ቅዱስ ሲኖዶስ 141 ሚልዮን ብር ዓመታዊ በጀት አጸደቀ፤ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ነገ ይጠናቀቃል፤ ጋዜጣዊ መግለጫም ይሰጣል

 • የቤተ ክርስቲያናችን የበጀት ዓመት÷ የአህጉረ ስብከት የፐርሰንት ፈሰስ ተጠቃሎ ገብቶ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተቀምሮና ተደልድሎ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚጸድቅበት ወቅት አንጻር ቢጤንስ?
Holy Synod Fathers

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ኹሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ናቸው፡፡ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እያንዳንዱ ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ነው፡፡

ውጥረት በተመላበት ኹኔታ ተጀምሮ ተጋግሎ የሰነበተውና በመጨረሻም ወደ መግባባትና አንድነት የመጣው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ÷ ለኹለት ሱባዔ ያኽል ሲያካሒድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ነገ፣ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀትር በፊት ያጠናቅቃል፡፡

his holiness abune Mathias

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጎችን፣ የተላለፉ መመሪያዎችንና የተሰጡ ውሳኔዎችን ለሚመለከታቸው ኹሉ በፊርማቸው ያስተላልፋሉ

በስብሰባው ማጠናቀቂያ÷ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰንበቻውን ስለተነጋገረባቸው ጉዳዮች፣ ስላሳለፋቸው ውሳኔዎችና ስለወሰዳቸው አቋሞች የምልአተ ጉባኤው ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በንባብ የሚያሰሙት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ሲኾን የቅዱስ ሲኖዶሱ ቃል አቀባይ በኾኑት በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የሚመራ ጋዜጣዊ ጉባኤም ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

001kklkkk 003

የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና ቃል አቀባይ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች በተግባር ላይ መዋላቸውን ይከታተላሉ፤ ውሳኔዎቹ በሥራ ላይ ካልዋሉ ኹኔታዎቹን በመከታተል ከነምክንያቶቹ ለቅ/ሲኖዶሱ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡

 

ምልአተ ጉባኤው በትላንት ከቀትር በኋላና በዛሬው ውሎው፣ በሥራ ላይ በቆየባቸው ቀናት የመከረባቸውንና ውሳኔ ያሳለፈባቸውን ቃለ ጉባኤዎች በመናበብ የአባላቱ ፊርማ እንዲያርፍባቸው አድርጓል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተወሰኑ ውሳኔዎች፣ የወጡ ሕገጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች በቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት አማካይነት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት የሚተላለፉ ሲኾን በተግባር ላይ ስለመዋላቸው በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ክትትል ተደርጎ ስለአፈጻጸማቸው ለቅዱስ ሲኖዶሱ የሥራ አፈጻጸም ዘገባ የሚቀርብባቸው ይኾናል፡፡

ጥቅምት ፲፩ ቀን በመክፈቻ ሥርዐት ጸሎት በተጀመረው የምልአተ ጉባኤው ስብሰባው ለቀናት ሲመክር የሰነበተው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ተወያይቶ ካጸደቃቸው ዐበይት አጀንዳዎች አንዱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ አስተዳደርና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውለው ዓመታዊ በጀት ነው፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት÷ የቤተ ክርስቲያናችንን አጠቃላይ የምጣኔ ሀብትና የሙዓለ ንዋይ አስተዳደር መመሪያዎችን (ፖሊሲዎችን) የመወሰን፣ ዓመታዊ በጀቷን የማጽደቅና ተግባራዊነቱን የመቆጣጠር ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

 

 

ዓመታዊ የሥራ ዕቅዱንና በጀቱን በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን አካላትና የሥራ ዘርፎች ተሰብስቦ በሒሳብና በጀት መምሪያ አማካይነት እንዲዘጋጅ የሚያደርገው፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ሲጸድቅም በበጀት የተመደበውን ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊውና ከፋይናንስ መምሪያው ሓላፊ ጋራ በመኾን በፊርማው የሚያንቀሳቅሰው የቤተ ክህነቱ ዋና ባለሥልጣን ደግሞ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ነው፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተጠንቶና ተዘጋጅቶ በቋሚ ሲኖዶሱ በቀረበለት የ፳፻፯ ዓ.ም. የሥራ ዕቅድና በጀት ላይ የመከረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ታዲያ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ አስተዳደርና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል ብር 141 ሚልዮን ዓመታዊ በጀት ማጽደቁ ነው የተገለጸው፡፡

His Grace Abune Mathewos

ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስፈጻሚ፣ የገንዘብና ንብረት አስተዳደር የበላይ ሓላፊ በጠቅላላው የቤተ ክህነት ዋና ባለሥልጣን የኾኑት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ÷ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ያስፈጽማሉ፤ በበጀት የጸደቀውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ገንዘብና ንብረት በፊርማቸው ያንቀሳቅሳሉ፤ በየሦስት ወሩ ለቋሚ ሲኖዶስ፣ በየዓመቱ ለአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በዓመት ኹለት ጊዜ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሥራ አፈጻጸም ዘገባና በበጀት የተደገፈ የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ያቀርባሉ፡፡

በምልአተ ጉባኤው ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብና በጀት መምሪያ ሓላፊዎች ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው÷ ከበጀቱ በአመዛኙ ከሐዋርያዊ ተልእኮ (ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋትና ከማጠናከር) ጋራ ለተያያዙ ተግባራት፤ ለአብነት ት/ቤቶች እና ለገዳማት ድጋፍ እንዲኹም ለአህጉረ ስብከት የሥራ ማስኬጃ ድጎማ መደልደሉ የተመለከተ ሲኾን በካፒታል በጀት አንጻር የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በቸርችል ጎዳና ባንኮ ዲሮማ የሚያስገነባው ሕንፃ ማስጨረሻና የአኵስም ጽዮን ቤተ መዘክር ዲዛይን ክፍያም ተጠቃሽ ወጪዎች እንደኾኑ ተጠቅሷል፡፡

በበጀት ድልድሉ የሐዋርያዊ ተልእኮ እንቅስቃሴ ቀዳሚውን ድርሻ መያዙ÷ አዲስ አማንያንን በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጨመርና የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት ዋናው መፍትሔ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ ማድረግ ከመኾኑ አኳያ፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችን ተጠናክሮ የሚቀጥልበት አስፈላጊው ጥረት ኹሉ እንዲደረግ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከተያዘው አቋም የሚነሣ ነው፡፡

የአህጉረ ስብከት የበጀት ድጎማን በተመለከተ፣ በ፳፻፮ ዓ.ም. ከእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት በቀረበው የዘመኑ የገቢ ሪፖርት መሠረት÷ ከኃምሳው አህጉረ ስብከት ኻያ ሦስቱ ራሳቸውን በገቢ ችለው ትርፍ የሚያስገቡ ሲኾኑ ራሳቸውን ያልቻሉት ኻያ ሰባት አህጉረ ስብከት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድጎማ እንደሚደረግላቸው ተገልጧል፡፡

የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዐተ አምልኮት፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የማንነት፣ የሀገር በቀል ዕውቀቶች መሠረትና ምንጭ የኾኑ የአብነት ት/ቤቶቻችንን ከመጠበቅ፣ ከማሳደግና ከማስፋፋት አንፃርም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው አምስት ከመቶና ከመንበረ ፓትርያርክ የተመደበው ለመምህራኑና ለተማሪዎቹ ብቻ በትክክል እንዲደርስ ክትትሉና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት በአጠቃላይ ጉባኤ ደረጃ አቋም ተይዞበታል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃ የቤተ ክርስቲያናችን ዓመታዊ በጀት መሠረት የኾኑት ገቢዎች አጠቃላይ ምንጮች፡-

በቃለ ዓዋዲው እንደተደነገገው፡-

 • አህገረ ስብከት ከሰበካ ጉባኤ ክፍያና ከማናቸውም ገቢያቸው የሚከፍሉት 35 በመቶ ፈሰስ፤
 • የአ/አበባ ሀ/ስብከት ከሰበካ ጉባኤ ክፍያና ከማናቸውም ገቢው የሚከፍለው 65 በመቶ ፈሰስ፤

የልማት ድርጅቶች/ተቋማት ገቢ፡-

 • የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የኪራይ ገቢ
 • የቁልቢ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ
 • የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት የመጽሐፍ ሽያጭ
 • የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
 • የአልባሳት ማደራጃና ምርት ሥርጭት መምሪያ
 • የጎፋ ጥበበ እድ ካህናት ማሠልጠኛ፤
 • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የበጀት ድጎማ (እስከ አንድ ሚልዮን ብር)
 • የመንበረ ፓትርያርኩ ልዩ ልዩ የውስጥ ገቢዎች
 • ከመንግሥት የሚሰጥ ኹለት ሚልዮን ብር ድጎማ (ስላልተመለሱ ቤቶች) ናቸው፡፡

ይኹንና ከእኒኽ አጠቃላይ የገቢ ምንጮች ውስጥ÷ የአህጉረ ስብከትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፈሰስ፣ የቁልቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ እንዲኹም የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የኪራይ ገቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው በየዓመቱ ቀጣይ ዕድገት የሚመዘገብባቸውና ከፍተኛ ገቢ የሚገኘባቸው ኾነዋል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንደተደመጠው÷ በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በኩል በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት ከቤት ኪራይና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከብር 23 ሚልዮን በላይ /23‚634‚388.245.21/ ገቢ አድርጓል፡፡ ከሐምሌ ፳፻፭ ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ፳፻፮ ዓ.ም. ድረስ በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከብር 41 ሚልዮን በላይ /41‚680‚951.52/ ዓመታዊ ገቢ የተገኘ ሲኾን በጀታቸው ከገዳሙ ለኾኑ ተቋማት ከ14 ሚልዮን ብር በላይ /14‚365‚423.68/ ወጪ ተደርጎ በአኹኑ ወቅት 27 ሚልዮን ብር ያኽል/27‚315‚527.84/ በማደራጃ መምሪያው ሣጥን ውስጥ ይገኛል፡፡

the miraculous kulubi saint gabriel church

ተኣምራት ወመንክራት የሚታዩበት የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ከሐምሌ ፳፻፭ ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ፳፻፮ ዓ.ም. ድረስ በስእለትና መባዕ የገቡ ንዋያተ ቅድሳትን፣ ወርቅና ጌጣጌጦችን ሳይጨምር ከ41 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ አስገኝቷል፡፡

ብዙውን ጊዜ ከመደበኛው በጀት ሌላ ድንገተኛ ወጪ በሚያስፈልግበት ጊዜ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በቋሚ ሲኖዶስ እያስወሰኑ ወጪ በማድረግ በሥራ ላይ የሚውል የመጠባበቂያ በጀት ኾኖም ያገለግላል፡፡ ከጥሬ ገንዘቡ በተጨማሪ በተጠቀሱት ወራት በደብሩ ክብረ በዓላት በስእለት የገባው ወርቅ ተመርምሮ በብሔራዊ ባንክ እንዲቀመጥ ሲደረግ፣ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችም በማደራጃ መምሪያው ሣጥን እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ በስእለት የተገኙት ንዋያተ ቅድሳቱም እንደ ገበያው ኹኔታ በዓመት ሦስት ጊዜ የዋጋ ጥናትና ትመና ወጥቶላቸው በመሸጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

በ፴፫ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት ከእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ከኃምሳው አህጉረ ስብከት ከ95 ሚልዮን ብር በላይ የፐርሰንት ገቢ ተገኝቷል፤ ይህም ከአምናው ጋራ ሲነጻጸር ከ16 ሚልዮን ብር በላይ ብልጫ የተመዘገበበት ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ በዚኽን ያኽል ካደገ የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ገቢም ከዚኽ በበለጠ እያደገ ለመኾኑ አያጠያይቅም፡፡

በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ ፶ ንኡስ አንቀጽ (፬) እና (፭) መሠረት፣ በማናቸውም ደረጃ የሚገኘው የሰበካ አስተዳደር የበጀት ዓመት ሐምሌ ፩ ቀን ተጀምሮ ሰኔ ፴ ቀን ይዘጋል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በየደረጃው የተጠናቀረው የንብረት አያያዝና አጠባበቅ፣ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሒሳብና የሥራ ክንውን ሪፖርት እስከ ሐምሌ ፴ ቀን ድረስ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት መድረስ አለበት፤ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም የበኩሉን አጥንቶና አጣርቶ ዓመታዊው ሪፖርት እስከ ነሐሴ ፴ ቀን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡

የአህጉረ ስብከቱ ዓመታዊው የፈሰስ ሒሳብ መመዝገቢያ ቅጻቅጾችና ሪፖርቶች እስከ ነሐሴ ፴ ቀን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይድረሱ እንጂ አህጉረ ስብከቱ ፈሰሱን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ የሚያደርጉትና ገቢ ያደረጉበትን ቼክ እንደ ሥራ ፍሬ የሚያቀርቡት በጥቅምቱ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ወቅት ነው፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትም ከኹሉም አህጉረ ስብከት ባሰባሰበው ገቢ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ በጀት ከላይ እስከ ታች እንዲጠና አድርጎና ቀምሮ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በማቅረብ ሲወሰንለት ለልዩ ልዩ ሥራዎች ያውለዋል፡፡

እዚኽ ላይ የቤተ ክርስቲያናችንን የበጀት ዓመት (budget calendar) እና የበጀት ድጎማና ክፍፍል (budgetary accounting) የተመለከተ ጥያቄ መነሣቱ አልቀረም፡፡ ይኸውም በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት በማናቸውም ደረጃ የሚገኘው የሰበካ አስተዳደር የበጀት ዓመቱ ሐምሌ ፩ ቀን በሚጀምርበት ኹኔታ፣ በጀቱ የሚጸድቀው ግን መደበኛውን የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ጠብቆና በሦስት ወራት ዘግይቶ መኾኑ ጥያቄ እየተነሣበት ይገኛል፡፡ የበጀት ዓመቱ በቃለ ዓዋዲው ድንጋጌ መሠረት በሐምሌ ቢጀመርም በጀቱ እስከሚጸድቅበት ጥቅምት ወር ድረስ በታሳቢና በማብቃቃት እየሠሩ እንደሚቆዩ በመግለጽ አስተያየት የሰጡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ‹‹ባልገባና ባልጸደቀ በጀት እንዴት ሥራ ማስጀመር ይቻላል?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ከማቅረብ አኳያ÷ የአህጉረ ስብከት የፈሰስ አስተዋፅኦ እስከ ግንቦት ተሰብስቦ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ተቀምሮ የሚጸድቅበት፣ ሰኔ የዝግጅት ወር ኾኖ በሐምሌ የበጀት ዓመቱ የሚጀምርበት አሠራር እንዲጤን ይጠይቃሉ፤ አልያም የዘመን አቆጣጠር ባለቤት የኾነች ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የበጀት ዓመት ሊኖራት እንደሚችል በመጠቆም፣ የበጀት ዓመቱ በጥቅምት መባቻ የሚጀመርበትና መስከረም ፴ የሚዘጋበት አማራጭ ሊታይ እንደሚችልም ያመለክታሉ፡፡ ይህም በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን የየዓመቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሥራ ዕቅድ፣ በግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ በሰፈረው ድንጋጌ የተደገፈ መኾኑን ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን፣ በጀመርነው በጀት ዓመት ዘመናዊውንና ለቁጥጥር አመቺ የኾነውን የኹለትዮሽ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዐት ዝግጅትና ትግበራ የሚጀምርበት ሲኾን ከዚኹ ጋራም የመምሪያዎች ገቢዎች በአንድ ቋት የሚሰበሰብበት (የገቢ ማእከላዊነት) አሠራርም በቋሚ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ተፈጻሚ ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡

በዚኽም መሠረት ከኅዳር መጀመሪያ አንሥቶ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍትና ወመዘክር መምሪያ እና የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ለየራሳቸው የነበራቸው የሒሳብ ቋት ታጥፎ ገቢያቸው ወደ ማእከላዊ ቋት ገብቶ በበጀት እየወጣ እንዲጠቀሙ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

መምሪያዎቹ የገቢ ማእከላዊነቱን ቢደግፉትም የሥራ ማስኬጃ በጀታቸውን ግን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አለመደረጉ ለቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ እንደሚዳርጋቸው ይናገራሉ፡፡ የተተከለው የኹለትዮሽ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዐት ለቁጥጥርና ለተጠያቂነት አመቺ በመኾኑ የሥራ ማስኬጃ በጀቱን የሚጠቀሙበት አሠራር ከዚኹ የሒሳብ መመሪያ ጋራ እንዲጣጣም ይጠይቃሉ፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ለመግባት እየተንደረደረበት ላለው ዘመናዊው የኹለትዮሽ የሒሳብ ሥርዐት ውጤታማ አተገባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲዘረጉና ለየመምሪያዎቹ የተመደበላቸው በጀት በየዕቅዳቸው ከሚያስፈጽሙት ተልእኮ አንጻር ያለው ተገቢነት በሚገባ የሚታይበት አሳታፊ አሠራር እንዲኖር ያሳስባሉ፡፡

ይህም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አጠቃላይ ሪፖርት እንደተመለከተው÷ በያዝነው በጀት ዓመት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች በመምሪያዎቹና ድርጅቶቹ የታቀዱ፣ በአስተዳደር ጉባኤ የሚገመገሙና በተቋም ደረጃ ውጤት የሚያመጡ እንዲኾኑ ለማድረግ የሚያስችል የመልካም አስተዳደር የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሖ መሠረት የሚጣልበት ነው፡፡ በውጤቱም በተዋረድ በሚገኙት መዋቅሮች÷ ለአማሳኞች ሕገ ወጥ ጥቅምና ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች መተላለፊያ በር በመክፈት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና እየተፈታተነ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግራችንን በማስወገድ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ የሚያስችል አርኣያነት ነው፡፡

በዚኽ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በስትራተጅያዊ ዕቅድ ላይ ተመሥርቶ እንዲሠራ፣ የገንዘብ ሒሳብና ንብረት አጠባበቅም በዘመናዊው የፋይናንስ አሠራር ተግባራዊ እንዲደረግ ያሳለፈው ውሳኔ ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስፈጻሚ፣ የገንዘብና ንብረት አስተዳደር የበላይ ሓላፊ ዋና ባለሥልጣን ለኾነው ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሥራ አመራርና አቅጣጫ የሚሰጠው ነው፡፡

በአጠቃላይ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዳወሱት፣ በኃምሳ ሳንቲም የጀመረው የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የአቅም ማደግ፣ የራሷን አገልግሎትና የልማት ዕቅዶች በራሷ ጥሪት የመፈጸም ትልሟን የሚጠቁም ነው፡፡ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሳይኾን ደግሞ የተገኘውን የእግዚአብሔር ገንዘብ በተገቢው የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዐት በጥንቃቄ በማንቀሳቀስ ለሚገባው አገልግሎትና ልማት ለማዋል፤ የቤተ ክርስቲያንን የፋይናንስ አቅም አኹን በበጀት ከተመለከተው ብር 141 ሚልዮን በላይም ለማሳደግና በራሷ ምእመናንና ልማት ላይ የተመሠረተ ሉዓላዊ ክብሯን ለመጠበቅም ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡


 

በ፳፻፮ ዓ.ም. ለየአህጉረ ስብከቱ የጠላከ በጀት እና በ፳፻፮ ዓ.ም. የመንበረ ፓትርያርክ 35 በመቶ የዘመኑ ገቢ የልዩነት ደረጃ የሚያሳይ ዝርዝርYeTekelat betekihinet bedget reportYeTekelat betekihinet bedget report02ምንጭ፡- የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፤ ቃለ ዐዋዲ መጽሔት፤ ፯ኛ ዓመት ቁጥር ፲፤ ፳፻፯ ዓ.ም.

Advertisements

6 thoughts on “ቅዱስ ሲኖዶስ 141 ሚልዮን ብር ዓመታዊ በጀት አጸደቀ፤ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ነገ ይጠናቀቃል፤ ጋዜጣዊ መግለጫም ይሰጣል

 1. Anonymous November 5, 2014 at 6:31 am Reply

  አርጅቷል ስትሉት የነበረውን ቃለዓዋዲ መጥቀስ መጀመራችሁ የሚበረታታ ነው፡፡
  ቅ/ሲኖዶስ የመደበው 141 ሚሊዮን ብር በጀት ይበል ነው፡፡ይሄ ማለት እንግዲህ ማኅበሩ አበረከትኩ ከሚለው የ8 ሚሊዮን ብር አስተዋኦ ጋር ሲነጻጸር ማኅበሩ ይሄን ያህል የሚናገረው ገና 10 ፐርሰንት ያልሞላ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ያሳየናል፡፡ተረጋጋ በሉት ማኅበራችሁን፡፡ከጠቅላላው የቤ/ክ ገቢ ጋር ከተነጻጸረ ደግሞ ገቢያችን 1 ቢሊዮን ስላለፈ ማኅበሩ አደረግሁ የሚለው ከ10 ሚሊዮን ያልበለጠ አስተዋጽኦ የሕልውና ምንጭ ነኝ የሚያሰኝ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡አረጋጉት፡፡

  • Anonymous November 5, 2014 at 8:59 am Reply

   ምንኛ ጤና የጎደለህ ነህ ባክህ! የምን ጎራ መለየት ነዉ? የማኅበሩ አባላት እኮ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት በመሆንም እንደማንኛዉም ምእመን የሚሳተፉ ናቸዉ፡፡ አባላቱ የማኅበሩን አገልግሎት እንደ ተጨማሪ አገልግሎት እንጂ የቤተክርስቲያንን ተሳትፎ እንደሚተካ አይቆጥሩም፡፡ የአባልነት መስፈርትም የቤተክርስቲያኒቱ ልጅ መሆን ማለትም የሰበካ ጉባኤ ወይም የሰንበት ትምህርት ቤት አባል መሆን ነዉ፡፡ የማኅበሩ አባላት አሥራት በኩራት ለቤተክርስቲያን የሚከፍሉም ናቸዉ፡፡ ይህ ማለት አንተ ለጠቀስከዉ የቤተክርስቲያን ገቢ ማደግም የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነዉ፡፡ ምናልባትም አሥራት በመክፈል ረገድ በአራያነት ሊወሰዱ ይገባል እላለሁ፡፡ እዉነትን የምትፈልግ ከሆንክ ይህን ራስህ አጥንተህ ልትደርስበት ትችላለህ፡፡ ይህ ግን ክርስቲያናዊ ግዴታ እና የእግዚአብሔር ስጦታ ስለሆነ የሚያኩራራ እንዳልሆነ ሁሉም ጠንቅቆ ስለሚረዳ አንተ ያልከዉ አይነት ያለመረጋጋት ችግር አለ ብየ አላስብም፡፡ ክርስቲያን እንዲህ አያደርገም፡፡ ይህን የምናገረዉ እዉነቱን ለማያዉቁት ነዉ፡፡
   ማኅበሩ ቃለዓዋዲዉን የመጥቀስም ሆነ የማክበር ችግር እንደሌለበት አንተም የምታዉቅ ይመስለኛል፡፡ በተረፈ የቤተክርስቲያን በጀት ማደግም ሆነ የገቢዋ መጨመር ማኅበሩን የሚያስደስተዉ እንጂ የሚያስከፋዉ አይደለም፡፡ ከነገርህ ሁሉ በጣም የማያስደስተዉ የማኅበሩን አስተዋጽኦ ለማጣጣል ያደረግኸዉ ሙከራ ነዉ፡፡ በምን ለክተኸዉ ነዉ ያነሰብኽ? ግን አንተ ምን ያክል አስተዋጽኦ እያደረግኽ ነዉ? ከዜሮ በታች እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ያ ባይሆንማ እንደዚህ አይነት ነገር ባልተናገርክ ነበር፡፡ ያስተዋጽኦዉን መብዛትም ሆነ ማነስ ሁሉን ለሚያዉቅ አምላካችን እንተወዉ፡፡

   • Anonymous November 6, 2014 at 10:29 am

    Egizabher yistlign tikekel melisehiletal.

  • Anonymous November 6, 2014 at 11:09 am Reply

   ምንኛ ጤና የጎደለህ ነህ ባክህ!

   • Anonymous November 7, 2014 at 7:02 am

    ይሕ በሁለታችሁም በኩሌ ጎራ ለይቶ መወጋገዝ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለልማታችን ጠቃሚ ስላልሆነ ብትተዉት መልካም ነዉ ሁለታችሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን አትወክሉም ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የሠላም መድረክ እንጅ የመወጋገዣ መድረክ አይደለችም ይሕ መወጋገዝም የእናንተ የሥጋ ምኞት ነዉ ገ፡5-16

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: