብሩ አስተዳደር፣ የተሰጠውን መመሪያ በመጣስ አዲስ ሱቅ ሠርቶ ለማከራየት እየተንቀሳቀሰ መኾኑን የገለጸው ኮሚቴው፣ ለሕገ ወጥ ሥራው በሀገረ ስብከቱ በኩል ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ሱቆች ባለቤት ቢኾንም ኹሉም ለማለት በሚያስደፍር አኳኋን በሕጋዊ መንገድ ያልተከራዩ፣ በተከራዮች ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው (ቁልፋቸው ተሽጦ) በዕጥፍ የተከራዩ መኾናቸው ተገልጧል፡፡

የጥናት ተልእኮውን በሰነዶች ምርመራና በግምገማ ስልቶች እያከናወነ የሚገኘው ኮሚቴው፣ በየሱቆቹ በመዘዋወር የተከራይ አከራዮችን በማነጋገር ግልጽ መረጃዎችን መሰብሰቡን ገልጾ፣ የሦስተኛ ወገን ተከራዮች ለኮሚቴው ግልጽ መረጃዎችን በመስጠታቸው አንዳችም ችግር እንደማይደርስባቸው የየአብያተ ክርስቲያኑ አለቆች እንዳረጋገጡላቸው ጠቅሷል፡፡ ይኹን እንጂ ለኮሚቴው ግልጽ መረጃ የሰጡት የሦስተኛ ወገን ተከራዮች በአከራዮቻቸው ጫና እየደረሰባቸው ከመኾኑም በላይ የየአድባራቱ አለቆች በገቡላቸው ቃል መሠረት ከጫናው ሊታደጓቸው አልቻሉም ብሏል፡፡

ይህ አካሔድ የኮሚቴውን ቀጣይ የጥናት ሥራና የጥናቱን ውጤት ለችግር የሚያጋልጠው በመኾኑ የሦስተኛ ወገን ተከራዮች በአከራዮቻቸውም ይኹን በደብሩ ምንም ዐይነት ጫና እንዳይደርስባቸው፣ ተለዋጭ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስም ባሉበት ኹኔታ እየሠሩ እንዲቆዩ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንዲጻፍላቸው ኮሚቴው በማሳሰቢያው ጠይቋል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለጥናቱ የሚያደርጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚደነቅና የሚመሰገን ነው ብሏል – ኮሚቴው፡፡ ይኹንና የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር በአንድ በኩል በመሬትና በንግድ ተቋማት ኪራይ ዙሪያ የተጀመረውን ጥናት ተከትሎ ምንም ዐይነት የኪራይ ውል ይኹን ግንባታ እንዳይካሔድ ታግዶ ሳለ፣ የኪራይ ጨረታና ውል እንዲካሔድ የሚያስገድድ ደብዳቤ መጻፉ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያን መመሪያውን እንዲቃወሙና ውዝግብ እንዲነሣ ምክንያት ኾኗል፡፡

በሌላ በኩል የጥናት ኮሚቴው ስለመቋቋሙና ስለተልእኮው የሚገልጸውንና ለተመረጡት 69 አድባራት ማድረስ የሚገባውን ደብዳቤ በማዘግየትና ቆራርጦ በመበተን ዕንቅፋት ፈጥሯል፡፡ በዚኽ ረገድ ለጥናቱ ዐይነተኛ ማሳያ የሚኾኑ ግብዓቶች እንደሚገኙበት ለሚታመንበት ለገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ደብዳቤው ባለመዘጋጀቱና ባለመድረሱ ኮሚቴው ለእንግልት መዳረጉ ተጠቅሷል፤ በሀገረ ስብከቱ በጥቅም ትስስር የተንሰራፋው ግብረ ሙስና ማረጋገጫም ነው ተብሏል፡፡

በመኾኑም የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ዕንቅፋትና ውዝግብ ከሚፈጥሩ መሰል ተግዳሮቶች እንዲታቀብና ጥናቱን ከመደገፍና ከማስተባበር አኳያ ተገቢውን ትእዛዝ ለአድባራቱ በወቅቱ እንዲያስተላለፍ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በኩል ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጠው ኮሚቴው በአጽንዖት ጠይቋል፡፡ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከጥናት ኮሚቴው በዝርዝር የቀረቡት አስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች በሙሉ ተግባር ላይ ውለው አፈጻጸማቸው እንዲገለጽለት የካቲት ፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በቁጥር 2599/357/2007 በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት በአሳዛኝ አደጋ ላይ እንደኾነ በተጠቆመበት ጥናታዊ ሒደቱ÷ የቤተ ክርስቲያን መሬት ከአካባቢ ዋጋ በታች በካሬ ከ0.37 – 0.50 ሳንቲም ከ10 – 15 ዓመታት በማከራየት ከፍተኛ ምዝበራ እየተፈጸመ ስለመኾኑ ተረጋግጦበታል፤ የኪራይ ውላቸው ከተፈተሹ የንግድ ማዕከላት ከዘጠና በመቶ ያላነሱቱ ከተገቢው የኪራይ ዋጋቸው በታች እስከ 10 ዓመታት በተከራዩት ግለሰቦች ለሦስተኛ ወገን በኹለትና ሦስት ዕጥፍ በኪራይ በመተላለፋቸው ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለተከራይ ግለሰቦች የሚያደሉና የቤተ ክርስቲያን ጥቅም ተላልፎ የተሰጠባቸው መኾናቸው ታውቋል፡፡

የአድባራቱ የሰነዶች አያያዝና አደረጃጀት በአሳፋሪና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተስተውሏል፤ በመረጃ አሰጣጥ ረገድ አጥኚ ልኡካኑን ለመዋሸትና ለመደበቅ የሞከሩ ጥቂቶች አይደሉም፤ የጥናቱን ዓላማ ከአለመረዳት ጀምሮ ልኡካኑን በነዳጅና ውሎ አበል ስም በመደለያ የማባበል ዝንባሌዎችም ታይተዋል፡፡ በአንጻሩ ጠንካራ ሰበካ ጉባኤያት ባሉባቸው አድባራት የቦታና የሱቅ ኪራይ ውሎች የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ ጠብቀው፣ የፋይናንስ ሕጉንና ደንቡን አክብረው የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ጥቅም በሚያስጠብቅ አኳኋን መፈጸማቸው ተገልጧል፡፡ ለዚኽም እንደ አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት ያሉ አድባራት በአርኣያነት ተጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው ታኅሣሥ መባቻ ሥራውን የጀመረው ኮሚቴው ለጥናት ከመረጣቸው 69 አድባራት ውስጥ እስከ አኹን ከ18 ያላነሱትን ዳስሷል፡፡ ሒደቱ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባሉበት እየተገመገመ አቅጣጫ እንደሚሰጥበት ተነግሯል፡፡ በተቻለ መጠን እንዲቀላጠፍ ትእዛዝ የተሰጠበት ይኸው ጥናት በመሬትና በንግድ ተቋማት ኪራይ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች አሳይቶ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንደሚጠቁም የሚጠበቅ ሲኾን ይህም ቤተ ክርስቲያን የመሬት አጠቃቀምና የኪራይ ተመን ፖሊሲ ለማውጣት እንደሚያስችላት ተስፋ ተደርጓል፡፡

Advertisements

9 thoughts on “ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅምና በሚያስተች አኳኋን ለሦስተኛ ወገን የሚተላለፉ የአድባራት የንግድ ማዕከላት ኪራይ አሳሳቢ ኾኗል

 1. Anonymous February 16, 2015 at 11:23 am Reply
 2. Anonymous February 16, 2015 at 11:38 am Reply

  ያሳዝናል!
  ለመረጃው እናመሰግናለን
  በእውነት የሚያስተችና የሚያሳፍር ነው!

 3. Anonymous February 17, 2015 at 6:19 am Reply

  በገጠሪቷ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳማቱ፣ ቅዱሳና መካናቱ፣ አብያተ ክርስቲያናቱ፣ የአብነት ትምህርት ጉባኤያቱ፣ አገልጋይ ቀሳውስቱ፣ ምዕመናኑ …

  -በጠኔ፣ በችጋር፣ በረሀብ፣ በውሃ ጥም፣ በአልባሳት እጦት፣ በጤና ቀውስ፣ በአገልጋይ ካህናት ስደት፣ በመምህራኑ አስታዋሽ ማጣት፣ በተማሪዎቹ እንግልትና ስደት … ቀውስ ውስጥ ወድቀው፤
  የገጠሪቱ አብያተ ክርስቲያናትያናቱ ፈራርሰው… ጽላቱ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ … በየግለሰብ ቤት ተቀምጠው፤
  -በገጠሪቱ አብያተ ክርስቲያናትያናት ቀሳውስቱ መቀደሻ አልባሳት አጥተው በእናቶች ቀሚስ እየቀደሱ፣ መቅደሱን ማጠኛ ጡዋፍ እጣኑ ጠፍቶ በዛፍ ልጥ እያጠኑ፣
  -የገጠሩ ምዕመናን አገልጋይ ካህናት አጥተው፣ አስተማሪ አጥማቂ ካህን ናፍቀው፣ አጥምቁን፣ አስተምሩን እያሉ … በዋይታና በጭለማ ውስጥ ታጥረው፣
  -የአብነት የቆሎ ተማሪው በስደት በየከተማው፣ በየአዳባባዩ… የሎተሪ አዟሪ፣ የቀን ሰራተኛ፣ የጎዳና ተዳዳሪ ሆኖ፣… ማየቱ፤
  -የገጠሪቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማቱ፣ … በዓመት … አንድ ጊዜ ቀዳሽ ካህን፣ አገልጋይ ዲያቆናት … አጥተው፤ … በመናፍቃን፣ በተሀድሶውያ፣ በአረማውያን … ተከበው…
  የገጠሪቷ ቤተክርስቲያን አገልጋይ መምህራኑ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ፣ ተማሪዎቹ፣ ምዕመናቱ …. በዋይታ፣ በሀዘን፣ በለቅሶ፣…በጭለማ ተውጠው፡፡

  -በየከተማው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማቱና ካቴድራል ‹‹አስተዳዳሪዎቹ››፣ ‹‹ጸሀፊዎቹ››፣ የሀገረ ስብከቱ፣ ቤተክህነቱ ‹‹ሹማምንትና ሰራተኞች››፣ …. ግን የእግዚአብሔር ቤት የመቅደሱን ሀብት፣ ንብረት፣ … በመዝረፍ፣ በማዘረፍ፣ በምንፍቅና፣ በምድራዊ ፍልስፍና፣ በየፍርድ ቤቱ በወንጀል ክስ በውንብድና አጥፍቶ ጠፊ ታጣቂ ነት ውስጥ ተዘፍቀው፤ … ጥሩ ‹‹ገቢ›› ባላቸው የከተማ አድባራት ለሹመትና ለቅጥር እስከ ብር 300 ሺ እጅ መንሻ መስጠት መቀበል በአደባባይ ሲፈጽም ማየት፣ መስማት፣ ማውራቱ .. ፍጹም ልብ የሚነካ፣ ፍጹም የሚያሳዝን፣ ፍጹም ምሬት ውስጥ የሚከት፣ ፍጹም አንገት የሚያስደፋ … ለተናጋሪም ለሰሚም አሳፋሪ፣ አስደንጋጭ ተግባር ነው፡፡ ይህ አምላኩን በ30 ብር ከሸጠው የይሁዳ ተግባር ተለይቶ የማይታይ የዘመናችን ጥቁር ታሪክ ነው፡፡

  ግን የዚህ የጥፋት ተግባር ባለቤትና ተባባሪ ማነው ቢሉ ? እኛ ምዕመናኑን ጨምሮ፣ ከመንበረ ፕትርክናው ልዩ ጽ/ቤት ከተዘረጋው የሙስና፣ የምንፍቅና፣ የዘረኝነት፣ የፓለቲከኝነት … ሰንሰለት እስከ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ያለው የሰበካ ጉባኤያት ድክመት ተግባር ነው ውጤት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የከተማ ምዕመናኑ ምን ቸገረኝነት፣ ምን አገባኝነት፣ ፍጽም ተቆርቋሪ አልባነት…፤ የምዕመናኑ፣ የወጣቱ፣ የማህበራቱ … አሳዛኝ ባለቤት አልባ ስሜት፣ ፍጹም የዕምነት ተቆርቋሪ አልባ ስሜትና ተግባር ውጤት ነው፡፡

  -ምነው የከተማ ምዕመን ባለሀብቱ፣ ማህበራቱ ፣… በከተማው ላሉት አብያተክርስቲያናት ገንዘባቸውን ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ለዝርፊያ፣ ለሙስና፣ … አሳልፈው በመስጠት ዘራፊዎችን፣ ሙሰኞችን፣ መናፍቃኑን … በመቅደሱ ከሚያደራጁ፤ በዓላማ ለገጠሪቱ ቤተክርስቲያን ቢረዱ፣ ድጋፍ ቢያደርጉ፡፡ ምናው የጠረፋማ አካባቢ ቅዱሳን መካናቱ ከመፈታት ብንታደግ፣ አብነት መምህራኑ ከረሀብና ከስደት ብንታደጋቸው፣ ጉባኤያቱን ከመበተን ብንጠብቃቸው፣ ቅዱሳን ንዋያቱን ከዝርፊ ብንጠብቅ … ታላቅ የጽድቅ ተግባርና የትውልድን ኃላፊነት የመወጣት ተልዕኮ ነበር፡፡
  ግን ምን ያደርጋል! …. በታሪካችን እንደዚህ አይነቱን አሳዛኝ ተግባር ፈጽመን፣ ተባባሪ ሆነን … ከምንገኝ በዚህ የትውልድ የዘር ሀረግ ውስጥ ባልተቆጠርን ምነኛ በታደልን ነበር፡፡

  … ግን ምን ያደርጋል ዛሬ በጠቅላይ ቤተክህነቱ በተቋቋመው የአጥኚ ኮሚቴ የሚቀርበውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም የጥናት ዶክመንት ከወራት በኃላ ‹‹በአባ›› ኤልያስ አብርሃ፣ በሰረቀ … እጅ ወድቆ ምን እንደሚሆን… ውጤቱን ታዩታላችሁ፡፡ ከዚህ ቀደም እኮ ስንት ብዙ አባቶች … ይህን ሴጣናዊ ተግባር በቤ/ክ ላይ እንዳይፈጸም ደክመዋል፣ ጥረዋል ሆኖም ግን … ምድራዊ ዋጋቸው ውርደት፣ ከስራ መፍናቀል … ሆኖባቸው አይተናል ሰምተናል፡፡ ታዲያ ይህ ተግባር እኮ የኤልያስ አብርሀ፣ የሰረቀ፣… እና የግብር አበሮቻቸው ሰንሰለት ውጤት ነው፡፡ ኤልያስ አብርሃ እኮ ባለ 3 ፎቅ ቪላ፣ … ባለ ሀብት ባለቤት ነው፤ አባ … እኮ ባለ ገልባጭ ዩዲ ባለቤት ናቸው እኮ …፣ ታዲያ ይህ ከየት የመጣ ይመስላችኃል? ከልዩ ጽ/ቤት ከመንበረ ፕትርክናው የ4500 ብር ወርሃዊ ደመወዝ? የዋና ጸሃፊ እገሌስ …. ኪኪኪኪ!!!! የመንግስት የደህንነት ሀይል በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ከፕትርክና ወንበሩ .. ጀምሮ እጁ ለምን ይህንን ያህል የረዘመ ይመስለናል? ጮማ ባለቤት አልባ ጣፋጭ ስኳር ገጥሞት እኮ ነው፣ … ኪኪኪኪኪኪኪ!!!!….

  -መንግስት ከሀገሪቷ የቱሪዝም ዘርፍ በዓመት ከ10 ቢሊዮን (10,000,000,000.00) ብር በላይ ገቢ ያገኛል፤ ታዲያ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፉ ከ95% በላዩ ብቸኛ ባለቤቷ እኮ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ናት (አክሱም ብትል ላሊበላ፣ ጣና ኃይቅ ፣ የጎንደር ጥምቀተ ባህሩ፣ የደቡብ መስቀሉ … ) እንጂ! የሰረቀና የአሸናፊ … የተሃድሶ አዳራሽ አይደለም! … ፤ ታዲያ ይህንን ዘርፍ (ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ) ብቻ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በባለቤትነት በአግባቡ በህግና በሥርዓት መብቴን ላስከብር ተቋሜንም ጠቅሜ ሀገር ልጥቀም … ቢል እኮ ሌላ ጉድ ሊፈጠር ነው፡፡ … ይህ እንዴት ሆኖ? ይህች ‹‹የስራ ፈት ፊታውራሪ፣ የነፍጠኞች ምሽግ፣…›› ብሎ ለሰየማት፣ አዋጅ ላወጀባት፣ ጦር ለሰበቀባት የዕምነት ተቋም የዘመናችን ‹‹መንግስት›› በራሱ ላይ መቃብር እንደመቆፍ ነው የሚቆጥረው እኮ!
  ይህች ቤተክርስቲያን እንዴት አሳዛኝ ተቋም ናት!

  ሆኖም ግን ሴጣን ዝናሩን ይጨርሳል እንጂ ይህችን በክርስቶስ ደም የተመሰረተች ቤተክርስቲያን ሊያጠፋ ከቶ አይቻለውም!!!

  … እንደ ጥንቱ ይሁዳ አምላኩን በ30 ብር ሸጦ እራሱን በዛፍ ላይ እንደሰቀለ … ፤ የዘመኑም ይሁዳውያን መጨረሻቸው … እራሳቸውን በገመድ ሰቅሎ ማጥፋት ነው፡፡ በዘመናችንም ይህ ተግባር ሲፈጸም እያየን እየሰማን ነው …

  አጽራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን፡፡

 4. negash February 19, 2015 at 8:10 am Reply

  This is really shame for such church leaders. Please check similar thing in Kotebe Medhanealem church. Part of the church land is given to some one very recently.

 5. melaku February 19, 2015 at 3:19 pm Reply

  All these are fun! since, so many reform studies have been conducted. But none of them were accepted and implemented by Abune Mathias. Here also Aba Kelementos is also doing the same thing to get public acceptance and support for the time being. These all forms of corruption had been raised in the reform & good administration studies conducted before by the committee assigned by the Patriarch!

 6. Biruk February 20, 2015 at 5:52 am Reply

  I am also a witness for the house built at the foot of KOTEBE MEDHANIALEM CHURCH for a draft selling house. This land was directly given to a Pig (Asama) Seller who lives nearby the church and who corrupted the church leader and members of the Sebeka Gubae. I don’t know why the believers and other church staff looking quietly. Next time I am afraid the church leaders will give more land in the compound of Kidane Mihiret Church if he gives them more money than the previous.

  Cry! Cry! Cry! for your religion before our religion disappears by its HODAM Leaders.

  Biruk

 7. Anonymous February 20, 2015 at 7:58 am Reply

  yhe guday wsten yemiyangebegbegn guday neber mknyatum hulunm neger eziyaw bolebulbulaselalehu yemawkew slhon enam adebabay lay mewtatu des yilal mefthe sleminorew yabatachn yemedhanealem bet mechferiya medariya honuwalna ebakachu bertuna mela belu.. yedebru agelgay negn

 8. Anonymous February 27, 2015 at 7:21 am Reply

  All these are fun! since, so many reform studies have been conducted. But none of them were accepted and implemented by Abune Mathias. Here also Aba Kelementos is also doing the same thing to get public acceptance and support for the time being. These all forms of corruption had been raised in the reform & good administration studies conducted before by the committee assigned by the Patriarch! But this is not shame for such leaders because ከኩርንቸት…………………. አይጠበቅምና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: