ከፍተኛ ምዝበራ የተፈጸመበት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ሥራ ኦዲት ሪፖርት ይፋ ኾነ፤ የደብሩ አለቃ ከሪፖርቱ አስቀድሞ ያለሊቀ ጳጳሱ ስምምነት በፓትርያርኩ ትእዛዝ ተነሡ!

 • እስከ ልዩ ጽ/ቤት የተዘረጋው የአማሳኞች ሰንሰለት ለአለቃው መነሣት ተጠያቂ ኾኗል
 • ምእመናን፣ በተነሡት አለቃ ምትክ የሚደረግ ምደባን እንደማይቀበሉ አስጠንቅቀዋል
 • ፓትርያርኩ ለክብረ በዓል ወደ ቁሉቢ ሲያልፉ ለማነጋገር ዝግጅት እየተደረገ ነው
 • የኦዲት ሪፖርቱ የድሬዳዋ አገልጋዮች ና ምእመናን በአንድነት እንዲሰለፉ አድርጓል
 • ‹‹የአለቃው መነሣት ሙስናን ለሚዋጉ ሌሎች አስተዳዳሪዎች ዋስትና የሚያሳጣ ነው፡፡››
 • ‹‹ፓትርያርኩ በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነውን ስለማይቀበሉና መፍትሔ ማምጣት ስላልተቻለ ሕዝቡ ራሱ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠብቅ ብፁዓን አባቶች ነግረውናል፡፡››

/የተሟጋች ምእመናን ቡድን/

*            *           *

 • ከአምስት ሚልዮን በላይ ብር ከውል ውጭ መከፈሉ በኦዲት ምርመራው ተረጋግጧል
 • በ2.9 ሚልዮን ብር ለማገባደድ የታቀደው ኮንትራት ዋጋ ከ10 ሚልዮን በላይ ብር ደርሷል
 • የምእመናን የወርቅ ስጦታዎች በልክ ተሽጠው ገቢ ስለመኾናቸው ለማረጋገጥ አልተቻለም
 • የሕ/አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገንዘብ ተቀባይም ወጪ ጠያቂና አጽዳቂም ኾነው ፈርመዋል
 • የሰብሳቢውን የሥልጣን ምንጭና ሕጋዊነት የሚገልጽ ሰነድ ወይም ቃለ ጉባኤ አልተገኘም
 • ውጭ ሔጃለኹ ያሉት ተቋራጩ አ/አ ተቀምጠው ውሏቸውን በጠቅ/ቤ/ክህነት አድርገዋል
 • ደብሩ÷ ኮሚቴውን፣ ተቋራጩንና የግንባታ ተቆጣጣሪውን በሕግ እጠይቃለኹ ብሏል

(ኢትዮ ምኅዳር፤ ቅጽ 02 ቁጥር 77፤ ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.)

???????????????????????????????

 

በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ከታቀደለት ጊዜ በላይ በመጓተቱ እያወዛገበ በሚገኘው የሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ግንባታ፣ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ለሕንፃ ሥራ ተቋራጩ በተለያየ መልክ የከፈለው ከአምስት ሚልዮን በላይ ብር ከውል ስምምነት ውጭ የተፈጸመ እንደኾነ በሕንፃ ሥራው ሒሳብ ላይ የተካሔደው የገለልተኛ ኦዲተሮች ምርመራ አረጋገጠ፡፡

Dire Dawa Saba Saint Gabriel Church Audit Report by Habtewold Menkir and Co. Authoried Auditor

በደብሩ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የገቢና ወጪ መግለጫዎች ላይ ሀብተ ወልድ መንክርና ጓዶቹ በተሰኘ የተፈቀደለት ኦዲተር በተደረገ የሒሳብ ምርመራ÷ ኮሚቴው ሪል የሕንፃ ሥራ ለተሰኘ ተቋራጭ ለሕንፃ ግንባታ በሚል የፈጸማቸው ከፍተኛ ክፍያዎች፣ ኮሚቴው ከተቋራጩ ጋራ የገባውን የውስን ኮንትራት ውል ስምምነት በሚቃረንና በውሉ ለግንባታው መጠናቀቅ ከተያዘው ቀነ ገደብ ውጭ የተሻሻለ የማሟያ ስምምነት ከመፈራረም በፊት ያለአግባብ የተከናወኑ እንደኾኑ ከኦዲተሮቹ ሪፖርት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በኦዲት ሪፖርቱ እንደሰፈረው፣ የቤተ ክርስቲያኑን ሕንፃ በብር 2‚984‚562.51 እና በ730 ቀናት ገንብቶ ለማስረከብ ኮሚቴውና ተቋራጩ መስከረም 19 ቀን 1998 ዓ.ም. በተስማሙበት የውስን ኮንትራት ውል መሠረት ምንም ዓይነት ቅድመ ክፍያ እንደማይጠየቅ ቢገለጽም ለኮንትራክተሩ ከውል ውጭ ቅድመ ክፍያ ሲፈጸምለት ቆይቷል፡፡

እስከ 2004 ዓ.ም. የካቲት መጨረሻ ድረስ ለኮንትራክተሩ በተለያየ መልክ የተከፈለው 5‚565‚470.76 ያኽል ገንዘብ፣ በውስን ውል(Fixed contract) ሕንፃውን ለመሥራት ከተስማማበት ዋጋ ውጭና በዚያው ዓመት የካቲት 28 ቀን የተሻሻለ የሟሟያ ስምምነት ከመፈራረም በፊት የተፈጸመ ክፍያ ነው ያለው ሪፖርቱ፣ ‹‹ይህም ክፍያ የተጨማሪ የማሟያ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ሊፈጸም አይገባም ነበር፤›› ብሏል፡፡

የስምምነት ውሉን ከመቃረን በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኮንስትራክሽን ሕጉን በሚፃረር አኳኋን ተፈጽሟል በተባለው ክፍያ እስከ የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ የግንባታ ወጪው ወደ 7‚784‚985.22 ከፍ ማለቱን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹ይህ ከግምት ከገባ ኹለተኛ ተጫራች ያቀረበው ብር 3‚700‚770.15 ወይም ሦስተኛ ተጫራች ያስገባው ብር 4‚351‚881.05 ዋጋ በምናይበት ጊዜ ኹለተኛ ተጫራች ወይም ሦስተኛ ተጫራች ሊያሸንፉ የሚችሉበት ዕድሉ እንደነበረ›› ገልጧል፡፡ ይህም ለፕሮጀክቱ የጨረታ ወድድር በወጣበት ወቅት የሥራ ተቋራጩ ‹‹ከሌሎች የተሻለ ጥቅም አግኝቷል›› ሊያሰኝ እንደሚችል አመልክቷል፡፡

በጨረታዎች አስተዳደርና በዕቃ ግዥዎች መጠቃቀም

ሌሎች ጨረታዎችን በሚመለከት፣ ለኅትመት ሥራ የተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ዋጋቸውን አቅርበው እንዲወዳደሩ እንዳልተደረገ ሪፖርቱ ገልጾ፣ ከዕቃ ግዥዎች ጋራ በተያያዘም ዋጋቸው ከተወዳደሩት ውስጥ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረቡና በኮሚቴ የጸደቀላቸው እያሉ ከቃለ ጉባኤው ውጭ በጨረታ ላልተሳተፈ ተጫራች ድርጅት ሥራ መሰጠቱ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡

ሕገ ወጥ ደረሰኞችና ፋክቶሮች

በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ጽ/ቤት፣ አንድ የአነስተኛና መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረት ማኅበር ድርጅት ለተሳፋሪዎችና ለገንዘብ ከፋዮች የሚሰጣቸው የተለያዩ ፋክቶሮችና የደረሰኝ ጥራዞች መገኘታቸው ተዘግቧል፡፡ እነዚህ ደረሰኞች ለተጓዞች አገልግሎት በተሰጠበት (በተሳፈሩበት) ቀን በርግጥም ከድርጅቱ የተሰጠ መኾኑን ለማወቅ በተደረገው ምርመራ፣ መለያ ቁጥራቸው ተለይተው በተጠቀሱ ደረሰኞች ቁጥር መሐልና በተመሳሳይ ፋክቶሮች ነገር ግን በተለያዩ ዓመታት በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ገንዘብ ጥቅም ላይ ውለው በመገኘታቸው ክፍያው በትክክል መፈጸሙን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ፤ በተጨማሪም የአንዱን ደረሰኝ ዋናውን ለአንድ ሰው ቅጂውን ለሌላው ሰው በመጠቀም የተወራረደ ገንዘብ በሒሳብ ውስጥ እንደተካተተ፣ በተለያዩ ቦታዎች ተያይዘው የሚገኙና የሴሪ ቁጥራቸው የተጠቀሱ የተጓዥ ትራንስፖርት ደረሰኝ ጥራዞች ትክክለኛነት ለመቀበል አስቸጋሪ ኾኖ እንደተገኘ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ራሱ ተቀባይ፣ ራሱ ጠያቂ፣ ራሱ ፈራሚ፣ ራሱ አጽዳቂ

Payments which can not be accounted for

አብዛኞቹ የክፍያ ሰነዶች÷ በሒሳብ ሓላፊና በገንዘብ ከፋይ ያልተፈረመባቸው፣ የተቆጣጣሪ ፊርማ የሌላቸው አንዳንዴም የገንዘብ ተቀባይ የሚለው ክፍል ያልተፈረመባቸው በመኾናቸው የወጪዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ያመለከተው ሪፖርቱ÷ ለነዳጅ፣ ለአበልና ለአልጋ በሚል በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተጠይቀው ሲያበቁ በራሳቸው የጸደቁ ወጪዎችን በዝርዝር በማስፈር ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻለ በኦዲት ግኝቱ አስፍሯል፡፡ በማቆያ ሰነድ ተመዝግበው ከሚገኙ ያልተወራረደ ሒሳብ ብር 232‚520 ውስጥ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ያሉት ብር 39‚800 ለረዥም ጊዜ የቆዩና እስከ አኹን ያልተወራረዱ ኾነው እንደሚገኙም ሪፖርቱ አካትቷል፡፡

ሞዴላሞዴሎች የማያውቁት የንብረት ገቢና ወጪ

ከገንዘብ ውጭ ምእመናንና በጎ አድራጊዎች በተለያየ ጊዜ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ ለማገዝ በዓይነት ያበረከቷቸው ስጦታዎች፣ ገቢም ኾነ ወጪ ሲኾኑ ይዘታዊ መጠናቸው ከአኃዛዊ ብዛታቸው ጋራ በአግባቡ ተጠቅሶ የዕቃ ወይም የንብረት ገቢ ደረሰኝ – ሞዴል 19፣ የዕቃ ወይም የንብረት ወጪ ደረሰኝ – ሞዴል 22 በትክክል ስለማይቆረጥላቸው በስጦታ የተገኙት ንብረቶች በኮሚቴው በአግባቡ ተይዘው እንደኾነ ለማረጋገጥ ካለመቻሉም በላይ በተሰበሰቡበት ወቅት በሞዴል 19 ገቢ ለመደረጋቸው ሕጋዊ ሰነድ ያልተገኘላቸው ንብረቶች ጥቂት እንዳልኾኑ ኦዲተሮቹ በግኝት ሪፖርታቸው አስፍረዋል፡፡ ‹‹እንደ ጆሮ ጉትቻ፣ የጣት ቀለበት፣ የእጅ አምባር፣ የአንገት ማጫወቻ ሀብል የሀገር ውስጥ ወይም የውጭ ተብሎ ብዛቱን ብቻ ይጠቅሳል እንጂ ባለስንት ካራንትና ምን ያኽል ግራም እንደኾነ ባለመጠቀሱ ንብረቶቹ በትክክል ተሽጠው ገቢ መኾናቸውን ወይም በትክክል የተወራረዱና ያልተለወጡ መኾናቸውን ማረጋገጥ አልቻልንም፤›› ይላል ሪፖርቱ፡፡

ዜው የተላለፈው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴና ሕገ ወጡ ሰብሳቢው

የኦዲተሮቹ ሪፖርት በግኝቱ÷ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው የቆየበትን የሥራ ዘመን፣ ውል ለመፈራረም ያለውን የሥልጣን ወሰን፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ የሕጋዊነት ምንጭና በተለይም ወጪዎችን ለማጽደቅ ያላቸውን አግባብነትም ከቃለ ዐዋዲ ደንቡ የተለያዩ ድንጋጌዎች አንጻር ፈትሿል፡፡ በደንቡ መሠረት÷ ሦስት ዓመት የሥራ ዘመን ያለውን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በጠቅላላ ጉባኤ የማስመረጥና የማቋቋም፣ የሚወስነውን እየመረመረ የማጽደቅ፣ የማሻሻልና የመሻር ሥልጣን የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሲኾን ደብሩን በመወከል ውል የመዋዋል፣ የመክሠሥና የመከሠሥ ሥልጣንና ተግባርም አለው፡፡ በአንጻሩ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ከተቋራጩ ጋራ የመጀመሪያ ውል እንዲኹም የተሻሻለ የግንባታ ውል እንደተፈራረመ የሥልጣን ጊዜውም ከሦስት ዓመት እንዳለፈ ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

Lique Tiguhan Birhane Mehari00

አኹን ያሉት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ መሐሪ ከ2002 ዓ.ም. በፊት ረዳት ኦዲተር እንደነበሩ ሪፖርቱ አስታውሶ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሚቴውን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ቢኾንም ለዚኽ ሓላፊነታቸው የተመረጡበትና ወጪን ማጽደቅን ጨምሮ በተለያዩ ሰነዶች ላይ ለመፈረም ሥልጣን ከየትኛው የሚመለከተው አካል እንዳገኙ የሚገልጽ ሰነድ ወይም ቃለ ጉባኤ አለመገኘቱ ተገልጧል፡፡

ሙስና ያናረው የአጠቃላይ ኮንትራት ዋጋ

እስከ የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኮንትራክተሩ በተለያየ መልክ የተከፈለው ገንዘብ 7‚883‚884.72 መድረሱ በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲኾን አጠቃላይ የኮንትራት ዋጋ በሚል 10‚213‚675.15 መቀመጡም ተጠቁሟል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ ሔዷል ባለውና ሌሎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ግንባታ ጥራት ጋራ የተያያዙ ጉዳዮች ገለልተኛ በኾነ መሐንዲስ ትክክለኛነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ እየተካሔደ በሚገኘው የሕንፃ ግንባታው ምርመራ፣ ኮሚቴው የተጠቀመባቸው አሉሙኒየም ብረቶች የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ እንደኾኑና እየተነቃቀሉ የመወደቅ ችግር እንዳለባቸው መገለጹ የኦዲተሮቹን ማሳሰቢያ አጽንዖት እንደሚያሰጠው ተመልክቷል፡፡

የኦዲተሮች ሪፖርት ማጠቃለያ

ከሰኔ 30 ቀን 1995 – መጋቢት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ባለው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ዐሥራ ኹለት የበጀት ዓመታት ሒሳብ ላይ በማተኮር ለኹለት ወራት ተከናውኗል የተባለው ኦዲቱ÷ የኮሚቴው የሀብትና ዕዳ እና የገቢና ወጪ የሒሳብ መግለጫዎች ከሒሳብ ማብራሪያዎቹ ጋራ ሲታዩ፣ ሲፈጸሙ የቆዩት ክፍያዎች በርግጥም ለቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ግንባታ የወጡ ናቸው ብሎ ለማረጋገጥ እንደማይቻል በመግለጽ ነው ሪፖርቱን ያጠቃለለው – ‹‹የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን ሀብትና ዕዳ እንዲኹም በዚኹ ቀን ለተፈጸሙት 12 የበጀት ዓመታት የኮሚቴውን ገቢና ወጪ እንቅስቃሴ በሚገባ ያመለክታሉ ብሎ አስተያየት መስጠት አልቻልንም፡፡››

Audit Summary of the Auditors on Dire Dawa St GAbriel Church

ኦዲቱ የተካሔደው፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤና ምእመናን በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶስ ባቀረቡት አቤቱታና የአቤቱታው አግባብነት በቋሚ ሲኖዶስ ልኡካን ተጣርቶ መስከረም 8 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጋነነ ነው የተባለው የሕንፃ ሥራው ሒሳብና የግንባታ ጥራቱ በገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር በተላለፈው የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት እንደኾነ ተዘግቧል፡፡ በኮሚቴው የሒሳብ ሰነዶች ላይ ተመሥርቶ የተደረገው የኦዲት ምርመራ ውጤት አስተያየት ለመስጠት ያላስቻለ (Adverse opinion report) መኾኑ በግንባታው ስም ኾነ ተብሎም ይኹን በግድፈት የከፋ ስሕተት መፈጸሙን ያመለክታል ይላሉ ኢትዮ – ምኅዳር ያነጋገራቸው ባለሞያዎች፡፡

የደብሩ አስተዳደር እና የምእመናን ተሟጋች ቡድን ቀጣይ ዝግጅት

የኦዲት ሞያ በሚጠይቃቸውና ተቀባይነት ባለው የሒሳብ ምርመራ ስልት ተደርሶባቸዋል የተባሉት የሪፖርቱ ዝርዝር ግኝቶች፣ የደብሩን ሕጋዊ መብቶችና ጥቅሞች እንደሚያስከብሩ የሚያምኑ የደብሩ አገልጋዮችና ምእመናን በበኩላቸው፣ በተለይም የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን ሰብሳቢ በእምነት ማጉደልና ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም ወንጀል በሕግ እንደሚጠይቋቸው አስታውቀዋል፡፡

ከሰብሳቢው ጋራም ባልጸደቀ የክፍያ ምስክር ወረቀት ከውል ውጭ ገንዘብ ሲቀበል ቆይቷል፤ የሰው ኃይሉና ድርጅታዊ ብቃቱም አጠያያቂ ነው ያሉትን የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ፤ ያለሞያዊ ብቃት በሕገ ወጥ ጥቅም ላይ በተመሠረተ ግንኙነት ግንባታውን ይቆጣጠሩ ነበር በተባሉትና በዚኹ ሳቢያ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ዋና ሓላፊነት መባረራቸው በተነገረው በአቶ ሰሎሞን ካሳዬ ላይም ክሥ እንደሚመሠርቱ ለዚኽም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጋራ መነጋገራቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአማሳኞች ሽሽት እና የፓትርያርኩ ከለላነት

የደብሩ አገልጋዮችና ምእመናን እንዲኽ ቢሉም የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ መሐሪ፡- ደብሩን፣ ሰበካ ጉባኤውንና አስተዳዳሪውን በስም ማጥፋትና በኹከት ይወገድልኝ ከሠዋቸዋል፡፡ ግለሰቡ እንዲኽ ዓይነት ክሥ ለመመሥረት የሚያስችላቸው የባለቤትነት መብት በደብሩ ላይ እንደሌላቸውና ማስረጃም እንደማይኖራቸው ቢነገራቸውም ጉዳዩ በፍ/ቤት ተይዞ በቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

የሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ከውል ስምምነቱ በተቃራኒውና ከውሉ ውጭ እስከ 300% ጭማሪ የተደረገበትን ከአምስት ሚልዮን ብር በላይ ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ጋራ በመጠቃቀም ሲቀበሉ እንዳልቆዩ ኹሉ ተጨማሪ 2.7 ሚልዮን ብር እንዲከፈላቸው ደብሩን ጠይቀዋል፡፡ ተቋራጩ የኮንስትራክሽን ሕግን በሚፃረር አኳኋን ያቀረቡት ይኸው የተጨማሪ ክፍያ ጥያቄ ከተፈጸመ የሕንፃ ሥራውን ወጪ ብር 9‚554‚324.41 እንደሚያደርሰው ታውቋል፡፡

ይኹንና ተቋራጩ በተቆጣጣሪ መሐንዲስ የጸደቀ የክፍያ ምስክር ወረቀት(payment certificate) እንዲያቀርቡ በደብሩ አስተዳዳሪ ሲጠየቁ ‹‹ውጭ አገር ሔጃለኹ›› ብለው ውሏቸውን በጠቅላይ ቤተ ክህነት በማድረግ የኦዲት ሪፖርቱ ይፋ ከመኾኑ በፊት አንዳች ርምጃ እንዲወሰድ በመጠቃቀሙ እጃቸው እጃቸውን ያስገቡ ግለሰቦችን ‹‹እናንተንም ትከሠሣላችኹ›› በማለት እስከ ልዩ ጽ/ቤት የተዘረጋውን የምዝበራ ሰንሰለት ሲያንቀሳቅሱ ቆይተዋል፡፡

የግንባታ ሥራው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በመጠቃቀም ከተሰጣቸው ወዲኽ ሌላ ምንም ዓይነት ጨረታ አሸንፈውና ሥራ ሠርተው አያውቁም የተባሉት ተቋራጩ፣ ከቤተ ክርስቲያን ከወሰዱት ክፍያ ላይ ከ1.5 ሚልዮን በላይ ብር የሚገመት ግብር (ተ.እ.ታ) ለመንግሥት እንዳልከፈሉ ከሰነዶች ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም በብር 350‚000 ወጪ በደብሩ የተገዙና ከበጎ አድራጊ ምእመናን በዓይነት የቀረቡ እስከ ብር 600‚000 የሚገመቱ የግንባታ ዕቃዎች በጠቅላላው 900‚000 ያኽል ወጪ ከተፈጸመላቸው ክፍያ ላይ ተቀናሽ መኾን ሲገባው አለመቀነሱ ታውቋል፡፡

ኾኖም ተቋራጩ የከተማውን ፖሊስ ኮሚሽነር በአጋዥነት ይዘዋል ከተባሉት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋራ በመንቀሳቀስ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ሣህለ ማርያም፣ የኦዲት ሪፖርቱ ባለፈው ሳምንት እሑድ በዐውደ ምሕረት ይፋ ከመኾኑ ከቀናት አስቀድሞ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ አስተዳዳሪው የኦዲት ምርመራውን እስከ ግንባታው ፍፃሜ እንዲያዘገዩ በከተማው ፖሊስ ኮሚሽነር ግልጽ ጫና ሲደረግባቸው ቆይቷል፡ አለቃው በበኩላቸው፣ ኮሚሽነሩ ሙስናና አማሳኞች እንዲጋለጡ መደገፍ ሲገባቸው አሉታዊ ጫና መፍጠራቸው ጣልቃ ገብነት እንደኾነ በመግለጽ የከተማው አስተዳደር መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡

በኮሚሽነሩ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባል ነዎት ወይ?›› ተብለው የተጠየቁት አለቃው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጋራ በመተባበር አማሳኞችና የምዝበራ ሰንሰለታቸው እንዲጋለጥ ያደረጉት ጥረት አለቃው ራሳቸው በሚወለዱበት በ‹‹አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ›› ተደርጎ ተዝቶባቸዋል፤ ‹‹የከተማው ሰላም ጠንቅ ነው›› በሚል አያሌ ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል፤ በመጨረሻም በእነ አቶ ብርሃኔ መሐሪና በተቋራጩ አማካይነት ከኮሚሽነሩ ጋራ በስልክ እንደተገናኙ የተነገረላቸው ፓትርያርኩ፣ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለማስፈጸም በሊቀ ጳጳሱ መመሪያና በሀገረ ስብከቱ ድጋፍ ከሰበካ ጉባኤው ጋራ በአንድነት የተንቀሳቀሱትን መልአከ ሰላም አባ ሣህለ ማርያምን ከአስተዳዳሪነት ሓላፊነታቸው አንሥተዋቸዋል፡፡

ሕገ ወጡ ርምጃ የተወሰደው ከኦዲት ሪፖርቱ ጋራ በተያያዘ በደብሩ የተፈጠረ ችግር እንደሌለና እንደማይኖር፣ ካለም እንደሚያሳውቋቸው የክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ለፓትርያርኩ በገለጹበት ኹኔታ ውስጥ እንደኾነ ታውቋል፡፡ አለቃው ከሓላፊነት መነሣታቸውንና ሀገረ ስብከቱ ለሚወክለው አካል በእጃቸው ያለውን ንብረት እንዲያስረክቡ ፓትርያርኩ ትእዛዝ የሰጡበትን ደብዳቤ÷ የክፍሉ ሊቀ ጳጳስአለቃው፣ ሰበካ ጉባኤውና የከተማው ምእመን በአጠቃላይ አምርረው በጽኑ ከመቃወማቸውም በላይ ከኦዲት ምርመራው ጋራ በተያያዘ የፓትርያርኩን ተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነት የተመለከተ አቤቱታ በአለቃው በኩል ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤትና ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጁ መቅረቡ ተዘግቧል፡፡ ለአቤቱታው ‹‹ወደፊት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ባሉበት በቅዱስ ሲኖዶሱ ላይ ይቀርባል፤›› ከሚል በቀር የተገኘ እንደሌለ ተነግሯል፡፡

‹‹ሕዝቡ ራሱ ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቅ››

አገልጋዮቹና ምእመናኑ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በአህጉረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን እየመረጠ የመሾም ሥልጣን ያለው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ኾኖ ሳለ ፓትርያርኩ ያለሊቀ ጳጳሱ ስምምነት አስተዳዳሪውን ከሓላፊነታቸው ማንሣታቸው አስቆጥቶናል ብለዋል፡፡ በደብሩ የተፈጸመው ዘረፋና ብክነት ተቀባይነት ባለው የኦዲት ምርመራ እንዲጋለጥ በማድረግ የድርሻቸውን ተወጥተዋል ባሏቸው አስተዳዳሪ ቦታ የሚደረግ ምደባም ‹‹ሙስናና አማሳኞች በፓትርያርኩ ዙሪያ የያዙትን የበላይነት ከማጋለጥ ውጭ ሌላ ሊኾን እንደማይችል›› ገልጸዋል፤ ሕገ ወጥ በመኾኑም ፈጽሞ እንደማይቀበሉትና በጉዳዩ ላይ በመጪው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል አጋጣሚ ከፓትርያርኩ ጋራ ገጽ ለገጽ ተገናኝተው ለመነጋገር እንደሚሹ አስታውቀዋል፡፡

ስለጉዳዩ ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ጋራም መማከራቸውን አገልጋዮቹና ምእመናኑ ጠቅሰው፣ የፓትርያርኩ ትእዛዝ ራሳቸው በሰብሳቢነት ካሳለፏቸው የቋሚ ሲኖዶሱ የውሳኔዎች አፈጻጸም ጋራ የማይጣጣሙ መኾናቸውን አረጋግጠውልናል፤ የፓትርያርኩ ሌሎች አካሔዶችም የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔዎች የማይከበሩበትና ከአቅም በላይ እየኾኑ በመምጣታቸው ቅዱስ ሲኖዶሱን ለአስቸኳይ ስብሰባ ለመጥራት ተንቀሳቅሰው እንደነበር ገልጸውናል ብለዋል፡፡

የአስተዳዳሪው አላግባብ መነሣት ‹‹ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከመሠረቱ ለማስወገድ በመጣር ላይ ለሚገኙ ሌሎች አስተዳዳሪዎች ዋስትና የሚያሳጣ መኾኑን አክለው የገለጹት ምእመናኑ፣ ‹‹ሕዝቡ ራሱ ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቅ›› በሚል ከሊቃነ ጳጳሳቱ አግኝተነዋሉ ባሉት አባታዊ መመሪያና ምክር መሠረት የድሬዳዋ አገልጋዮችንና ምእመናን አንድ ባደረገው የሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ምርመራ ሪፖርት ዙሪያ ምዝበራንና ብኩንነትን በጽናት መቃወማቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት አሳስበዋል፡፡

***************************************************************

ሀብተ ወልድ መንክር እና ጓዶቹ በቻርተር የተመሠከረላቸው የሒሳብ ዐዋቂዎች/ለንደን/ የተፈቀደለት ኦዲተር/ኢትዮጵያ/ የቀረበው የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንፃ ሥራ የኦዲተሮች ሪፖርት እና የሒሳብ መግለጫ ሙሉ ይዘት፤

Advertisements

8 thoughts on “ከፍተኛ ምዝበራ የተፈጸመበት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ሥራ ኦዲት ሪፖርት ይፋ ኾነ፤ የደብሩ አለቃ ከሪፖርቱ አስቀድሞ ያለሊቀ ጳጳሱ ስምምነት በፓትርያርኩ ትእዛዝ ተነሡ!

 1. Workneh Ayele July 23, 2014 at 7:36 am Reply

  የሁሉ ነገር ምሳሌ የሆነች ቤተክርስቲያን መጨረሻዋ እንዲህ ይሁን እባካችሁ ምዕመናንና እውነተኖች አገልጋዮች አንድነታችን ይጠበቅ እኛ አንድ ከሆንን እግዚአብሄር ተጨምሮበት ሁሉም ይስተካከላል ደግሞም ሩቅ አይሆንም

 2. Kebede July 23, 2014 at 9:39 pm Reply

  The key is this :”ኾኖም ተቋራጩ የከተማውን ፖሊስ ኮሚሽነር በአጋዥነት ይዘዋል ከተባሉት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋራ በመንቀሳቀስ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ሣህለ ማርያም፣ የኦዲት ሪፖርቱ ባለፈው ሳምንት እሑድ በዐውደ ምሕረት ይፋ ከመኾኑ ከቀናት አስቀድሞ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ አስተዳዳሪው የኦዲት ምርመራውን እስከ ግንባታው ፍፃሜ እንዲያዘገዩ በከተማው ፖሊስ ኮሚሽነር ግልጽ ጫና ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡ አለቃው በበኩላቸው፣ ኮሚሽነሩ ሙስናና አማሳኞች እንዲጋለጡ መደገፍ ሲገባቸው አሉታዊ ጫና መፍጠራቸው ጣልቃ ገብነት እንደኾነ በመግለጽ የከተማው አስተዳደር መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡”

 3. Anonymous July 24, 2014 at 7:36 am Reply

  በቤተ ክርስቲያን የሚታየውን ሙስና እና ብልሱ አስራር ለመዋጔት ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሃላፊነት አለብን

 4. ንቁም በበኅላዌነ July 25, 2014 at 7:28 pm Reply

  ጉዳዩ ከርዕሱ ጋር ቢገጥምም ባይገጥምም ወገን እንንቃ!!!

  የመጀመሪያ ደወል:  ራሱን የሙስሊሞች ከሊፋ (መሪ) ብሎ የሰየመው የኢራቁ Islamic State of Iraq and the Syria (ISIS) መሪ በቅርቡ የሙስሊሞች ሀገር (Islamic State) ብሎ ባወጣው ካርታ መሠረት በአፍሪካ ውስጥ ሶስት ክፍላተ-ሐገራት ያካተተ ሲሆን አንደኛዋ ክፍለ ሀገር ሐበሻ (The Land of Habesha) የምትባል ስትሆን በውስጧም ጁቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያን ያከተተች መሆኑ ተዘግቧል።

  ምንጭ: Sudan Tribune, July 13, 2014

  ሁለተኛው ደወል:  የሱዳን መንግስት የቤተ ክርስቲያን ግንባታ በሀገሪቱ እንደማይካሄድ እና የቤተ ክርስቲያን መስሪያ ፍቃድ እንደማይሰጥ guidance and Religious Endowments ሚኒስትር ሳህሊል አብዱሏህ ማስታወቃቸው፣ ይህም ውሳኔ የተላለፈው ደቡብ ሱዳን ከተገነጠለች በኋላ በሀገሪቱ የሚኖሩ ሕዝበ ክርስቲያናት ቁጥር ዉስን በመሆኑ እና ያሉትም አብያተ-ክርስቲያናትም ለህዝብ-ክርስቲያኑ በቂ መሆናቸው መጠቀሱ፣ ነገር ግን በሀገሪቱ የሚኖሩ ቀሳውስት ውሳኔውን መቃወማቸው መታወቁ ተዘግቧል።

  ምንጭ: The Tablet, July 16,2014

 5. Abel Demissie July 25, 2014 at 7:49 pm Reply

  Your focus on the police commissioner of Dire Dawa is the hidden political side of this particular website. Why don’t you post the current status of the church? Why these much pressure excreted while the church is already finished? Who was there when the “auditor” has done auditing? Are you really sure that the committee has no legal right to defend itself? I am advising the people to examine the case from these angels and understand the reality. But how long you create confusion among our beloved church followers? Let us pray and again pray and again pray… the answer is in the hands of the almighty …Jesus Christ. I wish in the feature you will talk about peace, love, respect, support, ….

 6. Samrawit July 26, 2014 at 8:16 pm Reply

  ዛሬ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓልን ለማክበር ከሩቅም ከቅርብም የምንገኝ የድሬዳዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ማታ ከዋዜማው ተጀምሮ በዘለቀው ስርዓት ተሳታፊ በመሆን እጅግ ባማረ እና በደመቀ ሁናቴ ነበር መንፈሳዊው ስነስርኣት ስንሳተፍ የነበረው፡፡ በእናንተም ቀድሞ በተነገረው ዜና/መረጃ መሠረት ቅዱስነታቸውን ለማነጋገር የነበረው መርኀግብር ባልታሰበ ሁኔታ እንደማይቻል በመሆኑ እንደቀረ የወሬ ወሬ ብንሰማም እስኪ ስለነበረው ሁሉ ነገር ታቦተ ህጉን ከቦ በበአለ ንግሱ ለሚገኘው ሰው ይነገራል በሚል ትልቅ ተስፋ በመመላት ህዝበ ሁላችን በመጠባበቅ ላይ ነበርን፡፡ ከዚህ መርኃግብር በኋላ ለጥቆ ይቀርብ ይሆናል እያልን ስንጠብቅ ብንውልም አንዳች ሪፖርት መሳይ እንኳን ሳናይ ሰዓታት ተገባደዱ፡፡ የሆነው ሆኖ እጅግ ያማረ አጥንትን ዘልቆ የሚገባና ሁላችንንም ያጽናና ትምህርት በመጋቢ ብሉይ እና ቃለቡራኬና ቃለ ምዕዳኑ በብጹዕነታቸው አቡነ አምባቆም ተሰጠን በዚሁም ተቋጨ ተባልን፡፡ ምንም አይነት ሪፖርትም ሆነ ስለነበረው እና በሰንበት ተነቦልን የነበረውን እንኳን የኦዲት ሪፖርት ደግመው ሊያሰሙን አልቻሉም፡፡ ምክኒያቱ ምን ይሆን ብለን ብዙ ብናስስም ልናውቅ አልቻልንም እንዲያው በደፈናው ግን ከበላይ ምንም ሪፖርት እንዳይሰማ የሚል በመተላለለፉ እንደሆነ የወሬ ወሬ ሰማን፡፡ በእውነት ህዝበ ክርስቲያኑ በአጠቃላይ ማለት ይቻላል እየተሰራ ባለው ነገር እጅግ ተበሳጭቶ እና አዝኖ ወደ ቤቱ እንደገባ ለመጠቆም ስንወድ ዘርዘር ያሉ ነገሮችን ተከታትላችሁ እንደምታሰሙን በመጓጓት ነው፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

 7. ንቁም በበኅላዌነ July 29, 2014 at 3:10 pm Reply

  የማንቂያ ደወል ሦስት:- የኢራቁ ፅንፈኛ ቡድን ISIS Islamic Stateን የመፍጠር አላማውንአጥብቆ እንደሚደግፍ እና ሁሉን አቀፍ ከሊፌት የመፍጠር ውጥኑ የተቀደሰ እና መልካም ምግባርእንደሆነ የሱዳን ሰሊፊ ቡድን Al-Attasam bel-Ketab wa-al-Suna ማስታወቁ፣ ይህ ቡድን እራሱን እ.ኤ.አ በ1991 ከሱዳን
  ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ያገለለ መሆኑ እና strict የሆነ የእስልምና አምልኮ እንዲተገበር የሚተጋ
  ቡድን እንደሆነ ተዘግቧል።

  ምንጭ: Reuters, July 24, 2014

 8. haile derbew August 2, 2014 at 2:43 pm Reply

  amlak ende hatyatachin sayhon endechernetu ytebken!!!!!!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: