በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ኅልፈት ‹‹ሐዘኑ የቤተ ክርስቲያን ነው›› /ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/

  • ‹‹…ወንድማችንን እናውቃቸዋለን፤ በእውነቱ ለፌ ወለፌ የማይሉ ደረቅ ሊቅ ናቸው፤ በሃይማኖቱ ዘርፍ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንዲቱም ነጥብ እንዳትዛባ ከወንድሞቻቸው ጋራ ብዙ ትግል ያደረጉ አለኝታ ሊቅ ነበሩ፤ እርሳቸውን ማጣታችን ትልቅ ጉዳት ነው፤ ሐዘኑ የልጆቻቸውም አይደለም፤ ሐዘንተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ እግዚአብሔር ለዚኽች እናት ቤተ ክርስቲያን እርሳቸውን የመሰለ ይተካልን ከማለት በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡››

ከዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከል መላ ዘመናቸውን ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና መከበር በጽናት ሲያስተምሩ፣ ሲጽፉና ሲሟገቱ ኖረው ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ወደ ዘላለም ዕረፍት የተጠሩት የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ሥርዓተ ቀብር ታኅሣሥ ፳ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

የሊቁ ዜና ዕረፍት ከተሰማበት ጊዜ አንሥቶ ለሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱና ሥርዐተ ቀብሩ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት፣ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ለ፳ አጥቢያ ምሽት 3፡00 ጀምሮ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩና ከተለያዩ አድባራት የተሰባሰቡ ሊቃውንትና መዘምራን በመኖርያ ቤታቸው በመገኘት ሰዓታቱን ቆመው ማሕሌቱን ሲያደርሱ አድረዋል፡፡

ሊቁ አያሌ አገልግሎት የሰጡበት የሰበካቸው የቀበና መካነ ሕይወት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ሰዓታቱንና ማሕሌቱን የመሩ ሲኾን ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ ደግሞ ሥርዓተ ፍትሐቱን በማከናወን ጸሎተ ግንዘቱን ፈጽመዋል፡፡ በዚኹም ሰዓት መዘምራኑ አደራረሱን በዐቢይ ስብሐተ ነግህ አድርሰዋል፡፡

የሊቁ ዐፅም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ በብፁዓን አባቶችና በቤተሰቡ ምክር በተወሰነው መሠረት÷ ከቀኑ 5፡00 ሲኾን ግራና ቀኝ ተሰልፈው መዝሙረ ሐዘን የሚያሰሙ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችና ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፤ ቃጭል የሚመቱ፣ መስቀልና ጃንጥላ የያዙ ዲያቆናት፤ ጽንሐሕና ጃንጥላ የያዙ ካህናት፤ የሊቁን ሥዕለ ገጽና የማዕርግ አልባሳት የሚያሳዩ ልኡካን፤ የአድባራት አለቆችና ሐዘንተኞች ምእመናን እንደ ቅደም ተከተላቸው አስከሬኑን የያዘውን መኪና በመሐል አድርገውና በክብር አጅበው ጉዞ ወደ ካቴድራሉ ኾኗል፡፡

Lique Kahinat Kinfe Gabriel Funeral service

አስከሬኑን የያዘው መኪና በካቴድራሉ ሲደርስ የደወል ድምፅ ተሰምቷል፤ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መሪነትም ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖለታል፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው እንዳበቃ አስከሬኑ ወደ ዐውደ ምሕረት ወጥቶ መርሐ ግብሩ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል እየተመራ፣ ከየአድባራቱ የተሰባሰቡት ሊቃውንት ሰላም የተባለውን ድጓ አለዝበው ለዐሥራ አምስት ደቂቃ ያኽል አሸብሽበዋል፡፡ በማያያዝም ሊቁ በተለይም በየዓመቱ በኅዳር ጽዮን ማርያም ክብረ በዓል እየወረዱ የሚያገለግሏቸውና በርእሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ገዳም ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት መልሴ የሚመሩ የገዳሟ ሊቃውንትም፡- አበ ኵልነ አባ ክንፈ ገብርኤል እያሉግሳዊ ጣዕመ ዝማሬ በሽብሻቦ አሰምተዋል፡፡

ከሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ጋራ በሊቃውንት ጉባኤ ለረጅም ጊዜ አብረው እንደሠሩ የገለጹት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ‹‹ወንድማችን ስለኾኑና አብረን ብዙ ዘመን ስለሠራን ኹላችንም ሐዘንተኞች ነን›› ካሉ በኋላ የሊቀ ካህናትን ታላቅነትና የኅልፈታቸውን አስደናቂነት የሚዘክር አንድ ሥላሴ ቅኔ አበርክተዋል፤ ወዳጃቸው መልአከ አርያም ሐረገ ወይንም አንድ መወድስ ቅኔ አሰምተዋል፡፡

የሊቁን ዜና ሕይወት ወዕረፍት የሚናገረው ታሪክ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የአስተዳደር ሓላፊ በነበሩትና አኹን ሰባኬ ወንጌል በኾኑት መልአከ ብርሃን ኢሳይያስ ወንድምአገኘኹ በንባብ ከተማ በኋላ የዕለቱ ትምህርት በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ተሰጥቷል፡፡ ሊቁ በት/ቤት ብዙ ከደከሙ በኋላ በተለይም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳይዛባ በተገቢው መንገድ ያገለገሉና በሃይማኖት ጽናት የተከራከሩ አባት እንደነበሩ የመሰከሩት ብፁዕነታቸው፣ ተጠያቂውን ሊቅና ታላቁን ምሁር ማጣት ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ጉዳት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

የዐሥርት ዓመታት ድካም የሚጠይቀውን ትምህርት ተምሮ እንደሚገባው የሚያገለግል ሊቅ ለማግኘት ብዙ ጥረት የሚጠይቅ በመኾኑ፣ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር በሕይወት የቀሩትን በጣት የሚቆጠሩ ሊቃውንት ዕድሜ አርዝሞ በጤና እንዲያቆያቸው፣ እንደ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ድካማቸውን ፈጽመው በደኅና በተሸኙት ሊቃውንት እግር እንዲተካም ብፁዕነታቸው በትምህርታቸው ተማፅነዋል፡፡

የሊቁ ዕረፍት ክንፈ ገብርኤል ተብለው በተጠሩበት በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ዕለት መኾኑ ግን የአካሔዳቸውን መልካምነት የሚያሳይ ትልቅ ምልክት እንደኾነ በመግለጽ ቤተሰቦቻቸውንና ሐዘንተኞችን አጽናንተዋል – ‹‹የክንፈ ገብርኤል ዋጋ ተከፍሏል ማለት ነው›› ሲሉም የቅዱሳን አምላክ ነፍሳቸው በተድላ ገነት እንዲያሳርፍ ጸልየዋል፤ የሊቁን ሥርዓተ ቀብር ለማስፈጸም በአገልግሎት ሲደክሙ ያደሩና የዋሉ ሊቃውንትንና መዘምራንንም ‹‹ለእናንተም ብድር ይግባችኹ፤ መቼም መሸኛኘት አይቀርም፤ ለእናንተም እንደዚኹ የሚያከብር ይላክላችኹ›› ሲሉ አመስግነዋቸዋል፡፡

His Grace Abune Qewostos

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ

በመንፈስ ቅዱስ ይመራ የነበረው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የእያንዳንዱን ቅዱስ አባት፣ የእያንዳንዱን ሊቅ ቅድስና፣ የሕይወት ታሪክ ቀደም ብሎ ስለታየው ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ‹‹ይህ ቅዱስ አባት ከሕፃንነቱ ጀምሮ ባለ ዘመኑ ኹሉ ከቤተ እግዚአብሔር ሳይለይ እግዚአብሔርን ያገለገለ ቅዱስ ነው፡፡ እናት አባት ለሌላቸው አባት ነው፡፡ ችግር ለጸናባቸው ባልቴቶች ችግራቸውን የሚያስወግድ ነው፡፡ በተቀደሰ ክህነት እግዚአብሔርን ያገለገለ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡›› ሲል ለብዙዎቹ መስክሯል፡፡ ከብዙዎቹ መካከል አንዱ አኹን ታሪካቸው በዝርዝር የሰማነው ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ናቸው፡፡

እኒኽ ታላቅ ሊቅ ቅዱስ አባት ዛሬ በጥሩ አካሔድ ነው የሔዱት፡፡ ሐዘኑ የቤተ ክርስቲያን ነው፤ የልጆቻቸውም አይደለም፡፡ ልጆቻቸውን አስተካክለዋል፤ ለወግ ለማዕርግ አድርሰዋል፡፡ ሐዘንተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ተጠያቂ ሊቅ አጥታለች፤ ታላቅ ሊቅ ተለይቶናል፡፡

እኒኽ ታላቅ ሊቅ በትምህርት ቤት ብዙ ደክመዋል፤ ከት/ቤት በኋላ ቅድም በዜና ሕይወታቸው እንደተገለጸው በተገቢው መንገድ አገልግለዋል፡፡ ተጠያቂ ሊቅ ነበሩ፤ ለሃይማኖት የቆሙ ሊቅ ነበሩ፤ በሃይማኖቱም ዘርፍ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንዲቱም ነጥብ እንዳትዛባ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ፣ የቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ፣ ታላቅ ምሁር እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ እኒኽን ማጣት ትልቅ ሐዘን ነው፤ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡

አዎ! ብዙዎች ባለዲግሪዎች አሉ፤ ዲግሪ ይፈለጋል፤ የሚናቅም አይደለም፡፡ ዳሩ ግን እንዲኽ እንደ እርሳቸው በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳይደክሙ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በዲግሪው ብቻ ላገልግል ቢባል አይቻልም፤ ድግር ይኾናል ዲግሪው! የቤተ ክርስቲያን አካሔድ፣ ምስጢረ ሃይማኖቱ ከባድ ነው፡፡ ምስጢረ ተዋሕዶ ድካም ይጠይቃል፤ ኻያ፣ ሠላሳ፣ ዐርባ ዓመት የትምህርት ጊዜ ይጠይቃል፤ ኻያ፣ ሠላሳ፣ ዐርባ ዓመት ተምሮ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባው የሚያገለግል ሊቅ ለማግኘት ስንት ጥረት ይጠይቃል? ትልቅ ጉዳት ነው፡፡

ትልቅ ጉዳት ነው፤ ወንድማችንን እናውቃቸዋለን፤ በእውነቱ ደረቅ ሊቅ ናቸው፤ ለፌ ወለፌ የማይሉ፣ ከወንድሞቻቸው ጋራ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ብዙ ትግል ያደረጉ አለኝታ ሊቅ ነበሩ፡፡ እርሳቸውን በማጣታችን አዝነናል፡፡ እግዚአብሔር ለዚኽች እናት ቤተ ክርስቲያን እርሳቸውን የመሰለ ይተካልን ከማለት በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን÷ በእውነቱ ከሌሊቱ ሰዓት ጀምራችኹ ያቀረባችኹት አገልግሎት፣ የከፈላችኹት መሥዋዕት እጅግ በጣም የሚያስመሰግን ነው፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችኹ፤ ዋጋችኹን ይክፈላችኹ፤ ለእናንተም ብድር ይግባችኹ፡፡ መቼም መሸኛኘት አይቀርም፤ አይደለም? ለእናንተም እንደዚኹ የሚያከብር ይላክላችኹ፡፡

ልጆች ልታዝኑ አይገባችኁም፤ አስታማችኋል፤ እናውቃለን ተንገላታችኋል፤ መቼም ሥጋ የለበሰ መንገላታቱ አይቀርም፤ ነገር ግን አካሔዳቸው የቅዱሳን አካሔድ ነው፤ ደክመው ወጥተው ወርደው እጫፉ ላይ ደርሰዋል፤ ሰባ ሰማኒያ ዘመን አይደለም የተወሰነው፤ ሰባውን ጨርሰዋል፤ ትንሽ ነበር የቀራቸው በደኅና ተሸኝተዋል፡፡ በዚኽ ቅዱስ ቦታ ከወንድሞቻቸው አጠገብ እንዲያርፉ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ፈቅደው መካነ መቃብራቸው ተዘጋጅቷል፡፡

እንግዲኽ መቼም ምንም ቢኾን ጉዳይ ሲፈጽም የኖረ ታላቅ ሰው የተለየ ዕለት እሰይ ተብሎ አይሸኝም፡፡ በእውነቱ እኛ የምንወደው ሽማግሌዎቹ ሊቃውንት አልጋቸው ላይ ተኝተውም ቢኾን እንዲጠየቁ እንጂ እንዲለዩብን አንሻም፡፡ እዚያው እየተከባከብን ጥያቄ ሲመጣ እስኪ መምህር እገሌን ጠይቁ እያልን ብንልክ ነው ደስ የሚለን፡፡ አኹንም በጣት የሚቆጠሩ አባቶች ሊቃውንት አሉ፤ የእነርሱን ዕድሜ እግዚአብሔር ያርዝምልን፤ የወንድማችንን የሊቁን ነፍስ በተድላ ገነት ያኑርልን፡፡

እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ቃል ኪዳን ሲሰጥ፣ ‹‹በስምኽ የተጠራውን ከአንተ ጋራ ዋጋውን እከፍለዋለኹ›› አለ፡፡ ሊቁ ወንድማችን፣ ክንፈ ገብርኤል ተብለው ሲጠሩ ዕረፍታቸውን የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል በዓል በሚከበርበት ቀን አደረገው፡፡ ይህም አንድ ትልቅ ምልክት ነው፡፡ የክንፈ ገብርኤል ዋጋ ተከፍሏል ማለት ነው፡፡ የወንድማችንን የክንፈ ገብርኤልን ነፍስ በተድላ ገነት ያኑርልን፤ ለእናተንም የድካማችኹን ዋጋ ይክፈላችኹ፡፡


የሊቁ የሕይወት ታሪክ በሚነበብበት ወቅት በካቴድራሉ ደቡባዊ አንቀጽ ከሚገኝ ታላቅ የጥድ ዛፍ ላይ ማንም ሳይነካው አንድ ትልቅ ቅርንጫፍ ተገንድሶ መውደቁ ብፁዕነታቸው ከጠቀሱት የምልክት ጉዳይ ጋራ ተያይዞ የበርካታ ሐዘንተኞች መነጋገርያ ኾኗል፡፡ ይህንንም ድንቅ ከአስተዋሉት ሐዘንተኞች አንዱ የኾነው የነገረ ቤተ ክርስቲያን ተመራማሪው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የትልቁ ዋርካ ትልቁ ቅርንጫፍ በሚል ርእስ የሊቁን ዕረፍት አስመልክቶ በጡመራ መድረኩ ባሰፈረው ማስታዎሻ፡- ‹‹በቦታው የነበሩ፣ ይህንንም ነገር የተመለከቱ ኹሉ ታሪኩን በካሜራቸው ሲቀርፁና ከታላቋ ዋርካ ከቤተ ክርስቲያን ብዙዎችን የያዘው አንዱ ታላቅ ቅርንጫፍ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ዛሬ መሰናበቱን በሐዘን ሲተረጉሙ ነበር፤›› በማለት አትቶታል፤ የቅርንጫፉን ቅጠልም ብዙዎች ተሻምተው ሲወስዱ መመልከቱን ጦማሪው በማስታዎሻው ገልጧል፡፡

good omen on the funeral service of Archpriest Kinfe Gabriel

ከታላቋ ዋርካ ከቤተ ክርስቲያን አንዱ ታላቅ ቅርንጫፍ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ዛሬ ስለ መሰናበቱ…

ከርእሰ አድባራት ቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበዓል አከባበር ጉዟቸው እንደተመለሱ ከስፍራው መድረሳቸው የተገለጸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት ቃለ ምዕዳን÷ ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ጥሪውን ሲልክ ከሰዓቱ የሚያልፍ ባለመኖሩ ወንድማችን ከእኛ በሥጋ ተለይተዋል፤ በዐጸደ ነፍስ ግን ሕያው ናቸው፤ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ ሠርተዋልና›› በማለት ሐዘንተኞችን አጽናንተዋል፤ ለአስከሬኑ ዑደት ከተደረገ በኋላም በምሥራቃዊ አንቀጽ የተዘጋጀው መካነ መቃብር በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡

ከሊቃውንት የተበረከቱ ቅኔዎች

 ሥላሴ ዘመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን

እንዘ ሞት መሬታዊ ዘሰማያዊ ለእሊአኹ
መኑ አዘዘ ይዕዜ ወተአደወ ሥርዓተ
ገብርኤል በክንፉ ከመ ይጹር ሞተ
ወቤተ ክርስቲያን ዘኮንኪ ዘክንፈ ገብርኤል ቤተ
አስምዑ ምድረ ወሰማያተ
ይግበሩ ለኪ እምዕለት ዕለተ
ዘከማሁ አእላፈ ኖሎተ፡፡

መወድስ ዘመልአከ አርያም ሐረገ ወይን ደምሴ

እስራኤል አዕፅምት አመ ተጼወዉ መቃብረ አበው የኀድር
እንዘ በአካል ኢይፃሙ፡፡
ልዑከ ኤርሚያስ ባሮክ ለክንፈ ገብርኤል ዐፅሙ
በክሳደ ንስር አስቆቅዎ ለኤርሚያስ ከመ ተፈነወ
ጳውሎስ ማኅተሙ፡፡
ድቀተ እስራኤል ኀዘነ ልብ ከመ ለዘመን ቀርበ
ጽሑፈ ይንግሮሙ፡፡

ለዓለም

ዕረፍትሂ ዘይዕዜ ለአቤሜሌክ ንዋሙ
ለክንፈ ገብርኤል ይኤድሞ ወይትርአዮ በውስተ ሕልሙ፡፡
አምጣነ ፈነዎ ኤርሚያስ ባቢሎናዊ ሕማሙ
በቆጽለ በለስ ለሕሙማን ኃይላተ ፈጣሪ ይፈውሶሙ፡፡

የሊቁ በረከታቸው ይደረብን፤ እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን፤ አሜን፡፡

Advertisements

4 thoughts on “በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ኅልፈት ‹‹ሐዘኑ የቤተ ክርስቲያን ነው›› /ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/

  1. TIRSIT WUBIE January 1, 2015 at 6:20 am Reply

    የቤተክርስትያን ታላቅ መፅሀፍት ቤት ነበሩ በእውነት እንደሳቸው ያሉ ሊቃውንትን ይተካልን

  2. fekadeselassie January 2, 2015 at 9:45 pm Reply

    Telek warka telek sew atan.. Nefsachewun be’atsede Genet be’mekane kedusan yasarefelen….!!!

  3. Dereje January 3, 2015 at 8:14 am Reply

    Nefese yemarelene bereketachew yederebene.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: