ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ግብጽን ይጎበኛሉ

His Holiness Abune Mathias Patriarch of The Ethiopian Orthodox Church and His Holiness Abune Tawodros 118th Pope of Egypt Orthodox Church

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (በግራ) እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የእስክንድርያ ፻፲፰ኛ ፖፕ እና ፓትርያርክ ዘመንበረ ማርቆስ (በቀኝ)

ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በግብጽ የአምስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ነገ፣ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ማምሻውን ወደዚያው እንደሚያመሩ ተገለጸ፡፡

የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ግብጽን የሚጎበኙት፣ ከመንበረ ማርቆስ ፻፲፰ኛ ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በተደጋጋሚ ሲቀርብ በነበረ ግብዣ እንደኾነ ተገልጧል፡፡

ፓትርያርኩ ከጥር ፪ – ፮ ቀን በግብጽ በሚኖራቸው ቆይታ፣ የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያን በሃይማኖት አንድነት የመደጋገፍና የቆየውን ግንኙነት አጠናክሮ የመቀጠል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገሩ ቀደም ብለው የጠቆሙ ቢኾንም የታላቁ የሕዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በተመለከተ ከየአገሮቻቸው መንግሥታት አቋም አኳያ የሚኖራቸው ሚና የውይይታቸው ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚኾን ተመልክቷል፡፡

ከሢመተ ፕትርክናቸው አስቀድሞ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ፓትርያርኩ፣ ስለ ዴር ሡልጣን የታሪክና የቅድስና ይዞታችን ከኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የገባንበትን ውዝግብ ለመፍታት በዘመነ ፕትርክናቸው ስለሚኖረው አማራጭ መፍትሔ በሚያዝያ ወር ፳፻፭ ዓ.ም. ከታተመው ዜና ቤተ ክርስቲያን መጽሔት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ዴር ሡልጣን ከማርጀቱ የተነሣ አደጋ ላይ ነው ያለው፤ ልናድሰው ይፈቀድልን ስንል እስራኤላውያን ከግብጾች ጋራ ካልተስማማችኹ አይኾንም ብለውናል፡፡ በዚኽ የተነሣ እስከ አኹን ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ አኹን ያለው አማራጭ መፍትሔ የኛ ሲኖዶስ ከግብጽ ሲኖዶስ ጋራ ተወያይቶ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ የአኹኑ ጉብኝታቸው በግፍ መነጠቃችን ሳይበቃ ከእድሳት ማጣት የተነሣ ጥፋት ለሚያሰጋው የታሪክና የቅድስና ይዞታችን ሲኖዶሳዊ መፍትሔ የሚመቻችበት ስለመኾኑ ለጊዜው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከሢመተ ፕትርክናቸው በኋላ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚያካሒዱት ጉብኝት የመጀመሪያቸው ሲኾን በጥቅምት ወር ፳፻፮ ዓ.ም. በአሜሪካ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀጥሎ ደግሞ ኹለተኛው ይኾናል፡፡

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ብፁዓን አባቶች÷ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ አቡነ ገብርኤል የሲዳማና ጉጂ ሊበን ቦረና አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና አቡነ ያሬድ የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ አብረው እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አኃት አብያተ ክርስቲያን ጋራ ያላትንና የሚኖራትን ግንኙነት ከሃይማኖትና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር እየገመገመ የሚያስፋፋና የሚያጠናክር ሲኾን፣ የዚኹ ጉብኝት አስፈላጊነትም በቅዱስ ሲኖዶሱ ቀርቦ ከታየ በኋላ የታመነበትና የተወሰነበት መኾኑ ተጠቅሷል፡፡

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሐዋርያነት እንጂ ከግብጽ ሐዋርያ ተልኮላት አልነበረም፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ግን ከኢትዮጵያ ተልኮ ጵጵስናን የተቀበለው ከግብጽ ነው፡፡ ጵጵስናን ከእስክንድርያ ማምጣት ደግሞ ክርስትናን ማምጣት ማለት አይደለም፡፡ የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት የእናትነትና የልጅነት መሠረት እንዳለ ኾኖ ግንኙነቱ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው በእኩልነት ተዐቅቦ ነበር፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ›› በሚለው ጥቅምን መነሻ ያደረገ የግብጻውያን ሰው ሠራሽ ሐረግ እንደ አንድ የእስክንድርያ ሀገረ ስብከት እየተቆጠረች ለአያሌ ዓመታት ታስራ የኖረችው ቤተ ክርስቲያናችን፣ የመንበረ ፕትርክናዋን ነፃነት በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ከተቀዳጀች በኋላ ከእስክንድርያ ጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ በመንፈስ የምትተባበርበት ኹኔታ አጽጾ ቆይቷል፡፡

የኹለቱ አብያተ ክርስቲያን ግንኙነት በኹለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ምክንያት አድርጎ ክፉኛ ከሻከረበት ከ፲፱፻፷ዎቹ መጨረሻ ወዲኽ መሻሻል ያሳየው የቀድሞው ፓትርያርኮች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ ባደረጓቸው ጉብኝቶችና በተፈራረሟቸው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አንድነትን የማጠናከር ስምምነቶች ነው፡፡

ፖፕ ታዎድሮስ እና ፕሬዝዳንት አልሲሲ

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታሕ አልሲሲ በገና ክብረ በዓል ዋዜማ በድንገት በአባሲያ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የኮፕት ክርስቲያን ግብጻውያንን እንኳን አደረሳችኁ ብለዋቸዋል

በአኹኑ የፓትርያርኩ ጉብኝት ከሕዳሴው ግድብ ጋራ በተያያዘ ዋነኛ አጀንዳ ይኾናል የተባለው የዓባይ ወንዝ፣ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ስሜት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ነገሥታት የግብጽ ሡልጣኖች (ዛሬ በፎቶው ላይ እንደሚታየው ሳይኾን) በኮፕት ክርስቲያኖች ላይ ያከበዱትን የመከራ ቀንበር ለማቅለል ፍሰቱን የሚቀንሱ ርምጃዎችን እንደ ማስፈራሪያ ይጠቀሙበት እንደነበር ከዛጔ ነገሥታት አንዱ በነበረው በይምርሐነ ክርስቶስ ታሪክ እንረዳለን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎዶር ካልዕ በቅርቡ ላነጋገሯቸው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ልኡካን እንዳረጋገጡት ደግሞ፣ ‹‹የሕዳሴው ግድብ የግብጽን ጥቅም አይጎዳም፤ እንዲያውም ከግጭት ይልቅ የኹለቱ አገሮች ሰላምና መተባበር ምክንያት(ምንጭ) መኾን ይገባዋል፡፡›› ለዚኽም ከፖሊቲካ መሪዎች በተሻለ፣ በታሪክ ለኹለቱ አገሮች የውጭ ግንኙነት ወሳኝ አስተዋፅኦ የነበራቸው የሃይማኖት ተቋማት የበለጠ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል በልኡካን ቡድኑ ተገልጧል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: