ቅ/ሲኖዶስ: በመንበረ ፓትርያርኩ ዙሪያ ከቻይና ኩባንያ ጋራ በ3 ቢልዮን ብር ወጪ ለማልማት በልማት ድርጅቱ የታቀደው የሪል እስቴት ግንባታ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት እንዲተገበር ወሰነ

 • ልማቱ የሀብት ምንጭን በማስፋት አቅምን የመገንባት የድርጅቱ ስትራተጅያዊ ዕቅድ አካል ነው
 • ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እስከ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ያለው ይዞታችን ይለማል
 • 13 ሕንፃዎች፣ ባለ4 ኮከብ የእንግዳ ማረፊያ፣ የስብሰባ አዳራሽና ሙዝየም ሥራዎችን ያካትታል
 • የግንባታ 3ቢልዮን ብር ወጪ 85% በኩባንያው፣ 15% በአስተዳደርና ልማት ድርጅቱ ይሸፈናል
 • የከተማውን የቤት እጥረት ከማቃለልና የአካባቢውን ገጽታ ከመቀየር አገራዊ ጠቀሜታው ባሻገር ሐዋርያዊ ተልእኳችን የሚጠናከርበትን ኢኮኖሚያዊ አቅም እንደሚያጎልበት ተስፋ ተደርጎበታል

*            *            *

 • በአስተዳደርና ልማት ድርጅቱ÷ በቸርችል ጎዳና ባንኮ ዲሮማ ሕንፃችን አጠገብ ባለኹለት ፎቅና ባለኹለት ቤዝመንት ዘመናዊ ሕንፃ ሥራ በብር 118 ሚልዮን ብር ወጪ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ ፒያሳ በሚገኘው የዘውዲቱ ሕንፃ በስተጀርባና በዚኹ አቅራቢያ በሚገኘው መንበረ መንግሥት ሕንፃ ባለው 1122 ሜትር ካሬ ክፍት ይዞታችን ላይ ደግሞ ኹለት ባለአራት ፎቅ ሕንፃዎችን በ48 ሚልዮን ብር ጠቅላላ ወጪ ለመገንባት ለተያዘው ዕቅድ ዕብነ መሠረቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተቀምጧል፡፡
 • ‹‹ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎቿን አስከብራ በሪል እስቴት ዕድል ተጠቃሚ እንድትኾን ለማድረግ ከቢዝነስ ፕላኑ አዋጭነት አኳያ ለኩባንያው ወኪሎች ዋስትና ያላትና ታዋቂ መኾንዋን ማረጋገጥ ነበረብን፡፡ ስለዚኽም የቤተ ክርስቲያንን ታዋቂነት እና አንጋፋነት በተጨባጭ በማስረዳትና በማሳመን ከኩባንያው ጋራ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማው ሊፈጸም ችሏል፡፡››››

/የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሪፖርት/

 • ‹‹ከውርስ የተመለሱ ቤቶችን ማስተዳደር ብቻ ይሠራ የነበረው የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር በአኹኑ ጊዜ በርካታ የሪል እስቴት ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የሪል እስቴት ግንባታችን በነባር ይዞታችን ላይና በራሳችን የገቢ በጀት ይጀመር እንጂ ለወደፊቱ በምናገኛቸው ቦታዎችም ላይ ኾነ በገዳማትና አድባራት በሚገኙ ሰፋፊ የልማት ቦታዎች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረግን በሰፊው አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡››

/ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የበላይ ሓላፊ/

*              *            *

His grace abune samuel discussing with the rep of GOCC Co.

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከቻይና ጂ.ኦ.ሲ.ሲ ኩባንያ ወኪሎች ጋራ ሲወያዩ (ፎቶ: አ/አበባ ሀ/ስብከት)

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ጂ.ኦ.ሲ.ሲ ከተባለ የቻይና መንግሥታዊ የሪል እስቴት ልማት ድርጅት ጋራ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሪል እስቴት ተጠቃሚ ለማድረግ በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ላይ የይኹንታ ውሳኔ ሰጠ፡፡

ምልአተ ጉባኤው በትላንት፣ ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የቀትር በፊት ሦስተኛ ቀን ውሎው፣ በመንበረ ፓትርያርኩ ዙሪያ ስፋቱ 60‚000 ሄክታር በኾነ የቤተ ክርስቲያናችን ነባር ይዞታ ላይ በብር ሦስት ቢልዮን ወጪ ከቻይናው የሪል እስቴት ኩባንያ ጋራ ለማልማት መግባባት የተደረሰበትን ጅምር የመግባቢያ ሰነድ፣ ‹‹ሒደቱ በየደረጃው በጥንቃቄ እየታየ ይቀጥል›› ሲል ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የቋሚ ገቢ ምንጭ የኾኑ ሰፊና በርካታ ቦታዎችና ቤቶች ቢኖሯትም ለእንዲኽ ዐይነቱ ልማት ከሚያስፈልገው የካፒታል መጠን አንፃር በአኹኑ ጊዜ መንግሥት ከውጭ ባለሀብቶች ጋራ የሚፈጽመውን ስምምነት መከተልና የዘርፉን ባለሞያዎች በማማከር ከውጭ ባለሀብቶች ጋራ መሥራት ብቸኛ አማራጭ ኾኖ መገኘቱ በድርጅቱ ሓላፊዎች ተገልጧል፡፡ ይህም በርካታ ግዴታዎችን መፈጸም ከሚጠይቀው ካርታን አስይዞ ከልማት ባንክ የመበደር አማራጭ የተሻለ ኾኖ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ያሏት ክፍት ቦታዎች እየተነጠቁ ለሌላ አልሚ ተላልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ ከግምት በማስገባት የሪል እስቴት ሥራ ለመሥራት ከቻይና፣ ከአሜሪካ፣ ከሕንድ እና ከእስራኤል የሪል እስቴት አልሚዎች ጋራ ሲነጋገር መቆየቱ ተዘግቧል፡፡ የቻይናው ጂ.ኦ.ሲ.ሲ የሪል እስቴት ኩባንያ የተሻለ አማራጭ ኾኖ በመገኘቱ በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ በሐምሌ ወር ፳፻፮ ዓ.ም. የመግባቢያ ሰነድ የመፈራረም ሥራ ተከናውኗል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ከሦስት ቢልዮን ብር ጠቅላላ ወጪ ውስጥ ኩባንያው 85 በመቶ ሲሸፍን ድርጅቱ ደግሞ 15 በመቶ ሊሸፍን እንደሚችል የድርጅቱ ሓላፊዎች ለምልአተ ጉባኤው ገልጸዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የሰጠውን የይኹንታ ውሳኔ በመከተል ከኩባንያው ጋራ የመጨረሻው የስምምነት ሰነድ ፊርማ ከተከናወነ በኋላ በሚደረገው ውል መሠረት የአከፋፈል ስምምነት ውል እንደሚፈጸምም ታውቋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ውሉን በምትፈጽምበት ወቅት የምታስይዘው መያዣ ስለማይኖራት ድጋፍ ሰጪው ኩባንያ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ቅድመ ኹኔታዎች መካከል ዋነኛው የቢዝነስ ፕላኑን አዋጭነት እንደኾነ በባለሞያዎች ማብራሪያ ተጠቅሷል፡፡ ይኸውም የሚገነቡት ሕንፃዎች የገቢ ምንጭ የሚፈጠርባቸው በመኾኑና አብዛኞቹ ለኪራይ ስለሚውሉ ምን ያኽል የኪራይ ገቢ እንደሚያስገቡና በምን ያኽል ጊዜ ምን ያኽል ገቢ ሊገኝ እንደሚችል የሚሰላበት፣ በቀረበው ሳይት ፕላን መሠረት የቦታዎቹን የጥቅም ደረጃዎች፣ የሕንፃውን ተዋረድ፣ የልማቱን መስተጋብርና አዋጭነቱ የሚታይበት ነው፡፡

ለዚኽም እንዲረዳ የአስተዳደርና ልማት ድርጅቱ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ታዋቂነትና አንጋፋነት በተጨባጭ ለኩባንያው በማስረዳትና በማሳመን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ ሊፈጸም እንደቻለ በድርጅቱ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልና በዋና ሥራ አስኪያጁ *አቶ ተስፋዬ ውብሸት ሰፊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የጠቅላላ ወጪውን 15 በመቶ ክፍያን አስመልክቶ የበጀት እጥረት(መቃወስ) ሊገጥማት አይችልም ወይ የሚልና የክፍያውን አፈጻጸም የተመለከቱ ስጋቶች ከርእሰ መንበሩና ከምልአተ ጉባኤው አባላት መነሣታቸው ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ስጋቱ ቢኖርም ክፍያው በሒደትና በደረጃ የሚከፈል በመኾኑ የስምምነት ሥርዐቱ የቤተ ክርስቲያንን የበጀት አቅም አይፈታተነውም፤›› ያሉት ሓላፊዎቹ የበጀት ፍሰቱም መዋቅሩን በጠበቀና ሕጋዊነቱን በተላበሰ መልኩ በብሔራዊው ንግድ ባንክ በኩል እንደሚከናወን የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ስለ ሪል እስቴት ግንባታው ድርጅቱን በመደገፍ የሚሠሩ ከፍተኛ ባለሞያዎች ለምልአተ ጉባኤው በሰጡት ማብራሪያ÷ ሕንፃዎቹ የሚገነቡት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጎን ጀምረው እስከ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ድረስ ባለው 60‚000 ሄክታር መሬት ላይ ነው፤ ከእነርሱም መካከል አንድ ዘመናዊ አዳራሽ እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡ የአዳራሹ ዲዛይን የአኵስም፣ የላሊበላና የጎንደር ሥነ ሕንፃዎች ይዘት የሚንጸባረቅበት በመኾኑ የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊነት እንዲመሰክር ይኾናል፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጀርባ ባለአራት ኮከብ የእንግዳ ማረፊያና ደረጃውን የጠበቀ ሙዝየም ይገነባል፤ በሕንፃዎቹ መካከልም ባለፋውንቴን አዳራሽ ይኖራል፡፡

ከዚኽም በተጨማሪ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በር ጀምሮ ወደ ፒያሳ እስከሚወስደው ዋና አስፋልት ድረስ ባለው ቀኝ መደዳም ግንባታዎች ይካሔዳሉ፡፡ የሕንፃዎቹ ጠቅላላ ብዛት 13፣ ከፍታቸውም የብዙዎቹ እስከ አራት ፎቅ ሲኾን የአስፋልቱን ዳር ተከትለው የሚገነቡት ሕንፃዎች ግን እስከ ዐሥራ ኹለት ፎቅ ሊደርስ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

መንበረ ፓትርያርኩን የሚከበው የግንባታው ሥፍራዎች የቤተ ክርስቲያን ነባር ይዞታዎች ቢኾኑም አንዳንዶቹ አላግባብ ወደ ቀበሌ ዞረው በግለሰቦች ባለቤትነት የሚገኙ በመኾኑ በሚመለከተው አካል የይገባኛል ጥያቄ ቀርቦባቸዋል፤ መንግሥት በመልሶ ማልማት በወሰዳቸው ቦታዎችም ምትክ እንደሚሰጥ ተገልጧል፡፡

ይኸው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ የልማት ዕቅድ÷ የአካባቢውን የከተማ ገጽታ በማሻሻል የሚቀይር፤ የከተማውን ነዋሪ በተለይም ለአገልጋይ ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን የቤቶች እጥረትን በማቃለል በኩል ተደራሽ በምናደርገው ልማት አገራዊ ሚና የምንጫወትበት ከመኾኑም ባሻገር ለቤተ ክርስቲያናችን መሥመራዊ ለኾነው የሐዋርያዊ ተልእኮዋ መስፋፋትና መጠናከር ቋሚ የኢኮኖሚ ዋልታና ማገር እንደሚኾን ተስፋ ተደርጎበታል፡፡

His grace abune Samuel archbishop of DICAC and HBADOሰው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ለመሥራትና ለማልማት በሚነሣሣበት ጊዜ ከቤተ ሰብእ በስተጀርባ ብዙ ፈተናዎች ሊገጥመው ይችላል፡፡ ይኹን እንጂ መንፈሰ ጠንካራ በመኾን ለቆምንላቸው ዓላማዎች በንቃትና በታማኝነት መሥራት ይኖርበታል፡፡ መንፈሰ ጠንካራዎች ካልኾን ስኬታማ መኾን አንችልም፡፡ ትላንት የነበሩ አባቶቻችን አድካሚውን አቀበትና ቁልቁለት በማለፍ በመንፈሰ ጠንካራነትና በልበ ሙሉነት በመሰለፍ ሕያውና ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሠርተው አልፈዋል፡፡ ይህም በመኾኑ በዚኽ ዘመን ሃይማኖታቸው በጸና ምግባራቸው በቀና ቀደምት የአገራችን መሪዎችና በጎ አድራጊ ምእመናን አማካይነት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የበርካታ ሕንፃዎችና ቤቶች ባለሀብት ኾናለች፡፡ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር እንዲል በተመለሱላት ቤቶች የምታገኘው ገቢ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የተሟላ ማስረጃ እያላቸው በእጃችን ያልገቡት ቤቶችና ሕንፃዎች ከመንግሥት ጋራ በመወያየት አስፈላጊውን መፍትሔ ለማግኘት ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በመጨረሻም በየትኛውም የሥራ መስክ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ኹሉ ለጀመርነው ሰፊና ግዙፍ የልማት ሥራ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል እላለኹ፡፡ /ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፤ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የበላይ ሓላፊ/


የሪል እስቴት ልማቱ፣ ላለፉት ኻያ ዓመታት ከውርስ የተመለሱ ቤቶችን በማስተዳደር ላይ ተወስኖ የቆየውን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በተጨባጭ ወደ ልማት ተቋምነት የሚያሸጋግረው እንደኾነ የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ብፀዕ አቡነ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ ድርጅቱ፣ በራሱ የገቢ በጀትና በነባር ይዞታ ላይ የሪል እስቴት ግንባታዎችን እያካሔደ ሲኾን ወደፊትም ቤተ ክርስቲያንን የኹለገብ የሪል እስቴት ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ጥናት እያደረገ ወደ እንቅስቃሴ ይገባል፡፡ ይህም በጂ.ኦ.ሲ.ሲ ኩባንያ ድጋፍ ሰጪነት በእጃችን ባሉት ቦታዎች ይጀመር እንጂ በቀጣይ ከመንግሥት ከሚገኙት ቦታዎች ላይ ኾነ በአድባራትና ገዳማት በሚገኙ ሰፋፊ የልማት ቦታዎች ላይ አስፈላጊው ቅድመ ውይይት እየተደረገ የሪል እስቴት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡

Banko De Roma extension project

በፒያሳ ባንኮ ዲሮማ(ቸርችል ጎዳና) አጠገብ ግንባታው የሚፋጠነው ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ፕላን

ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው እንደገለጹት በበላይ ሓላፊነት የሚመሩት ድርጅቱ፣ በቸርችል ጎዳና በተለምዶ ባንኮ ዲሮማ እየተባለ ከሚጠራው ሕንፃችን አጠገብ ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ሥራ በብር 118 ሚልዮን ወጪ እያፋጠነ ይገኛል፡፡ ግንቦት ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ይህ ሕንፃ በአኹኑ ወቅት ሥራው ሰባተኛ ደርብ ላይ ይገኛል፤ በመጪው ሐምሌ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ለማጠናቀቅም የጊዜ ሰሌዳ እንደተያዘለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሥፍራው ተዘዋውረው ሒደቱን በጎበኙበት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ከተሰጠው የባለሞያዎች ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

piyassa zewditu and Menbere Mengist hintsa design

በፒያሳ በዘውዲቱና መንበረ መንግሥት ሕንፃዎች መካከል የሚገነባው ሕንፃ ፕላን

በሌላ በኩል በተያዘው በጀት ዓመት ድርጅቱ ፒያሳ አካባቢ ኹለት ባለአራት ፎቅ ሕንፃዎችን ለመገንባት ዐቅዶ ዕብነ መሠረቱ ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ ከዘውዲቱ ሕንፃ በስተጀርባ ባለው 794 ሜትር ካሬ ክፍት ይዞታ ላይ የሚያርፈው አንዱ ሕንፃ 28 ሚልዮን ብር ጠቅላላ ወጪ የሚጠይቅ ሲኾን ኹለት ቤዝመንቶችን ጨምሮ ባለ 2 እና 3 መኝታ ቤት መኖሪያ፣ ዘመናዊ ሱቆችና የሥነ ጥበብ(አርት) ጋለሪ ያለው እንደሚኾን ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በዚኹ በዘውዲቱ ሕንፃ አቅራቢያ መንበረ መንግሥት እየተባለ በሚጠራው ሕንፃ ጎን ባለአራት ፎቅ ሕንፃ የሚገነባ ሲኾን አጠቃላይ ግንባታው 20 ሚልዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ በ328 ሜትር ካሬ ላይ የሚያርፈው ሕንፃው÷ አንድ ከመሬት በታች የመኪና ማቆሚያ፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችና ለንግድ የሚኾኑ ክፍሎች ይይዛል፤ ሥራውም በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

*************************************************************
Ato Tesfaye Wubshet, general manager of the dev't organization

አቶ ተስፋዬ ውብሸት፤ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

…ለወደፊት በምንገነባቸው አዲስና ታሪካዊ ሕንፃዎች ዙሪያ ጂ.ኦ.ሲ.ሲ ከተባለ መንግሥታዊ የቻይና ኩባንያ ጋራ ውይይቶችን አድርገን ነበር፡፡ በምን መልክ ነው የምንሠራው የሚለውን በጽሑፍ አስደግፈንላቸዋል፤ የኩባንያው ባለቤቶችም የሚለሙ ቦታዎችን ለይተው ተመልክተዋል፤ ቤተ ክርስቲያናችን ትልቁ የማይንቀሳቀስ ሀብቷ መሬት ነውና፡፡ በተጨማሪም በቴክኒክ ብቃት ያላቸው ልጆችም አሏት፡፡

ልማቱን የምናለማበት የፋይናንስ እጥረት ግን አለብን ብለን ነገርናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ሊኖራቸው የሚችለውን አብሮ የመሥራት ፍላጎት ስንመላለስበት ቆይተን እኛ ያለን መሬት ነው በሚል ተግባብተን ከስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀው ይኸው ሥራችን ከቅድስተ ማርያም በታች ባለው ቁልቁለት ወደ ኹለተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታጠፊያ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሚይዘውን መንገድና በቅድስተ ማርያም ትይዩ ከማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ አንሥቶ በተለምዶ ጎንደር በር እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ድረስ ባሉት ቦታዎች ላይ የቤተ ክርስቲያናችንን ማንነትና ታሪክ የሚያንፀባርቅ ዲዛይንና ገዳማዊ ገጽታ የሚኖራቸው ሕንፃዎችን መገንባት እንዳለብን ተማምናል፡፡

የድርጅቱ ቦርድም ጊዜውን መሥዋዕት አድርጎና ሥራውን ገምግሞ መኾን የሚገባውን ለግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጥኚው ቡድን እንዲቀርብ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የቀረበውን ጥናት ተመልክቶ በመልካም ጎን ተቀብሎታል፡፡ ከምንሠራቸው ሕንፃዎች መካከል ለንግድ ማዕከል፣ ለመኖሪያ፣ ለመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚኾኑ ይኖራሉ፡፡

የግንባታዎቹን ዲዛየን በተመለከተ ለጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያናችን ለማንነቷ መገለጫ የሚኾን ሕንፃ ሊቀመጥበት ይገባል ከሚል ስምምነት ላይ ነው የደረስነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ፣ የቅርስ፣ የሥነ ሕንፃ፣ የሥነ ፊደል ባለቤት መኾንዋን የሚያሳዩ ሕንፃዎች መቀመጥ አለባቸው ብለን ነው የወሰድነው፡፡ የአካባቢው ማስተር ፕላን ምንም ይበል ምን ቅርፁን ይዞ፣ ስታንዳርዱን ጠብቆ ይሠራል፡፡ የገዳም ሠፈር መኾኑን ሊያሳይ የሚችል ይዘት ያለው ሕንፃ እንዲቀመጥ ነው ያሰብነው፡፡ መጪው ትውልድ ሕንፃውን በማየት ቤተ ክርስቲያንዋ ትላንት ምን ነበረች? ዛሬስ ከምን ላይ ናት? ነገስ ምን መኾን አለባት? የሚለውን አቅጣጫ ያሳያል በሚል አሳቤ ነው ዲዛይኑ እንዲቀመጥ የተደረገው፡፡

ስለዚህ አኹን ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ የሚታየው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠን አቅጣጫ ሥራውን ሀ ብለን እንሠራለን፤ ነገር ግን አኹን የሚታየው የቤተ ክርስቲያን የኢኮኖሚ አቅም ውስን በመኾኑ ከቻይናዎች ጋራ የምንሠራቸው እንደተጠበቀ ኾኖ ጥቃቅን ልማቶችን ማለትም ኹለት ባለአራት ሕንፃዎች በመሐል ፒያሳ እየሠራነው እንዳለው ዓይነት ሰፊ ካፒታል በማይጠይቁት ኪስ ቦታዎች ላይ በራሳችን አቅም ለመሥራት ዐቅደናል፡፡ ይህን ለመሥራት ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ በመምከር ቀጣዮቹን ሥራዎች እንሔድባቸዋለን ብለን እናምናለን፡፡

…ጠቅለል ባለመልኩ ስናይ ከበፊቱ ፳ ዓመት ከነበረው አሠራር በተሻለ ወደፊት ለመግፋት እየሔድን ነው ያለነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም እያሳሰበን ያለው ቦታዎቹ ካለሙ ቁጭ ብለው የሚጠብቁን ስላልኾነ መንግሥት ከተማዋን ለማልማት ካለው ፈጣን ፍላጎት ጋራ በካሳ እየተስተናገድን መሥራት አለብን የሚል ነው፡፡ እኛም ፈርሰው የሚለሙ ቦታዎችን በመለየት እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው፡፡ ወደ ልማት ለመግባት ቀዳሚው ጉዳይ ባለቤት ኾኖ መገኘት ነው፡፡ ፈጥነን ወደ ልማት ለመግባት ይዞታዎችን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ከዚኽ አንፃር ሰፊ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንድ ቦታ ላይ ፎቁ የእኛ፣ ምድሩ የሌላ ኾኖ የተቸገርንበት ኹኔታ አለ፡፡ ካርታ የጠየቅንላቸውን በፎቁ ብቻ ነው የተባልንበት ኹኔታ አለ፡፡ ስለዚኽ ካርታ ማውጣት ቀላል ፈተና አልነበረም፡፡ አኹንም ቢኾን በካርታ ማውጣት ሒደት እየገጠመን ያለው ሌላው ችግር ሳሎኑ የእኛ፣ መኝታ ቤቱ የሌላ መኾኑ ነው፡፡ ይህንን እያጣጣምን የምንሔድበት ኹኔታ ነው ያለው፡፡ በክፍለ ከተማ ያቀረብነውን ጥያቄ በሥርዓት በመመልከት ሕጋዊ ድጋፍ እየሰጡን ይገኛሉ፡፡

በመጨረሻም ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አካል በግለሰብ ይኹን በተቋም ደረጃ እያለማን ካለነው የቤቶች ግንባታ አንፃር ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ ስለኾነ ኹሉም አካል ለተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ በቅንነት መደገፍ ይገባዋል፡፡ የጥንቶቹ አባቶች ድንጋይ ተሸክመው፣ ውኃ ቀድተው የሠሩልንን ሕንፃ እኛ ደግሞ ደንጋይ ባንሸከም፣ ውኃ ባንቀዳ፣ እነሱ የሰበሰቡልንን ሀብትና ንብረት በአግባቡ ጠብቀንና ተጨማሪ ልማት ሠርተን ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ፣ በመንፈሳዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች የመሪነቷን ደረጃ ይዛ እንድትንቀሳቀስ ማድረግ አለብን፡፡ ቀደም ሲል በአገራችን የጎላ ሚና ስለነበራት ያን ሚናዋን ለማስቀጠል በምናደርገው ጥሪ በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በሞራል ኹላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች በተቋም ይኹን በግል አብረን እንሥራ በማለት ጥሪዬን አስተላልፋለኹ፡፡

/አቶ ተስፋዬ ውብሸት፤ በ፳፻፮ ዓ.ም. ለአ/አበባ ሀ/ስብከት ድረ ገጽ ከሰጡት ቃለ ምልልስ/

************************************************************
አንዳንድ ነጥቦች ስለ ቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት
 • ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ብሔራዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በፊት የነበሩት ደጋግ የሀገሪቱ መሪዎችና በጎ አድራጊ ምእመናን በሕይወት በነበሩበት ወቅት በስጦታ፣ በሚያልፉበት ወቅት በኑዛዜ ለገዳማትና አድባራት መተዳደርያ ያወረሷቸው፣ በየጊዜውም ራሷ ያስገነባቻቸው ቤቶችና ሕንፃዎች የኪራይ ገቢ መተዳደርያ ነበራት፡፡ ይኹን እንጂ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ባደረገው ዐዋጅ ቁጥር 47/1967 መሬቶቿ፣ ሕንፃዎቿና ቤቶቿ ተወርሰውባት በዓመት አራት ሚልዮን ብር አነስተኛ ድጎማ እያገኘች በተጽዕኖ ስትኖር ቆይታለች፡፡
 • የቤተ ክርስቲያናችን ውለታ የሚታሰብበት ጊዜ ደርሶ የተወረሱ ቋሚ ሀብቶቻችን የትና በምን ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ ቁጥራቸውንና ይዘታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ የማሰባሰብ ሒደት ከተከናወነ በኋላ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የካቲት ፯ ቀን ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. ለወቅቱ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ ባሳሰቡት መሠረት ከየካቲት ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ጀምሮ ከመንግሥት የቤቶች ኤጀንሲና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋራ በመነጋገር ቦታዎቿ፣ ንብረቶቿ፣ ሕንፃዎቿ፣ ቪላዎቿ፣ አፓርትመንቶቿ፣ ቁጠባ ቤቶቿና መጋዘኖቿ ተመልሰውላት እንደ ቀድሞው በመጠቀም ላይ ናት፡፡
 • በቤቶችና ሕንፃዎች አስመላሽ ኮሚቴ አማካይነት እስከ አኹን የተመለሱላት ቤቶች ብዛት በአጠቃላይ 626 ሲኾኑ ከእኒኽም 342 ለመኖሪያ ቤቶች፣ 284 ደግሞ ለድርጅቶች የኪራይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በ፳፻፮ ዓ.ም. የበጀት ዓመት ከብር ኻያ ስድሰት ሚልዮን በላይ /26‚802‚923.26/ ዓመታዊ የኪራይ ገቢ አስገኝተዋል፡፡
 • ለሕንፃዎቹና ቪላዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማግኘት ከቀረቡት ቤቶች ውስጥ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ልማት ማኔጅመንት የ57 ቤቶች፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ማኔጅመንት የ23 ቤቶች በድምሩ የ80 ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተረክበናል፡፡ ቀደም ሲል ያለአግባብ ካርታ የወጣባቸው ቤቶች አስከትለውት ከነበረው ውጣ ውረድና የቤቶች ርክክብ በሚፈጸምበት ጊዜ ተፈጥረው ከነበሩት ግድፈቶች በመማር ቀሪዎቹ ቤቶች በ፳፻፯ ዓ.ም. የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡
 • ድርጅቱ አኹንም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እጅ ባሉና ጨርሰው ባልተመለሱ 283 ቀሪ ቤቶች እና ሕንፃዎች ዙሪያ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋራ በአስመላሽ ኮሚቴው አማካይነት በመመካከር የመጨረሻ እልባት ለማግኘት የተጠናከረ ክትትል በማድረግ ላይ ነው፡፡
 • ኮሚቴው በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አሮጌ ቄራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ስም በቤት ቁጥር 073 የተመዘገበውን ባለ23 ክፍል ሆቴል ሕንፃ የተረከበ ሲኾን በሐረር ከተማ የሚገኙ 25 ቤቶችና ሕንፃዎች የርክክብ አፈጻጸም ደግሞ በሒደት ላይ ይገኛል፡፡
Arat Kilo twins tower

ቤተ ክርስቲያን ካልተረከበቻቸው ሕንፃዎች መካከል ከመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት ጋራ ተያያዥነት ያላቸውና ከዳግማዊ ሚኒልክ ት/ቤት ፊት ለፊት ያሉት ባለ12 ፎቅ መንትያ ሕንፃዎች

 • ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጋራ ተያያዥነት ያላቸውን ከዳግማዊ ሚኒልክ ት/ቤት ፊት ለፊት ያሉት ባለ12 ፎቅ መንትያና መለስተኛ ሕንፃዎች እንዲመለሱ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያቀረበው አቤቱታ ክትትል እየተደረገበት ይገኛል፡፡

  The Freedom Tower

 • የፊንፊኔ/ዱክ/ ሆቴል፣ የተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሕንፃዎች እንዲመለሱላት ያቀረበችው ጥያቄ ‹‹ከጸጥታ ሥራ አንፃር›› የታየ በመኾኑ በምትኩ ተገቢው የካሳ ግምትና ተመጣጣኝ የሕንፃ መሥሪያ ቦታ ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲሰጣት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በፊርማቸው ያስታወቁበትና በቁጥር ጠ80-አጠ8/02/19 በቀን 10/03/2000 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ለሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
 • ለአራቱም ሕንፃዎች የቀረበው ጠቅላላ የካሳ ግምት ብር ሰባ አንድ ሚልዮን /71‚051‚557.80/ ያኽል ሲኾን ምትክ ቦታን በተመለከተ 22‚800 ካሬ የመሥሪያ ቦታ መሬት እንድንረከብ የቦታ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ የካሳ ግምቱ መጠን ከፍተኛ ክትትል ተደርጎበት ውጤቱ በባለሞያ የታመነበት ነው ያለው ሪፖርቱ ምትክ መሬቱም አንደኛ ደረጃ መኾኑን ገልጧል፡፡
 • ለቤተ ክርስቲያናችን ሕንፃዎችና ቤቶች በወቅቱ ተገቢውን ዕድሳትና ጥገና እያደረገ መከባከብ የሚጠበቅበት ድርጅቱ፣ የወቅቱን ገበያ ባማከለና የተከራዮችን አቅም ባገናዘበ መልኩ በባለሞያ የኪራይ ዋጋ አስጠንቶ በተግባር ላይ አውሏል፡፡ ለቤቶችና ሕንፃዎች ዋስትና እንዲገባላቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቦ ውሳኔ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ሥሪታቸው የጭቃ በኾኑት ቤቶች ዙሪያ የተሻሉ ቤቶችን መገንባት የሚቻልበት የባለሞያ ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ወደ ተግባር እንዲለወጥ ጥረት አድርጓል፡፡
 • የንግድ ፈቃድ (ስያሜ) ሽያጭ ላይ ድርጅቱ ማግኘት ያለበትን ገቢ አኹን ካለው በተሻለ መልኩ ለማግኘት የሚያስችል ሕግ ተጠንቶ ቀርቦ እንዲጸድቅና በተግባር ላይ እንዲውል፤ ከቤት ኪራይ ከሚገኘው ገቢ 30 ፐርሰንቱ በፈንድ ሪዘርቪንግ ሥር እንዲኖር ለማድረግም እየሠራ ነው፡፡
 • በሪል እስቴት ግንባታ ዘርፍ በሀገር ውስጥ ካሉት ተመሳሳይ ተቋማት ጋራ ተፎካካሪ ለመኾን፤ የተሻለ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የቤተ ክርስቲያናችን ውስጣዊ አኮኖሚ እንዲጠናከርና መንፈሳዊ ተልኮዋን በብቃትና በጥራት እንድትወጣ የማስቻል ዓላማ ያነገበው ድርጅቱ÷ የግንባታ ፈቃድ በወቅቱ አለመሰጠት፣ የነባር ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቅ፣ የበቂ በጀት፣ የሰው ኃይልና የግብአት አቅርቦት ችግሮች፣ ከደንበኞች ጋራ የግንኙነት ክፍተት፣ ደንበኞች የተከራዩትን ቤት ከድርጅት ወደ መኖርያ፣ ከመኖርያ ወደ ድርጅት በራሳቸው ፈቃድ መቀየር ለቤቶችና ሕንፃዎች ዕድሳት ለማድረግ ሲፈለግ የተሠሩበትን ማቴሪያል የተመለከተ የተሟላ መረጃ አለመገኘቱ ዋና ዋና የዕቅድ ስጋት ነጥቦቹ እንደኾኑ ዘርዝሯል፡፡
Advertisements

8 thoughts on “ቅ/ሲኖዶስ: በመንበረ ፓትርያርኩ ዙሪያ ከቻይና ኩባንያ ጋራ በ3 ቢልዮን ብር ወጪ ለማልማት በልማት ድርጅቱ የታቀደው የሪል እስቴት ግንባታ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት እንዲተገበር ወሰነ

 1. Anonymous October 26, 2014 at 7:21 am Reply

  Yes nice God bless ethiopia

 2. leul seyoum October 27, 2014 at 9:18 am Reply

  betam des yemel zena new amelak lefetsame yabekalen

 3. Anonymous October 27, 2014 at 10:33 am Reply

  በጣም ደስ ይላል። ፈጣሪ እንደኛ ሃጢያት ሳይሆን በቸርነቱ ያሰበን ይክበር ይመስገን።

 4. Anonymous October 27, 2014 at 11:18 am Reply

  with China? no Ethiopians at all for 3billion birr???

 5. Dereje Mengesha October 27, 2014 at 11:40 am Reply

  God bless my Ethiopia !

 6. Emu Zer October 27, 2014 at 5:07 pm Reply

  Bemechrashaw zemen bet seri yebazal, gen aynorubetm.

 7. Anonymous October 31, 2014 at 9:49 am Reply

  ሰው እያፈረሱ ድንጋይ መቆለል

 8. Hailemariam Bogale October 31, 2014 at 9:53 am Reply

  seew mafres dingay mekolel yezemenachin beteshristian getsta

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: