በሦስት አህጉረ ስብከት ከ3200 በላይ ወገኖች ተጠመቁ – ዜና ጥምቀትን ያሰማን ጃንደረባው ባኮስ የተጠመቀበት የፊልጶስ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽበት እየተጠየቀ ነው

 • በአህጉረ ስብከት እና በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም በተደረገው የአምስት ዓመታት መተባበር ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት በጥምቀተ ክርስትና የተጨመሩት ምእመናን ቁጥር ከ፴ ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡
 • ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ የተጠመቀበትን የፊልጶስ ምንጭ (ቤት ሶሮን) በማቅናት የቤተ ፊልጶስ ገዳም (ቤተ ክርስቲያንና የመነኰሳት መኖርያ) የመመሥረት ውጥን ሳይፈጸም ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
 • የፊልጶስ ምንጭን ይዞታ በማስከበር ጥንተ ክርስትናችን የሚገለጽበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ እና የጃንደረባውን መታሰቢያ ለማቆም የቀድሞው ፓትርያርክ በዕሥራ ምእቱ በዓል ዋዜማ ለእስራኤል መንግሥት ላቀረቡት ጥያቄ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡
 • አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ተሳላሚዎችና ነዋሪ ምእመናን የቦታውን ይዞታ ለማስከበርና ለግንባታ ሥራዎች የሞያ፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡

*       *       *

 • የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ ፮ኛ ከፍተኛ ባለሥልጣን(የገንዘብ ሚኒስትሯ) ባኮስ፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በወንጌላዊው ቅ/ፊልጶስ ፈጻሚነት በተጠመቀበት ወቅት ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ አምናለኹ›› በማለት የሰጠው ምስክርነት ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት ሥርዐተ ተአምኖ/የጥምቀት ፎርሙላ/ ኾኖ አገልግሏል፡፡
 • በመጀመሪያው ስብከተ ሐዋርያት ክርስትናን የተቀበለ ቀዳሚው አፍሪቃዊ ክርስቲያንና በኋላም የኢትዮጵያ ሐዋርያ ጃንደረባው ባኮስ(አቤላክ)÷ ከአኵስም ቀጥሎ በኑቢያ አስተምሯል፤ ወደ የመን ተሻግሮ ከሰበከ በኋላ ወደ ሀገረ እንድያ (ሕንድ) አምርቶ ጥንት ታፕሮባና ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ ሳለ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡

*       *       *

 • ‹‹የክርስትና እምነታችን ታሪክ መነሻ፣ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በወንጌላዊው ቅ/ፊልጶስ እጅ የተጠመቀበት ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ዳር ያለው ምንጭ በመኾኑ ከእስራኤል መንግሥት ተረክበን በዚያ ቦታ ላይ የኹለተኛውን ሺሕ ዓመት (ዕሥራ ምእት) ፍጻሜ ታላቅ በዓል ለማክበር ሙሉ ተስፋ አለን፡፡››

/ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፤ በጥቅምት ወር ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. አምስተኛና የመጨረሻ የኢየሩሳሌም ጉብኝታቸው ወቅት ለእስራኤል ፕሬዝዳንት በቤተ መንግሥት ተገኝተው እንዳሳሰቡት/

 • ‹‹ቅዱስ ፊልጶስ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሥርዐተ ጥምቀት ያበረከተ ሐዋርያ በመኾኑ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አባትነቱን በታላቅ ደረጃ ትመለከታዋለች፡፡ በመምህራችንና በመንፈሳዊ አባታችን ቅዱስ ፊልጶስ ስም የጸሎት ቤት አዘጋጅተን በየዓመቱ መታሰቢያው እንዲከበር ማድረጋችን ተገቢ ነው፤ መምህርን ማስታወስ ትምህርቱን አለመዘንጋት ነውና፡፡››

/ሰባተኛው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ የቅ/ፊልጶስ ቤተ መቅደስ በፊልጶስ ምንጭ እስከሚታነጽ ድረስ ጽላቱ በመንበረ ሊቀ ጵጵስናው ግቢ በተደራጀው ጸሎት ቤት ጥቅምት ፲፬ ቀን ፲፱፻፸፱ ዓ.ም. ገብቶ እንዲያርፍ በተደረገበት ወቅት ከተናገሩት/

 • ‹‹ጥንታዊውንና ያለፈውን ታሪክ አኹን ያለው ተቀባዩ ትውልድ አክብሮ ታሪክነቱ በዋቢነት የሚጠበቅበትን አቋም ካላጠናከረ፣ እርሱም በዘመኑ የሠራውን ወይም ያቆየውን ታሪክ አክብሮ ታሪካዊ አቋም የሚሰጥለት ሌላ ተቀባይ ትውልድ አያገኝም፡፡ ስለዚኽ ነው በኢየሩሳሌም የሚገኙት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ይዞታዎች የሚጠበቁበት አቋም ሊጠናከሩ ይገባል የምንለው፡፡››

/በኢየሩሳሌም ለኹለት ጊዜ በሊቀ ጵጵስና ተመድበው የመሩት ነፍስ ኄር ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ካልዕ፣ በ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. የፊልጶስ ምንጭን በእስራኤል ለኢትዮጵያ አምባሳደር ባስጎበኙበት ወቅት ከተናገሩት/

*        *        *

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፣ ሰው ኹሉ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይችልም፡፡ ይኸውም በሚታይ ሥርዐት ማለትም በውኃ በሚደረገው ጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግም የምንወለድበት፣ ከጌታ ሞትና ትንሣኤ ተሳታፊ የምንኾንበት ምሥጢር ነው፡፡ /ዮሐ. ፫÷፫-፮፤ ቆላ. ፪÷፲፪/ በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉድ የምታሰኘው አማናዊቷ ጥምቀት አንድ ክርስቶስ የሚመለክባት፣ በአንዲት ሃይማኖትና በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የምትፈጸም፣ የማትደገም የማትከለስ እንጂ በተለያዩ እምነቶች ውስጥ የምትገኝ አይደለችም፡፡ /ኤፌ. ፬÷፭/

The Ethiopian Eunch Baptized by St Philipጃንደረባው ባኮስ የአትዮጵያዊቷ ንግሥት ፮ኛ ሕንደኬ የገንዘብዋ ኹሉ ሓላፊ(በጅሮንድ) ነበር፡፡ በመጀመሪያው ስብከተ ሐዋርያት የክርስትናን እምነት ለመቀበል የታደለ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪቃዊ ክርስቲያን ነው፡፡ ጃንደረባው በመንፈሰ እግዚአብሔር መሪነትና አስፈጻሚነት በወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ እጅ ተጠምቆ ከመንፈስ ቅዱስ የመወለድን ዕድል አግኝቷል፡፡ ክርስትናውም ከአረማዊነት በመመለስ ሳይኾን በቀጥታ ከሕገ ኦሪት(ብሉይ ኪዳን) እምነት የተሸጋገረ ነበር፡፡ ይህን የምንረዳው በራሱ ቋንቋ በግእዝ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መካከል የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ መገኘቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ዘመን ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ በበዓለ ፋሲካ፣ በበዓለ መጸለትና በበዓለ ናዕት በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው፣ ጃንደረባውም ከአራት ሺሕ ማይልስ በላይ ተጉዞ ሥርዐተ አምልኮቱን ፈጽሞ በጋዛ በኩል አድርጎ ወደ ሀገሩ በሚመለስበት ወቅት ይህን ታላቅ ጸጋ ሊያገኝ በቅቷል፡፡ ይህ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የተመሠረተው የክርስትና እምነት ታሪካችን ኢትዮጵያ በዘመነ አኵስም ከምሥራቃውያንና ከምዕራባውያን ከሌሎችም የአፍሪቃ አገሮች ቀድማ ከአይሁድ ቀጥላ ክርስትናን በመጀመሪያው ምእት ዓመት መቀበልዋን ያረጋግጣል፡፡

በጅሮንድ ባኮስ በዚኽ ሃይማኖታዊ ጉዞው የሕገ ኦሪትንና የሕገ ወንጌልን ጽድቅ በመፈጸም የራሱንና የአገሩን ስም በቅዱስ መጽሐፍ በማስጠራት ለሐዲስ ኪዳን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያስገኘ የቤተ ክርስቲያናችን መሥራች ኾኗል፡፡ በሌላም በኩል ከክርስትናም በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ እምነት አምልኮተ እግዚአብሔር እንጂ አምልኮተ ጣዖት እንዳልነበረ የጃንደረባው ሕይወት ኹነኛ ምስክር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም ሲወለድ በንጉሧ ባዜን መባ በማቅረብ ያወቀችውና ልደቱን ያከበረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መባሉዋ በትክክል ነው፡፡ በትውልዱ አኵስማዊ ኾኖ በአኵስም ማእከልነት ክርስትናን ያስፋፋውንና ያጠናከረውን ጃንደረባው ባኮስን የሌላ ማንነት ለመስጠት መሞከር፣ አልያም አገራችን ክርስትናን የተቀበለችበትን የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ታሪክ መካድና መቀነስ ጊዜ ተገኘ ተብሎ ርእዮታዊና ሃይማኖታዊ ጥላቻን ከማንጸባረቅ የተለየ ተደርጎ ሊታይ አይችልም!!


ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አሕዛብን ኹሉ እንድታስተምርና እንድታሳምን፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድታጠምቅ ታዝዛለች፡፡ /ማቴ. ፳፰÷፲፱/ ፊትም በሕገ ልቡና በኋላም ሕገ ኦሪትን ተቀብላ ስለ ድኅነተ ዓለም የተነገረውን ትንቢት የተቆጠረውን ሱባኤ ስትጠባበቅ የኖረችው አገራችን ኢትዮጵያ፣ የክርስትና እምነት መሠረት ከተጣለበት ከፍልስጥኤም ውጭ ከምሥራቃውያንና ከምዕራባውያን ከሌሎችም የአፍሪቃ አገሮች ቀድማ የራስዋ ሐዋርያ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ የመወለድን ዕድል በማግኘቱ የሰማችውንና በአበው ትምህርትና ሰማዕትነት ያጸናችውን ዜና ጥምቀት በምልዓት የማስፋፋትና የማጠናከር ጥረት ላይ ትገኛለች፡፡

Timket Be Metkel

ማኅበረ ቅዱሳን ከመተከል ሀገረ ስብከት ጋራ በመተባበር በሚያከናውነው የማጥመቅና ወደ አሚነ ሥላሴ የመመለስ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም በድባጤ ወረዳ 2132 የጉምዝ ተወላጆች ጥር ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጥምቀተ ክርስትና ተፈጽሞላቸዋል፡፡

ጥረቱ አዳዲስ አማንያንን በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጨመር የኾነውን ያኽል፣ በየምክንያቱ ከጉያዋ የተነጠቁ የገዛ ልጆቿን ከያሉበት መልሳ የምትሰበስብበት የስብከተ ወንጌል ቀዳሚው ተልእኮዋ ተደርጎም የሚታይ ነው፡፡ የወቅቱን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የተመለሱ ምእመናንን ቁጥጥር በንጽጽር የመዘነው ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ጥረቱ ‹‹ከችግሩ ብዛት ጋራ ፈጽሞ የማይመጣጠንና እጅግ አነስተኛ›› መኾኑን በመገምገም ስብከተ ወንጌልን ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በበለጠ በማስፋፋትና በማጠናከር አዲስ አማንያንን በትምህርተ ወንጌል ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማምጣት፣ ያሉትንም በሃይማኖት ለማጽናት ተግቶ እንደሚሠራ በአቋም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ምእመናንን በስብከተ ወንጌል ለመጠበቅና ለማትረፍ የሚደረገው ትጋት÷ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን፣ ሰበካ ጉባኤን ከማጠናከር፣ ሰንበት ት/ቤቶችን ከማደራጀትና የአብነት ት/ቤቶችን ከመደገፍ ጋራ ተመጋግቦ መፈጸም እንደሚገባው አጠቃላይ ጉባኤው አሳስቧል፡፡ ይኸው የአጠቃላይ ጉባኤው የጋራ መግለጫም የ፳፻፯ ዓ.ም. የበጀት ዓመት የሥራ መመሪያ ኾኖ እንዲሠራበት የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ መመሪያ እየተቀበለ አገልግሎቱን የቀጠለው ማኅበረ ቅዱሳንም፣ በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍሉ በኩል በዘረጋው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራሙ አማካይነት የምእመናን ቁጥር በአኃዝ ይኹን በትምህርተ ወንጌል የላቀ እንዲኾን በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡

ማኅበሩ ከ፳፻፫ – ፳፻፲፩ ዓ.ም. የዘረጋውና ከአህጉረ ስብከት ጋራ በመተባበር የሚያስፈጽመው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራሙ አካል በኾነው የሰሞኑ የማጥመቅ ክንውኑ፣ በሦስት አህጉረ ስብከት 3321 ያኽል አዲስ አማንያን ከአምልኮ ባዕድና ከሌሎች እምነቶች ተመልሰው በርትዕት ሃይማኖት አምነው ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲጨመሩ አድርጓል፡፡ ይኸው አኃዝ ፕሮግራሙ በአምስተኛ ዓመት የማጥመቅና ወደ አሚነ ሥላሴ የመመለስ መርሐ ግብሩ ያተረፋቸውን ጥሙቃን ጠቅላላ ቁጥር 30 ሺሕ እንደሚያደርሰው ተገልጧል፡፡

የማጥመቅ መርሐ ግብሩ ከጥር ፱ – ፲፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የተከናወነ ሲኾን ሦስቱ አህጉረ ስብከትም መተከል፣ ጋሞጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ናቸው፡፡ ጥር ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በመተከል ሀ/ስብከት ድባጤ ወረዳ 2132 የጉምዝ ተወላጆች የሥላሴ ልጅነት ለማግኘት በቅተዋል፡፡ ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በጋሞጎፋ ሀ/ስብከት ኮንሶ ወረዳ ለ569 የኮንሶ ተወላጆች ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ለማሰጠት ተችሏል፡፡ ጥር ፲፪ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በዚያው በጋሞጎፋ ሀ/ስብከት ገዋዳ ወረዳ 120 የኮንሶ ተወላጆች ከጥምቀት ልጅነት ተሳትፈዋል፡፡ ጥር ፲፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በደቡብ ኦሞ-ጂንካ ሀ/ስብከት ማሌ ወረዳ 400 የማሌ ተወላጆች ለእግዚአብሔር ልጅነት በቅተዋል፡፡

በየስብከት ኬላዎች ለወራት የተሰጠውን የቅድመ ጥምቀት ትምህርተ ወንጌል ከተከታተሉ በኋላ እንደ ጃንደረባው ‹‹እንዳንጠመቅ የሚከለክለን ምንድን ነው?›› በማለት በፍጹም ልባቸው አምነውና ፈቅደው የተቀበሏትን አማናዊት ጥምቀት በቀጣይነት ለማጽናት የሚያስችሉ ኹኔታዎች(ቤተ ክርስቲያን ማነጽ፣ ካህናትና ሰባክያነ ወንጌል መመደብ የመሳሰሉትም) ተሟልተውላቸዋል፡፡

ለአብነት ያኽል በመተከል ሀ/ስብከት በግልገል በለስ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዕብነ መሠረት በዕለቱ ተቀምጧል፤ የመሥሪያው ቆርቆሮና ሚስማርም ቀርቧል፡፡ አራት ሰባክያነ ወንጌልን በመመደብ አገልግሎታቸውን ከሚያግዙ የኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎች ጀምሮ ሞተር ሳይክልና ቋሚ ድጎማ ተወስኖላቸዋል፤ ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤትም የኮምፒዩተር ልገሳ ተደርጓል፡፡ በአንጻሩ ጥሙቃኑ፣ የስብከተ ወንጌል ልኡካኑን ለሰዓታት ተጉዘው በዝማሬ በመቀበል የመንፈስ ብርታት ሰጥተዋል፤ ለሥርዐተ ጥምቀቱ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ጭምር በማቅረብ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ቀናዒነት አረጋግጠዋል፡፡

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን÷ ጌታችን ሥርዐተ ጥምቀትን/ዳግም ልደትን/ ለመሥራት፣ ትሕትናን ለማስተማርና ውኃውን ለመባረክ የተጠመቀበትን በዓለ ጥምቀት የመታሰቢያ በዓል አድርጋ በምታከብርበት ዘመነ አስተርእዮ የተፈጸመው የማጥመቅና ወደ አሚነ ሥላሴ የመመለስ አገልግሎት በሌሎችም አህጉረ ስብከት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመርሐ ግብሩ ዝርዝር ይጠቁማል፡፡

ጌታችን እንደ ጌትነቱ በማር በወተት ያልተጠመቀበት፣ ለጥምቀቱ ውኃን የመረጠበት ምክንያት ቅሉ÷ ውኃ በሀብታሙም በድኻውም ቤት ያለ በመኾኑ በጥምቀት የሚገኘው ድኅነትም በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፤ በወልድ ዋሕድ በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ላመነ ኹሉ የተፈቀደ መኾኑን ለማጠየቅ አይደለምን? አንድም ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርሳል፤ የዓለምን ክሕደትና ኑፋቄ ባለመከተል ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ እንደኾነ አምናለኹ›› በሚለው የጃንደረባው ምስክርነት በመጀመሪያው ምእት በ፴፬ ዓ.ም. የሰማናትና የተቀበልናት ዜና ጥምቀትና ክርስትና፣ በአበው ትምህርትና ሰማዕትነት ጸንታ እንደቆየችን ኹሉ ዛሬም በትጉሃን ላእካነ ወንጌል ቅትልት እስከ ጽንፍ መድረሷን ትቀጥላለች፡፡

Ethiopian Piligrims at Beth Soron where St. Philip baptized the Ethiopian Eunchበበዓለ ትንሣኤ ከመላው ዓለም ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የመጡ ኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በተጠመቀበት የፊልጶስ ምንጭ ተገኝተው ስፍራውን ይጎበኛሉ፤ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት ከጠበሉ በረከት ይቀበላሉ፡፡ ይህ ቅዱስ ስፍራ የጥንታዊነት መሠረተ ታሪካችንን ከማስጠበቅ አንጻር ይዞታውን በማስከበር በቅ/ፊልጶስ ስም ቤተ ክርስቲያን ለማነጽና የጃንደረባውን መታሰቢያ ለማቆም ለእስራኤል መንግሥት ለቀረበው ጥያቄ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፤ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከትም ዝግጁ እንደኾኑ በተለይም በዘንድሮው የልደትና የጥምቀት ክብረ በዓላት አጋጣሚ በተለያዩ መድረኮች በአጽንዖት ሲናገሩ ተስተውለዋል፡፡

ከተሳላሚዎችና ነዋሪ ምእመናን መካከል በኢየሩሳሌም ለአራት ዐሥርት ዓመታት ያኽል የኖሩትና የቅድስናና የታሪክ ይዞታዎቻችንን በተመለከተ ኹለት መጻሕፍትን ያሳተሙት አቶ አማከለ ገበየሁ ግርማዬ፣ ‹‹ቅድስት ሀገር›› በሚል ርእስ በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው ስለ ቅዱስ ፊልጶስ ምንጭ ሲያብራሩ፡- ‹‹ከኢየሩሳሌም ወደ ኬብሮን ለመጓዝ በጥንት ጊዜ መንገዱ አንድ አውራ ጎዳና ነበር፡፡ ዛሬ ግን እስራኤል ጊሎ ከሚባል ከተማ ወደ ኬብሮን ከተማ የሚያደርስ ዘመናዊ አውራ ጎዳና ዘርግታለች፡፡

ከቤተ ልሔም በኺብሮን ጎዳና ተጉዞ በእኩሌታው መንገድ ላይ እንደተደረሰ በግራ በኩል የሚገኝ አንድ የምንጭ ውኃ ያለበት ስፍራ አለ፡፡ በቀድሞ ዘመን በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበት እንደነበር ይነገራል፤ ነገር ግን ቱርኮች አገሩን ከያዙት ወዲኽ ቤተ ክርስቲያኑን መስጊድ አድርገውት ነበር፤ ስሙንም ‹‹ዓይነ ዱር›› ብለው ይጠሩታል፡፡ ክርስቲያኖች ግን ከዘመነ ሐዲስ ወዲኽ የፊልጶስ ምንጭ ነው ይላሉ፤ ቅዱስ ፊልጶስ ሕፅዋ ለሕንደኬ(የኢትዮጵያ ንግሥት ዋና መልእክተኛዋን) ያጠመቀበት ቦታና ምንጩ ይህ እንደኾነ ይታመናልና፡፡/ግብ ሐዋ. 8÷27/

ኢትዮጵያ ከምሥራቃውያንም ኾነ ከምዕራባውያን ሕዝብ በፊት በመጀመሪያው ምእት በ፴፬ ዓ.ም. ክርስቲያንነት እንዳገኘች መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ኢትዮጵያ በዚኽ ቦታ ላይ ጥንተ ክርስትናዋ የሚገለጽበት አንድ ቤተ ክርስቲያን መሥራት የተገባት ነው፡፡ /ገጽ 92 – 93/


ይህ በእንዲኽ እንዳለ፣ ወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ በመንፈሰ እግዚአብሔር መሪነትና አስፈጻሚነት የኢትዮጵያን ንግሥት ሕንደኬ የገንዘብ ሚኒስቴር(ጃንደረባ ባኮስ) ያጠመቀበትን ስፍራ ለመረከብና ይዞታውን ለማስከበር ለእስራኤል መንግሥት የቀረበው ጥያቄ በቂ ግፊትና ክትትል እየተደረገለት እንዳልኾነ የቅድስት ሀገር ተሳላሚዎችና በዚያው ያሉ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከዘመነ ሐዲስ ወዲኽ በክርስቲያኖች ዘንድ ‹‹የቅዱስ ፊልጶስ ምንጭ››/Beth-Soron/ ተብሎ የሚታወቀው ስፍራ የቀዳማዊነት መሠረተ ታሪካችንን ከማስጠበቅ አኳያ ያለውን ፋይዳ የተገነዘቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይዞታውን ለመረከብና ለማስከበር ከዓመታት በፊት የጀመሩት ጥረት እልባት ያገኝ ዘንድ በገዳማቱ አስተዳደርና በመንበረ ፓትርያርኩ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው፣ በመንግሥትም በኩል አስፈላጊው እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሥርዐተ ጥምቀት ያበረከተ ሐዋርያ በመኾኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አባትነቱን በታላቅ ደረጃ እንደምትመለከተው የገለጹት ምእመናኑ፣ ጥንተ ክርስትናዋ የሚገለጽበት በቅዱስ ፊልጶስ ስም የሚጠራ ቤተ ክርስቲያንና የጃንደረባው ባኮስ መታሰቢያ በስፍራው ማቆም ይገባታል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውና ለዚኽም አስፈላጊውን የሞያ፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ በጥቅምት ወር ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ባደረጉት አምስተኛና የመጨረሻ ጉብኝታቸው የወንጌላዊው ፊልጶስ ምንጭን የመረከብና ይዞታውን የማስከበር ጉዳይ ለወቅቱ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሙሼ ካትዛቭና ለቱሪዝም ሚኒስትሩ ይሥሓቅ ሔርዞግ አንሥተው እንደተነጋገሩበት ተመልክቷል፡፡

የክርስትና እምነታችን ታሪክ መነሻ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ እጅ የተጠመቀበት ወደ ጋዛ የሚወስደው መንገድ ዳር ያለው ምንጭ እንደኾነ ለፕሬዝዳቱና ለመንግሥቱ ባለሥልጣናት የጠቅሱት ፓትርያርኩ፣ ይኸው የታሪካችን መነሻ ቦታ እንዲሰጠን ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል ለእስራኤል መንግሥት የጻፈችውን ደብዳቤ በውይይታቸው አስታውሰዋል፡፡ ወደ ሦስተኛው ሺሕ ዓመት ሽግግር ከመደረጉ በፊት ቦታውን ሳይዘገይ በመረከብ የዕሥራ ምእቱን(ኹለተኛውን ሺሕ ዓመት) ፍጻሜ ዋዜማ በዚያው ቦታ ለማክበር ሙሉ ተስፋ እንዳላቸው ለፕሬዝዳንቱ ገልጸውላቸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡

Patriarch Abune Pawlos visiting Beth Soron(YeFilpos Minch)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የዕሥራ ምእቱን ፍጻሜ ዋዜማ ለማክበር እንደኾነ በተዘገበው የኢየሩሳሌም የመጨረሻ ጉብኝታቸው፣ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ከእስራኤል ባለሥልጣናት፣ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከገዳማቱ ማኅበረ መነኰሳት ጋራ በመኾን የንግሥት ሕንደኬ ከፍተኛ ሹም የተጠመቀበትንና የክርስትና ታሪካችን መነሻ የኾነውን ‹‹የቅዱስ ፊልጶስ ምንጭ››ና በዙሪያው ያለውን አካባቢ ጎብኝተዋል፡፡ /ፎቶና መግለጫ: አማከለ ገበየሁ ግርማዬ/

ፕሬዝዳንቱና የቱሪዝም ሚኒስትሩ በፓትርያርኩ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ጉዳዩን በማጤን ተጠንቶና ተጣርቶ እንዲቀርብላቸውና አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡበት በመግለጽ ቢያሰናብቷቸውም እስከ አኹን በተጨባጭ የታየ ተግባራዊ ርምጃ አለመኖሩ ታውቋል፡፡ የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጥር ፲ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ያነጋገራቸውና ላለፉት አርባ ዓመታት ኑሯቸውን በኢየሩሳሌም ያደረጉት አማከለ ገበየሁ ግርማዬ÷ ጉዳዩ በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ ማትያስ (አኹን ፓትርያርክ) በሚገባ እንደሚታወቅ ገልጸው፣ ልመናው ቀጥሎ በቦታው ቤተ ክርስቲያንና የመነኮሳት መኖርያ ቢታነጽበት ታላቅ ታሪክ ጥሎ ማለፍ በመኾኑ ትኩረት እንዲሰጡት በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡

Patriarch Abune Pawulos and the architect,YeFilpos Minch

ገዳሙ የወከለው አርኪቴክት ኮቢ በቦታው ላይ የሚገኙትን የጥንት ሕንፃዎች እንደምን መልሶ መጠገን ማደስና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል አብራርቶላቸዋል፤ በባለሞያው የተሠራ የሕንፃ ፕላንም ቀርቦ ተመልክተዋል፡፡ በሕንፃው ንድፍ ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎችም ቢሳተፉበትና አስተያየት ቢሰጡበት የበለጠ እንደሚኾን የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ይዞታው በተፈቀደ ጊዜ የቦታው የጥንት ሕንፃዎች እንደሚጠገኑ ገልጸዋል፤ጠበቃው ባራቅም ቦታውን ለማግኘት በሚያስችል አግባብ ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርግ አሳስበውት ነበር፡፡/ፎቶ: አማከለ ገበየሁ ግርማዬ/

 ምእመኑ ለሬዲዮው እንዳስረዱት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከጥቅምት ፳፪ እስከ ኅዳር ፩ ቀን በነበራቸው ቆይታ የንግሥት ሕንደኬ ከፍተኛ ባለሥልጣን የተጠመቀበትንና ክርስትናችን የተመሠረተበትን የፊልጶስ ምንጭና አካባቢውን ጎብኝተው ጸሎት አድርሰዋል፤ የገዳማቱ አስተዳደር የወከለው አርኪቴክትም በቦታው የሚገኙትን ጥንታዊ ሕንፃዎች መልሶ ለመጠገንና ጥቅም ላይ ለማዋል እንዴት እንደሚቻል አብራርተውላቸው ነበር፡፡ ከጉብኝታቸው በኋላ በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ከሕግ ጠበቃውና ከአርኪቴክቱ ጋራ ሰፊ ውይይት ያካሔዱ ሲኾን ቦታው የሚያመለክተው ፕላንና ካርታ በእስራኤል መሐንዲስ ተፈቅዶ ከተሰጠ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎችን (የሕግ፣ የአርክቴክቸርና የምሕንድስና) ወደ ስፍራው ልኮ ለማስጠናት ዕቅድ እንደነበራቸው፣ ጠበቃውም ቦታውን ለማግኘት በሚያስችል አግባብ ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋቸው ነበር ብለዋል፡፡

አማከለ ገበየሁ ግርማዬ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትን ታሪክና ወቅታዊ ችግር የሚዳስሱ ‹‹ቅድስት አገር›› እና ‹‹በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ታሪካዊና ሥዕላዊ ቤተ መዘክር›› የተሰኙ ኹለት መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡ ከ፲፱፻፸፯ – ፲፱፻፹፭ ዓ.ም. ሰባተኛው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስና በገዳማቱ አበው መነኰሳት አሳሳቢነት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተባርኮ የተላከ የወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ ጽላት በኢየሩሳሌም መንበረ ሊቀ ጵጵስና ግቢ በተደራጀው የጸሎት ቤት ጥቅምት ፲፬ ቀን ፲፱፻፸፱ ዓ.ም. በክብር ገብቶ ቅዳሴ ቤቱ መከበሩን ጽፈዋል፡፡ በወቅቱ ‹‹የቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያዊ ምግባር በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነት ከፍተኛ የቅድስና ማዕርግ የሚሰጠው ነው፤›› ያሉት ሊቀ ጳጳሱ የጸሎት ቤቱ ‹‹ታሪኩ በተፈጸመበት አገር በወንጌላዊው ስም ቤተ መቅደስ እስከሚታነጽ ድረስ›› የተደራጀ መኾኑን መናገራቸውን አቶ አማከለ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡

በኢየሩሳሌም ይዞታ ያላቸው የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች፣ የአገራቸው ስሞች በተገለጹባቸው የታረክ ቦታዎች ላይ መታሰቢያ እየሠሩ፣ ቤተ ክርስቲያን እያሳነጹ፣ ገዳማት እየገደሙ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያበረክቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ጸሐፊው እንደሚሉት የወንጌላዊውን ቤተ መቅደስ በቦታው ለማነጽና የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ መታሰቢያ ለመመሥረት የገዳማቱ አስተዳደር እንዲኹም እንደ ኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ያሉት አካላት ሙከራ ከማድረግ አልቦዘኑም ነበር፡፡

ይኹንና ታሪኩ የተፈጸመበት ቅዱስ ቦታ ይዞታነቱ ከክርስትና እምነት በተለዩ ወገኖች እጅ ስለኾነ አማካይ ቦታ ለማግኘት አዳግቷል፡፡ አኹንም ቢኾን የገዳማቱ አስተዳደር ታሪኩ በተፈጸመበት ቦታ አቅራቢያ መለስተኛ ቦታ አግኝቶ መታሰቢያውን ለማቋቋም በማጠያየቅና በማስጠየቅ ላይ ሲኾን፤ ለዚኹ አቋምም የኢትዮጵያ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም በገንዘብ በኩል ትብብርና ድጋፍ እንደሚሰጥ መገለጹን ዘግበዋል፡፡ የወንጌላዊው ቤተ መቅደስ የገዳሙ ማኅበር ከሚያከብራቸው ዐበይት በዓላት እንደ አንዱ ኾኖ በየወሩና በየዓመቱ ሥርዐተ ቅዳሴ ይፈጸምበታል – ‹‹በመምህራችንና በመንፈሳዊ አባታችን ቅዱስ ፊልጶስ ስም የጸሎት ቤት አዘጋጅተን በየዓመቱ መታሰቢያው እንዲከበር ማድረጋችን ተገቢ ነው፤ መምህርን ማስታወስ ትምህርቱን አለመዘንጋት ነውና›› ብለዋል ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አትናቴዎስ ፡፡

Ye Filpos Minch

በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ካልዕ ሊቀ ጳጳስ ዘኢየሩሳሌም በ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ለነበሩት ፊታውራሪ ዘውዴ ኦቶሮ የቅዱስ ፊልጶስ ምንጭን ባስጎበኙበት ወቅት በስፍራው ላይ ቤተ ክርስቲያን ለማሳነጽ የነበራቸውን ዕቅድ ገልጸውላቸው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኙት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ይዞታዎች የሚጠበቁበት አቋም ሊጠናከር እንደሚገባ ለአምባሳደሩ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕነታቸው፣ በዐሥራ አንድ ዓመታት አገልግሎታቸው በአስተዳደር ችሎታቸው ለገዳማቱ ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ባለውለታ አባት በመኾናቸው ስመ ዝክራቸው በቅዳሴና በዘወትር ጸሎተ ማኅበር ሲታወስ ይኖራል፡፡/ፎቶና መግለጫ: አማከለ ገበየሁ ግርማዬ/

አቶ አማከለ የወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ ምንጭ ይዞታ ከመረከብና ከማስከበር ጋራ በተያያዘ በመጽሐፎቻቸው ያካተቱት ሌላው ዘገባ፣ ለኹለተኛ ጊዜ በሊቀ ጵጵስና ተመድበው ከጥቅምት ፲፱፻፹፭ – ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ድረስ ገዳማቱን የመሩት ነፍስ ኄር ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ካልዕ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው በ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩትን ፊታውራሪ ዘውዴ ኦቶሮን ምንጩን ባስጎበኟቸው ወቅት ባስተላለፉት መልእክት÷ በኢየሩሳሌም የሚገኙት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ይዞታዎች የሚጠበቁበት አቋም ሊጠናከር እንደሚገባና ለዚኽም የፊልጶስ ምንጭ ከተባለው ቦታ ላይ የኢትዮጵያ ጥንተ ክርስትናዋ የሚገለጽበት ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸውላቸው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፡- በአሮጌዋና አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳምን ጨምሮ የደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም፣ ቤተ ዮርዳኖስ ገዳም፣ ቤተ ገብርኤል ገዳም፣ ምስካበ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳምና ደብረ ኢየሱስ ገዳም የመሳሰሉ ሰባት የታሪክና የቅድስና ይዞታዎች ያሏት ሲኾን ይዞታቸው የተገኘውም በንጉሣዊ ስጦታ፣ በውርስና በግዥ መኾኑን ጸሐፊው ያብራራሉ፡፡ በኢየሩሳሌም የቤተ ፊልጶስ፣ በናዝሬት ከተማ የቤተ ማርያም(ሚካኤል ወገብርኤል) እና በናባው ተራራ የቤተ ሙሴ ገዳማት ምሥረታም በቀጣዩ ዘመን በዕቅድ የሚጠበቅ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

St.Philip and the Ethiopian Eunch St. Backos

ወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ እና ቅዱስ ሕፅዋ ለሕንደኬ ንግሥተ ኢትዮጵያ

በቂሳርያ ዘፍልስጥኤም የወደብ ከተማ ተወልዶ ያደገው ወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሳርያ ሲያስተምር አምኖ ተከትሎታል፤ ከሞተ እስጢፋኖስ በኋላ በሰማርያ ወንጌልን ማስተማር የጀመረው ወንጌላዊው ቅዱስ ፊልጶስ ከትምህርቱ ጣዕምና ከሚያደርገው ተኣምራት የተነሣ ብዙ ሕዝብ በክርስቶስ ስም እያመነ ተጠምቋል፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በገንዘብ ለመግዛት የፈለገውን ጠንቋዩን ሲሞን መሠርይንም በትምህርትና በተኣምራቱ አሳምኖታል፡፡ (ግብ.፰÷፱ – ፳፬) በቂሳርያ አስተምሮ በዚያው ዐርፏል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፊልጶስ የክርስትና አባቷ ስለኾነ በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንፃ ጽላት ቀርፃ ታከብረዋለች፤ በጸሎቱና በአማላጅነቱም ትታመናለች፡፡

በመጀመሪያው ስብከተ ሐዋርያት የክርስትናን እምነት ለመቀበል የታደለው የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪቃዊ ክርስቲያን ጃንደረባው ባኮስም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእምነትና ሥርዐተ አምልኮ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ነው፡፡ ጃንደረባው በኢየሩሳሌም የአክብሮ በዓል ጉዞው ወደ አገሩ ተመልሶ ከቅዱስ ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የሰማውን ለወገኖቹ ኢትዮጵያውያን አስተምሯል፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት›› የሚባለው አውሳብዮስ የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስን ግብረ ሐዋርያት መሠረት አድርጎ፣ ‹‹ሕፅው ለወገኖቹ ሐዋርያ ኾነ፤ የኢትዮጵያ ሐዋርያ እርሱ ነው›› ይለዋል፡፡ ትውፊትና ታሪክ እንደሚያስረዱት ጃንደረባው ወደ አኵስም ከመጣ በኋላ መጀመሪያ ያጠመቀው ንግሥት ሕንደኬን ሲኾን ከእርሷም በኋላ መሳፍንቱና መኳንንቱ አምነው ተጠምቀዋል፡፡

ከአኵስም ቀጥሎ ኑቢያን አስተምሯል፡፡ በዚኽ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በጃንደረባው ይሰጥ በነበረው ትምህርተ ወንጌል ላይ የበለጠ ሐዋርያዊ ብርሃን አበራበት፡፡ ከጃንደረባው ጋራ ብዙ ቦታዎችን በማስተማሩም ታሪክ ጸሐፊዎቹ ሩፊኖስና ሶቅራጥስ ቅዱስ ማቴዎስን የኢትዮጵያ ሐዋርያ፣ ኢትዮጵያንም መንበረ ማቴዎስ በማለት ይጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከሀገሩ ቀጥሎ ወደ የመን በመሻገር ክርስትናን ከሰበከ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ አምርቷል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ ሳለ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ስለ ጃንደረባው በደረሱት ድርሰት፡-

በርስትኽ በኢትዮጵያ
በአቅራቢያዋ በኖብያ፣ በአሎድያ፣
ዳግመኛም እስከ ናፕታና ሶባ ድረስ
ክርስትናን ለመስበክ የዞርኽ የሕንደኬና የሕዝብዋ ሹም ሆይ፣
በአፍሪቃ ችግር እንዳይኖር ጠብቃት እያልኽ ወደ ጌታኽ ጸልይ፤

በማለት ጃንደረባው ለኢትዮጵያ የክርስትና ሰባኪ ብቻ ሳይኾን ስለ አፍሪቃ ኹሉ የምልጃ ጸሎት ማቅረብ የሚችል ቅዱስ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም እኒኹ ብሔራዊ ሊቃውንት፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ፊልጶስን ትምህርት ከጃንደረባው ሰምተው ለድንግል ማርያም ልጅ ይሰግዳሉ…›› በማለት ይገልጣሉ፡፡ ይህ አገላለጥ ጃንደረባው በመንፈስ ቅዱስ ከተላከለት አስተማሪው ከቅዱስ ፊልጶስ የተማረውን ትምህርት ለኢትዮጵያውያን በማስተማሩ ቅ/ዳዊት በመዝሙሩ ፸፩÷፱ ‹‹በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ›› ሲል የተናገረው ትንቢት እንደተፈጸመ ያሳያል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሕፅዋ ለሕንደኬ ንግሥተ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን ቅዱሳን አንዱ እንደኾነ ታስተምራለች፡፡ /የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.፣ ገጽ 211/

Advertisements

5 thoughts on “በሦስት አህጉረ ስብከት ከ3200 በላይ ወገኖች ተጠመቁ – ዜና ጥምቀትን ያሰማን ጃንደረባው ባኮስ የተጠመቀበት የፊልጶስ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽበት እየተጠየቀ ነው

 1. Mulusew Andualem February 2, 2015 at 7:29 am Reply

  Endenezare Egziabehair kemechewum belay tegeboal or desbelotal k 3200 belay beteseb magegnety mechem yemayetaseb new. yepetros sebket zarem bemert yebetekerstiyan legoch tedegem enam medehanit alem yabertachuh yetetemekutenem meketatelena yemigelegelubeten masefafat yegebal elaslehu
  Mulusew Andualem

 2. መምሩ February 3, 2015 at 11:10 am Reply

  ዜና ጥምቀትን ያሰማን ጃንደረባው ባኮስ የተጠመቀበት የፊልጶስ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽበት እየተጠየቀ ነው
  ሃሳቡ ጥሩ ነበር የጉዞ ወኪሎችም በዚህ ይተባበሩ ማለታችሁ ብዙም ስሜት አልሰጠኝም
  ከጉዞ ወኪል ማነው የሚተባበረው?
  ኢየሩሳሌም መተሰቢያ ነው? ለራሱ የጡረተኞች ማከማቻ
  ዮድ አቢሲኒያ ነው ? አርፎ ክትፎውን ይቸርችር እንጂ
  እጅጋየሁ ነች? ከግብረ ሰዶማዊው አሸናፊ መኮንን ጋር ሆና ታጨብጭብ እንጂ
  ሀሳባችሁ ቅንነት የተሞላው ከሆነ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊያንን ሰብስቦ መላ መፈለግ ይሻላል።
  ሌላ ሌላውን ተዉት

 3. መምሩ February 9, 2015 at 4:53 am Reply

  ይህን አንባችሀል
  ለምን ስለግብረ ሰዶማዊው አሸናፊ መኮንን አትጽፉም?
  የኃጢአት ትንሽ ባይኖረውም ከሴት ጋር ከመተኛት ወንድ ከወንድ ጋር መተኛቱ በጣም ያስከፋል። ቃሉም ለማይረባ አዕምሮ ተላልፎ መሰጠት ነው የሚለው። ተከስተ አገልግሎት አቁሟል አሸናፊ መኮንን ግን አይኑን በጨው አጥቦ አሁንም ያገለግላል። ያድማል ያሳድማል። ከጥቂት አውደልዳይ ሰባኪ እና ሀብታም ሴቶች በቀር ለእግዚአብሔር ክብር የሚቀኑ መንፈሳዊ ሰዎች ሁሉ ንስሀ ግባ ተመለስ ቢሉት እምቢ ብሎ ስላስቸገረ ተለይተውታል።

  ከጎንደር እስከ ባሌ ድረስ ያሉ ግብረ ሰዶማዊያንን ሰብስቦ በአዲስ አበባ ያሉ ግብረ ሰዶማዊያንን እና ጥቄት የዋህ ምዕመናንን ሰብስቦ በኢየሱስ ስም የሚቀልድ ደፋርና ባለጌ ሰውን መግለጽና ማጋለጥ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው።

 4. Anonymous February 11, 2015 at 4:09 pm Reply

  why you forget the church crisis in Joburg and Pretoria ?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: